የአንባብያን ጥያቄዎች
የዳንኤልን ትንቢቶች “ በመጠበቂያ ግንብ” ላይ በተብራራው መሠረት በማጥናታችን ተደስተናል። ይሁን እንጂ በራእይ 11:3 ላይ ያለው የሦስት ዘመን ተኩል የጊዜ ርዝመት “ የራእይ መደምደሚያ” በተባለው መጽሐፍ ላይ ካለው የተለየ ማብራሪያ የተሰጠው ለምንድን ነው?
እርግጥ ነው፣ የኅዳር 1, 1993 መጠበቂያ ግንብ ራእይ 11:3 ዘመናዊ ፍጻሜ ያገኘበትን የጊዜ ርዝመት በተመለከተ ትንሽ ማስተካከያ አድርጓል። ለምን?
በመጀመሪያ ስለ “አርባ ሁለት ወር” የሚናገረውን ራእይ 11:2ን እንመልከት። ከዚያም ቁጥር 3 ላይ በመቀጠል “ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ” የሚል እናነባለን። ይህ የተፈጸመው መቼ ነው?
“የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” በ1914 ካበቁ በኋላ ይህ ትንቢት በመንፈስ በተቀቡት ክርስቲያኖች ላይ ፍጻሜውን እንዳገኘ የይሖዋ ምሥክሮች ቀደም ብለው ተገንዝበው ነበር። (ሉቃስ 21:24፤ 2 ቆሮንቶስ 1:21, 22) ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!a (1988) የተባለው መጽሐፍ ይህን አስመልክቶ ሐሳብ ሲሰጥ በገጽ 164 ላይ እንዲህ ይላል፦ “የአምላክ ሕዝቦች እዚህ ላይ በትንቢት ከተነገረው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ከባድ ሁኔታ የደረሰባቸው ለሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ነበር። ይህም ጊዜ አንደኛው የዓለም ጦርነት ከጀመረበት ከ1914 ማብቂያ እስከ 1918 የመጀመሪያ ወራት ድረስ ያለው ነው።”
እዚህ ላይ የቀረበው የጊዜ ርዝመት “አንደኛው የዓለም ጦርነት ከጀመረበት ከ1914 ማብቂያ እስከ 1918 የመጀመሪያ ወራት ድረስ ያለው” መሆኑን ልብ በል። ይህም “ በዚያን ጊዜ የአምላክ ምስጢር አለቀ” (1969)b በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 261–4 ላይ በተደጋጋሚ ከቀረበው የጊዜ ርዝመት ጋር ይመሳሰላል።
ይሁን እንጂ መጠበቂያ ግንቡ ያተኮረው በዳንኤል ውስጥ ባሉት ትንቢቶች ላይ ነው። የዳንኤል መጽሐፍ ደግሞ በኋላ በራእይ ውስጥ 3 1/2 ዓመት ወይም 42 ወር በሚል ከተገለጸው ጋር የሚመጣጠነውን የጊዜ ርዝመት ሁለት ጊዜ ይገልጻል። በቀጥታ ለመጥቀስ ያህል ዳንኤል 7:25 የአምላክ ቅዱሳን “እስከ ዘመንና እስከ ዘመናት እስከ እኩሌታ ዘመንም” ወይም እስከ 3 1/2 ዘመን እንደሚንገላቱ ይናገራል። ከዚያም በኋላ ዳንኤል 12:7 “ለዘመንና ለዘመናት ለዘመንም እኩሌታ” ወይም ለ3 1/2 ዘመን “የተቀደሰውም ሕዝብ ኃይል መበተን በተጨረሰ ጊዜ ይህ ሁሉ ይፈጸማል” በማለት ትንቢት ይናገራል።
ስለዚህ በዳንኤል 7:25፣ በዳንኤል 12:7 እና በራእይ 11:2, 3 እንዲሁም በራእይ 13:5 ላይ ተመሳሳይ ስለሆነ የጊዜ ርዝመት የሚናገሩ ትንቢቶችን እናገኛለን። እነዚህ ትንቢቶች በሙሉ ከ1914–18 ባለው ጊዜ ውስጥ ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ጽሑፎቻችን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህን ትንቢቶች በተናጠል ሲያብራሩ ቀኖቹ የሚጀምሩበትና የሚያበቁበት ጊዜ ትንሽ ይለያያል።
ሆኖም የኅዳር 1, 1993 መጠበቂያ ግንብ “እነዚህ ሁሉ ጎን ለጎን የሚሄዱ ትንቢቶች የተፈጸሙት እንዴት ነበር?” ሲል ጠይቋል። አዎን፣ በዳንኤል 7:25፣ በዳንኤል 12:7 እና በራእይ 11:3 ላይ ያሉት ስለ ሦስት ዘመን ተኩል የሚናገሩት ትንቢቶች “ጎን ለጎን የሚሄዱ” እንደሆኑ ተደርገው ተወስደዋል። ስለዚህ የሚጀምሩበትም ሆነ የሚያበቁበት ጊዜ ተመሳሳይ ይሆናል።
መጽሔቱ እነዚህ ትንቢቶች የሚያበቁበትን ጊዜ አስመልክቶ በሰኔ 1918 ጄ ኤፍ ራዘርፎርድና ሌሎች የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ዲሬክተሮች “በሐሰት ተከስሰው የረጅም ጊዜ እስራት በተበየነባቸው” ጊዜ በአምላክ ቅቡአን (ዳንኤል 7:25) ላይ የሚደርሰው አስጨናቂ መከራ እንዴት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ገልጿል። ይህ ሁኔታ በዳንኤል 12:7 ላይ እንደተገለጸው ‘የተቀደሰው ሕዝብ ኃይል መበተን የተጨረሰበት ጊዜ’ እንደሆነ የተረጋገጠ ነው።
ከሰኔ 1918 ጀምረን ወደኋላ ስንቆጥር የ3 1/2 ዘመን የጀመረበት ታኅሣሥ 1914 ላይ እንደርሳለን። በዚህ የ1914 የመጨረሻ ወር ላይ በምድር ላይ ያሉት የአምላክ ቅቡዓን “‘እኔ ልጠጣው ያለውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁን?’ የሚለው ማቴዎስ 20:20–23” የመጪው ዓመት ጥቅስ እንደሚሆን ተገንዝበው ነበር። ይህን ጥቅስ ያስተዋወቀው ርዕስ “በ1915 ከበጉ ጎን በሚቆሙት ታማኝ ተከታዮች ላይ የሚደርስ አንድ ልዩ ፈተናና የመከራ ጽዋ ወይም መዋረድ ይኖር እንደሆነ ማን ያውቃል!” ሲል አስጠንቅቆ ነበር። በዳንኤል 7:25 እንደተተነበየው ይህ የ3 1/2 ዘመን ጊዜ ‘የልዑሉን ቅዱሳን ማስጨነቅ ቀጠለ።’ መንግሥታት ወደ አንደኛው የዓለም ጦርነት ገብተው ስለነበረ በእነርሱ ላይ የፈለጉትን ግፍ ለመሥራት ቀላል ሆኖላቸው ነበር። ወደማ ጠቃለያው ስንመጣ በዳንኤል 7:25፣ 12:7 እና በራእይ 11:3 ላይ ያሉት ሦስቱም ተመሳሳይ ጥቅሶች 3 1/2 ዓመታት ወይም 42 ወራት ፍጻሜያቸውን ያገኙት ከታኅሣሥ 1914 እስከ ሰኔ 1918 ድረስ ባለው የጊዜ ርዝመት ነው።
ይህም ራእይ 11:3 ፍጻሜውን ያገኘበትን ጊዜ በተመለከተ የተደረገውን ትንሽ ማሻሻያ ይገልጻል። ወደፊት የራእይ መደምደሚያ የተባለውን መጽሐፍ በምናጠናበትም ሆነ በምንጠቀምበት ጊዜ ይህን ማስተካከያ በአእምሮአችን መያዝ እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
b በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።