“በጉጉት እየተጠባበቃችሁኝ ኑሩ”
“ስለዚህ በጉጉት እየተጠባበቃችሁኝ ኑሩ ይላል ይሖዋ”—ሶፎንያስ 3:8 አዓት
1. ነቢዩ ሶፎንያስ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር? ይህስ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩትን ሰዎች ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው?
“ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል።” ይህ ነቢዩ ሶፎንያስ በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አጋማሽ ላይ ያሰማው ማስጠንቀቂያ ነው። (ሶፎንያስ 1:14) ትንቢቱ በ40 ወይም በ50 ዓመት ውስጥ ይሖዋ በኢየሩሳሌምና ሕዝቦቹን በማሠቃየት ሉዓላዊነቱን በተገዳደሩት ብሔራት ላይ የቅጣት እርምጃ በወሰደ ጊዜ ፍጻሜውን አግኝቷል። ይህ ሁኔታ በ20ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው? የምንኖረው የይሖዋ የመጨረሻው ‘ታላቅ ቀን’ በፍጥነት እየቀረበ ባለበት ጊዜ ውስጥ ነው። ልክ እንደ ሶፎንያስ ዘመን የይሖዋ ‘የቁጣ ትኩሳት’ የኢየሩሳሌም አምሳያ በሆነችው በሕዝበ ክርስትና ላይ እንዲሁም የይሖዋን ሕዝቦች በሚያሠቃዩና የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት በሚገዳደሩ ብሔራት ላይ ሊፈስስ ነው።—ሶፎንያስ 1:4፤ 2:4, 8, 12, 13፤ 3:8፤ 2 ጴጥሮስ 3:12, 13
ደፋር ምሥክር የነበረው ሶፎንያስ
2, 3. (ሀ) ስለ ሶፎንያስ ምን የምናውቀው ነገር አለ? ደፋር የይሖዋ ምሥክር እንደነበረ የሚያሳየውስ ምንድን ነው? (ለ) ሶፎንያስ ትንቢቱን መቼና የት እንደተናገረ ለማወቅ የሚያስችሉን እውነታዎች የትኞቹ ናቸው?
2 ስለ ነቢዩ ሶፎንያስ ብዙም አይታወቅም። ስሙ (በዕብራይስጥ ሴፋንያህ) “ይሖዋ ሸሸገ (ተንከባከበ)” የሚል ትርጉም አለው። ሆኖም ሶፎንያስ ከሌሎቹ ነቢያት በተለየ ሁኔታ የትውልድ ሐረጉን እስከ አራተኛ ትውልድ ማለትም እስከ “ሕዝቅያስ” ድረስ ዘርዝሯል። (ሶፎንያስ 1:1፤ ከኢሳይያስ 1:1፤ ከኤርምያስ 1:1 እና ከሕዝቅኤል 1:3 ጋር አወዳድር።) ይህ ያልተለመደ ስለሆነ አብዛኞቹ ተንታኞች የሶፎንያስ ቅመ አያት ታማኙ ንጉሥ ሕዝቅያስ እንደሆነ ይናገራሉ። እንዲህ ከሆነ ሶፎንያስ የተወለደው ከንጉሣዊ ቤተሰብ ነበር ማለት ነው። ይህም በይሁዳ አለቆች ላይ ለተናገረው ኃይለኛ የፍርድ መልእክቱ ክብደት ከመስጠቱም በላይ ሶፎንያስ ደፋር የይሖዋ ምሥክርና ነቢይ እንደሆነ ያሳያል። የኢየሩሳሌምን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ይከናወኑ የነበሩ ነገሮችን ጥሩ አድርጎ የሚያውቅ መሆኑ የይሖዋን የፍርድ መልእክት ያወጀው እዚያው ዋና ከተማው ውስጥ ሊሆን እንደሚችል ያሳያል።—ሶፎንያስ 1:8-11 የአዓት የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት።
3 ሶፎንያስ በይሁዳ የሕዝብ “አለቆች” (መኳንንት ወይም የነገድ አለቆች) እና ‘የንጉሥ ልጆች’ ላይ የሚመጣውን ፍርድ በማወጅ ሲያወግዛቸው መለኮታዊ ንጉሡን አለመጥቀሱ ትኩረት የሚስብ ነገር ነው።a (ሶፎንያስ 1:8፤ 3:3) ይህም ወጣቱ ንጉሥ ኢዮስያስ ወደ ንጹሑ አምልኮ አዘንብሎ እንደነበረ ያሳያል። ሆኖም ሶፎንያስ ካወገዛቸው ሁኔታዎች ማየት እንደሚቻለው ኢዮስያስ ሃይማኖታዊ ተሃድሶውን ገና አልጀመረም ነበር። እነዚህ ሁኔታዎች ሶፎንያስ ትንቢቱን በይሁዳ የተናገረው ከ659 እስከ 629 ከዘአበ ድረስ በገዛው በኢዮስያስ የመጀመሪያዎቹ የንግሥና ዓመታት መሆኑን ያመለክታሉ። ኃይለኛ መልእክት የያዙት የሶፎንያስ ትንቢቶች ወጣቱ ኢዮስያስ በጊዜው የጣዖት አምልኮ፣ ዓመፅና ምግባረ ብልሹነት ምን ያህል እንደተስፋፋ ይበልጥ እንዲያውቅ ያደረገው ከመሆኑም በተጨማሪ ከጊዜ በኋላ ጣዖታትን የማጥፋት ዘመቻ እንዲያካሂድ እንደገፋፋው ምንም አያጠራጥርም።—2 ዜና መዋዕል 34:1-3
ይሖዋን ያስቆጡት ነገሮች
4. ይሖዋ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ቁጣውን የገለጸው እንዴት ነው?
4 ይሖዋ በይሁዳና በዋና ከተማዋ በኢየሩሳሌም ይኖሩ በነበሩ አለቆችና ነዋሪዎች ላይ የተቆጣበት በቂ ምክንያት ነበረው። በነቢዩ ሶፎንያስ በኩል እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “እጄንም በይሁዳ ላይ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ላይ እዘረጋለሁ፤ ከዚህም ስፍራ የበኣልን ቅሬታና የጣዖታቱን ካህናት ስም አጠፋለሁ፤ በሰገነትም ላይ ለሰማይ ሠራዊት የሚሰግዱትን፣ በእግዚአብሔርና በንጉሣቸው በሚልኮም ምለው የሚሰግዱትን።”—ሶፎንያስ 1:4, 5
5, 6. (ሀ) በሶፎንያስ ዘመን ይሁዳ ውስጥ የነበረው ሃይማኖታዊ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? (ለ) ይሁዳ የሕዝብ አለቆችና በእነርሱ ሥር የነበሩት ሰዎች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኙ ነበር?
5 ይሁዳ በበኣል አምልኮ ውስጥ በሚከናወኑት ነውረኛ በሆኑ የመራባት ሥርዓተ አምልኮዎች፣ አጋንንታዊ በሆነ ኮከብ ቆጠራና የአረማውያን አምላክ በሆነው የሚልኮም አምልኮ ተበክላ ነበር። አንዳንዶች እንደሚሉት ሚልኮም ተብሎ የሚጠራው ሞሎክ የተባለው ጣዖት ከሆነ የይሁዳ የሐሰት አምልኮ ዘግናኝ የሆነውን ልጆችን መሥዋዕት የማድረግ ሥርዓት ያካትት ነበር ማለት ነው። እንደነዚህ ያሉ ሃይማኖታዊ ተግባራት በይሖዋ ዘንድ አጸያፊ ነበሩ። (1 ነገሥት 11:5, 7፤ 14:23, 24፤ 2 ነገሥት 17:16, 17) ጣዖት አምላኪዎቹ ይህን ሁሉ እያደረጉ በይሖዋ ስም ይምሉ ስለነበር በጣም አስቆጥተውታል። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ሃይማኖታዊ ርኩሰት ዝም ብሎ መመልከት ስላልቻለ አረማዊና ከሃዲ የሆኑትን ካህናት ለማጥፋት ተነሳ።
6 ከዚህም በተጨማሪ የይሁዳ የሕዝብ አለቆችም ምግባረ ብልሹዎች ሆነው ነበር። አለቆችዋ ተርበው “እንደሚያገሡ አንበሶች” ሆነው የነበረ ሲሆን ፈራጆችዋ የተራቡ “ተኩላዎች” ይመስሉ ነበር። (ሶፎንያስ 3:3) በእነርሱ ሥር የነበሩት ሰዎች ‘የጌቶቻቸውን ቤት ዓመፃንና ሽንገላን ይሞላሉ’ የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። (ሶፎንያስ 1:9) ፍቅረ ነዋይ በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቶ ነበር። ብዙዎቹ በጊዜው በተፈጠረው ሁኔታ ተጠቅመው ሀብት ለማጋበስ ይሯሯጡ ነበር።—ሶፎንያስ 1:13
ስለ ይሖዋ ቀን የነበሩ ጥርጣሬዎች
7. ሶፎንያስ ትንቢቱን የተናገረው ‘ከታላቁ የእግዚአብሔር ቀን’ ምን ያህል ቀደም ብሎ ነው? አብዛኞቹ አይሁዶች በምን ዓይነት መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ ይገኙ ነበር?
7 ቀደም ብለን እንደተመለከትነው በሶፎንያስ ዘመን ተስፋፍቶ የነበረው ከፍተኛ ውድቀት የሚያስከትል ሃይማኖታዊ ሁኔታ ሶፎንያስ ምሥክርና ነቢይ ሆኖ ሥራውን ያከናወነው ንጉሥ ኢዮስያስ የጣዖት አምልኮን ለማስወገድ ዘመቻ ከመጀሩ በፊት በ648 ከዘአበ ገደማ እንደነበረ ያሳያል። (2 ዜና መዋዕል 34:4, 5) በመሆኑም ሶፎንያስ ትንቢቱን የተናገረው “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን” በይሁዳ መንግሥት ላይ ከመምጣቱ ከ40 ዓመታት በፊት ሳይሆን አይቀርም። በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ አይሁዳውያን ጥርጣሬ አድሮባቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ ግዴለሾች በመሆን ይሖዋን ከማገልገል ‘ተመልሰው ነበር።’ ሶፎንያስ የሚናገረው ‘እግዚአብሔርን ስላልፈለጉትና ስላልጠየቁት’ ሰዎች ነው። (ሶፎንያስ 1:6) ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው በይሁዳ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ስለ አምላክ ምንም የማይገዳቸው ነበሩ።
8, 9. (ሀ) ይሖዋ ‘በአተላቸው ላይ የሚቀመጡትን ሰዎች’ የመረመረው ለምን ነበር? (ለ) ይሖዋ በይሁዳ ነዋሪዎች እንዲሁም በአለቆቻቸውና በሃይማኖታዊ መሪዎቻቸው ላይ ትኩረት ያደረገው በምን መንገድ ነው?
8 ይሖዋ የእርሱ ሕዝብ እንደሆኑ የሚናገሩትን ሰዎች ለመመርመር ዓላማዎቹን አሳወቀ። ይሖዋን እናመልካለን ብለው ይናገሩ ከነበሩት ሰዎች መካከል ይሖዋ በሰዎች ጉዳዮች ጣልቃ ለመግባት ያለውን ችሎታ ወይም ዓላማ የሚጠራጠሩ ሰዎች እየፈለገ ነበር። ይሖዋ “በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን በመብራት እመረምራለሁ፤ በአተላቸውም ላይ የሚቀመጡትን፣ በልባቸውም፦ እግዚአብሔር መልካምን አያደርግም፣ ክፉም አያደርግም የሚሉትን ሰዎች እቀጣለሁ” በማለት ተናግሯል። (ሶፎንያስ 1:12) “በአተላቸውም ላይ የሚቀመጡ” (ከወይን ጠጅ አጠማመቅ ጋር የተያያዘ አገላለጽ ነው) የሚለው አነጋገር አተላ በመጥመቂያው ውስጥ ዘቅጦ እንደሚቀመጥ ተደላድለው የተቀመጡ ሰዎችን ያመለክታል። እነዚህ ሰዎች አምላክ በቅርብ ጊዜ በሰዎች ጉዳይ ውስጥ እጁን ያስገባል በሚል ማንኛውም አዋጅ መታወክ አይፈልጉም።
9 ይሖዋ ትኩረቱን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዲሁም የእርሱን አምልኮ ከአረማውያን አምልኮ ጋር በቀላቀሉ ካህናቶቻቸው ላይ አድርጎ ነበር። በኢየሩሳሌም ቅጥሮች ውስጥ ጨለማን ተገን ያደረጉ ያህል ምንም እንደማይደርስባቸው ተማምነው ቢቀመጡ የተሸሸጉበትን መንፈሳዊ ጨለማ ወገግ አድርጎ የሚያሳይ መብራት በማብራት ፈልጎ ያገኛቸው ነበር። በሃይማኖታዊ ቸልተኝነታቸው የተነሳ መጀመሪያ አስፈሪ በሆኑ የፍርድ መልእክቶች ከዚያም እነዚህን የፍርድ መልእክቶች በማስፈጸም ያስጨንቃቸዋል።
“ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል”
10. ሶፎንያስ ‘ታላቁን የእግዚአብሔር ቀን’ የገለጸው እንዴት ነው?
10 ሶፎንያስ በይሖዋ መንፈስ ተነሳስቶ “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል፤ ኃያሉም በዚያ በመራራ ለቅሶ ይጮኻል” በማለት ጽፏል። (ሶፎንያስ 1:14) በእርግጥም ማስጠንቀቂያውን ሰምተው ወደ ንጹሕ አምልኮ ለመመለስ አሻፈረኝ ያሉ ካህናትን፣ ልዑላንና ተራ ሰዎች መራራ ቀን ይጠብቃቸው ነበር። ትንቢቱ በመቀጠል በዚያ ቀን ስለሚወሰደው የቅጣት እርምጃ እንዲህ ይላል፦ “ያ ቀን የመዓት ቀን፣ የመከራና የጭንቀት ቀን፣ የመፍረስና የመጥፋት ቀን፣ የጨለማና የጭጋግ ቀን፣ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን፣ በተመሸጉ ከተሞችና በረዘሙ ግንቦች ላይ የመለከትና የሰልፍ ጩኸት ቀን ነው።”—ሶፎንያስ 1:15, 16
11, 12. (ሀ) በኢየሩሳሌም ላይ የተነገረው የፍርድ መልእክት ምን ነበር? (ለ) ቁሳዊ ሀብት አይሁዳውያንን ከጥፋት አድኗቸው ነበርን?
11 በጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ የባቢሎን ሠራዊት ይሁዳን ወረረ። ኢየሩሳሌምም ከወረራው አላመለጠችም። የመኖሪያና የንግድ ሰፈሮችዋ ድምጥማጣቸው ጠፋ። “በዚያ ቀን፣ ይላል እግዚአብሔር፣ ከዓሣው በር የጩኸት ድምፅ፣ ከከተማውም በሁለተኛው ክፍል ውካታ፣ ከኮረብቶቹም ታላቅ ሽብር ይሆናል። እናንተ በመክቴሽ [ኢየሩሳሌም ውስጥ የሚገኝ ሰፈር] የምትኖሩ ሆይ፣ የከነዓን ሕዝብ [“ነጋዴዎች የነበሩት፣” አዓት] ሁሉ ጠፍተዋልና፣ ብርም የተሸከሙ ሁሉ ተቆርጠዋልና አልቅሱ።”—ሶፎንያስ 1:10, 11 የአዓት የግርጌ ማስታወሻ
12 አብዛኞቹ አይሁዳውያን የይሖዋ ቀን መቅረቡን አምኖ ለመቀበል አሻፈረኝ በማለት ከፍተኛ ትርፍ በሚያስገኙ የንግድ እንቅስቃሴዎች ተውጠው ነበር። ሆኖም ይሖዋ በታማኝ ነቢዩ በሶፎንያስ አማካኝነት ሀብታቸው ‘እንደሚማረክና ቤታቸው እንደሚፈርስ’ ተንብዮአል። ከተከሉት ወይን አይጠጡም እንዲሁም “በእግዚአብሔርም ቁጣ ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም [ነበር]”—ሶፎንያስ 1:13, 18
ሌሎችም ብሔራት ተፈረደባቸው
13. ሶፎንያስ በሞዓብ፣ በአሞንና በአሦር ላይ የተናገረው የፍርድ መልእክት ምንድን ነው?
13 በተጨማሪም ይሖዋ ሕዝቡን ባሠቃዩት ብሔራት ላይ ያለውን ቁጣ በነቢዩ ሶፎንያስ አማካኝነት ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “በሕዝቤም ላይ ያላገጡባትን፣ በድንበራቸውም ላይ እየታበዩ የተናገሩባትን የሞዓብን ማላገጥና የአሞንን ልጆች ስድብ ሰምቻለሁ። ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና በእርግጥ ሞዓብ እንደ ሰዶም፣ የአሞንም ልጆች እንደ ገሞራ፣ የሳማ ስፍራና የጨው ጉድጓድ ለዘላለምም ምድረ በዳ ሆነው ይኖራሉ፤ . . . እርሱም በሰሜን ላይ እጁን ይዘረጋል፣ አሦርንም ያጠፋል፤ ነነዌንም ባድማ፣ እንደ በረሃም ደረቅ ያደርጋታል።”—ሶፎንያስ 2:8, 9, 13
14. የውጪ ብሔራት በእስራኤላውያንና በአምላካቸው በይሖዋ ላይ ‘እንደታበዩ’ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
14 ሞዓብና አሞን የእስራኤላውያን የረጅም ጊዜ ጠላቶች ነበሩ። (ከመሳፍንት 3:12-14 ጋር አወዳድር።) ፓሪስ ውስጥ በሉቭር ሙዚየም በሚገኘው የሞዓባውያን ጽላት ላይ የተቀረጸው ጽሑፍ የሞዓባውያን ንጉሥ የነበረው ሞሳ የተናገራቸውን የጉራ ቃላት ይዟል። ካሞሽ በተባለው አምላኩ እርዳታ ብዙ የእስራኤል ከተሞችን እንደያዘ በኩራት ይተርካል። (2 ነገሥት 1:1) አሞናውያን ሚልኮም በተባለው አምላካቸው ስም ጋድ ተብሎ የሚጠራውን የእስራኤል ክልል እንደያዙ በሶፎንያስ ዘመን ይኖር የነበረው ኤርምያስ ተናግሯል። (ኤርምያስ 49:1) በተጨማሪም የአሦራውያን ንጉሥ ስልምናሶር አምስተኛ ሶፎንያስ ከኖረበት ዘመን አንድ መቶ ዓመት ቀደም ብሎ ሰማርያን በመውረር በቁጥጥሩ ሥር አውሏት ነበር። (2 ነገሥት 17:1-6) ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንጉሥ ሰናክሬም በይሁዳ ላይ ጥቃት በመሰንዘር በይሁዳ የሚገኙ አያሌ የተመሸጉ ከተሞች በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ነበር። አልፎ ተርፎም ኢየሩሳሌምን እንደሚወጋ ዝቶ ነበር። (ኢሳይያስ 36:1, 2) የአሦር ንጉሥ ቃል አቀባይ ኢየሩሳሌምን አሳልፈው እንዲሰጡ ሲጠይቅ በይሖዋ ላይ የትዕቢት ቃል ተናግሮ ነበር።—ኢሳይያስ 36:4-20
15. ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ የታበዩ ብሔራት የሚያመልኳቸውን አማልክት ያዋረደው እንዴት ነበር?
15 መዝሙር 83 “ኑ ከሕዝብ እናጥፋቸው፣ ደግሞም የእስራኤል ስም አይታሰብ” ብለው ጉራቸውን በመንዛት በእስራኤል ላይ የታበዩ እንደ ሞዓብ፣ አሞንና አሦር ያሉ ብዙ ብሔራት ይጠቅሳል። (መዝሙር 83:4) የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እነዚህን ሁሉ ትዕቢተኛ ብሔራትና አማልክቶቻቸውን እንደሚያዋርድ ነቢዩ ሶፎንያስ በድፍረት አስታውቋል። “በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ አላግጠዋልና፣ እየታበዩም ተናግረዋልና ይህ ስለ ትዕቢታቸው ያገኛቸዋል። እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የተፈራ ይሆናል፣ የምድርንም አማልክት ሁሉ ያከሳቸዋል፤ በአሕዛብም ደሴቶች ሁሉ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በስፍራቸው ሆነው ለእርሱ ይሰግዳሉ።”—ሶፎንያስ 2:10, 11
‘በጉጉት ተጠባበቁ’
16. (ሀ) የይሖዋ ቀን በመቅረቡ የተደሰቱት እነማን ናቸው? ለምንስ? (ለ) ለእነዚህ ታማኝ ቀሪዎች ምን ቀስቃሽ ትእዛዝ ተሰጥቷል?
16 አብዛኞቹ የይሁዳ አለቆችና ነዋሪዎች መንፈሳዊ ድብታ፣ ጥርጣሬ፣ የጣዖት አምልኮ፣ ምግባረ ብልሹነትና ፍቅረ ነዋይ ቢንጸባረቅባቸውም አንዳንድ ታማኝ አይሁዶች ሶፎንያስ የተናገራቸውን የማስጠንቀቂያ ትንቢቶች ሰምተው እንደነበር ግልጽ ነው። የይሁዳ ነገሥታት፣ መሳፍንትና ካህናት የፈጸሟቸው አጸያፊ ተግባራት አሳዝኗቸው ነበር። ሶፎንያስ ያወጃቸው መልእክቶች እነዚህን ታማኝ ሰዎች የሚያጽናኑ ነበሩ። የይሖዋ ቀን እንደነዚህ ያሉትን አስጸያፊ ተግባራት ስለሚያስወግድ እነዚህ ታማኝ ሰዎች የይሖዋ ቀን በመቅረቡ የተነሳ ከመጨነቅ ይልቅ ተደስተው ነበር። እነዚህ ታማኝ ቀሪዎች የሚከተለውን ቀስቃሽ የይሖዋ ትእዛዝ ተከትለዋል፦ “መዓቴንና የቁጣዬን ትኩሳት ሁሉ አፈስስባቸው ዘንድ ፍርዴ አሕዛብን ለመሰብሰብ፣ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነውና፣ . . . ስለዚህ ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ፣ [“በጉጉት እየተጠባበቃችሁኝ ኑሩ፣” አዓት] ይላል እግዚአብሔር።”—ሶፎንያስ 3:8
17. የሶፎንያስ የፍርድ መልእክት በብሔራት ላይ መፈጸም የጀመረው መቼና እንዴት ነው?
17 ይህንን ማስጠንቀቂያ የሰሙ ሰዎች በተፈጠረው ሁኔታ አልተደናገጡም ነበር። ብዙዎቹ በሕይወት ቆይተው የሶፎንያስ ትንቢት ሲፈጸም አይተዋል። ባቢሎናውያን፣ ሜዶናውያን እና ሲዚያንስ ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱት ከሰሜን የመጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ኅብረት በመፍጠር በ632 ከዘአበ ነነዌን ወርረው አጥፍተዋት ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት እንዲህ ብለዋል፦ “በናቦፖላሳር የሚመራው የባቢሎናውያን ሠራዊት በሲያክስሬዝ ከሚመራው የሜዶናውያን ሠራዊትና በኮከሶስ ከሚኖሩት የሲዚያንስ ሠራዊት ጋር በመተባበር በሚያስደንቅ ፍጥነትና ያለምንም ችግር የከተማይቱን የሰሜን ቅጥር ተቆጣጠረ። . . . አሦር በአንድ ጊዜ ከታሪክ ማኅደር ተሰረዘች።” ሶፎንያስ ይህ እንደሚሆን በትክክል ተንብዮ ነበር።—ሶፎንያስ 2:13-15
18. (ሀ) ኢየሩሳሌም መለኮታዊ ቅጣት የደረሰባት እንዴት ነበር? ለምንስ? (ለ) ሶፎንያስ ሞዓብንና አሞንን በተመለከተ የተናገረው ትንቢት የተፈጸመው እንዴት ነበር?
18 ይሖዋን በጉጉት ይጠባበቁ የነበሩ አያሌ አይሁዳውያን ይሖዋ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ የወሰዳቸው የቅጣት እርምጃዎች ለማየት በቅተዋል። ሶፎንያስ ኢየሩሳሌምን በተመለከተ እንዲህ በማለት ተንብዮ ነበር፦ “ለዓመፀኛይቱና ለረከሰች ለአስጨናቂይቱም ከተማ ወዮላት! ድምፅን አልሰማችም፣ ተግሣጽንም አልተቀበለችም፤ በእግዚአብሔርም አልታመነችም፣ ወደ አምላክዋም አልቀረበችም።” (ሶፎንያስ 3:1, 2) ኢየሩሳሌም ታማኝ ሆና ባለመገኘቷ የተነሳ ሁለት ጊዜ በባቢሎናውያን ከመወረሯም በላይ በመጨረሻ በ607 ከዘአበ ጠፍታለች። (2 ዜና መዋዕል 36:5, 6, 11-21) የአይሁዳውያን ታሪክ ጸሐፊ የሆነው ጆሴፈስ እንደተናገረው ኢየሩሳሌም በጠፋች በአምስተኛው ዓመት ባቢሎናውያን በሞዓብና በአሞን ላይ ጦርነት ከፍተው ድል አድርገዋቸዋል። ከዚያም በተተነበየው መሠረት ሞዓባውያንና አሞናውያን ከምድረ ገጽ ጠፉ።
19, 20. (ሀ) ይሖዋ በጉጉት ይጠባበቁት የነበሩትን ሰዎች የካሳቸው እንዴት ነው? (ለ) እነዚህ ጉዳዮች እኛን የሚያሳስቡን ለምንድን ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ምን እንመረምራለን?
19 እነዚህና በዝርዝር የተቀመጡት ሌሎቹ የሶፎንያስ ትንቢቶች መፈጸማቸው ይሖዋን በጉጉት ይጠባበቁ የነበሩትን አይሁዶችና አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎችን እምነት አጠንክሯል። በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው ጥፋት ከተረፉት መካከል ኤርምያስ፣ ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክና የኢዮናዳብ ቤተሰብ የሆኑት ሬካባውያን ይገኙበታል። (ኤርምያስ 35:18, 19፤ 39:11, 12, 16-18) ይሖዋን በመጠባበቅ የቀጠሉት በግዞት ሥር የነበሩ ታማኝ አይሁዳውያንና ልጆቻቸው በ537 ከዘአበ ከባቢሎን ምርኮ ነፃ ከወጡትና ንጹሕ የሆነውን አምልኮ እንደገና ለማቋቋም ወደ ይሁዳ ከተመለሱት ደስተኛ ቀሪዎች መካከል መሆን ችለዋል።—ዕዝራ 2:1፤ ሶፎንያስ 3:14, 15, 20
20 ይህ ሁሉ ለዘመናችን ምን ትርጉም አለው? በሶፎንያስ ዘመን የነበረው ሁኔታ በዛሬው ጊዜ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ከሚፈጸሙት አስጸያፊ ነገሮች ጋር በብዙ መንገድ ይመሳሰላል። በተጨማሪም በዚያን ጊዜ አይሁዳውያን የነበሯቸው የተለያዩ አመለካከቶች በዛሬው ጊዜ በሰዎች ላይ አልፎ ተርፎም አንዳንድ ጊዜ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ሊኖር ከሚችለው ዝንባሌ ጋር ይመሳሰላል። የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጉዳዮች ይዳስሳል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የኢዮስያስ ልጆች በወቅቱ በጣም ትንንሽ ስለ ነበሩ ‘የንጉሡ ልጆች’ የሚለው አባባል በንጉሣዊ ቤተሰብ ውስጥ ያሉትን ልዑላን በሙሉ ያመለክታል።
ለክለሳ ያህል
◻ በሶፎንያስ ዘመን በይሁዳ የነበረው ሃይማኖታዊ ሁኔታ ምን ነበር?
◻ የሕዝቡ አለቆች ምን ሁኔታዎች ይንጸባረቁባቸው ነበር? የአብዛኛው ሕዝብ አመለካከትስ እንዴት ነበር?
◻ ብሔራት በይሖዋ ሕዝብ ላይ የታበዩት እንዴት ነው?
◻ ሶፎንያስ ለይሁዳና ለሌሎች ብሔራት ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል?
◻ ይሖዋን በጉጉት ይጠባበቁ የነበሩ ሰዎች የተካሱት እንዴት ነበር?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሞዓባውያን ጽላት የሞዓብ ንጉሥ የነበረው ሞሳ በጥንቷ እስራኤል ላይ የነቀፋ ቃላት እንደሰነዘረ ያረጋግጣል
[ምንጭ]
የሞዓባውያን ጽላት፦ Musée du Louvre, Paris
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሶፎንያስ ትንቢት ጋር በመስማማት የባቢሎናውያን ታሪክ የሰፈረበት ይህ የኪዩኒፎርም ጽላት ብሔራት ኅብረት ፈጥረው ነነዌን እንዳጠፉ ይናገራል
[ምንጭ]
የኪዩኒፎርም ጽላት፦ Courtesy of The British Museum