ምዕራፍ 18
በጌታ ቀን የደረሰ ልዩ ልዩ የምድር መናወጥ
1, 2. (ሀ) በጣም ኃይለኛ የምድር መናወጥ ባለበት አካባቢ መኖር ምን ስሜት ያሳድራል? (ለ) ስድስተኛው ማህተም በተፈታ ጊዜ ዮሐንስ የገለጸው ምን ነገር ነበር?
ከፍተኛ የምድር መናወጥ በደረሰበት አካባቢ ኖረህ ታውቃለህን? ደስ የሚያሰኝ አጋጣሚ አይደለም። ከሚያናውጥ ውካታና ጩኸት በኋላ ትልቅ መንቀጥቀጥ ይፈጠራል። መጠለያ በምትፈልግበትና ምናልባትም ጠረጴዛ ሥር ለመደበቅ በምትሞክርበት ጊዜ ነውጡ እየተባባሰ ይሄዳል። አለበለዚያም የምድር መናወጥ መኖሩን ያወቅከው በድንገት የቤት ውስጥ ዕቃዎች ሲወድቁና ሲተረማመሱ ወይም ሕንጻዎች ሲደረማመሱ ይሆናል። ጉዳቱ በጣም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። በተደጋጋሚ የሚመላለሰው ነውጥ የጉዳቱንና የሥቃዩን መጠን ከፍተኛ ያደርገዋል።
2 ይህንን በአእምሮአችን እንያዝና ዮሐንስ ስድስተኛው ማህተም ሲፈታ የሆነውን ነገር ሲገልጽልን እንመልከት:- “ስድስተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ አየሁ፣ ታላቅም የምድር መናወጥ ሆነ።” (ራእይ 6:12ሀ) ይህ የተፈጸመው ሌሎቹ ማህተሞች በተፈቱበት አካባቢ መሆን ይኖርበታል። ይህ የምድር መናወጥ የሆነው በየትኛው የጌታ ቀን ክፍል ነው? የምድር መናወጡስ ምን ዓይነት ነውጥ ነው?—ራእይ 1:10
3. (ሀ) ኢየሱስ ስለመገኘቱ ምልክት በተናገረው ትንቢት ምን እንደሚፈጸም ተናግሮ ነበር? (ለ) እውነተኛ የምድር መናወጦች በራእይ 6:12 ላይ ከተገለጸው ምሳሌያዊ የምድር መናወጥ ጋር የሚዛመዱት እንዴት ነው?
3 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃል በቃልም ሆነ በምሳሌያዊ ሁኔታ የምድር መናወጦች ብዙ ጊዜ ተጠቅሰዋል። ኢየሱስ በመንግሥታዊ ሥልጣን መገኘቱን በሚያመለክተው ታላቅ ትንቢት ውስጥ “የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ሥፍራ ይሆናል” ብሎ ተንብዮ ነበር። ይህም “የምጥ ጣር መጀመሪያ” ከሚሆኑት ነገሮች ክፍል ይሆናል። ከ1914 ጀምሮ የምድር ነዋሪዎች ብዛት በጣም ጨምሮ በሺህ ሚልዮን በሚቆጠርበት ደረጃ ላይ በደረሰበት በዚህ ዘመን እውነተኛ የምድር መናወጦች ለዘመናችን መከራ መብዛት የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል። (ማቴዎስ 24:3, 7, 8) ይሁን እንጂ እነዚህ የምድር መናወጦች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ቢሆኑም የተፈጥሮና አካላዊ አደጋዎች ናቸው። በራእይ 6:12 ላይ ለተገለጸው ታላቅና ምሳሌያዊ የምድር መናወጥ መቅድም የሚሆኑ ክስተቶች ናቸው። ይህ መናወጥ የሰይጣንን ሰብዓዊና ምድራዊ ሥርዓት ከመሠረቱ የሚያናውጡ ተከታታይ መንቀጥቀጦች ከደረሱ በኋላ የመጨረሻው አውዳሚ ነውጥ በመሆን ይመጣል።a
የሰብዓዊው ኅብረተሰብ መንቀጥቀጥ
4. (ሀ) የይሖዋ ሕዝቦች ከ1914 ጀምሮ ትልቅ እልቂት የሚያስከትሉ ሁኔታዎች እንደሚኖሩ የተናገሩት ከመቼ ጀምሮ ነበር? (ለ) 1914 የየትኛው ዘመን ፍጻሜ ሆነ?
4 የይሖዋ ሕዝቦች ከ1870ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ጀምሮ የአሕዛብ ዘመን በ1914 እንደሚፈጸምና ከዚያ ዓመት ጀምሮ ከፍተኛ እልቂት የሚያስከትሉ ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ ሲጠባበቁ ቆይተው ነበር። ይህ የአሕዛብ ዘመን በኢየሩሳሌም የነበረው የዳዊት ዘሮች መንግሥት ከተገለበጠበት ከ607 ከዘአበ ጀምሮ ኢየሱስ በሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ዙፋን ላይ እስከተቀመጠበት እስከ 1914 እዘአ የቆየው “የሰባት ዘመናት” (2,520 ዓመት) ጊዜ ነው።—ዳንኤል 4:24, 25፤ ሉቃስ 21:24፣ ኪንግ ጀምስ ትርጉምb
5. (ሀ) ጥቅምት 2 ቀን 1914 ወንድም ሲ ቲ ራስል ምን ማስታወቂያ ተናገረ? (ለ) ከ1914 ጀምሮ ምን ዓይነት የፖለቲካ ነውጥ ተፈጠረ?
5 በዚህም ምክንያት ወንድም ሲ ቲ ራስል ጥቅምት 2 ቀን 1914 ጠዋት በኒውዮርክ ቤቴል ቤተሰብ መካከል ለማለዳ አምልኮ በተገኘ ጊዜ “የአሕዛብ ዘመን ተፈጸመ፣ የንጉሦቻቸውም ዘመን ተፈጸመ” የሚል ማስታወቂያ ተናገረ። በእውነትም በ1914 የጀመረው ነውጥ ሥር ነቀል ስለነበረ ለረዥም ዘመናት የኖሩ ብዙ ንጉሣዊ መንግሥታት ጠፍተዋል። የዛሮች አገዛዝ በ1917 በተነሳው የቦልሼቪኮች አብዮት መገልበጡ በማርክሲዝምና በካፒታሊዝም መካከል ለታየው የረጅም ጊዜ ግጭት ምክንያት ሆኖአል። የፖለቲካ ለውጥ ያስከተለው ልዩ ልዩ ነውጥ በመላው ምድር ላይ የሚገኘውን ሰብዓዊ ኅብረተሰብ መበጥበጣቸውን ቀጥለዋል። በዛሬው ጊዜ ብዙ መንግሥታት ከአንድ ወይም ከሁለት ዓመት በላይ ሥልጣን ላይ መቆየት ተስኖአቸዋል። በፖለቲካው ዓለም ውስጥ የሚታየውን አለመረጋጋት በምሳሌ ለማስረዳት የኢጣልያን ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል። በኢጣልያ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ በ42 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ 47 አዳዲስ መንግሥታት ተቋቁመዋል። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ነውጥ ለመጨረሻ ጊዜ ለሚሆነው ከፍተኛ የመንግሥት ግልበጣ መቅድም ነው። ይህ ከፍተኛ የመንግሥት ግልበጣ ምን ያስከትላል? የአምላክ መንግሥት ብቸኛዋ የምድር አስተዳዳሪ ትሆናለች።—ኢሳይያስ 9:6, 7
6. (ሀ) ኤች ጂ ዌልስ አዲሱን የታሪክ ምዕራፍ የገለጹት እንዴት ነው? (ለ) አንድ ፈላስፋና አንድ የመንግሥት ባለ ሥልጣን ከ1914 ወዲህ ስለተከፈተው የታሪክ ምዕራፍ ምን ሲሉ ጽፈዋል?
6 የታሪክ ሊቃውንት፣ ፈላስፎችና የፖለቲካ መሪዎች 1914 አዲስና ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ የተከፈተበት ዓመት እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ የታሪክ ምዕራፍ ከተከፈተ አሥራ ሰባት ዓመታት ካለፉ በኋላ ታሪክ ጸሐፊው ኤች ጂ ዌልስ እንደሚከተለው በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር:- “ነቢዩ ጥሩ ሁኔታዎች እንደሚመጡ በደስታ ይተነብይ ነበር። ይሁን እንጂ የእርሱ ግዴታ የተመለከተውን ነገር መናገር ብቻ ነው። ነቢዩ የተመለከተው ዓለም ወታደሮች፣ አርበኞች፣ ቀማኞች፣ የገንዘብ ሰዎች የሚቆጣጠሩትን ዓለም፤ ጥርጣሬና ጥላቻ የነገሠበት ዓለም፣ ግላዊ ነጻነት የተመናመነበት፣ የከረረ የመደብ ጥላቻ የተስፋፋበትና ለአዳዲስ ጦርነቶች ዝግጅት የሚደረግበት ዓለም ነው።” በ1953 በርትራንድ ራስል የተባሉት ፈላስፋ የሚከተለውን ጽፈው ነበር:- “ከ1914 ጀምሮ የዓለምን ሁኔታ የሚከታተል ማንኛውም ሰው ወደ ባሰ አደጋና እልቂት በሚደረገው ጭፍን ሩጫ መረበሹ አይቀርም። . . . የሰው ልጅ ጨካኝ በሆነ አንድ የግሪኮች አምላክ እየተነዳ ወደ አሳዛኝ ሁኔታ በመገስገስ ላይ ያለና የራሱን ዕድል ለመወሰን የተሳነው ልብ ወለድ ሰው ሆኖ ይታየዋል።” በ1980 ደግሞ ሐሮልድ ማክሚላን የተባሉት አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን 20ኛው መቶ ዘመን ሲጀምር የነበረውን ሰላማዊ ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ብለዋል:- “ማንኛውም ነገር ከቀን ወደ ቀን እየተሻሻለ በመሄድ ላይ ነበር። የተወለድኩበት ዓለም ይህን የመሰለ ነበር። . . . ይህ ሁሉ በ1914 አንድ ቀን ጠዋት ሳይታሰብ በድንገት ተለወጠና ድምጥማጡ ጠፋ።”
7-9. (ሀ) ከ1914 ጀምሮ ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ ያናጉት የትኞቹ ነውጦች ናቸው? (ለ) ከኢየሱስ መገኘት ጋር በተያያዘ ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ ያናወጡት ነገሮች የትኞቹን ሁኔታዎች ይጨምራሉ?
7 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ደግሞ ሌላ የነውጥ ማዕበል አምጥቷል። አነስተኛ ጦርነቶችና ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት ምድርን ማናወጣቸውን ቀጥለዋል። አሸባሪዎች ጥቃት ይሰነዝሩ ይሆናል ወይም መንግሥታት ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ የሚለው ሥጋት ብዙ ሰዎችን ያሳስባቸዋል። ደስ የሚያሰኘው ነገር ግን የዚህ ጥያቄ መልስ በሰው ልጆች ላይ ሳይሆን በአምላክ ላይ የተመካ መሆኑ ነው።—ኤርምያስ 17:5
8 ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ ከ1914 ጀምሮ ያናጋው ጦርነት ብቻ አይደለም። በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ቁስል ካስከተሉት ነውጦች አንዱ ጥቅምት 29 ቀን 1929 በዩናይትድ ስቴትስ የደረሰው የአክሲዮን ገበያ ውድቀት ነው። ይህ ውድቀት ለታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት ምክንያት ሲሆን ካፒታሊስት አገሮችን በሙሉ ነክቶአል። የኢኮኖሚው ድቀት ከ1932 እስከ 1934 ባለው ጊዜ ውስጥ ቢወገድም እንኳን አሁንም ቢሆን ካስከተለው ጠንቅ ፈጽሞ አልተላቀቅንም። ከ1929 ጀምሮ የኢኮኖሚ በሽታ የተጠናወተው ይህ ዓለም አንዳንድ የጥገና እርምጃዎች ተወስደውለታል። መንግሥታት በብድር ባጀት ይንቀሳቀሳሉ። በ1973 የደረሰው የነዳጅ ዘይት ችግርና የ1987ቱ የአክሲዮን ገበያ ውድቀት በገንዘቡ ዓለም ላይ ተጨማሪ ነውጥ አምጥቶአል። በዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚንቀሳቀሱት በብድር ነው። ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሰዎች በፍጥነት ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ በተለያዩ የቁማር መጫወቻ መሣሪያዎችና እንደ ሎተሪና ቶምቦላ በመሰሉት ስውር የቁማር ዓይነቶች ይበዘበዛሉ። ብዙዎቹን የሎተሪ ጨዋታዎች የሚያስፋፉት ዜጎቻቸውን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው መንግሥታት ናቸው። የሕዝበ ክርስትና የቴሌቪዥን ወንጌላውያን እንኳን ድርሻቸውን ለመቦጨቅ እጃቸውን ከመሰንዘር አልተቆጠቡም።—ከኤርምያስ 5:26-31 ጋር አወዳድር።
9 ቀደም ሲል የኢኮኖሚው ችግር ሙሶሎኒንና ሂትለርን ሥልጣን እርካብ ላይ እንዲወጡ አስችሎአቸው ነበር። ታላቂቱ ባቢሎንም ምንም ጊዜ ሳታባክን የእነዚህን አምባገነኖች ሞገስ ለማግኘት ጥረት አድርጋለች። ቫቲካን በ1929 ከኢጣልያ ጋር፣ በ1933 ደግሞ ከጀርመን ጋር ውል ተፈራረመች። (ራእይ 17:5) ከዚያ በኋላ የተከሰቱት የጨለማ ጊዜያት ኢየሱስ መገኘቱን አስመልክቶ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ክፍል መሆናቸው ግልጽ ነበር። ከእነዚህም መካከል “አሕዛብ . . . እያመነቱ ይጨነቃሉ፣ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሳ ይደክማሉ” የሚለው ይገኝበታል። (ሉቃስ 21:7-9, 25-31)c አዎ፣ ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ በ1914 ማንቀጥቀጥ የጀመረው ነውጥ አስደንጋጭ ሁኔታዎችን በማስከተል እስከ ዛሬ ድረስ ቀጥሎአል።
ይሖዋም ነውጥ አመጣ
10. (ሀ) በሰው ልጆች ጉዳይ ውስጥ እነዚህን የሚያክሉ ነውጦች የኖሩት ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ለምን ነገር በመዘጋጀት ላይ ነው? ለዚህስ ምን በማድረግ ላይ ይገኛል?
10 እንደነዚህ ያሉት ነውጦች በሰው ልጆች ጉዳይ ውስጥ በተደጋጋሚ የተከሰቱት የሰው ልጅ የራሱን አካሄድ ለመምራት የማይችል በመሆኑ ነው። (ኤርምያስ 10:23) ከዚህም በላይ “ዓለምን ሁሉ የሚያስተው” አሮጌው እባብ፣ ሰይጣን ዲያብሎስ የሰው ልጆችን በሙሉ ከይሖዋ አምልኮ ለማራቅ በሚያደርገው የመጨረሻ የመፍጨርጨር ሙከራ በምድር ላይ ከፍተኛ ወዮታ በማምጣት ላይ ነው። ዘመናዊው ቴክኖሎጂ ዓለምን እንደ አንድ መንደር አድርጐ አቀራርቧታል። በዚህ ዓለም ውስጥ የብሔርና የዘር ጥላቻ የሰው ልጆችን ማኅበረሰብ ከመሠረቱ እያናጋው ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ቢሆን እንደ ስሙ ፈዋሽ መድኃኒት ሊያገኝለት አልቻለም። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ ሰው ሰውን ለጉዳቱ እየገዛው ነው። (ራእይ 12:9, 12፤ መክብብ 8:9) ይሁንና የምድርና የሰማይ ፈጣሪ የሆነው የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ይሖዋ፣ ባለፉት 70 ዓመታት የምድርን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚፈታበትን መንገድ ለማዘጋጀት ከዚህ በተለየ ሁኔታ ምድርን ሲያናውጥ ቆይቶአል። እንዴት?
11. (ሀ) በሐጌ 2:6, 7 ላይ ምን ዓይነት የማናወጥ ድርጊት ተገልጾአል? (ለ) የሐጌ ትንቢት በመፈጸም ላይ የሚገኘው እንዴት ነው?
11 በሐጌ 2:6, 7 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እንዲህ ይላልና፣ ገና አንድ ጊዜ በቅርብ ዘመን እኔ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስንም አናውጣለሁ፣ አሕዛብን ሁሉ አናውጣለሁ፣ በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውም ዕቃ ይመጣል። ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW]።” ይሖዋ በተለይ ከ1919 ወዲህ ምሥክሮቹ ለሰብዓዊው ማኅበረሰብ የተለያዩ ክፍሎች በሙሉ የፍርድ መልዕክቱን እንዲናገሩ አድርጎአል። በዚህ ምድር አቀፍ የማስጠንቀቅ ዘመቻ አማካኝነት የሰይጣን ዓለማዊ ሥርዓት ስለ ፍርዱ እንዲያውቅ ተደርጓል።d ማስጠንቀቂያው እየተፋፋመ በሄደ መጠን “የተመረጠ ዕቃ” የሆኑት ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ከአሕዛብ ለመለየት ተነሳስተዋል። በሰይጣን ድርጅት ውስጥ በተከሰተው ነውጥ ምክንያት አይሸበሩም። ከዚህ ይልቅ ሁኔታውን በማስተዋል የይሖዋን የአምልኮ ቤት በክብር በመሙላቱ ሥራ ከቅቡዓን የዮሐንስ ክፍል አባሎች ጋር ለመካፈል ይወስናሉ። ይህስ የሚፈጸመው እንዴት ነው? የተቋቋመችውን የአምላክ መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ ቀናተኞች በመሆን ነው። (ማቴዎስ 24:14) ይህ ኢየሱስና ቅቡዓን ተከታዮቹ አባላት የሚሆኑበት መንግሥት “የማይናወጥ መንግሥት” ሆኖ ለይሖዋ ክብር ለዘላለም ጸንቶ ይቆማል።—ዕብራውያን 12:26-29
12. በማቴዎስ 24:14 ላይ ለተተነበየው የስብከት ሥራ ምላሽ መስጠት ጀምረህ ከሆነ የራእይ 6:12 ታላቅ የምድር መናወጥ ከመጀመሩ በፊት ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
12 አንተስ ይህን ስብከት ሰምተህ ምላሽ መስጠት የጀመርክ ሰው ነህን? ምናልባት በቅርቡ በተደረገው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ ከተገኙት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ነህን? ከሆንክ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማጥናት በምታደርገው ጥረት ወደፊት ግፋበት። (2 ጢሞቴዎስ 2:15፤ 3:16, 17) ለጥፋት የተወሰነውን የሰይጣን ምድራዊ ኅብረተሰብ ብልሹ አኗኗር ሙሉ በሙሉ ትተህ ውጣ። የመጨረሻው ታላቅ “የምድር መናወጥ” የሰይጣንን ዓለም በሙሉ ሰባብሮ ከማድቀቁ በፊት ወደ ክርስቲያናዊው የአዲስ ዓለም ኅብረተሰብ ግባና በዚህ ኅብረተሰብ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሙሉ በሙሉ ተካፈል። ይሁን እንጂ ይህ ታላቅ “የምድር መናወጥ” ምንድን ነው? እስቲ እንመልከት።
ታላቁ የምድር መናወጥ!
13. ታላቁ የምድር መናወጥ ለሰው ልጅ አዲስ ተሞክሮ የሚሆነው በምን መንገድ ነው?
13 አዎ፣ ይህ አስጨናቂ የመጨረሻ ዘመን ምሳሌያዊም ሆኑ ቃል በቃል የሆኑ የምድር መናወጦች የታዩበት ዘመን ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ይሁን እንጂ ከእነዚህ የምድር መናወጦች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ዮሐንስ ስድስተኛው ማህተም በተፈታ ጊዜ የተመለከተውን የመጨረሻ ታላቅ የምድር መናወጥ አልሆኑም። ከታላቁ የምድር መናወጥ በፊት ለሚመጡት ነውጦች ጊዜው አልቆአል። አሁን የሚመጣው ለሰው ልጅ ፈጽሞ አዲስ የሆነ ታላቅ የምድር መናወጥ ነው። ነውጡ በጣም ታላቅ ስለሆነ የሚያስከትለው የምድር መገልበጥና መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል መለኪያ ወይም በማንኛውም ሰው ሠራሽ የመለኪያ መሣሪያ ሊለካ አይችልም። መላውን “ምድር” ማለትም ወራዳውን የሰው ልጅ ኅብረተሰብ በሙሉ የሚያወድም አጥፊ ነውጥ ነው እንጂ በአንድ አካባቢ ብቻ ተወስኖ የሚቀር የምድር መንቀጥቀጥ አይደለም።
14. (ሀ) ስለ ታላቁ የምድር መናወጥና ስለሚያስከትላቸው ውጤቶች የተናገረው የትኛው ትንቢት ነው? (ለ) የኢዩኤልና የራእይ 6:12, 13 ትንቢት ምን የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል?
14 ሌሎችም የይሖዋ ነቢያት ይህን የመሰለ የምድር መናወጥና በምድር መናወጡ ምክንያት የሚከተለውን እልቂት ተንብየዋል። ለምሳሌ ኢዩኤል በ820 ከዘአበ ስለ “ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ቀን” ሲናገር “ፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል” ብሎአል። ቆየት ብሎም የሚከተሉትን ቃላት ጨምሮአል:- “የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ቀን በፍርድ ሸለቆ ቀርቦአልና የብዙ ብዙ ሕዝብ ውካታ በፍርድ ሸለቆ አለ። ፀሐይና ጨረቃ ጨልመዋል፣ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ሰውረዋል። እግዚአብሔርም [“ይሖዋም፣” NW] በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፣ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፣ ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ፣ ለእስራኤልም ልጆች መጠጊያ ይሆናል።” (ኢዩኤል 2:31፤ 3:14-16) ይህ ዓይነቱ ነውጥ ሊያመለክት የሚችለው ይሖዋ በታላቁ መከራ ጊዜ የሚፈጽመውን የቅጣት ፍርድ ብቻ ነው። (ማቴዎስ 24:21) ስለዚህ በራእይ 6:12, 13 ላይ የሚገኘው ትንቢትም ተመሳሳይ ትርጉም ሊኖረው ይገባል።—በተጨማሪም ኤርምያስ 10:10ንና ሶፎንያስ 1:14, 15ን ተመልከት።
15. ነቢዩ ሐጌ ምን ታላቅ መናወጥ እንደሚሆን ትንቢት ተናግሮ ነበር?
15 ከኢዩኤል ዘመን 200 ዓመት ያህል ቆይቶ ነቢዩ ዕንባቆም ለአምላኩ ሲጸልይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “አቤቱ [“ይሖዋ ሆይ፣” NW] ዝናህን ሰምቼ ፈራሁ፣ አቤቱ [“ይሖዋ ሆይ፣” NW] በዓመታት መካከል ሥራህን ፈጽም በዓመታት መካከል ትታወቅ በመዓት ጊዜ ምሕረትን አስብ።” ይህ “መዓት” ምን ይሆን? ዕንባቆም በመቀጠል ስለ ይሖዋ የሚከተለውን በመናገር ታላቁ መከራ ምን ዓይነት ገጽታ እንደሚኖረው ይገልጽልናል። “ቆመ፣ ምድርንም አወካት ተመለከተ፣ አሕዛብንም አናወጠ . . . በምድር ላይ በመዓት ተራመድህ አሕዛብን በቁጣ አሄድሃቸው እኔ ግን በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ደስ ይለኛል በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።” (ዕንባቆም 3:1, 2, 6, 12, 18) ይሖዋ አሕዛብን በሙሉ በሚወቃበት ጊዜ በምድር ሁሉ ላይ በጣም ኃያል የሆነ ነውጥ ያመጣል።
16. (ሀ) ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ የመጨረሻ ጥቃቱን በሚፈጽምበት ጊዜ ስለሚሆነው ነገር ሕዝቅኤል ምን ትንቢት ተናግሮአል? (ለ) የራእይ 6:12 የምድር መናወጥ ምን ውጤት ያስከትላል?
16 ሕዝቅኤልም የማጎጉ ጎግ (ከነበረበት ቦታ ዝቅ የተደረገው ሰይጣን) በአምላክ ሕዝቦች ላይ የመጨረሻ ጥቃቱን በሚፈጽምበት ጊዜ ይሖዋ “በእስራኤል ምድር” ሁሉ ላይ “ታላቅ መናወጥ” እንደሚያመጣ ተንብዮአል። (ሕዝቅኤል 38:18, 19) ቃል በቃል የምድር መናወጥ ሊኖር ቢችልም የራእይ መጽሐፍ በምልክቶች የቀረበ መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። ይህም ትንቢት ሆነ ሌሎቹ የጠቀስናቸው ትንቢቶች በጣም ምሳሌያዊ የሆነ አገላለጽ አላቸው። ስለዚህ የስድስተኛው ማህተም መፈታት በዚህ ምድራዊ ሥርዓት ላይ ለሚደርሱት ነውጦች ሁሉ ማሳረጊያ የሚሆነውንና የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚቃወሙ ሁሉ የሚጠፉበትን ታላቅ የምድር መናወጥ የሚያሳይ ይመስላል።
የጨለማ ጊዜ
17. ታላቁ የምድር መናወጥ ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን የሚነካው እንዴት ነው?
17 ዮሐንስ ቀጥሎ እንደሚገልጽልን የምድር መናወጡ በሰማያት ላይ እንኳን ውጤት በአስከተሉ አስደንጋጭ ሁኔታዎች ታጅቦአል። እንዲህ ይላል:- “ፀሐይም እንደ ማቅ ጠጉር ጥቁር ሆነ፣ ጨረቃም በሞላው እንደ ደም ሆነ፣ በለስም በብርቱ ነፋስ ተናውጣ ቃርያዋን ፍሬ እንደምትጥል የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ወደቁ።” (ራእይ 6:12ለ, 13) በጣም የሚያስፈራ ሁኔታ ነው። ይህ ትንቢት ቃል በቃል የሚፈጸም ቢሆን ምን ያህል አስፈሪና አስደንጋጭ ጨለማ እንደሚፈጠር ልትገምቱ ትችላላችሁ። በቀን ሙቀት የሚሰጥና ሰውነት የሚያዝናና የፀሐይ ብርሃን አይኖርም። በሌሊት ደግሞ ልብ የሚያረጋጋ ብርማ ቀለም የጨረቃ ብርሃን አይኖርም። በጠራው ሰማይ ላይ ይንቆጠቆጡ የነበሩት እልፍ አእላፍ ከዋክብት አይታዩም። በእነዚህ ሁሉ ፋንታ ቀዝቃዛ የሆነና ጥቅጥቅ ያለ አስፈሪ ጨለማ ይኖራል።—ከማቴዎስ 24:29 ጋር አወዳድር።
18. በ607 ከዘአበ ሰማያት ለኢየሩሳሌም ጨለማ የሆኑት እንዴት ነበር?
18 በጥንትዋ እሥራኤል ላይ ይህን የመሰለ መንፈሳዊ ጨለማ እንደሚመጣ ትንቢት ተነግሮ ነበር። ኤርምያስ እንደሚከተለው በማለት አስጠንቅቆ ነበር። “ምድር ሁሉ ባድማ ትሆናለች፣ ነገር ግን ፈጽሜ አላጠፋትም። ስለዚህ ምድር ታለቅሳለች፣ በላይም ሰማይ ይጠቁራል።” (ኤርምያስ 4:27, 28) ይህ ትንቢት በ607 ከዘአበ በተፈጸመ ጊዜ ሁኔታው ሁሉ ለይሖዋ ሕዝቦች ጨለማ ሆኖ ነበር። ዋና ከተማቸው የነበረችው ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን እጅ ወድቃ ነበር። ቤተ መቅደሳቸው ጠፍቶ፣ ምድራቸው ባድማ ሆኖ ነበር። ምንም ዓይነት የሚያጽናና ብርሃን ከሰማይ አልመጣላቸውም። ኤርምያስ ለይሖዋ እያለቀሰ የተናገረው ሁኔታ ደርሶባቸዋል። “በቁጣ ከደንኸን አሳደድኸንም ገደልኸን፣ አልራራህም። ጸሎት እንዳያልፍ ራስህን በደመና ከደንህ።” (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:43, 44) ይህ ሰማያዊ ጨለማ ለኢየሩሳሌም ሞትና ጥፋት አስከትሎባት ነበር።
19. (ሀ) የአምላክ ነቢይ የነበረው ኢሳይያስ ለጥንትዋ ባቢሎን ሰማያት እንደሚጨልሙ ትንቢት የተናገረው እንዴት ነው? (ለ) የኢሳይያስ ትንቢት የተፈጸመው እንዴትና መቼ ነው?
19 ከዚህ ቆየት ብሎ በጥንትዋ ባቢሎን ላይ የደረሰው አደጋና ጥፋት በጨለማ ተመስሎአል። የአምላክ ነቢይ ስለዚህ ጉዳይ የሚከተለውን እንዲጽፍ በመንፈስ ተነሳስቶ ነበር:- “እነሆ፣ ምድሪቱን ባድማ ሊያደርግ ኃጢአተኞችዋንም ከእርስዋ ዘንድ ሊያጠፋ ጨካኝ ሆኖ በመዓትና በጽኑ ቁጣ ተሞልቶ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ቀን ይመጣል። የሰማይም ከዋክብትና ሠራዊቱ ብርሃናቸውን አይሰጡም፣ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፣ ጨረቃም በብርሃኑ አያበራም። ዓለሙን ስለ ክፋታቸው ክፉዎቹንም ስለ በደላቸው እቀጣለሁ የትዕቢተኞችንም ኩራት እሽራለሁ፣ የጨካኞችንም ኩራት አዋርዳለሁ።” (ኢሳይያስ 13:9-11) ይህ ትንቢት ባቢሎን በሜዶናውያንና በፋርሳውያን እጅ በ539 ከዘአበ በወደቀች ጊዜ ተፈጽሞአል። ባቢሎን የዓለም ዋነኛ ኃያል መንግሥት ከመሆን ደረጃዋ በወደቀች ጊዜ የደረሰባትን ተስፋ ቢስነት፣ የወደቀባትን ድቅድቅ ጨለማና ምንም ዓይነት የሚያጽናና ብርሃን ማጣትዋን በጥሩ ሁኔታ የሚገልጽ ትንቢት ነው።
20. ታላቁ የምድር መናወጥ ሲጀምር በዚህ ሥርዓት ላይ ምን ዓይነት አስፈሪ ሁኔታ ይፈጸማል?
20 ታላቁ የምድር መናወጥ ምድርን መምታት በሚጀምርበት ጊዜ ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ ይህ መላው የዓለም ሥርዓት በፍርሐትና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ይዋጣል። የሰይጣን ምድራዊ ሥርዓት ደማቅ ብርሃን ሰጪዎች ምንም ዓይነት የተስፋ ብርሃን መፈንጠቅ ያቅታቸዋል። በዛሬው ጊዜ እንኳን የምድር ፖለቲካዊ መሪዎች፣ በተለይ በሕዝበ ክርስትና አገሮች ውስጥ የሚገኙት መሪዎች በምግባረ ብልሹነታቸው፣ በውሸታምነታቸው፣ በጉቦኛነታቸው በጣም የታወቁ ሆነዋል። (ኢሳይያስ 28:14-19) ፈጽሞ ሊታመኑ በማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ሲፈነጥቁ የቆዩት የብርሃን ጭላንጭል ይሖዋ የቅጣት ፍርዱን በሚያስፈጽምበት ጊዜ ፈጽሞ ይዳፈናል። በምድር ጉዳዮች ላይ የነበራቸው ጨረቃ መሰል ተጽእኖ ሞት የሚያስከትልና በደም የተበከለ መሆኑ ይጋለጣል። እንደ ከዋክብት የሚታዩት ዓለማዊ ዝነኞቻቸው ተቃጥለው እንደሚጠፉ ተወርዋሪ ኮከቦችና በአውሎ ነፋስ ተበታትኖ እንደሚረግፍ ያልበሰለ ፍሬ ይሆናሉ። መላው ምድራችን ‘ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ ሆኖ በማያውቅና ከእንግዲህ ወዲያም በማይሆን ታላቅ መከራ’ ይናወጣል። (ማቴዎስ 24:21) ምንኛ የሚያስፈራ ሁኔታ ነው!
“ሰማይ” አለፈ
21. ዮሐንስ በራእዩ ውስጥ ስለ ‘ሰማይ’፣ ስለ ‘ተራራዎችና’ ስለ ‘ደሴቶች’ ምን ተመልክቶአል?
21 የዮሐንስ ራእይ ይቀጥላል:- “ሰማይም እንደ መጽሐፍ ተጠቅልሎ አለፈ፣ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወሰዱ።” (ራእይ 6:14) እነዚህ ቃል በቃል እውነተኛ ሰማይን ወይም እውነተኛ ተራሮችንና ደሴቶችን የሚያመለክት ትንቢት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ታዲያ የምን ነገር ምሳሌ ነው?
22. በኤዶም ‘እንደ መጽሐፍ ጥቅልል የተጠቀለሉት’ እንዴት ያሉ “ሰማያት” ናቸው?
22 “ሰማይ” የሚለው ቃል ምን እንደሆነ ለመረዳት ይሖዋ በአሕዛብ ላይ ስላወረደው ቁጣ የሚናገር ሌላ ተመሳሳይ ትንቢት ልንመለከት እንችላለን። “የሰማይም ሠራዊት ሁሉ ይበሰብሳሉ፣ ሰማያትም እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ።” (ኢሳይያስ 34:4) በተለይ ኤዶም የተለየ መከራ ደርሶባታል። እንዴት? ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ ከጠፋች በኋላ በባቢሎናውያን ተወርራ ነበር። በዚያ ጊዜ በግዑዙ ሰማይ ላይ የደረሰ ምንም ነገር አልነበረም። ይሁን እንጂ በኤዶም “ሰማያት” ላይ የደረሰ መቅሠፍት ነበር።e የመንግሥት ባለ ሥልጣኖችዋ እንደ ሰማይ ከፍ ብለው ይታዩበት ከነበረው ከፍተኛ ደረጃ ተዋርደው ወድቀዋል። (ኢሳይያስ 34:5) ለማንም እንደማያገለግል አሮጌ መጽሐፍ ተጠቅልለው ከቦታቸው ተወግደዋል።
23. እንደ ‘መጽሐፍ ጥቅልል የሚሸሸው’ “ሰማይ” ምንድን ነው? ይህስ አተረጓጎም በጴጥሮስ ቃላት የተረጋገጠው እንዴት ነው?
23 ስለዚህ ‘እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ተጠቅልሎ የሚሸሸው’ ሰማይ ይህን ምድር ሲገዙ የቆዩትን ጸረ አምላክ መንግሥታትን ያመለክታል። ድል አድራጊ የሆነው የነጩ ፈረስ ጋላቢ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከቦታቸው ያስወግዳቸዋል። (ራእይ 19:11-16, 19-21) ይህም ሐዋርያው ጴጥሮስ ስድስተኛው ማህተም በሚፈታበት ጊዜ ስለሚሆኑት ነገሮች በገለጸው ቃል ተረጋግጦአል። “አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል።” (2 ጴጥሮስ 3:7) “ተራራዎችና ደሴቶች ሁሉ ከሥፍራቸው ተወገዱ” የሚለው አነጋገርስ ምን ትርጉም አለው?
24. (ሀ) ተራሮችና ደሴቶች እንደተናወጡ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ የተነገረው መቼ ነበር? (ለ) ነነዌ በወደቀች ጊዜ ተራሮች የተናወጡት እንዴት ነበር?
24 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ ታላቅ የፖለቲካ ለውጥ በሚደረግበት ጊዜ ተራሮችና ደሴቶች እንደ ተናወጡ ወይም እንደ ተሸበሩ ይነገራል። ለምሳሌ ያህል ነቢዩ ናሆም በነነዌ ላይ ስለሚደርሰው የይሖዋ ፍርድ ሲናገር “ተራሮችም ከእርሱ የተነሳ ታወኩ፣ ኮረብቶችም ቀለጡ ምድርና ዓለም የሚኖሩበትም ሁሉ ከፊቱ ተናወጡ” ሲል ጽፎአል። (ናሆም 1:5) ነነዌ በ632 ከዘአበ በወደቀች ጊዜ ቃል በቃል ተራሮች እንደተሰነጠቁ ወይም እንደታወኩ የሚገልጽ የታሪክ ማስረጃ አናገኝም። ይሁን እንጂ በኃይሉና በታላቅነቱ ተራራ መስሎ ይታይ የነበረ የዓለም ኃያል መንግሥት በድንገት ተሰባብሮአል።—ከኤርምያስ 4:24 ጋር አወዳድር።
25. ይህ የነገሮች ሥርዓት በሚጠፋበት ጊዜ “ተራራዎችና ደሴቶች” ከቦታቸው የሚወገዱት እንዴት ነው?
25 ስለዚህ ስድስተኛው ማህተም ሲፈታ የታዩት “ተራራዎች ደሴቶች ሁሉ” ለአብዛኞቹ የሰው ልጆች የጸና መሠረት ያላቸው መስለው ይታዩ የነበሩት የዚህ ዓለም የፖለቲካ መንግሥታትና በእነዚሁ መንግሥታት ሥር የሚተዳደሩት ድርጅቶች መሆን ይኖርባቸዋል። ከቦታቸው ተናውጠው ሲወገዱ ቀድሞ ይታመኑባቸው የነበሩ የሰው ልጆች በታላቅ ፍርሐትና መሰቀቅ ይመለከቱአቸዋል። ትንቢቱ ቀጥሎ እንደሚገልጸው የይሖዋና የልጁ የቁጣ ቀን፣ የሰይጣንን ድርጅት በሙሉ የሚያስወግደው የመጨረሻ ነውጥ ለታላቅ በቀል እንደመጣ በማያጠያይቅ ሁኔታ ይረጋገጣል።
“በላያችን ውደቁ . . . ሰውሩን”
26. የአምላክን ልዕልና የሚቃወሙ ሰዎች በድንጋጤ ምን ያደርጋሉ? ከፍርሐታቸውስ የተነሳ ምን ይላሉ?
26 የዮሐንስ ቃል እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ፣ ተራራዎችንና ዓለቶችንም:- በላያችን ውደቁ በዙፋኑም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቁጣ ሰውሩን ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፣ ማንስ ሊቆም ይችላል? አሉአቸው።”—ራእይ 6:15-17
27. ታማኝ ያልነበሩት የሰማርያ እስራኤላውያን ምን ዓይነት ጩኸት አሰምተው ነበር? እነዚህስ ቃላት የተፈጸሙት እንዴት ነበር?
27 ነቢዩ ሆሴዕ የሰሜኑ የእሥራኤል መንግሥት ዋና ከተማ በነበረችው በሰማርያ ላይ ስለሚደርሰው የይሖዋ ፍርድ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር:- “የእሥራኤል ኃጢአት የሆኑት የአዌን የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፣ እሾህና አሜከላ በመሠዊያዎቻቸው ላይ ይበቅላል፣ ተራሮችንም ክደኑን፣ ኮረብቶችንም:- ውደቁብን ይሉአቸዋል።” (ሆሴዕ 10:8) እነዚህ ቃላት የተፈጸሙት እንዴት ነበር? ሰማርያ በ740 ከዘአበ በአሶራውያን እጅ በወደቀች ጊዜ እሥራኤላውያን የሚሸሹበት ምንም ቦታ አልነበራቸውም። የሆሴዕ ቃል ድል የተደረጉት ሰዎች የተሰማቸውን የረዳት የለሽነት፣ የመደናገጥና የመጣል ስሜት ይገልጻል። ከዚህ በፊት ጥንካሬ ያላቸው መስለው ይታዩ የነበሩት የሰማርያ ተራራ መሰል ድርጅቶችም ሆኑ ግዑዞቹ ኮረብታዎች ሊያድኑአቸው አልቻሉም።
28. (ሀ) ኢየሱስ ለኢየሩሳሌም ሴቶች ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር? (ለ) ኢየሱስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ የተፈጸመው እንዴት ነው?
28 ኢየሱስ ወደሚገደልበት ሥፍራ በሮማውያን ወታደሮች በሚወሰድበት ጊዜም በተመሳሳይ ለኢየሩሳሌም ሴቶች እንዲህ ብሎ ነበር:- “መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። በዚያን ጊዜ ተራራዎችን በላያችን ውደቁ፣ ኮረብቶችንም ሰውሩን ይሉ ዘንድ ይጀምራሉ።” (ሉቃስ 23:29, 30) ኢየሩሳሌም በ70 እዘአ በሮማውያን የጠፋችበት ሁኔታ በታሪክ በሚገባ የተመዘገበ ነው። የኢየሱስ ትንቢትም የሆሴዕን ትንቢት በመሰለ ሁኔታ እንደተፈጸመ ግልጽ ነው። በዚያ ዘመን በይሁዳ ምድር ለቀሩት አይሁዳውያን ምንም ዓይነት መሸሸጊያ አልተገኘላቸውም። በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ በማንኛውም ሥፍራ ቢሰወሩ፣ በተራራ አናት ላይ ወደ ተሠራው የማሳዳ ምሽግ ቢሸሹ እንኳን ከይሖዋ የቁጣ ፍርድ ሊያመልጡ አልቻሉም።
29. (ሀ) የይሖዋ የቁጣ ቀን ሲመጣ ይህንን የነገሮች ሥርዓት ደግፈው ለመቆም የቆረጡ ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል? (ለ) ይሖዋ ቁጣውን በሚገልጥበት ጊዜ ኢየሱስ የተናገረው የትኛው ትንቢት ይፈጸማል?
29 አሁንም የስድስተኛው ማህተም መፈታት የይሖዋ የቁጣ ቀን በሚመጣበት ጊዜ ይህንኑ የሚመስል ነገር እንደሚፈጸም ያመለክታል። ይህ ምድራዊ የነገሮች ሥርዓት ለመጨረሻ ጊዜ በሚናወጥበት ጊዜ ሥርዓቱን ጠብቆ ለማቆየት የቆረጡ ሰዎች ሁሉ ተደናግጠው መሸሸጊያ ሥፍራ ይፈልጋሉ። ግን ሊያገኙ አይችሉም። የሐሰት ሃይማኖት ድርጅት የሆነችው ታላቂቱ ባቢሎንም ቀደም ብሎ በአሳዛኝ ሁኔታ አሳፍራቸዋለች። በግዑዝ ተራሮች ሥር የሚገኙት ዋሻዎችም ሆኑ ምሳሌያዊ ተራራ መሰል የፖለቲካና የንግድ ድርጅቶች የገንዘብ ዋስትናም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት ሌላ እርዳታ ሊሰጡ አይችሉም። ከይሖዋ ቁጣ ሊሰውራቸው የሚችል ምንም ነገር አይኖርም። የሚሰማቸውን ፍርሐትና ድንጋጤ ኢየሱስ በጥሩ ሁኔታ ገልጾታል። “በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፣ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል።”—ማቴዎስ 24:30
30. (ሀ) “ማን ሊቆም ይችላል?” የሚለው ጥያቄ ምን ያመለክታል? (ለ) በይሖዋ ፍርድ ቀን ለመቆም የሚችሉ ሰዎች ይኖራሉን?
30 አዎ፣ የድል አድራጊውን የነጭ ፈረስ ጋላቢ ሥልጣን ለመቀበል እምቢተኞች የሆኑ ሁሉ ስህተታቸውን ለመቀበል ይገደዳሉ። የእባቡ ዘሮች ለመሆን የመረጡ ሁሉ የሰይጣን ዓለም በሚያልፍበት ጊዜ ድምጥማጣቸው ይጠፋል። (ዘፍጥረት 3:15፤ 1 ዮሐንስ 2:17) በዚያ ጊዜ የሚኖረው የዓለም ሁኔታ ብዙ ሰዎች “ማን ሊቆም ይችላል?” ብለው እንዲጠይቁ የሚያደርጋቸው ይሆናል። በዚህ የፍርድ ቀን የይሖዋን ድጋፍና ሞገስ አግኝቶ የሚቆም ሰው ሊኖር የማይችል መስሎ ይታያል። ይሁን እንጂ የራእይ መጽሐፍ ቀጥሎ እንደሚያመለክተው ይህ ግምት ትክክል አይሆንም።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ቃል በቃል እውነተኛ የምድር መናወጥ በሚሆንበት ጊዜ ከምድር መናወጡ በፊት ውሾች እንዲጮሁ፣ አሶችና ሌሎች እንስሳት እንዲረበሹና እንዲቅበጠበጡ የሚያደርጉ አሸባሪ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። ሰዎች ግን የምድሩ መናወጥ እስኪጀምር ድረስ ምንም ነገር አያውቁም።—ሐምሌ 8, 1982 ንቁ! መጽሔት ገጽ 14 ተመልከት።
b ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ገጽ 22 እና 24 ተመልከት።
c ከ1895 እስከ 1931 በነበሩት ከ35 የሚበልጡ ዓመታት በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሽፋን ላይ በማዕበልና በባሕር ሞገድ በተናወጠ ሰማይ ፊት ለፊት የሚታይ የብርሃን ቤት ያለበት ሥዕልና የሉቃስ 21:25, 28, 31 ቃላት ይወጡ ነበር።
d ለምሳሌ ያህል በ1931 በተደረገው ልዩ ዘመቻ የይሖዋ ምሥክሮች የዓለም ተስፋ የሆነው መንግሥት የተባለውን ንዑስ መጽሐፍ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ቅጂዎች በምድር በሙሉ ለሚገኙ ቀሳውስት፣ ፖለቲከኞችና የንግድ ሰዎች አሰራጭተዋል።
e በተመሳሳይ መንገድ “ሰማያት” የሚለው ቃል አጠቃቀም አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ በተስፋይቱ ምድር በተቋቋመው ዘሩባቤል ገዥ፣ ኢያሱ ሊቀ ካህናት በሆኑበት አዲስ መስተዳድራዊ መዋቅር ውስጥ በኢሳይያስ 65:17, 18 ላይ ስለ “አዲስ ሰማያት” የተነገረው ትንቢት የመጀመሪያ ተፈጻሚነቱን እንዳገኘ ተጠቅሶአል።—2 ዜና 36:23፤ ዕዝራ 5:1, 2፤ ኢሳይያስ 44:28
[በገጽ 105 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በ1914 ምን እንደሚሆን በቅድሚያ ታውቆ ነበር
“የአምላክ መንግሥት ፍጻሜ የሆነው በ606 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበር። በዚያ ጊዜ ዘውዱ ተወሰደና መላዋ ምድር በአሕዛብ ግዛት ሥር ሆነች። ከ606 ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምረን 2520 ዓመት ስንቆጥር 1914 ዓ.ም. ላይ ያደርሰናል።”f—ሦስቱ ዓለማት፣ በ1877 የታተመ፣ ገጽ 83
“‘የአሕዛብ ዘመን’ ከ606 ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ እስከ 1914 ዓ.ም. የሚቆይ የ2520 ዓመት ጊዜ እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽና ጠንካራ ማስረጃ ይሰጠናል።”—የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት፣ ጥራዝ 2 በሲቲ ራስል ተጽፎ በ1889 የታተመ፣ ገጽ 79
ቻርልስ ቴዝ ራስልና ባልንጀሮቹ የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች 1914 የአሕዛብ ዘመን የሚፈጸምበት ዓመት እንደሚሆን የተረዱት ከአሥርተ ዓመታት በፊት ነበር። (ሉቃስ 21:24) በጊዜው የዚህ ዘመን ፍጻሜ ምን ትርጉም እንደሚኖረው ሙሉ በሙሉ ባይረዱም 1914 በታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ዓመት እንደሚሆን እርግጠኛ ሆነው ነበር። በዚህም አልተሳሳቱም ነበር። የሚከተለውን የጋዜጣ ሐተታ ልብ በል:-
“ይህ አስፈሪ ጦርነት በአውሮፓ ውስጥ መፈንዳቱ የአንድ ታላቅ ትንቢት ፍጻሜ ነበር። ‘ሚሊኒያል ዶውነርስ’ በመባል የሚታወቁት ‘ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች’ በሰባኪዎቻቸውና በጽሑፎቻቸው አማካኝነት 1914 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተተነበየው የቁጣ ቀን መባቻ እንደሚሆን ሲያውጁ ከሩብ መቶ ዓመት በላይ ሆኖአል። እነዚህ በመቶ የሚቆጠሩ ተጓዥ ወንጌላውያን ‘1914ን ጠብቁ!’ ሲሉ ቆይተዋል።”—ዘ ወርልድ፣ ነሐሴ 30 ቀን 1914 ታትሞ የወጣ፣ የኒው ዮርክ ጋዜጣ
[የግርጌ ማስታወሻ]
f እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች “ከክርስቶስ ልደት በፊትና” “በዓ.ም.” መካከል ዜሮ ዓመት አለመኖሩን አለመረዳታቸው የአምላክ ፈቃድ ነበር። ከጊዜ በኋላ ተጨማሪ ጥናት ተደርጎ ትክክለኛው ዓመት 606 ከዘአበ ሳይሆን 607 ከዘአበ መሆኑን በተረዱ ጊዜ ዜሮውንም ዓመት ከቁጥር ማውጣት እንደሚያስፈልግ አስተዋሉ። ይህም በመሆኑ ስለ “1914 ዓ.ም.” የተነገረው ትንቢት ትክክለኛነት ሳይለወጥ ቀርቶአል።—በ1943 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን “እውነት ነጻ ያወጣችኋል” የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 239 ተመልከት።
[በገጽ 106 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
1914—አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ዓመት
ፖለቲከንስ ፈርደን ሂስቶሪ—ሂስቶሪየንስ ማግት ኦግ ሜኒንግ (የፖለቲከን የዓለም ታሪክ—የታሪክ ኃይልና ትርጉም) የተባለው በ1987 በኮፐንሃገን የታተመ መጽሐፍ በገጽ 40 ላይ የሚከተለውን ሐተታ አስፍሮአል:-
“19ኛው መቶ ዘመን ስለ እድገት የነበረው እምነት ከፍተኛ አደጋ ደርሶበት የሞተው በ1914 ነበር። ፒተር ሙንች የተባለው የዴንማርክ ታሪክ ጸሐፊና ፖለቲከኛ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ‘በታላላቆቹ የአውሮፓ መንግሥታት መካከል ጦርነት ይነሳ ይሆናል ብለን የምንሰጋበት ምንም ምክንያት የለም በማለት በትምክህት ጽፎ ነበር። ወደፊትም ቢሆን “የጦርነት አደጋ” ከ1871 ጀምሮ እንደታየው ፈጽሞ ይጠፋል።’
“ከጊዜ በኋላ የጻፉት የግል ማስታወሻ ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነበር:- ‘በ1914 ጦርነት በፈነዳ ጊዜ አዲስ የሰው ልጅ የታሪክ ምዕራፍ ተከፈተ። ማንም ሰው የተመኘውን ሊያገኝ ይችል የነበረበት የዕድገት ዘመን አልፎ የአደጋ፣ የመከራ፣ የጥላቻና የስጋት ዘመን ተተካ። በዚያ ጊዜ የወደቀብን ጨለማ የሰው ልጅ ባለፉት ሺህ ዓመታት ሲገነባ የቆየው ባሕላዊ መዋቅር ጠፍቶ እንዲቀር ያደርግ እንደሆነና እንዳልሆነ ሊያውቅ የሚችል ሰው አልነበረም፣ አሁንም የለም።’”
[በገጽ 110 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ተራሮች ከቦታቸው ተወገዱ’
[በገጽ 111 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዋሻዎች ውስጥ ተሸሸጉ