-
ዳንኤል—ክስ የቀረበበት መጽሐፍየዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል!
-
-
7. (ሀ) ዳንኤል ስለ ብልጣሶር መጥቀሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎችን ሲያስደስታቸው የኖረው ለምንድን ነው? (ለ) ብልጣሶር ልብ ወለድ ሰው ነው የሚለው ሐሳብ ምን ገጥሞታል?
7 ዳንኤል የባቢሎን ከተማ ስትወድቅ ንጉሥ ሆኖ ያስተዳድር የነበረው የናቡከደነፆር ‘ልጅ’ ብልጣሶር እንደሆነ ጽፏል። (ዳንኤል 5:1, 11, 18, 22, 30) ተቺዎች ብልጣሶር የሚለው ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ሌላ የትም ቦታ ተጠቅሶ ስለማይገኝ ይህ አባባል ስህተት ነው እያሉ ለረጅም ጊዜ ሲተቹ ቆይተዋል። የጥንት ታሪክ ጸሐፊዎች ናቡከደነፆርን እንደተካና የባቢሎን የመጨረሻ ንጉሥ እንደነበር የሚናገሩለት ናቦኒደስ ነው። በመሆኑም በ1850 ፈርዲናንድ ሂትሲክ፣ ብልጣሶር የጸሐፊው ሐሳብ የወለደው ሰው እንደሆነ ግልጽ ነው ብለው ነበር። ነገር ግን ሂትሲክ ትንሽ የቸኮሉ አይመስልህም? ደግሞስ በዚያ የታሪካዊ መዛግብት ቁጥር እጅግ ውስን በነበረበት ዘመን የአንድ ንጉሥ ስም ተጠቅሶ አለመገኘቱ ጭራሽ እንደዚያ የሚባል ንጉሥ አልነበረም ለማለት በእርግጥ ማስረጃ ሊሆን ይችላልን? የሆነ ሆኖ በ1854 በዛሬዋ ኢራቅ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው ኡር በምትባለው የጥንቷ የባቢሎን ከተማ አካባቢ በተደረገው ቁፈራ አንዳንድ ትናንሽ ሞላላ ሸክላዎች ተገኙ። የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፈባቸው እነዚህ የንጉሥ ናቦኒደስ መዛግብት ስለ “ታላቁ ልጄ ብልሳርሱር” በሚል ያቀረበውን ጸሎት ይዘው ተገኝተዋል። ተቺዎች ሳይቀሩ ይህ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው ብልጣሶር መሆኑን ለመቀበል ተገደዋል።
-
-
ዳንኤል—ክስ የቀረበበት መጽሐፍየዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል!
-
-
9. (ሀ) ብልጣሶር የናቡከደነፆር ልጅ መሆኑን ዳንኤል ሊጠቅስ የሚችልበት መንገድ ምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ተቺዎች ዳንኤል የናቦኒደስን መኖር የሚጠቁም ትንሽም እንኳ ፍንጭ አልሰጠም ማለታቸው ስህተት የሚሆነው እንዴት ነው?
9 ይህም ያላረካቸው አንዳንድ ተቺዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ብልጣሶር የናቡከደነፆር ልጅ እንደሆነ እንጂ የናቦኒደስ ልጅ እንደሆነ አይደለም ብለው ተቃውሞ ያሰማሉ። አንዳንዶችም ዳንኤል፣ ናቦኒደስ የሚባል ሰው ስለመኖሩ እንኳን ምንም የጠቀሰው ነገር የለም ይላሉ። ይሁን እንጂ ቀረብ ብለን ከመረመርናቸው ሁለቱም ተቃውሞዎች መሠረት የላቸውም። ናቦኒደስ የናቡከደነፆርን ሴት ልጅ ያገባ ይመስላል። በዚህ መሠረት ብልጣሶር የናቡከደነፆር የልጅ ልጅ ይሆናል ማለት ነው። የዕብራይስጡም ሆነ የአረማይኩ ቋንቋ “አያት” ወይም “የልጅ ልጅ” የሚል ቃል የሌላቸው በመሆኑ “ልጅ” ከተባለ “የልጅ ልጅ” አልፎ ተርፎም “ዝርያ” ማለት ሊሆን ይችላል። (ከማቴዎስ 1:1 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ብልጣሶር የናቦኒደስ ልጅ ነው መባሉን አይቃወምም። ብልጣሶር በግድግዳው ላይ በታየው አስደንጋጭ ጽሕፈት በተጨነቀ ጊዜ የቃሉን ፍቺ ለሚነግረው ሰው በመንግሥቱ ውስጥ ሦስተኛውን ቦታ እንደሚሰጠው ቃል ገብቶ ነበር። (ዳንኤል 5:7) በመንግሥቱ ውስጥ ሁለተኛውን ሳይሆን ሦስተኛውን ቦታ እንደሚሰጥ ቃል የገባበት ምክንያት ምንድን ነው? ይህ አባባሉ አንደኛውና ሁለተኛው ቦታ በወቅቱ ተይዞ የነበረ መሆኑን ይጠቁማል። አዎን፣ በናቦኒደስና በልጁ በብልጣሶር ተይዞ ነበር።
-