ጥናት 42
ግንዛቤ የሚያሰፋ
ንግግርህ የአድማጮችን ግንዛቤ የሚያሰፋ እንዲሆን ርዕሰ ጉዳዩ ጥሩ መሆኑ ብቻ በቂ አይደለም። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘እነዚህ አድማጮች ይህን ትምህርት መስማታቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ከንግግሩ ጠቃሚ ትምህርት እንደገበዩ እንዲሰማቸው ለማድረግ ምን ነጥቦችን መዘጋጀት ይኖርብኛል?’
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ ለሌላ ሰው እንዴት መመሥከር እንደሚቻል የሚያሳይ ክፍል እንድናቀርብ ከተመደብን አድማጫችን እንደሆነ ተደርጎ የሚቆጠረው ረዳት ሆኖ የተመደበልን ሰው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በጉባኤ ንግግር እየሰጠን ከሆነ አድማጮቻችን በዚያ የተገኙት ተሰብሳቢዎች ናቸው ማለት ነው።
አድማጮችህ ያላቸው እውቀት ምን ያህል ነው? ‘አድማጮች ስለ ርዕሰ ጉዳዩ ያላቸው እውቀት ምን ያህል ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ንግግርህን ማዳበር የምትጀምረው ይህንን መሠረት በማድረግ መሆን ይኖርበታል። ብዙ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ባሉበት ጉባኤ ንግግር ስትሰጥ አብዛኞቹ የሚያውቋቸውን መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁ መድገም ጥቅም የለውም። ከዚህ ይልቅ እነዚህን መሠረታዊ እውነቶች አዳብረህና አብራርተህ ለማቅረብ ጥረት አድርግ። እርግጥ ብዙ አዲስ ሰዎች በስብሰባው ላይ ከተገኙ የእነርሱንም ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል።
አድማጮችህ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ ያላቸውን እውቀት ግምት ውስጥ በማስገባት የምትናገርበትን ፍጥነት እንደ ሁኔታው አስተካክል። አብዛኞቹ አድማጮች የሚያውቋቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ስትጠቅስ ፈጠን ልትል ትችላለህ። ለአብዛኞቹ አድማጮች አዲስ የሆነ ሐሳብ በምትጠቅስበት ጊዜ ግን በደንብ እንዲጨብጡት ዝግ ብለህ ተናገር።
ግንዛቤ የሚያሰፋ ሲባል ምን ማለት ነው? አንድ ንግግር ግንዛቤ የሚያሰፋ እንዲሆን የግድ አዲስ ሐሳብ መጠቀስ አለበት ማለት አይደለም። አንዳንድ ተናጋሪዎች የሚያብራሩበት መንገድ ለመረዳት በጣም ቀላል ከመሆኑ የተነሣ ብዙዎቹ አድማጮች ቀደም ሲል የሚያውቁት እውነት እንኳ እንደዚያ ዕለት ግልጽ ሆኖላቸው እንደማያውቅ ይሰማቸዋል።
በአገልግሎት ላገኘኸው ሰው በመጨረሻው ዘመን ላይ እንደምንኖር ለማስረዳት የሰማኸውን አንድ ዜና መጥቀስ ብቻ በቂ አይሆንም። ይህ ሁኔታ ምን ትርጉም እንዳለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሰህ ልታስረዳው ይገባል። የሰውዬውን ግንዛቤ የምታሰፋው እንዲህ ካደረግህ ነው። ስለ ተፈጥሮ ሕግጋት፣ ስለ ዕፅዋት ወይም ስለ እንስሳት ሕይወት ብትጠቅስለት እንኳን ዓላማህ የማያውቃቸውን ሳይንሳዊ ግኝቶች በመንገር እርሱን ማስደመም ሊሆን አይገባም። ከዚህ ይልቅ ግብህ የተፈጥሮ ማስረጃዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር አያይዘህ በማቅረብ የሚወድደን ፈጣሪ መኖሩን ማስገንዘብ መሆን ይኖርበታል። ይህም ሰውዬው ስለ ጉዳዩ አዲስ ግንዛቤ እንዲያገኝ ይረዳዋል።
አድማጮች በተደጋጋሚ ጊዜ የሰሙትን ንግግር መልሶ ማቅረብ ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ይሁንና የተዋጣልህ አስተማሪ ለመሆን የሚያውቁትንም ትምህርት ቢሆን ሕያው አድርገህ ማቅረብን መማር ይኖርብሃል። ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
ምርምር ማድረግ አስፈላጊ ነው። የተለመዱትን ነጥቦች ብቻ ከመጥቀስ ይልቅ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ከገጽ 33 እስከ 38 ላይ የተዘረዘሩትን ጽሑፎች ተጠቅመህ ምርምር አድርግ። ምርምር ስታደርግ ዓላማህ ምን ሊሆን እንደሚገባ በእነዚህ ገጾች ላይ የተሰጠውንም ሐሳብ አትዘንጋ። በዚህ ወቅት ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር ተዛማጅነት ያለው ነገር ግን አድማጮች ብዙም የማያውቁት ታሪክ ታገኝ ይሆናል። ወይም ደግሞ በቅርቡ የሰማኸው አንድ ዜና ልታብራራው ያሰብከውን ነጥብ በምሳሌ ለማስረዳት የሚጠቅም ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ።
ትምህርቱን ስትዘጋጅ ምን? ለምን? መቼ? የት? ማን? እና እንዴት? የሚሉትን ጥያቄዎች እያነሳህ አእምሮህን ማመራመር ይኖርብሃል። ለምሳሌ ያህል እንዲህ እያልክ ልትጠይቅ ትችላለህ:- ይህ ነጥብ እውነት መሆኑን ማረጋገጥ የምችለው እንዴት ነው? አንዳንዶች ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዳይቀበሉ እንቅፋት የሚሆንባቸው የትኛው አስተሳሰብ ነው? ትምህርቱ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሰዎች በሕይወታቸው ለውጥ እንዲያደርጉ ሊረዳቸው የሚገባው እንዴት ነው? ይህን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ የሚያሳይ ምን ምሳሌ መጥቀስ እችላለሁ? ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስለ ይሖዋ ባሕርይ ምን ያስተምረናል? እንደ ትምህርቱ ይዘት እንዲህ እያልክ ራስህን ልትጠይቅ ትችላለህ:- ይህ የሆነው መቼ ነው? ዛሬ ትምህርቱ እኛን ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው? ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ ሳይቀር ከእነዚህ ጥያቄዎች አንዳንዶቹን በማንሳትና መልስ በመስጠት ትምህርቱን ሕያው አድርገህ ማቅረብ ትችል ይሆናል።
በንግግርህ ውስጥ አድማጮች የሚያውቋቸው ጥቅሶች ይኖሩ ይሆናል። እነዚህን ጥቅሶች ትምህርት ሰጪ አድርገህ ማቅረብ የምትችለው እንዴት ነው? እንዲሁ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ጥሩ አድርገህ ማብራራት ይኖርብሃል።
አድማጮች የሚያውቁትን ጥቅስ በምትጠቅስበት ጊዜ ከትምህርቱ ጭብጥ ጋር የሚያያዘውን የጥቅሱን ክፍል ነጥለህ በማውጣት የምታብራራ ከሆነ አቀራረብህ ይበልጥ ትምህርት ሰጪ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ሚክያስ 6:8ን እንደ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም እንዴት ልታብራራው እንደምትችል ልብ በል። “ፍትሕ” ምንድን ነው? እዚህ ላይ የተጠቀሰው ፍትሕ የማን ነው? ‘ፍትሕን በተግባር ማሳየት’ ወይም ‘ደግነትን መውደድ’ ምን ማለት እንደሆነ በምሳሌ ማስረዳት የምትችለው እንዴት ነው? ልክን ማወቅ ምን ማለት ነው? በዕድሜ ከገፋ አንድ ሰው ሁኔታ ጋር በተያያዘ እንዴት ልትጠቀምበት ትችላለህ? እርግጥ የምትሰጠው ማብራሪያ በንግግርህ ጭብጥና ዓላማ፣ በአድማጮችህ ሁኔታ እንዲሁም ባለህ ጊዜ ላይ የተመካ ነው።
የአንዳንዶቹን ቃላት ፍቺ መናገር ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በማቴዎስ 6:10 ላይ የተጠቀሰው “መንግሥት” የሚለው ቃል ትርጉም ምን እንደሆነ ብታብራራ አንዳንዶች አዲስ እውቀት ሊያገኙ ይችላሉ። ለረጅም ጊዜ የቆዩ ክርስቲያኖችም ቢሆኑ የቃሉን ፍቺ እንደገና ሲሰሙ የጥቅሱን ትርጉም ይበልጥ በትክክል ሊያስተውሉ ይችላሉ። ይህን ማድረጋችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የምንገነዘበው እንደ 2 ጴጥሮስ 1:5-8 ያሉትን ጥቅሶች አንብበን ለማብራራት ስንሞክር ነው። በዚህ ጥቅስ ውስጥ እንደ እምነት፣ በጎነት፣ እውቀት፣ ራስን መግዛት፣ ጽናት፣ እግዚአብሔርን መምሰል፣ የወንድማማች መዋደድና ፍቅር ያሉት የተለያዩ ነገሮች ተዘርዝረዋል። በጣም ተቀራራቢ ትርጉም ያላቸው ቃላት አንድ ላይ በሚጠቀሱበት ጊዜ ፍቺያቸውን መግለጽህ አንዱን ከሌላው ለመለየት ይረዳል። በምሳሌ 2:1-6 ላይ የተገለጹት እንደ ጥበብ፣ እውቀትና ማስተዋል ያሉት ቃላት ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆናሉ።
አንዳንድ ጊዜ ጥቅሱን ከጉዳዩ ጋር ማገናዘብ ብቻ የአድማጮችን ግንዛቤ ሊያሰፋ ይችላል። በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ዘፍጥረት 2:7 አዳም ሕያው ነፍስ እንደሆነ ሲገልጽ ሕዝቅኤል 18:4 ደግሞ ነፍስ እንደምትሞት ይናገራል። ብዙ ሰዎች ይህን እውነት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያስተውሉ ይገረማሉ። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ከሰዱቃውያን ጋር ሲነጋገር እነርሱ እናምንበታለን የሚሉትን ዘጸአት 3:6ን ጠቅሶ የሙታን ትንሣኤ እንዳለ ሲያስረዳቸው በጣም ተገርመዋል።—ሉቃስ 20:37, 38
አንዳንድ ጊዜ በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ፣ ጥቅሱ በተጻፈበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታ እንዲሁም የተናጋሪውን ወይም መልእክቱ የሚነገራቸውን ሰዎች ማንነት መግለጽ የአድማጮችን ግንዛቤ ሊያሰፋ ይችላል። ፈሪሳውያኑ በመዝሙር 110 ላይ ያለውን ሐሳብ በሚገባ ያውቁ ነበር። ያም ሆኖ ኢየሱስ በመጀመሪያው ቁጥር ላይ በሚገኝ አንድ አስፈላጊ ነጥብ ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓል። “ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው? ብሎ ጠየቃቸው። የዳዊት ልጅ ነው አሉት። እርሱም:- እንኪያስ ዳዊት:- ጌታ ጌታዬን:- ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፣ እንዴት ልጁ ይሆናል? አላቸው።” (ማቴ. 22:41-45) እንደ ኢየሱስ ጥቅሶችን ጥሩ አድርገህ ከጉዳዩ ጋር በማገናዘብ የምታስረዳ ከሆነ ሰዎች የአምላክን ቃል አስተውለው እንዲያነብቡ ልታነሳሳቸው ትችላለህ።
አንድ ተናጋሪ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈበትን ወይም ታሪኩ የተከናወነበትን ጊዜ ሲጠቅስ በወቅቱ የነበረውንም ሁኔታ አያይዞ መግለጽ ይኖርበታል። ይህም አድማጮች መጽሐፉ ወይም ክንውኑ ምን ያህል ጉልህ ድርሻ እንዳለው እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል።
የተለያዩ ነገሮችን እያነጻጸሩ ማቅረብ የምትናገረው ነገር ይበልጥ ግንዛቤ የሚያሰፋ እንዲሆን ይረዳሃል። አንድን ጉዳይ በተመለከተ አብዛኞቹ ሰዎች ያላቸውን አስተሳሰብ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚገልጸው ሐሳብ ጋር ልታነጻጽር ትችላለህ። ወይም ሁለት ተመሳሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ማወዳደር ትችላለህ። በመካከላቸው ልዩነት አለ? ለምን? ልዩነቱን በማወዳደር ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? ይህን ማድረግህ አድማጮችህ ስለ ጉዳዩ ያላቸው ግንዛቤ እንዲሰፋ ሊያደርግ ይችላል።
ስለ አንዳንድ የክርስቲያናዊ አገልግሎት ዘርፎች ንግግር እንድትሰጥ ከተመደብህ መግቢያህ ላይ ጠቅለል ያለ መግለጫ መስጠትህ ንግግርህን ይበልጥ ትርጉም ያለው ያደርግልሃል። ምን መደረግ እንዳለበት፣ ለምን እንዳስፈለገና ከክርስቲያናዊ ግባችን ጋር እንዴት እንደሚዛመድ አብራራ። ከዚያም ሥራው የት፣ መቼና እንዴት እንደሚከናወን ግለጽ።
ንግግሩ ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ የሚያብራራ ከሆነስ? (1 ቆሮ. 2:10) ስትጀምር የርዕሰ ጉዳዩን ቁልፍ ነጥቦች ከጠቀስህ ዝርዝር ነጥቦቹን ለመረዳት ቀላል ይሆናል። ትምህርቱን ባጭሩ በመከለስ ከደመደምክ ደግሞ አድማጮችህ ጠቃሚ ትምህርት እንደገበዩ ይሰማቸዋል።
ክርስቲያናዊ አኗኗርን የሚመለከት ምክር። ትምህርቱን እንዴት በሕይወታቸው ሊሠሩበት እንደሚችሉ ካስገነዘብካቸው አድማጮችህ ይበልጥ ይጠቀማሉ። በንግግርህ ውስጥ ያሉትን ጥቅሶች ስትመረምር ‘ይህ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ እስከ ዘመናችን ድረስ የቆየው ለምንድን ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። (ሮሜ 15:4፤ 1 ቆሮ. 10:11) አድማጮችህ በሕይወታቸው የሚገጥሟቸውን ችግሮች አስብ። ቀጥሎ እነዚህን ችግሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ምክርና መሠረታዊ ሥርዓት አንጻር ለመመርመር ሞክር። ከዚያም ንግግሩን ስታቀርብ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ተንተርሰህ ምክሮቹና መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ችግሮቹን በጥበብ ለመወጣት የሚረዱት እንዴት እንደሆነ ግለጽ። መስተካከል ያለበትን ችግር ለይተህ መጥቀስ እንጂ በደፈናው መናገር የለብህም።
መጀመሪያ ላይ እስካሁን ከተዘረዘሩት ነጥቦች መካከል አንዱን ወይም ሁለቱን ብቻ ተግባራዊ ማድረግህ በቂ ነው። ልምድ እያገኘህ ስትሄድ ግን የምትሠራባቸውን ነጥቦች ብዛት ልትጨምር ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህን ከቀጠልህ አድማጮች ከምታቀርባቸው ንግግሮች ጠቃሚ ትምህርት እንደሚያገኙ ስለሚሰማቸው ንግግርህን ለመስማት ይጓጓሉ።