ምዕራፍ አራት
የአንድ ግዙፍ ምስል አነሳስና አወዳደቅ
1. ንጉሥ ናቡከደነፆር ዳንኤልንና ሌሎችን በምርኮ ከወሰደ ከአሥር ዓመታት በኋላ የተፈጠረው ሁኔታ ትኩረታችንን የሚስብ የሆነው ለምንድን ነው?
ንጉሥ ናቡከደነፆር ዳንኤልንና ሌሎች የይሁዳን ‘ታላላቅ ሰዎች’ በግዞት ወደ ባቢሎን ከወሰደ አሥር ዓመታት አልፈዋል። (2 ነገሥት 24:15) ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ በተፈጠረበት ጊዜ ወጣቱ ዳንኤል በንጉሡ ቤተ መንግሥት ውስጥ በማገልገል ላይ ነበር። ይህ ጉዳይ ትኩረታችንን የሚስብ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ አምላክ በጉዳዩ ውስጥ እጁን ጣልቃ ማስገባቱ የዳንኤልንና የሌሎችን ሕይወት ከማትረፍም አልፎ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት እስከ ጊዜያችን ድረስ ስለተፈራረቁት የዓለም ኃያላን እንድናስተውል ስለሚረዳን ነው።
አንድ ንጉሠ ነገሥት ከባድ ችግር ገጠመው
2. ናቡከደነፆር የመጀመሪያውን ትንቢታዊ ሕልም ያየው መቼ ነበር?
2 ነቢዩ ዳንኤል “ናቡከደነፆርም በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ናቡከደነፆር ሕልም አለመ፤ መንፈሱም ታወከ፣ እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ” ሲል ጽፏል። (ዳንኤል 2:1) ሕልሙን ያለመው የባቢሎንን ግዛት የሚያስተዳድረው ንጉሥ ናቡከደነፆር ነበር። በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን እንዲያጠፋ ይሖዋ አምላክ በፈቀደለት ጊዜ ናቡከደነፆር የዓለም ገዥ ሆኖ ነበር። ናቡከደነፆር የዓለም ገዥ በሆነበት በሁለተኛው ዓመት (606/605 ከዘአበ) አምላክ አስፈሪ ሕልም አሳየው።
3. የናቡከደነፆርን ሕልም እነማን ሊፈቱለት አልቻሉም? እርሱስ ምን ምላሽ ሰጠ?
3 ናቡከደነፆር በሕልሙ እጅግ ከመረበሹ የተነሣ እንቅልፉ ሁሉ ጠፋ። የሕልሙን ትርጓሜም ለማወቅ ጓጉቶ ነበር። ይሁን እንጂ ኃያሉ ንጉሥ ሕልሙን ረስቶታል! በመሆኑም የባቢሎንን አስማተኞችና መተተኞች ሁሉ ወደ እርሱ አስጠርቶ ሕልሙን እንዲነግሩትና ፍቺውን እንዲያሳውቁት ጠየቀ። ይህ ከአቅማቸው በላይ ነበር። ናቡከደነፆርም በዚህ እጅግ ተቆጥቶ “የባቢሎንን ጠቢባን ሁሉ ያጠፉ ዘንድ አዘዘ።” ይህ ትእዛዝ ደግሞ ነቢዩ ዳንኤልን ፍርዱን እንዲያስፈጽም ከተሾመው ሰው ጋር ፊት ለፊት የሚያገጣጥም ነበር። ለምን? ምክንያቱም ዳንኤልም ሆነ ሦስቱ ዕብራውያን ጓደኞቹ ማለትም አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ የሚቆጠሩት እንደ ባቢሎን ጠቢባን ተደርገው ነበር።—ዳንኤል 2:2-14
ዳንኤል ከመገደል አተረፋቸው
4. (ሀ) ዳንኤል የናቡከደነፆርን ሕልም ይዘትና ትርጓሜውን ሊያውቅ የቻለው እንዴት ነው? (ለ) ዳንኤል ለይሖዋ ያለውን አድናቆት ምን በማለት ገልጿል?
4 ናቡከደነፆር ይህን ከባድ ውሳኔ ያደረገበትን ምክንያት ካወቀ በኋላ ዳንኤል “ፍቺውን ለንጉሡ የሚያስታውቅበት ጊዜ ይሰጠው ዘንድ ንጉሡን ለመነ፤” ተፈቀደለት። ዳንኤል ወደ ቤቱ ተመልሶ ከሦስቱ ዕብራውያን ጓደኞቹ ጋር በመሆን “ምሕረትን ከሰማይ አምላክ” ለመኑ። በዚያው ዕለት ሌሊት ይሖዋ በራእይ የሕልሙን ፍቺ ለዳንኤል አሳወቀው። ዳንኤል በአመስጋኝነት ስሜት ተውጦ እንዲህ ብሏል:- “ጥበብና ኃይል ለእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፤ ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል፤ ነገሥታትን ያፈልሳል፣ ነገሥታትንም ያስነሣል፤ ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል። የጠለቀውንና የተሠወረውን ይገልጣል፤ በጨለማ ያለውን ያውቃል፣ ብርሃንም ከእርሱ ጋር ነው።” ዳንኤል እንዲህ ያለውን ጥልቅ ማስተዋል በማግኘቱ ይሖዋን ከፍ ከፍ አድርጓል።—ዳንኤል 2:15-23
5. (ሀ) ዳንኤል በንጉሡ ፊት በቀረበ ጊዜ ይሖዋ እንዲመሰገን ያደረገው እንዴት ነው? (ለ) ዳንኤል የሰጠው ማብራሪያ ዛሬ የእኛን ትኩረት የሚስብ የሆነው ለምንድን ነው?
5 በማግስቱ ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን እንዲያጠፋ ወደ ተሾመው ወደ ዘበኞቹ አለቃ ወደ አርዮክ ሄደ። ዳንኤል ሕልሙን ሊፈታ እንደሚችል ሲያውቅ አርዮክ ፈጥኖ ወደ ንጉሡ አስገባው። ዳንኤል ለራሱ አንዳችም ምስጋና ሳይፈልግ ለናቡከደነፆር እንዲህ አለ:- “ምሥጢር የሚገልጥ አምላክ በሰማይ ውስጥ አለ፣ እርሱም በኋለኛው ዘመን የሚሆነውን ለንጉሡ ለናቡከደነፆር አስታውቆታል።” ዳንኤል የባቢሎንን ግዛት የወደፊት ዕጣ ለመግለጽ ብቻ ሳይሆን ከናቡከደነፆር ዘመን አንስቶ እስከ እኛ ጊዜ ብሎም ከዚያ በኋላ የሚከናወኑትን ነገሮች ለመዘርዘር ተዘጋጅቶ ነበር።—ዳንኤል 2:24-30
ተረስቶ የነበረው ሕልም
6, 7. ዳንኤል ለንጉሡ ያስታወሰው ሕልም ምን ነበር?
6 ዳንኤል እንደሚከተለው ብሎ ሲያብራራ ናቡከደነፆር በትኩረት ይከታተል ነበር:- “ንጉሥ ሆይ! እጅግ የሚያንጸባርቅና ብልጭልጭታው ለማየት የሚያስፈራ ታላቅ ምስል በፊትህ ቆሞ በራእይ አየህ። የምስሉ ራስ ከንጹሕ ወርቅ ደረቱና እጆቹ ከብር፣ ሆዱና ጭኖቹ ከነሐስ፤ ቅልጥሞቹ ከብረት፣ እግሮቹ እኩሌታው ከብረት፣ እኩሌታው ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ። አንተ ምስሉን ስትመለከት ሳለ ታላቅ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ወረደ፤ ከብረትና ከሸክላ በተሠሩት በምስሉ እግሮች ላይ ወድቆ ሰባበራቸው። ብረቱ፣ ሸክላው፣ ነሐሱ፣ ብሩና ወርቁ ሁሉ ወዲያውኑ ተንከታክቶ በበጋ ወራት በአውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅ ሆነ፤ ምንም ሳያስቀር ነፋስ ጠራርጎ ወሰደው፤ በምስሉ ላይ የወደቀው ድንጋይ ግን ምድርን ሁሉ እስኪሞላ ድረስ ከፍ ከፍ ብሎ ታላቅ ተራራ ሆነ።”—ዳንኤል 2:31-35 የ1980 ትርጉም
7 ዳንኤል ሕልሙን ሲነግረው ናቡከደነፆር በታላቅ ደስታ ተውጦ መሆን አለበት! ይሁን እንጂ ቆይ ገና የሚቀር ነገር አለ! የባቢሎን ጠቢባን በሕይወት የሚተርፉት ዳንኤል የሕልሙን ፍቺ ማሳወቅ ከቻለ ብቻ ነው። ዳንኤል ራሱንና ሦስቱን ዕብራውያን ጓደኞቹን ጨምሮ እንዲህ አለ:- “ሕልሙ ይህ ነው፤ አሁንም ፍቺውን በንጉሡ ፊት እንናገራለን።”—ዳንኤል 2:36
ታላቅ ግርማ የነበረው መንግሥት
8. (ሀ) በዳንኤል ትርጓሜ መሠረት የወርቁ ራስ ማን ወይም ምንድን ነው? (ለ) የወርቁ ራስ ወደ ሕልውና የመጣው መቼ ነው?
8 “አንተ፣ ንጉሥ ሆይ፣ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ኃይልን፣ ብርታትንና ክብርን የሰጠህ የነገሥታት ንጉሥ አንተ ነህ። በሚቀመጡበትም ስፍራ ሁሉ የሰው ልጆችንና የምድር አራዊትን የሰማይ ወፎችንም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፣ ለሁሉም ገዥ አድርጎሃል፤ አንተ የወርቁ ራስ ነህ።” (ዳንኤል 2:37, 38) እነዚህ ቃላት ይሖዋ በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት ከተጠቀመበት በኋላ የነበረውን የናቡከደነፆር ሁኔታ የሚያመለክቱ ናቸው። ይህም የሆነው በኢየሩሳሌም ይቀመጡ የነበሩት ነገሥታት ይሖዋ በቀባው ንጉሥ በዳዊት የዘር መስመር የሚመጡ በመሆናቸው ነው። ኢየሩሳሌም ይሖዋ የምድር ሉዓላዊ ገዥ የመሆኑ መግለጫና የአምላክ መንግሥት ተምሳሌት የሆነችው የይሁዳ ዋና ከተማ ነበረች። በ607 ከዘአበ ከተማዋ ስትጠፋ የይሁዳ የአምላክ መንግሥት ተምሳሌትነት አከተመ። (1 ዜና መዋዕል 29:23፤ 2 ዜና መዋዕል 36:17-21) በምስሉ የብረታ ብረት አካላት የተመሰሉት በተከታታይ የተነሡት የዓለም ኃያላን ከዚህ በኋላ የአምላክ መንግሥት ተምሳሌት ጣልቃ ሳይገባባቸው የዓለም የበላይነታቸውን ሊያሳዩ ይችላሉ። በጥንቱ ዓለም እጅግ ውድ በነበረው የብረት ዓይነት ማለትም በወርቅ የተመሰለው የምስሉ ራስ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን በማጥፋት ይህንን መንግሥት የመገልበጥ ልዩ ክብር አግኝቷል።—በገጽ 63 ላይ የሚገኘውን “አንድ ጦረኛ ንጉሥ ሰፊ ግዛት መሠረተ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
9. በወርቁ ራስ የተመሰለው ምንድን ነው?
9 ለ43 ዓመታት ያህል የገዛው ናቡከደነፆር የባቢሎንን ግዛት የሚያስተዳድረው ሥርወ መንግሥት ቁንጮ ነበር። ሥርወ መንግሥቱ አማቹን ናቦኒደስንና ታላቁን ልጁን ኢቭል ሜሮዳክን ይጨምራል። ይህ ሥርወ መንግሥት የናቦኒደስ ልጅ የሆነው ብልጣሶር እስከሞተበት እስከ 539 ከዘአበ ድረስ ለተጨማሪ 43 ዓመታት ቀጥሏል። (2 ነገሥት 25:27፤ ዳንኤል 5:30) በመሆኑም በሕልሙ ውስጥ የታየው ምስል የወርቅ ራስ የሚያመለክተው ናቡከደነፆርን ብቻ ሳይሆን መላውን የባቢሎናውያን የአገዛዝ መስመር ነው።
10. (ሀ) የናቡከደነፆር ሕልም የባቢሎን የዓለም ኃይል እንደማይዘልቅ የጠቆመው እንዴት ነው? (ለ) ነቢዩ ኢሳይያስ ባቢሎንን ድል ስለሚያደርጋት ሰው ምን ትንቢት ተናግሯል? (ሐ) ሜዶ ፋርስ ከባቢሎን ያነሰ የሆነው በምን መልኩ ነው?
10 ዳንኤል ለናቡከደነፆር እንዲህ አለ:- “ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል።” (ዳንኤል 2:39) የናቡከደነፆርን ሥርወ መንግሥት የሚተካው በምስሉ የብር ደረትና እጆች የተመሰለው መንግሥት ነው። ከ200 ዓመታት በፊት ኢሳይያስ የድል አድራጊው ንጉሥ ስም ቂሮስ እንደሚሆን ሳይቀር በመጥቀስ ስለዚህ መንግሥት ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 13:1-17፤ 21:2-9፤ 44:24–45:7, 13) ይህ የሜዶ ፋርስ ግዛት ነበር። ሜዶ ፋርስ ከባቢሎን ግዛት የማይተናነስ ታላቅ ሥልጣኔ የነበረው ግዛት ቢሆንም ከኋላ የተነሣው ይህ መንግሥት ከወርቅ ያነሰ ዋጋ ባለው ብር ተመስሏል። ኢየሩሳሌምን መዲናው ያደረገውንና የአምላክ መንግሥት ተምሳሌት የሆነውን የይሁዳን መንግሥት የመገልበጥ ክብር ሳያገኝ በመቅረቱ ከባቢሎን የዓለም ኃይል ያነሰ እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል።
11. የናቡከደነፆር ሥርወ መንግሥት ከሕልውና ውጭ የሆነው መቼ ነው?
11 ዳንኤል ይህን ሕልም ከፈታ ከ60 ዓመታት በኋላ የናቡከደነፆር ሥርወ መንግሥት ሲገለበጥ በዓይኑ ተመልክቷል። ዳንኤል በ539 ከዘአበ ጥቅምት 5/6 ሌሊት የሜዶ ፋርስ ሠራዊት የማትደፈር መስላ ትታይ የነበረችውን ባቢሎንን ድል አድርጎ ብልጣሶርን ሲገድል እዚያው ነበር። ብልጣሶር ሲሞት በሕልም በታየው ምስል እንደ ወርቅ ራስ ሆኖ የተገለጸው የባቢሎን ግዛት አከተመ።
ግዞተኞቹ ሕዝቦች በአንድ መንግሥት አማካኝነት ነፃ ወጡ
12. ቂሮስ በ537 ከዘአበ ያወጣው አዋጅ በግዞት የነበሩትን አይሁዳውያን የጠቀማቸው እንዴት ነው?
12 በ539 ከዘአበ ሜዶ ፋርስ ገናና የዓለም ኃያል በመሆን የባቢሎንን ግዛት ተካች። ሜዶናዊው ዳርዮስ በ62 ዓመት ዕድሜው ድል የተነሳችው የባቢሎን ከተማ የመጀመሪያ ገዥ ሆነ። (ዳንኤል 5:30, 31) እርሱና የፋርሱ ቂሮስ ጥምረት ፈጥረው የሜዶ ፋርስን ግዛት ለጥቂት ጊዜ አስተዳድረዋል። ዳርዮስ ሲሞት ቂሮስ የፋርስ ግዛት ብቸኛ ራስ ሆነ። የቂሮስ መንገሥ በባቢሎን የነበሩት አይሁዳውያን ከምርኮ ነፃ እንዲወጡ አድርጓል። በ537 ከዘአበ ቂሮስ በባቢሎን የነበሩት አይሁዳውያን ግዞተኞች ወደ አገራቸው ተመልሰው ኢየሩሳሌምንና የይሖዋን ቤተ መቅደስ መልሰው እንዲገነቡ የሚፈቅድ አዋጅ አወጣ። ይሁንና በይሁዳና በኢየሩሳሌም የአምላክ መንግሥት ተምሳሌት የሆነ መንግሥት መልሶ አልተቋቋመም።—2 ዜና መዋዕል 36:22, 23፤ ዕዝራ 1:1–2:2ሀ
13. ናቡከደነፆር በሕልሙ ያየው ምስል የብር ደረትና እጆች ምን ያመለክታሉ?
13 በሕልሙ ውስጥ የታየው ምስል የብር ደረትና እጆች ከታላቁ ቂሮስ ጀምሮ ያሉትን የፋርስ ነገሥታት መስመር የሚያመለክት ነው። ይህ ሥርወ መንግሥት ከ200 ለሚበልጡ ዓመታት ዘልቋል። ቂሮስ የሞተው በ530 ከዘአበ በወታደራዊ ዘመቻ ላይ እያለ መሆኑ ይታመናል። በፋርስ ግዛት ከእርሱ በኋላ ከተነሡት 12 ነገሥታት መካከል ቢያንስ ሁለቱ ለተመረጡት የይሖዋ ሕዝቦች ጥሩ አመለካከት ነበራቸው። ከእነርሱ መካከል አንዱ ቀዳማዊ ዳርዮስ (ፋርሳዊ) ሲሆን ሌላው ደግሞ ቀዳማዊ አርጤክስስ ነው።
14, 15. ታላቁ ዳርዮስና ቀዳማዊ አርጤክስስ ለአይሁዳውያኑ ምን እገዛ አድርገውላቸዋል?
14 ቀዳማዊ ዳርዮስ በፋርስ ነገሥታት መስመር ከታላቁ ቂሮስ በኋላ የተነሣ ሦስተኛ ንጉሥ ነው። ከእርሱ በፊት የነበሩት ሁለቱ ዳግማዊ ካምቢሰስና ወንድሙ ባርዲያ (ወይም ጋውማታ በሚል ስም የሚታወቀው አስመሳዩ ካህን) ናቸው። ታላቁ ዳርዮስ በመባል የሚታወቀው ቀዳማዊ ዳርዮስ መንበረ ሥልጣኑን በጨበጠበት በ521 ከዘአበ የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ መልሶ የመገንባቱ ሥራ በእገዳ ሥር ነበር። አሕምታ በተባለው ቦታ በነበረው ቤተ መጻሕፍት የቂሮስ አዋጅ የሰፈረበት መዝገብ በተገኘ ጊዜ ዳርዮስ በ520 ከዘአበ እገዳውን ከማንሳት የበለጠ ነገርም አድርጎላቸዋል። ከንጉሡ ገንዘብ ለቤተ መቅደሱ መልሶ ግንባታ የሚሆን ወጪ ሳይቀር ሰጥቷቸዋል።—ዕዝራ 6:1-12
15 የአይሁዳውያንን የመልሶ መቋቋም ጥረት የደገፈው ቀጣዩ የፋርስ ገዥ ደግሞ በአባቱ በአሕሻዊሮስ (ቀዳማዊ ዜርሰስ) ፋንታ በ475 ከዘአበ የነገሠው ቀዳማዊ አርጤክስስ ነው። አርጤክስስ ቀኝ እጁ ከግራ እጁ ይረዝም ስለነበር ሎንጊማነስ በሚል የቅጽል ስምም ይታወቅ ነበር። በነገሠ በ20ኛው ዓመት ማለትም በ455 ከዘአበ አይሁዳዊ ወይን ጠጅ አሳላፊውን ነህምያን በይሁዳ ላይ ገዥ እንዲሆን በመሾም የኢየሩሳሌምን ቅጥር መልሶ የመገንባት ተልእኮ ሰጠው። ይህም በዳንኤል ምዕራፍ ዘጠኝ ውስጥ የተጠቀሰውና መሲሕ ወይም ክርስቶስ የሆነው የናዝሬቱ ኢየሱስ የሚገለጥበትንና የሚሞትበትን ጊዜ የሚጠቁመው ‘ሰባ የዓመታት ሳምንት’ መጀመሩን የሚያበስር ነበር።—ዳንኤል 9:24-27፤ ነህምያ 1:1፤ 2:1-18
16. የሜዶ ፋርስ የዓለም ኃይል ወደ ፍጻሜው የመጣው መቼና በየትኛው ንጉሥ ወቅት ነው?
16 ከስድስቱ ነገሥታት መካከል የመጨረሻ የሆነውና ከቀዳማዊ አርጤክስስ ቀጥሎ መንበረ ሥልጣኑን የጨበጠው ሳልሳዊ ዳርዮስ ነው። በ331 ከዘአበ በጥንቷ ነነዌ አቅራቢያ በምትገኘው በጋውጋሜላ በታላቁ እስክንድር ከፍተኛ ሽንፈት በደረሰበት ጊዜ ግዛቱ በድንገት እንዳልነበር ሆኗል። ይህ ሽንፈት በናቡከደነፆር ሕልም በታየው ምስል የብር አካሎች የተመሰለው የሜዶ ፋርስ የዓለም ኃይል እንዲያከትም አድርጓል። ከዚህ ተከትሎ የሚመጣው ኃይል ደግሞ በአንድ ጎኑ አየል ያለ ሲሆን በሌላ ጎኑ ደግሞ ደከም ያለ ነው። ዳንኤል የናቡከደነፆርን ሕልም ሲፈታ የተናገራቸውን ተጨማሪ ነገሮች ስንመለከት ይህ ይበልጥ ግልጽ ይሆንልናል።
ሰፊ ግን አናሳ መንግሥት
17-19. (ሀ) የናስ ሆዱና ጭኑ የሚያመለክቱት የትኛውን የዓለም ኃይል ነው? ግዛቱስ ምን ያህል ሰፊ ነበር? (ለ) ሳልሳዊ እስክንድር ማን ነበር? (ሐ) ግሪክኛ ዓለም አቀፍ ቋንቋ የሆነው እንዴት ነው? ለምንስ ሥራ እጅግ ተስማሚ ሆኖ ተገኝቷል?
17 ዳንኤል የዚያ ግዙፍ ምስል ሆድና ጭን “በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ ሌላ ሦስተኛ የናስ መንግሥት” መሆኑን ለናቡከደነፆር ነግሮታል። (ዳንኤል 2:32, 39) ይህ ሦስተኛ መንግሥት ከባቢሎኒያና ከሜዶ ፋርስ ተከትሎ የሚመጣ ነው። ናስ ከብር እንደሚያንስ ሁሉ አዲሱ የዓለም ኃይልም የይሖዋን ሕዝቦች ነፃ ማውጣትን የመሰለ መብት ስለማያገኝ ከሜዶ ፋርስ ያነሰ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንደ ናስ የተመሰለው መንግሥት “በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ” መሆኑ ከባቢሎኒያም ሆነ ከሜዶ ፋርስ ይበልጥ ሰፊ እንደሚሆን የሚጠቁም ነው። ይህንን የዓለም ኃያል በሚመለከት ታሪክ ምን ይላል?
18 ልበ ትልቁ ሳልሳዊ እስክንድር በ336 ከዘአበ በ20 ዓመቱ የመቄዶንያን የሥልጣን ኮርቻ ከተቆናጠጠ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የወረራ ዘመቻውን ተያያዘው። ከተቀዳጃቸው ወታደራዊ ድሎች የተነሣ ታላቁ እስክንድር ተብሏል። ድል በድል ላይ እየተቀዳጀ ወደ ፋርስ ግዛት ገሰገሰ። በ331 ከዘአበ ሳልሳዊ ዳርዮስን በጋውጋሜላ ድል ሲያደርገው የፋርስ ግዛት መንኮታኮት በመጀመሩ እስክንድር፣ ግሪክ አዲስ የዓለም ኃይል ሆና ብቅ እንድትል አድርጓል።
19 እስክንድር በጋውጋሜላ ከተቀዳጀው ድል በኋላ እንደ ባቢሎን፣ ሱሳ፣ ፐርሴፐለስና አሕምታ ያሉትን የፋርስ መዲናዎች በየተራ ያዛቸው። የቀረውንም የፋርስ ግዛት በመጠቅለል በወረራ የተያዘ ግዛቱን እስከ ምዕራብ ሕንድ ድረስ አስፋፋ። በወረራው በተያዙት ግዛቶች ውስጥ የግሪክ ማኅበረሰቦች ተቋቋሙ። በዚህ መንገድ የግሪክ ቋንቋና ባሕል በመላው ግዛት ተስፋፋ። እንዲያውም የግሪካውያኑ ግዛት ከዚያ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ሆኖ ነበር። ዳንኤል አስቀድሞ እንዳለው የናሱ መንግሥት ‘በምድር ሁሉ ላይ ነግሷል።’ የዚህ ውጤት ከሆኑት ነገሮች አንዱ ግሪክኛ (ኮይኔ) ዓለም አቀፍ ቋንቋ መሆኑ ነው። ሐሳብን በትክክል ለመግለጽ የሚያስችል ቋንቋ በመሆኑ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለመጻፍና የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማስፋፋት እጅግ አመቺ ሆኖ ተገኝቷል።
20. ታላቁ እስክንድር ከሞተ በኋላ የግሪክ ግዛት ምን ሆነ?
20 ታላቁ እስክንድር የዓለም ገዥ ሆኖ የቆየው ለስምንት ዓመታት ብቻ ነው። እስክንድር ገና የ32 ዓመት ሰው ሳለ በአንድ ትልቅ ግብዣ ላይ ከተገኘ በኋላ ታምሞ ብዙም ሳይቆይ በ323 ከዘአበ ሰኔ 13 ዕለት ሞተ። ከጊዜ በኋላም ግዙፍ የነበረው ግዛቱ ለአራት ክልሎች ተከፋፍሎ በእርሱ አራት ጄኔራሎች ይተዳደር ጀመር። በዚህ መንገድ ከአንዱ ታላቅ መንግሥት ወጥተው የነበሩት አራት መንግሥታትም ከጊዜ በኋላ በሮማ ግዛት ተውጠዋል። ከእነዚህ አራት መንግሥታት መካከል የመጨረሻ የሆነውና በግብጽ የነበረው የቶልማይክ ሥርወ መንግሥት በ30 ከዘአበ በሮም እጅ እስከወደቀበት ጊዜ ድረስ እንደ ናስ ያለው የዓለም ኃይል ቀጥሏል።
የሚያደቅቅና የሚፈጭ መንግሥት
21. ዳንኤል ‘አራተኛውን መንግሥት’ የገለጸው እንዴት ነው?
21 ዳንኤል በሕልም ስለታየው ምስል የሚሰጠውን ገለጻ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “አራተኛውም መንግሥት [ከባቢሎን፣ ከሜዶፋርስና ግሪክ በኋላ ያለው] ሁሉን እንደሚቀጠቅጥና እንደሚያደቅቅ ብረት ይበረታል፤ እነዚህንም ሁሉ እንደሚፈጭ ብረት ይቀጠቅጣል ይፈጭማል።” (ዳንኤል 2:40) ለመፍጨት ባለው ጥንካሬና ችሎታ ረገድ ይህ የዓለም ኃይል እንደ ብረት ሆኗል፤ ማለትም በወርቅ፣ በብር ወይም በናስ ከተመሰሉት ግዛቶች የበለጠ ጥንካሬ አለው ማለት ነው። የሮማ ግዛት እንዲህ ያለ ኃይል ነበር።
22. የሮማ ግዛት እንደ ብረት የነበረው በምን መንገድ ነው?
22 ሮም የግሪክን ግዛት ፈጭቶና አድቅቆ የዓለም ኃይል የነበሩትን የሜዶ ፋርስና የባቢሎን ቅሪቶች ሁሉ ውጧቸው ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ያውጀው ለነበረው የአምላክ መንግሥት ደንታ ቢስ በመሆን በ33 እዘአ በመከራ እንጨት ላይ ሰቅሎ ገድሎታል። ሮም እውነተኛውን ክርስትናም ለማድቀቅ በማሰብ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት አሳድዷል። ከዚህም በላይ ሮማውያን በ70 እዘአ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን አውድመዋል።
23, 24. የምስሉ ቅልጥሞች ከሮማ ግዛት በተጨማሪ ማንን ያመለክታሉ?
23 በናቡከደነፆር ሕልም ውስጥ የታየው ምስል የብረት ቅልጥሞች የሚያመለክቱት የሮማን ግዛት ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ቅጥያዎቹንም ጭምር ነው። በራእይ 17:10 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን የሚከተሉትን ቃላት ልብ በል:- “ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል አንዱም አለ፣ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም፣ ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል።” ሐዋርያው ዮሐንስ እነዚህን ቃላት የጻፈው በሮማውያን ተይዞ በፍጥሞ ደሴት እስር ላይ በነበረበት ጊዜ ነው። አምስቱ የወደቁት ነገሥታት ወይም የዓለም ኃይሎች ግብጽ፣ አሦር፣ ባቢሎን፣ ሜዶ ፋርስና ግሪክ ናቸው። ስድስተኛ የሆነው የሮማ ግዛት ገና ሥልጣን ላይ ነበር። ይሁን እንጂ እሱም ቢሆን ሊያልፍና በሮማ ተይዘው ከነበሩት ግዛቶች መካከል ሰባተኛ የዓለም ኃይል ሊነሳ ይገባ ነበር። ይህስ ምን ዓይነት የዓለም ኃይል ይሆን?
24 በአንድ ወቅት ብሪታንያ የሮማ ግዛት ሰሜናዊ ምዕራብ ክፍል ነበረች። ይሁን እንጂ በ1763 ብሪታንያ ሰፊ ግዛት ሆና ማለትም ሰባቱን ባሕሮች የተቆጣጠረችው ብሪታንያ ተብላ ነበር። በ1776 አሥራ ሦስት የአሜሪካ ግዛቶች ነፃነታቸውን በማወጅ ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ ተባሉ። ይሁን እንጂ በኋለኞቹ ዓመታት ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ በጦርነትና በሰላም ጊዜ አጋሮች መሆናቸውን አሳይተዋል። በዚህ መልኩ የአንግሎ አሜሪካ ጥምረት በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት ሰባተኛው የዓለም ኃይል ሆኖ ብቅ ብሏል። ልክ እንደ ሮማ ግዛት “የብረት ብርታት” ያለውና እንደ ብረት የበረታ ሥልጣን ያለው ግዛት ሆኗል። በመሆኑም የምስሉ የብረት ቅልጥም የሮማን ግዛትና የአንግሎ አሜሪካን ጥምር የዓለም ኃይል የሚጨምር ነው።
በቀላሉ የሚፈረካከስ ውሕደት
25. ዳንኤል ስለ ምስሉ እግሮችና ስለ እግሮቹ ጣቶች ምን ብሏል?
25 ዳንኤል በመቀጠል ለናቡከደነፆር እንዲህ አለው:- “እግሮቹና ጣቶቹም እኩሉ ሸክላ እኩሉም ብረት ሆኖ እንዳየህ፣ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፤ ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየሁ[ህ]፣ የብረት ብርታት ለእርሱ ይሆናል። የእግሮቹም ጣቶች እኩሉ ብረት እኩሉም ሸክላ እንደ ነበሩ፣ እንዲሁ መንግሥቱ እኩሉ ብርቱ እኩሉ ደካማ ይሆናል። ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየህ፣ እንዲሁ ከሰው ዘር ጋር ይደባለቃሉ፤ ነገር ግን ብረት ከሸክላ ጋር እንደማይጣበቅ፣ እንዲሁ እርስ በርሳቸው አይጣበቁም።”—ዳንኤል 2:41-43
26. በእግሩና በእግሮቹ ጣቶች የተመሰለው አገዛዝ ብቅ የሚለው መቼ ነው?
26 ናቡከደነፆር በሕልሙ ባየው ምስል የተለያዩ አካሎች የተወከሉት የዓለም ኃይሎች መፈራረቅ ከራሱ አንስቶ እስከ እግሮቹ ድረስ ቀጥሏል። “እኩሉ ብረት እኩሉ ሸክላ” የሆኑት እግሮቹና የእግሮቹ ጣቶች ‘በፍጻሜው ዘመን’ የሚኖረውን የሰው ልጅ የመጨረሻ የአገዛዝ ዓይነት የሚያመለክት ነው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ይሆናል።—ዳንኤል 12:4
27. (ሀ) እኩሉ ብረት እኩሉ ሸክላ የሆኑት እግሮቹና የእግሮቹ ጣቶች የሚያመለክቱት በዓለም ላይ ያለውን ምን ዓይነት ሁኔታ ነው? (ለ) የምስሉ አሥር የእግር ጣቶች ምን ያመለክታሉ?
27 በሃያኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ የእንግሊዝ ግዛት በምድር ላይ ካለው አራት ሰዎች በአንዱ ላይ ይገዛ ነበር። ሌሎች የአውሮፓ ግዛቶች ደግሞ በሚልዮን በሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ላይ ሥልጣን ነበራቸው። ይሁን እንጂ አንደኛው የዓለም ጦርነት በእነዚህ ግዛቶች ፋንታ የብሔራት ቡድኖች ብቅ ብቅ እንዲሉ ምክንያት ሆኗል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ደግሞ ይህ ዓይነቱ አዝማሚያ በፍጥነት ጨምሯል። ብሔራዊ ስሜት እየተስፋፋ ሲመጣ በዓለም ላይ ያሉ መንግሥታትም ቁጥር በአስገራሚ መጠን ጨምሯል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ ጊዜ አሥር ቁጥር ምድራዊ ሙላትን ስለሚያመለክት የምስሉ አሥር ጣቶች እንደዚህ ያሉትን አብረው የሚኖሩ ኃይሎችና መንግሥታት በሙሉ የሚወክሉ ናቸው።—ከዘጸአት 34:28፤ ማቴዎስ 25:1፤ ራእይ 2:10 ጋር አወዳድር።
28, 29. (ሀ) እንደ ዳንኤል ገለጻ ሸክላው የሚያመለክተው ማንን ነው? (ለ) ስለ ብረቱና ሸክላው ቅልቅል ምን ማለት ይቻላል?
28 ዛሬ የምንኖረው በፍጻሜው ዘመን በመሆኑ የምስሉ የእግር ጣቶች ላይ ደርሰናል። እኩሉ ብረት እኩሉ ሸክላ በሆኑት የምስሉ እግሮችና የእግር ጣቶች የተመሰሉት አንዳንዶቹ መንግሥታት እንደ ብረት ያለ ጥንካሬ ያላቸው ማለትም ፈላጭ ቆራጭ ወይም ጨቋኞች ናቸው። ሌሎች ደግሞ እንደ ሸክላ ናቸው። በምን መንገድ? ዳንኤል ሸክላውን “ከሰው ዘር ጋር” አያይዞ ገልጾታል። (ዳንኤል 2:43) የሰው ልጆች የተሠሩበት ሸክላ በቀላሉ የሚፈረካከስ ነገር ቢሆንም የብረት ጥንካሬ ያላቸው የቆዩት አገዛዞች በመስተዳድሩ ውስጥ ተሰሚነት እንዲኖረው የሚፈልገውን የተራውን ሕዝብ ሐሳብ ለማስተናገድ እየተገደዱ መጥተዋል። (ኢዮብ 10:9 የ1980 ትርጉም) ይሁንና ብረትና ሸክላ ሊጣበቁ እንደማይችሉ ሁሉ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዞችና ተራው ሕዝብም ኅብረት ሊኖራቸው አይችልም። ምስሉ የሚጠፋበት ጊዜ ሲደርስ የዓለም ፖለቲካዊ ሁኔታ የተከፋፈለ ይሆናል!
29 የተከፋፈለው የእግሮቹና የእግሮቹ ጣቶች ሁኔታ መላው ምስል እንዲወድቅ ምክንያት ይሆናልን? ምስሉ የሚገጥመው ዕጣ ምን ይሆን?
አስገራሚ መደምደሚያ!
30. የናቡከደነፆር ሕልም መደምደሚያ ምን እንደሆነ ግለጽ።
30 የሕልሙ መደምደሚያ ምን እንደሆነ ተመልከት። ዳንኤል ለንጉሡ እንዲህ አለ:- “እጅም ሳይነካው ድንጋይ ከተራራው ተፈንቅሎ ከብረትና ከሸክላ የሆነውን የምስሉን እግሮች ሲመታና ሲፈጭ አየህ። የዚያን ጊዜም ብረቱና ሸክላው፣ ናሱና ብሩ ወርቁም በአንድነት ተፈጨ፣ በመከርም ጊዜ በአውድማ ላይ እንዳለ እብቅ ሆነ፤ ነፋስም ወሰደው፣ ቦታውም አልታወቀም፤ ምስሉንም የመታ ድንጋይ ታላቅ ተራራ ሆነ ምድርንም ፈጽሞ ሞላ።”—ዳንኤል 2:34, 35
31, 32. ከናቡከደነፆር ሕልም የመጨረሻ ክፍል ጋር በተያያዘ ምን ነገር በትንቢት ተነግሯል?
31 ትንቢቱ ማብራሪያ በመስጠት ይቀጥላል:- “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች። ድንጋዩም እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ ብረቱንና ናሱን ሸክላውንና ብሩን ወርቁንም ሲፈጨው እንዳየህ፣ እንዲሁ ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ታላቁ አምላክ ለንጉሡ አስታውቆታል፤ ሕልሙም እውነተኛ ፍቺውም የታመነ ነው።”—ዳንኤል 2:44, 45
32 ናቡከደነፆር፣ ዳንኤል ሕልሙን ከማስታወስም አልፎ ትርጓሜውን እንደነገረው ባስተዋለ ጊዜ ‘የነገሥታት ጌታና ምሥጢርን ገላጭ’ የሆነው የዳንኤል አምላክ ብቻ መሆኑን ተናግሯል። ንጉሡም ለዳንኤልና ለሦስቱ ዕብራውያን ጓደኞቹ ትልቅ የኃላፊነት ቦታ ሰጣቸው። (ዳንኤል 2:46-49) ይሁንና ‘የታመነው’ የዳንኤል የሕልም ፍቺ ዛሬ ምን ትርጉም አለው?
‘ምድርን የሞላ ተራራ’
33. ‘ድንጋዩ’ ተፈንቅሎ የወጣው ከየትኛው “ተራራ” ነው? ይህስ የሆነው መቼና እንዴት ነው?
33 ‘የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት’ በጥቅምት 1914 ሲያበቁ “የሰማይ አምላክ” የተቀባውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” አድርጎ በመሾም ሰማያዊ መንግሥት አቋቁሟል።a (ሉቃስ 21:24 NW፤ ራእይ 12:1-5፤ 19:16) በመሆኑም የመሲሐዊው መንግሥት “ድንጋይ” እንደ “ተራራ” ከተመሰለው የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት የወጣው በመለኮታዊ ኃይል እንጂ በሰው እጅ አይደለም። ይህ ሰማያዊ መንግሥት አምላክ ያለመሞትን ባሕርይ ባላበሰው በኢየሱስ ክርስቶስ እጅ ያለ መንግሥት ነው። (ሮሜ 6:9፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:15, 16) በመሆኑም ይህ “የጌታችን [የአምላክ] እና እርሱ የሾመው ክርስቶስ መንግሥት” በሌላ አባባል የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት መግለጫ የሆነው መንግሥት ለማንም አልፎ የሚሰጥ አይደለም። ለዘላለም ጸንቶ ይቆማል።—ራእይ 11:15 NW
34. የአምላክ መንግሥት ‘በእነዚያ ነገሥታት ዘመን’ ተወለደ ለማለት የሚቻለው እንዴት ነው?
34 የዚህ መንግሥት ልደት የተከናወነው ‘በእነዚያ ነገሥታት ዘመን’ ነው። (ዳንኤል 2:44) እነዚህ በአሥሩ የእግሩ ጣቶች የተመሰሉት መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ በብረቱ በናሱ፣ በብሩና በወርቁ የተመሰሉትን መንግሥታትም ይጨምራሉ። እንደ ባቢሎን፣ ፋርስ፣ ግሪክና ሮም ያሉት መንግሥታት የዓለም ኃያላን መሆናቸው ያከተመ ቢሆንም መንግሥቶቻቸው በ1914ም ነበሩ። የቱርኮች የኦቶማን ግዛት በወቅቱ የባቢሎኒያን የግዛት ክልል ይዞ የነበረ ሲሆን በፋርስ (በኢራን) እና በግሪክ እንዲሁም በሮም ኢጣሊያ የሚንቀሳቀሱ ብሔራዊ መንግሥታት ነበሩ።
35. ‘ድንጋዩ’ ምስሉን የሚመታው መቼ ነው? ምስሉስ ሙሉ በሙሉ የሚወገደው በምን መልክ ነው?
35 የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት በቅርቡ የዚህን ምሳሌያዊ ምስል እግሮች ይመታል። በዚህ መንገድ በእግሮቹ የተወከሉት መንግሥታት በሙሉ ደቅቀው ይጠፋሉ። በእርግጥም ‘ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን በሚሆነው’ ጦርነት ያ “ድንጋይ” የሚያደቅበት ኃይል እጅግ ብርቱ ስለሚሆን ምስሉ ዓመድ ይሆናል፤ ከአምላክ የሚመጣውም ነፋስ በመከር ጊዜ በአውድማ ላይ እንዳለ እብቅ ጥርግርግ አድርጎ ይወስደዋል። (ራእይ 16:14, 16) ድንጋዩ ተራራ እስከሚያክል ድረስ ትልቅ እንደሆነና ምድርን እንደሞላ ሁሉ የአምላክ መንግሥትም ‘በመላው ምድር’ ላይ ለውጥ የሚያመጣ መስተዳድራዊ ተራራ ይሆናል።—ዳንኤል 2:35
36. መሲሐዊው መንግሥት የተደላደለ መንግሥት ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
36 መሲሐዊው መንግሥት ሰማያዊ ቢሆንም ሥልጣኑን ወደ ምድራችን በመዘርጋት ለታዛዥ የምድር ነዋሪዎች በረከት ያመጣል። ይህ የተደላደለ መስተዳድር “የማይፈርስ” ከመሆኑም ሌላ ‘ለሌላ ሕዝብ አይሰጥም።’ ሟች የሆኑ ሰብዓዊ ገዥዎች ካሏቸው መንግሥታት በተለየ መልኩ ‘ለዘላለም ጸንቶ ይቆማል።’ (ዳንኤል 2:44) የዚህ መንግሥት ዘላለማዊ ተገዥዎች ከሚሆኑት ሰዎች መካከል ለመሆን ያብቃህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የዚህን መጽሐፍ 6ኛ ምዕራፍ ተመልከት።
ምን አስተውለሃል?
• ናቡከደነፆር በሕልሙ ባየው ግዙፍ ምስል የተለያዩ ክፍሎች የተገለጹት የዓለም ኃይሎች የትኞቹ ናቸው?
• እኩሉ ብረት እኩሉ ሸክላ የሆነው የምስሉ እግርና የእግሮቹ ጣቶች ምን ዓይነት የዓለም ሁኔታ እንደሚኖር ያመለክታሉ?
• ‘ድንጋዩ’ ተፈንቅሎ የወጣው መቼና ከየትኛው “ተራራ” ነው?
• ‘ድንጋዩ’ ምስሉን የሚመታው መቼ ነው?
[ከገጽ 63-67 የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
አንድ ጦረኛ ንጉሥ ሰፊ ግዛት መሠረተ
የባቢሎን አልጋ ወራሽና ሠራዊቱ በሶርያ በምትገኘው ከርከሚሽ በግብጹ ፈርዖን ኑካዑ ሠራዊት ላይ ድል ይቀዳጃል። ድል የተነሡት ግብጻውያን በስተ ደቡብ ወደ ግብጽ ሲሸሹ ባቢሎናውያኑ ያሳድዷቸው ጀመር። ሆኖም ከባቢሎን የመጣ አንድ መልእክት ባለ ድሉ መስፍን ግብጻውያኑን ማሳደድ ትቶ ወደኋላ እንዲመለስ አስገደደው። መልእክቱ አባትህ ናቦፖላሳር ሞቷል የሚል ነበር። ምርኮኞቹንና የዘረፉትን ዕቃ ይዞ የመመለሱን ኃላፊነት ለጄኔራሎቹ ሰጥቶ ናቡከደነፆር በፍጥነት ወደ አገሩ በመመለስ የአባቱን ቦታ ያዘ።
በዚህ መንገድ ናቡከደነፆር በ624 ከዘአበ በባቢሎን የንግሥና መንበር ላይ በመቀመጥ የአዲሱ የባቢሎን ግዛት ሁለተኛ ንጉሥ ሆነ። ለ43 ዓመታት በቆየው የግዛት ዘመኑ በአንድ ወቅት የዓለም ኃይል በነበረው አሦር ተይዘው የነበሩትን አካባቢዎች በመያዝ በስተ ሰሜን ሶርያን፣ በስተ ምዕራብ ፍልስጤምን እስከ ግብፅ ድንበር ድረስ በመጠቅለል ግዛቱን አስፍቷል።—ካርታውን ተመልከት
ናቡከደነፆር በነገሠ በአራተኛ ዓመቱ (በ620 ከዘአበ) ይሁዳን በእንደራሴ የምትተዳደር ግዛቱ አደረጋት። (2 ነገሥት 24:1) ከሦስት ዓመታት በኋላ የአይሁዳውያኑ ማመፅ ኢየሩሳሌም በባቢሎን እንድትከበብ ምክንያት ሆኗል። ናቡከደነፆር ዮአኪንን፣ ዳንኤልንና ሌሎችንም በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። ከዚህም ሌላ ንጉሡ የይሖዋን ቤተ መቅደስ አንዳንድ ንዋየ ቅድሳት አግዟል። ከዚያም የዮአኪንን አጎት ሴዴቅያስን በይሁዳ እንደራሴ ንጉሥ አድርጎ ሾመው።—2 ነገሥት 24:2-17፤ ዳንኤል 1:6, 7
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሴዴቅያስም ከግብፅ ጋር በማበር ዓመፀ። ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን በድጋሚ የከበበ ሲሆን በ607 ከዘአበ ቅጥሩን በማፍረስ ቤተ መቅደሷን አቃጥሏል፣ ከተማዋንም አውድሟል። የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች በሙሉ ገድሎ ሴዴቅያስን ዓይኑን በማሳወር በእስረኛነት ወደ ባቢሎን ወስዶታል። ናቡከደነፆር አብዛኛውን ሕዝብ በምርኮ ከመውሰዱም ሌላ የቀረውን የቤተ መቅደሱን ንዋየ ቅድሳት ወደ ባቢሎን አግዟል። በዚህ መንገድ “ይሁዳ ከአገሩ ተማረከ።”—2 ነገሥት 24:18–25:21
ናቡከደነፆር 13 ዓመታት የፈጀ ከበባ በማድረግ የጢሮስንም ከተማ በቁጥጥሩ ሥር አድርጓል። በከበባው ወቅት ከራስ ቁሩ መፈጋፈግ የተነሣ የወታደሮቹ ፀጉር ‘ተመልጦና’ በከበባው ወቅት ካከናወኑት የግንባታ ሥራ የተነሣ ትከሻቸውም ‘ተልጦ’ ነበር። (ሕዝቅኤል 29:18) በመጨረሻም ጢሮስ በባቢሎናውያኑ እጅ ወደቀች።
ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው የባቢሎናውያኑ ንጉሥ ብልህ የጦር መሪ ነበር። አንዳንድ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች በተለይም ባቢሎናዊ ምንጭ ያላቸው፣ ፍትሐዊ ንጉሥ እንደሆነም አድርገው ይናገሩለታል። ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ ናቡከደነፆር ፍትሐዊ ነው ብለው አይናገሩም፤ ነገር ግን ሴዴቅያስ ቢያምፅም ‘ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ቢወጣ’ የከፋ ነገር እንደማይገጥመው ኤርምያስ ተናግሮ ነበር። (ኤርምያስ 38:17, 18) ከኢየሩሳሌም ጥፋት በኋላ ደግሞ ናቡከደነፆር ኤርምያስን በአክብሮት ይዞታል። ንጉሡ፣ ኤርምያስን በሚመለከት “ውሰደውና በመልካም ተመልከተው፣ የሚሻውንም ነገር አድርግለት እንጂ ክፉን ነገር አታድርግበት” የሚል ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር።—ኤርምያስ 39:11, 12፤ 40:1-4
ናቡከደነፆር አስተዳዳሪ እንደመሆኑ መጠን የዳንኤልንና የሦስቱ ጓደኞቹን ማለትም አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ የሚል ዕብራዊ ስም የነበራቸውን የሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎን ባሕርይና ችሎታ ለማስተዋል ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም። ከዚህም የተነሣ ንጉሡ በመንግሥቱ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ እንዲያገለግሉ ሾሟቸዋል።—ዳንኤል 1:6, 7, 19-21፤ 2:49
ናቡከደነፆር በተለይ የባቢሎን ዋነኛ አምላክ ለሆነው ለማርዱክ አምልኮ ያደረ ሰው ነበር። ንጉሡ ለዚያ ሁሉ ድል እንዳበቃው አድርጎ የሚያስበው ማርዱክን ነው። በባቢሎን የማርዱክንና የሌሎችን በርካታ የባቢሎን አማልክት ቤተ መቅደሶች ገንብቷል፤ አስውቧልም። በዱራ ሜዳ ያቆመው የወርቅ ምስል በማርዱክ ስም የተሠራ ሳይሆን አይቀርም። ናቡከደነፆር የውጊያ ዕቅድ ሲያወጣ በጥንቆላ በእጅጉ ይጠቀም የነበረ ይመስላል።
ናቡከደነፆር በቅጥር የተከበበችውን የዘመኑን ታላቅ ከተማ ባቢሎንን መልሶ ለመገንባት በመቻሉ ይኩራራ ነበር። ናቡከደነፆር አባቱ ጀምሮት የነበረውን የከተማዋን ግዙፍ የድርብ ቅጥር ግንባታ በማጠናቀቅ ዋና ከተማዋ ጨርሶ የማትደፈር መስላ እንድትታይ አድርጓል። ንጉሡ በከተማዋ እምብርት የሚገኘውን አንድ ቤተ መንግሥት ከማደሱም ሌላ ሁለት ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ ተለዋጭ ቤተ መንግሥት አሠርቷል። ናቡከደነፆር የአገሯን ኮረብቶችና ደኖች ትናፍቅ የነበረችውን ሜዶናዊቷን ንግሥቱን ፍላጎት ለማርካት ሲል ከጥንቱ ዓለም ሰባት ድንቅ ነገሮች መካከል አንዱ እንዲሆን የተመረጠውን ገደል ላይ እንዳለ ሆኖ የተገነባ የአትክልት ስፍራ እንዳዘጋጀ ይነገራል።
ንጉሡ ባቢሎን በሚገኘው ቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ሲመላለስ “ይህች እኔ በጉልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?” ብሎ ነበር። “ቃሉም ገና በንጉሡ አፍ ሳለ” እንደ እንስሳ ሆነ። ዳንኤል አስቀድሞ እንደተናገረው ለሰባት ዓመታት ያህል ለንግሥና የማይበቃ ሆኖ ሣር በልቷል። ዘመኑ ሲፈጸምም መንግሥቱ ለናቡከደነፆር ተመልሶለት እስከሞተበት እስከ 582 ከዘአበ ድረስ ገዝቷል።—ዳንኤል 4:30-36
ምን አስተውለሃል?
ስለ ናቡከደነፆር ምን ማለት ይቻላል?
• የጦር መሪነቱን በሚመለከት
• አስተዳዳሪነቱን በሚመለከት
• የማርዱክ አምላኪ መሆኑን በሚመለከት
• የግንባታ ሥራውን በሚመለከት
[ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የባቢሎን ግዛት
ቀይ ባሕር
ኢየሩሳሌም
የኤፍራጥስ ወንዝ
የጤግሮስ ወንዝ
ነነዌ
ሱሳ
ባቢሎን
ኡር
[ሥዕል]
በዘመኑ እጅግ ታላቅ የነበረችው ባለቅጥሯ የባቢሎን ከተማ
[ሥዕል]
የማርዱክ ምልክት ደራጎን ነበር
[ሥዕል]
ገደል ላይ እንዳለ ሆኖ የተሠራው ዝነኛው የባቢሎን የአትክልት ስፍራ
[በገጽ 56 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
በዳንኤል ትንቢት የተገለጹት የዓለም ኃይሎች
ግዙፉ ምስል (ዳንኤል 2:31-45)
ባቢሎኒያ ከ607 ከዘአበ ጀምሮ
ሜዶ ፋርስ ከ539 ከዘአበ ጀምሮ
ግሪክ ከ331 ከዘአበ ጀምሮ
ሮም ከ30 ከዘአበ ጀምሮ
የአንግሎ አሜሪካ ዓለም ኃይል ከ1763 ጀምሮ
በፖለቲካ የተከፋፈለው ዓለም በፍጻሜው ዘመን
[በገጽ 47 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]
[በገጽ 58 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]