ይሖዋ አይዘገይም
“[ራእዩ ] ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም።”—ዕንባቆም 2:3
1. የይሖዋ ሕዝቦች ምን ቁርጥ አቋም ወስደዋል? ይህስ ምን እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል?
“በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ።” ይህ የአምላክ ነቢይ የነበረው የዕንባቆም ቁርጥ አቋም ነው። (ዕንባቆም 2:1) በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች ተመሳሳይ ቁርጥ አቋም ወስደዋል። በመሆኑም በመስከረም ወር 1922 ተደርጎ በነበረው አዲስ ምዕራፍ ከፋች ስብሰባ ላይ ለቀረበው “ይህ የቀናት ሁሉ ቀን ነው። እነሆ፣ ንጉሡ ነግሷል። እናንተ ደግሞ አዋጅ ነጋሪዎቹ ናችሁ። ስለዚህ ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ” ለሚለው ጥሪ ቅንዓት የተሞላበት ምላሽ ሰጥተዋል።
2. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ወደ ከፍተኛ እንቅስቃሴአቸው ሲመለሱ ምን ብለው መናገር ይችሉ ነበር?
2 ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ይሖዋ ታማኞቹን ቅቡዓን ቀሪዎች ወደ ከፍተኛ እንቅስቃሴ መልሶ ስለነበረ እንደ ዕንባቆም “በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ፣ በአምባ ላይም እወጣለሁ፤ የሚናገረኝንም . . . አውቅ ዘንድ እመለከታለሁ” በማለት እያንዳንዳቸው መናገር ይችሉ ነበር። “እቆማለሁ፣” “እጠብቃለሁ” የሚሉት የዕብራይስጥ ቃላት በብዙ ትንቢቶች ውስጥ ይገኛሉ።
“አይዘገይም”
3. ነቅተን መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው?
3 ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን ማስጠንቀቂያ በሚያሰሙበት ጊዜ ሁሉ ኢየሱስ ስለ ቀኑና ስለ ሰዓቱ የተናገረውን ታላቅ ትንቢት ሲያጠቃልል የተናገረውን ቃል ለመፈጸም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ንቁዎች መሆን ይገባቸዋል:- “እንግዲህ በማታ ቢሆን ወይም በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ወይም በማለዳ ቢሆን ባለቤቱ መቼ እንዲመጣ አታውቁምና ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ስለዚህ ትጉ [“ነቅታችሁ ጠብቁ፣” NW]። ለእናንተም የምነግራችሁን ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ [“ነቅታችሁ ጠብቁ፣” NW ]።” (ማርቆስ 13:35-37) ከኢየሱስ ቃላት ጋር በመስማማት ልክ እንደ ዕንባቆም ነቅተን መጠበቅ ይገባናል!
4. ዛሬ እኛ ያለንበት ሁኔታ በ628 ከዘአበ ዕንባቆም ከነበረበት ሁኔታ ጋር የሚነጻጸረው እንዴት ነው?
4 ዕንባቆም ትንቢቱን ጽፎ ያጠናቀቀው በ628 ከዘአበ ሳይሆን ስለማይቀር ትንቢቱ የተጻፈው ገና ባቢሎን ኃያል መንግሥት ከመሆኗ በፊት ነበር። ይሖዋ በከዳተኛይቱ ኢየሩሳሌም ላይ የሚያስፈጽመው ፍርድ ማስጠንቀቂያ መነገር ከጀመረ በርካታ ዓመታት አልፈዋል። ይሁን እንጂ ይህ ፍርድ መቼ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ የሚያመለክት ምንም ዓይነት ግልጽ ምልክት አልነበረም። ለጥፋቱ የቀረው ጊዜ 21 ዓመት ብቻ እንደሆነና ባቢሎን የይሖዋ ፍርድ አስፈጻሚ እንደምትሆን ማን ሊያምን ይችል ነበር? ዛሬም ቢሆን በተመሳሳይ ይህ ሥርዓት የሚያከትምበትን ‘ቀንና ሰዓት’ አናውቅም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና” በማለት አስጠንቅቋል።—ማቴዎስ 24:36, 44
5. በዕንባቆም 2:2, 3 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የአምላክ ቃል የሚያጽናና የሆነው ለምንድን ነው?
5 ይሖዋ ለዕንባቆም የሰጠው የሚከተለው ቀስቃሽ ተልዕኮ ምንኛ የተገባ ነበር! “አንባቢው ይፈጥን ዘንድ ራእዩን ጻፍ፣ በጽላትም ላይ ግለጠው። ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፣ ወደ ፍጻሜውም ይቸኩላል፣ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም።” (ዕንባቆም 2:2, 3) ዛሬ ክፋትና ዓመፅ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በሁሉም የምድር ክፍሎች ተስፋፍቶ ይገኛል። ይህም “ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን” በጣም ቅርብ መሆኑን ያመለክታል። (ኢዩኤል 2:31) ይሖዋ ራሱ “አይዘገይም” ሲል የሰጠው የማረጋገጫ ቃል በእርግጥም የሚያጽናና ነው።
6. ከመጪው የቅጣት ፍርድ በሕይወት ልንተርፍ የምንችለው እንዴት ነው?
6 ታዲያ ከመጪው የፍርድ ቀን በሕይወት ልንተርፍ የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል ያለውን ልዩነት በመግለጽ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። “እነሆ፣ ነፍሱ ኮርታለች፣ በውስጡም ቅን አይደለችም፤ ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል።” (ዕንባቆም 2:4) ኩሩና ስግብግብ ገዥዎች አንዲሁም ሕዝቦች የዘመናችንን የታሪክ ገጾች በሁለቱ የዓለም ጦርነቶችና በሌሎች የጎሣ ግጭቶች ባፈሰሷቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ንጹሐን ሰዎች ደም በክለዋል። ሰላም ወዳድ የሆኑት ቅቡዓን የአምላክ አገልጋዮች ግን ከእነዚህ የተለየ አቋም በመያዝ በታማኝነታቸው ጸንተዋል። “እውነትን የሚጠብቅ ጻድቅ ሕዝብ” የተባሉት እነርሱ ናቸው። ይህ ሕዝብ ከተባባሪዎቹ “ሌሎች በጎች” ጋር ሆኖ “ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም አምባ ነውና፣ ለዘላለም በእግዚአብሔር ታመኑ” የሚለውን ምክር ይከተላል።—ኢሳይያስ 26:2-4፤ ዮሐንስ 10:16
7. ጳውሎስ ዕንባቆም 2:4ን ከተጠቀመበት መንገድ ጋር በሚስማማ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
7 ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በሚጽፍበት ጊዜ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፣ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም፤ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፣ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም” ያለው ከዕንባቆም 2:4 ጠቅሶ ነው። (ዕብራውያን 10:36-38) አሁን እጃችንን የምናዝልበት ወይም ፍቅረ ንዋይና ተድላን ማሳደድ ባሰከረው የሰይጣን ዓለም የምንጠመድበት ጊዜ አይደለም። ታዲያ የቀረው ‘ጥቂት ጊዜ’ እስኪያልቅ ድረስ ምን ማድረግ ይኖርብናል? የይሖዋ ቅዱስ ብሔር ክፍል እንደመሆናችን መጠን እንደ ጳውሎስ ‘በፊታችን ያለውን ለመያዝ እየተዘረጋን’ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ግባችንን እንከታተል። (ፊልጵስዩስ 3:13, 14) እንደ ኢየሱስ ‘ከፊታችን ያለውን ደስታ እየተመለከትን መጽናት ይኖርብናል።’—ዕብራውያን 12:2
8. በዕንባቆም 2:5 ላይ የተገለጸው “ሰው” ማን ነው? ጥረቱ የማይሳካለትስ ለምንድን ነው?
8 ዕንባቆም 2:5 ከይሖዋ አገልጋዮች በተለየ መልኩ ‘ስስቱን እንደ ሲኦል ቢያሰፋም’ የፈለገው ግብ ላይ ሊደርስ ስላልቻለ “ሰው” ይገልጻል። ይህ ‘የማይጠግብ’ ሰው ማን ነው? እንደ ፋሽስት፣ ናዚ፣ ኮምኒስት ያሉትንም ሆነ ዲሞክራሲያዊ ናቸው የሚባሉትን የተለያዩ ፖለቲካዊ ኃይሎችን የሚወክለው ይህ “ሰው” በዛሬው ጊዜ በዕንባቆም ዘመን እንደነበረችው ባቢሎን በመስገብገብ ግዛቱን ለማስፋፋት ጦርነት ይገጥማል። በተጨማሪም ሲኦልን ወይም መቃብርን በንጹሐን ነፍሳት ይሞላል። ይሁን እንጂ ይህ በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያለ የተለያየ ወገኖችን የሚወክል “ሰው” በኩራትና በማን አለብኝነት የሰከረ ቢሆንም ‘አሕዛብን ሁሉ ወደ ራሱ ለመሰብሰብና ወገኖችንም ለማከማቸት’ የሚያደርገው ጥረት አይሳካለትም። የሰው ልጆችን አንድ ማድረግ የሚችለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ይህንንም በመሲሐዊ መንግሥቱ አማካኝነት ይፈጽማል።—ማቴዎስ 6:9, 10
ከአምስቱ ወዮታዎች የመጀመሪያው
9, 10. (ሀ) ቀጥሎ ይሖዋ በዕንባቆም በኩል ምን ተናገረ? (ለ) አላግባብ የሚገኝን ትርፍ በተመለከተ ዛሬ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
9 ይሖዋ በነቢዩ ዕንባቆም አማካኝነት ምድርን ለአምላክ ታማኝ አምላኪዎች ለማዘጋጀት መወሰድ የሚኖርባቸውን የፍርድ እርምጃዎች የሚያመለክቱ አምስት ተከታታይ ወዮታዎችን ማስታወቅ ይጀምራል። እነዚህ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ይሖዋ የተናገረውን ምሳሌ ይመስላሉ። በዕንባቆም 2:6 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “የእርሱ ያልሆነውን ወደ እርሱ ለሚሰበስብ መያዣውንም ለራሱ የሚያበዛ ወዮለት! እስከ መቼ ነው?”
10 እዚህ ላይ አጽዕኖት የተሰጠው አለአግባብ የሚገኝ ትርፍ ነው። በዙሪያችን ባለው ዓለም ሀብታሞች ይበልጥ እየከበሩ ሲሄዱ ድሆች ግን ይበልጥ እየደኸዩ ይሄዳሉ። ዕፅ አዘዋዋሪዎችና አጭበርባሪ ነጋዴዎች ሀብታቸውን እያደለቡ ሲሄዱ በርካታ ተራ ሰዎች ግን በረሐብ ያልቃሉ። ከዓለም ሕዝቦች መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑት በድህነት ኑሮ እንደሚማቅቁ ይነገራል። በብዙዎቹ አገሮች ያለው የኑሮ ሁኔታ እጅግ የሚዘገንን ነው። በምድር ላይ ጽድቅ እንዲሰፍን የሚናፍቁ ሰዎች ሁሉ እንዲህ ያለው የኑሮ መበላለጥ የሚቀጥለው “እስከ መቼ ነው?” ብለው ይጠይቃሉ! ይሁንና ፍጻሜው በጣም ቅርብ ነው! በእርግጥም ራእዩ “አይዘገይም።”
11. ዕንባቆም የሰውን ደም ስለማፍሰስ ምን ይላል? ዛሬ በምድር ላይ ብዙ የደም ዕዳ አለ የምንለው ለምንድን ነው?
11 ነቢዩ ለኃጢአተኛው እንዲህ ይላል:- “የሰውን ደም ስላፈሰስህ፣ በምድሪቱና በከተማይቱም በእርስዋም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፣ አንተ ብዙዎችን አሕዛብን በዝብዘሃልና ከአሕዛብ የቀሩት ሁሉ ይበዘብዙሃል።” (ዕንባቆም 2:8) በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የደም አፍሳሽነት ወንጀል በእጅጉ ተስፋፍቶ ይገኛል! ኢየሱስ በግልጽ እንደተናገረው “ሰይፍ የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ።” (ማቴዎስ 26:52) በ20ኛው መቶ ዘመን ብቻ ደም አፍሳሽ ብሔራትና ጎሣዎች ከአንድ መቶ ሚልዮን ለሚበልጡ ሰዎች መሞት ምክንያት ሆነዋል። ይህን የሚያክል የደም ጎርፍ በማፍሰስ ለተካፈሉ ወገኖች ወዮላቸው!
ሁለተኛው ወዮታ
12. ዕንባቆም የመዘገበው ሁለተኛው ወዮታ ምንድን ነው? አላግባብ የተገኘ ብልጽግና ከንቱ መሆኑን እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን?
12 በዕንባቆም 2:9-11 ላይ የተመዘገበው ሁለተኛ ወዮታ የሚወርደው “ከክፉ እንዲድን ጎጆውን በከፍታ ላይ ያደርግ ዘንድ ለቤቱ ክፉ ትርፍን” በሚሰበስብ ላይ ነው። መዝሙራዊው ግልጽ እንዳደረገው አለአግባብ የሚገኝ ትርፍ ምንም እርባና አይኖረውም። “የሰው ባለጠግነት የቤቱም ክብር በበዛ ጊዜ አትፍራ፣ በሞተ ጊዜ ከእርሱ ጋር ምንም አይወስድምና፣ ክብሩም ከእርሱ በኋላ አይወርድምና።” (መዝሙር 49:16, 17) ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠው ጥበብ ያለበት ምክርም ልብ ሊባል የሚገባው ነው። “በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው።”—1 ጢሞቴዎስ 6:17
13. የአምላክን ማስጠንቀቂያ ማሰማታችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?
13 በዚህ በእኛ ዘመን የአምላክ የፍርድ መልእክት መሰማቱ ምንኛ አስፈላጊ ነው! ሕዝቡ ኢየሱስን ‘በይሖዋ ስም የመጣ ንጉሥ’ ብሎ ማወደሱን ፈሪሳውያን በተቃወሙ ጊዜ ኢየሱስ “እላችኋለሁ፣ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 19:38-40) በተመሳሳይ የአምላክ ሕዝቦች በዚህ ዓለም የሚታየውን ክፋት ሳያጋልጡ ቢቀሩ “ድንጋይም ከግንብ ውስጥ ይጮሃል።” (ዕንባቆም 2:11) እንግዲያውስ የአምላክን ማስጠንቀቂያ ማሰማታችንን በድፍረት እንቀጥል!
ሦስተኛው ወዮታና የደም ባለ ዕዳነት
14. የዓለም ሃይማኖቶች ለየትኛው ደም መፋሰስ ተጠያቂዎች ሆነዋል?
14 ዕንባቆም የተናገረው ሦስተኛው ወዮታ የደም ባለዕዳነትን የሚመለከት ነው። ዕንባቆም 2:12 “ከተማን በደም ለሚሠራ፣ ከተማንም በኃጢአት ለሚመሠርት ወዮለት” ይላል። በዚህ ሥርዓት ውስጥ ኃጢአተኝነትና ደም አፍሳሽነት የማይነጣጠሉ ነገሮች ሆነዋል። የዓለም ሃይማኖቶች፣ ደም እንደጎርፍ በማፍሰስ በአንደኛነት የሚጠቀሱ ሆነዋል። ክርስቲያን ነን ባዮችን ከሙስሊሞች ጋር ያጋደሉትን የመስቀል ጦርነቶች፣ በስፔይንና በላቲን አሜሪካ የተፈጸመውን የካቶሊክ ኢንኩዊዝሽን፣ በአውሮፓ በፕሮቴስታንቶችና በካቶሊኮች መካከል የተደረገውን የሠላሳ ዓመት ጦርነት፣ ከእነዚህ ሁሉ የሚከፉትንና በሕዝበ ክርስትና ግዛት ውስጥ የተቆሰቆሱትን ሁለት የዓለም ጦርነቶች መጥቀሱ ብቻ ይበቃል።
15. (ሀ) በአብያተ ክርስቲያናት ድጋፍ ወይም ስምምነት ብሔራት ምን ማድረጋቸውን ቀጥለዋል? (ለ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለምን የጦር መሣሪያ ትጥቅ ሊያስቆም ይችላልን?
15 ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት አስከፊ ገጽታዎች አንዱ በሚልዮን ለሚቆጠሩ አይሁዶችና ሌሎች በአውሮፓ የነበሩ ንጹሐን ሰዎች እልቂት ምክንያት የሆነው የናዚ ሆሎኮስት ነው። የፈረንሳይ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አመራር በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ንጹሐን ሰዎች ወደ ናዚ የግድያ ሥፍራዎች እንዳይወሰዱ አለመቃወሙን አምኖ የተቀበለው አሁን በቅርቡ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም ብሔራት በቤተ ክርስቲያን ድጋፍና ስምምነት ለተጨማሪ ደም መፋሰስ የሚያደርጉትን ዝግጅት ቀጥለዋል። ታይም መጽሔት (ዓለም አቀፍ እትም) ስለ ሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በቅርቡ እንዲህ ብሏል:- “በአዲስ መልክ የተቋቋመው የሩስያ ቤተ ክርስቲያን በአንድ ወቅት ፈጽሞ ሊታሰብ በማይችል መስክ፣ ማለትም በሩስያ የጦር ኃይል ላይ ወሳኝ የሆነ ተጽእኖ በማሳደር ላይ ነው። . . . ተዋጊ አውሮፕላኖችንና የጦር ሠፈሮችን መባረክ በጣም የተለመደ ተግባር ሆኗል። በኅዳር ወር የሩስያ መንበረ ፓትርያርክ በሚገኝበት በዳኒሎቭስኪ ገዳም፣ ቤተ ክርስቲያን የሩስያን የኑክሌር ጦር መሣሪያ እስከ መቀደስ ደርሳለች።” ይህ ዓለም በአጋንንታዊ የጦር መሣሪያዎች ለመታጠቅ የሚያደርገውን ጥድፊያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለማስቆም ይችላል? በፍጹም አይችልም! አንድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ በእንግሊዝ አገር በለንደን ከተማ በሚታተመው ዘ ጋርድያን ጋዜጣ ላይ እንደሚከተለው ብለዋል:- “በእርግጥ ሁኔታውን በይበልጥ ተስፋ ቢስ የሚያደርገው ዋነኛዎቹ አምስት የጦር መሣሪያ ሻጭ አገሮች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ቋሚ አባላት የሆኑት አምስት መንግሥታት መሆናቸው ነው።”
16. ይሖዋ ጦርነት ወዳድ የሆኑ ብሔራትን በተመለከተ ምን ያደርጋል?
16 ይሖዋ በጦርነት ወዳድ ብሔራት ላይ ይፈርድ ይሆን? ዕንባቆም 2:13 እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ አሕዛብ ስለ እሳት እንዲሠሩ፣ ወገኖችም ስለ ከንቱነት እንዲደክሙ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ አይደለምን?” ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር!’ አዎን፣ ይሖዋ በሰማይ የጦርነት ወዳድ ሕዝቦችንና ብሔራትን ድምጥማጥ ለማጥፋት በመሣሪያነት የሚያገለግል መላእክታዊ ሠራዊት አለው።
17. ይሖዋ በዓመፀኞቹ ብሔራት ላይ የቅጣት ፍርዱን ካስፈጸመ በኋላ ምድር በይሖዋ እውቀት የምትሞላው እስከ ምን ድረስ ነው?
17 በእነኚህ ጠብ ወዳድ ብሔራት ላይ የይሖዋ የቅጣት ፍርድ ከወረደ በኋላ ምን ይከተላል? ዕንባቆም 2:14 መልሱን ይሰጠናል:- “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ ትሞላለችና።” እንዴት ያለ ታላቅ ተስፋ ነው! የይሖዋ ልዕልና በአርማጌዶን ለአንዴና ለዘላለም ይረጋገጣል። (ራእይ 16:16) ‘የእግሩ ስፍራ’ የሆነችው ይህችን የምንኖርባትን ምድር ግርማ እንደሚያላብሳት ያረጋግጥልናል። (ኢሳይያስ 60:13) የሰው ዘር በሙሉ የአምላክን የሕይወት መንገድ ስለሚማር ስለ ክብራማው የይሖዋ ዓላማ ያላቸው እውቀት የባሕር አዘቅቶችን እንደሚሞላው የውቅያኖስ ውኃ ይሆናል።
አራተኛውና አምስተኛው ወዮታ
18. ዕንባቆም የተናገረለት አራተኛ ወዮታ ምንድን ነው? ይህስ ዛሬ ባለው የሥነ ምግባር ሁኔታ የሚንጸባረቀው እንዴት ነው?
18 አራተኛው ወዮታ በዕንባቆም 2:15 ላይ በሚከተሉት ቃላት ተገልጿል:- “ኀፍረተ ሥጋውን ለማየት ባልንጀራውን ለሚያጠጣ፣ ክፉንም ለሚጨምርበት፣ ለሚያሰክረውም ወዮለት!” ይህ የሚያመለክተው ዘመናዊው ዓለም ከትክክለኛው ጎዳና ምን ያህል ርቆ የሄደ መሆኑን ነው። ስድ በሆኑ ሃይማኖታዊ አካላት ሳይቀር የሚደገፈው ምግባረ ቢስነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መንገድ ተስፋፍቷል። እንደ ኤድስ ያሉት ወረርሽኝ በሽታዎችና ሌሎች የአባለ ዘር በሽታዎች በመላው ምድር በመስፋፋት ላይ ናቸው። ይህ የዛሬው “እኔ ብቻ ልቅደም” ባይ ትውልድ ስለ ‘ይሖዋ ክብር’ ከማሰላሰል ይልቅ ወደባሰ ወራዳነት እያዘቀጠ በመሄዱ የይሖዋን የቅጣት ፍርድ ለመቀበል ራሱን አዘጋጅቷል። ይህ በብልግና የተዋጠ ዓለም “በክብር ፋንታ እፍረት” ስለተሞላ ይሖዋ ለዚህ ዓለም ያለውን ፈቃድ የሚያመለክተውን የይሖዋን የቁጣ ጽዋ ሊጠጣ ነው። ‘ክብሩ በእፍረት ይለወጣል።’—ዕንባቆም 2:16
19. ዕንባቆም የተናገረው የአምስተኛው ወዮታ መቅድም ከምን ነገር ጋር የተዛመደ ነው? እነዚህስ ቃላት ዛሬ ላለው ዓለም ትርጉም አዘል የሆኑት እንዴት ነው?
19 የአምስተኛው ወዮታ መቅድም የተቀረጹ ምስሎች እንዳይመለኩ አጥብቆ ያስጠነቅቃል። ይሖዋ የሚከተሉትን ኃይለኛ ቃላት ነቢዩ እንዲናገር ያዘዋል:- “እንጨቱን:- ንቃ፣ ዲዳውንም ድንጋይ:- ተነሣ ለሚለው ወዮለት! በውኑ ይህ ያስተምራልን? እነሆ፣ በወርቅና በብር ተለብጦአል፣ ምንም እስትንፋስ የለበትም።” (ዕንባቆም 2:19) እስከ ዛሬ ድረስ ሕዝበ ክርስትናም ሆነች አረማውያን የሚባሉት ሕዝቦች ለሥነ ስቅለታቸው፣ ለድንግሊቱ እመቤታቸው፣ ለሌሎች ሥዕሎቻቸውና በሰውና በእንስሳት አምሳል ለተሠሩ ምስሎቻቸው ይሰግዳሉ። ከእነዚህም መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ይሖዋ የቅጣት ፍርዱን በሚያወርድበት ጊዜ ነቅተው አምላኪዎቻቸውን ከጥፋት ሊያድኑ አይችሉም። የተለበጡበት ወርቅና ብር ዘላለማዊ አምላክ ከሆነው ከይሖዋ ታላቅነትና ከሕያዋን ፍጥረታቱ ግርማ ጋር ሲወዳደር ትርጉም የለሽ ስለሚሆን አንጸባራቂነቱን ያጣል። ሁላችንም አቻ የማይገኝለትን ስሙን ለዘላለም ከፍ ከፍ እናድርግ!
20. በደስታ የማገልገል መብት ያገኘው በየትኛው የቤተ መቅደስ ዝግጅት ውስጥ ነው?
20 አዎን፣ አምላካችን ይሖዋ ሊወደስ የሚገባው አምላክ ነው። ለእርሱ ቅድስና ባለን ፍርሃት ተነሳስተን ይህን ጣዖት ስለማምለክ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ እንበል። ይሁን እንጂ አሁንም አዳምጡ። ይሖዋ መናገሩን አላቆመም። “እግዚአብሔር ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፣ ምድርም ሁሉ በፊቱ ዝም ትበል።” (ዕንባቆም 2:20) በነቢዩ አእምሮ ውስጥ የነበረው የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እንደሆነ አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ እኛ ከዚህ እጅግ በላቀ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ሆኖ በተሾመበት መንፈሳዊ የቤተ መቅደስ ዝግጅት ውስጥ የማምለክ መብት አግኝተናል። በዚህ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ ለታላቅ ስሙ የሚገባውን ክብር ለይሖዋ በመስጠት እንሰበሰባለን፣ እናገለግላለን፣ እንጸልያለን። አፍቃሪ ለሆነው ሰማያዊ አባታችን ከልብ የመነጨ አምልኮ ለማቅረብ በመቻላችን ያገኘነው ደስታ ምንኛ ታላቅ ነው!
ታስታውሳለህን?
• “አይዘገይም” ስለሚለው የይሖዋ ቃል ምን ይሰማሃል?
• ዕንባቆም የተናገራቸው ወዮታዎች ዛሬ ያላቸው ትርጉም ምንድን ነው?
• የይሖዋን ማስጠንቀቂያ ማሰማታችንን መቀጠል የሚኖርብን ለምንድን ነው?
• በየትኛው ቤተ መቅደስ አደባባይ የማገልገል መብት አግኝተናል?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንደ ዕንባቆም ዛሬ ያሉት የአምላክ አገልጋዮችም ይሖዋ እንደማይዘገይ ያውቃሉ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋን በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ሆነህ ለማምለክ ያገኘኸውን መብት ታደንቃለህ?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
U.S. Army photo