ይሖዋ ጽድቅንና ፍትሕን ይወድዳል
በሳራዬቮ ውስጥ የምትኖር አንዲት ወጣት በምትኖርበት ከተማ የሚገኙ ሕፃናት ለምን ብዙ መከራ እንደሚደርስባቸው ዘወትር ራስዋን ትጠይቃለች። “ይህ ሁሉ መከራ እንዲደርስብን የሚያደርግ ምንም መጥፎ ነገር አልሠራንም። ንጹሖች ነን” በማለት ትናገራለች። ወንዶች ልጆቻቸው የደረሱበት ሳይታወቅ በመቅረቱ ምክንያት የተጨነቁ አርጀንቲናውያን እናቶች በወቅቱ የነበረውን መንግሥት በመቃወም በአንድ አደባባይ ለ15 ዓመታት ያህል ትዕይንተ ሕዝብ ሲያደርጉ ቆይተዋል። የጎሣ ብጥብጥ በፈነዳበት ወቅት እናቱና ሦስት እህቶቹ በጭካኔ የተገደሉበት ኢማኑየል የተባለ አንድ አፍሪካዊ “እያንዳንዱ ሰው የሚገባውን ቅጣት መቀበል ይኖርበታል። ፍትሕ እንፈልጋለን” ሲል በምሬት ተናግሯል።
ከይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት አንዱ ፍትሕ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “መንገዱ ሁሉ ፍትሕ ነው” ይላል። በእርግጥም ይሖዋ “ጽድቅንና ፍርድን [“ፍትሕን፣” አዓት] ይወድዳል።” (ዘዳግም 32:4 አዓት፤ መዝሙር 33:5) አምላክን በሚገባ ለማወቅ ከፈለግን ለፍትሕ ያለውን ስሜት መረዳትና እሱን መምሰልን መማር ይኖርብናል።—ሆሴዕ 2:19, 20፤ ኤፌሶን 5:1
ሰዎች ለዚህ ባሕርይ የሚሰጡት ትርጉም ለፍትሕ ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ አገሮች ሰዎች ብዙውን ጊዜ ፍትሕን ዓይኖቿ በጨርቅ በታሰሩ፣ ሰይፍና ሁለት ሚዛኖች በያዘች ሴት ይመስሉታል። ይህም ሰብዓዊው ፍትሕ አድልዎ የሌለበት ማለትም ሀብት ወይም ሥልጣን ተጽዕኖ የማያደርግበት እንደሆነ ተደርጎ ስለሚታሰብ ነው። ፍትሕ ክስ የቀረበበት ግለሰብ ጥፋተኛ መሆኑን ወይም አለመሆኑን በጥንቃቄ መርምሮ ፍርድ መስጠትን ይጠይቃል። ፍትሕ በሰይፉ ተጠቅሞ ንጹሑን ሰው መጠበቅና ወንጀለኞችን መቅጣት አለበት።
ራይት ኤንድ ሪዝን—ኢቲክስ ኢን ቲዮሪ ኤንድ ፕራክቲስ የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ “ፍትሕ ከሕግ፣ ከመብትና ግዴታ ጋር የተያያዘ ሲሆን አድልዎ የሌለበት ወይም ተገቢ የሆነ ፍርድ እንዲሰጥ ይጠይቃል” ይላል። ሆኖም የይሖዋ ፍትሕ ይህ ፍቺ ከሚያስተላልፈው ሐሳብ በጣም የላቀ ነው። ከሰማዩ አባቱ ጋር በጣም የሚመሳሰለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ተግባራትና ባሕርያት ስንመረምር ይህን ለመረዳት እንችላለን።—ዕብራውያን 1:3
የወንጌል ጸሐፊው ማቴዎስ በኢሳይያስ 42:3 ላይ የሚገኙት ቃላት በኢየሱስ ላይ እንደሚሠሩ ሲገልጽ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፣ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ [“የኩራዝ፣” አዓት] ክርም አያጠፉም።” ኢየሱስ እንደ ተቀጠቀጠ ሸምበቆ ለሆኑት መከራና ጭቆና የደረሰባቸው ሰዎች የሚያጽናና መልእክት አውጅዋል። የመኖር ተስፋቸው ጭል ጭል ወደማለት ደረጃ ደርሶ ስለ ነበር እነዚህ ሰዎች እንደሚጤስ የኩራዝ ክር ሆነው ነበር። ኢየሱስ በምሳሌያዊ አነጋገር የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ ከመስበርና ይጤስ የነበረውን የኩራዝ ክር ከማጥፋት ይልቅ ለተዋረዱና እንግልት ለደረሰባቸው ሰዎች በመራራት እነሱን ከማስተማሩና ከመፈወሱም በላይ የይሖዋ አምላክን ፍትሕ አብራርቶላቸዋል። (ማቴዎስ 12:10-21) ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው እንዲህ ዓይነቱ ፍትሕ ብሩሕ ተስፋ የሚፈነጥቅ ነው።
ምሕረትና የይሖዋ ፍትሕ
ምሕረት የአምላክ ፍትሕ መሠረታዊ ክፍል ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ይህ ጠባይ በጉልህ ሁኔታ ታይቶበታል። ኢየሱስ የአምላክን የፍትሕና የጽድቅ ደረጃዎች ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። ሆኖም አይሁዳውያን ጸሐፊዎችና ፈሪሳውያን በአብዛኛው ራሳቸው ያወጧቸውን የማያፈናፍኑ ሕግጋት በመከተል ጽድቅ ለማግኘት ይፈልጉ ነበር። ድርቅ ባሉ ሕግጋት ላይ ተመሥርተው የሚሰጡት ፍርድ ብዙውን ጊዜ ምሕረትን ከግምት ውስጥ የሚያስገባ አልነበረም። በኢየሱስና በፈሪሳውያን መካከል የተፈጠሩት ብዙዎቹ ግጭቶች እውነተኛ ፍትሕና ጽድቅ ምንድን ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ ያተኮሩ ነበሩ።—ማቴዎስ 9:10-13፤ ማርቆስ 3:1-5፤ ሉቃስ 7:36-47
ኢየሱስ ሌሎች ሰዎችን በፍትሕና በጽድቅ መያዝ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረድቷል። በአንድ ወቅት አንድ በሕጉ የተካነ ሰው የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን እንደሚያስፈልግ ኢየሱስን ጠይቆት ነበር። ኢየሱስ ለዚህ መልስ ሲሰጥ አንድ ጥያቄ አቀረበለትና ሰውዬው ከሁሉ የበለጡት ሁለት ሕግጋት አምላክን በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ነፍስ፣ በፍጹም አሳብና በፍጹም ኃይል መውደድና ባልንጀራን እንደ ራስ አድርጎ መውደድ ናቸው ብሎ ሲመልስለት አመሰገነው። ከዚያ በኋላ ሰውዬው “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” በማለት ጥያቄ አቀረበ። ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚገልጸውን ምሳሌ በመናገር መልስ ሰጠ።—ሉቃስ 10:25-37
ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ በተናገረው ምሳሌ ላይ የይሖዋ ጽድቅና ምሕረታዊ ፍትሕ ተገልጿል። ሳምራዊው ሰው ተጎድቶ የነበረውን የማያውቀውን ሰው በለጋስነት በመርዳቱ ትክክለኛ፣ አድልዎ የሌለበትና ምሕረት የተሞላበት ተግባር ፈጽሟል። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ተመሳሳይ ዝንባሌ አሳይቷል። ጻድቅና የማያዳላ ሰው ነበር። ከዚህም በላይ ለመከራ፣ ለሕመምና ለሞት ለተዳረጉት ችግረኛ፣ ኃጢአተኛና ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ ጽድቅን ከቤዛው ዝግጅት ጋር አያይዞታል። “በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኲነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደ መጣ፣ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ [ወይም “በአንድ የጽድቅ ተግባር፣” የአዓት የግርጌ ማስታወሻ] ምክንያት ስጦታው ሕይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ” በማለት ጽፏል። (ሮሜ 5:18) ይህ ‘አንድ የጽድቅ ተግባር’ አምላክ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን በቀጥታ ተጠያቂ ከማይሆኑበት የአዳም ኃጢአት አስከፊ ውጤቶች የሚያድንበት መንገድ ነው።
የአምላክ ፍትሕ ኃጢአተኛ የሰው ልጆች እንዲቤዡና የዚያኑ ያህል ደግሞ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲከበሩ ይጠይቃል። ኃጢአትን በቸልታ ማለፍ ዓመፅን ማበረታታት ስለሚሆን እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ ትክክል ያልሆነና ፍቅር የሌለበት ተግባር ይፈጽም ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የአምላክ ፍትሕ ሽልማት ወይም ቅጣት ብቻ በመስጠት የተወሰነ ቢሆን ኖሮ የሰው ልጅ ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ይሆን ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው” በመሆኑም ‘አንድ እንኳ ጻድቅ ሰው የለም።’ (ሮሜ 3:10፤ 6:23) ይሖዋ ለኃጢአት ማስተሰርያ የሚሆን መሥዋዕት ሲያዘጋጅ በራሱም ሆነ በውድ ልጁ በኩል ከፍተኛ ዋጋ ጠይቆበታል።—1 ዮሐንስ 2:1, 2
መለኮታዊ ፍትሕ በመሠረታዊ ሥርዓት ከሚመራው ፍቅር (በግሪክኛ አጋፔ) ጋር በቅርብ የተቆራኘ መሆኑን ቤዛው በግልጽ አሳይቷል። የአምላክ ፍትሕ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹና የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃው ነጸብራቅ ነው። በመሆኑም አምላክ አጋፔ የተባለውን ፍቅር በሚያሳይበት ወቅት በመለኮታዊ ፍትሕ ላይ የተመሠረተ ፍቅር ያሳያል። (ማቴዎስ 5:43-48) ስለዚህ የአምላክን ፍትሕ ካስተዋልን በፍርድ ውሳኔዎቹ ሙሉ በሙሉ እንተማመናለን። “የምድር ሁሉ ፈራጅ” እንደመሆኑ መጠን ሁልጊዜ ትክክል የሆነውን ነገር ያደርጋል።—ዘፍጥረት 18:25፤ መዝሙር 119:75
በፍትሕ ረገድ ይሖዋን ምሰሉት
መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክን እንድንመስለው’ አጥብቆ ይመክረናል። (ኤፌሶን 5:1 የ1980 ትርጉም) ይህም ፍትሑንም ሆነ ፍቅሩን መምሰል ይኖርብናል ማለት ነው። ሆኖም ፍጹም ስላልሆንን መንገዳችን እንደ ይሖዋ አምላክ መንገድ ከፍ ያለ አይደለም። (ኢሳይያስ 55:8, 9፤ ሕዝቅኤል 18:25) ታዲያ ጽድቅንና ፍትሕን እንደምንወድ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ‘በእውነተኛ ጽድቅና ቅድስና እግዚአብሔርን ለመምሰል የተፈጠረውን አዲሱን ሰውነት በመልበስ’ ነው። (ኤፌሶን 4:24 የ1980 ትርጉም) እንዲህ ካደረግን አምላክ የሚወደውን እንወዳለን እንዲሁም እርሱ የሚጠላውን እንጠላለን። ዓመፅ፣ የሥነ ምግባር ጉድለት፣ ርኩሰትና ክህደት ቅዱስ ከሆነው ነገር ጋር ስለሚጻረሩ “እውነተኛ ጽድቅ” ከእነዚህ ነገሮች ይርቃል። (መዝሙር 11:5፤ ኤፌሶን 5:3-5፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:16, 17) በተጨማሪም አምላካዊ ፍትሕ ለሌሎች ሰዎች ልባዊ አሳቢነት እንድናሳይ ይገፋፋናል።—መዝሙር 37:21፤ ሮሜ 15:1-3
ከዚህም በላይ ምሕረት የአምላክ ፍትሕ መሠረታዊ ገጽታ እንደሆነ ከተገነዘብን በመንፈሳዊ ወንድሞቻችን ወይም እህቶቻችን ላይ አንፈርድም። ይሖዋ የእነሱን ሁኔታ የሚረዳውን ያህል እኛም መረዳት የምንችለው እንዴት ነው? በእነሱ ላይ የምንፈርደው በራሳችን አድልዎ ያለበት አመለካከት ተገፋፍተን አይደለምን? ኢየሱስ ስለዚህ ሁኔታ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል፦ “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፣ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። በወንድምህም ዓይን ያለውን ጕድፍ ስለ ምን ታያለህ፣ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? ወይም ወንድምህን፦ ከዓይንህ ጕድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም፣ በዓይንህ ምሰሶ አለ። አንተ ግብዝ፣ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፣ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጕድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።” (ማቴዎስ 7:1-5) የራሳችንን ጉድለቶች በሐቀኝነት መመርመራችን ይሖዋ እንደ ዓመፅ አድርጎ የሚመለከተውን ፍርድ ከመስጠት እንድንቆጠብ ያደርገናል።
ከባድ ኃጢአቶች በሚፈጸሙበት ወቅት የተሾሙ የጉባኤ ሽማግሌዎች ፍርድ የመስጠት ግዴታ አለባቸው። (1 ቆሮንቶስ 5:12, 13) ይህን በሚያደርጉበት ወቅት የአምላክ ፍትሕ በተቻለ መጠን ምሕረት ማድረግን እንደሚጠይቅ ያስታውሳሉ። ሆኖም ይህን ለማድረግ የሚያበቃ ምክንያት ከሌለ ማለትም ኃጢአት የሠራው ግለሰብ ንስሐ የማይገባ ከሆነ ምሕረት ሊደረግ አይችልም። ይሁን እንጂ ሽማግሌዎች እንደዚህ ያለውን ኃጢአተኛ ከጉባኤ የሚያስወግዱት ለመበቀል ብለው አይደለም። የውገዳ እርምጃው ጥፋቱን እንዲገነዘብ ይረዳዋል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። (ከሕዝቅኤል 18:23 ጋር አወዳድር።) ሽማግሌዎች በክርስቶስ አመራር ሥር ሆነው ፍትሕን ያራምዳሉ፤ ይህም “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ” መሆንን ይጨምራል። (ኢሳይያስ 32:1, 2) ስለዚህ አድልዎ የሌለበት ፍርድ መስጠትና ምክንያታዊ መሆን አለባቸው።—ዘዳግም 1:16, 17
ጽድቅን ዝሩ
ጽድቅ የሚሰፍንበትን የአምላክ አዲስ ዓለም እየተጠባበቅን መለኮታዊ ሞገስ ለማግኘት ‘ጽድቅን መፈለግ’ ይኖርብናል። (ሶፎንያስ 2:3፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) ይህ ሐሳብ በሆሴዕ 10:12 ላይ “እግዚአብሔር መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የምትሹበት ዘመን ነውና ለእናንተ ጽድቅን ዝሩ፣ እንደ ምሕረቱም መጠን እጨዱ፣ ጥጋታችሁንም እረሱ” በሚሉት ቃላት ውብ በሆነ ሁኔታ ተገልጿል።
ኢየሱስ በደጉ ሳምራዊ ምሳሌ ላይ እንደገለጸው በዘመናችን ‘ጽድቅን የምንዘራባቸው’ ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። ይሖዋ ‘እንደ ፍቅራዊ ደግነቱ መጠን እንድናጭድ’ ያደርጋል። ‘በፍትሕ ጎዳና’ መጓዛችንን ካላቋረጥን በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር ጽድቅን መማራችንን እንቀጥላለን። (ኢሳይያስ 40:14) ጊዜ እያለፈ በሄደ መጠን ይሖዋ ጽድቅንና ፍትሕን እንደሚወድ በይበልጥ እየተገነዘብን መሄዳችን አያጠራጥርም።—መዝሙር 33:4, 5
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ደጉ ሳምራዊ ለይሖዋ ፍትሕ ምሳሌ ይሆናል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ እንደ ተቀጠቀጠ ሸምበቆ ለሆኑት የተዋረዱና የተንገላቱ ሰዎች ያዝን ነበር