በእምነታቸው ምሰሏቸው
ምሕረት ስለ ማሳየት ትምህርት አግኝቷል
ዮናስ ስለተሰጠው ተልእኮ ለማሰብ ብዙ ጊዜ ነበረው። ከ800 ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ ወደሚገኝ ቦታ ለመጓዝ ተዘጋጅቷል፤ ጉዞው አንድ ወር ምናልባትም ከዚያ በላይ ሊፈጅበት ይችላል። ዮናስ በመጀመሪያ፣ አቋራጭ ከሆነው መንገድና ረጅም ቢሆንም ለአደጋ ከማያጋልጠው መንገድ አንዱን መምረጥ ይኖርበታል። ከዚያም በርካታ ሸለቆዎችንና ተራራማ አካባቢዎችን አልፎ መጓዝ አለበት። ሰፊ የሆነውን የሶሪያ ምድረ በዳ ዳርቻ ተከትሎ መጓዝ፣ እንደ ታላቁ ኤፍራጥስ ያሉ ወንዞችን ማቋረጥ እንዲሁም በሶርያ፣ በሜሶጶጣሚያ እና በአሶር በሚገኙ ከተሞችና መንደሮች የማያውቃቸው ሰዎች ጋ ማደር ነበረበት። ቀናት እያለፉ ሲሄዱ ዮናስ በጣም ወደፈራው መድረሻው ማለትም ወደ ነነዌ ከተማ ይበልጥ እየቀረበ መጣ።
ዮናስ፣ የተሰጠውን ተልእኮ ሳይፈጽም በምንም ዓይነት ወደኋላ መመለስ እንደማይችል ያውቅ ነበር። ከዚህ በፊት እንዲህ ለማድረግ ሞክሯል። ይሖዋ ታላቅ ወደሆነችው ወደዚህች የአሦር ከተማ ሄዶ የፍርድ መልእክት እንዲናገር ዮናስን ለመጀመሪያ ጊዜ በላከው ወቅት ይህ ነቢይ ወደተቃራኒው አቅጣጫ በሚሄድ መርከብ ላይ ተሣፈረ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ባሕሩ በከባድ ማዕበል እንዲናወጥ አደረገ፤ ዮናስም በይሖዋ ላይ በማመጹ የተነሳ በመርከቡ ላይ ያሉት ሰዎች ሁሉ ሕይወት አደጋ ላይ እንደወደቀ ተገነዘበ። በመሆኑም የሰዎቹ ሕይወት እንዲተርፍ ሲል የመርከቡን ሠራተኞች ወደ ባሕሩ እንዲወረውሩት ነገራቸው። ሰዎቹ እያመነቱ ዮናስን ወደ ባሕሩ የጣሉት ሲሆን እሱም መሞቱ እንደማይቀር ተሰምቶት ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ አንድ ትልቅ ዓሣ ዮናስን እንዲውጠውና ከሦስት ቀናት በኋላ ምንም ጉዳት ሳያደርስበት ባሕሩ ዳርቻ ላይ እንዲተፋው ዝግጅት አደረገ። በዚህ ጊዜ ዮናስ በተከሰተው ሁኔታ በጣም ከመደነቁም በላይ ለመታዘዝ ይበልጥ ፈቃደኛ ሆኖ ነበር።a—ዮናስ ምዕራፍ 1, 2
ይሖዋ፣ ዮናስን በስተ ምሥራቅ ወደምትገኘው ወደ ነነዌ እንዲሄድ በድጋሚ ሲያዘው ነቢዩ አለምንም ማመንታት ረጅሙን ጉዞ ተያያዘው። (ዮናስ 3:1-3) ይሁን እንጂ ይሖዋ የሰጠው ተግሣጽ ነቢዩን ሙሉ በሙሉ ለውጥ እንዲያደርግ ረድቶት ይሆን? ለምሳሌ ያህል፣ ባሕር ውስጥ እንዳይሰምጥ በማድረግ፣ ታዛዥ ባይሆንም ሳይቀጣው በመቅረት እንዲሁም የተሰጠውን ተልእኮ እንዲወጣ ሌላ ዕድል በመስጠት ይሖዋ ለነቢዩ ምሕረት አሳይቶታል። ዮናስ ይህ ሁሉ ከተደረገለት በኋላ ለሌሎች ምሕረት ማሳየትን ተምሮ ይሆን? ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ለመማር ከሚከብዷቸው ነገሮች አንዱ ምሕረት ማሳየት ነው። ዮናስ ይህንን ባሕርይ ለማዳበር ካደረገው ትግል ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት።
ለፍርድ መልእክቱ አስገራሚ ምላሽ ሰጡ
ዮናስ ስለ ነነዌ ከይሖዋ የተለየ አመለካከት ነበረው። መጽሐፍ ቅዱስ “በዚህ ጊዜ ነነዌ [‘በአምላክ ዘንድ፣’ NW] ታላቅ ከተማ ነበረች” ይላል። (ዮናስ 3:3) ይሖዋ ነነዌን ሦስት ጊዜ ‘ታላቂቱ ከተማ’ በማለት እንደጠራት ዮናስ ጽፏል። (ዮናስ 1:2፤ 3:2፤ 4:11) ይህቺ ከተማ በይሖዋ ዘንድ ታላቅ የተባለችው ወይም ትልቅ ቦታ የሚሰጣት የሆነችው ለምን ነበር?
ነነዌ፣ ከጥፋት ውኃ በኋላ ናምሩድ ከቆረቆራቸው ከተሞች አንዷ በመሆኗ ረጅም ዘመን ያስቆጠረች ጥንታዊ ከተማ ነች። ነነዌ፣ እንቅስቃሴ የሚበዛባት እንዲሁም በውስጧ በርካታ ከተሞችን ያቀፈችና ሰፊ አካባቢ የምትሸፍን ትልቅ ከተማ መሆን አለባት፤ አንድ ሰው ከአንድ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ ለመሄድ ሦስት ቀን ይፈጅበታል። (ዘፍጥረት 10:11፤ ዮናስ 3:3) ነነዌ፣ ግርማ ሞገስ ያላቸው ግዙፍ ቤተ መቅደሶች፣ ረጃጅም ቅጥሮችና ሌሎች ሕንጻዎች ስለነበሯት በጣም አስደናቂ ከተማ ነበረች። ሆኖም ከተማዋ በይሖዋ ዘንድ ትልቅ ቦታ እንዲሰጣት ያደረጓት እነዚህ ነገሮች አይደሉም። ይሖዋ ትኩረት ያደረገው በሕዝቡ ላይ ነበር። በዚያን ጊዜ ከነበሩ ሌሎች ከተሞች አንጻር ነነዌ በጣም ብዙ ሕዝብ ነበራት። ነዋሪዎቿ እጅግ ክፉ የነበሩ ቢሆኑም ይሖዋ ያስብላቸው ነበር። ይሖዋ ለሁሉም ሰው ፍቅር ያለው ከመሆኑም ሌላ እያንዳንዱ ሰው ንስሐ መግባትና ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግን መማር እንደሚችል ይሰማዋል።
ዮናስ ረጅሙን ጉዞውን አጠናቅቆ ነነዌ ሲደርስ ከ120,000 በላይ የሆነው የከተማዋ ሕዝብ ብዛት ፍርሃቱን ሳያባብስበት አልቀረም።b መልእክቱን ለማሰማት የሚያስችለው ማዕከላዊ ቦታ ለማግኘት ሳይሆን አይቀርም ለአንድ ቀን ያህል በመጓዝ ሕዝብ ወደሚርመሰመስባት ወደዚህች ከተማ ይበልጥ ዘልቆ ገባ። ነቢዩ ለእነዚህ ሰዎች መልእክቱን የሚነግራቸው እንዴት ነው? የአሦራውያንን ቋንቋ ተምሮ ይሆን? ወይስ ቋንቋውን እንዲናገር ይሖዋ ተአምራዊ ችሎታ ሰጥቶት ይሆን? ምንም የምናውቀው ነገር የለም። ዮናስ የአፍ መፍቻ ቋንቋው በሆነው በዕብራይስጥ መልእክቱን ከተናገረ በኋላ አንድ ሰው ለነነዌ ነዋሪዎች እንዲተረጉምላቸው አድርጎ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ፣ “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትገለበጣለች” የሚለው ግልጽ መልእክቱ ለዮናስ ተወዳጅነት የሚያተርፍለት አልነበረም። (ዮናስ 3:4) ነቢዩ ይህንን አዋጅ ያለ ፍርሃት ደጋግሞ በመናገር ከፍተኛ ድፍረትና እምነት እንዳለው ያሳየ ሲሆን በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖችም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እነዚህ ባሕርያት ያስፈልጓቸዋል።
የነነዌ ሰዎች ለዮናስ መልእክት ጆሯቸውን ሰጡ። ዮናስ፣ ነዋሪዎቹ መልእክቱን ሲሰሙ ሊጠሉትና በቁጣ ሊነሱበት እንደሚችሉ ጠብቆ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። የሚገርመው ግን የሕዝቡ ምላሽ የተገላቢጦሽ ነበር። ሕዝቡ መልእክቱን አዳምጦ እርምጃ ወሰደ! መልእክቱ እንደ ሰደድ እሳት በፍጥነት ተሠራጨ። ብዙም ሳይቆይ ዮናስ የተናገረው የፍርድ መልእክት በመላው ከተማ ይወራ ጀመር። ዮናስ የጻፈው ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ጾምንም ዐወጁ፤ ሰዎቹም ሁሉ ከትልቁ እስከ ትንሹ ማቅ ለበሱ።” (ዮናስ 3:5) ሀብታም ድሃ፣ ብርቱ ደካማ፣ ወጣት አረጋዊ ሳይል ሁሉም ሰው ንስሐ ገባ። ሕዝቡ የወሰደው እርምጃ ብዙም ሳይቆይ ንጉሡ ጆሮ ደረሰ።
ንጉሡም ቢሆን አምላካዊ ፍርሃት አደረበት። ከዙፋኑ ወረደ፤ ልብሰ መንግሥቱንም አወለቀ፤ እንደ ሕዝቡ ማቅ ለብሶ “በዐመድ ላይ ተቀመጠ።” ንጉሡ “ከመሳፍንቱ” ጋር በመተባበር፣ ሕዝቡ የጀመረው ጾም በመንግሥት ደረጃ እንዲፈጸም የሚደነግግ አዋጅ አወጣ። ሕዝቡ ሁሉ፣ ሌላው ቀርቶ የቤት እንሳሳትም እንኳ ማቅ እንዲለብሱ አዘዘ።c ሕዝቡ በክፋታቸውና በዓመፃቸው በደለኞች መሆናቸውን በትሕትና አምኖ ተቀበለ። ከዚህም በላይ ንጉሡ ‘እኛ እንዳንጠፋ አምላክ ከጽኑ ቍጣው ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?’ በማለት እውነተኛው አምላክ ንስሐ መግባታቸውን ሲመለከት ሊራራላቸው እንደሚችል ያለውን ተስፋ ገለጸ።—ዮናስ 3:6-9
አንዳንድ ተቺዎች፣ የነነዌ ሰዎች እንዲህ በፍጥነት ልባቸው መቀየሩን መቀበል ይከብዳቸዋል። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን እንደሚገልጹት ከሆነ በአጉል እምነት በተተበተቡትና ስሜታዊ በሆኑት የጥንት ሕዝቦች ዘንድ እንዲህ ማድረግ የተለመደ ነገር ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስም እንኳ የነነዌ ሰዎች ንስሐ ስለ መግባታቸው ጠቅሷል። (ማቴዎስ 12:41) ኢየሱስ እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ በሰማይ ሆኖ ስለተመለከተ የተናገረው ነገር በትክክል የተፈጸመ ስለመሆኑ እርግጠኛ ነበር። (ዮሐንስ 8:57, 58) ታዲያ ይሖዋ፣ የነነዌ ሰዎች ንስሐ መግባታቸውን ሲያይ ምን አደረገ?
በአምላክ ምሕረትና በሰው ፍርድ መካከል ያለው ልዩነት
ከጊዜ በኋላ ዮናስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እግዚአብሔርም ምን እንዳደረጉና ከክፉ መንገዳቸውም እንዴት እንደ ተመለሱ ባየ ጊዜ ራራላቸው፤ በእነርሱም ላይ ሊያመጣ ያሰበውን ጥፋት አላደረገም።”—ዮናስ 3:10
ይህ ሲባል ታዲያ ይሖዋ፣ በነነዌ ሰዎች ላይ ያስተላለፈው ፍርድ የተሳሳተ እንደነበር ተሰምቶታል ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤ የማይሳሳት ታማኝ አምላክ . . . ነው” ይላል። (ዘዳግም 32:4) ይሖዋ ምሕረት ማድረጉ በነነዌ ሰዎች ላይ የተቆጣው የጽድቅ ቁጣ መቀዝቀዙን የሚያመለክት ነው። ሰዎቹ ያደረጉትን ለውጥ ሲመለከት፣ በወቅቱ ካሳዩት የንስሐ ዝንባሌ አንጻር በእነሱ ላይ ሊወስድ ያሰበው የቅጣት እርምጃ ተስማሚ እንደማይሆን ተሰማው። በዚያን ወቅት ይሖዋ ምሕረት ማሳየቱ የተገባ ነበር።
ብዙውን ጊዜ የሃይማኖት መሪዎች እንደሚያስተምሩት ይሖዋ ግትር፣ የማያዝንና ጨካኝ አምላክ አይደለም። እንዲያውም ምክንያታዊና ከሁኔታዎች ጋር የሚስማማ እርምጃ የሚወስድ መሐሪ አምላክ ነው። በክፉዎች ላይ የቅጣት እርምጃ ለመውሰድ ሲያስብ፣ መጀመሪያ በምድር ላይ ያሉ ወኪሎቹን በመላክ ማስጠንቀቂያ ያስነግራል፤ ይህንን የሚያደርገው ክፉዎች ልክ እንደ ነነዌ ሰዎች ንስሐ ገብተው አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ ስለሚፈልግ ነው። (ሕዝቅኤል 33:11) ይሖዋ ለነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ብሎታል፦ “አንድ ሕዝብ ወይም መንግሥት እንዲነቀል፣ እንዲፈርስና እንዲጠፋ በተናገርሁ ጊዜ፣ ያስጠነቀቅሁት ሕዝብ ከክፋቱ ቢመለስ፣ እኔ ላደርስበት ያሰብሁትን ክፉ ነገር እተዋለሁ።”—ኤርምያስ 18:7, 8
ታዲያ ዮናስ የተናገረው ትንቢት የተሳሳተ ነበር ማለት ነው? አይደለም፤ ትንቢቱ ሕዝቡን ስላስጠነቀቀ የታለመለትን ግብ መቷል። ማስጠንቀቂያው የተሰጠው የነነዌ ሰዎች ክፉ ድርጊት ይፈጽሙ ስለነበር ነው፤ በኋላ ግን ክፉ ሥራቸውን ትተው ንስሐ ገቡ። የነነዌ ሰዎች እንደገና ወደ ክፉ ሥራቸው ቢመለሱ አምላክ የፍርድ እርምጃ ይወስድባቸዋል። ከጊዜ በኋላ የተከሰተውም ይኸው ነው።—ሶፎንያስ 2:13-15
ዮናስ እሱ ባሰበው ጊዜ ከተማዋ አለመጥፋቷን ሲመለከት ምን ተሰማው? ዘገባው “ዮናስ ግን ፈጽሞ አልተደሰተም፤ ስለዚህም ተቈጣ” ይላል። (ዮናስ 4:1) ይባስ ብሎም ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ እያረመ እንዳለ የሚያስመስልበት ጸሎት አቀረበ! ዮናስ በአገሩ አርፎ ቢቀመጥ ይሻለው እንደነበር ተናገረ። ነቢዩ፣ ቀድሞውንም ቢሆን ይሖዋ ነነዌን እንደማያጠፋት ያውቅ እንደነበርና ወደ ተርሴስ የሸሸውም ለዚህ እንደሆነ ገለጸ። ከዚያም “ከመኖር መሞት ይሻለኛል” በማለት መሞት እንደሚፈልግ ተናገረ።—ዮናስ 4:2, 3
ዮናስን ያሳሰበው ምን ነበር? ዮናስ ምን ያስብ እንደነበር ሙሉ በሙሉ ማወቅ ባንችልም በነነዌ ሕዝብ ፊት የጥፋት መልእክት እንዳወጀ እናውቃለን። ሕዝቡም አምነውት ነበር። ሆኖም ከተማዪቱ ሳትጠፋ ቀረች። ዮናስ፣ ሕዝቡ እንዳያፌዝበትና ሐሰተኛ ነቢይ እንደሆነ አድርጎ እንዳይመለከተው ፈርቶ ይሆን? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ዮናስ፣ ሕዝቡ ንስሐ በመግባቱም ሆነ ይሖዋ ምሕረት በማሳየቱ አልተደሰተም። ከዚህ ይልቅ በሁኔታው እጅግ ከመመረሩም በላይ ክብሩ እንደተነካ ስለተሰማው ለራሱ ማዘን ጀመረ። ይሁን እንጂ መሐሪ የሆነው አምላክ፣ በዚህ ጊዜም ቢሆን ዮናስ ያሉትን መልካም ባሕርያት እንደተመለከተ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ይሖዋ፣ ዮናስ አክብሮት የጎደለው ነገር በመናገሩ ከመቅጣት ይልቅ “በውኑ ልትቈጣ ይገባሃልን?” በማለት ልብ የሚኮረኩር ጥያቄ በደግነት አቀረበለት። (ዮናስ 4:4) ዮናስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቶ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ነገር የለም።
ይሖዋ ዮናስን ለማስተማር ምን አደረገ?
በተፈጸሙት ሁኔታዎች የተከፋው ነቢይ ነነዌን ለቅቆ ወጣ፤ ከዚያም ወደ አገሩ ከመሄድ ይልቅ ከተማዋን ለማየት ወደሚያስችለው በስተ ምሥራቅ ወደሚገኝ ተራራማ ሥፍራ ሄደ። በዚያም ዳስ ሠርቶ በመቀመጥ በነነዌ ላይ የሚደርሰውን ለማየት መጠባበቅ ጀመረ። አሁንም ከተማዪቱ እንደምትጠፋ ተስፋ አድርጎ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ምሕረት ማሳየት የተሳነውን ዮናስን ይህን ባሕርይ እንዲያዳብር የሚያስተምረው እንዴት ይሆን?
ይሖዋ አንድ የቅል ተክል በአንድ ጀምበር እንዲበቅል አደረገ። ዮናስ ማለዳ ላይ ሲነሳ ሰፋፊ ቅጠሎች ያሉት ይህ ተክል እሱ ከሠራት አነስተኛ ዳስ የበለጠ ጥላ እንደሚሰጠው ተመለከተ። በዚህ ጊዜ በጣም ተደሰተ። ዮናስ ቅሉ ተአምራዊ በሆነ መንገድ መብቀሉ አምላክ እንደባረከውና እንደተደሰተበት የሚያሳይ ምልክት እንደሆነ ስለተሰማው ሳይሆን አይቀርም “ስለ ቅሉ እጅግ ደስ አለው።” ሆኖም ይሖዋ ይህን ያደረገው ለዮናስ ጥላ ለመስጠትና ቁጣውን ለማብረድ ብቻ አይደለም። የዮናስን ልብ የሚነካ ትምህርት ለመስጠት ፈልጎ ነበር። በመሆኑም አምላክ፣ አንድ ትል ተክሉን እንዲበላና እንዲያደርቀው አደረገ። ከዚያም “የሚያቃጥል የምሥራቅ ነፋስ” አመጣ፤ በዚህ ጊዜ ዮናስ ከሙቀቱ የተነሳ “ተዝለፈለፈ።” አሁንም ዮናስ መንፈሱ የተደቆሰ ሲሆን መሞት እንደሚፈልግ ለአምላክ ተናገረ።—ዮናስ 4:6-8
በዚህ ጊዜ ይሖዋ፣ ቅሉ በመድረቁ “ልትቈጣ ይገባሃል?” በማለት ዮናስን ጠየቀው። ዮናስ ስሕተቱን አምኖ ከመቀበል ይልቅ “በእርግጥ እስከ ሞት ልቈጣ ይገባኛል” በማለት ድርጊቱ ትክክል እንደሆነ ተናገረ። አሁን ይሖዋ ለዮናስ ሊያስተምረው የፈለገውን ቁም ነገር ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ተፈጠረ።—ዮናስ 4:9
ነቢዩ ያልተከለውም ሆነ ያላሳደገው በአንድ ጀምበር የበቀለ ተክል በመድረቁ አዝኗል፤ ይሖዋ ለዮናስ ይህን ሐቅ ከገለጸለት በኋላ እንዲህ አለው፦ “ታዲያ እኔ ቀኝና ግራቸውን ለይተው መናገር የማይችሉ፣ ከአንድ መቶ ሃያ ሺህ በላይ ሰዎችና አያሌ እንስሶች ለሚኖሩባት ለታላቋ ከተማ ለነነዌ ማዘን አይገባኝምን?”—ዮናስ 4:10, 11d
ይሖዋ ለማስተማር የፈለገውን ቁም ነገር አስተዋልክ? ዮናስ ያንን ተክል ለመንከባከብ ያደረገው አንዳች ነገር የለም። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ፣ ለነነዌ ሰዎች ሕይወት ከመስጠት ባሻገር በምድር ላይ ለሚኖሩ ፍጥረታት በሙሉ እንደሚያደርገው ለእነሱም በሕይወት እንዲኖሩ የሚያስችላቸውን ነገር ሁሉ አሟልቶላቸዋል። ዮናስ 120,000 ለሚሆኑ ሰዎችና ለእንስሶቻቸው ሳያስብ ለአንዲት ተራ ተክል እንዴት ሊቆረቆር ይችላል? የራስ ወዳድነት ዝንባሌ እንዲያድርበት ስለፈቀደ አይደለም? ዮናስ ለተክሉ ያዘነው ለእሱ ጥቅም ስላስገኘለት ብቻ ነው። ነነዌ ባለመጥፋቷ የተበሳጨውም ቃሉ ባለመፈጸሙ በሰው ፊት እንዳያፍር ስለፈራ በሌላ አነጋገር ራስ ወዳድ ስለነበረ ነው።
በእርግጥም ይህ ትልቅ ቁም ነገር ነው! አሁን የሚነሳው ጥያቄ፣ ‘ዮናስ ከዚህ ተሞክሮ ትምህርት አግኝቷል?’ የሚል ነው። በስሙ የተሰየመው መጽሐፍ የሚያበቃው ይሖዋ በጠየቀው ጥያቄ ነው። አንዳንድ ተቺዎች ዮናስ ለዚህ ጥያቄ ፈጽሞ መልስ እንዳልሰጠ ይናገሩ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን መልሱ ራሱ መጽሐፉ ነው። በዮናስ ስም የተሰየመው መጽሐፍ ጸሐፊ፣ ራሱ ዮናስ እንደሆነ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። ይህ ነቢይ አገሩ ሆኖ ይህንን ዘገባ ሲጽፍ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። አስተዋይና ትሑት የሆነ አንድ አረጋዊ ከዚህ ቀደም የሠራውን ስህተት፣ ዓመፀኝነቱን እና ምሕረት ለማሳየት እምቢተኛ የነበረ መሆኑን እያሰበ በጸጸት ጭንቅላቱን ሲነቀንቅ መመልከት ትችላለህ። ዮናስ፣ ይሖዋ ከሰጠው ጥበብ ያዘለ ትምህርት እንደተጠቀመ ግልጽ ነው። ምሕረት ማሳየትን ተምሯል። እኛስ?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በጥር 1, 2009 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “በእምነታቸው ምሰሏቸው—ከሠራው ስህተት ተምሯል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b በዮናስ ዘመን የእስራኤል ዋና ከተማ የነበረችው ሰማርያ ከ20,000 እስከ 30,000 የሚጠጋ ሕዝብ ይኖርባት እንደነበር ይገመታል። የነነዌ ሕዝብ ደግሞ ከዚህ በአራት እጥፍ ገደማ ይበልጣል። ነነዌ በብልጽግናዋ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰችበት ወቅት በዓለም ላይ ትልቋ ከተማ የነበረች ይመስላል።
c ንጉሡ የወሰደው እንዲህ ያለው እርምጃ ያልተለመደ ነገር ሊመስል ቢችልም ከዚያ በፊት ተደርጎ የማያውቅ ነገር አይደለም። ግሪካዊው የታሪክ ምሑር ሄሮዶተስ፣ የጥንቶቹ ፋርሳውያን አንድ ተወዳጅ ጄኔራል በሞተ ጊዜ በሐዘን ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከብቶቻቸውም እንዲካፈሉ እንዳደረጉ ገልጿል።
d አምላክ የነነዌ ሰዎች ቀኝና ግራቸውን ለይተው መናገር እንደማይችሉ ሲገልጽ መለኮታዊ መሥፈርቶችን እንደማያውቁ መናገሩ ነበር።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አምላክ፣ ክፉዎች ልክ እንደ ነነዌ ሰዎች ንስሐ ገብተው አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ ይፈልጋል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አምላክ ዮናስን ምሕረት ስለ ማሳየት ለማስተማር አንድን የቅል ተክል ተጠቅሟል