የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 35—ዕንባቆም
ጸሐፊው:- ዕንባቆም
የተጻፈበት ቦታ:- ይሁዳ
ተጽፎ ያለቀው:- ከክ.ል. በፊት በ628 ገደማ (?)
የዕንባቆም መጽሐፍ፣ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኙት ንዑሳን ነቢያት ወይም ደቂቀ ነቢያት ተብለው ከሚጠሩት መጻሕፍት አንዱ ነው። ያም ሆኖ ግን ነቢዩ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተመለከታቸው ራእዮችና የተናገራቸው ትንቢቶች ለአምላክ ሕዝቦች የሚሰጡት ጠቀሜታ አነስተኛ አይደለም። የዕንባቆም ትንቢት የሚያበረታታና የሚያጠናክር በመሆኑ የአምላክን ሕዝቦች በጭንቀት ጊዜ ይደግፋቸዋል። መጽሐፉ ሁለት ማራኪ እውነቶችን ጎላ አድርጎ ይገልጻል:- ይሖዋ አምላክ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ ነው፤ እንዲሁም ጻድቅ በእምነት ይኖራል። ከዚህም በላይ የዕንባቆም መጽሐፍ የአምላክን አገልጋዮች የሚቃወሙ ሰዎችንና ሕዝቦቹ እንደሆኑ በሐሰት የሚናገሩትን ግብዞች ለማስጠንቀቅ ያገለግላል። የውዳሴ መዝሙሮች ሁሉ ሊቀርቡለት በሚገባው በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት በማሳደር ረገድ ምሳሌ ይሆናል።
2 የዕንባቆም መጽሐፍ “ነቢዩ ዕንባቆም የተቀበለው ንግር” በማለት ይጀምራል። (ዕን. 1:1) ዕንባቆም (በዕብራይስጥ ቻቫኩክ) የሚለው ስም “የጋለ ስሜት” የሚል ትርጉም አለው። ይሁን እንጂ ይህ ነቢይ ማን ነበር? ስለ ዕንባቆም ወላጆች፣ ስለ ነገዱ እንዲሁም ስለ አኗኗሩ ወይም ስለ አሟሟቱ ሁኔታ የሚገልጽ ምንም መረጃ አልተሰጠም። በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም፣ በመጽሐፉ መደምደሚያ ላይ ከሚገኘው “ለመዘምራን አለቃ፣ በባለ አውታር መሣሪያዎቼ የተዘመረ መዝሙር” ከሚለው ሐሳብ በመነሳት ዕንባቆም ሌዋዊ የቤተ መቅደስ ዘማሪ ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል።
3 ዕንባቆም ትንቢቱን መናገር የጀመረው መቼ ነበር? በመጽሐፉ መደምደሚያ ላይ የሰፈረው ከላይ የተጠቀሰው ሐሳብ እንዲሁም “እግዚአብሔር ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ” የሚሉት ቃላት፣ ትንቢቱ በተነገረበት ወቅት በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ ገና እንዳልጠፋ ያሳያሉ። (2:20) ይህንን ሁኔታ በዕንባቆም መጽሐፍ ውስጥ ከሰፈረው መልእክት ጋር አያይዘን በመመልከት፣ ትንቢቱ የተነገረው ኢየሩሳሌም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከመጥፋቷ ጥቂት ቀደም ብሎ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ ትንቢቱ የተነገረው ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ ምን ያህል ዓመት ቀደም ብሎ ነው? ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ659-629 ከገዛውና ፈሪሃ አምላክ ከነበረው ከንጉሥ ኢዮስያስ የግዛት ዘመን በኋላ መሆን አለበት። የዕንባቆም መጽሐፍ፣ የይሁዳ ሰዎች ቢተረክላቸውም እንኳ ለማመን የሚከብዳቸው ክንውን እንደሚፈጸም በመተንበይ እንዲህ ለማለት የሚያስችለን ፍንጭ ይሰጠናል። ይህ ክንውን ምንድን ነው? አምላክ፣ እምነተ ቢስ የነበሩትን አይሁዳውያን ለመቅጣት ከለዳውያንን (ባቢሎናውያንን) ማስነሳቱ ነው። (1:5, 6) ጣዖት አምላኪ የሆነው ንጉሥ ኢዮአቄም በነገሠባቸው በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በይሁዳ እምነት ማጣትና ግፍ ተስፋፍቶ ነበር። ኢዮአቄምን ዙፋን ላይ ያስቀመጠው ፈርዖን ኒካዑ ሲሆን ብሔሩ በግብፃውያን ቁጥጥር ሥር ነበር። በመሆኑም ሕዝቡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያሉ ባቢሎን ልትወራቸው እንደምትችል ለማመን የሚያበቃ ምክንያት እንደሌለ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ናቡከደነፆር፣ በ625 ከክርስቶስ ልደት በፊት በከርከሚሽ በተደረገው ጦርነት ፈርዖን ኒካዑን ድል በማድረግ የግብፅን ኃይል አንኮታኮተው። ስለዚህም ትንቢቱ የተነገረው ይህ ሁኔታ ከመከሰቱ በፊት መሆን አለበት። ማስረጃዎቹ እንደሚያሳዩት ዕንባቆም ትንቢት መናገር የጀመረው በኢዮአቄም ግዛት መጀመሪያ ላይ (በ628 ከክርስቶስ ልደት በፊት) ሲሆን ይህም ነቢዩ ዕንባቆም በኤርምያስ ዘመን እንደኖረ ይጠቁማል።
4 መጽሐፉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ እንዴት ማወቅ እንችላለን? የጥንቶቹ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የመጻሕፍት ዝርዝሮች የዕንባቆም መጽሐፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መሆኑን ያረጋግጣሉ። በእነዚህ ዝርዝሮች ውስጥ መጽሐፉ በስም ባይጠቀስም ‘አሥራ ሁለቱ ንዑሳን ነቢያት’ ከሚባሉት መጻሕፍት መካከል እንደተካተተ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም የዕንባቆም መጽሐፍ በዚህ ክፍል ውስጥ ካልተጨመረ 12 መጻሕፍት ሊሆኑ አይችሉም። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የዕንባቆምን ትንቢት በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት እንደ አንዱ አድርጎ የተቀበለው ሲሆን “ነቢያት እንዲህ ብለው የተናገሩት” በማለት ከዕንባቆም 1:5 ላይ በቀጥታ ጠቅሷል። (ሥራ 13:40, 41) ከዚህም በላይ ጳውሎስ በደብዳቤዎቹ ውስጥ ከዕንባቆም መጽሐፍ በርካታ ጥቅሶችን አስፍሯል። ዕንባቆም፣ በይሖዋ ስም ተጠቅሞና ለእርሱ ክብር በሚያመጣ መንገድ ስለ ይሁዳና ስለ ባቢሎን የተናገራቸው ትንቢቶች በትክክል መፈጸማቸው እውነተኛ የይሖዋ ነቢይ መሆኑን ያረጋግጣሉ።
5 የዕንባቆም መጽሐፍ ሦስት ምዕራፎች አሉት። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ምዕራፎች በጸሐፊውና በይሖዋ መካከል ስለተደረገው ውይይት ያወሳሉ። እነዚህ ምዕራፎች የከለዳውያንን ጥንካሬ የሚገልጹ ሲሆን የተሰረቀውን ለራሱ የሚያከማቸው፣ በተጭበረበረ ትርፍ መኖሪያውን የሚገነባው፣ ከተማን ደም በማፍሰስ የሚሠራውና የተቀረጸ ጣዖት የሚያመልከው የባቢሎን ሕዝብ የሚጠብቀውን ሐዘንም ይዘረዝራሉ። ሦስተኛው ምዕራፍ ደግሞ ይሖዋ በጦርነት ቀን ስለሚኖረው አስደናቂ ግርማ ይተርካል፤ ይህ ምዕራፍ መልእክቱን ሕያውና ኃይለኛ በሆነ መንገድ በማስፈር ረገድ ተወዳዳሪ የለውም። ምዕራፍ ሦስት በሐዘን እንጉርጉሮ መልክ የቀረበ ጸሎት ሲሆን “በዕብራይስጥ ቋንቋ ከተጻፉት ግጥሞች መካከል በጣም ግሩምና ዕጹብ ድንቅ እንደሆነ” ተገልጿል።a
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
12 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የዕንባቆም መጽሐፍ ለማስተማር ጠቃሚ መሆኑን በመገንዘብ ዕንባቆም ምዕራፍ 2 ቁጥር 4ን በሦስት የተለያዩ ወቅቶች ጠቅሶታል። ወንጌሉ፣ አምላክ እምነት ያላቸውን ሁሉ የሚያድንበት ኃይል መሆኑን ጠንከር አድርጎ ሲገልጽ “ጽድቁም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በእምነት የሆነ ነው፣ ‘ጻድቅ በእምነት ይኖራል’ ተብሎ እንደ ተጻፈው” በማለት በሮም ለሚገኙት ክርስቲያኖች ጽፏል። ለገላትያ ክርስቲያኖች ሲጽፍ ደግሞ “‘ጻድቅ በእምነት ይኖራል’ ስለ ተባለ፣ ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንደማይጸድቅ ግልጽ ነው” በማለት በረከት የሚገኘው እምነት በማሳየት እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። በተጨማሪም ጳውሎስ በዕብራውያን ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ ክርስቲያኖች ሕያው የሆነና ለመዳን የሚያስችል እምነት ማሳየት እንዳለባቸው ሲገልጽ ይሖዋ ለዕንባቆም የተናገራቸውን ቃላት ጠቅሷል። ሆኖም ጳውሎስ “ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል” የሚሉትን የዕንባቆም ቃላት ብቻ ሳይሆን በግሪክኛው የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ላይ የሚገኘውን “ወደ ኋላ ቢያፈገፍግ፣ ነፍሴ በእርሱ ደስ አትሰኝም” የሚለውን ሐሳብም አስፍሯል። በመጨረሻም “እኛ ግን አምነው ከሚድኑት ወገን” እንደሆንን በመግለጽ ሐሳቡን ደምድሟል።—ሮሜ 1:17፤ ገላ. 3:11፤ ዕብ. 10:38, 39
13 የዕንባቆም ትንቢት ኃይል ለሚያስፈልጋቸው በአሁኑ ጊዜ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። መጽሐፉ በአምላክ መተማመን እንደሚገባ ያስተምራል። በተጨማሪም ስለ አምላክ ፍርድ ለሌሎች ለማሳወቅ ይጠቅማል። የያዘው የማስጠንቀቂያ መልእክት ኃይለኛ ነው:- የአምላክ የፍርድ እርምጃ በጣም እንደዘገየ አድርጋችሁ አታስቡ፤ ፍርዱ “በእርግጥ ይመጣል።” (ዕን. 2:3) ደግሞም ባቢሎን ይሁዳን እንደምታጠፋት የተነገረው ትንቢት በትክክል ተፈጽሟል፤ ከዚያም በ539 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባቢሎን ራሷ ተማርካ ከተማዋ በሜዶንና በፋርስ ቁጥጥር ሥር ስትሆን የአምላክ የፍርድ እርምጃ ተፈጽሟል። የአምላክን ቃል ለማመን የሚያስችል እንዴት ያለ ማስጠንቀቂያ ነው! በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩትን አይሁዳውያን እምነተ ቢስ እንዳይሆኑ በሚያስጠነቅቅበት ጊዜ ከዕንባቆም መጽሐፍ መጥቀሱ ጠቃሚ ሆኖ አግኝቶታል:- “ነቢያት እንዲህ ብለው የተናገሩት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ ‘እናንት ፌዘኞች፤ ተመልከቱ፤ ተደነቁ፤ ጥፉም፤ ማንም ቢነግራችሁ፣ የማታምኑትን ሥራ፣ እኔ በዘመናችሁ እሠራለሁና።’” (ሥራ 13:40, 41፤ ዕን. 1:5 LXX) እምነት የለሾቹ አይሁዳውያን፣ ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋት የተናገረውን ማስጠንቀቂያ እንዳላመኑ ሁሉ ጳውሎስንም ሰምተው እርምጃ አልወሰዱም። የሮም ሠራዊት በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሩሳሌምን በደመሰሰ ጊዜ የእጃቸውን አግኝተዋል።—ሉቃስ 19:41-44
14 ዛሬም በተመሳሳይ የዕንባቆም ትንቢት፣ ዓመጽ በሞላበት ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ጠንካራ እምነት እንዲያዳብሩ ያበረታታቸዋል። ሌሎችን ለማስተማርና በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች ለሚያነሱት ‘አምላክ ክፉዎችን ይበቀላል?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ይረዳቸዋል። የትንቢቱን ቃላት እንደገና ልብ በል:- “ጠብቀው፤ በእርግጥ ይመጣል፤ ከቶም አይዘገይም።” (ዕን. 2:3) የአምላክ መንግሥት ወራሽ የሆኑት ቅቡዓን ቀሪዎች በምድር ላይ ምንም ዓይነት ሁከት ቢነሳ፣ ይሖዋ ባለፉት ዘመናት የወሰደውን የበቀል እርምጃ አስመልክቶ ዕንባቆም የተናገራቸውን “ሕዝብህን ለመታደግ፣ የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ” የሚሉትን ቃላት ያስታውሳሉ። (3:13) በእርግጥም ይሖዋ ከዘላለም ጀምሮ የእነርሱ “ቅዱስ” ነው፤ እንዲሁም ዓመጸኞችን የሚቀጣና በፍቅሩ ለሚያቅፋቸው ሕይወት የሚሰጥ “ዐለት” ነው። ጽድቅን የሚወድዱ ሁሉ በመንግሥቱና በሉዓላዊነቱ ሐሴት በማድረግ እንዲህ ይላሉ:- “እኔ ግን በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ደስ ይለኛል፤ በድነቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ። ጌታ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ኀይሌ ነው” ይላሉ።—1:12፤ 3:18, 19
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በ1868 በሃንደርሰን የተዘጋጀው ዘ ቡክ ኦቭ ዘ ትዌልቭ ማይነር ፕሮፌትስ የተባለው መጽሐፍ ገጽ 285