የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 31—አብድዩ
ጸሐፊው:- አብድዩ
ተጽፎ ያለቀው:- በ607 ከክ. ል. በፊት ገደማ
ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በጣም አጭር የሆነው የአብድዩ መጽሐፍ ባሉት 21 ቁጥሮች፣ ለአንድ ብሔር ፈጽሞ መጥፋት ምክንያት የሆነውን የይሖዋ ፍርድ ያወጀ ከመሆኑም በላይ ውሎ አድሮ የአምላክ መንግሥት ድል ማድረጉ እንደማይቀር አስታውቋል። ይህ መጽሐፍ የሚጀምረው “የአብድዩ ራእይ” በሚል አጭር መግቢያ ነው። አብድዩ መቼና የት እንደተወለደ፣ ከየትኛው ነገድ እንደሆነ እንዲሁም ሕይወቱ ምን እንደሚመስል ምንም የተገለጸልን ነገር የለም። ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው አስፈላጊው ነገር መልእክቱ እንጂ የነቢዩ ማንነት አይደለም። ምክንያቱም አብድዩ ራሱ እንደተናገረው መልእክቱ ‘ከይሖዋ ዘንድ’ የመጣ ነበር።
2 መልእክቱ በዋነኛነት የሚያተኩረው በኤዶም ላይ ነው። ከሙት ባሕር በስተ ደቡብ ከዓረባ ትይዩ የሚገኘው የኤዶም ምድር፣ የሴይር ተራራ በመባልም የሚታወቅ ሲሆን ረጃጅም ተራሮችና ጥልቅ ሸለቆዎች የሚበዙበት ወጣ ገባ ምድር ነው። በአንዳንድ ቦታዎች ከዓረባ በስተ ምሥራቅ ያለው የተራሮች ሰንሰለት እስከ 1,700 ሜትር ከፍታ ይደርሳል። የቴማን አውራጃ በሕዝቦቹ ጥበበኝነትና ድፍረት የታወቀ ነበር። የኤዶም ምድር አቀማመጥ ለጠላት ወረራ የማይመች መሆኑ ነዋሪዎቹ በዚህ ተፈጥሯዊ መከላከያ በመመካት ኩሩዎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።a
3 ኤዶማውያን የያዕቆብ ወንድም የሆነው የዔሳው ዝርያዎች ናቸው። የያዕቆብ ስም ተለውጦ እስራኤል በመባሉ ኤዶማውያን የእስራኤላውያን የቅርብ ዘመዶች ስለነበሩ እንደ ‘ወንድማማች’ የሚታዩ ሕዝቦች ነበሩ። (ዘዳ. 23:7) ይሁን እንጂ ኤዶማውያን ያደረጉት ነገር ከወንድም የሚጠበቅ አልነበረም። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ሙሴ፣ የኤዶም ንጉሥ አገሩን አቋርጠው በሰላም እንዲያልፉ እንዲፈቅድለት መልእክተኛ ልኮ ነበር። ኤዶማውያን ግን የጠላትነት መንፈስ ከማሳየታቸውም በላይ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ለመግለጽ ጥቃት ለመሰንዘር ተነስተው ነበር። (ዘኁ. 20:14-21) ዳዊት፣ ኤዶማውያንን ድል አድርጎ ቢገዛቸውም ከጊዜ በኋላ በኢዮሣፍጥ ዘመን ከአሞናውያንና ከሞዓባውያን ጋር በማበር ይሁዳን ወግተዋል። የኢዮሣፍጥ ልጅ በነበረው በንጉሥ ኢዮራም ላይ ዓምጸዋል። ከጋዛና ከጢሮስ እስራኤላውያን ምርኮኞችን ወስደዋል። ይባስ ብለው በንጉሥ አካዝ ዘመን ደግሞ ይሁዳን ወርረው ተጨማሪ ምርኮኞች ወስደዋል።— 2 ዜና 20:1, 2, 22, 23፤ 2 ነገ. 8:20-22፤ አሞጽ 1:6, 9፤ 2 ዜና 28:17
4 ይህ ጠላትነት፣ ኢየሩሳሌም በባቢሎን ጭፍሮች በወደመችበት በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ። ኤዶማውያን ይህን ጥፋት በደስታ ከመመልከትም አልፈው ወራሪዎቹ ኢየሩሳሌምን ፈጽመው እንዲያወድሟት ማበረታቻ ሰጥተዋል። “አፍርሷት፤ ፈጽማችሁ አፈራርሷት!” ብለው ነበር። (መዝ. 137:7) ወራሪዎቹ የመዘበሩትን ንብረት ለመከፋፈል ዕጣ በተጣጣሉ ጊዜ ኤዶማውያን ተካፋይ ሆነዋል። በተጨማሪም ከይሁዳ ሸሽተው ለማምለጥ የሞከሩትን አይሁዳውያን መንገድ ዘግተው በመያዝ ለጠላቶቻቸው አሳልፈው ሰጥተዋቸዋል። አብድዩ ለጻፈው ውግዘት ምክንያት የሆነው ኢየሩሳሌም በጠፋችበት ጊዜ የፈጸሙት ይህ ግፍ ነበር። አብድዩ መጽሐፉን የጻፈው ይህ የኤዶማውያን የጭካኔ ድርጊት ገና ከአእምሮው ሳይጠፋ እንደነበር አያጠራጥርም። (አብ. 11, 14) ኤዶም ራሷ ኢየሩሳሌም ከጠፋች በኋላ አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በናቡከደናነፆር ተወርራ ስለተመዘበረች የአብድዩ መጽሐፍ የተጻፈው ይህ ከመሆኑ ቀደም ብሎ መሆን ይኖርበታል። ስለዚህ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ እንደተጻፈ ይታሰባል።
5 አብድዩ በኤዶም ላይ የተናገረው ትንቢት ሙሉ በሙሉ ተፈጽሟል! ትንቢቱ በስተ መጨረሻው ላይ እንዲህ ይላል:- “‘የዔሳው ቤት ገለባ ይሆናል፤ ያቃጥሉታል፤ ይበሉትማል፤ ከዔሳው ቤት የሚተርፍ፣ አይኖርም’ እግዚአብሔር ተናግሮአል።” (ቁጥር 18) ኤዶም የኖረው በሰይፍ ኃይል ነበር፣ በዚያው በሰይፍ ጠፍቷል፤ ዘሮቹም ድምጥማጣቸው ጠፍቷል። ስለዚህ የአብድዩ መጽሐፍ እውነተኛና ትክክለኛ መሆኑ ተረጋግጧል። አብድዩ የእውነተኛ ነቢይ መታወቂያ የሆኑት ማረጋገጫዎች በሙሉ አሉት:- ትንቢቱን የተናገረው በይሖዋ ስም ነው፣ የተናገረው ትንቢት ይሖዋን አስከብሯል እንዲሁም በታሪክ እንደተረጋገጠው ትንቢቱ በትክክል ተፈጽሟል። የስሙ ትርጉም “የይሖዋ አገልጋይ” መሆኑ ተገቢ ነው።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
10 ይሖዋ፣ በኤዶም ላይ የተነገረው ይህ የፍርድ መልእክት አለምንም ጥርጥር እንደሚፈጸም ሲያረጋግጥ ሌሎች ነቢያቱም ተመሳሳይ ትንቢት እንዲናገሩ አድርጓል። ከእነዚህ መካከል በኢዩኤል 3:19፣ አሞጽ 1:11, 12፣ ኢሳይያስ 34:5-7፣ ኤርምያስ 49:7-22፣ ሕዝቅኤል 25:12-14፣ 35:2-15 ላይ የሚገኙት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው። ቀደም ባሉት ዓመታት የተነገሩት ትንቢቶች ጥንት የተፈጸሙትን የጠላትነት ድርጊቶች የሚያመለክቱ ሲሆኑ በኋለኞቹ ዓመታት የተነገሩት ኤዶምን የሚያወግዙ ቃላት ደግሞ አብድዩ በጠቀሰውና ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን በወረሩ ጊዜ በፈጸሙት ይቅር ሊባል የማይችል ግፍ ምክንያት የተነገሩ እንደሆኑ ግልጽ ነው። ይህ በትንቢት የተነገረ ጥፋት በኤዶም ላይ የተፈጸመበትን ሁኔታ ብንመረምር በይሖዋ ትንቢት የመናገር ችሎታ ያለን እምነት ይጠናከራል። ከዚህም በላይ ይሖዋ የተናገረውን ዓላማውን የሚፈጽም አምላክ መሆኑን ሙሉ በሙሉ እንድንተማመን ያደርጋል።—ኢሳ. 46:9-11
11 አብድዩ በኤዶም ላይ የሚነሱትና የሚያሸንፉት ‘ወዳጆቹና ጓደኞቹ’ እንደሚሆኑ ተንብዮ ነበር። (አብ. 7) ኤዶም ከባቢሎን ጋር የመሠረተው ሰላም ለብዙ ጊዜ አልቆየም። በስድስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በንጉሥ ናቦኒደስ ይመሩ የነበሩት የባቢሎን ጭፍሮች ኤዶምን ወረሩ።b ያም ቢሆን ናቦኒደስ ምድሪቱን ከወረረ ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ እንኳን ኤዶማውያን እንደገና ለማንሰራራት ይመኙ ነበር። ሚልክያስ 1:4 ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ብሏል:- “ኤዶምያስ፣ ‘ብንደመሰስም እንኳ የፈረሰውን መልሰን እንሠራዋለን’ ይል ይሆናል። እግዚአብሔር ጸባኦት ግን እንዲህ ይላል፤ ‘እነርሱ ይሠሩ ይሆናል፤ እኔ ግን አፈርስባቸዋለሁ’።” ኤዶም እንደገና ለመቋቋም ብዙ ጥረት ቢያደርግም በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት መላው ምድር በናባቲያውያን ተይዞ ነበር። ኤዶማውያን ከገዛ አገራቸው ተገፍተው ወጥተው ኤዶምያስ ተብሎ መጠራት በጀመረው የይሁዳ ምድር ደቡባዊ ክፍል መኖር ጀመሩ። የሴይርን ተራራ ግን መልሰው መያዝ ፈጽሞ አልሆነላቸውም።
12 ጆሴፈስ እንደዘገበው በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ቀዳማዊ ጆን ሂርካነስ የተባለው የአይሁድ ንጉሥ የቀሩትን ኤዶማውያን ድል አድርጎ ከተቆጣጠራቸው በኋላ በግድ እንዲገረዙ አደረገ፤ ውሎ አድሮም በአይሁዳውያን ግዛት ተዋጡና በአይሁዳዊ ገዢ ይተዳደሩ ጀመር። ሮማውያን ኢየሩሳሌምን በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሲያጠፏት የኤዶማውያን ስም ከታሪክ ገጾች ፈጽሞ ተደመሰሰ።c አብድዩ “ለዘላለምም ትጠፋለህ . . . ከዔሳው ቤት የሚተርፍ፣ አይኖርም” በማለት የተናገረው ትንቢት በትክክል ተፈጽሞባቸዋል።—አብ. 10, 18
13 አይሁዳውያን ግን እንደ ኤዶማውያን ጠፍተው አልቀሩም። ከዚህ ይልቅ በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት በገዢው ዘሩባቤል አመራር ወደ አገራቸው ተመልሰውና ቤተ መቅደሳቸውንም በኢየሩሳሌም ሠርተው በገዛ አገራቸው መኖር ጀምረዋል።
14 ኩራትና ትዕቢት ውድቀት እንደሚያስከትል በግልጽ መመለከት ይቻላል! ራሳቸውን በኩራት ከፍ ከፍ የሚያደርጉና በአምላክ አገልጋዮች ላይ የሚደርሰውን መከራ ተመልክተው በጭካኔ የሚፈነድቁ ሁሉ በኤዶም ላይ የደረሰውን አይተው ይጠንቀቁ። እንደ አብድዩ ‘መንግሥት የይሖዋ መሆኑን’ አምነው ይቀበሉ። ከይሖዋና ከሕዝቦቹ ጋር የሚዋጉ ሁሉ ለዘላለም ይጠፋሉ፤ የይሖዋ ክብራማ መንግሥትና ዘላለማዊ ንግሥናው ግን ምንጊዜም ጸንቶ ይኖራል!—ቁጥር 21
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1፣ ገጽ 679
b ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 682
c ጂዊሽ አንቲክዊትስ XIII, 257, 258 (iX, 1); XV 253, 254 (Vii, 9)