የጥናት ርዕስ 14
ከሰሜን የሚመጣ ጥቃት!
“ኃያል የሆነ . . . ብሔር ምድሬን ወሮታል።”—ኢዩ. 1:6
መዝሙር 95 ብርሃኑ እየደመቀ ነው
ማስተዋወቂያa
1. ወንድም ራስልና አጋሮቹ የትኛውን የጥናት ዘዴ ይጠቀሙ ነበር? ይህ ዘዴ ውጤታማ የነበረውስ ለምንድን ነው?
ከመቶ ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስል እና የአምላክ ቃል ተማሪ የሆኑ አጋሮቹ በቡድን መሰብሰብ ጀመሩ። እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ አምላክ፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታና ስለ ቤዛው ምን እንደሚያስተምር ማወቅ ፈልገው ነበር። የሚያጠኑበት ዘዴ ቀላል ነበር። በቅድሚያ ከመካከላቸው አንዱ ጥያቄ ይጠይቃል፤ ከዚያም ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥቅሶች በሙሉ ይመረምራሉ። በመጨረሻም የደረሱበትን መደምደሚያ በጽሑፍ ያሰፍራሉ። ቅን ልብ ያላቸው እነዚህ ክርስቲያን ወንዶች ያደረጉትን ጥረት ይሖዋ ስለባረከው እስከ ዛሬም ድረስ ትልቅ ቦታ የምንሰጣቸውን መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች መረዳት ችለዋል።
2. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ለመረዳት ስንሞክር አንዳንድ ጊዜ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ የሚያደርገን ምን ሊሆን ይችላል?
2 ብዙም ሳይቆይ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንደተገነዘቡት ግን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ያለውን ትርጉም በትክክል መረዳት አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርት ከመረዳት ይበልጥ ይከብዳል። ለምን? አንደኛ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ብዙውን ጊዜ ይበልጥ ግልጽ የሚሆኑልን እየተፈጸሙ ሳሉ ወይም ፍጻሜያቸውን ካገኙ በኋላ ነው። ሆኖም ሌላም ምክንያት አለ። በጥቅሉ ሲታይ፣ አንድን ትንቢት በትክክል ለመረዳት አውዱን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል። በትንቢቱ አንድ ገጽታ ላይ ብቻ ትኩረት ካደረግንና ሌሎቹን ችላ ካልናቸው የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ልንደርስ እንችላለን። በኢዩኤል መጽሐፍ ላይ ከተጠቀሰው ትንቢት ጋር በተያያዘም ያጋጠመው ይህ ሳይሆን አይቀርም። እስቲ ይህን ትንቢት በመመርመር አሁን ባለን ግንዛቤ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈለገው ለምን እንደሆነ እንመልከት።
3-4. በኢዩኤል 2:7-9 ላይ የሚገኘውን ትንቢት የምንረዳው እንዴት ነበር?
3 ኢዩኤል 2:7-9ን አንብብ። ኢዩኤል፣ የአንበጣ መንጋ የእስራኤልን ምድር እንደሚያወድም ትንቢት ተናግሯል። የአንበሳ ዓይነት ጥርስና መንገጭላ ያላቸው እነዚህ የማይጠግቡ ነፍሳት በምድሩ ላይ ያለውን ነገር ሁሉ በሉ! (ኢዩ. 1:4, 6) ላለፉት በርካታ ዓመታት፣ ይህ ትንቢት የሚያመለክተው የይሖዋ ሕዝብ ምንም የሚያስቆመው ነገር እንደሌለ የአንበጣ መንጋ የስብከቱን ሥራ የሚያከናውንበትን መንገድ እንደሆነ እናምን ነበር። የስብከቱ ሥራ ‘በምድሩ’ ማለትም በሃይማኖት መሪዎች ቁጥጥር ሥር ባለው ሕዝብ ላይ ውድመት እንደሚያስከትልም እናስብ ነበር።b
4 በኢዩኤል 2:7-9 ላይ በሚገኘው ትንቢት ላይ ብቻ ካተኮርን ይህ ማብራሪያ ትክክል ሊመስል ይችላል። ሆኖም ሙሉውን ትንቢት ስንመረምር በግንዛቤያችን ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልገን እንረዳለን። እንዲህ ለማለት የሚያበቁ አራት ምክንያቶችን እስቲ እንመልከት።
ማስተካከያ ለማድረግ የሚያነሳሱ አራት ምክንያቶች
5-6. (ሀ) በኢዩኤል 2:20 ላይ የሚገኘው ሐሳብ የትኛውን ጥያቄ ያስነሳል? (ለ) በኢዩኤል 2:25 ላይ የሚገኘው ሐሳብስ የትኛውን ጥያቄ ያስነሳል?
5 አንደኛ፣ ይሖዋ የአንበጣውን መንጋ በተመለከተ “የሰሜኑን ሠራዊት [አንበጦቹን] ከእናንተ አርቃለሁ” ብሎ ቃል እንደገባ ልብ በል። (ኢዩ. 2:20) አንበጦቹ የሚያመለክቱት የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በተመለከተ ኢየሱስ የሰጠውን መመሪያ የሚታዘዙትን የይሖዋ ምሥክሮች ከሆነ ይሖዋ እነሱን እንደሚያባርር ቃል የሚገባበት ምን ምክንያት አለ? (ሕዝ. 33:7-9፤ ማቴ. 28:19, 20) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ይሖዋ የሚያባርረው ታማኝ አገልጋዮቹን ሳይሆን የሕዝቡ ጠላት የሆነን ነገር ወይም አካል መሆን አለበት።
6 ሁለተኛውን ምክንያት ለማየት ደግሞ በኢዩኤል 2:25 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እንመልከት። በዚህ ጥቅስ ላይ ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “በመካከላችሁ የሰደድኩት ታላቁ ሠራዊቴ ይኸውም የአንበጣ መንጋው፣ ኩብኩባው፣ የማይጠግበው አንበጣና አውዳሚው አንበጣ ሰብላችሁን ለበሉባቸው ዓመታት ማካካሻ እሰጣችኋለሁ።” ይሖዋ፣ አንበጦቹ ላስከተሉት ጉዳት ‘ማካካሻ እንደሚሰጥ’ ቃል መግባቱን ልብ በል። አንበጦቹ የሚያመለክቱት የመንግሥቱን ሰባኪዎች ከሆነ መልእክታቸው ጉዳት ያደርሳል ማለት ነው። ሆኖም እነሱ የሚያውጁት ሕይወት አድን መልእክት ክፉ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ የሚያነሳሳ ነው። (ሕዝ. 33:8, 19) በእርግጥም መልእክቱ ለሰዎች በጣም ጠቃሚ ነው!
7. በኢዩኤል 2:28, 29 ላይ የሚገኘው “ከዚያ በኋላ” የሚለው ሐረግ ምን እንድንገነዘብ ይረዳናል?
7 ኢዩኤል 2:28, 29ን አንብብ። ሦስተኛው ምክንያት፣ በትንቢቱ ውስጥ ክንውኖቹ ከተጠቀሱበት ቅደም ተከተል ጋር የተያያዘ ነው። በጥቅሱ ላይ ይሖዋ “ከዚያ በኋላ” ማለትም አንበጦቹ የተሰጣቸውን ሥራ ከጨረሱ በኋላ “መንፈሴን አፈሳለሁ” እንዳለ ልብ አልክ? አንበጦቹ የአምላክ መንግሥት ሰባኪዎችን የሚያመለክቱ ከሆነ የምሥክርነት ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ይሖዋ በእነሱ ላይ መንፈሱን የሚያፈስበት ምን ምክንያት ይኖራል? እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ኃያል የሆነው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እነዚህን ክርስቲያኖች ባይረዳቸው ኖሮ ተቃውሞ አልፎ ተርፎም እገዳ እያለም እንኳ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት መስበካቸውን መቀጠል አይችሉም ነበር።
8. በራእይ 9:1-11 ላይ የተጠቀሱት አንበጦች ማንን ያመለክታሉ? (ሽፋኑን ተመልከት።)
8 ራእይ 9:1-11ን አንብብ። አሁን ደግሞ አራተኛውን ምክንያት እንመልከት። በኢዩኤል ትንቢት ላይ የተገለጸው የአንበጣ መንጋ ወረራ ከስብከቱ ሥራችን ጋር እንደሚያያዝ እናምን የነበረው በራእይ መጽሐፍ ላይ በሚገኝ ተመሳሳይ ትንቢት የተነሳ ነበር። በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ትንቢት የሰው ፊት ስላላቸውና “የወርቅ አክሊሎች የሚመስሉ ነገሮች” በራሳቸው ላይ ስለጫኑ አንበጦች ይናገራል። (ራእይ 9:7) አንበጦቹ “የአምላክ ማኅተም በግንባራቸው ላይ የሌላቸውን ሰዎች” ማለትም የአምላክን ጠላቶች ለአምስት ወር (የአንድ አንበጣ አማካይ ዕድሜ ያህል ማለት ነው) እንዲያሠቃዩ ተፈቀደላቸው። (ራእይ 9:4, 5) ይህ ትንቢት የሚገልጸው በመንፈስ ስለተቀቡት የይሖዋ አገልጋዮች መሆን አለበት። አምላክ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ ያስተላለፈውን የፍርድ መልእክት በድፍረት ስለሚያውጁ የሥርዓቱን ደጋፊዎች አሠቃይተዋቸዋል ሊባል ይችላል።
9. ኢዩኤል ባያቸውና ዮሐንስ በገለጻቸው አንበጦች መካከል ምን ጉልህ ልዩነቶች አሉ?
9 በራእይ መጽሐፍና በኢዩኤል መጽሐፍ ላይ በተጠቀሱት ትንቢቶች መካከል ተመሳሳይነት እንዳለ አይካድም። ሆኖም ጉልህ ልዩነቶች አሏቸው። ለምሳሌ፣ በኢዩኤል ትንቢት ላይ የተጠቀሱት አንበጦች ሰብሉን አውድመዋል። (ኢዩ. 1:4, 6, 7) ዮሐንስ ባየው ራእይ ላይ ያሉት አንበጦች ግን “ማንኛውንም የምድር ተክል . . . እንዳይጎዱ” ተነግሯቸዋል። (ራእይ 9:4) ኢዩኤል የጠቀሳቸው አንበጦች የመጡት ከሰሜን ነው። (ኢዩ. 2:20) ዮሐንስ ያያቸው አንበጦች የወጡት ግን ከጥልቁ ነው። (ራእይ 9:2, 3) በኢዩኤል መጽሐፍ ላይ የተጠቀሱትን አንበጦች ይሖዋ አባርሯቸዋል። በራእይ መጽሐፍ ላይ ያሉት አንበጦች ግን ከመባረር ይልቅ ሥራቸውን እንዲያጠናቅቁ ተፈቅዶላቸዋል። እነዚህ አንበጦች በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጡ የሚያደርግ ነገር እንደፈጸሙ የሚጠቁም ነገር የለም።—“ስለ አንበጦች የተነገሩ ትንቢቶች—ተመሳሳይ ሆኖም ልዩነት ያላቸው” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
10. በኢዩኤል ትንቢት ላይ የተጠቀሱት ‘አንበጦች’ እና በራእይ መጽሐፍ ላይ የተገለጹት “አንበጦች” የተለያዩ ነገሮችን ሊያመለክቱ እንደሚችሉ የሚያሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ጥቀስ።
10 በእነዚህ ሁለት ትንቢቶች መካከል ያሉት ጉልህ ልዩነቶች ራእዮቹ ግንኙነት የላቸውም ብለን እንድንደመድም ያደርጉናል። ታዲያ በኢዩኤል ትንቢት ላይ የተጠቀሱት አንበጦች በራእይ መጽሐፍ ላይ ከተገለጹት አንበጦች ጋር አንድ እንዳልሆኑ እየገለጽን ነው? አዎ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው አንድ ነገር በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር የተለያዩ ነገሮችን ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ፣ በራእይ 5:5 ላይ ኢየሱስ “ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ” ተብሎ የተጠራ ሲሆን በ1 ጴጥሮስ 5:8 ላይ ደግሞ ዲያብሎስ “እንደሚያገሳ አንበሳ” ተደርጎ ተገልጿል። አሁን ያለን ግንዛቤ ከሚያስነሳቸው ጥያቄዎች አንጻር በኢዩኤል መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን ትንቢት በተመለከተ ሌላ ማብራሪያ ማግኘት ያስፈልገናል። ታዲያ ይህ ማብራሪያ ምንድን ነው?
የሚያመለክተው ምንን ነው?
11. በኢዩኤል 1:6 እና 2:1, 8, 11 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ስለ አንበጦቹ ማንነት ምን ፍንጭ ይሰጠናል?
11 የኢዩኤልን ትንቢት አውድ በሚገባ ስንመለከተው ነቢዩ ትንቢት የተናገረው ስለ ወታደራዊ ጥቃት እንደሆነ እንገነዘባለን። (ኢዩ. 1:6፤ 2:1, 8, 11) ይሖዋ ‘ታላቅ ሠራዊቱን’ (የባቢሎን ወታደሮችን) ተጠቅሞ ዓመፀኛ የሆኑ እስራኤላውያንን እንደሚቀጣ ገልጾ ነበር። (ኢዩ. 2:25) ወራሪው ኃይል ‘የሰሜኑ ሠራዊት’ መባሉ የተገባ ነው፤ ምክንያቱም ባቢሎናውያኑ እስራኤልን የሚወሩት ከሰሜን መጥተው ነው። (ኢዩ. 2:20) ይህ ሠራዊት በደንብ ከተደራጀ የአንበጣ መንጋ ጋር ተመሳስሏል። ኢዩኤል ስለ ሠራዊቱ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እያንዳንዱ [ወታደር] መንገዱን ይዞ ይገሰግሳል። . . . ወደ ከተማዋ እየተጣደፉ ይገባሉ፤ በቅጥርም ላይ ይሮጣሉ። ቤቶችም ላይ ይወጣሉ፤ እንደ ሌባ በመስኮት ይገባሉ።” (ኢዩ. 2:8, 9) እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ሁሉም ቦታ ወታደሮች አሉ። ከእነሱ መደበቅ የሚቻልበት ቦታ የለም። ከባቢሎናውያን ሰይፍ የሚያመልጥ አንድም ሰው የለም!
12. ስለ አንበጦች የሚናገረው የኢዩኤል ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
12 ባቢሎናውያን (ወይም ከለዳውያን) በ607 ዓ.ዓ. ልክ እንደ አንበጣ ኢየሩሳሌምን ወረሯት። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “[የከለዳውያን] ንጉሥ . . . ወጣቶቻቸውን . . . በሰይፍ ገደለ፤ ለወጣቱም ሆነ ለድንግሊቱ፣ ለሽማግሌውም ሆነ ለአቅመ ደካማው አልራራም። አምላክ ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው። የእውነተኛውን አምላክ ቤት አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሰ፤ የማይደፈሩ ማማዎቿን ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ እንዲሁም ውድ የሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ አወደመ።” (2 ዜና 36:17, 19) ባቢሎናውያን ካደረሱት ውድመት በኋላ ምድሪቱን የተመለከቱ ሰዎች “ሰውም ሆነ እንስሳ የማይኖርባት ጠፍ መሬት ናት፤ ለከለዳውያንም ተሰጥታለች” ማለታቸው አያስገርምም።—ኤር. 32:43
13. የኤርምያስ 16:16, 18ን ትርጉም ግለጽ።
13 የኢዩኤል ትንቢት ከተነገረ ከ200 ዓመት ገደማ በኋላ ይሖዋ፣ ነቢዩ ኤርምያስ ስለዚህ ጥቃት ሌላ መረጃ እንዲጽፍ አድርጓል። ኤርምያስ፣ ወራሪዎቹ በክፉ ድርጊቶች የሚካፈሉ እስራኤላውያንን ለማግኘት አሰሳ እንደሚያደርጉና ሁሉንም አድነው እንደሚይዟቸው ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “‘እነሆ፣ እኔ ብዙ ዓሣ አጥማጆችን እሰዳለሁ’ ይላል ይሖዋ፤ ‘እነሱንም ያጠምዷቸዋል። ከዚያም በኋላ ብዙ አዳኞችን እሰዳለሁ፤ እነሱም ከየተራራው፣ ከየኮረብታውና ከየቋጥኙ ስንጣቂ አድነው ይይዟቸዋል። . . . ለሠሩት በደልና ኃጢአት የሚገባቸውን ሙሉ ዋጋ እከፍላቸዋለሁ።’” ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ያልሆኑት እስራኤላውያን ከባቢሎናውያን ወራሪዎች መሸሸግ የሚችሉበት ባሕርም ሆነ ጫካ አይኖርም።—ኤር. 16:16, 18
ተሃድሶ
14. ኢዩኤል 2:28, 29 ፍጻሜውን ያገኘው መቼ ነው?
14 በመቀጠል ኢዩኤል የተሃድሶ ዘመን እንደሚመጣ የሚገልጽ መልካም ዜና ተናገረ። ምድሩ ዳግመኛ ፍሬያማ ይሆናል። (ኢዩ. 2:23-26) ወደፊት ደግሞ መንፈሳዊ ምግብ የሚትረፈረፍበት ጊዜ ይመጣል። ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ መንፈሴን አፈሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ . . . በወንዶች ባሪያዎቼና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ሳይቀር መንፈሴን አፈሳለሁ።” (ኢዩ. 2:28, 29) አምላክ መንፈሱን ያፈሰሰው እስራኤላውያን ከባቢሎን ወደ ትውልድ አገራቸው እንደተመለሱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይህ የሆነው በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ካለፉ በኋላ ማለትም በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ ዕለት ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን?
15. በሥራ 2:16, 17 ላይ እንደተገለጸው ጴጥሮስ ኢዩኤል 2:28ን ጠቅሶ ሲናገር ምን ለውጥ አድርጓል? ይህስ ምን ይጠቁማል?
15 ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ በጴንጤቆስጤ ዕለት የተከናወነ አንድ አስደናቂ ነገር በኢዩኤል 2:28, 29 ላይ ከሚገኘው ትንቢት ጋር እንደሚገናኝ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ገልጾ ነበር። በዚያ ዕለት ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ መንፈስ ቅዱስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ በሰዎች ላይ ፈሰሰ፤ ሰዎቹም “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” መናገር ጀመሩ። (ሥራ 2:11) ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የኢዩኤልን ትንቢት ጠቅሶ ሲናገር የተጠቀመባቸው ቃላት ከመጀመሪያው ሐሳብ በተወሰነ መጠን ይለያሉ። ልዩነቱ ምን እንደሆነ አስተውለሃል? (የሐዋርያት ሥራ 2:16, 17ን አንብብ።) ጴጥሮስ ሐሳቡን የጀመረው “ከዚያ በኋላ” ብሎ ሳይሆን “በመጨረሻው ቀን” በማለት ነው፤ ጴጥሮስ “በመጨረሻው ቀን” አምላክ መንፈሱን “በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ” እንደሚያፈስስ ተናገረ፤ “በመጨረሻው ቀን” የሚለው ሐረግ በዚህ አገባቡ የአይሁድን ሥርዓት የመጨረሻ ቀን ያመለክታል። ይህም የኢዩኤል ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው ትንቢቱ ከተነገረ ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደሆነ ይጠቁማል።
16. የአምላክ መንፈስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በተከናወነው የስብከት ሥራ ላይ ምን ውጤት ነበረው? በዛሬው ጊዜስ?
16 የአምላክ መንፈስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን አስደናቂ በሆነ መንገድ ከፈሰሰ በኋላ የስብከቱ ሥራ እስከዚያ ድረስ ሆኖ በማያውቅ ስፋት መከናወን ጀመረ። ሐዋርያው ጳውሎስ በ61 ዓ.ም. ገደማ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ደብዳቤ ሲጽፍ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ” እንደተሰበከ መናገር ችሏል። (ቆላ. 1:23) “ፍጥረት ሁሉ” የሚለው አገላለጽ በወቅቱ የሚታወቀውን ዓለም ያመለክታል። ኃያል በሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ በዛሬው ጊዜ የስብከቱ ሥራ ከዚያ በሚበልጥ ስፋት እየተከናወነ ሲሆን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ተሰብኳል።—ሥራ 13:47፤ “መንፈሴን አፈሳለሁ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
የተለወጠው ነገር ምንድን ነው?
17. ስለ አንበጦች የሚገልጸውን የኢዩኤል ትንቢት በምንረዳበት መንገድ ላይ ምን ለውጥ አድርገናል?
17 ለውጥ ያደረግነው በምን ላይ ነው? በኢዩኤል 2:7-9 ላይ ስለሚገኘው ትንቢት ይበልጥ ትክክለኛ ግንዛቤ አግኝተናል። በአጭሩ ለማስቀመጥ ያህል፣ ይህ ትንቢት የሚያመለክተው በቅንዓት የምናከናውነውን የስብከት ሥራ ሳይሆን በ607 ዓ.ዓ. የባቢሎናውያን ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ ያካሄደውን ወረራ ነው።
18. ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር በተያያዘ ያልተለወጠው ነገር ምንድን ነው?
18 ያልተለወጠው ነገርስ ምንድን ነው? የይሖዋ ሕዝቦች በሁሉም ቦታ እንዲሁም ሁሉንም ዓይነት ዘዴ በመጠቀም ምሥራቹን መስበካቸውን ይቀጥላሉ። (ማቴ. 24:14) መንግሥት የሚጥለው የትኛውም እገዳ የስብከት ተልእኳችንን እንዳንወጣ ሊያደርገን አይችልም። ደግሞም ይሖዋ ጥረታችንን ስለባረከው የስብከት እንቅስቃሴያችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የጨመረ ሲሆን የመንግሥቱን ምሥራች በድፍረት እየሰበክን ነው! በተጨማሪም ይሖዋ በትክክለኛው ጊዜ “ወደ እውነት ሁሉ” እንደሚመራን በመተማመን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በተመለከተ የጠራ ግንዛቤ ለማግኘት የእሱን አመራር በትሕትና መፈለጋችንን እንቀጥላለን!—ዮሐ. 16:13
መዝሙር 97 የአምላክ ቃል ሕይወት ነው
a ባለፉት በርካታ ዓመታት፣ በኢዩኤል ምዕራፍ 1 እና 2 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ትንቢት በዘመናችን ስለሚከናወነው የስብከት ሥራ እንደሚናገር እናምን ነበር። ሆኖም በኢዩኤል ትንቢት ላይ የሚገኘውን ይህን ዘገባ በምንረዳበት መንገድ ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልገን የሚጠቁሙ አራት አጥጋቢ ምክንያቶች አሉ። እነዚህ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?
b ለምሳሌ ያህል፣ በሚያዝያ 15, 2009 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ፍጥረት የይሖዋን ጥበብ በግልጽ ያሳያል” የሚለውን ርዕስ ከአንቀጽ 14-16 ተመልከት።