እስኩቴስ—እንቆቅልሽ የሆነ ጥንታዊ ሕዝብ
ኮሮጆዎቻቸውን በምርኮ ያጨቁ ፈረሰኛ ዘላኖች በአቧራ ውስጥ እየጋለቡ በዩራሲያን አውላላ ሜዳ ላይ ደረሱ። እንቆቅልሽ የሆኑት እነዚህ ሰዎች ከ700 ገደማ አንስቶ እስከ 300 ከዘአበ ድረስ አካባቢውን በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው ቆዩ። ከዚያም በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ አንድ አሻራ ትተው ከምድረ ገጽ ጠፉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንኳን ስለ እነርሱ ተጠቅሷል። እነርሱም እስኩቴሶች ናቸው።
ለብዙ መቶ ዓመታት በምሥራቅ አውሮፓ ከካርፓቲያን ተራራዎች አንስቶ በአሁኑ ጊዜ ደቡብ ምሥራቅ ሩሲያ እስከሚባለው አካባቢ ድረስ ያለውን የሣር ምድር ዘላኖችና የዱር ፈረሶች መንጋ ይፈነጩበት ነበር። በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የቻይና ንጉሠ ነገሥት ሹዋን የሰነዘረው ወታደራዊ ጥቃት ፍልሰት አስከተለ። እስኩቴሶች ወደ ምዕራብ አቅጣጫ በማቅናት ካውካሰስንና የጥቁር ባሕርን ሰሜናዊ አካባቢ ይቆጣጠሩ የነበሩትን ሱሜራውያን በመውጋት ከአካባቢው አፈናቀሏቸው።
እስኩቴሶች ሃብት አማልሏቸው የአሦር ዋና ከተማ የነበረችውን ነነዌን በዘበዙ። ከጊዜ በኋላ ምድያምን፣ ባቢሎንንና ሌሎች ብሔራትን ለመውጋት ከአሦር ጋር ግንባር ፈጠሩ። ሰሜናዊው የግብፅ ግዛትም ቢሆን ከጥቃታቸው አላመለጠም። በሰሜን ምሥራቅ እስራኤል የምትገኘው የቤትሳን ከተማ ከጊዜ በኋላ እስቶፖሊስ ተብላ መጠራቷ በእስኩቴሶች እጅ የወደቀችበት ጊዜ እንደነበረ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።—1 ሳሙኤል 31:11, 12
ከጊዜ በኋላ እስኩቴሶች በዛሬዎቹ ሩማንያ፣ ሞልዶቫ፣ ዩክሬይን እና ደቡባዊ ሩሲያ በሚገኙ ሜዳማ አካባቢዎች ላይ መኖር ጀመሩ። እዚያም በግሪካውያንና እህል አምራች በሆኑት በዛሬዎቹ ዩክሬናውያንና ደቡብ ሩሲያውያን መካከል ሆነው በሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ የናጠጡ ሃብታሞች እስከመሆን ደርሰው ነበር። እስኩቴሶች በእህል፣ በማር፣ በእንስሳት ቆዳና በቀንድ ከብቶች የግሪክ ወይን፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ የጦር መሣሪያና የሥነ ጥበብ ሥራዎችን ይለውጣሉ። በዚህ መንገድ ይህ ነው የማይባል ሃብት ለማካበት ቻሉ።
ድንቅ ፈረሰኞች
በተንጣለለ ሜዳ ላይ ለሚኖሩት ለእነዚህ ጦረኞች ፈረስ ማለት በበረሃ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ለግመል ከነበራቸው አመለካከት ጋር የሚመሳሰል ነው። እስኩቴሶች ድንቅ ፈረሰኞች ሲሆኑ ኮርቻና እርካብ በመጠቀም ረገድ ከቀዳሚዎቹ የሚደመሩ ናቸው። እስኩቴሶች የፈረስ ሥጋ ይበላሉ፤ እንዲሁም የፈረስ ወተት ይጠጣሉ። በተጨማሪም ፈረሶችን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር። አንድ የእስኩቴስ ጦረኛ ሲሞት ፈረሱ ይገደልና ከነሙሉ እቃውና ጌጡ በከፍተኛ የቀብር ሥነ ሥርዓት ይቀበራል።
ታሪክ ጸሐፊው ሄሮዶቱስ እንደገለጸው እስኩቴሶች የገደሏቸውን ሰዎች ራስ ቅል እንደ ኩባያ መጠቀምን ጨምሮ ሌሎች ዘግናኝ ልማዶች ነበሯቸው። ጠላቶቻቸውን በድንገት ይወርሩና በጎራዴ፣ በቆመጥ፣ በጦርና ሥጋን እንዲተለትል ተደርጎ በተዘጋጀ ጫፈ ቆልማማ ቀስት ይደመስሱ ነበር።
ለዘላለማዊ ሕይወት የተደራጁ መቃብሮች
እስኩቴሶች በጥንቆላና በሙታን መናፍስት የሚያምኑ ሲሆን እሳትንና እንስት አምላክን ያመልኩ ነበር። (ዘዳግም 18:10-12) መቃብሮችን የሙታን ማደሪያ ቦታዎች እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ። ባሪያዎችና እንስሳት የሞተውን ጌታቸውን እንዲያገለግሉ ሲባል መሥዋዕት ይደረጉ ነበር። ሃብትና የቤት ውስጥ አገልጋዮች ከአለቆቻቸው ጋር “ወደሚቀጥለው ዓለም” ይሄዳሉ ተብሎ ይታመናል። በአንድ ንጉሣዊ መቃብር ውስጥ ተነስተው ሥራቸውን መቀጠል ይችሉ ዘንድ እግሮቻቸውን ወደ ጌታቸው ዘርግተው የተቀበሩ አምስት ወንድ አገልጋዮች ተገኝተዋል።
ገዥዎች ሲሞቱ ከበርካታ ስጦታዎች ጋር የሚቀበሩ ሲሆን እስኩቴሶች ሐዘናቸውን ለመግለጽ ደማቸውን ያዘራሉ እንዲሁም ፀጉራቸውን ይላጫሉ። ሄሮዶቱስ “ጆሯቸውን ይቆርጣሉ፣ ራሳቸውን ይላጫሉ፣ ክንዳቸውን ዙሪያውን ይተለተላሉ፣ ግንባራቸውንና አፍንጫቸውን ይቧጭራሉ እንዲሁም ግራ እጃቸውን በቀስት ይበሳሉ” በማለት ጽፏል። ከዚህ በተቃራኒ በዚያው ዘመን ይኖሩ የነበሩ እስራኤላውያን ይመሩበት የነበረው የአምላክ ሕግ “ስለ ሞተውም ሥጋችሁን አትንጩ፣ ገላችሁንም አትንቀሱት” በማለት አዝዟቸዋል።—ዘሌዋውያን 19:28
እስኩቴሶች በሺህ የሚቆጠሩ ኩርጋኖችን (የመቃብር ጉብታዎችን) ትተው አልፈዋል። በእነዚህ መቃብሮች ውስጥ የተገኙት ብዙ ቁሳ ቁሶች የአንድን እስኩቴስ የዕለት ተዕለት ሕይወት በግልጽ ያሳያሉ። ታላቁ ፒተር የተባለ የሩሲያ ዛር በ1715 እነዚህን እቃዎች ማሰባሰብ ጀምሮ የነበረ ሲሆን እነዚህ አንጸባራቂ እቃዎች በአሁኑ ጊዜ በሩሲያና በዩክሬይን ሙዚየሞች ውስጥ ይገኛሉ። ይህ “የእንስሳት ሥነ ጥበብ” ፈረሶች፣ ንስሮች፣ ጭልፊቶች፣ ድመቶች፣ አነሮች፣ ኀየሎች (elk)፣ አእዋፍ መሰልና አንበሳ መሰል ፍጥረታት (ክንፍ ያለው ወይም የሌለው የእንስሳ አካል ላይ የሌላ እንስሳ ራስ እንዲኖረው ተደርጎ የተሣለ አፈ ታሪካዊ ፍጥረት) ይገኙበታል።
እስኩቴሶች እና መጽሐፍ ቅዱስ
መጽሐፍ ቅዱስ እስኩቴሶችን የሚጠቅሰው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ቆላስይስ 3:11 “በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፣ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፣ በሁሉም ነው” ይላል። ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን ቃላት በጻፈበት ወቅት “እስኩቴስ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል አንድን ብሔር ሳይሆን በጭካኔያቸው የታወቁ ሰዎችን ያመለክት ነበር። ጳውሎስ እንደነዚህ ያሉ ግለሰቦች እንኳ በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል እርዳታ አምላካዊ ባሕርያትን መልበስ እንደሚችሉ ጎላ አድርጎ መግለጹ ነበር።—ቆላስይስ 3:9, 10
አንዳንድ አርኪኦሎጂስቶች በኤርምያስ 51:27 ላይ የሚገኘው አስከናዝ የሚለው ስም እስኩቴሶችን ለማመልከት ከሚሠራበት አሽጉዛይ ከሚባለው የአሦራውያን ስም ጋር ይመሳሰላል የሚል እምነት አላቸው። የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፉ ጽላቶች በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እነዚህ ሕዝቦችና ማናዮች በአሦር ላይ ለማመፅ ኅብረት ፈጥረው እንደነበር ይጠቅሳሉ። ኤርምያስ ትንቢት መናገር ከመጀመሩ ትንሽ ቀደም ብሎ እስኩቴሶች ወደ ግብፅ ሲሄዱና ሲመለሱ ምንም ጉዳት ሳያደርሱ ይሁዳን አቋርጠው አልፈዋል። ስለሆነም ኤርምያስ ከሰሜን አቅጣጫ በይሁዳ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት እንደሚኖር ትንቢት ሲናገር የሰሙ ብዙ ሰዎች ፍጻሜውን የሚያገኝ ስለመሆኑ ተጠራጥረው ሊሆን ይችላል።—ኤርምያስ 1:13-15
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን በኤርምያስ 50:42 ላይ የሚገኘው “ቀስትንና ጦርን ይይዛሉ፤ ጨካኞች ናቸው ምሕረትም አያደርጉም፤ ድምፃቸው እንደ ባሕር ይተምማል በፈረሶችም ላይ ይቀመጣሉ፤ የባቢሎን ሴት ልጅ ሆይ፣ ለሰልፍ እንደ ተዘጋጀ ሰው እያንዳንዳቸው በአንቺ ላይ ተሰለፉ” የሚለው ትንቢት እስኩቴሶችን ያመለክታል ብለው ያስባሉ። ሆኖም ይህ ጥቅስ በመጀመሪያ ደረጃ የሚያመለክተው በ539 ከዘአበ ባቢሎንን ድል ያደረጉትን ሜዶንን እና ፋርስን ነው።
በሕዝቅኤል ምዕራፍ 38 እና 39 ላይ የተጠቀሰው ‘የማጎግ ምድር’ የእስኩቴስን ጎሳዎች ያመለክታል የሚል ሐሳብ ተሰጥቷል። ይሁን እንጂ ‘የማጎግ ምድር’ ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው ነው። በሰማይ ከተደረገው ጦርነት በኋላ ሰይጣንና መላእክቱ የተጣሉበትን የምድር አካባቢ ያመለክታል።—ራእይ 12:7-17
ናሆም ስለ ነነዌ ውድቀት በተናገረው ትንቢት አፈጻጸም ረገድ እስኩቴሶች አስተዋጽኦ አድርገዋል። (ናሆም 1:1, 14) ከለዳውያን፣ እስኩቴሶችና ሜዶናውያን ነነዌን በ632 ከዘአበ በመበዝበዝ የአሦርን የንጉሠ ነገሥት አገዛዝ እንዲያከትም አድርገዋል።
እንቆቅልሽ የሆነው አጠፋፍ
እስኩቴሶች ጠፍተዋል፤ ይሁን እንጂ ምክንያቱ ምንድን ነው? የአንድ የዩክሬን አርኪኦሎጂስት ቡድን መሪ “እንደ እውነቱ ከሆነ ምን እንደደረሰባቸው አናውቅም” በማለት ተናግረዋል። አንዳንድ ምሁራን በነበራቸው ድሎት በመዘናጋታቸው በአንደኛውና በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ከእስያ በፈለሱ አዲስ ዘላኖች ይኸውም በሳርማታውያን ጠፍተዋል ብለው ያምናሉ።
ሌሎች ምሁራን በተለያዩ የእስኩቴስ ወገኖች መካከል ግጭት እንደተነሳና ይህም ለጥፋት እንደዳረጋቸው ያስባሉ። አሁንም ቢሆን በካውካሰስ በሚኖሩ ኦሴትያውያን መካከል ከጥፋት የተረፉ አንዳንድ እስኩቴሶች ይኖራሉ የሚሉም አልታጡም። ግራም ነፈሰ ቀኝ እንቆቅልሽ የሆነው ይህ ሕዝብ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ አንድ አሻራ ጥሎ አልፏል። ይኸውም የጭካኔ መገለጫ የሆነውን እስኩቴስ የሚል ስም ትተው አልፈዋል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
◻ ጥንት የነበረች ከተማ
• ዛሬ ያለች ከተማ
ዳኑብ
እስኩቴስ ← የፈለሱበት አቅጣጫ
• ኪየቭ
ድኒፕሮ
ድኒስቴር
ጥቁር ባሕር
ኦሴቲያ
የካውካሰስ ተራሮች
የካስፒያን ባሕር
አሦር ← ወረራ ያደረጉባቸው አቅጣጫዎች
◻ ነነዌ
ጤግሮስ
ሜዶን ← ወረራ ያደረጉባቸው አቅጣጫዎች
ሜሶጶጣሚያ
ባቢሎኒያ ← ወረራ ያደረጉባቸው አቅጣጫዎች
◻ ባቢሎን
ኤፍራጥስ
የፋርስ ግዛት
◻ ሱሳ
የፋርስ ባሕረ ሰላጤ
ጳለስጢና
• ቤትሳን (እስቶፖሊስ)
ግብፅ ← ወረራ ያደረጉባቸው አቅጣጫዎች
ናይል
ሜዲትራንያን ባሕር
ግሪክ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እስኩቴሶች ጦረኛ ሕዝብ ነበሩ
[ምንጭ]
The State Hermitage Museum, St. Petersburg
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እስኩቴሶች ሸቀጦቻቸውን በግሪክ የሥነ ጥበብ ሥራዎች በመለወጥ የናጠጡ ሃብታሞች ሆነው ነበር
[ምንጭ]
Courtesy of the Ukraine Historic Treasures Museum, Kiev