ወደ አምላክ ቅረብ
“በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ”
መጽሐፍ ቅዱስ “በየትኛውም ጊዜ ቢሆን አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም” በማለት ይናገራል። (ዮሐንስ 1:18) የአምላክ ክብር እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ እሱን አይቶ ሊኖር የሚችል ሥጋ ለባሽ የለም። (ዘፀአት 33:20) ይሁን እንጂ ይሖዋ በሰማይ ያሉ ነገሮችን በራእይ እንዲመለከቱ መብት ስለሰጣቸው ሰዎች የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች አሉ። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ነቢዩ ዳንኤል ነው። ዳንኤል የተመለከተው ነገር በአድናቆት እንዲዋጥ አድርጎት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፤ እኛም ይህን ራእይ ስናነብ የዳንኤል ዓይነት ስሜት እንደሚያድርብን የታወቀ ነው። ዳንኤል በራእይ የተመለከተውን አስደናቂ ነገር እንዴት እንደገለጸው እስቲ እንመልከት።a—ዳንኤል 7:9, 10ን አንብብ።
“በዘመናት የሸመገለው።” (የ1954 ትርጉም) “በዘመናት የሸመገለው” የሚለውን የማዕረግ ስም የተጠቀመው ዳንኤል ብቻ ነው። (ዳንኤል 7:9, 13, 22) ይሖዋ የሸመገለ ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ‘የዘላለም ንጉሥ’ እንደመሆኑ መጠን መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ የለውም። (1 ጢሞቴዎስ 1:17፤ ይሁዳ 25) አምላክ ዘላለማዊ በመሆኑ ይህ ነው የማይባል ጥበብ እንዳለው እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ረጅም ዕድሜ መኖርን ጠቢብ ከመሆን ጋር ያያይዘዋል። (ኢዮብ 12:12) የማሰብ ችሎታችን ውስን በመሆኑ አምላክ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ የለውም የሚለውን ሐሳብ መረዳት አዳጋች እንደሚሆንብን የታወቀ ነው። ለነገሩ በጥበቡ ተወዳዳሪ የሌለውን አምላክ ሙሉ በሙሉ ማወቅ እንዴት ይቻላል?—ሮም 11:33, 34
ጥቅሱ በዘመናት የሸመገለው “ተቀመጠ” እንደሚል ልብ በል። የተቀመጠው ለምንድን ነው? በዙሪያው ባሉ ጥቅሶች ላይ የሚገኙት “የፍርድ ጉባኤ፣” “እስኪፈርድላቸው” እና “የፍርድ ዙፋን” የሚሉት አገላለጾች ፍንጭ ይሰጡናል። (ዳንኤል 7:10, 22, 26) ከእነዚህ ጥቅሶች በመነሳት ይሖዋ በራእዩ ላይ የተቀመጠው ፍርድ ለመስጠት እንደሆነ መረዳት እንችላለን። ይሖዋ የሚፈርደው በማን ላይ ነው? ቀደም ሲል ዳንኤል ባየው ራእይ ላይ በአራዊት በተመሰሉት በምድር መንግሥታት ላይ ነው።b (ዳንኤል 7:1-8) ታዲያ ይሖዋ ምን ዓይነት ዳኛ ነው?
“ልብሱ እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፤ የራሱም ጠጕር እንደ ጥጥ ነጭ ነበረ።” ነጭ የሚለው ቃል ጻድቅ እና ንጹሕ መሆንን ያመለክታል። ፀጉሩ እንደ ጥጥ ነው መባሉም ነጭ መሆኑን ያመለክታል። ዳንኤል በራእይ የተመለከተው ምን እንደሆነ በዓይነ ሕሊናህ መሳል ትችላለህ? ፀጉሩ ነጭ የሆነና ምናልባትም እንደ በረዶ የነጣ መጎናጸፊያ የለበሰ ዳኛ ወደ አእምሮህ መጣ? ይህ ሥዕላዊ አገላለጽ ይሖዋ የሚፈርደው በጽድቅና በጥበብ እንደሆነ እንድንተማመን ያደርገናል። በእርግጥም ይሖዋ በሙሉ ልባችን ልንተማመንበትና ጥልቅ አክብሮት ልንቸረው የሚገባ ዳኛ ነው።
ይሖዋ በሙሉ ልባችን ልንተማመንበትና ጥልቅ አክብሮት ልንቸረው የሚገባ ዳኛ ነው
“ሺህ ጊዜ ሺሆች ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍ በፊቱ ቆመዋል።” እነዚህ በሰማይ ያሉ አገልጋዮች እነማን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ መላእክትን “[የአምላክ] አገልጋዮች” ብሎ ይጠራቸዋል። (መዝሙር 104:4) በመቶ ሚሊዮኖች እንደሚቆጠሩ የሚገመቱት የአምላክ መላእክት ምንጊዜም ‘ለቃሉ ይታዘዛሉ’ እንዲሁም ‘ፈቃዱን ይፈጽማሉ።’ (መዝሙር 103:20, 21) ይህስ ቢሆን አምላክ ይህ ነው የማይባል ጥበብ እንዳለው የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ አይደለም? ደግሞስ ከይሖዋ ሌላ ይህን የሚያህል ግዙፍ የሰማይ ሠራዊት ማደራጀትና ሕልቆ መሣፍርት ለሌላቸው ዘመናት በሥራ እንዲጠመዱ ማድረግ የሚችለው ማን ነው?
ዳንኤል የተመለከተው ራእይ በዘመናት በሸመገለው ማለትም በይሖዋ ላይ እምነት እንድንጥል ይረዳናል። ፍርዶቹ ትክክል ሲሆኑ ጥበቡም ቢሆን እንድንተማመንበት የሚያደርግ ነው። ታዲያ እጅግ ጠቢብ ወደሆነው አምላክ ይበልጥ መቅረብ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለምን አትማርም?
በጥቅምት ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦
ከዳንኤል 4-12 እስከ ሆሴዕ 1-14
a እርግጥ ነው፣ ዳንኤል ቃል በቃል አምላክን አላየውም። ከዚህ ይልቅ አምላክ፣ ዳንኤል በአእምሮው ውስጥ ጥርት ያለ ምስል እንዲታየው አድርጓል። ዳንኤል፣ የተመለከተውን ራእይ ለመግለጽ ለሰዎች የሚሠራባቸውን መግለጫዎች ተጠቅሟል። እነዚህ ዘይቤያዊ አገላለጾች አምላክን ሊገባን በሚችል መንገድ ለመግለጽ የተቀመጡ ናቸው፤ በመሆኑም እነዚህን መግለጫዎች ቃል በቃል ልንወስዳቸው አይገባም።
b ዳንኤል በራእይ ስለተመለከታቸው አራዊት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ተመልከት።