የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 32—ዮናስ
ጸሐፊው:- ዮናስ
ተጽፎ ያለቀው:- ከክ. ል. በፊት በ844 ገደማ
ዮናስ በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በባዕድ አገር እንዲያገለግል የተመደበ ሚስዮናዊ ነበር። ይህ ሰው ይሖዋ የሰጠውን ሥራ እንዴት ተመለከተው? ይህስ ምን አዲስ ተሞክሮ እንዲያገኝ አስችሎታል? በተመደበበት አገር ይኖሩ የነበሩት ሰዎች መልእክቱን ተቀብለውታል? የስብከት ሥራው ምን ያህል የተሳካ ነበር? አስደናቂ ዘገባ የያዘው የዮናስ መጽሐፍ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። የይሖዋ ምርጥ ሕዝቦች ከእርሱ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰው ወደ አረማውያን ጣዖት አምልኮ ዘወር ባሉበት ጊዜ ላይ የተጻፈው ይህ ትንቢታዊ ዘገባ የአምላክ ምህረት እንደ እስራኤል ላለ አንድ ሕዝብ ብቻ የተወሰነ አለመሆኑን ያሳያል። ከዚህም በላይ ፍጹም ባልሆኑት የሰው ልጆች ላይ ከሚታየው ምህረት የለሽነት እንዲሁም ትዕግሥትና እምነት የማጣት ዝንባሌ በተቃራኒ ታላቅ የሆነውን የይሖዋ ምህረትና ፍቅራዊ ደግነት ከፍ አድርጎ ይገልጻል።
2 ዮናስ (በዕብራይስጥ ዮህናህ) የሚለው ስም “ርግብ” የሚል ትርጉም አለው። ዮናስ የዛብሎን ዘሮች ርስት በሆነው በገሊላ አውራጃ፣ በጋትሔፌር ይኖር የነበረው የነቢዩ የአማቴ ልጅ ነው። በሁለተኛ ነገሥት 14:23-25 ላይ ኢዮርብዓም የተባለው የእስራኤል ንጉሥ ይሖዋ በነቢዩ ዮናስ በኩል በተናገረው ቃል መሠረት የግዛቱን ድንበር እንዳሰፋ እናነባለን። በዚህ መሠረት ዮናስ ትንቢት የተናገረው ዳግማዊ ኢዮርብዓም በእስራኤል ዙፋን ላይ በተቀመጠበት ዓመት ማለትም በ844 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ ይሆናል። ይህም ዋና ከተማዋ በነነዌ የነበረችው አሦር እስራኤልን መግዛት ከመጀመሯ ከበርካታ ዓመታት በፊት ማለት ነው።
3 መላው የዮናስ መጽሐፍ እውነተኛ ታሪክ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም። ‘የእምነታችን ፍጹም አድራጊ የሆነው ኢየሱስ’ ዮናስ በእርግጥ የነበረ ሰው መሆኑን ከማመልከቱም ሌላ በዮናስ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹ ሁለት ትንቢታዊ ክንውኖች ያላቸውን ትርጉም ገልጿል። በዚህ መንገድ የዮናስ መጽሐፍ እውነተኛ ትንቢት የያዘ መሆኑን አረጋግጧል። (ዕብ. 12:2፤ ማቴ. 12:39-41፤ 16:4፤ ሉቃስ 11:29-32) አይሁዳውያን ምን ጊዜም ቢሆን የዮናስን መጽሐፍ ከቅዱሳን መጻሕፍት አንዱ እንደሆነ የተቀበሉት ከመሆኑም በላይ እንደ ታሪክ መጽሐፍ አድርገው ይመለከቱታል። ዮናስ የራሱን ስህተቶችና ድክመቶች ሳይሸፋፍን በፍጹም ግልጽነትና በሐቀኝነት መግለጹ መጽሐፉ ትክክለኛ መሆኑን ያረጋግጣል።
4 ዮናስን ስለዋጠው “ትልቅ ዓሣ” ምን ለማለት ይቻላል? የዚህን ዓሣ ዝርያ በተመለከተ ብዙ ዓይነት የግምት ሐሳቦች ተሰጥተዋል። ስፐርም ዌል የተባለው ዓሣ ነባሪም ሆነ ትልቁ ነጭ ሻርክ አንድን ሰው ሙሉ በሙሉ መዋጥ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናገኘው ዘገባ “እግዚአብሔር ግን ዮናስን የሚውጥ ትልቅ ዓሣ አዘጋጀ” የሚል ብቻ ነው። (ዮናስ 1:17) የዓሣው ዓይነት ተለይቶ አልተገለጸም። ስፐርም ዌልም ይሁን ወይም ትልቅ ነጭ ሻርክ አሊያም ሌላ በውል ያልተገለጸ የባሕር ፍጡር ማወቅ አይቻልም።a በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው መሠረት “ትልቅ ዓሣ” መሆኑን ማወቃችን ብቻ በቂ ነው።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
9 ዮናስ የወሰደው እርምጃና ድርጊቱ ያስከተለው ውጤት ለእኛ ማስጠንቀቂያ ሊሆነን ይገባል። አምላክ እንደሚረዳው ተማምኖ የተሰጠውን ሥራ መጀመር ሲገባው ይሖዋ ከሰጠው ሥራ ሸሽቷል። (ዮናስ 1:3፤ ሉቃስ 9:62፤ ምሳሌ 14:26፤ ኢሳ. 6:8) ወዳልተላከበት አቅጣጫ መጓዝ በጀመረ ጊዜ ‘የሰማይን አምላክ ይሖዋን’ እንደሚያመልክ ለመርከበኞቹ በግልጽ ሳይናገር በመቅረቱ አፍራሽ ዝንባሌ አሳይቷል። ድፍረት ጎድሎት ነበር። (ዮናስ 1:7-9፤ ኤፌ. 6:19, 20) ዮናስ ስለ ራሱ ክብር ብቻ ማሰቡ፣ ይሖዋ ለነነዌ ያሳየው ምህረት እርሱን እንዳዋረደው እንዲሰማው አድርጎታል። ይሖዋ ከመጀመሪያውም ቢሆን ውጤቱ እንዲህ እንደሚሆን ስለሚያውቅ እሱን ነቢይ አድርጎ መላኩ አስፈላጊ እንዳልነበረ በመግለጽ የወሰደው እርምጃ ትክክል እንደነበረ ለማሳየት ሞክሯል። ዮናስ እንደዚህ ያለ አክብሮት የጎደለውና የአጉረምራሚነት መንፈስ በማሳየቱ ተገስጿል፤ እኛም ዮናስ ካጋጠመው ሁኔታ በመማር በይሖዋ ምህረትና ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ ረገድ ስህተት ከመፈላለግ ዝንባሌ መራቅ ይኖርብናል።—ዮናስ 4:1-4, 7-9፤ ፊልጵ. 2:13, 14፤ 1 ቆሮ. 10:10
10 በዮናስ መጽሐፍ ውስጥ ከተገለጹት ነገሮች በሙሉ ጎልተው የሚታዩት ድንቅ የሆኑት የይሖዋ ባሕርያት ይኸውም ፍቅራዊ ደግነትና ምህረት ናቸው። ይሖዋ፣ የነነዌ ሰዎች ጥፋት እንደሚመጣባቸው ለማስጠንቀቅ ነቢዩን ወደ እነርሱ መላኩ ፍቅራዊ ደግነቱን ያሳያል፤ የነነዌ ሰዎች ንስሐ በገቡ ጊዜ ደግሞ ምህረቱን አሳይቷቸዋል። በዚህም የተነሳ ነነዌ በ632 ከክርስቶስ ልደት በፊት በሜዶናውያንና በባቢሎናውያን እስከጠፋችበት ጊዜ ድረስ ለ200 ዓመታት ያህል መቆየት ችላለች። ዮናስንም በማዕበል ከሚናወጠው ባሕር በማዳንና “ከጭንቀቱም ታድነው ዘንድ” [የ1954 ትርጉም] አንዲት ቅል በማዘጋጀት ለዮናስ ምህረት አሳይቶታል። ይሖዋ ለዮናስ ጥላ የሆነችለትን ቅል በማዘጋጀትና በኋላም እንድትጠፋ በማድረግ እርሱ እንደወደደና እንደ ፈቀደ ምህረትና ፍቅራዊ ደግነት እንደሚያሳይ ለዮናስ አሳውቆታል።—ዮናስ 1:2፤ 3:2-4, 10፤ 2:10፤ 4:6, 10, 11
11 ኢየሱስ በማቴዎስ 12:38-41 ላይ ለሃይማኖት መሪዎች “ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር” ሌላ ምልክት እንደማይሰጣቸው ነግሯቸዋል። ዮናስ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ‘በመቃብር ጥልቅ’ ከቆየ በኋላ ወደ ነነዌ ሄዶ በመስበኩ ለነነዌ ሰዎች “ምልክት” ሆኖላቸዋል። (ዮናስ 1:17፤ 2:2፤ 3:1-4) ኢየሱስም በተመሳሳይ ሦስት ቀን ያህል መቃብር ውስጥ ከቆየ በኋላ ተነስቷል። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህ መፈጸሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃ በማቅረብ ሲሰብኩ ኢየሱስ ለዚያ ትውልድ ምልክት ሆኗል። በኢየሱስ ላይ የተፈጸመውን ሁኔታ ከአይሁዳውያን የጊዜ አቆጣጠር ጋር አገናዝበን ስንመለከት ከሦስት ሙሉ ቀናት ያነሰው ይህ ጊዜ “ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት” ሊባል ይችላል።b
12 ኢየሱስ በዚሁ ጊዜ፣ የነነዌ ሰዎች ያሳዩትን የንስሐ መንፈስ አይሁዳውያን በአገልግሎቱ ወቅት እርሱን ለመቀበል አሻፈረኝ ከማለታቸውና ልበ ደንዳና ከመሆናቸው ጋር በማነጻጸር እንዲህ ብሏል:- “የነነዌ ሰዎችም በፍርድ ጊዜ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ የዮናስን ስብከት ሰምተው ንስሓ ገብተዋልና፤ እነሆ፣ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።” (በተጨማሪም ማቴዎስ 16:4 እና ሉቃስ 11:30, 32ን ተመልከት።) ኢየሱስ “ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? “ንስሓ ግቡ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና” ብሎ እንዲሰብክ ይሖዋ የላከው ከነቢያት ሁሉ የሚበልጥ ነቢይ እርሱ መሆኑን ማመልከቱ ነበር። (ማቴ. 4:17) ይሁን እንጂ በዚያ ትውልድ ከነበሩት አይሁዶች አብዛኞቹ ‘የዮናስን ምልክት’ ሳይቀበሉ ቀሩ። ዛሬስ? አብዛኞቹ ሰዎች የይሖዋን የማስጠንቀቂያ መልእክት ለመስማት የማይፈልጉ ቢሆንም በመላው ምድር የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች “የሰው ልጅ” የተባለው ኢየሱስ የሰበከውን የአምላክ መንግሥት ምሥራች የማዳመጥ ታላቅ አጋጣሚ ተዘርግቶላቸዋል። ንስሐ የገቡ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት በማዳመጣቸው እንደተባረኩ ሁሉ እነዚህ ሰዎችም ይሖዋ በምህረቱ ካደረገው የዘላለም ሕይወት ዝግጅት ሊካፈሉ ይችላሉ። በእርግጥም ‘ድነት ከይሖዋ ዘንድ ነው።’—ዮናስ 2:9
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 99-100
b ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 593