አንድ ንጉሥ የይሖዋን መቅደስ አረከሰ
“ነገር ግን አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ይበረታሉ [ያሸንፋሉ አዓት]። ” — ዳንኤል 11:32
1, 2. የሰው ልጅ ታሪክ ከ2,000 ለሚበልጡ ዓመታት ምን ከፍተኛ ግጭት አልተለየውም?
ሁለት ተቀናቃኝ ነገሥታት የበላይነትን ለመቀዳጀት ባላቸው ኃይል ሁሉ ይታገላሉ። ጦርነቱ በቀጠለባቸው ባለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት እየተፈራረቁ አንዳቸው ሌላውን ሲጥለውና የበላይነቱን ሲቀዳጅ ኖረዋል። ይህ ትግል በዘመናችን በምድር የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ ነክቷቸዋል፣ የአምላክንም ሕዝቦች ንጹሕ አቋም ፈትኗል። ትግላቸው ሁለቱም ኃይሎች ከሩቁ ባላዩት ክንዋኔ አማካኝነት ወደ ፍጻሜው ይመጣል። ይህ ታሪካዊ ድራማ በጥንት ዘመን ለነበረው ለነቢዩ ዳንኤል አስቀድሞ ተገልጦለት ነበር። — ዳንኤል ከምዕራፍ 10 እስከ ምዕራፍ 12
2 ትንቢቱ እስካሁን ባላቋረጠው የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ ጠላትነት ላይ ያተኮረ መሆኑ “ፈቃድህ በምድር ይሁን ”a በተባለው በእንግሊዝኛ ቋንቋ በታተመ መጽሐፍ ላይ በሰፊው ተብራርቷል። በመጀመሪያ የሰሜኑ ንጉሥ ከእስራኤል በስተሰሜን ይገኝ የነበረው ሶርያ መሆኑ በዚያ መጽሐፍ ላይ ተገልጾ ነበር። ከጊዜ በኋላ የሱን ቦታ የሮም መንግሥት ወሰደ። መጀመሪያ ላይ የደቡቡ ንጉሥ ግብፅ ነበር።
በፍጻሜ ዘመን ውስጥ የታየው ግጭት
3. በመልአኩ መግለጫ መሠረት ስለ ሰሜኑ ንጉሥና ስለ ደቡቡ ንጉሥ የሚናገረውን ትንቢት መረዳት የሚቻለው መቼ ነው? እንዴትስ?
3 እነዚህን ነገሮች ለዳንኤል የሚገልጥለት መልአክ እንዲህ አለ:- “ዳንኤል ሆይ፣ አንተ ግን እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ፣ መጽሐፉንም አትም፤ ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፣ እውቀትም ይበዛል።” (ዳንኤል 12:4) አዎን፣ ትንቢቱ በ1914 ከጀመረው የፍጻሜ ዘመን ጋር የተያያዘ ነገር አለው። በዚህ ታሪካዊ ዘመን ብዙዎች ቅዱሳን ጽሑፎችን “ይመረምራሉ”፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን መረዳትን የሚጨምረው እውነተኛ እውቀት ይበዛል። (ምሳሌ 4:18) ወደዚህ ዘመን ጠልቀን በገባን ቁጥር ስለ ዳንኤል ትንቢቶች የተገኘው ዝርዝር እውቀት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ታዲያ አሁን “ፈቃድህ በምድር ይሁን ” የተባለው መጽሐፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ታትሞ ከወጣ ከ35 ዓመታት በኋላ በ1993 የሰሜኑን ንጉሥና የደቡቡን ንጉሥ የሚመለከተውን ትንቢት እንዴት አድርገን መረዳት አለብን?
4, 5. (ሀ) ስለ ሰሜኑ ንጉሥና ስለ ደቡቡ ንጉሥ በሚናረገው የዳንኤል ትንቢት ውስጥ 1914 የተጠቀሰው የት ላይ ነው? (ለ) በመልአኩ መግለጫ መሠረት በ1914 ምን ነገር ይሆናል?
4 በ1914 የጀመረው የፍጻሜ ዘመን በአንደኛው የዓለም ጦርነትና ኢየሱስ በትንቢቱ በገለጻቸው ሌሎች መከራዎች ተለይቶ ታውቋል። (ማቴዎስ 24:3, 7, 8) ይህንን ዓመት በዳንኤል ትንቢት ውስጥ ማመልከት እንችላለንን? አዎ፣ እንችላለን። የፍጻሜው ዘመን መጀመሪያ በዳንኤል 11:29 ላይ ‘የተወሰነው ጊዜ’ ተብሎ ተገልጿል። (“ፈቃድህ በምድር ይሁን ” የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ገጽ 269–270 ተመልከት።) በዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ በትንቢት ተለይቶ በተጠቀሰው 2,520 ዓመታት ማለቂያ ላይ የተፈጸመ ነገር ስለሆነ፣ ይህ ዘመን በዳንኤል ጊዜ በይሖዋ አስቀድሞ የተወሰነ ዘመን ነበር።
5 ዳንኤል ወጣት ከነበረበትና ኢየሩሳሌም ከጠፋችበት ከ607 ከዘአበ ጀምሮ እስከ 1914 ድረስ ያሉት እነዚህ 2,520 ዓመታት “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” ተብለው ተጠርተዋል። (ሉቃስ 21:24 አዓት) እነዚህ ቀናት ማብቃታቸውን የሚያስታውቁ ምን ዓይነት ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ይከሰታሉ? አንድ መልአክ የሚሆነውን ነገር ለዳንኤል ገልጦለታል። መልአኩ “በተወሰነውም ጊዜ [የሰሜኑ ንጉሥ] ይመለሳል ወደ ደቡብም ይመጣል፤ ነገር ግን ኋለኛው እንደ ፊተኛው አይሆንም” በማለት ተናገረ። — ዳንኤል 11:29
ንጉሡ በአንድ ጦርነት ላይ ተሸነፈ
6. በ1914 የሰሜኑ ንጉሥ ማን ነበር? የደቡቡስ ንጉሥ ማን ነበር?
6 በ1914 የሰሜኑን ንጉሥ ቦታ በቄሣር ቪልኸልም የሚመራው የጀርመን መንግሥት ወስዶት ነበር። (“ቄሣር” የሚለው ከሮማውያን የተወሰደ የማዕረግ ስም ነው።) በአውሮፓ የተቀሰቀሰው ጦርነት በሰሜኑ ንጉሥና በደቡቡ ንጉሥ መካከል ባለው ያላሰለሰ ግጭት ውስጥ የታየ ሌላው ገጽታ ነው። በዚህ ጊዜ የደቡቡን ንጉሥ የተካው የመጀመሪያው የደቡብ ንጉሥ ግዛት የነበረችውን ግብጽን ቶሎ ብሎ የተቆጣጠረው የእንግሊዝ መንግሥት ነው። ጦርነቱ እየገፋ ሲሄድ እንግሊዝ የቀድሞ ቅኝ ግዛቷ በነበረችው በዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ መታገዝ ጀመረች። የደቡቡ ንጉሥ የእንግሊዝና የአሜሪካ ጥምር የዓለም ኃያል በመሆን በታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ኃያል መንግሥት ሆነ።
7, 8. (ሀ) በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የኋለኛው “እንደ ፊተኛው” ያልሆነው እንዴት ነበር? (ለ) የአንደኛው የዓለም ጦርነት ውጤት ምን ነበር? ነገር ግን በትንቢቱ መሠረት የሰሜኑ ንጉሥ ከዚህ የተነሣ ምን አደረገ?
7 በመጀመሪያዎቹ የሁለቱ ነገሥታት ግጭቶች የሰሜን ንጉሥ የነበረው የሮማ መንግሥት ያለማቋረጥ ድልን ሲቀዳጅ ቆይቶ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን፣ ‘ኋለኛው እንደ ፊተኛው አልሆነለትም።’ ለምን? ምክንያቱም የሰሜኑ ንጉሥ በጦርነቱ ተሸናፊ ስለሆነ ነው። ለመሸነፉ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ “የኪቲም መርከቦች” የሰሜኑን ንጉሥ ለመውጋት ስለ መጡ ነበር። (ዳንኤል 11:30) እነዚህ መርከቦች ምን ነበሩ? በዳንኤል ዘመን ኪቲም የተባለችው ቆጵሮስ ነበረች፤ አንደኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ደግሞ ቆጵሮስ የእንግሊዝ ግዛት ክፍል ተደርጋ ነበር። ከዚህም በላይ ዘ ዞንደርቫን ፒክቶሪያል ኢንሳይክሎፒድያ ኦቭ ዘ ባይብል ኪቲም የሚለው ስም “በአጠቃላይ የምዕራቡን ክፍል በስፋት ሲያመለክት በተለይ እስከ ምዕራቡ የባሕር ዳርቻ ድረስ የተዘረጋውን ክፍል ያመለክታል” ብሏል። ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “የኪቲም መርከቦች” የሚለውን “በምዕራባዊው የባሕር ዳርቻ የሚገኙት መርከቦች” በማለት ተርጉሞታል። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የኪቲም መርከቦች የተባሉት በአውሮፓ ምዕራባዊ የባሕር ጠረፍ ላይ የነበሩት የእንግሊዝ መርከቦች ነበሩ። ቆይቶም የእንግሊዝ የባሕር ኃይል ከምዕራባዊው ክፍለ ዓለም ከሰሜን አሜሪካ በመጡት መርከቦች ተጠናክሮ ነበር።
8 እንደዚህ በመሰለ ጥቃት የሰሜኑ ንጉሥ “አዝኖ” በ1918 መሸነፉን አምኖ ተቀበለ። ነገር ግን ፈጽሞ አልጠፋም ነበር። “በቅዱሱም ቃል ኪዳን ላይ ይቆጣል፣ ፈቃዱንም ያደርጋል፤ ተመልሶም ቅዱሱን ቃል ኪዳን የተዉትን ይመለከታል።” (ዳንኤል 11:30) መልአኩ ከላይ ያለውን ትንቢት ተናገረ፤ እንደተናገረውም ተፈጸመ።
ንጉሡ ፈቃዱን ያደርጋል
9. ለአዶልፍ ሂትለር ሥልጣን መያዝ ምክንያት የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው? ‘የፈቀደውን ያደረገውስ’ እንዴት ነው?
9 ጦርነቱ ካበቃ በኋላ በ1918 ድል አድራጊዎቹ ሕብረ ብሔራት የጀርመንን ሕዝቦች ላልተወሰነ ጊዜ በረሃብ ለመቅጣት የሚያስችላቸውን የሰላም ውል ከጀርመን ጋር ተፈራረሙ። ከዚህም የተነሣ በከባድ መከራ ለጥቂት ዓመታት ከተዋጠች በኋላ ጀርመን ለአዶልፍ ሂትለር መነሣት ተመቻችታ ነበር። ሂትለር በ1933 ሥልጣኑን ከጨበጠ በኋላ ወዲያውኑ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች በተወከለው “በቅዱሱ ቃል ኪዳን ላይ” አስከፊ ጥቃት መሰንዘር ጀመረ። በዚህ አድራጎቱም ብዛት ያላቸውን እነዚህን ታማኝ ክርስቲያኖች በጭካኔ በማሳደድ የፈቀደውን አድርጎ ነበር።
10. ሂትለር ድጋፍ ለማግኘት ከእነማን ጋር ተወዳጀ? ከምንስ ውጤት ጋር?
10 ሂትለር በኢኮኖሚያዊና በዲፕሎማሲያዊ መስክም ተሳክቶለት ነበር። በዚህም መስክ የፈቀደውን ለማድረግ ችሎ ነበር። በጥቂት ዓመታት ውስጥ ጀርመንን ቀላል ግምት የማይሰጣት ኃያል መንግሥት አደረጋት። በዚህ ጥረቱ ‘ቅዱሱን ቃል ኪዳን በተዉት ሰዎች’ ታግዟል። እነዚህ ቃል ኪዳኑን የተዉ ሰዎች እነማን ነበሩ? ማስረጃዎቹ እንደሚያረጋግጡት ከአምላክ ጋር የቃል ኪዳን ዝምድና አለን ብለው የሚናገሩ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናቸውን ካቆሙ ግን ዘመናት ያለፉአቸው የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ናቸው። ሂትለር እነዚህን “ቅዱሱን ቃል ኪዳን የተዉትን ሰዎች” እንዲደግፉት በመጥራት የተሳካ ውጤት አግኝቷል። በሮም የነበሩት ጳጳስ ከእሱ ጋር የጋራ ስምምነት አድርገው የነበረ ሲሆን የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም ሆነች በጀርመን ይገኙ ይነበሩት የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያኖች በአሸባሪ ሁኔታ በገዛባቸው 12 ዓመታት ሙሉ ድጋፋቸውን ለሂትለር ሰጥተዋል።
11. የሰሜኑ ንጉሥ ‘መቅደሱን ያረከሰው’ እና ‘የዘወትሩን መሥዋዕት ያስቀረው’ እንዴት ነበር?
11 መልአኩ አስቀድሞ በትክክል እንደ ተናገረው ሂትለር ስለ ተሳካለት ወደ ጦርነቱ ገሰገሰ። “ከእርሱም ጋር ሠራዊቶች ይቆማሉ፣ መቅደሱንም ግንቡንም ያረክሳሉ፣ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ፣ የጥፋትንም ርኩሰት ያቆማሉ።” (ዳንኤል 11:31) በጥንቷ እስራኤል መቅደሱ በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ ክፍል ነበር። ይሁንና አይሁዳውያን ኢየሱስን አንቀበልም ባሉ ጊዜ ይሖዋ እነርሱንም ቤተ መቅደሳቸውንም ሰረዛቸው። (ማቴዎስ 23:37 እስከ 24:2) ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ጀምሮ የይሖዋ ቤተ መቅደስ መንፈሳዊ ሆኗል። ቅዱሰ ቅዱሳኑ በሰማይ ውስጥ ሲሆን መንፈሳዊው አደባባይ ደግሞ የታላቁ ካህን የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች አገልግሎታቸውን የሚያቀርቡበት ምድር ነው። ከ1930ዎቹ ጀምሮ እጅግ ብዙ ሰዎች ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር ተባብረው ይሖዋን ማምለክ ጀምረዋል። ስለሆነም ‘በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ’ ያገለግሉታል ሊባል ይቻላል። (ራእይ 7:9, 15፤ 11:1, 2፤ ዕብራውያን 9:11, 12, 24) የሰሜኑ ንጉሥ ግዛቱን በዘረጋባቸው አገሮች ሁሉ በሚገኙት ቅቡዓን ቀሪዎችና ጓደኞቻቸው ላይ በሚደርሰው የማያቋርጥ ስደት ምክንያት የቤተ መቅደሱ ምድራዊ አደባባይ ረክሶ ነበር። ስደቱ በጣም ጽኑ ከመሆኑ የተነሣ የዘወትሩ መሥዋዕት ማለትም ለይሖዋ ስም ክብር የሚቀርበው ሕዝባዊ መሥዋዕት እንዲቀር ተደረገ። (ዕብራውያን 13:15) ያም ሆኖ ግን ታሪክ እንደሚመሰክረው ያ ሁሉ አሠቃቂ መከራ እየደረሰባቸው ታማኞቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከ“ሌሎች በጎች” ጋር በመሆን በድብቅ መስበካቸውን ቀጥለው ነበር። — ዮሐንስ 10:16
‘ርኩሰቱ’
12, 13. “ርኩሰት” የተባለው ምን ነበር? በታማኝና ልባም ባሪያ አስቀድሞ እንደታየውስ እንደገና የተቋቋመው መቼና እንዴት ነበር?
12 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወደ ማለቂያው እየተቃረበ ሲሄድ ሌላም ነገር ተከሰተ። “የጥፋትንም ርኩሰት ያቆማሉ።” (ዳንኤል 11:31) ኢየሱስም ጭምር የጠቀሰው ይህ “ርኩሰት” በራእይ መጽሐፍ መሠረት ወደ ጥልቁ ሄደ የተባለው ቀይ አውሬ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር እንደሆነ አስቀድሞ ለማወቅ ተችሎ ነበር። (ማቴዎስ 24:15፤ ራእይ 17:8፤ ብርሃን የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ሁለተኛ ክፍል ገጽ 94 ተመልከት።) ወደ ጥልቅ የወረደው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ ነው። ይሁን እንጂ በ1942 በተደረገው የአዲሲቱ ዓለም ቲኦክራሲያዊ የይሖዋ ምስክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ሦስተኛ ፕሬዘዳንት የነበረው ናታን ኤች ኖር በራእይ ምዕራፍ 17 ላይ የሚገኘውን ትንቢት አብራራና አውሬው ከጥልቁ እንደገና እንደሚወጣ አስጠነቀቀ።
13 የእሱን ቃል እውነተኛነት ታሪክ አረጋግጧል። በነሐሴና በጥቅምት 1944 መካከል ላይ በአሜሪካን አገር ዋሽንግተን ዲ ሲ ውስጥ በደምባርተን ኦክስ ሕንፃ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ተብሎ ለሚጠራው ድርጅት ቻርተር የሚሆኑት ሐሳቦች መነደፍ ጀመሩ። ቻርተሩ የቀድሞዋን ሶቪየት ሕብረት ጨምሮ በ51 መንግሥታት ጸደቀና ከጥቅምት 24, 1945 ጀምሮ ድርጅቱ ሥራውን ሲጀምር ሞቶ የነበረው የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ከጥልቁ ውስጥ ወጣ።
14. የሰሜኑ ንጉሥ ማንነት የተለወጠው መቼና እንዴት ነበር?
14 በሁለቱም የዓለም ጦርነቶች ወቅት ጀርመን የደቡቡ ንጉሥ ቀንደኛ ጠላት ሆና ቆይታ ነበር። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የጀርመን ግማሹ ክፍል ከሕብረ ብሔሩ የደቡቡ ንጉሥ ጋር ኅብረት እንዲፈጥር ተደረገ። ሌላው ክፍል ግን ከሌላው ኃይለኛ መንግሥት ጎን እንዲሰለፍ ተደረገ። ከጀርመን የተወሰነውን ክፍል ጨምሮ የኮሙኒስት ፍልስፍናን የሚከተሉ አገሮች የአንግሎ አሜሪካንን ሕብረ ብሔር በጽኑ በመቃወማቸው በሁለቱ ነገሥታት መካከል ያለው ፉክክር ቀዝቃዛውን ጦርነት አስከተለ። — “ፈቃድህ በምድር ይሁን ” የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 264–284 ተመልከት።
ንጉሡና ቃል ኪዳኑ
15. ‘ቃል ኪዳኑን የሚበድሉት’ እነማን ናቸው? ከሰሜኑ ንጉሥስ ጋር ምን ዝምድና ነበራቸው?
15 አሁን መልአኩ “ቃል ኪዳኑን የሚበድሉትንም በማታለል ያስታል” በማለት ተናገረ። (ዳንኤል 11:32) እነዚህ ቃል ኪዳኑን ይበድላሉ የተባሉት እነማን ናቸው? ክርስቲያን ነን ከሚሉት ነገር ግን በድርጊታቸው ክርስትናን ከሚያረክሱት የሕዝበ ክርስትና መሪዎች በቀር ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት “የሶቪየት መንግሥት እናት አገርን ለመከላከል እንዲያስችል ቤተ ክርስቲያኖች ቁሳዊና ሞራላዊ ድጋፍ እንዲሰጡት ለማድረግ ሞክሮ ነበር።” (በዎልተር ኮላርስ የተጻፈው ሪሊጅን ኢን ዘ ሶቪየት ዩኒየን ) ከጦርነቱ በኋላ አሁን የሰሜን ንጉሥ የሆነው ኃያል መንግሥት አምላክ የለሽ አቋም ቢይዝም እንኳ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የቀድሞው ወዳጅነታቸው እንዲቀጥል ለማድረግ ጥረት አድርገዋል።b ከዚህም የተነሣ ሕዝበ ክርስትና ከመቼውም ይበልጥ የዓለም ክፍል በመሆን በይሖዋ ዓይን ርኩስ ከሀዲ ሆናለች። — ዮሐንስ 17:14፤ ያዕቆብ 4:4
16, 17. “ጥበበኞች” የተባሉት እነማን ናቸው? በሰሜኑ ንጉሥ ግዛት ሥርስ ምን ሁኔታዎች አጋጠሟቸው?
16 ታዲያ ስለ እውነተኛ ክርስቲያኖችስ ምን ሊባል ይቻላል? “ነገር ግን አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ይበረታሉ [ያሸንፋሉ አዓት]፣ ያደርጋሉም። በሕዝቡም መካከል ያሉ ጥበበኞች ብዙ ሰዎችን ያስተምራሉ [ለብዙ ሰዎች ማስተዋልን ይሰጣሉ አዓት]፤ ነገር ግን በሰይፍና በእሳት ነበልባል በምርኮና በመበዝበዝ ብዙ ዘመን ይወድቃሉ።” (ዳንኤል 11:32, 33) በሰሜኑ ንጉሥ ሥር የሚኖሩ ክርስቲያኖች በተገቢ መንገድ ‘በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ቢገዙም’ የዓለም ክፍል ግን አልሆኑም። (ሮሜ 13:1፤ ዮሐንስ 18:36) የቄሣርን ለቄሣር ለመክፈል ጠንቃቆች ቢሆኑም “የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር” ደግሞ ያስረክባሉ። (ማቴዎስ 22:21) በዚህም ምክንያት ንጹሕ አቋማቸው ፈተና ደርሶበት ነበር። — 2 ጢሞቴዎስ 3:12
17 ውጤቱስ ምን ሆነ? ‘አሸነፉም’ ‘ወደቁም።’ ወደቁ ሲባል ተሰደዱ፣ ከባድ መከራ ደረሰባቸው ማለት ነው። አንዳንዶቹም ተገድለዋል። ያሸነፉት ደግሞ በአብዛኛው የታመኑ ሆነው በመጽናታቸው ነው። አዎን፣ ኢየሱስ ዓለምን እንዳሸነፈ እነርሱም ዓለምን አሸንፈዋል። (ዮሐንስ 16:33) በተጨማሪም እስር ቤት ወይም ማጎሪያ ካምፖች ቢገቡም እንኳ መስበካቸውን አላቆሙም ነበር። ይህን በማድረጋቸውም ‘ለብዙዎች ማስተዋልን ሰጥተዋል።’ የሰሜኑ ንጉሥ በሚገዛባቸው አብዛኞቹ አገሮች ውስጥ ስደት ቢኖርም የይሖዋ ምስክሮች ቁጥር ጨምሯል። ‘ጥበበኞቹ’ የታመኑ ሆነው በመሥራታቸው በእነዚህ አገሮች በቁጥር ሁልጊዜ እያደጉ የሄዱ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ተገኝተዋል። — ራእይ 7:9–14
18. በሰሜኑ ንጉሥ ግዛት ሥር የሚኖሩት ቅቡዓን ቀሪዎች ምን “ጥቂት እርዳታ” ተቀብለዋል?
18 በአምላክ ሕዝቦች ላይ ስለሚደርሰው ስደት ሲናገር መልአኩ “በወደቁም ጊዜ በጥቂት እርዳታ ይረዳሉ” በማለት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ዳንኤል 11:34) ይህስ የተፈጸመው እንዴት ነበር? በአንድ በኩል የደቡቡ ንጉሥ በማሸነፉ ምክንያት በተቀናቃኙ ንጉሥ ግዛት ሥር ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች ትልቅ እፎይታን በማምጣቱ ነው። (ከራእይ 12:15, 16 ጋር አወዳድር።) ከዚያም በተተኪው የሰሜን ንጉሥ ስደት ሲደርስባቸው የነበሩት ክርስቲያኖች ቀዝቃዛው ጦርነት እያከተመ ሲመጣ ብዙ የፖለቲካ መሪዎች ታማኝ ክርስቲያኖች አደገኞች አለመሆናቸውን እየተገነዘቡ በመምጣታቸው ሕጋዊ እውቅና ስለሰጧቸው እፎይታን አግኝተዋል።c በማቴዎስ 25:34–40 ላይ እንደተገለጸው ቅቡዓኑ ለሚያቀርቡት የታመነ ስብከት አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡት የእጅግ ብዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በማደጉና ቅቡዓኑን በመርዳታቸው ታላቅ እርዳታ በዚህም በኩል ተገኝቷል።
የአምላክን ሕዝቦች ማንጻት
19. (ሀ) አንዳንዶች “ወደ እነርሱ በግብዝነት ተባብረው” የተሰበሰቡት እንዴት ነው? (ለ) “እስከ ፍጻሜ ዘመን” የሚለው አባባል ምን ማለት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
19 በዚህ ዘመን አምላክን ለማገልገል ፍላጎት እንዳላቸው ያሳዩ ሁሉ ጥሩ የልብ ዓላማ አልነበራቸውም። መልአኩ “ብዙ ሰዎችም በግብዝነት ወደ እነርሱ ተባብረው ይሰበሰባሉ። እስከ ተወሰነውም ዘመን ይሆናልና ከጥበበኞቹ አያሌዎቹ እስከ ፍጻሜ ዘመን ይነጥሩና ይጠሩ ይነጡም ዘንድ ይወድቃሉ” በማለት አስጠንቅቋል።d (ዳንኤል 11:34, 35) አንዳንዶች ለእውነት ፍላጎት አሳይተዋል ነገር ግን አምላክን ለማገልገል ከልብ ራሳቸውን ለመወሰን ፈቃደኞች አልነበሩም። ሌሎቹ ምሥራቹን የተቀበሉ ይመስሉ የነበሩ ሰዎች የባለ ሥልጣኖቹ ሰላዮች ነበሩ። ከአንድ አገር የተላከው ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “ወደ ጌታ ድርጅት ሰርገው የገቡትና ከፍተኛ ቅንዓት ያሳዩት እነዚህ አጭበርባሪ ተዋንያን በይሖዋ ድርጅት ውስጥ በጣም ከፍተኛ በሆኑ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የተሾሙ ሙሉ በሙሉ ለኮሙኒስት አገዛዝ ያደሩ ሰዎች ነበሩ።”
20. ሰርገው በገቡ ግብዞች ምክንያት አንዳንድ ታማኝ ክርስቲያኖች ‘እንዲወድቁ’ ይሖዋ የፈቀደው ለምንድን ነው?
20 ሰርጎ ገቦቹ አንዳንዶቹን ታማኞች በባለ ሥልጣኖች እንዲያዙ አድርገዋቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ነገር እንዲደርስ ይሖዋ ለምን ፈቀደ? ለማንጠርና ለማጥራት ብሎ ነው። ልክ ኢየሱስ ‘ከተቀበለው መከራ መታዘዝን እንደ ተማረ’ እነዚህም ታማኝ ነፍሳት ከእምነታቸው መፈተን መጽናትን ሊማሩ ችለዋል። (ዕብራውያን 5:8፤ ያዕቆብ 1:2, 3፤ ከሚልክያስ 3:3 ጋር አወዳድር።) በዚህ መንገድ ‘የነጠሩ፣ የጠሩና የነጹ’ ሆነዋል። መጽናታቸው የሚያስገኝላቸውን ሽልማት የሚቀበሉበት የተወሰነው ዘመን ሲደርስ እንደነዚህ ያሉ ታማኞች ታላቅ ደስታ ይጠብቃቸዋል። ይህም በዳንኤል ትንቢት ላይ ተጨማሪ ውይይት ስናደርግ የሚታይ ነገር ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በ1958 “መለኮታዊ ፈቃድ” በተባለው የይሖዋ ምስክሮች ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ በእንግሊዝኛ ታትሞ የወጣ መጽሐፍ።
b በኅዳር 1992 የወጣው ወርልድ ፕረስ ሪቪው በአንድ ርዕስ ሥር የወጣን አንድ ሐተታ ዘ ቶሮንቶ ስታር ከሚባል መጽሔት ጠቅሶ አውጥቶ ነበር። እንዲህም አለ:- “ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ሩስያውያን የአገራቸውን ታሪክ በተመለከተ በዓይናቸው ፊት ተንኮታኩተው የተፈረካከሱ በደርዘን የሚቆጠሩ የማይበገሩ ቅዠቶች ነበሯቸው። ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያን ከኮሙኒስቱ አገዛዝ ጋር የነበራት ቁርኝት ሲጋለጥ ከሁሉም በላይ የከፋውን ውርደት ተቀብላለች።”
c የሐምሌ 15, 1991 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 8–11 ተመ ልከት።
d “እስከ ፍጻሜ ዘመን” የሚለው አባባል “በፍጻሜው ዘመን ውስጥ” ማለትም ሊሆን ይችላል። “እስከ” ተብሎ እዚህ ላይ የተተረጎመው ቃል በአረማይክ ጽሑፍ በዳንኤል 7:25 ላይ ይገኛል። እዚያም ላይ “ውስጥ” እና “ለ” የሚል ትርጉም አለው። ይኸው ቃል በ2 ነገሥት 9:22፤ በኢዮብ 20:5 እና በመሳፍንት 3:26 ላይ በዕብራይስጡ ጽሑፍ ተመሳሳይ ትርጉም አለው። ሆኖም በብዙ ትርጉሞች በዳንኤል 11:35 ላይ “እስከ” ተብሎ ተተርጉሟል። ትክክለኛው አረዳድ ይኸኛው ከሆነ “የፍጻሜው ዘመን” የሚለው የአምላክ ሕዝቦችን ጽናት ፍጻሜ የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል። — “ፈቃድህ በምድር ይሁን ” ከተባለው መጽሐፍ ገጽ 286 ጋር አወዳድር።
ታስታውሳለህን?
◻ በዛሬው ጊዜ የዳንኤል ትንቢት በግልጽ ይገባናል ብለን ልጠብቅ የሚገባን ለምንድን ነው?
◻ የሰሜኑ ንጉሥ ‘የተቆጣውና የፈቀደውን ያደረገው’ እንዴት ነው?
◻ ‘ርኩሰቱ’ እንደገና ብቅ እንደሚል በባሪያው ክፍል አስቀድሞ የታየው እንዴት ነበር?
◻ ቅቡዓን ቀሪዎች ‘የወደቁት፣ ያሸነፉትና ጥቂት እርዳታ የተቀበሉት’ እንዴት ነበር?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሰሜኑ ንጉሥ በ1918 ከደቡቡ ንጉሥ ከደረሰበት ጉዳት በሂትለር ዘመን ሙሉ በሙሉ አገገመ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ከሰሜኑ ንጉሥ ጋር ዝምድና ለማጠናከር ጥረት አድርገዋል
[ምንጭ]
Zoran/Sipa Press