ምዕራፍ ሦስት
ተፈትነው ለይሖዋ ታማኝ ሆነው የተገኙ!
1, 2. ለዳንኤል ዘገባ እንደ መቅድም ሆነው ያገለገሉት ጉልህ ክንውኖች ምንድን ናቸው?
በትንቢታዊው የዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የትዕይንቱ መጋረጃ የሚገለጠው በዓለም አቀፉ መድረክ እጅግ ከፍተኛ ለውጦች በሚካሄዱበት ወቅት ነው። አሦር ዋና ከተማዋን ነነዌን ካጣች ብዙም አልቆየችም። ግብጽ ከይሁዳ ምድር በስተ ደቡብ የምትገኝ እምብዛም ጉልህ ሥፍራ የሌላት ግዛት ሆናለች። ባቢሎን ደግሞ የዓለምን የበላይነት ለመቀዳጀት በሚደረገው ትግል ልዕለ ኃያል ለመሆን እየገሰገሰች ነው።
2 በ625 ከዘአበ የግብጹ ፈርዖን ኒካዑ ባቢሎናውያን በስተ ደቡብ በኩል የሚያደርጉትን መስፋፋት ለመግታት የሞት ሽረት ትግል አድርጎ ነበር። ለዚህም ሲል ሠራዊቱን በላይኛው ኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ከርከሚሽ አንቀሳቀሰ። የከርከሚሽ ጦርነት በመባል የሚታወቀው ይህ ውጊያ ወሳኝ ታሪካዊ ክስተት ነበር። በአልጋ ወራሹ በናቡከደነፆር የሚመራው የባቢሎናውያን ሠራዊት የፈርዖን ኒካዑን ኃይሎች ድባቅ መታቸው። (ኤርምያስ 46:2) ናቡከደነፆር በድል ግስጋሴው ቀጥሎ ሶርያንና ፍልስጤምን ሁሉ በመጠራረግ በአካባቢው የነበረውን የግብፅ የበላይነት ሊያዳፍነው ምንም አልቀረውም ነበር። ትንሽም ዘመቻው እንዲገታ ያደረገው የአባቱ የናቦፖላሳር ሞት ነው።
3. ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ላይ ያደረገው የመጀመሪያው ዘመቻ ውጤት ምን ነበር?
3 የባቢሎን ንጉሥ ተብሎ መንበረ ሥልጣኑን የጨበጠው ናቡከደነፆር በቀጣዩ ዓመት ትኩረቱን ዳግም በሶርያና በፍልስጤም ላይ ወደሚያደርገው ወታደራዊ ዘመቻ መለስ አደረገ። ወደ ኢየሩሳሌምም ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣው በዚህ ወቅት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይዘግባል:- “በእርሱም ዘመን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወጣ፣ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ተገዛለት፤ ከዚያም በኋላ ዘወር አለና ዐመፀበት።”—2 ነገሥት 24:1
ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም
4. በዳንኤል 1:1 ላይ የሚገኘውን “ኢዮአቄም በነገሠ በሦስተኛው ዓመት” የሚለውን መግለጫ ልንረዳው የሚገባን እንዴት ነው?
4 “ሦስት ዓመት” የሚለው መግለጫ በእጅጉ ትኩረታችንን የሚስብ ነው። ምክንያቱም የዳንኤል መጽሐፍም የሚጀምረው እንደሚከተለው በማለት ነው:- “የይሁዳ ንጉሥ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ከበባት።” (ዳንኤል 1:1) ከ628 እስከ 618 ከዘአበ ያስተዳደረው ኢዮአቄም ንጉሥ በሆነ በሦስተኛው ዓመት ናቡከደነፆር ገና አልጋ ወራሽ እንጂ “የባቢሎን ንጉሥ” አልነበረም። ናቡከደነፆር በ620 ከዘአበ ኢዮአቄም ግብር እንዲከፍል ጭኖበት ነበር። ይሁን እንጂ ኢዮአቄም ከሦስት ዓመታት ገደማ በኋላ ዓመፀ። በመሆኑም ንጉሥ ናቡከደነፆር ዓመፀኛውን ኢዮአቄም ለመቅጣት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም የመጣው በ618 ከዘአበ ወይም ኢዮአቄም የባቢሎን እንደራሴ ሆኖ ንግሥናውን በጨበጠ በሦስተኛው ዓመት ነበር።
5. ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ላይ ያካሄደው ሁለተኛ ዘመቻ ውጤት ምን ነበር?
5 የከበባው ውጤት “ጌታም የይሁዳን ንጉሥ ኢዮአቄምን ከእግዚአብሔርም ቤት ዕቃ ከፍሎ በእጁ አሳልፎ ሰጠው” ተብሎ ተገልጿል። (ዳንኤል 1:2) ሆነ ተብሎ በተቀነባበረ ሴራም ይሁን በተቀሰቀሰው ዓመፅ ኢዮአቄም የተገደለው በከበባው መጀመሪያ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። (ኤርምያስ 22:18, 19) በ618 ከዘአበ የ18 ዓመት ልጁ ዮአኪን በእርሱ ፋንታ ነገሠ። ይሁን እንጂ የዮአኪን ግዛት የዘለቀው ለሦስት ወር ከአሥር ቀን ብቻ ሲሆን ከዚያ በኋላ በ617 ከዘአበ ሥልጣኑን አስረክቧል።—ከ2 ነገሥት 24:10-15 ጋር አወዳድር።
6. ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የወሰዳቸውን ንዋየ ቅድሳት ምን አደረጋቸው?
6 ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ንዋየ ቅድሳት ዘርፎ “ወደ ሰናዖር ምድር ወደ አምላኩ ቤት ወሰደው፣ ዕቃውንም” ማርዱክ ወይም በዕብራይስጥ ሜሮዳክ ወደሚባለው “አምላኩ ግምጃ ቤት አስገባው።” (ዳንኤል 1:2፤ ኤርምያስ 50:2) ናቡከደነፆር የማርዱክን ቤተ መቅደስ በሚመለከት እንደሚከተለው ማለቱን የሚዘግብ አንድ የባቢሎናውያን ጽሑፍ ተገኝቷል:- “በውስጡም ብርና ወርቅ እንዲሁም የከበሩ ድንጋዮችን አኖርኩ . . . የመንግሥቴም ግምጃ ቤት አደረግሁት።” ከንጉሥ ብልጣሶር ዘመነ መንግሥት ጋር ተያይዞም ስለ እነዚሁ ንዋየ ቅድሳት ተጠቅሶ እናገኛለን።—ዳንኤል 5:1-4
የኢየሩሳሌም ወጣቶች ቁንጮ
7, 8. ከዳንኤል 1:3, 4 እና 6 ስለ ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ትውልድ ምን ብለን መደምደም እንችላለን?
7 ወደ ባቢሎን የተጋዘው በይሖዋ ቤተ መቅደስ ያለው ዕቃ ብቻ አልነበረም። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ንጉሡም ነውር የሌለባቸውንና መልከ መልካሞቹን፣ በጥበብ ሁሉ የሚያስተውሉትን እውቀትም የሞላባቸውን ብልሃተኞችና አስተዋዮች የሆኑትን፣ በንጉሡም ቤት መቆም የሚችሉትን ብላቴኖች ከእስራኤል ልጆች ከነገሥታቱና ከመሳፍንቱ ዘር ያመጣ ዘንድ . . . ለጃንደረቦቹ አለቃ ለአስፋኔዝ ነገረ።”—ዳንኤል 1:3, 4
8 የተመረጡት እነማን ነበሩ? እንዲህ የሚል እናነባለን:- “በእነዚህም መካከል ከይሁዳ ልጆች ዳንኤልና አናንያ ሚሳኤልና አዛርያ ነበሩ።” (ዳንኤል 1:6) ይህም የዳንኤልና የጓደኞቹን ትውልድ እንድናውቅ ፍንጭ ይሰጠናል። ይህ መግለጫ ባይሰጥ ኖሮ ስለ ትውልድ ሐረጋቸው ማወቅ አንችልም ነበር። ለምሳሌ ያህል ‘የይሁዳ ልጆች’ እንደሆኑ መገለጹ የነገሥታት መገኛ ከሆነው ነገድ የመጡ መሆናቸውን ያሳያል። በነገሥታት መስመር የነበሩ ሆኑም አልሆኑ ቢያንስ ከፍ ያለ ግምት ከሚሰጣቸው ቤተሰቦች የተገኙ ናቸው ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ይሆናል። ሁሉም “ልጆች” በሚባሉበት በለጋ ዕድሜያቸው፣ ምናልባትም በአሥራዎቹ ዕድሜያቸው መጀመሪያ ላይ ሳይሆን አይቀርም ጤናማ አእምሮና አካል እንዲሁም ጥልቅ ማስተዋል፣ ጥበብና እውቀት ነበራቸው። ዳንኤልና ጓደኞቹ ግሩም ችሎታ የነበራቸው በሌላ አባባል የኢየሩሳሌም ወጣቶች ቁንጮ ነበሩ ለማለት ይቻላል።
9. ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች ነበሯቸው ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?
9 ዘገባው የእነዚህ ልጆች ወላጆች እነማን እንደነበሩ አይነግረንም። የሆነ ሆኖ የወላጅነት ኃላፊነታቸውን አክብደው ይመለከቱ የነበሩ አምላካዊ አክብሮት ያላቸው ግለሰቦች እንደነበሩ ግልጽ ነው። በወቅቱ በኢየሩሳሌም በተለይም ደግሞ ‘በንጉሣዊ ቤተሰብ ልጆችና በመኳንንቱ’ ዘንድ በእጅጉ ተስፋፍቶ የነበረውን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ውድቀት ስናስብ ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ያሳዩአቸው ድንቅ ባሕርያት እንዲሁ ባጋጣሚ የመጡ እንዳልሆኑ የታወቀ ነው። እነዚህ ወላጆች የልጆቻቸው ወደ ሩቅ አገር መወሰድ እጅግ እንዳሳዘናቸው መገመት አያዳግትም። የመጨረሻውን ውጤት ማወቅ ቢችሉ ኖሮ በልጆቻቸው እጅጉን በኮሩ ነበር! ወላጆች ልጆቻቸውን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” ማሳደጋቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው!—ኤፌሶን 6:4
አእምሮአቸውን ለመቅረጽ የተደረገ ትግል
10. ወጣቶቹ ዕብራውያን የተሰጣቸው ትምህርት ምን ነበር? ዓላማውስ ምንድን ነው?
10 ብዙም ሳይቆይ በግዞት የተወሰዱትን የእነዚህን ወጣቶች አእምሮ ለመቅረጽ ትግል ተጀመረ። ዕብራውያኑ ልጆች ከባቢሎናውያን ሥርዓት ጋር እንዲስማሙ ለማድረግ ሲባል ናቡከደነፆር “የከለዳውያንንም ትምህርትና ቋንቋ ያስተምሯቸው ዘንድ” ጃንደረቦቹን አዘዘ። (ዳንኤል 1:4) ይህ ዝም ብሎ ተራ ትምህርት አልነበረም። ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክለፒዲያ እንዳብራራው “የሱሜሪያንን፣ የአካድያንን፣ የአረማይክን . . . እንዲሁም ሌሎች ቋንቋዎችንና በእነዚህ ቋንቋዎች የተጻፉ ሰፊ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ማጥናትን የሚጨምር ነበር።” ይህ “ሰፊ የሥነ ጽሑፍ ሥራ” ታሪክን፣ ሒሳብን፣ የከዋክብትን ጥናትና የመሳሰሉትን ነገሮች የሚያካትት ነው። ይሁን እንጂ “ትልቁን ቦታ የያዙት ከዚሁ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው የአውደ ነገሥትና የኮከብ ቆጠራ ሃይማኖታዊ ጽሑፎች . . . ነበሩ።”
11. ወጣቶቹ ዕብራውያን ከባቢሎናውያን የቤተ መንግሥት ኑሮ ጋር እንዲዋሃዱ ለማድረግ ምን እርምጃዎች ተወስደዋል?
11 እነዚህ ዕብራውያን ወጣቶች የባቢሎን ቤተ መንግሥት ሕይወት ክፍል ከሆኑት ልማዶችና ባሕል ጋር እንዲዋሃዱ ሲባል ንጉሡ “ሦስት ዓመት ያሳድጓቸው ዘንድ፣ ከዚያም በኋላ በንጉሡ ፊት ይቆሙ ዘንድ ከንጉሡ መብል ከሚጠጣውም ጠጅ በየዕለቱ ድርጓቸውን አዘዘላቸው።” (ዳንኤል 1:5) “የጃንደረቦቹም አለቃ ስም አወጣላቸው፤ ዳንኤልን ብልጣሶር፣ አናንያንም ሲድራቅ፣ ሚሳኤልንም ሚሳቅ፣ አዛርያንም አብደናጎ ብሎ ጠራቸው።” (ዳንኤል 1:7) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ሰው በሕይወቱ የገጠመውን ጉልህ ክስተት ለማመልከት ሲባል ለግለሰቡ አዲስ ስም መስጠት የተለመደ ነገር ነበር። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ የአብራምንና የሦራን ስም አብርሃምና ሣራ በሚል ቀይሮታል። (ዘፍጥረት 17:5, 15, 16) አንድ ሰው የሌላውን ስም መቀየሩ ሥልጣኑን ወይም የበላይነቱን የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው። ዮሴፍ በግብጽ የእህል ግምጃ ቤት ኃላፊ ሆኖ በተሾመ ጊዜ ፈርዖን ጸፍናት ጰዕናህ ብሎ ስሙን ቀይሮት ነበር።—ዘፍጥረት 41:44, 45፤ ከ2 ነገሥት 23:34፤ 24:17 ጋር አወዳድር።
12, 13. የወጣት ዕብራውያኑ ስም መቀየሩ በእምነታቸው ላይ የተሸረበ ሴራ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
12 በዳንኤልና በሦስቱ ዕብራውያን ጓደኞቹ ሁኔታ የስማቸው መለወጥ ትልቅ ትርጉም ነበረው። ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስሞች ከይሖዋ አምልኮ ጋር የሚስማሙ ነበሩ። “ዳንኤል” ማለት “ፈራጄ አምላክ ነው” ማለት ነው። የ“አናንያ” ስም ትርጉም “ይሖዋ ሞገሱን አሳየን” የሚል ነው። “ሚሳኤል” ማለት “እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” ማለት ሳይሆን አይቀርም። “አዛርያ” ማለት ደግሞ “ይሖዋ ረድቶናል” ማለት ነው። ወላጆቻቸው ልጆቹ በይሖዋ አምላክ መመሪያ አድገው የእርሱ ታማኝ አገልጋዮች ይሆኑልናል የሚል ትልቅ ተስፋ እንደነበራቸው ምንም ጥርጥር የለውም።
13 ይሁን እንጂ ለአራቱ ዕብራውያን የወጣላቸው አዲስ ስም ከሐሰት አማልክት ጋር የተቆራኘ ሲሆን ይህም እውነተኛው አምላክ እንደዚህ ባሉት ጣዖታት ድል ተደርጓል የሚያሰኝ ነበር። ይህ በእነዚህ ወጣቶች እምነት ላይ የተሸረበ እንዴት ያለ ሴራ ነው!
14. ለዳንኤልና ለሦስቱ ጓደኞቹ የተሰጣቸው ስም ትርጉም ምንድን ነው?
14 የዳንኤል ስም ወደ ብልጣሶር ተቀይሮ የነበረ ሲሆን ትርጓሜውም “የንጉሡን ሕይወት ጠብቅ” ማለት ነው። ይህም ለቤል ወይም የባቢሎናውያን ዋነኛ አምላክ ለሆነው ለማርዱክ የሚቀርብ ልመና አጭር ቃል እንደሆነ ከሁኔታዎቹ ለመረዳት ይቻላል። ለዳንኤል ይህን ስም በማውጣት ረገድ ናቡከደነፆር እጁ ኖረበትም አልኖረበት ከጊዜ በኋላ ግን “እንደ አምላኬ ስም” የሆነ በማለት በመኩራራት ተናግሮለታል። (ዳንኤል 4:8) ለአናንያ የተሰጠው ሲድራቅ የሚለው ስም ደግሞ አንዳንድ ምንጮች እንደሚያምኑት “የአኩ ትእዛዝ” የሚል ትርጉም ያለው የሁለት ቃላት ጥምረት ነው። የሚያስገርመው አኩ የሱሜሪያን አምላክ ስም ነው። ለሚሳኤል የተሰጠው አዲሱ ስም ሚሳቅ (ሚሻአኩ ሊሆንም ይችላል) ሲሆን “እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” ከሚለው ተቀድቶ ይመስላል፣ “አኩን የሚመስል ማን ነው?” የሚል ትርጉም አለው። የአዛርያ ባቢሎናዊ ስም ደግሞ አብደናጎ ነው። ይህም “የናጎ ባርያ” ማለት ሳይሆን አይቀርም። “ናጎ” ደግሞ “ናቦ” የሚባለውና ብዙ የባቢሎን ገዥዎች የሚጠሩበት ጣዖት ሌላ ስም ነው።
ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ለመገኘት የቆረጡ
15, 16. ዳንኤልና ጓደኞቹ ምን አደገኛ ሁኔታ ገጠማቸው? ይሁን እንጂ ምን ምላሽ ሰጡ?
15 ባቢሎናውያን ስሞቻቸው፣ የትምህርት ፕሮግራሙ እንዲሁም የቀረበላቸው ልዩ ምግብ፣ ይህ ሁሉ ዳንኤልና ሦስቱ ወጣት ዕብራውያን ጓደኞቹ ከባቢሎናውያኑ የአኗኗር መንገድ ጋር እንዲተዋወቁ ብቻ ሳይሆን ከአምላካቸው ከይሖዋና በልጅነታቸው ካገኙት ሃይማኖታዊ ሥልጠና ጨርሶ እንዲርቁ ለማድረግ የታሰቡ ነበሩ። እነዚህ ወጣቶች ይህ ሁሉ ተጽዕኖና ፈተና እያለባቸው ምን ያደርጉ ይሆን?
16 በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ዘገባ “ዳንኤልም በንጉሡ መብልና በሚጠጣው ጠጅ እንዳይረክስ በልቡ አሰበ” ይላል። (ዳንኤል 1:8ሀ) እዚህ ላይ በስም የተጠቀሰው ዳንኤል ብቻ ይሁን እንጂ ሦስቱ ጓደኞቹም የእርሱን ውሳኔ እንደደገፉ ቀጥሎ ያለው ታሪክ ያሳያል። “በልቡ አሰበ” የሚሉት ቃላት ዳንኤል በአገሩ ሳለ ከወላጆቹና ከሌሎችም ያገኘው ትምህርት በልቡ ውስጥ ተተክሎ እንደነበረ ያሳያል። የቀሩት ሦስቱ ዕብራውያንም ቢሆኑ ያገኙት ተመሳሳይ ሥልጠና ለውሳኔያቸው እንደረዳቸው ምንም አያጠራጥርም። ይህም ልጆቻችንን ገና ሕፃናት ናቸው ብለን ከምናስብበት ጊዜ አንስቶ የማስተማሩን አስፈላጊነት በጉልህ የሚያንጸባርቅ ምሳሌ ነው።—ምሳሌ 22:6፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15
17. ዳንኤልና ጓደኞቹ የንጉሡን ዕለታዊ ቀለብ ብቻ ተቃውመው ሌሎቹን ዝግጅቶች ያልተቃወሙት ለምንድን ነው?
17 ወጣቶቹ ዕብራውያን ሌሎቹን ዝግጅቶች ሳይቃወሙ ደስ የሚያሰኘውን የንጉሡን ምግብና ወይን ጠጁን ብቻ የተቃወሙት ለምን ነበር? የዳንኤል ሐሳብ ምክንያቱን በግልጽ ይጠቁመናል፤ “እንዳይረክስ” ነበር። ‘የከለዳውያንን ትምህርትና ቋንቋ መማር’ እንዲሁም በባቢሎናዊ ስሞች መጠራት የሚወደስ ነገር ባይሆንም አንድን ሰው ያረክሰዋል ማለት ላይሆን ይችላል። ከዚህ ጊዜ 1,000 ዓመት ቀደም ብሎ የኖረውን የሙሴን ሁኔታ ተመልከት። “የግብፆችን ጥበብ ሁሉ” ቢማርም ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። በገዛ ወላጆቹ እንክብካቤ ማደጉ ጠንካራ መሠረት እንዲኖረው ረድቶታል። ከዚህም የተነሣ “ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ . . . ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ።”—ሥራ 7:22፤ ዕብራውያን 11:24, 25
18. የንጉሡ መብል ወጣቶቹን ዕብራውያን ሊበክላቸው የሚችለው በምን መንገዶች ነበር?
18 የባቢሎን ንጉሥ መብል ወጣቶቹን ሊያረክሳቸው የሚችለው በምን መንገድ ነበር? በመጀመሪያ ደረጃ እነዚያ ደስ የሚያሰኙ ምግቦች በሙሴ ሕግ የተከለከሉ ምግቦችን የሚጨምሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ባቢሎናውያን ንጹሕ ያልሆኑ እንስሳትን ይበሉ ነበር፤ ይህ ደግሞ በሙሴ ሕግ ሥር ለነበሩት እስራኤላውያን የተከለከለ ነገር ነው። (ዘሌዋውያን 11:1-31፤ 20:24-26፤ ዘዳግም 14:3-20) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ባቢሎናውያን ሥጋውን ለመብላት እንስሳ በሚያርዱበት ጊዜ ደሙን የማፍሰስ ልማድ አልነበራቸውም። ደሙ ያልፈሰሰ ሥጋ መብላት ደግሞ ይሖዋ ስለ ደም የሰጠውን ሕግ በቀጥታ የሚቃረን ነገር ነበር። (ዘፍጥረት 9:1, 3, 4፤ ዘሌዋውያን 17:10-12፤ ዘዳግም 12:23-25) በሦስተኛ ደረጃ የሐሰት አማልክት አገልጋዮች ምግባቸውን በጋራ ማዕድ ቀርበው ከመብላታቸው በፊት ለጣዖታቱ የማቅረብ ልማድ ነበራቸው። የይሖዋ አገልጋዮች ደግሞ እንደዚህ ባለው ድርጊት አይካፈሉም! (ከ1 ቆሮንቶስ 10:20-22 ጋር አወዳድር።) ደግሞም በየዕለቱ ከባድ ምግቦችንና ጠንካራ መጠጦችን መውሰድ፣ ለወጣቶች ይቅርና በማንኛውም ዕድሜ ላይ ለሚገኝ ሰውም ቢሆን ለጤና የሚበጅ አይደለም።
19. ወጣቶቹ ዕብራውያን ምን ብለው ሊያስቡ ይችሉ ነበር? ይሁን እንጂ ወደ ትክክለኛው መደምደሚያ እንዲደርሱ የረዳቸው ምንድን ነው?
19 ምን መደረግ እንዳለበት ማወቅ አንድ ነገር ቢሆንም ውጥረት ውስጥ ሆኖ ወይም ፈታኝ ሁኔታ እያለ ትክክለኛውን ነገር በድፍረት ማድረግ ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው። ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ከወላጆቻቸውና ከወዳጆቻቸው ርቀው ስለሚገኙ ምን እያደረጉ እንዳሉ እንደማያውቁባቸው አድርገው ሊያስቡ ይችሉ ነበር። የንጉሥ ትእዛዝ ስለሆነ ሌላ ምንም ምርጫ የለንም ብለውም ሊያስቡ ይችሉ ነበር። ከዚህም በላይ ሌሎቹ ወጣቶች ይህን ዝግጅት አሜን ብለው ተቀብለውትና እንደ ፈተና ሳይሆን እንደ መብት ቆጥረውት እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው የተሳሳተ አስተሳሰብ ድብቅ ኃጢአት ወደ መሥራት ሊመራ የሚችል ሲሆን ይህ ብዙ ወጣቶች የሚወድቁበት ወጥመድ ነው። ዕብራውያኑ ወጣቶች ‘የይሖዋ ዓይኖች በስፍራው ሁሉ’ እንደሆኑና እውነተኛው አምላክ “ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፣ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፣ ወደ ፍርድ” እንደሚያመጣው አውቀው ነበር። (ምሳሌ 15:3፤ መክብብ 12:14) ሁላችንም ከእነዚህ የታመኑ ወጣቶች አካሄድ መማር አለብን።
ድፍረታቸውና ጽናታቸው መልሶ ክሷቸዋል
20, 21. ዳንኤል ምን እርምጃ ወሰደ? ውጤቱስ ምን ነበር?
20 ዳንኤል የሚበክሉ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም በልቡ ቆርጦ ስለነበር ከዚህ ውሳኔው ጋር የሚስማማ ነገር ማድረጉን ቀጠለ። “እንዳይረክስም የጃንደረቦቹን አለቃ ለመነ [“መለመኑን ቀጠለ፣” NW]።” (ዳንኤል 1:8ለ) “መለመኑን ቀጠለ” የሚለውን መግለጫ ልብ ልንለው ይገባል። ብዙውን ጊዜ አንድን ፈታኝ ሁኔታ ለመወጣት ወይም አንዳንድ ድክመቶቻችንን ለማሸነፍ የምንፈልግ ከሆነ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል።—ገላትያ 6:9
21 ከዳንኤል ሁኔታ እንደምንማረው ያሳየው ጽናት መልሶ ክሶታል። “እግዚአብሔርም በጃንደረቦቹ አለቃ ፊት ለዳንኤል ሞገስንና ምሕረትን ሰጠው።” (ዳንኤል 1:9) ዳንኤልና ጓደኞቹ የተሳካላቸው መልከ መልካምና ብልህ ሰዎች ስለነበሩ ሳይሆን ይሖዋ ስለባረካቸው ነው። ዳንኤል “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” የሚለውን የዕብራውያን ምሳሌ አስታውሶ እንደነበር እሙን ነው። (ምሳሌ 3:5, 6) በእርግጥም ይህንን ምክር መከተላቸው የሚክስ ነበር።
22. የጃንደረቦቹ አለቃ ምን ምክንያታዊ ተቃውሞ አነሳ?
22 የጃንደረቦቹ አለቃ መጀመሪያ ሐሳቡን ተቃውሞት ነበር:- “መብሉንና መጠጡን ያዘዘላችሁን ጌታዬን ንጉሡን እፈራለሁ፤ በዕድሜ እንደ እናንተ ካሉ ብላቴኖች ይልቅ ፊታችሁ ከስቶ ያየ እንደሆነ፣ ከንጉሡ ዘንድ በራሴ ታስፈርዱብኛላችሁ።” (ዳንኤል 1:10) ይህ ተቃውሞውና ፍርሃቱ ያለ ምክንያት አልነበረም። ንጉሥ ናቡከደነፆርን ተቃውሞ በፊቱ የሚቆም ሰው የለም። በመሆኑም አለቃው ከንጉሡ መመሪያ ውጭ ቢሄድ ‘ራሱ’ እንደሚቀላ ተገንዝቦ ነበር። ታዲያ ዳንኤል ምን ያደርግ ይሆን?
23. ዳንኤል ጥልቅ ማስተዋልና ጥበብ የተንጸባረቀበት እርምጃ የወሰደው እንዴት ነው?
23 ጥበብና ማስተዋል ትልቅ ሚና የተጫወቱት እዚህ ላይ ነበር። ወጣቱ ዳንኤል “የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች፤ ሸካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች” የሚለውን ምሳሌ ሳያስታውስ አልቀረም። (ምሳሌ 15:1) ጥያቄው እንዲሟላለት ከመነዝነዝና ሌሎች ሕይወታቸውን እንዲያጡ ምክንያት ከመሆን ይልቅ ዳንኤል ነገሩን ተወት አደረገው። ተስማሚ ጊዜ ጠብቆ ‘መጋቢውን’ ቀርቦ አነጋገረው። ይህ ሰው በንጉሡ ፊት ቀጥተኛ ተጠያቂም ስላልነበር ትንሽ መፈናፈኛ ለመስጠት ፈቃደኛ ነበር።—ዳንኤል 1:11 የ1980 ትርጉም
የአሥር ቀን ሙከራ እንዲደረግ ሐሳብ ቀረበ
24. ዳንኤል ምን ሙከራ እንዲደረግ ሐሳብ አቀረበ?
24 ዳንኤል መጋቢው እንዲፈትናቸው እንዲህ ሲል ሐሳብ አቀረበ:- “እኛን ባሪያዎችህን አሥር ቀን ያህል ትፈትነን ዘንድ እለምንሃለሁ፤ የምንበላውንም ጥራጥሬ [“አትክልት፣” የ1980 ትርጉም] የምንጠጣውንም ውኃ ይስጡን፤ ከዚያም በኋላ የእኛን ፊትና ከንጉሡ መብል የሚበሉትን የብላቴኖችን ፊት ተመልከት፤ እንዳየኸውም ሁሉ ከባሪያዎችህ ጋር የወደድኸውን አድርግ።”—ዳንኤል 1:12, 13
25. ለዳንኤልና ለሦስቱ ጓደኞቹ የቀረበላቸው “አትክልት” ምን ነገር የሚጨምር ሳይሆን አይቀርም?
25 ለአሥር ቀናት ያህል ‘አትክልትና ውኃ’ ሊመገቡ ነው። ከሌሎቹ ጋር ሲወዳደሩ ‘ፊታቸው ከስቶ ይታይ’ ይሆን? “አትክልት” የሚለው ቃል የተተረጎመው “ዘር” የሚል መሠረታዊ ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል ነው። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ጥራጥሬ” ብለው ተርጉመውታል። ይህም (እንደ አተር፣ ባቄላ ወይም ምስር ያሉትን) ለምግብነት የሚያገለግሉ የአዝዕርት ዓይነቶችን የሚያመለክት ነው። አንዳንድ ምሁራን ከጥቅሱ አገባብ መረዳት እንደሚቻለው ይህ ለምግብነት የሚያገለግሉ ጥራጥሬዎች ብቻ ያሉበት ምግብ አይደለም ይላሉ። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዳለው “ዳንኤልና ጓደኞቹ የጠየቁት ሥጋ ከበዛበት የንጉሡ ከባድ ምግብ ይልቅ ብዙሐኑ የሚመገበው የአትክልት ምግብ እንዲቀርብላቸው ነበር።” በመሆኑም አትክልት ሲባል ባቄላ፣ የፈረንጅ ዱባ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ባሮ፣ ምስር፣ ከርቡሽና ሽንኩርት ያለበት እንዲሁም ከተለያየ የእህል ዓይነት የተሠሩ ዳቦዎችን ያካተተ ገንቢ ምግብ ሊሆን ይችላል። ማንም ሰው ቢሆን እንዲህ ዓይነቱን ምግብ ስለተመገቡ ተርበዋል ብሎ እንደማያስብ የታወቀ ነው። መጋቢው ነጥቡ የገባው ይመስላል። “ይህንንም ነገራቸውን ሰምቶ አሥር ቀን ፈተናቸው።” (ዳንኤል 1:14) ውጤቱስ ምን ሆነ?
26. የአሥሩ ቀን ፈተና ውጤት ምን ሆኖ ተገኘ? ውጤቱስ እንደዚያ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
26 “ከአሥር ቀንም በኋላ ከንጉሡ መብል ከበሉ ብላቴኖች ሁሉ ይልቅ ፊታቸው አምሮ ሥጋቸውም ወፍሮ ታየ።” (ዳንኤል 1:15) ይህ አትክልት መመገብ ሥጋ ያለበት ከባድ ምግብ ከመመገብ ይሻላል ለማለት እንደ ማስረጃ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። ለማንኛውም አመጋገብ ቢሆን በአንድ ሰው ላይ ጉልህ ለውጥ ለማምጣት አሥር ቀን አጭር ጊዜ ነው። ለይሖዋ ግን ዓላማውን ለማስፈጸም በቂ ነበር። ቃሉ “የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፣ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም” ይላል። (ምሳሌ 10:22) አራቱ ወጣት ዕብራውያን እምነታቸውንና ትምክህታቸውን በይሖዋ ላይ ጥለው ነበር። እርሱም አልተዋቸውም። ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ ለ40 ቀናት ያህል ያለ ምግብ ቆይቶ ነበር። ይህንኑ በሚመለከት “ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት” አይኖርም የሚሉትን የዘዳግም 8:3 ቃላት ጠቅሶ ተናግሯል። በዚህ ረገድ የዳንኤልና የጓደኞቹ ተሞክሮ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል።
በንጉሡ ምግብና ወይን ፋንታ ጥልቅ ማስተዋልና ጥበብ
27, 28. ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ የተከተሉት የአመጋገብ ልማድ ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው የበለጠ ነገር ያዘጋጃቸው እንዴት ነበር?
27 አሥሩ ቀናት እንዲሁ ለሙከራ ያክል ብቻ የተወሰኑ ቢሆኑም ውጤቱ እጅግ አሳማኝ ነበር። በመሆኑም መጋቢው “መብላቸውንና የሚጠጡትን ጠጅ አስቀርቶ ጥራጥሬውን ሰጣቸው።” (ዳንኤል 1:16) በሥልጠናው ውስጥ የነበሩት ሌሎች ወጣቶች ስለ ዳንኤልና ስለ ጓደኞቹ ምን ያስቡ እንደነበር መገመት አስቸጋሪ አይሆንም። የንጉሡን ግብዣ አንፈልግም ብለው በየዕለቱ አትክልት ለመብላት መምረጣቸው ትልቅ ሞኝነት መስሎ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ የዕብራውያኑን ወጣቶች ንቃትና ትጋት የሚመዝኑ ፈተናዎች ከፊታቸው ይጠብቋቸው ነበር። ከሁሉም በላይ ደግሞ በእምነታቸው ላይ የሚመጣውን ፈተና ለመወጣት የሚረዳቸው በይሖዋ ላይ ያላቸው እምነትና ትምክህት ነበር።—ከኢያሱ 1:7 ጋር አወዳድር።
28 ይሖዋ ከእነዚህ ወጣቶች ጋር እንደነበረ ከሚቀጥለው ሐሳብ መረዳት እንችላለን:- “ለእነዚህም ለአራቱ ብላቴኖች እግዚአብሔር በትምህርትና በጥበብ ሁሉ እውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፤ ዳንኤልም በራእይና በሕልም ሁሉ አስተዋይ ነበረ።” (ዳንኤል 1:17) ከፊታቸው ያሉትን አስቸጋሪ ጊዜያት ለመወጣት የሚያስፈልጋቸው አካላዊ ጥንካሬና ጥሩ ጤንነት ብቻ አልነበረም። “ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለች እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፤ ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል፣ ከክፉ መንገድ አንተን ለማዳን።” (ምሳሌ 2:10-12) ይሖዋ አራቱን የታመኑ ወጣቶች ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ነገር ለማስታጠቅ ሲል የሰጣቸውም ይህንኑ ነው።
29. ዳንኤል “በራእይና በሕልም ሁሉ አስተዋይ” ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
29 ዳንኤል “በራእይና በሕልም ሁሉ አስተዋይ” መሆኑ ተጠቅሷል። ከሰው በላይ የሆነውን ነገር የማወቅ ችሎታ ነበረው ማለት አይደለም። እንዲያውም የሚያስገርመው ዳንኤል ከታላላቆቹ ዕብራውያን ነቢያት እንደ አንዱ ይቆጠር የነበረ ቢሆንም አንድም ቦታ በመንፈስ አነሳሽነት ‘ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ወይም “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል” ብሎ አልጻፈም። (ኢሳይያስ 28:16 የ1980 ትርጉም፤ ኤርምያስ 6:9 NW) ይሁንና ዳንኤል የይሖዋን ዓላማ የሚያሳውቁ ራእይዎችንና ሕልሞችን ሊረዳና ሊተረጉም የቻለው በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ነው።
በመጨረሻ ወሳኝ የሆነው ፈተና መጣ
30, 31. ዳንኤልና ጓደኞቹ የመረጡት ጎዳና እንደጠቀማቸው የታየው እንዴት ነው?
30 የሦስት ዓመቱ ተኃድሶ ትምህርትና እንክብካቤ አበቃ። ከዚያ በኋላ ወሳኝ የሆነው ፈተና ማለትም ከንጉሡ ጋር በግል ቃለ ምልልስ የሚያደርጉበት ጊዜ ደረሰ። “እነርሱም ይገቡ ዘንድ ንጉሡ ያዘዘው ቀን በተፈጸመ ጊዜ፣ የጃንደረቦቹ አለቃ ወደ ናቡከደነፆር ዘንድ አገባቸው።” (ዳንኤል 1:18) ይህ አራቱ ወጣቶች ለየራሳቸው መልስ የሚሰጡበት ጊዜ ነበር። ከባቢሎናውያን መንገዶች ይልቅ የይሖዋን ሕግ ሙጥኝ ማለታቸው ይጠቅማቸው ይሆን?
31 “ንጉሡም በተነጋገራቸው ጊዜ ከብላቴኖቹ ሁሉ እንደ ዳንኤልና እንደ አናንያ እንደ ሚሳኤልና እንደ አዛርያ ያለ አልተገኘም፤ በንጉሡም ፊት ቆሙ።” (ዳንኤል 1:19) ከዚያ በፊት በነበሩት ሦስት ዓመታት ውስጥ የተከተሉት ጎዳና ትክክለኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ እንዴት ያለ ማስረጃ ነበር! እምነታቸውና ሕሊናቸው ይፈቅድላቸው የነበረውን የአመጋገብ ልማድ መከተላቸው እብደት አልነበረም። ዳንኤልና ጓደኞቹ ትንሽ መስሎ ይታይ በነበረው ነገር የታመኑ ሆነው በመገኘታቸው የበለጡ ነገሮችን በማግኘት ተባርከዋል። ‘በንጉሥ ፊት የመቆም መብት’ በሥልጠናው ፕሮግራም ውስጥ ታቅፈው የነበሩት የሁሉም ወጣቶች ግብ ነበር። የተመረጡት አራቱ ዕብራውያን ወጣቶች ብቻ ስለመሆናቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው ነገር የለም። ያም ሆነ ይህ የታመኑ ሆነው በመመላለሳቸው ‘እጅግ ተጠቅመዋል።’—መዝሙር 19:11
32. ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ በንጉሡ ቤተ መንግሥት ከመገኘት የበለጠ መብት አግኝተዋል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
32 መጽሐፍ ቅዱስ “በሥራው የቀ[ለ]ጠፈ ሰውን አይተሃልን? በነገሥታት ፊት ይቆማል” ይላል። (ምሳሌ 22:29) በመሆኑም ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ በንጉሥ ፊት እንዲቆሙ ማለትም የቤተ መንግሥቱ አባላት እንዲሆኑ ናቡከደነፆር መርጧቸዋል። በዚህ ሁሉ መሃል በእነዚህ ወጣቶች በተለይም በዳንኤል አማካኝነት የመለኮታዊው ዓላማ አስፈላጊ ዘርፎች እንዲታወቁ ለማድረግ ይሖዋ ነገሮችን እንዴት መልክ ያስይዝ እንደነበር እናስተውላለን። የናቡከደነፆር ቤተ መንግሥት አባል እንዲሆኑ መመረጣቸው ትልቅ መብት ቢሆንም የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ንጉሥ የሆነው ይሖዋ በዚህ ድንቅ መንገድ በእነርሱ መጠቀሙ ደግሞ ከሁሉ የላቀ ታላቅ መብት ነው።
33, 34. (ሀ) ንጉሡ በወጣቶቹ ዕብራውያን የተደነቀው ለምንድን ነው? (ለ) ከአራቱ ዕብራውያን ተሞክሮ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?
33 ናቡከደነፆር ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ለእነዚህ አራት ዕብራውያን ወጣቶች የሰጣቸው ጥበብና ጥልቅ ማስተዋል በቤተ መንግሥቱ ካሉት አማካሪዎችና ጠቢባን ሁሉ እጅግ የላቀ መሆኑን አስተዋለ። “ንጉሡም በጠየቃቸው በጥበብና በማስተዋል ነገር ሁሉ በግዛቱ ሁሉ ከሚኖሩ የሕልም ተርጓሚዎችና አስማተኞች ሁሉ እነርሱ አሥር እጅ የበለጡ ሆነው አገኘባቸው።” (ዳንኤል 1:20) ድሮውንስ ሌሎቹ እንዴት ሊበልጧቸው ይችላሉ? ‘የሕልም ተርጓሚዎቹና’ ‘አስማተኞቹ’ የሚመኩት በባቢሎናውያን ዓለማዊና የአጉል እምነት ትምህርቶች ላይ ነበር። ዳንኤልና ጓደኞቹ ግን ትምክህታቸው በመለኮታዊው ጥበብ ላይ ነው። እነዚህን ሁለት ነገሮች ማወዳደር ከቶውንም የሚታሰብ አይደለም!
34 ከዚያ ጊዜ ወዲህ ባሉት ዘመናትም ቢሆን ሁኔታው እምብዛም አልተለወጠም። የግሪካውያን ፍልስፍናና የሮማውያን ሕግ ገንነው በነበረበት በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “የዚች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና። እርሱ ጥበበኞችን በተንኰላቸው የሚይዝ፤ ደግሞም:- ጌታ የጥበበኞችን አሳብ ከንቱ እንደ ሆነ ያውቃል ተብሎ ተጽፎአልና። ስለዚህም ማንም በሰው አይመካ።” (1 ቆሮንቶስ 3:19-21) ዛሬ ይሖዋ ያስተማረንን ነገር ሙጥኝ ብለን ልንመላለስ ይገባል እንጂ በዓለም ብልጭልጭ ነገሮች በቀላሉ ልንወሰድ አይገባም።—1 ዮሐንስ 2:15-17
እስከ መጨረሻው ድረስ የታመኑ መሆን
35. ስለ ዳንኤል ሦስት ጓደኞች የምናውቀው እስከ ምን ድረስ ነው?
35 አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ያሳዩት ጠንካራ እምነት ናቡከደነፆር በዱራ ሜዳ ካቆመው የወርቅ ምስልና ከእቶን እሳቱ ፈተና ጋር በተያያዘ መንገድ በዳንኤል ምዕራፍ 3 ውስጥም በጉልህ ተንጸባርቋል። እነዚህ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ዕብራውያን እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ለይሖዋ የታመኑ ሆነው እንደቆሙ ምንም ጥርጥር የለውም። እንደዚህ ለማለት ምክንያት የሚሆነን ሐዋርያው ጳውሎስ “እነርሱ በእምነት . . . የእሳትን ኃይል አጠፉ” በማለት ስለ እነርሱ በተዘዋዋሪ መንገድ መጥቀሱ ነው። (ዕብራውያን 11:33, 34) ወጣት አዋቂ ሳይል ለሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ግሩም ምሳሌ ናቸው።
36. ዳንኤል ምን ዓይነት ጥሩ ሕይወት አሳልፏል?
36 ዳንኤልን በሚመለከት ደግሞ የምዕራፍ 1 የመደምደሚያ ቁጥር “ዳንኤልም እስከ ንጉሡ እስከ ቂሮስ መጀመሪያ ዓመት ተቀመጠ” ይላል። ቂሮስ በ539 ከዘአበ ባቢሎንን በአንድ ጀምበር እንደገለበጣት ታሪክ ይነግረናል። ከሁኔታው ለመረዳት እንደምንችለው ዳንኤል ጥሩ ስምና ክብር ስለነበረው በቂሮስ ቤተ መንግሥት ውስጥም ማገልገሉን ቀጥሏል። እንዲያውም ዳንኤል 10:1 ላይ እንደምናነበው ይሖዋ “በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በሦስተኛው ዓመት” ለዳንኤል አንድ አስገራሚ ነገር ገልጦለታል። በ617 ከዘአበ ወደ ባቢሎን በመጣበት ጊዜ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ነበር ብንል እንኳ ይህን የመጨረሻ ራእይ ሲቀበል ዕድሜው ወደ 100 ዓመት ገደማ ተጠግቶ ነበር ማለት ነው። ዳንኤል ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል የተባረከ ረጅም ሕይወት አሳልፏል!
37. ዳንኤል ምዕራፍ 1ን በመመርመራችን ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?
37 የዳንኤል መጽሐፍ የመክፈቻ ምዕራፍ የያዘው አራት የታመኑ ወጣቶች የገጠማቸውን ፈተና በተሳካ ሁኔታ ስለ መወጣታቸው የሚገልጽ ታሪክ ብቻ አይደለም። ይሖዋ ዓላማውን ለማስፈጸም ሲል የመረጠውን ማንኛውንም ሰው ሊጠቀም እንደሚችል ያሳየናል። ዘገባው ይሖዋ የፈቀደው ከሆነ እንደ መከራ መስሎ የሚታየው ነገር እንኳ ጠቃሚ ዓላማ ሊያከናውን እንደሚችል ይጠቁማል። በጥቂቱ የታመኑ ሆኖ መገኘትም ትልቅ በረከት ሊያስገኝልን እንደሚችል ይጠቁመናል።
ምን አስተውለሃል?
• ስለ ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ትውልድ ምን ማለት ይቻላል?
• የአራቱ ወጣት ዕብራውያን መልካም አስተዳደግ በባቢሎን ውስጥ ፈተና ላይ የወደቀው እንዴት ነበር?
• አራቱ ዕብራውያን ለወሰዱት የድፍረት አቋም ይሖዋ መልሶ የካሳቸው እንዴት ነው?
• በዛሬው ጊዜ ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች ከዳንኤልና ከሦስቱ ጓደኞቹ ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ?
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]