“በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ”
“ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤ እኔም ልቀሰቅሰው ወደዚያ እሄዳለሁ።”—ዮሐ. 11:11
1. ማርታ ወንድሟን በተመለከተ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበረች? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅና ተከታይ የሆነችው ማርታ በሐዘን ተውጣለች። ወንድሟ አልዓዛር በሞት አንቀላፍቷል። በሐዘን የተሰበረ ልቧን ሊጠግንላት የሚችል ነገር ይኖር ይሆን? ኢየሱስ “ወንድምሽ ይነሳል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷታል። እርግጥ ይህ ተስፋ ሐዘኗን ሙሉ በሙሉ አያስወግድላትም፤ ያም ሆኖ ማርታ፣ ኢየሱስ በሰጣት ማረጋገጫ ላይ እምነት ነበራት። “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ” ማለቷ ይህን ያሳያል። (ዮሐ. 11:20-24) ወደፊት ትንሣኤ እንደሚኖር እርግጠኛ ነበረች። ኢየሱስ ግን በዚያው ቀን አንድ ተአምር ፈጸመ። ዓይናቸው እያየ አልዓዛርን ከሞት አስነሳው።
2. እንደ ማርታ ዓይነት የመተማመን ስሜት ማዳበርህ ምን ጥቅም አለው?
2 ኢየሱስም ሆነ አባቱ በዛሬው ጊዜ እንዲህ ያለ ተአምር ይፈጽሙልናል ብለን እንድንጠብቅ የሚያደርግ መሠረት የለንም። ይሁን እንጂ በሞት ያጣሃቸው ሰዎች ወደፊት ትንሣኤ እንደሚኖራቸው አንተም የማርታን ያህል እርግጠኛ ነህ? ምናልባትም የትዳር ጓደኛህን፣ እናትህን፣ አባትህን አሊያም አያትህን በሞት አጥተህ ይሆናል። ወይም ደግሞ ሞት ልጅህን ነጥቆህ ሊሆን ይችላል። የሞተብህን ሰው እቅፍ ለማድረግ እንዲሁም ከእሱ ጋር ለመጫወትና ለመሳቅ ትናፍቅ ይሆናል። ደስ የሚለው ነገር፣ ‘በሞት ያጣሁት ሰው በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ’ በማለት አንተም እንደ ማርታ አፍህን ሞልተህ መናገር ትችላለህ። ያም ቢሆን እያንዳንዱ ክርስቲያን እንዲህ ብሎ በልበ ሙሉነት መናገር የሚችለው ለምን እንደሆነ ቆም ብሎ ማሰቡ ጠቃሚ ነው።
3, 4. ማርታ፣ ኢየሱስ ከሞት ያስነሳቸው ሰዎች እንዳሉ ማወቋ እምነቷን አጠናክሮላት የሚሆነው እንዴት ነው?
3 ማርታ የምትኖረው በኢየሩሳሌም አካባቢ ስለነበር ኢየሱስ በገሊላ በምትገኘው በናይን አቅራቢያ የአንዲትን መበለት ልጅ ሲያስነሳ የመመልከት አጋጣሚዋ ጠባብ ነው። ሆኖም ስለተከናወነው ነገር ሰምታ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ የኢያኢሮስን ሴት ልጅ ከሞት እንዳስነሳም ማርታ ሳትሰማ አትቀርም። በኢያኢሮስ ቤት ውስጥ የነበሩት ሁሉ “ልጅቷ እንደሞተች ያውቁ” ነበር። ሆኖም ኢየሱስ እጇን በመያዝ “አንቺ ልጅ፣ ተነሽ!” አላት፤ እሷም ወዲያውኑ ተነሳች። (ሉቃስ 7:11-17፤ 8:41, 42, 49-55) ኢየሱስ የታመሙትን መፈወስ እንደሚችል ማርታም ሆነች እህቷ ማርያም ያውቁ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በቦታው ቢኖር ኖሮ አልዓዛር እንደማይሞት ተሰምቷቸዋል። አሁን ግን የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ ሞቷል፤ ታዲያ ተስፋው ምንድን ነው? ማርታ፣ ወደፊት ማለትም “በመጨረሻው ቀን” አልዓዛር ሕያው እንደሚሆን መናገሯን ልብ እንበል። ይህን ያህል እርግጠኛ የሆነችው ለምንድን ነው? አንተስ በሞት ያጣሃቸውን ሰዎች ጨምሮ ሌሎችም ወደፊት ትንሣኤ ሊያገኙ እንደሚችሉ መተማመን የምትችለው ለምንድን ነው?
4 ትንሣኤ እንደሚኖር ለመተማመን የሚያበቁህ አጥጋቢ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ ምክንያቶች አንዳንዶቹን ቀጥለን እንመረምራለን፤ ይህን ስናደርግ፣ ስለ ትንሣኤ ካለህ ተስፋ ጋር ተያያዥነት እንዳላቸው ብዙውን ጊዜ የማታስባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ታገኝ ይሆናል።
ተስፋ እንዲኖረን ያደረጉ ክንውኖች!
5. ማርታ ወንድሟ ከሞት እንደሚነሳ እንድትተማመን ያደረጋት ምንድን ነው?
5 ማርታ ‘ወንድሜ በትንሣኤ እንደሚነሳ ተስፋ አደርጋለሁ’ አላለችም። ከዚህ ይልቅ “በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ” እንዳለች ልብ እንበል። ማርታ በትንሣኤ እንድትተማመን ያደረጋት ኢየሱስ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት ስለተፈጸሙ ተአምራት የነበራት እውቀት ሊሆን ይችላል። ከልጅነቷ ጀምሮ ስለ እነዚህ ተአምራት በቤት ውስጥ እንዲሁም በምኩራብ ተምራለች። በመንፈስ መሪነት በተጻፉት ዘገባዎች ውስጥ የሰፈሩትን ስለ ትንሣኤ የሚያወሱ ሦስት ታሪኮች እስቲ እንመልከት።
6. ማርታ፣ ኤልያስ ስለፈጸመው ስለ የትኛው ተአምር ሰምታ መሆን አለበት?
6 የመጀመሪያው ትንሣኤ የተከናወነው፣ ነቢዩ ኤልያስ ከአምላክ ባገኘው ኃይል ተአምራት ይፈጽም በነበረበት ወቅት ነው። ኤልያስን፣ የፊንቄ የወደብ ከተማ በሆነችው በሰራፕታ የምትኖር አንዲት ደሃ መበለት አስተናገደችው። አምላክም ለዚህ ቤተሰብ አንድ ተአምር ፈጸመ፤ ይህች ሴትና ልጇ የነበራቸው ዱቄትና ዘይት እንዳያልቅ በማድረግ በረሃብ እንዳይሞቱ ታደጋቸው። (1 ነገ. 17:8-16) ከጊዜ በኋላ ግን የሴትየዋ ልጅ ታምሞ ሞተ። በዚህ ጊዜ ኤልያስ ይህችን ሴት ረዳት። ነቢዩ “አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ የዚህ ልጅ ሕይወት ይመለስለት” በማለት ጸለየ። የጠየቀውም ተፈጸመለት! አምላክ የኤልያስን ጸሎት በመስማት ልጁ ከሞት እንዲነሳ አደረገ። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የምናገኘው የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው። (1 ነገሥት 17:17-24ን አንብብ።) ማርታ ስለዚህ አስደናቂ ክንውን እንደምታውቅ ጥርጥር የለውም።
7, 8. (ሀ) ኤልሳዕ የአንዲትን ሴት ሐዘን ያስወገደላት እንዴት ነው? (ለ) ኤልሳዕ የፈጸመው ተአምር ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?
7 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የምናገኘውን ሁለተኛውን ትንሣኤ ያከናወነው ደግሞ የኤልያስ ተተኪ የሆነው ነቢዩ ኤልሳዕ ነው። በሹነም የምትኖር አንዲት ታዋቂ እስራኤላዊት ለኤልሳዕ ታላቅ ደግነት አሳየችው። አምላክ በነቢዩ አማካኝነት በገባው ቃል መሠረት፣ ልጅ የሌላትን ይህችን ሴትና በዕድሜ የገፋውን ባለቤቷን ስለባረካቸው ልጅ መውለድ ቻሉ። የሚያሳዝነው ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ልጃቸው ሞተ። እናትየው ምን ያህል በሐዘን እንደምትደቆስ መገመት አያዳግትም። ሴትየዋ፣ ወደ ኤልሳዕ እንደምትሄድ ለባሏ ከነገረችው በኋላ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ የነበረውን ይህን ነቢይ ለማግኘት 30 ኪሎ ሜትር ያህል ተጓዘች። ነቢዩም አገልጋዩን ግያዝን ወደ ሹነም ቀድሟቸው እንዲሄድ ላከው። ሆኖም ግያዝ የሞተውን ልጅ ሊያስነሳው አልቻለም። ብዙም ሳይቆይ፣ ልጇን ያጣችው እናትና ኤልሳዕ ሹነም ደረሱ።—2 ነገ. 4:8-31
8 በዚያም ኤልሳዕ የልጁ አስከሬን ወዳለበት ክፍል ገብቶ መጸለይ ጀመረ። የሞተውም ልጅ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ሕያው ሆነ! እናትየው ልጇን ስታገኝ በደስታ ፈነደቀች። (2 ነገሥት 4:32-37ን አንብብ።) ይህች እናት፣ ቀደም ሲል መሃን የነበረችው ሐና በማደሪያው ድንኳን ውስጥ እንዲያገለግል ሳሙኤልን ስታመጣው ያቀረበችውን ጸሎት አስታውሳ ሊሆን ይችላል፤ ሐና በጸሎቷ ላይ “ይሖዋ . . . ወደ መቃብር ያወርዳል፤ ከዚያም ያወጣል” ብላ ነበር። (1 ሳሙ. 2:6) አምላክ፣ በሹነም የነበረው ልጅ ዳግመኛ ሕያው እንዲሆን ማድረጉ ሙታንን የማስነሳት ኃይል እንዳለው የሚያረጋግጥ ነው።
9. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ሦስተኛው ትንሣኤ ከኤልሳዕ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?
9 ከኤልሳዕ ጋር በተያያዘ የተፈጸመው አስደናቂ ክንውን ግን ይህ ብቻ አይደለም። ኤልሳዕ ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት በነቢይነት ካገለገለ በኋላ “ለሞት በዳረገው በሽታ [ተያዘ]”፤ ውሎ አድሮም በሞት አንቀላፋ። ይህ ከሆነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወራሪ ቡድኖች ወደ እስራኤል መጡ፤ በዚህ ወቅት ኤልሳዕ ከሞተ ዓመታት ስላለፉ በመቃብሩ ውስጥ የቀረው አፅሙ ብቻ ነበር። አንድ ቀን፣ የተወሰኑ እስራኤላውያን የሞተ ሰው ሊቀብሩ ሲሄዱ ወራሪውን ቡድን ተመለከቱ። እነሱም፣ የሞተውን ሰው የኤልሳዕ አፅም ያለበት መቃብር ውስጥ ወርውረው ከጠላቶቻቸው ሸሹ። ጥቅሱ “ሰውየውም የኤልሳዕን አፅም በነካ ጊዜ ሕያው ሆነ፤ በእግሩም ቆመ” ይላል። (2 ነገ. 13:14, 20, 21) ስለ ትንሣኤ የሚገልጹት እነዚህ ዘገባዎች ለማርታ ምን ትርጉም እንደነበራቸው እስቲ አስበው! አምላክ ሙታንን የማስነሳት ኃይል እንዳለው አረጋግጠውላታል። እነዚህ ዘገባዎች ለአንተስ ምን ትርጉም አላቸው? የአምላክ ኃይል ታላቅና ገደብ የለሽ ስለመሆኑ ያለህን እምነት ሊያጠናክሩልህ ይገባል።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተፈጸሙ ክንውኖች
10. ጴጥሮስ፣ ጣቢታ ከተባለች አንዲት ክርስቲያን ጋር በተያያዘ ምን አድርጓል?
10 የአምላክ ወኪሎች ሙታንን እንዳስነሱ የሚገልጹ ዘገባዎችን በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥም እናገኛለን። ኢየሱስ፣ በናይን ከተማ አቅራቢያ እንዲሁም በኢያኢሮስ ቤት ያከናወናቸውን ትንሣኤዎች እንደ ምሳሌ መጥቀስ እንችላለን። ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ ዶርቃ (ጣቢታ) የተባለችን አንዲት ክርስቲያን ከሞት አስነስቷል። ጴጥሮስ በቦታው የደረሰው አስከሬኗ ለቀብር ተዘጋጅቶ በነበረበት ወቅት ነው። ሐዋርያው፣ አስከሬኑ አጠገብ ሆኖ ጸለየ። ከዚያም “ጣቢታ፣ ተነሽ!” ሲላት ወዲያውኑ ተነሳች፤ ጴጥሮስም የእምነት ባልንጀሮቹን ጠርቶ “ሕያው መሆኗን አሳያቸው።” ይህ ክንውን ‘ብዙዎች በጌታ እንዲያምኑ’ አስተዋጽኦ አድርጓል። እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ስለ ኢየሱስ ምሥራቹን መናገር እንዲሁም ይሖዋ ሙታንን የማስነሳት ኃይል እንዳለው ለሌሎች መመሥከር ችለዋል።—ሥራ 9:36-42
11. ሐኪሙ ሉቃስ ከአንድ ወጣት ጋር በተያያዘ ምን ዘገባ አስፍሯል? የተፈጸመው ነገር በቦታው በነበሩት ሰዎች ላይ ምን ስሜት አሳድሯል?
11 በብዙ የዓይን ምሥክሮች ፊት ስለተከናወነ ትንሣኤ የሚገልጽ ዘገባ ደግሞ እንመልከት። በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ በጥሮአስ (አሁን ያለችው በሰሜን ምዕራብ ቱርክ ነው) በሚገኝ አንድ ፎቅ ላይ ከወንድሞች ጋር ተሰብስቦ ነበር። ጳውሎስ ንግግሩን እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ አስረዘመ። አውጤኪስ የሚባል ወጣት መስኮት ላይ ተቀምጦ ንግግሩን እያዳመጠ ሳለ እንቅልፍ ስላሸነፈው ከሁለተኛ ፎቅ ላይ ወደቀ። አውጤኪስ ጋ ቀድሞ በመድረስ ሁኔታውን የተመለከተው ሐኪሙ ሉቃስ ሳይሆን አይቀርም፤ ሉቃስ፣ ወጣቱ ጉዳት እንደደረሰበት ወይም ራሱን እንደሳተ ሳይሆን እንደሞተ ገልጿል። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ከፎቅ ላይ ወርዶ የወጣቱን አስከሬን አቀፈው፤ ከዚያም ወጣቱ ‘በሕይወት እንዳለ’ ተናገረ። በቦታው የነበሩት ሰዎች ይህን ተአምር መመልከታቸው ምን ስሜት አሳድሮባቸው እንደሚሆን መገመት አያዳግትም! እነዚህ ሰዎች ወጣቱ እንደሞተ በገዛ ዓይናቸው ተመልክተዋል፤ በመሆኑም ጳውሎስ ከሞት ሲያስነሳው “እጅግ ተጽናኑ።”—ሥራ 20:7-12
አስተማማኝ ተስፋ
12, 13. ቀደም ሲል ከተመለከትናቸው ስለ ትንሣኤ የሚያወሱ ዘገባዎች አንጻር የትኞቹ ጥያቄዎች ይነሳሉ?
12 ቀደም ሲል የተመለከትናቸው ዘገባዎች እንደ ማርታ በትንሣኤ እንድንተማመን ሊያደርጉን ይገባል። በሌላ አባባል አምላካችንና ሕይወት ሰጪያችን የሆነው ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን የማስነሳት ኃይል እንዳለው ያረጋግጡልናል። እነዚያ ትንሣኤዎች በተከናወኑበት በእያንዳንዱ አጋጣሚ እንደ ኤልያስ፣ ኢየሱስ ወይም ጴጥሮስ ያሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በቦታው የነበሩ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነገር ነው። በተጨማሪም ትንሣኤዎቹ የተከናወኑት ይሖዋ ተአምራትን ይፈጽም በነበረበት ጊዜ ነው። ይሁንና እንዲህ ያሉ ተአምራት በማይፈጸሙባቸው ዘመናት ስለሞቱ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እንዲህ ባሉ ዘመናት የኖሩ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች፣ አምላክ ሙታንን ወደፊት ከሞት እንደሚያስነሳ መጠበቅ ይችላሉ? “[ወንድሜ] በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ” ብላ እንደተናገረችው እንደ ማርታ ዓይነት የመተማመን ስሜት ሊኖራቸው ይችላል? ማርታ እንዲህ ዓይነት እምነት ሊኖራት የቻለው ለምንድን ነው? አንተስ እንዲህ ብለህ ማመን የምትችለው ለምንድን ነው?
13 የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ወደፊት ትንሣኤ እንደሚኖር ያውቁ እንደነበር የሚጠቁሙ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።
14. ስለ ትንሣኤ ከአብርሃም ምን እንማራለን?
14 አብርሃም ለረጅም ጊዜ ጠብቆ ያገኘውን ወራሹን ይስሐቅን በተመለከተ ምን ዓይነት ትእዛዝ እንደተሰጠው እስቲ እንመልከት። ይሖዋ፣ አብርሃምን “እባክህ ልጅህን፣ በጣም የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን . . . የሚቃጠል መባ አድርገህ አቅርበው” ብሎት ነበር። (ዘፍ. 22:2) እንዲህ ያለ ትእዛዝ ምን ዓይነት ስሜት ሊያሳድር እንደሚችል እስቲ አስበው። ይሖዋ በአብርሃም ዘር አማካኝነት የምድር ብሔራት ሁሉ እንደሚባረኩ ቃል ገብቷል። (ዘፍ. 13:14-16፤ 18:18፤ ሮም 4:17, 18) ከዚህም በላይ ይሖዋ፣ ይህ ዘር የሚመጣው “በይስሐቅ በኩል” እንደሚሆን ገልጿል። (ዘፍ. 21:12) ይሁን እንጂ አብርሃም ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበው ይህ ተስፋ እንዴት ሊፈጸም ነው? አምላክ ይስሐቅን ከሞት ሊያስነሳው እንደሚችል አብርሃም እምነት እንደነበረው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት አብራርቷል። (ዕብራውያን 11:17-19ን አንብብ።) አብርሃም እንደታዘዘው ልጁን መሥዋዕት ቢያደርገው ይስሐቅን በትንሣኤ የሚያገኘው ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ይሁን ከአንድ ቀን አሊያም ከሳምንት በኋላ፣ ማወቅ የሚችልበት መንገድ አልነበረም። ይህ የአምላክ አገልጋይ፣ ልጁ መቼ እንደሚነሳ ያውቅ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ አይገልጽም። ሆኖም ይሖዋ ይስሐቅን እንደሚያስነሳው አብርሃም ይተማመን ነበር።
15. ኢዮብ ምን ተስፋ እንዳለው ተናግሯል?
15 በተመሳሳይም በጥንት ዘመን የኖረው ኢዮብ ወደፊት ትንሣኤ እንደሚከናወን እምነት ነበረው። ኢዮብ፣ አንድ ዛፍ ቢቆረጥ መልሶ እንደሚያቆጠቁጥና እንደ አዲስ ተክል እንደሚሆን ተናግሯል። የሰው ልጆች ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። (ኢዮብ 14:7-12፤ 19:25-27) አንድ ሰው ከሞተ፣ ራሱን ከመቃብር ማውጣትና ዳግመኛ ሕያው መሆን አይችልም። (2 ሳሙ. 12:23፤ መዝ. 89:48) ይህ ሲባል ግን አምላክም የሞተን ሰው ማስነሳት ያቅተዋል ማለት አይደለም። እንዲያውም ኢዮብ፣ ይሖዋ እሱን የሚያስነሳበት ጊዜ እንዳለ እምነት ነበረው። (ኢዮብ 14:13-15ን አንብብ።) ኢዮብ፣ ይህ ጊዜ መቼ እንደሆነ ማወቅ አይችልም። ያም ቢሆን ለሰው ልጆች ሕይወትን የሰጠው አምላክ፣ እሱን አስታውሶ ከሞት ለማስነሳት ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ እንዳለው ይተማመን ነበር።
16. አንድ መልአክ ለነቢዩ ዳንኤል ምን ማበረታቻ ሰጥቶታል?
16 በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሰውን ታማኙን ዳንኤልንም መውሰድ እንችላለን። ዳንኤል ለብዙ አሥርተ ዓመታት አምላክን በታማኝነት ያገለገለ ሲሆን የይሖዋ ድጋፍም አልተለየውም። በአንድ ወቅት አንድ መልአክ ዳንኤልን “እጅግ የተወደድክ” ብሎ ከጠራው በኋላ “ሰላም ለአንተ ይሁን። በርታ” ብሎታል።—ዳን. 9:22, 23፤ 10:11, 18, 19
17, 18. ዳንኤል የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ምን ተስፋ ተሰጥቶታል?
17 በወቅቱ 100 ዓመት ገደማ የሆነው ዳንኤል ወደ ሕይወቱ መገባደጃ እየተቃረበ ነበር። ምናልባትም ወደፊት ምን እንደሚጠብቀው ሳያስብ አልቀረም። ዳንኤል ትንሣኤ አግኝቶ እንደገና በሕይወት ይኖር ይሆን? እንዴታ! በዳንኤል መጽሐፍ መጨረሻ ላይ አምላክ “አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ። ታርፋለህ” የሚል ማረጋገጫ ለነቢዩ እንደሰጠው ተገልጿል። (ዳን. 12:13) በዕድሜ የገፋው ዳንኤል ሙታን እንደሚያርፉ እንዲሁም “በመቃብር . . . ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ” እንደሌለ ያውቅ ነበር። ዳንኤልም ወደ መቃብር መሄዱ አይቀርም። (መክ. 9:10) ሆኖም መጨረሻው እዚያው መቅረት አይደለም። ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስደሳች ተስፋ ሰጥቶታል።
18 ለነቢዩ ዳንኤል የተነገረው መልእክት ሲቀጥል “በዘመኑ ፍጻሜ ዕጣ ፋንታህን ለመቀበል ትነሳለህ” ይላል። ይህ መቼ እንደሚሆን ዳንኤል የሚያውቀው ነገር አልነበረም። አንድ ቀን በሞት ማንቀላፋቱ እንደማይቀር ያውቃል። ይሁን እንጂ ዳንኤል ወደፊት ‘ዕጣ ፋንታውን ለመቀበል እንደሚነሳ’ የተነገረው መሆኑ፣ እሱ ከሞተ ከረጅም ጊዜ በኋላ ትንሣኤ እንደሚኖር በግልጽ ቃል የተገባ ያህል ነው። ይህ የሚሆነው “በዘመኑ ፍጻሜ” ነው።
19, 20. (ሀ) እስከ አሁን የተመለከትናቸው ነጥቦች ማርታ ለኢየሱስ ከተናገረችው ነገር ጋር የሚያያዙት እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
19 ማርታ፣ ታማኝ የሆነው ወንድሟ አልዓዛር “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ” ለመተማመን የሚያበቃ አጥጋቢ ምክንያት እንደነበራት በግልጽ ማየት ይቻላል። ለዳንኤል የተገባለት ቃል እንዲሁም ማርታ ለኢየሱስ የሰጠችው እርግጠኝነት የተሞላበት ምላሽ፣ በዛሬው ጊዜ የምንገኘው ክርስቲያኖችም ትንሣኤ እንደሚኖር እንድንተማመን ያደርጉናል።
20 ቀደም ባሉት ዘመናት የተፈጸሙ ክንውኖች፣ ሙታን እንደገና ሕያው መሆን ይኸውም ትንሣኤ ማግኘት እንደሚችሉ አረጋግጠውልናል። የአምላክ አገልጋዮች የነበሩ ወንዶችና ሴቶችም ወደፊት ትንሣኤ እንደሚኖር ይጠብቁ ነበር። ይሁንና የሞተ ሰው ትንሣኤ እንደሚያገኝ ቃል ከተገባ ከብዙ ዓመታት በኋላ እንኳ ይህ ተስፋ ሊፈጸም እንደሚችል የሚያሳይ ማስረጃ ይኖር ይሆን? ይህን የሚያሳይ ማስረጃ ካለ ትንሣኤ የሚከናወንበትን ጊዜ በጉጉት እንድንጠባበቅ የሚያደርግ ተጨማሪ ምክንያት እናገኛለን። በሌላ በኩል ደግሞ ትንሣኤ የሚከናወነው መቼ ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እነዚህን ነጥቦች እንመረምራለን።