የይሖዋ ቀን ቀርቧል
“እናንተ ሽማግሌዎች፣ ይህን ስሙ፤ በምድርም የምትኖሩ ሁሉ፣ አድምጡ።”—ኢዩኤል 1:2
1, 2. ይሖዋ ኃይለኛ ትንቢቱን እንዲናገር ኢዩኤልን ያነሣሣው በይሁዳ በተፈጸመ በየትኛው ሁኔታ ምክንያት ነው?
“የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና ለቀኑ ወዮ! እርሱም ሁሉን ከሚችል ከአምላክ ዘንድ እንደ ጥፋት ይመጣል።” እንዴት ያለ የሚያሸብር መልእክት ነው! ይህ በነቢዩ ኢዩኤል በኩል አምላክ ያስነገረው መልእክት ነበር።
2 እነዚህ የኢዩኤል 1:15 ቃላት የተጻፉት በይሁዳ ምድር ሲሆን የተጻፉበት ዘመን 820 ከዘአበ ሳይሆን አይቀርም። በዚያ ጊዜ ምድሪቱ በደን በተሸፈኑ ኮረብታዎች አጊጣ ነበር። ፍራፍሬና እህል የተትረፈረፈበት ጊዜ ነበር። ሰፋፊና ለምለም መስኮች ነበሩ። ቢሆንም ከባድ ስህተት ተፈጽሞ ነበር። በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምድር የበኣል አምልኮ ተስፋፍቷል። ሕዝቦቹ በዚህ የሐሰት አምላክ ፊት ይሰክሩና ይፈነጥዙ ነበር። (ከ2 ዜና መዋዕል 21:4-6, 11 ጋር አወዳድር።) ታዲያ ይሖዋ ይህ ሁሉ እንዲቀጥል ይፈቅድ ይሆን?
3. ይሖዋ ስለ ምን ነገር ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል? አሕዛብስ መዘጋጀት የነበረባቸው ለምን ነገር ነው?
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የኢዩኤል መጽሐፍ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ እንዳይኖረን ያደርጋል። ይሖዋ አምላክ ልዕልናውን ያረጋግጣል፣ ስሙንም ይቀድሳል። የይሖዋ ታላቅ ቀን ቀርቦ ነበር። አምላክ በወቅቱ “በኢዮሳፍጥ ሸለቆ” የቅጣት ፍርዱን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ሊያወርድ ነበር። (ኢዩኤል 3:12) ሁሉን ከሚችለው ይሖዋ ጋር ለመዋጋት ይዘጋጁ። ይህ ታላቅ የይሖዋ ቀን እኛንም ይነካናል። ስለዚህ ስለ ዘመናችንና ስለ ቀድሞው ዘመን የተነገሩትን የኢዩኤል ትንቢታዊ ቃላት እንመርምር።
የበራሪ ነፍሳት ወረራ
4. ኢዩኤል ማስጠንቀቂያ የሰጠበት ነገር ምን ያህል ታላቅ ነበር?
4 ይሖዋ በነቢዩ በኩል እንዲህ ይላል:- “እናንተ ሽማግሌዎች፣ ይህን ስሙ፤ በምድርም የምትኖሩ ሁሉ፣ አድምጡ። ይህ በዘመናችሁ ወይስ በአባቶቻችሁ ዘመን ሆኖ ነበርን? ይህን ለልጆቻችሁ ንገሩ፤ ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው፣ ልጆቻቸውም ለኋለኛው ትውልድ ይንገሩ።” (ኢዩኤል 1:2, 3) ሽማግሌዎቹና ሕዝቡ በአጠቃላይ በራሳቸው ዘመንም ሆነ በአባቶቻቸው ዘመን ሆኖ የማያውቅ ነገር ሊመለከቱ ነው። ነገሩ በጣም የሚያስደንቅ ከመሆኑ የተነሣ እስከ ሦስተኛ ትውልድ ድረስ ሲተረክ ይቆያል! ይህ አስደናቂ የሆነ ክስተት ምንድን ነው? ይህን ለማወቅ ራሳችንን በኢዩኤል ዘመን እንዳለን አድርገን እናስብ።
5, 6. (ሀ) ኢዩኤል ትንቢት የተናገረለትን መቅሠፍት ግለጽ። (ለ) የዚህ መቅሠፍት ምንጭ ማን ነበር?
5 አድምጡ! ኢዩኤል ከሩቅ የሚመጣ የሚያስገመግም ድምፅ ይሰማል። ሰማዩ መጨለም ይጀምራል፣ ጨለማው ምድሪቱን እየሸፈነ በሄደ መጠን ጆሮ ጭው የሚያደርገው ድምፅ ይጨምራል። ከዚያ በኋላ እንደ ጭስ ያለ ዳመና ከሰማይ መውረድ ይጀምራል። ይህ በሚልዮን የሚቆጠሩ የተለያዩ ነፍሳት ያሉት ሠራዊት ነው። ይህ ሠራዊት የሚያስከትለው ውድመት እንዴት የከፋ ይሆናል! አሁን ኢዩኤል 1:4ን እንመልከት። እነዚህ ወራሪ ነፍሳት በራሪ የሆኑ አንበጦች ብቻ አይደሉም። ሌሎችም አሉ! በልተው የማይጠግቡ በመሬት ላይ የሚርመሰመሱ ክንፍ የሌላቸው አንበጦችም አብረዋቸው እየመጡ ነው። አንበጦቹ የሚመጡት በነፋስ ተገፍተው በድንገት ሲሆን ድምፃቸው እንደ ሠረገሎች ድምፅ ነው። (ኢዩኤል 2:5) በሚልዮን የሚቆጠሩት እነዚህ ነፍሳት በቃኝ ማለትን የማያውቁ ከመሆናቸው የተነሣ እንደ ገነት የለመለመውን አካባቢ በቅጽበት ምድረ በዳ ሊያስመስሉት ይችላሉ።
6 ከእነርሱም ሌላ ገና ወደ እሳት ራትነት ወይም ወደ ቢራቢሮነት ያልተለወጡ አባ ጨጓሬዎች በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው። እነዚህ የተራቡ የአባ ጨጓሬ ሠራዊቶችም እንደ አንበጦቹ፣ እጸዋት አረንጓዴነታቸውን ፈጽመው እስኪያጡ ድረስ ቀነጣጥበው በልተው ሊጨርሱ የሚችሉ ናቸው። ከእነዚህ የሚቀር ነገር ቢኖር አንበጣዎች ይበሉታል። ከአንበጣዎቹ የተረፈውን ደግሞ ፈጣን የሆኑ ኩብኩባዎች ልቅምቅም አድርገው ይበሉታል። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ ልብ በሉ። አምላክ በኢዩኤል ምዕራፍ 2 ቁጥር 11 ላይ የአንበጦቹ ጭፍራ ‘የእርሱ ሠራዊት’ እንደሆነ ይናገራል። አዎን፣ ምድሪቱን የሚያወድመውንና ከባድ ችጋር የሚያስከትለውን የአንበጣ መቅሠፍት የሚያመጣው እሱ ነው። መቼ? “ከይሖዋ ቀን” በፊት።
‘እናንተ ሰካራሞች፣ ንቁ’!
7. (ሀ) የይሁዳ ሃይማኖታዊ መሪዎች ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? (ለ) በአሁኑ ጊዜ ያሉት የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ሁኔታ የይሁዳ ሃይማኖታዊ መሪዎች ከነበሩበት ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
7 የሚከተለው ትእዛዝ ሲሰጥ ወራዳ የሆኑ ሰዎችን ማለትም የይሁዳ ሃይማኖታዊ መሪዎችን ለይቶ ጠቅሷል:- “በተሃ ወይን ጠጃችሁ ከአፋችሁ ተወግዶአልና እናንተ ሰካራሞች፣ ነቅታችሁ አልቅሱ፤ እናንተም የወይን ጠጅ የምትጠጡ ሁሉ፣ ዋይ በሉ።” (ኢዩኤል 1:5) አዎን፣ መንፈሳዊ ስካር ያደነገዛቸው የይሁዳ ሰካራሞች ‘ከስካራችሁ ንቁ’ ተብለዋል። ይሁን እንጂ ይህ ጥንት የተፈጸመ ያለፈ ታሪክ ነው ብላችሁ አታስቡ። ከይሖዋ ታላቅ የጦርነት ቀን በፊት ባለው በዚህ ዘመንም ቢሆን የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በምሳሌያዊ ሁኔታ በተሃ ጠጅ ስለጠገቡ ይህን ከልዑል አምላክ የተላከባቸውን መልእክት ማስተዋል አልቻሉም። ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን ከስካራቸው ሲያነቃቸው ምንኛ ይደነግጡ ይሆን!
8, 9. (ሀ) ኢዩኤል አንበጣዎቹንና ያስከተሉትን ጉዳት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ አንበጦቹ የሚወክሉት እነማንን ነው?
8 አሁን ታላቁን የአንበጣ ጭፍራ ተመልከቱ! “ቁጥርም የሌለው ብርቱ ሕዝብ በምድሬ ላይ ወጥቶአልና፤ ጥርሳቸው እንደ አንበሳ ጥርስ፣ መንጋጋቸውም እንደ እንስቲቱ አንበሳ መንጋጋ ነው። ወይኔን ባዶ ምድር አደረገው፣ በለሴንም ሰበረው፤ ባዶም አደረገው፣ ጣለውም፤ ቅርንጫፎቹም ነጡ። ለቁንጅናዋ ባል ማቅ ለብሳ እንደምታለቅስ ድንግል አልቅሺ።”—ኢዩኤል 1:6-8
9 ይህ፣ የአንበጦች “ብሔር” ማለትም የአንበጦች መንጋ ይሁዳን እንደሚወርር ብቻ የሚናገር ትንቢት ነውን? የለም፣ ከዚህ የበለጠ ትርጉም አለው። በኢዩኤል 1:6 እና ራእይ 9:7 ላይ የአምላክ ሕዝቦች በአንበጣ ተመስለዋል። ዘመናዊው የአንበጦች ሠራዊት በአሁኑ ጊዜ 5,600,000 በሚያክሉት የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ከሚታገዙት ከይሖዋ ቅቡዓን ‘የአንበጦች ሠራዊት’ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም። (ዮሐንስ 10:16) ታዲያ የዚህ ታላቅ የይሖዋ አምላኪዎች ሠራዊት ክፍል በመሆናችሁ ደስ አይላችሁም?
10. የአንበጣው መቅሠፍት በይሁዳ ላይ ምን ውጤት ነበረው?
10 ኢዩኤል 1:9-12 የአንበጦቹ መቅሠፍት የሚያስከትላቸውን አንዳንድ ውጤቶች ይዘረዝራል። እየተከታተሉ የሚመጡት የአንበጣ ጭፍራዎች ምድሪቱን ሙሉ በሙሉ ባድማ ያደርጓታል። ከሃዲዎቹ ካህናት እህል፣ ወይን ጠጅና ዘይት ስለሚያጡ የክህነት አገልግሎታቸውን ማከናወን አይችሉም። አንበጦቹ አዝርእቱን ስለሚያወድሙና የፍራፍሬ ተክሎችን ፍሬ አልባ አድርገው ስለሚያስቀሯቸው ምድሪቱ ሳትቀር ታለቅሳለች። የወይን ተክሎች ስለሚበላሹ በመንፈሳዊ የሰከሩት የበዓል አምላኪዎችም የሚቀምሱት ወይን ጠጅ አያገኙም።
‘እናንተ ካህናት ደረታችሁን እየመታችሁ አልቅሱ’
11, 12. (ሀ) በዛሬው ጊዜ የአምላክ ካህናት ነን የሚሉት እነማን ናቸው? (ለ) የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች በዘመናዊው የአንበጣ መቅሠፍት የተነኩት እንዴት ነው?
11 አምላክ ለእነዚህ መንገዳቸውን ለሳቱ ካህናት የላከውን መልእክት አዳምጡ:- “እናንተ ካህናት ማቅ ታጥቃችሁ አልቅሱ፤ እናንተም የመሠዊያ አገልጋዮች፣ ዋይ በሉ።” (ኢዩኤል 1:13) የኢዩኤል ትንቢት በመጀመሪያ ፍጻሜውን ባገኘበት ጊዜ ሌዋውያን ካህናት በመሠዊያ ላይ ያገለግሉ ነበር። በመጨረሻው ፍጻሜ ጊዜስ? በዛሬው ጊዜ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የአምላክ አገልጋዮችና “ካህናት” ነን ስለሚሉ በአምላክ መሠዊያ የማገልገል ሥልጣን አለን ብለዋል። ይሁን እንጂ የአምላክ ዘመናዊ አንበጦች እንቅስቃሴያቸውን በሚያካሂዱበት በአሁኑ ጊዜ ምን እየሆነ ነው?
12 የሕዝበ ክርስትና “ካህናት” የይሖዋን ሕዝቦች እንቅስቃሴ በሚመለከቱበትና የሚያሰሙትን የመለኮታዊ ፍርድ ማስጠንቀቂያ በሚያዳምጡበት ጊዜ በፍርሐት ይርበደበዳሉ። የመንግሥቱ መልእክት ባለው የአውዳሚነት ውጤት ምክንያት በብስጭትና በቁጣ ደረታቸውን እየመቱ ያለቅሳሉ። መንጎቻቸው ከጉያቸው እየሾለኩ ሲወጡባቸው ወዮ ይላሉ። የግጦሽ መስካቸው ባድማ ስለሆነባቸው የገቢ ምንጫቸው መቋረጡን እያሰቡ ማቅ ለብሰው ሌሊቱን በሙሉ ያለቅሳሉ። በቅርቡ ደግሞ ፈጽመው ሥራ አጥ ይሆናሉ! እንዲያውም አምላክ ፍጻሜያቸው ስለቀረበ ሌሊቱን በሙሉ እንዲያለቅሱ ይነግራቸዋል።
13. ሕዝበ ክርስትና በቡድን ደረጃ ለይሖዋ ማስጠንቀቂያ አዎንታዊ ምላሽ ትሰጣለችን?
13 ኢዩኤል 1:14 እንደሚለው ንስሐ ከመግባትና ‘ይሖዋ እንዲረዳቸው ከመጮህ’ በስተቀር ሌላ ምንም ተስፋ አይኖራቸውም። ይሁን እንጂ የሕዝበ ክርስትና የቀሳውስት ክፍል እንዳለ ወደ ይሖዋ ይመለሳል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን? በፍጹም አንችልም! በመካከላቸው የሚገኙ አንዳንድ ግለሰቦች ለይሖዋ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ይሰጡ ይሆናል። ይሁን እንጂ በቡድን ደረጃ የቀሳውስቱና የምዕመናኖቻቸው መንፈሳዊ ረሐብ ይቀጥላል። ነቢዩ አሞጽ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “እነሆ፣ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም።” (አሞጽ 8:11) በአንፃሩ ግን እኛ አምላክ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል ለሚያቀርብልን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ድግስ ምንኛ አመስጋኞች ነን!— ማቴዎስ 24:45-47
14. የአንበጦቹ መቅሠፍት መንገድ ጠራጊ የሆነው ለምን ነገር ነው?
14 በአሁኑ ጊዜ ያለውም ሆነ በጥንት ጊዜ የነበረው የአንበጦቹ መቅሠፍት የሌላ ነገር መንገድ ጠራጊ ነው። የምን ነገር? ኢዩኤል እንዲህ በማለት በግልጽ ይነግረናል:- “የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና ለቀኑ ወዮ! እርሱም ሁሉን ከሚችል ከአምላክ ዘንድ እንደ ጥፋት ይመጣል።” (ኢዩኤል 1:15) በዛሬው ጊዜ የአምላክ የአንበጣ ሠራዊት መላዋን ምድር መውረሩ ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን ቅርብ መሆኑን በግልጽ ያመለክታል። በክፉዎች ላይ መለኮታዊ ፍርድ የሚወርድበትንና ይሖዋ በድል አድራጊነት ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱን የሚያረጋግጥበትን ይህን ልዩ የሆነ ቀን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ሁሉ እንደሚናፍቁ የተረጋገጠ ነው።
15. መለኮታዊውን ማስጠንቀቂያ የተቀበሉት ሰዎች የምድሪቱን አስከፊ ገጽታ በመመልከት ምን ተሰምቷቸው ነበር?
15 ኢዩኤል 1:16-20 እንደሚያመለክተው ከጥንትዋ የይሁዳ ምድር ለምግብነት የሚያገለግል ነገር ጠፍቶ ነበር። ስለዚህ ደስታ የሚባል ነገር አልነበረም። መጋዘኖች ወና ሆነዋል፣ ጎተራዎችም ፈራርሰዋል። ሣሩ በአንበጦቹ ተጠራርጎ ስለተበላ ከብቶች ይቅበዘበዙ ነበር። ብዙ የበግ መንጋዎችም በችጋር አልቀዋል። እንዴት ያለ ታላቅ እልቂት ነበር! እንዲህ ባለው ሁኔታ ኢዩኤል ምን ያደርግ ይሆን? ቁጥር 19 እንደሚለው “አቤቱ . . . [“ይሖዋ፣” NW] ወዳንተ እጮሃለሁ” ብሏል። ዛሬም ቢሆን ብዙዎች መለኮታዊውን ማስጠንቀቂያ ያከብራሉ፤ በእምነት ይሖዋ አምላክን ይጠራሉ።
‘የይሖዋ ቀን መጥቷል’
16. ‘በምድር የሚኖሩ’ መንቀጥቀጥ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
16 የሚከተለውን የአምላክ ትእዛዝ አዳምጡ:- “በጽዮን መለከትን ንፉ፣ በቅዱሱም ተራራዬ ላይ እሪ በሉ፣ በምድርም የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ።” (ኢዩኤል 2:1) እንዲህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? ትንቢቱ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “የእግዚአብሔር ቀን መጥቶአልና፣ እርሱም ቀርቧልና . . . የጨለማና የጭጋግ ቀን፣ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው፣ ታላቅና ብርቱ ሕዝብ በተራሮች ላይ እንደ ወገግታ ተዘርግቶአል።” (ኢዩኤል 2:1, 2) ታላቁ የይሖዋ ቀን ልባዊ የጥድፊያ ስሜት የሚጠይቅ እንደሆነ ተገልጾአል።
17. በይሁዳ የሚገኘው ምድርና ሕዝቡ በአንበጦቹ መቅሠፍት የተነኩት እንዴት ነበር?
17 ደከመኝ የማይሉት አንበጦች እንደ ኤደን ገነት የተዋበውን አካባቢ ወደ ትቢያነት በሚለውጡበት ጊዜ የነቢዩ ራእይ ምን ዓይነት ውጤት እንደሚኖረው ገምቱ። የአንበጦቹ ሠራዊት ምን እንደሚመስል ሲገልጽ አዳምጡ:- “መልካቸው እንደ ፈረስ መልክ ነው፣ እንደ ፈረሶችም ይሮጣሉ። በተራራ ላይ እንዳሉ ሰረገሎች ድምፅ፣ ገለባውንም እንደሚበላ እንደ እሳት ነበልባል ድምፅ፣ ለሰልፍም እንደ ተዘጋጀ እንደ ብርቱ ሕዝብ ያኮበኩባሉ። ከፊታቸው አሕዛብ ይንቀጠቀጣሉ፤ የሰውም ፊት ሁሉ ይጠቁራል።” (ኢዩኤል 2:4-6) በኢዩኤል ዘመን የአንበጦቹ መቅሠፍት በወረደ ጊዜ የበዓል አምላኪዎች ድንጋጤና ፍርሐት በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ፊታቸው በጭንቀት ጠቁሮ ነበር።
18, 19. በዛሬው ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች እንቅስቃሴ እንደ አንበጣ መቅሠፍት የሆነው እንዴት ነው?
18 ደከመኝ የማይሉትንና በሥርዓት የሚንቀሳቀሱትን አንበጦች የሚያቆም ነገር አልተገኘም። “እንደ ኃያላን ይሮጣሉ፣” በቅጥሮች ላይ ሳይቀር ይወጣሉ። ‘አንዳንዶቹ በሰልፉ መካከል ቢወድቁ እንኳን ሌሎቹ መንገዳቸውን ሳያቋርጡ ይቀጥላሉ።’ (ኢዩኤል 2:7, 8) የዘመናችንን የአምላክ ምሳሌያዊ የአንበጦች ሠራዊት በትክክል የሚገልጽ እንዴት ያለ ሥዕላዊ ትንቢት ነው! ዛሬም የይሖዋ የአንበጦች ሠራዊት ወደፊት በመግፋት ላይ ይገኛል። የትኛውም የጥላቻ “ቅጥር” ሊያግዳቸው አልቻለም። የጀርመኑን የናዚ መሪ ሂትለርን ሃይል! ባለማለታቸው ‘በሰልፉ መካከል እንደወደቁት’ በሺህ የሚቆጠሩ ምሥክሮች ሞትን ለመጋፈጥ ፈቃደኞች ናቸው። ለአምላክ ያላቸውን የጸና አቋም በምንም መንገድ አያላሉም።
19 የዘመናችን የአምላክ የአንበጣ ሠራዊት በሕዝበ ክርስትና “ከተማ” ውስጥ የተጣራ ምሥክርነት ሰጥተዋል። (ኢዩኤል 2:9) እንዲያውም ይህን ምሥክርነታቸውን ያሰሙት በመላው ዓለም ነው። አሁንም ቢሆን ማንኛውንም ዓይነት እንቅፋት እየተወጡ በሚልዩን ወደሚቆጠሩ ቤቶች ይሄዳሉ፣ ሰዎችን በመንገድ ላይ፣ በስልክና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በማነጋገር የይሖዋን መልእክት እያወጁ ነው። በቢልዮን የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን ያሠራጩ ሲሆን በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት በሚያደርጉት ቀጣይ አገልግሎታቸው ገና እጅግ በጣም ብዙ ጽሑፎች ያሠራጫሉ።— ሥራ 20:20, 21
20. ዘመናዊዎቹን አንበጦች የሚደግፋቸው ማን ነው? ከምንስ ውጤት ጋር?
20 በጣም ብዙ የሆነው የአንበጣ ጭፍራ እንደ ዳመና ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ሊሸፍን እንደሚችል ኢዩኤል 2:10 ያመለክታል። (ከኢሳይያስ 60:8 ጋር አወዳድር።) ከዚህ ወታደራዊ ኃይል በስተጀርባ ያለው ማን እንደሆነ የሚያጠራጥር ነገር ሊኖር ይችላልን? ከአንበጦቹ የሚያስገመግም ድምፅ በላይ የሚከተሉትን የኢዩኤል 2:11 ቃላት እንሰማለን:- “እግዚአብሔርም በሠራዊቱ ፊት ድምፁን ይሰጣል፤ ሰፈሩ እጅግ ብዙ ነውና፣ ቃሉንም የሚያደርግ እርሱ ኃያል ነውና፤ የእግዚአብሔርም ቀን ታላቅና እጅግ የሚያስፈራ ነውና ማንስ ይችለዋል?” አዎን፣ ይሖዋ አምላክ ታላቁ ቀን ከመምጣቱ በፊት የአንበጦች ሠራዊቱን በመላክ ላይ ነው።
‘ይሖዋ አይዘገይም’
21. ‘የይሖዋ ቀን እንደ ሌባ ሆኖ ሲመጣ’ ውጤቱ ምን ይሆናል?
21 ሐዋርያው ጴጥሮስም ልክ እንደ ኢዩኤል ስለ ታላቁ የይሖዋ ቀን ተናግሯል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፣ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይቀልጣል፣ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።” (2 ጴጥሮስ 3:10) ክፉዎቹ መንግሥታዊ “ሰማያት” በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ሆነው “ምድርን” ማለትም ከአምላክ የራቀውን የሰው ልጅ ክፍል ይገዛሉ። (ኤፌሶን 6:12፤ 1 ዮሐንስ 5:19) እነዚህ ምሳሌያዊ ሰማያትና ምድር በታላቁ የይሖዋ ቀን የሚወርደውን የመለኮታዊ ቁጣ ትኩሳት መቋቋም አይችሉም። ከዚህ ይልቅ እነዚህ ሰማያትና ምድር በምንጠባበቀው የተስፋ ቃል መሠረት ‘ጽድቅ በሚሰፍንባቸው አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር’ ይተካሉ።—2 ጴጥሮስ 3:13
22, 23. (ሀ) ይሖዋ በምሕረቱ ላሳየው ትዕግሥት እንዴት ሊሰማን ይገባል? (ለ) እየቀረበ ስላለው የይሖዋ ቀን እንዴት ሊሰማን ይገባል?
22 በዛሬው ጊዜ እምነትን የሚፈትኑና የሚያዘናጉ ነገሮች በመብዛታቸው የጊዜያችንን አጣዳፊነት መርሳት ልንጀምር እንችላለን። ይሁን እንጂ ምሳሌያዊዎቹ አንበጦች ወደፊት በገፉ መጠን በርካታ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ጥሩ ምላሽ በመስጠት ላይ ናቸው። ለዚህ ሥራ የሚያስፈልገውን ጊዜ የሰጠው አምላክ ራሱ በመሆኑ የእርሱን ትዕግሥት እንደ መዘግየት አድርገን ልንመለከተው አይገባም። “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፤ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።”—2 ጴጥሮስ 3:9
23 ታላቁን የይሖዋ ቀን ስንጠባበቅ በ2 ጴጥሮስ 3:11, 12 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የሐዋርያው ቃል ልብ እንበል:- “ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኮላችሁ፣ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ፣ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይፈታል።” መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ከይሖዋ የአንበጣ ሠራዊት ጋር ጎን ለጎን በመሄድ በመንግሥቱ ምሥራች ስብከት የማያሰልስና ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረጋችን የዚህ ቅዱስ ኑሮ ክፍል እንደሆነ አያጠራጥርም።—ማርቆስ 13:10
24, 25. (ሀ) ከይሖዋ የአንበጦች ሠራዊት ጋር ለመሥራት ላገኘኸው መብት ምን ምላሽ ትሰጣለህ? (ለ) ኢዩኤል የትኛውን ተገቢ ጥያቄ አንስቷል?
24 የማይበገሩት የአምላክ የአንበጣ ሠራዊቶች መላዋን ምድር በማዳረስ ላይ ከመሆናቸውም በላይ ታላቁ የይሖዋ ቀን ከመፈንዳቱ በፊት ዘመቻቸውን አያቆሙም። ምንም ዓይነት ኃይል የማያቆመው የዚህ ሠራዊት መኖር ራሱ የይሖዋ ቀን የቀረበ መሆኑን ያረጋግጣል። ከሚያስፈራውና ከታላቁ የይሖዋ ቀን በፊት በሚደረገው የመጨረሻ ዘመቻ ከአምላክ ቅቡዓን አንበጦችና ረዳቶቻቸው ጎን ተሰልፋችሁ ለማገልገል በመቻላችሁ ደስ አይላችሁም?
25 በእርግጥም የይሖዋ ቀን በጣም ታላቅ ቀን ይሆናል! “ማንስ ይችለዋል?” የሚለው ጥያቄ መነሳቱ ምንም አያስደንቀንም። (ኢዩኤል 2:11) ይህን ጥያቄና ሌሎች ብዙ ጉዳዮችንም በሚቀጥሉት ሁለት ርዕሰ ትምህርቶች ላይ እንመለከታለን።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ይሖዋ የነፍሳት መቅሠፍት በይሁዳ ላይ እንደሚመጣ ያስጠነቀቀው ለምን ነበር?
◻ በኢዩኤል ትንቢት ዘመናዊ ፍጻሜ መሠረት የይሖዋ አንበጦች እነማን ናቸው?
◻ የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ለአንበጦቹ መቅሠፍት ምን ምላሽ ሰጥተዋል? አንዳንዶችስ መቅሠፍቱ ከሚያስከትለው ነገር ሊያመልጡ የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ በ20ኛው መቶ ዘመን የአንበጦቹ መቅሠፍት ምን ያህል ተስፋፍቶ ነበር? መቅሠፍቱ የሚቀጥለውስ እስከ መቼ ነው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የነፍሳቱ መቅሠፍት ለከፋ ነገር መንገድ ጠራጊ ነበር
[ምንጭ]
መለመላውን የቀረ ዛፍ:- FAO photo/G. Singh
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
[ምንጭ]
አንበጣ:- FAO photo/G. Tortoli; የአንበጦች መንጋ:- FAO photo/Desert Locust Survey
ከዘመናዊው የአንበጦች መቅሠፍት በስተጀርባ ያለው ይሖዋ አምላክ ነው