የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 37—ሐጌ
ጸሐፊው:- ሐጌ
የተጻፈበት ቦታ:- ኢየሩሳሌም
ተጽፎ ያለቀው:- ከክ. ል. በፊት በ520
ታሪኩ የሚሸፍነው ጊዜ:- 112 ቀናት (ከክ. ል. በፊት 520)
ስሙ ሐጌ ይባላል፤ ነቢይና “የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] መልእክተኛ” ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሰው ማን ነው? የተወለደውስ የት ነው? (ሐጌ 1:13) ሐጌ፣ ንዑሳን ነቢያት ከሚባሉት መካከል አሥረኛው ሲሆን አይሁዳውያን በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ከነበሩት ሦስት ነቢያቶች መካከል የመጀመሪያው ነበር። አብረውት ያገለገሉት ሌሎቹ ነቢያት ዘካርያስና ሚልክያስ ናቸው። ሐጌ የሚለው ስም (በዕብራይስጥ ቻጋይ) “በበዓል ቀን [የተወለደ]” ማለት ነው። ይህም በበዓል ቀን መወለዱን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
2 የአይሁዳውያን አፈ ታሪክ እንደሚለው ከሆነ ሐጌ በባቢሎን አገር ተወልዶ ከዘሩባቤልና ከሊቀ ካህኑ ከኢያሱ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ይመስላል። ሐጌ ከዘካርያስ ጋር አብሮ ያገለገለ ነቢይ ሲሆን በዕዝራ 5:1 እና 6:14 ላይ እንደተገለጸው ሁለቱም ነቢያት የግዞተኞቹ ልጆች ቤተ መቅደሱን መሥራታቸውን እንደገና እንዲጀምሩ ማበረታቻ ሰጥተዋል። ሐጌ፣ የይሖዋ ነቢይ ሆኖ ያገለገለው በሁለት መንገዶች ነው:- አይሁዳውያኑ በአምላክ ዘንድ የሚጠበቅባቸውን ሥራ እንዲያከናውኑ አሳስቧል፤ እንዲሁም ከሌሎች ትንቢቶች በተጨማሪ ብሔራት እንደሚናወጡም ተናግሯል።—ሐጌ 2:6, 7
3 ይሖዋ ሐጌን ለዚህ ተልእኮ የመረጠው ለምንድን ነው? ምክንያቱ ይህ ነበር:- በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ቂሮስ፣ አይሁዳውያኑ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው የይሖዋን ቤት እንዲገነቡ የሚፈቅድ አዋጅ አውጥቶ ነበር። ሐጌ ወደ ሕዝቡ የተላከው በ520 ከክርስቶስ ልደት በፊት ቢሆንም በዚህ ወቅት የቤተ መቅደሱ ግንባታ ገና ብዙ ይቀረዋል። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት አይሁዳውያኑ የጠላቶቻቸውን ተቃውሞ በመፍራታቸው፣ እነርሱ ራሳቸው ግድየለሾች በመሆናቸውና በፍቅረ ንዋይ በመጠመዳቸው ምክንያት ወደ አገራቸው የተመለሱበትን ዋና ዓላማ ዘንግተው ነበር።—ዕዝራ 1:1-4፤ 3:10-13፤ 4:1-24፤ ሐጌ 1:4
4 ዘገባው እንደሚያሳየው በ536 ከክርስቶስ ልደት በፊት የቤተ መቅደሱ መሠረት ከተጣለ ብዙም ሳይቆይ “የምድሪቱ ነዋሪዎች የይሁዳን ሕዝብ ተስፋ ማስቈረጥና ሥራውንም እንዳይቀጥሉ ማስፈራራት ጀመሩ። . . . ዕቅዶቻቸውን የሚያሰናክሉ መካሪዎችን በገንዘብ ገዙባቸው።” (ዕዝራ 4:4, 5) በመጨረሻም በ522 ከክርስቶስ ልደት በፊት አይሁዳዊ ያልሆኑት እነዚህ ተቃዋሚዎቻቸው ሥራው እንዲቆም የሚያዝዝ ሕጋዊ እገዳ እንዲጣል አደረጉ። ሐጌ ትንቢቱን መናገር የጀመረው የፋርስ ንጉሥ ዳርዮስ ሂስታስፒስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ማለትም በ520 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን እርሱ የተናገረው መልእክትም አይሁዳውያን ቤተ መቅደሱን የመገንባቱን ሥራ እንደገና እንዲጀምሩ አበረታቷቸዋል። በዚህ ጊዜ በአቅራቢያቸው የሚገኙት አገረ ገዢዎች ዳርዮስ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥበት የሚጠይቅ ደብዳቤ ላኩለት። ዳርዮስም ቂሮስ ያስተላለፈውን ውሳኔ እንደገና በማጽደቅ አይሁዳውያኑ ከጠላቶቻቸው ጥቃት እንዳይደርስባቸው ተከላከለላቸው።
5 የሐጌ ትንቢት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ስለመሆኑ በአይሁዳውያን ዘንድ ጥያቄ ተነስቶ አያውቅም። በዕዝራ 5:1 ላይ ሐጌ “በእስራኤል አምላክ ስም” እንደሚተነብይ መጠቀሱና ዕዝራ 6:14ም ይህንን የሚደግፍ ሐሳብ መያዙ ተጨማሪ ማስረጃ ይሆናል። ጳውሎስ በዕብራውያን 12:26 ላይ “አሁን ግን፣ ‘ምድርን ብቻ ሳይሆን፣ ሰማያትንም አንድ ጊዜ ደግሜ አናውጣለሁ’ ብሎ ቃል ገብቶአል” በማለት ከሐጌ መጽሐፍ መጥቀሱ የሐጌ ትንቢት ‘የአምላክ መንፈስ ካለባቸው ቅዱሳት መጻሕፍት’ አንዱ መሆኑን ያረጋግጣል።—ሐጌ 2:6
6 የሐጌ ትንቢት በ112 ቀናት ውስጥ የተነገሩ አራት መልእክቶችን ይዟል። የአጻጻፉ ስልት ቀላልና ቀጥተኛ ሲሆን በተለይ ደግሞ የይሖዋን ስም ጎላ አድርጎ መጥቀሱ ትኩረት የሚሰጠው ነው። ሐጌ፣ በመጽሐፉ ውስጥ በሚገኙት 38 ቁጥሮች ውስጥ 35 ጊዜ በይሖዋ ስም የተጠቀመ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 14 ጊዜ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ” [NW] በሚለው አገላለጽ ተጠቅሟል። ይህ ነቢይ መልእክቶቹን ከይሖዋ መቀበሉን በተመለከተ ምንም ጥርጣሬ እንዳይኖር እንዲህ የሚል ሐሳብ አስፍሯል:- “የእግዚአብሔር መልእክተኛ ሐጌ፣ ይህን የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ ‘እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ’ ይላል እግዚአብሔር።”—1:13
7 ይህ በአምላክ ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ወቅት ሲሆን የሐጌ ሥራም ከፍተኛ ጠቀሜታ አበርክቷል። ሐጌ በነቢይነት የተሰጠውን ኃላፊነት ከመወጣትም ሆነ ለአይሁዶች ኃይለኛ የሆነውን መልእክት ከመንገር ወደኋላ አላለም። አይሁዳውያን የተሰጣቸውን ሥራ ለሌላ ጊዜ ማስተላለፋቸውን አቁመው ለሥራው የሚነሱበት ወቅት መሆኑን በግልጽ ነግሯቸዋል። ከይሖዋ እጅ ማንኛውንም ዓይነት ብልጽግና ለማግኘት የሚፈልጉ ከሆነ የይሖዋን ቤት የሚያድሱበትና ንጹሕ አምልኮን እንደገና የሚያቋቁሙበት ጊዜ አሁን ነው። የሐጌ መጽሐፍ ዋነኛ መልእክት፣ አንድ ሰው የይሖዋን በረከት ማግኘት የሚፈልግ ከሆነ እውነተኛውን አምላክ ማገልገልና ይሖዋ ያዘዘውን ሥራ ማከናወን እንዳለበት የሚገልጽ ነው።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
13 ይሖዋ በሐጌ በኩል ያስተላለፋቸው አራት መልእክቶች በዚያን ጊዜ ለነበሩት አይሁዳውያን ጠቃሚ ነበሩ። ሕዝቡ ለሥራው እንዲነሱ በመበረታታታቸው በእስራኤል እውነተኛ አምልኮ እንዲስፋፋ የሚያደርገው ቤተ መቅደስ ግንባታ በአራት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ተጠናቀቀ። (ዕዝራ 6:14, 15) ይሖዋም ቅንዓት የተሞላበት እንቅስቃሴያቸውን ባርኮላቸዋል። የፋርስ ንጉሥ ዳርዮስ የቤተ መንግሥት መዛግብቱን መርምሮ ቂሮስ ያስተላለፈውን ውሳኔ እንደገና ያጸደቀው የቤተ መቅደሱ ግንባታ እየተከናወነ ባለበት ጊዜ ነበር። በመሆኑም የቤተ መቅደሱ ሥራ እንዲጠናቀቅ የፋርስ መንግሥት ድጋፍ አድርጓል።—ዕዝራ 6:1-13
14 የሐጌ ትንቢት ለጊዜያችን የሚሆን ጥበብ ያዘለ ምክርም ይዟል። እንዴት? አንደኛ ነገር፣ ማንኛውም ፍጡር የይሖዋን አምልኮ ከግል ጥቅሞቹ ማስቀደሙ አስፈላጊ መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። (ሐጌ 1:2-8፤ ማቴ. 6:33) ከዚህም በላይ ራስ ወዳድ መሆን ለውድቀት እንደሚጋብዝና ቁሳዊ ሀብትን ማሳደድ ከንቱ መሆኑን እንዲሁም ባለጸጋ የሚያደርገው የይሖዋ ሰላምና በረከት እንደሆነ የሚገልጽ ነጥብ ያስተላልፋል። (ሐጌ 1:9-11፤ 2:9፤ ምሳሌ 10:22) በተጨማሪም አንድ ሰው ለአምላክ የሚያቀርበው አገልግሎት ንጹሕና ከሙሉ ልብ የመነጨ እንዲሁም በርኩስ ድርጊቶች ያልተበከለ ካልሆነ በቀር አምላክን ማገልገሉ ብቻ ንጹሕ እንደማያደርገው ጎላ አድርጎ ይገልጻል። (ሐጌ 2:10-14፤ ቆላ. 3:23፤ ሮሜ 6:19) የሐጌ መጽሐፍ፣ የአምላክ አገልጋዮች “የቀድሞውን መልካም ጊዜ” እያስታወሱ አሉታዊ አመለካከት ከመያዝ ይልቅ ስለ ወደፊቱ በማሰብ ‘መንገዳቸውን ልብ ማለት’ እንዲሁም ለይሖዋ ክብር ለማምጣት መጣር እንዳለባቸው ያሳያል። እንዲህ ካደረጉ ይሖዋ ከእነርሱ ጋር ይሆናል።—ሐጌ 2:3, 4፤ 1:7, 8, 13፤ ፊልጵ. 3:13, 14፤ ሮሜ 8:31
15 አይሁዳውያን ቤተ መቅደሱን መገንባት ሲጀምሩ የይሖዋን ሞገስና ብልጽግና አገኙ። እንቅፋቶቹ ሁሉ ተወገዱ። ሥራውም በጥሩ ጊዜ ተጠናቀቀ። በድፍረትና በቅንዓት ይሖዋን ማገልገል ሁልጊዜም ይክሳል። ፊት ለፊት የሚያጋጥሙንንም ሆነ ያጋጥሙን ይሆናል ብለን የምናስባቸውን ችግሮች ጠንካራ እምነት በማዳበር ማሸነፍ ይቻላል። ‘ለይሖዋ ቃል’ ታዛዥ መሆን ውጤቱ ያማረ ነው።—ሐጌ 1:1 NW
16 ይሖዋ ‘ሰማያትንና ምድርን እንደሚያናውጥ’ ስለ ተናገረው ትንቢትስ ምን ማለት ይቻላል? ሐዋርያው ጳውሎስ ሐጌ 2:6 የሚኖረውን ተፈጻሚነት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “አሁን ግን፣ ‘ምድርን ብቻ ሳይሆን፣ ሰማያትንም አንድ ጊዜ ደግሜ አናውጣለሁ’ ብሎ ቃል ገብቶአል። አንድ ጊዜ ‘ደግሜ’ የሚለው ቃል የሚያመለክተው የማይናወጡት ጸንተው ይኖሩ ዘንድ፣ የሚናወጡት ይኸውም የተፈጠሩት የሚወገዱ መሆናቸውን ነው። ስለዚህ ከቶ የማይናወጥ መንግሥት ስለምንቀበል እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ደግሞም ደስ በሚያሰኘው መንገድ በአክብሮትና በፍርሀት እናምልከው፤ አምላካችን የሚያጠፋ እሳት ነውና።” (ዕብ. 12:26-29) ሐጌ፣ መናወጡ የሚከናወነው ‘የመንግሥታትን ዙፋን ለመገልበጥና የባዕዳንን መንግሥታት ኀይል ለማጥፋት’ እንደሆነ ያመለክታል። (ሐጌ 2:21, 22) ጳውሎስ ይህን ትንቢት ሲጠቅስ ከእነዚህ መንግሥታት በተቃራኒ የአምላክ መንግሥት “የማይናወጥ” መሆኑን ተናግሯል። የዚህን መንግሥት ተስፋ እያሰብን ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ ‘በርትተን እንሥራ።’ ይሖዋ በምድር ላይ የሚገኙትን መንግሥታት ከመገልበጡ በፊት ውድ የሆነን ነገር እንደሚያናውጥና ይህም ሀብት ከእነርሱ መካከል ወጥቶ ለመዳን እንደሚበቃ ልብ እንበል። “‘ሕዝቦችን ሁሉ አናውጣለሁ፤ የሕዝቦችም ሀብት ሁሉ ወደዚህ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር።”—2:4, 7