ምዕራፍ ስምንት
ከአንበሶች መንጋጋ ዳነ!
1, 2. (ሀ) ሜዶናዊው ዳርዮስ የተስፋፋውን ግዛቱን ያደራጀው እንዴት ነው? (ለ) መሳፍንቱ ምን ዓይነት ሥራና ሥልጣን እንደነበራቸው ግለጽ።
ባቢሎን ወድቃለች! አንድ ምዕተ ዓመት ለሚያህል ጊዜ ይዛው የቆየችው የዓለም ኃያልነት ክብርዋ በጥቂት ሰዓታት አክትሟል። የሜዶንና የፋርስ አዲስ የግዛት ዘመን ጀምሯል። በብልጣሶር ምትክ የነገሠው ሜዶናዊው ዳርዮስ የተስፋፋውን ግዛቱን የማደራጀት ከባድ ሥራ ይጠብቀዋል።
2 ዳርዮስ ከወሰዳቸው የመጀመሪያ እርምጃዎች መካከል አንዱ 120 መሳፍንት መሾም ነበር። በዚህ የሥልጣን ቦታ ላይ የሚያገለግሉት ሰዎች አንዳንድ ጊዜ የሚመረጡት ከንጉሣዊ ቤተሰብ መካከል እንደሆነ ይታመናል። ያም ሆነ ይህ እያንዳንዱ መስፍን [ሳትራፕ ] በአንድ ጠቅላይ ግዛት ወይም በተወሰነው የንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ላይ ይሾማል። (ዳንኤል 6:1) ሥራው ቀረጥ መሰብሰብንና ለንጉሣዊው ቤተ መንግሥት ግብር ማስገባትን ይጨምራል። አልፎ አልፎ እየመጣ የሚቆጣጠር የንጉሡ ወኪል ቢኖርም የመስፍኑ ሥልጣን ከፍተኛ ነበር። የማዕረጉ ትርጉም “የንጉሣዊ መንግሥቱ ጠባቂ” የሚል ነው። መስፍኑ በጠቅላይ ግዛቱ ውስጥ ሙሉ ሥልጣን ያለው እንደራሴ ንጉሥ ነው ለማለት ይቻላል።
3, 4. ዳርዮስ ለዳንኤል ለየት ያለ አመለካከት የነበረው ለምንድን ነው? ምንስ ሥልጣን ሰጥቶታል?
3 በዚህ አዲስ ዝግጅት ውስጥ ዳንኤል ምን ቦታ ይኖረው ይሆን? ሜዶናዊው ዳርዮስ በዘጠናዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘውን ይህን ዕድሜው የገፋ አይሁዳዊ ነቢይ ጡረታ ያስወጣው ይሆን? በፍጹም! ዳንኤል የባቢሎንን ውድቀት በትክክል መተንበዩንና እንዲህ ዓይነቱ ትንበያም ከሰው ችሎታ በላይ የሆነ ማስተዋል የሚጠይቅ መሆኑን ዳርዮስ ሳይገነዘብ አልቀረም። ከዚህም በተጨማሪ ዳንኤል በባቢሎን የነበረውን ከተለያየ ወገን የተውጣጣ የምርኮኞች ማኅበረሰብ በማስተዳደር በኩል የአሥርተ ዓመታት ተሞክሮ አካብቷል። ዳርዮስ ድል ከተነሡት አዲሶቹ ተገዥዎቹ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረው አጥብቆ ይሻ ስለነበር የዳንኤልን ዓይነት ጥበብና ተሞክሮ ያለው በመንግሥቱ ውስጥ ከእርሱ ጋር በቅርብ የሚሠራ ሰው እንደሚፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። በምን ዓይነት የሥልጣን ቦታ?
4 ዳርዮስ አይሁዳዊ ምርኮኛ የሆነውን ዳንኤልን መስፍን አድርጎ ቢሾመው እጅግ የሚያስገርም ይሆናል። ዳርዮስ ግን ጭራሽ መስፍኖቹን ከሚቆጣጠሩት ሦስት አለቆች መካከል አንዱ አድርጎ ዳንኤልን መሾሙን ሲያሳውቅ ምን ያህል ጉም ጉምታ እንደተፈጠረ አስበው! ከዚህም በላይ ዳንኤል በመንግሥቱ አለቆችም መካከል የላቀ መሆኑን በሚያስመሰክር መንገድ ‘ለየት ብሎ መታየቱን ቀጥሎ ነበር።’ በእርግጥም ‘የላቀ መንፈስ’ የነበረው ሰው ነው። ዳርዮስ የጠቅላይ ሚንስትርነትን ቦታ ሊሰጠውም አስቦ ነበር።—ዳንኤል 6:2, 3
5. ሌሎቹ ባለ ሥልጣኖችና መሳፍንቱ ስለ ዳንኤል ሹመት ምን ተሰምቷቸው መሆን አለበት? ለምንስ?
5 ሌሎቹ የመንግሥቱ አለቆችና መሳፍንት በንዴት በግነው መሆን አለበት። ሜዶናዊ ወይም ፋርሳዊ ዝርያ የሌለው ወይም ደግሞ የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል ያልሆነው ዳንኤል ከእነርሱ በሚበልጥ የሥልጣን ቦታ ላይ መቀመጡ አልዋጥ ብሏቸው ነበር! ዳርዮስ ከአገሩ ልጆች አልፎ ተርፎም ከገዛ ቤተሰቡ አስበልጦ ለአንድ የባዕድ አገር ሰው እንዴት እንዲህ ዓይነት ከፍተኛ ሥልጣን ሊሰጠው ቻለ? ድርጊቱ ፍትሐዊነት የጎደለው ሊመስል ይችላል። ከዚህም በላይ የዳንኤል ጽኑ አቋም ጉቦ መብላት ለለመዱትና በሙስና ለተዘፈቁት መሳፍንት ጋሬጣ ሆኖባቸው ሊሆን ይችላል። ይሁንና የመንግሥቱ አለቆቹም ሆኑ መሳፍንቱ ስለ ጉዳዩ በቀጥታ ዳርዮስን ለማነጋገር አልደፈሩም። ደግሞም ዳርዮስ ለዳንኤል ትልቅ ግምት ነበረው።
6. የመንግሥቱ አለቆችና መሳፍንቱ ዳንኤልን ለማጣጣል የሞከሩት እንዴት ነው? ይህስ ጥረታቸው ከንቱ የሆነው ለምንድን ነው?
6 በመሆኑም እነዚህ ቅናት ያንገበገባቸው ፖለቲከኞች እርስ በርሳቸው ተማከሩ። “ስለ መንግሥቱ በዳንኤል ላይ ሰበብ ይፈልጉ ነበር።” የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ እንከን ይገኝበት ይሆን? ያጭበረብር ነበርን? የመንግሥቱ አለቆችና መሳፍንቱ ዳንኤል የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ፈጽሟል የሚሉት አንድም ቸልተኝነት ወይም ሙስና ማግኘት አልቻሉም። “ከአምላኩ ሕግ በቀር በዚህ በዳንኤል ላይ ሌላ ሰበብ አናገኝበትም” ብለው አሰቡ። በመሆኑም እነዚህ መሰሪ ሰዎች አንድ ሴራ ጠነሰሱ። ዳንኤል የሚባለው ሰው ከምድረ ገጽ የሚጠፋበት ጊዜ ቅርብ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል።—ዳንኤል 6:4, 5
የግድያ ሴራ ተጠነሰሰ
7. የመንግሥቱ አለቆችና መሳፍንቱ ለንጉሡ ምን ሐሳብ አቀረቡ? ይህንንስ ያደረጉት እንዴት ነበር?
7 የመንግሥቱ አለቆችና መሳፍንት አንድ ላይ ‘ስብስብ ብለው’ ዳርዮስ ዘንድ ገቡ። እዚህ ላይ የተሠራበት የአረማይክ አገላለጽ ድብልቅልቅ ያለ ውካታን የሚያመለክት ነው። እነዚህ ሰዎች ወደ ዳርዮስ የቀረቡት እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ እንዳላቸው አድርገው ነው። እነርሱ ያመኑበትና አፋጣኝ እርምጃ የሚያሻው ነገር እንደሆነ አድርገው ቢያቀርቡት ዳርዮስ ሐሳባቸውን ለመቀበል ብዙም እንደማያንገራግር አስበው ሊሆን ይችላል። በመሆኑም በቀጥታ ወደ ፍሬ ጉዳያቸው በመሄድ እንዲህ አሉ:- “የመንግሥቱ አለቆች ሁሉ ሹማምቶችና መሳፍንት አማካሪዎችና አዛዦች:- ንጉሥ ሆይ፣ ከአንተ በቀር ማንም እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ልመና ከአምላክ ወይም ከሰው ቢለምን፣ በአንበሶች ጒድጓድ ውስጥ ይጣል የሚል የንጉሥ ሕግና ብርቱ ትእዛዝ ይወጣ ዘንድ ተማከሩ።”a—ዳንኤል 6:6, 7
8. (ሀ) ዳርዮስ የቀረበው የሕግ ረቂቅ ጥሩ እንደሚሆን የተሰማው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) የመንግሥቱ አለቆችና የመሳፍንቱ እውነተኛ ዓላማ ግን ምን ነበር?
8 የመሶጴጣሚያ ነገሥታት እንደ መለኮት መታየታቸውና መመለካቸው የተለመደ ነገር እንደነበር ታሪካዊ መዛግብትም ይመሠክራሉ። በመሆኑም ዳርዮስ በዚህ ሐሳብ ተደልሎ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ደግሞም ሐሳቡ ጠቃሚ ሊሆን የሚችልበት ጎን ታይቶት ይሆናል። በባቢሎን ለሚኖሩት ሰዎች ዳርዮስ የባዕድ አገር ሰውና መጤ መሆኑን አትዘንጋ። ይህ አዲስ ሕግ እንደ ንጉሥ አድርገው እንዲቀበሉትና በባቢሎን ያሉት በጣም ብዙ ነዋሪዎችም ለአዲሱ አገዛዝ ታማኝነታቸውንና ድጋፋቸውን እንዲገልጹ የሚያበረታታ ሊሆን ይችላል። የመንግሥቱ አለቆችና መሳፍንቱ ግን ይህንን ነገር ሲወጥኑ ያሳሰባቸው የንጉሡ ጥቅም አልነበረም። እውነተኛው ዓላማቸው ዳንኤልን ወጥመድ ውስጥ ማስገባት ነበር። ምክንያቱም ዳንኤል በቤቱ አናት ላይ ወዳለው እልፍኝ ገብቶ መስኮቶችን ከፍቶ በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ የመጸለይ ልማድ እንደነበረው ያውቃሉ።
9. አዲሱ ሕግ አይሁዳውያን ላልሆኑ ለአብዛኛዎቹ ሰዎች እምብዛም ችግር የማይፈጥርባቸው ለምንድን ነበር?
9 በጸሎት ላይ የተደረገው ይህ እገዳ በባቢሎን በነበሩት ሃይማኖታዊ ወገኖች ሁሉ ላይ ችግር የሚፈጥር ነበርን? በተለይ እገዳው የሚቆየው ለሠላሳ ቀናት ብቻ ስለነበር እንደዚያ ማለት ላይሆን ይችላል። ከዚህም በላይ ለጊዜውም ቢሆን ለሰው አምልኮ መስጠትን አቋምን እንደማላላት የሚቆጥሩት አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች እጅግ ጥቂት ናቸው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ከማንኛውም ብሔር ይበልጥ ጣዖት አምላኪ ለሆኑት ሰዎች የነገሥታት አምልኮ ያን ያህል እንግዳ የሆነ ነገር የሚጠይቅባቸው አልነበረም። በመሆኑም ባቢሎናውያን ለጣዖት አምላክ የሚገባውን ክብር ለድል አድራጊው ለሜዶናዊው ዳርዮስ እንዲሰጡ ሲጠየቁ ጥያቄውን በእሺታ ተቀብለውታል። እንዲህ ያለውን ጥያቄ ሳይቀበሉ የቀሩት አይሁዳውያኑ ብቻ ናቸው።”
10. ሜዶናውያንና ፋርሳውያን ንጉሣቸው የሚያወጣውን ሕግ የሚያዩት እንዴት ነበር?
10 ያም ሆነ ይህ ወደ ዳርዮስ የመጡት ሰዎች “እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና ፋርስ ሕግ፣ እንዳይለወጥ ትእዛዙን አጽና፣ ጽሕፈቱንም ጻፍ” ሲሉ ወተወቱት። (ዳንኤል 6:8) በጥንቱ የምሥራቃውያን ዓለም የንጉሡ ፈቃድ ብዙውን ጊዜ እንደ ፍጹም ተደርጎ ይታይ ነበር። ይህም ንጉሡ አይሳሳትም የሚለው ሐሳብ እንዲሰፍን አድርጓል። የንጹሐን ደም እንዲፈስ ምክንያት የሚሆን ሕግም እንኳ ቢሆን አይለወጥም ነበር!
11. የዳርዮስ ትእዛዝ ዳንኤልን የሚነካው እንዴት ነው?
11 ዳርዮስ ስምምነቱን ሲፈርም ዳንኤል ጨርሶ ወደ አእምሮው አልመጣም። (ዳንኤል 6:9) ሳያውቀው ግን እጅግ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ባለ ሥልጣኑ እንዲገደል መፈረሙ ነበር። አዎን፣ ይህ ትእዛዝ ዳንኤልን እንደሚነካው ግልጽ ነው።
ዳርዮስ የማይስማማበትን ፍርድ ለማስፈጸም ተገደደ
12. (ሀ) ዳንኤል ስለ አዲሱ ሕግ እንዳወቀ ወዲያውኑ ምን አደረገ? (ለ) ዳንኤልን እነማን ይመለከቱት ነበር? ለምንስ?
12 ብዙም ሳይቆይ ዳንኤልም ጸሎትን የሚከለክል ሕግ መውጣቱን አወቀ። ወዲያውም ወደ ቤቱ ሄዶ በኢየሩሳሌም አንጻር መስኮቶቹ ወደ ተከፈቱት በቤቱ አናት ላይ ወደሚገኘው ክፍል ገባ።b በዚያም ዳንኤል ‘ቀድሞ ያደርገው እንደ ነበር’ ወደ አምላክ መጸለይ ጀመረ። ዳንኤል ብቻውን እንደሆነ አስቦ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ያሴሩበት ሰዎች እየተመለከቱት ነበር። በድንገት ‘ስብስብ’ ብለው መጡ። በዚህ ጊዜም ወደ ዳርዮስ በቀረቡ ጊዜ የነበራቸው ዓይነት ሁኔታ እንዳሳዩ ምንም አያጠራጥርም። አሁን ዳንኤል “በአምላኩ ፊት ሲጸልይና ሲለምን” በገዛ ዓይናቸው ተመልክተውታል። (ዳንኤል 6:10, 11) የመንግሥቱ አለቆችና መሳፍንቱ ዳንኤልን በንጉሡ ፊት ለመክሰስ የሚያስችላቸው በቂ ማስረጃ አገኙ።
13. የዳንኤል ጠላቶች ለንጉሡ ምን ሪፖርት አቀረቡ?
13 የዳንኤል ጠላቶች እንደሚከተለው ሲሉ ለዳርዮስ ተንኮል ያዘለ ጥያቄያቸውን አቀረቡ:- “ንጉሥ ሆይ፣ ከአንተ በቀር እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ከአምላክ ወይም ከሰው የሚለምን ሰው ሁሉ በአንበሶች ጒድጓድ ውስጥ እንዲጣል ትእዛዝ አልጻፍህምን?” ዳርዮስም “ነገሩ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ እውነት ነው” ሲል መለሰ። በዚህ ጊዜ እነዚህ ሴረኞች ቶሎ ብለው ወደ ፍሬ ነገሩ ሄዱ። “ከይሁዳ ምርኮኞች የሆነው ዳንኤል በየዕለቱ ሦስት ጊዜ ልመናውን ይለምናል እንጂ አንተንና የጻፍኸውን ትእዛዝ አይቀበልም አሉት።”—ዳንኤል 6:12, 13
14. ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው የመንግሥቱ አለቆችና መሳፍንቱ ዳንኤልን ‘የይሁዳ ምርኮኛ’ ሲሉ የጠሩት ለምንድን ነው?
14 የመንግሥቱ አለቆችና መሳፍንቱ ዳንኤልን ‘የይሁዳ ምርኮኛ’ ብለው መጥራታቸውን ልብ በል። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ዳርዮስ ይህን ያህል ክብር ሰጥቶ ከፍ ከፍ ያደረገው ዳንኤል አንድ አይሁዳዊ ባርያ እንጂ ሌላ ምንም እንዳይደለ መግለጽ ፈልገው ነበር። በመሆኑም ንጉሡ ስለ እርሱ ምንም ይሰማው ምን ዳንኤል ከሕጉ በላይ ሊሆን አይችልም የሚል ሐሳብ ነበራቸው!
15. (ሀ) ዳርዮስ የመንግሥቱ አለቆችና መሳፍንት ባመጡለት ሪፖርት ምን ተሰማው? (ለ) የመንግሥቱ አለቆችና መሳፍንቱ ለዳንኤል ያላቸውን ንቀት እንደገና የገለጹት እንዴት ነው?
15 ምናልባትም የመንግሥቱ አለቆችና መሳፍንቱ የዳንኤልን ድርጊት በማጋለጣቸው ንጉሡ ይሸልመናል ብለው ጠብቀው ሊሆን ይችላል። እንደዚያ አስበው ከሆነ አስገራሚ ምላሽ ይጠብቃቸዋል። ዳርዮስ በሰማው ነገር እጅግ ተረበሸ። በዳንኤል ከመቆጣት ወይም ወዲያውኑ ወደ አንበሳዎቹ ጉድጓድ እንዲጥሉት ከማዘዝ ይልቅ ዳርዮስ ቀኑን ሙሉ እርሱን የሚያድንበትን መንገድ ሲፈልግ ዋለ። ይሁን እንጂ ጥረቱ ሁሉ አልተሳካለትም። ወዲያው የሴራው ጠንሳሾች ተመልሰው በመምጣት የዳንኤል ደም እንዲፈስ ዓይን አውጥተው ጠየቁ።—ዳንኤል 6:14, 15
16. (ሀ) ዳርዮስ ለዳንኤል አምላክ አክብሮት የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) ዳርዮስ ዳንኤልን በሚመለከት ምን ተስፋ ነበረው?
16 ዳርዮስ ምንም ማድረግ እንደማይችል ተገነዘበ። ሕጉ ሊሻርም ሆነ የዳንኤል “በደል” ሊደመሰስ አይችልም። ዳርዮስ “ሁልጊዜ የምታመልከው [“ሳታወላውል የምታገለግለው፣” NW] አምላክህ እርሱ ያድንህ” ከማለት ሌላ ምንም ሊያደርግ አልቻለም። ዳርዮስ ለዳንኤል አምላክ አክብሮት የነበረው ይመስላል። ዳንኤል ስለ ባቢሎን ውድቀት ትንቢት እንዲናገር ያስቻለው ይሖዋ ነው። ከሌሎቹ የመንግሥቱ ባለ ሥልጣናት ሁሉ ለየት ብሎ እንዲታይ ያደረገውን “የላቀ መንፈስ የሰጠውም” አምላክ ነው። ምናልባትም ዳርዮስ ከብዙ አሥርተ ዓመታት በፊት ይኸው አምላክ ሦስቱን ወጣት ዕብራውያን ከእሳት እቶን ውስጥ እንዳወጣቸው ሳይሰማ አይቀርም። ዳርዮስ በፊርማው ያጸደቀውን ትእዛዝ መሻር ስላልቻለ አሁንም ይሖዋ ዳንኤልን ሊያድነው እንደሚችል ተስፋ ሳያደርግ አልቀረም። ከዚህ በኋላ ዳንኤል ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ ተጣለ።c “ድንጋይም አምጥተው በጉድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙበት፤ ንጉሡም በዳንኤል ላይ የተደረገው እንዳይለወጥ በቀለበቱና በመኳንንቱ ቀለበት አተመው።”—ዳንኤል 6:16, 17
ሁኔታዎች በአስገራሚ መንገድ ተለወጡ
17, 18. (ሀ) ዳርዮስ የዳንኤል ሁኔታ በጣም እንዳስጨነቀው የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ንጉሡ ወደ አንበሳው ጉድጓድ ሲመለስ ምን ዓይነት ሁኔታ ጠበቀው?
17 በሐዘን የተዋጠው ዳርዮስ ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ። በዚህ ወቅት ደስታው ሁሉ ጠፍቶ ስለነበር ሙዚቀኞች ወደ እርሱ እንዲገቡ አልፈለገም። ከዚህ ይልቅ ዳርዮስ ምንም እህል ሳይቀምስና ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ በዓይኑ ሳይዞር አደረ። “እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ።” ሲነጋም ዳርዮስ እየተጣደፈ ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ ሄደ። በሐዘንም በተሰበረ ድምፅ “የሕያው አምላክ ባሪያ ዳንኤል ሆይ፣ ሁልጊዜ የምታመልከው [“ሳታወላውል የምታገለግለው፣” NW] አምላክህ ከአንበሶች ያድንህ ዘንድ ችሎአልን?” ሲል ጠራው። (ዳንኤል 6:18-20) ዳርዮስ መልስ ሲሰማ ምንኛ ተገርሞና እፎይ ብሎ ይሆን!
18 “ንጉሥ ሆይ፣ ሺህ ዓመት ንገሥ።” ዳንኤል ይህን አክብሮት የተሞላበት ሰላምታ በማቅረብ በንጉሡ ላይ ምንም የጥላቻ ስሜት እንዳላደረበት አሳይቷል። ለደረሰበት ስደት ዋነኛ ቆስቋሾች በቅናት ያረሩት የመንግሥት አለቆችና መሳፍንት እንጂ ዳርዮስ እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። (ከማቴዎስ 5:44፤ ሥራ 7:60 ጋር አወዳድር።) ዳንኤል በመቀጠል:- “በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና፣ በአንተም ፊት ደግሞ፣ ንጉሥ ሆይ፣ አልበደልሁምና አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ፣ እነርሱም አልጎዱኝም አለው።”—ዳንኤል 6:21, 22
19. ዳርዮስ በመንግሥቱ አለቆችና በመሳፍንቱ የተታለለው እንዴት ነው?
19 ዳርዮስ እነዚህን ቃላት ሲሰማ እጅግ ተሰምቶት መሆን አለበት! ደግሞም ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ለመጣል የሚያበቃ ምንም ነገር እንዳልሠራ ያውቅ ነበር። ዳርዮስ፣ የመንግሥቱ አለቆችና መሳፍንቱ ዳንኤል እንዲገደል አሲረው እንደነበርና እርሱንም የራስ ወዳድነት ዓላማቸው ማስፈጸሚያ እንዳደረጉት በሚገባ ተረድቷል። በእነርሱ ውትወታ “የመንግሥቱ አለቆች ሁሉ” ውሳኔው እንዲተላለፍ ደግፈው የነበረ ሲሆን ጉዳዩን ዳንኤልም ጭምር እንደሚያውቀው አስመስለው አቅርበውት ነበር። ዳርዮስ ከእነዚህ መሠሪ ሰዎች ጋር ያለውን ጉዳይ በኋላ ይጨርሳል። መጀመሪያ ግን ዳንኤልን ከአንበሶቹ ጉድጓድ እንዲያወጡት አዘዘ። ዳንኤል ትንሽ እንኳ ሳይጫር በተዓምራዊ ሁኔታ ወጣ!—ዳንኤል 6:23
20. ተንኮለኞቹ የዳንኤል ጠላቶች መጨረሻቸው ምን ሆነ?
20 ዳንኤል ደህና መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ዳርዮስ የሚጨርሰው ሌላ ጉዳይ ነበረው። “ንጉሡም አዘዘ፣ ዳንኤልንም የከሰሱ እነዚያን ሰዎች አመጡአቸው፣ እነርሱንና ልጆቻቸውንም ሚስቶቻቸውንም በአንበሶች ጉድጓድ ጣሉአቸው፤ ወደ ጉድጓዱም መጨረሻ ሳይደርሱ አንበሶች ያዙአቸው አጥንታቸውንም ሁሉ ሰባበሩ።”d—ዳንኤል 6:24
21. ኃጢአት የፈጸሙ የቤተሰብ አባላትን በሚመለከት በሙሴ ሕግና በጥንት ባሕሎች ሕግ መካከል ምን ልዩነት ነበር?
21 ያሴሩትን ሰዎች ብቻ ሳይሆን ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ጨምሮ ማስገደሉ ምክንያታዊነት የጎደለው ጭካኔ ሊመስል ይችላል። ከዚህ በተቃራኒ አምላክ ለሙሴ የሰጠው ሕግ “አባቶች ስለ ልጆች አይገደሉ፣ ልጆችም ስለ አባቶች አይገደሉ፤ ነገር ግን ሁሉ እያንዳንዱ በኃጢአቱ ይገደል” ይላል። (ዘዳግም 24:16) ሆኖም በአንዳንድ የጥንት ባሕሎች ውስጥ ከባድ ወንጀል በሚፈጸምበት ጊዜ ከበደለኛው ሰው ጋር የቤተሰቡን አባላት ጨምሮ መግደል እንግዳ ነገር አልነበረም። ይህም የሚደረገው የቤተሰቡ አባላት የኋላ ኋላ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ እንዳይነሳሱ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ በመንግሥቱ አለቆችና በመሳፍንቱ ቤተሰቦች ላይ በተወሰደው በዚህ እርምጃ የዳንኤል እጅ እንደሌለበት ግልጽ ነው። እነዚህ ክፉ ሰዎች በቤተሰቦቻቸው ላይ ባመጡት መከራ እጅግ እንዳዘነ ምንም ጥርጥር የለውም።
22. ዳርዮስ ምን አዲስ አዋጅ አስነገረ?
22 ሲዶልቱ የነበሩት የመንግሥት አለቆችና መሳፍንት ተሰናብተዋል። ዳርዮስ እንዲህ የሚል አዋጅ አስነገረ:- “በመንግሥቴ ግዛት ሁሉ ያሉ ሰዎች በዳንኤል አምላክ ፊት እንዲፈሩና እንዲንቀጠቀጡ አዝዣለሁ፤ እርሱ ሕያው አምላክ ለዘላለም የሚኖር ነውና፤ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፣ ግዛቱም እስከ መጨረሻ ድረስ ይኖራል። ያድናል ይታደግማል፣ በሰማይና በምድርም ተአምራትንና ድንቅን ይሠራል፣ ዳንኤልንም ከአንበሶች አፍ አድኖታል።”—ዳንኤል 6:25-27
አምላክን ሳታወላውል አገልግል
23. ዳንኤል ሰብዓዊ ሥራውን በሚመለከት ምን ምሳሌ ትቷል? እኛስ እርሱን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
23 ዳንኤል ዛሬ ላሉት የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ግሩም ምሳሌ ትቷል። አኗኗሩ ምን ጊዜም ከነቀፋ ነፃ ነበር። ዳንኤል በሰብዓዊ ሥራው ‘የታመነ ሰው የነበረ ሲሆን ስህተትና በደል አልተገኘበትም።’ (ዳንኤል 6:4) በተመሳሳይም አንድ ክርስቲያን ተቀጥሮ የሚሠራውን ሥራ በትጋት ማከናወን አለበት። ይህ ማለት ግን ራሱ ብቻ በቁሳዊ ነገሮች ለመበልጸግ ሲል በሰዎች ጉሮሮ ላይ የሚቆምና በሌሎች ላይ እየተረማመደ ለማደግ የሚሞክር ሰው መሆን አለበት ማለት አይደለም። (1 ጢሞቴዎስ 6:10) አንድ ክርስቲያን ‘ለይሖዋ እንደሚያደርገው በማሰብ’ ሌሎች ግዴታዎቹን በሐቀኝነትና በሙሉ ልብ መፈጸም እንዳለበት ቅዱሳን ጽሑፎች ያዝዛሉ።—ቆላስይስ 3:22, 23፤ ቲቶ 2:7, 8፤ ዕብራውያን 13:18
24. ዳንኤል በአምልኮ ጉዳዮች ረገድ አቋሙን የሚያላላ ሰው አለመሆኑን ያረጋገጠው እንዴት ነው?
24 ዳንኤል በአምልኮ ጉዳዮች ረገድ አቋሙን የሚያላላ ሰው አልነበረም። የጸሎት ልማዱ በግልጽ የሚታወቅ ነበር። ከዚህም በላይ የመንግሥቱ አለቆችና መሳፍንቱ ዳንኤል ለአምልኮቱ ጥብቅ እንደሆነ ያውቁ ነበር። ሕግም ቢከለክለው እንኳ ልማዱን እንደማይተው እርግጠኞች ነበሩ። በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! እነርሱም ቢሆኑ ለአምላክ ለሚያቀርቡት አምልኮ ቀዳሚውን ቦታ በመስጠት በኩል ጥሩ ስም አትርፈዋል። (ማቴዎስ 6:33) ይህ ለተመልካች ሁሉ ግልጽ ሆኖ መታየት ያለበት ነገር ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዲህ ብሎ አዝዟል:- “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።”—ማቴዎስ 5:16
25, 26. (ሀ) አንዳንዶች ዳንኤል ስላደረገው ነገር ምን ብለው ይደመድሙ ይሆናል? (ለ) ዳንኤል ልማዱን መተዉ አቋሙን እንዳላላ ሊያስቆጥርበት እንደሚችል አድርጎ የተመለከተው ለምንድን ነው?
25 አንዳንድ ሰዎች:- ዳንኤል ለ30 ቀናት ያህል ብቻ በምሥጢር ወደ ይሖዋ በመጸለይ ከስደቱ ሊያመልጥ ይችል ነበር። ደግሞም አምላክ ጸሎታችን እንዲሰማው የግድ አንድ ዓይነት ቦታ ወይም አቀማመጥ ሊኖረን አያስፈልግም። እርሱ የልባችንን ሐሳብ እንኳ ማስተዋል ይችላል ይሉ ይሆናል። (መዝሙር 19:14) የሆነ ሆኖ ዳንኤል ከታወቀው ልማዱ የተለየ ነገር ቢያደርግ አቋሙን እንዳላላ ሊያስቆጥርበት እንደሚችል አድርጎ ተመልክቶታል። ለምን?
26 የዳንኤል የጸሎት ልማድ በሰፊው የታወቀ ነገር ስለነበር ድንገት ይህን ልማዱን ቢያቋርጥ ምን ማለት ይሆን ነበር? ይህን ያዩ ሰዎች ዳንኤል ሰውን እንደሚፈራና የንጉሡ ሕግ ከይሖዋ ሕግ እንደሚልቅ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። (መዝሙር 118:6) ይሁንና ዳንኤል ያደረገው ነገር ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ አምልኮ እንደሚያቀርብ የሚያሳይ ነበር። (ዘዳግም 6:14, 15፤ ኢሳይያስ 42:8) እርግጥ ዳንኤል ይህን ሲያደርግ ለንጉሡ ሕግ ንቀት አሳይቷል ማለት አይደለም። አቋሙን በማላላትም ወደ ኋላ አላፈገፈገም። ዳንኤል ንጉሡ ትእዛዙን ከማውጣቱ በፊትም ‘ያደርገው እንደ ነበረ’ በቤቱ አናት ላይ ባለው እልፍኙ መጸለዩን ቀጥሏል።
27. ዛሬ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች (ሀ) በበላይ ላሉ ባለ ሥልጣኖች በመገዛት ረገድ (ለ) ከአምላክ ይልቅ ለሰው በመታዘዝ ረገድ (ሐ) ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም በመኖር ረገድ የዳንኤልን ምሳሌ ሊከተሉ የሚችሉት እንዴት ነው?
27 ዛሬ ያሉት የአምላክ አገልጋዮችም ከዳንኤል ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ። የሚኖሩበትን አገር ሕግ በመታዘዝ ‘በበላይ ላሉ ባለ ሥልጣኖች ይገዛሉ።’ (ሮሜ 13:1) ይሁን እንጂ የሰዎች ሕግ ከአምላክ ሕግ ጋር በሚጋጭበት ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ሲሉ በድፍረት የተናገሩትን የኢየሱስን ሐዋርያት አቋም ይከተላሉ። (ሥራ 5:29) ክርስቲያኖች ይህን ማድረጋቸው ክህደትን ወይም ዓመፅን ማበረታታቸው አይደለም። ከዚህ ይልቅ እንዲያውም ‘ለአምላክ ያደሩ በመሆን በጭምትነት ጸጥና ዝግ ብለው መኖር ይችሉ ዘንድ’ ግባቸው ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም መኖር ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2፤ ሮሜ 12:18
28. ዳንኤል ይሖዋን ‘ሳያወላውል ያገለገለው’ እንዴት ነው?
28 ዳንኤል አምላክን ‘ሳያወላውል ማገልገሉን’ ዳርዮስ በሁለት የተለያዩ አጋጣሚዎች ጠቅሷል። (ዳንኤል 6:16, 20 NW) “ያለማወላወል” ተብሎ የተተረጎመው የአረማይክ መሠረታዊ ቃል “በእሽክርክሪት ውስጥ መዞር” የሚል ትርጉም አለው። ማቆሚያ የሌለውን ዑደት ወይም ዘላቂነት ያለውን ነገር ያመለክታል። የዳንኤል የአቋም ጽናትም እንደዚሁ ነበር። ወጥ የሆነ ጎዳና ተከትሏል። ትንሽም ይሁን ትልቅ ዳንኤል ፈተና ሲገጥመው ምን እንደሚያደርግ ለማንም ግልጽ ነበር። ከብዙ አሥርተ ዓመታት በፊት በጀመረው ለይሖዋ ታማኝ የመሆን ጎዳና መመላለሱን ይቀጥላል።
29. ዛሬ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ከዳንኤል የታማኝነት ጎዳና የሚጠቀሙት እንዴት ነው?
29 የዘመናችን የአምላክ አገልጋዮችም የዳንኤልን ዓይነት ጎዳና ለመከተል ይፈልጋሉ። ሐዋርያው ጳውሎስም፣ ሁሉም ክርስቲያኖች ጥንት የነበሩትን ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ምሳሌ እንዲያስቡ መክሯል። በእምነት “ጽድቅን አደረጉ፣ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ” ካለ በኋላ ዳንኤልን ሲጠቅስ ይመስላል፣ “የአንበሶችን አፍ ዘጉ” ብሏል። በዛሬው ጊዜ የምንኖር የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ዳንኤል የነበረውን ዓይነት እምነት በማሳየትና ያለማወላወል በማገልገል “በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት [“በጽናት፣” NW] እንሩጥ።”—ዕብራውያን 11:32, 33፤ 12:1
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የምሥራቃውያን ገዥዎች ብዙውን ጊዜ አራዊት ያሉባቸው መናፈሻዎች እንደነበሯቸው የሚገልጹ ተቀርጸው የተገኙ ጥንታዊ ጽሑፎች በባቢሎን ‘የአንበሶች ጉድጓድ’ መኖሩን የሚደግፉ ማስረጃዎች ናቸው።
b በቤቱ አናት ላይ የሚገኘው ክፍል አንድ ሰው እንዳይረበሽ ሲፈልግ ከሰው ገለል ብሎ የሚያርፍበት እልፍኝ ነው።
c የአንበሶቹ ጉድጓድ ከላይ አፍ ያለው የምድር ውስጥ ቤት ሊሆን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ለእንስሶቹ መግቢያ የሚሆን በር ወይም ተከፋች እንደነበረው እሙን ነው።
d ‘መክሰስ’ የሚለው ቃል “ስም ማጥፋት” ተብሎም ሊተረጎም ከሚችል የአረማይክ አገላለጽ የተተረጎመ ነው። ይህም የዳንኤል ጠላቶች የነበራቸውን ተንኮል ያዘለ ሐሳብ የሚያጎላ ነው።
ምን አስተውለሃል?
• ሜዶናዊው ዳርዮስ ዳንኤልን በከፍተኛ የሥልጣን ቦታ ላይ ለማስቀመጥ የፈለገው ለምንድን ነው?
• የመንግሥቱ አለቆችና መሳፍንቱ የጠነሰሱት መሠሪ ሴራ ምን ነበር? ይሖዋ ዳንኤልን ያዳነው እንዴት ነው?
• የዳንኤልን የታማኝነት ምሳሌ በትኩረት በመከታተል ምን ትምህርት አግኝተሃል?
[በገጽ 114 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]
[በገጽ 121 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]
[በገጽ 127 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳንኤል ‘ሳያወላውል’ ይሖዋን አገልግሏል። አንተስ?