አምላክ በእርግጥ ስለ አንተ ያስባል?
እንደምትወደድ ይሰማሃል? ወይስ ስለ አንተ የሚጨነቅ እንደሌለ የሚሰማህ ጊዜ አለ? ይህ የምንኖርበት ዓለም በሩጫ የተሞላና ራስ ወዳድ በመሆኑ እዚህ ግባ የምትባል ሰው እንዳልሆንክና ማንም ከመጤፍ እንደማይቆጥርህ ቢሰማህ የሚያስገርም አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የእኛን ዘመን አስመልክቶ እንደሚናገረው፣ በአሁኑ ጊዜ በርካታ ሰዎች ስለራሳቸው ብቻ ስለሚያስቡ ለሌሎች ሰዎች አሳቢነት ማሳየት የሚባል ነገር እየጠፋ ሄዷል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2
ሰዎች ዕድሜያቸው፣ ባሕላቸው፣ ቋንቋቸው ወይም ዘራቸው ምንም ይሁን ምን የመውደድም ሆነ የመወደድ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት በሰውነታችን ውስጥ ያለው የነርቭ ሥርዓት የተሠራው በተለይ ፍቅርንና አሳቢነትን እንዲለይ ተደርጎ ነው። ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ በሌሎች የመወደድና የመደነቅ ፍላጎት እንዳለን ከማንም በተሻለ ያውቃል። ይሖዋ ለእሱ ውድ እንደሆንክ ሲናገር ብትሰማ ምን ስሜት ያድርብሃል? ይህን አስተያየት ከዚህ በፊት ከሰማኸው ከየትኛውም አስተያየት አስበልጠህ እንደምትመለከተው ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና ይሖዋ ፍጽምና ለጎደላቸው የሰው ልጆች ትኩረት እንደሚሰጥ እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን? በግለሰብ ደረጃ ስለ እኛ ያስባል? ከሆነስ አንድ ሰው በእሱ ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው?
አምላክ ያስብልናል
የዛሬ 3,000 ዓመት ገደማ ፈሪሃ አምላክ ያለው አንድ መዝሙራዊ በከዋክብት የተሞላው ሰማይ ያለውን ውበትና ግርማ ሞገስ ከተመለከተ በኋላ ልቡ በአድናቆት ተሞልቶ ነበር። በዚያን ወቅት ይህ መዝሙራዊ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ከዋክብት የፈጠረ አምላክ ከሁሉ የላቀ ግርማ ሞገስ እንዳለው ተረድቶ ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። መዝሙራዊው የይሖዋን ታላቅነት ከሰው ኢምንትነት ጋር ካወዳደረ በኋላ የይሖዋን ፍቅራዊ አሳቢነት በተመለከተ እንዲህ ሲል በአድናቆት ተናግሯል፦ “የጣቶችህ ሥራ የሆኑትን ሰማያትን ስመለከት፣ አንተ የሠራሃቸውን ጨረቃንና ከዋክብትን፣ በሐሳብህ ቦታ ትሰጠው ዘንድ ሟች የሆነ ሰው ምንድን ነው? ትንከባከበውስ ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?” (መዝሙር 8:3, 4 NW) አንድ ሰው ከሁሉ የላቀው አምላክ ፍጽምና ከጎደላቸው የሰው ልጆች በጣም ርቆ እንደሚገኝ ወይም ለእነሱ ትኩረት ለመስጠት ጊዜ እንደሌለው ይሰማው ይሆናል። መዝሙራዊው ግን እኛ የሰው ልጆች ታላቅ ከሆነው አምላክ ጋር ስንወዳደር እዚህ ግባ የማንባልና ሟቾች እንደሆንን ቢያውቅም አምላክ ከፍ ያለ ግምት እንደሚሰጠን ተገንዝቦ ነበር።
አንድ ሌላ መዝሙራዊ ደግሞ “እግዚአብሔር በሚፈሩት፣ በምሕረቱ በሚታመኑትም ይደሰታል” በማለት የተሰማውን ተናግሯል። (መዝሙር 147:11) በእነዚህ ሁለት መዝሙሮች ላይ የተገለጸው ሐሳብ ልብ የሚነካ ነው። እጅግ ታላቅ የሆነው ይሖዋ የሰዎችን ሁኔታ በማወቅ ብቻ አይወሰንም። ከዚህ ይልቅ ‘ይንከባከባቸዋል’ እንዲሁም ‘ደስ ይሰኝባቸዋል።’
በዘመናችን የሚፈጸሙ ክንውኖችን አስመልክቶ የሚናገር አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ይህን ሐቅ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ይሖዋ በነቢዩ ሐጌ በኩል የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩ ሥራ በዓለም ዙሪያ እንደሚከናወን ጠቁሟል። ውጤቱስ ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ሥራው ካስገኛቸው ውጤቶች መካከል አንዱን ሲናገር “የሕዝቦችም ሀብት ሁሉ ወደዚህ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ” ይላል።—ሐጌ 2:7
ታዲያ ከአሕዛብ ሁሉ የሚሰበሰበው “ሀብት” ምንድን ነው? ቁሳዊ ሀብት ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው። (ሐጌ 2:8) የይሖዋን ልብ ደስ ሊያሰኝ የሚችለው ብርና ወርቅ አይደለም። ይሖዋ ደስ የሚሰኘው ፍጽምና የሚጎድላቸው ቢሆንም እንኳ በፍቅር ተነሳስተው እሱን በሚያመልኩ ሰዎች ነው። (ምሳሌ 27:11) ከአሕዛብ ሁሉ የሚሰበሰብ “ሀብት” የተባሉት ለእሱ ክብር የሚያመጡት እነዚህ ሰዎች ናቸው፤ ይሖዋ በሙሉ ልባቸው በቅንዓት የሚያከናውኑትን አገልግሎት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። አንተስ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ነህ?
ኢምንት የሆኑትና ፍጽምና የሚጎድላቸው የሰው ልጆች በጽንፈ ዓለሙ ታላቅ ፈጣሪ ዘንድ እንደ ውድ ሀብት ይታያሉ የሚለው ሐሳብ የማይታመን ሊመስል ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይህ ሐቅ አምላክ ወደ እሱ እንድንቀርብ ያቀረበልንን ሞቅ ያለ ግብዣ እንድንቀበል ሊያነሳሳን ይገባል።—ኢሳይያስ 55:6፤ ያዕቆብ 4:8
‘አንተ እጅግ የተወደድህ ነህ’
ነቢዩ ዳንኤል ዕድሜው ገፍቶ እያለ አንድ ምሽት የሚያስገርም ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። ዳንኤል እየጸለየ ሳለ አንድ ለየት ያለ እንግዳ በድንገት መጣ። የእንግዳው ስም ገብርኤል ነው። ዳንኤል ቀደም ሲል ከዚህ እንግዳ ጋር ተገናኝቶ ስለነበር የይሖዋ መልአክ መሆኑን አውቋል። ገብርኤል ለምን በድንገት እንደመጣ እንዲህ በማለት ገለጸለት፦ “ዳንኤል ሆይ፤ አሁን ጥበብንና ማስተዋልን ልሰጥህ መጥቻለሁ። . . . አንተ እጅግ የተወደድህ [ነህ]።”—ዳንኤል 9:21-23
በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ከይሖዋ መላእክት አንዱ ዳንኤልን “እጅግ የተወደድህ ዳንኤል ሆይ” በማለት ጠርቶት ነበር። ከዚያም መልአኩ ዳንኤልን ለማበረታታት “እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ፤ አትፍራ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎታል። (ዳንኤል 10:11, 19) ዳንኤል ሦስት ጊዜ “እጅግ የተወደድህ” ተብሎ ተጠርቷል። “እጅግ የተወደድህ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው” አልፎ ተርፎም “አብልጦ የሚወደድ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል።
ዳንኤል ቀድሞውንም ቢሆን ከአምላኩ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳለው እንዲሁም ይሖዋ በቅንዓት የሚያከናውነውን አገልግሎት እንደሚቀበለው ተረድቶ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። አምላክ በመላእክቱ አማካኝነት ለእሱ ያለውን ታላቅ ፍቅር ሲገልጽለት ደግሞ በጣም ተበረታቶ ሊሆን እንደሚችል እርግጠኞች ነን። ዳንኤል “አበርትተኸኛል” የሚል መልስ መስጠቱ የሚያስደንቅ አይደለም።—ዳንኤል 10:19
ይሖዋ ለታማኙ ነቢይ ስለነበረው ጥልቅ አሳቢነት የሚናገረው ይህ ልብን ደስ የሚያሰኝ ዘገባ በአምላክ ቃል ውስጥ እንዲሰፍር የተደረገው ለእኛ ጥቅም ሲባል ነው። (ሮም 15:4) ዳንኤል በተወው ምሳሌ ላይ ማሰላሰላችን በሰማይ በሚገኘው አፍቃሪ አባታችን ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን ምን ማድረግ እንደምንችል እንድንገነዘብ ያደርገናል።
ዘወትር የአምላክን ቃል አጥና
ዳንኤል ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት ያጠና ነበር። “እኔ ዳንኤል . . . የኢየሩሳሌም[ን] መፈራረስ . . . ከቅዱሳት መጻሕፍት አስተዋልሁ” ብሎ እሱ ራሱ ከጻፈው ሐሳብ ይህን መረዳት እንችላለን። (ዳንኤል 9:2) በጊዜው ከነበሩት መጻሕፍት መካከል ሙሴ፣ ዳዊት፣ ሰለሞን፣ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል እና ሌሎች ነቢያት በመንፈስ መሪነት የጻፏቸው ጽሑፎች ሳይገኙበት አይቀሩም። ዳንኤል የተለያዩ ጥቅልሎችን በዙሪያው አስቀምጦ፣ ተመስጦ ሲያነብና እውነተኛው አምልኮ በኢየሩሳሌም እንደገና ስለመቋቋሙ የሚናገሩትን ትንቢቶች እርስ በርስ ሲያመሣክር በዓይነ ሕሊናችን መሳል እንችላለን። ዳንኤል ጸጥ ባለውና በሰገነት ላይ በሚገኘው ክፍል ውስጥ ተቀምጦ፣ ትንቢቶቹ ምን ትርጉም እንዳላቸው በጥልቅ እንዳሰላሰለ ምንም ጥርጥር የለውም። ትርጉም ባለው መንገድ ያደረገው ጥናት እምነቱን አጠናክሮለታል፤ እንዲሁም ወደ ይሖዋ እንዲቀርብ ረድቶታል።
በተጨማሪም ዳንኤል የአምላክን ቃል ማጥናቱ ባሕርይውን እንዲያሻሽል የረዳው ከመሆኑም በላይ በመላ ሕይወቱ ላይ ለውጥ አምጥቷል። ወጣት ሳለ ያገኘው ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ አምላክ አመጋገብን በተመለከተ የሰጠውንና በወቅቱ ይሠራ የነበረውን ሕግ ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ እንዲያደርግ ረድቶት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። (ዳንኤል 1:8) ከጊዜ በኋላ ደግሞ አምላክ ለባቢሎን መሪዎች የሰጠውን መልእክት በድፍረት አውጇል። (ምሳሌ 29:25፤ ዳንኤል 4:19-25፤ 5:22-28) ዳንኤል በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው ትጉ፣ ሐቀኛና ታማኝ በመሆኑ ነበር። (ዳንኤል 6:4) ከዚህም በላይ የራሱን ሕይወት ለማዳን ሲል አቋሙን ከማላላት ይልቅ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ታምኗል። (ምሳሌ 3:5, 6፤ ዳንኤል 6:23) ዳንኤል በአምላክ ዓይን “እጅግ የተወደደ” መሆኑ ምንም አያስደንቅም!
ከአንዳንድ ሁኔታዎች አንጻር ሲታይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግ ከዳንኤል ይልቅ ለእኛ በጣም ቀላል ነው። ግዙፍ የሆኑት ጥቅልሎች፣ አመቺ በሆነ መንገድ በተዘጋጁ መጻሕፍት ተተክተዋል። በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የዳንኤል ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እንዴት እንዳገኙ የሚናገሩትን ዘገባዎች ጨምሮ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ አለን። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና ምርምር ለማድረግ የሚረዱ በርካታ መሣሪያዎች አሉን።a እነዚህን መሣሪያዎች ጥሩ አድርገህ እየተጠቀምክባቸው ነው? ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን የምታነብበትና የምታሰላስልበት ቋሚ ፕሮግራም አለህ? ከሆነ ዳንኤል ያገኘው ዓይነት ውጤት ታገኛለህ። ጠንካራ እምነት መገንባት እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና ማጠናከር ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደማይለይህ የሚያረጋግጥልህ ከመሆኑም በላይ ለሕይወትህ አስተማማኝ መመሪያ ይሆንልሃል።
በጽናት ጸልይ
ዳንኤል የጸሎት ሰው ነበር። ተገቢ የሆነውን ነገር ሁሉ አምላክን ከመጠየቅ ወደኋላ አይልም ነበር። ወጣት ሳለ የባቢሎን ንጉሥ የሆነውን የናቡከደነፆርን ሕልም ካልፈታ እንደሚገደል የሚገልጽ ማስፈራሪያ ደርሶት ነበር። በዚህ ጊዜ ዳንኤል ምንም ሳያቅማማ እንዲረዳውና እንዲጠብቀው ይሖዋን ተማጽኗል። (ዳንኤል 2:17, 18) ከዓመታት በኋላ ይህ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ፍጽምና የሚጎድለው መሆኑን በትሕትና በመረዳት የራሱንም ሆነ የሕዝቡን ኃጢአት የተናዘዘ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ ይቅር እንዲላቸው ለምኗል። (ዳንኤል 9:3-6, 20) በመንፈስ መሪነት ለእሱ የተነገሩትን ሐሳቦች መረዳት ባቃተው ጊዜ የአምላክን እርዳታ ጠይቋል። በአንድ ወቅት ለዳንኤል ተጨማሪ ማስተዋል ለመስጠት ወደ እሱ የመጣ አንድ መልአክ “ቃልህ ተሰምቶአል” በማለት አረጋግጦለታል።—ዳንኤል 10:12
ታማኝ የሆነው ዳንኤል ለአምላክ ልመና በማቅረብ ብቻ አልተወሰነም። ዳንኤል 6:10 “ቀድሞ ያደርግ እንደ ነበረው በቀን ሦስት ጊዜ ተንበርክኮ ጸለየ፤ አምላኩንም አመሰገነ” በማለት ይናገራል። ዳንኤል ይሖዋን ለማመስገንና ለማወደስ የሚያስችሉትን ምክንያቶች ይፈልግ ነበር። ይህንንም ዘወትር ያደርግ ነበር። ጸሎት የአምልኮው ዋና ክፍል ስለነበር መጸለዩ ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል በሆነበት ጊዜም እንኳ እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ አላለም። በይሖዋ እንዲወደድ ያደረገው ይህ ጽናቱ እንደሆነ ጥርጥር የለውም።
የጸሎት መብት እንዴት ያለ ታላቅ ስጦታ ነው! በሰማይ ወደሚኖረው አባትህ ሳትጸልይ አንድም ቀን እንዲያልፍብህ አትፍቀድ። ላሳየህ ጥሩነት እሱን ማመስገንና ማወደስ እንዳለብህ አትርሳ። ጭንቀትህንና የሚያሳስቡህን ነገሮች በነፃነት ንገረው። አምላክ ለጠየቅከውና ለለመንከው ነገር እንዴት ምላሽ እንደሚሰጥህ ተከታተል፤ እንዲሁም ምስጋናህን በጸሎት ግለጽ። ረጅም ጸሎት ጸልይ። በጸሎት አማካኝነት እንዲህ ልባችንን ለይሖዋ ስንከፍት እሱ በግለሰብ ደረጃ እንደሚወደን ይሰማናል። ይህ ደግሞ ‘በጽናት ለመጸለይ’ ይበልጥ ያነሳሳናል።—ሮም 12:12
የይሖዋን ስም አስከብር
አንድ ሰው ስለ ራሱ ብቻ የሚያስብ ከሆነ የመሠረተው ጓደኝነት ሊጠናከር አይችልም። ከይሖዋ ጋር ባለን ግንኙነትም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ዳንኤል ይህን ሐቅ ተገንዝቦ ነበር። የይሖዋን ስም የማስከበሩ ጉዳይ ምን ያህል ያሳስበው እንደነበር እንመልከት።
አምላክ የናቡከደነፆርን ሕልምና ትርጓሜውን በመግለጽ ለጸሎቱ ምላሽ በሰጠው ጊዜ ዳንኤል “ጥበብና ኀይል የእርሱ ነውና፣ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ” ብሏል። ከዚያም ለናቡከደነፆር ሕልሙንና ትርጓሜውን ባሳወቀበት ወቅት ‘ምስጢርን የሚገልጠው’ ይሖዋ ብቻ እንደሆነ ጎላ አድርጎ በመግለጽ በተደጋጋሚ ጊዜ ክብሩን ለእሱ ሰጥቷል። በተጨማሪም ይቅር እንዲላቸውና ነፃ እንዲያወጣቸው አምላክን በተማጸነ ጊዜ ዳንኤል “ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአል” በማለት ጸልዮአል።—ዳንኤል 2:20, 28፤ 9:19
በዚህ ረገድ የዳንኤልን ምሳሌ የምንከተልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉን። በምንጸልይበት ጊዜ የአምላክ ‘ስም የመቀደሱ’ ጉዳይ እንደሚያሳስበን መግለጽ እንችላለን። (ማቴዎስ 6:9, 10) እንዲሁም ምግባራችን የይሖዋን ቅዱስ ስም የሚያስነቅፍ እንዳይሆን እንጠነቀቃለን። በሌላ በኩል ደግሞ ስለ መንግሥቱ ምሥራች የተማርነውን ለሌሎች በመናገር ምንጊዜም የይሖዋን ስም እናስከብራለን።
በዙሪያችን ባለው ዓለም ውስጥ ፍቅርና አሳቢነት እየጠፋ መሆኑ የሚያሳዝን ነው። እኛ ግን ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለአገልጋዮቹ እንደሚያስብ ማወቃችን በእጅጉ ያጽናናል። መዝሙራዊው እንደገለጸው ይሖዋ “በሕዝቡ ደስ ይለዋልና፤ የዋሃንንም በማዳኑ ውበት ያጐናጽፋል።”—መዝሙር 149:4
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ጠቃሚ በሆነ መንገድ ለማንበብ የሚያስችሉ በርካታ የምርምርና የጥናት መሣሪያዎችን አዘጋጅተዋል። እነዚህን መሣሪያዎች ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ማንኛውንም የይሖዋ ምሥክር መጠየቅ ትችላለህ።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አምላክ፣ ዳንኤልን እንዲያበረታታው መልአኩ ገብርኤልን በመላክ ለእሱ ያለውን ፍቅር ገልጿል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ዳንኤል በትጋት ማጥናቱና መጸለዩ የተሻለ ባሕርይ እንዲያዳብርና በአምላክ የተወደደ እንዲሆን አድርጎታል