የይሖዋ ደስታ ምሽጋችን ነው
“ዛሬ ለጌታችን የተቀደሰ ቀን ነው፤ የይሖዋም ደስታ ምሽጋችሁ ነውና አትዘኑ።”—ነህምያ 8:10 አዓት
1, 2. (ሀ) ምሽግ ምንድን ነው? (ለ) ዳዊት ይሖዋን መጠጊያው እንዳደረገ ያሳየው እንዴት ነው?
ይሖዋ ተወዳዳሪ የሌለው ምሽግ ነው። ምሽግ ምንድን ነው? ከጥቃት ከለላ የሚገኝበት ወይም ሕይወትን ማትረፍ የሚቻልበት የተጠናከረ መሸሸጊያ ቦታ ነው። በጥንት እስራኤል ዘመን የነበረው ዳዊት አምላክን እንደ ምሽጉ አድርጎ ተመልክቶታል። ለምሳሌ ያህል ዳዊት “ከሳኦል እጅና ከጠላቶቹ ሁሉ እጅ እግዚአብሔር ባዳነው ቀን” ለልዑሉ አምላክ የዘመረውን መዝሙር ተመልከት።—መዝሙር 18 መግቢያው ላይ ያለው ሐሳብ።
2 ዳዊት ያንን ቀስቃሽ መዝሙር የከፈተው በሚከተሉት ቃላት ነው፦ “አቤቱ ጉልበቴ ሆይ፣ እወድድሃለሁ። እግዚአብሔር ዓለቴ፣ አምባዬ [ምሽጌ]፣ መድኃኒቴ፣ አምላኬ፣ በእርሱም የምተማመንበት ረዳቴ፣ መታመኛዬና የደህንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው።” (መዝሙር 18:1, 2) አላግባብ የተወነጀለውና ንጉሥ ሳኦል ያሳድደው የነበረው ጻድቁ ዳዊት አንድ ሰው ከሆነ አደጋ ለማምለጥ ወደ ተመሸገ ቦታ እንደሚሸሽ ሁሉ እርሱም ይሖዋን መጠጊያው አድርጓል።
3. በዕዝራ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን ‘ታላቅ ደስታ’ ያገኙት ለምን ነበር?
3 ይሖዋ የሚሰጠው ደስታ ንጹሕ አቋማቸውን ሳያጎድፉ በመንገዱ ለሚመላለሱ ምን ጊዜም የማይከዳ ምሽግ ነው። (ምሳሌ 2:6–8፤ 10:29) እርግጥ ሰዎች አምላክ የሚሰጠውን ደስታ ለማግኘት መለኮታዊውን ፈቃድ ማድረግ አለባቸው። በዚህ ረገድ በ468 ከዘአበ በኢየሩሳሌም ምን እንደተፈጸመ ተመልከት። ጸሐፊው ዕዝራና ሌሎች ሕጉን ሊገባ በሚችል መንገድ በማንበብ ለሕዝቡ እውቀትን ይሰጡ ነበር። ከዚያም ሕዝቡ እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ተሰጣቸው፦ “ሂዱ፣ የሰባውንም ብሉ፣ ጣፋጩንም ጠጡ፣ ለእነዚያም ላልተዘጋጀላቸው እድል ፈንታቸውን ስደዱ፤ ዛሬ ለጌታችን የተቀደሰ ቀን ነው፤ የእግዚአብሔርም ደስታ ኃይላችሁ [“ምሽጋችሁ” አዓት] ነውና አትዘኑ።” አይሁዳውያን ያገኙትን እውቀት በሥራ ሲያውሉና አስደሳች የዳስ በዓል ሲያደርጉ ‘ታላቅ ደስታ’ ሆነ። (ነህምያ 8:1–12) ‘የይሖዋን ደስታ ምሽጋቸው ያደረጉ’ ለይሖዋ አምልኮና አገልግሎት የሚውል ብርታት አገኙ። እነዚህ ሕዝቦች የይሖዋ ደስታ ምሽጋቸው እንደነበረ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉትም የአምላክ ሕዝቦች ደስተኛ ይሆናሉ ብለን መጠበቅ ይኖርብናል። ታዲያ በዛሬው ጊዜ ለደስታ ምክንያት የሆኗቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
‘ፈጽሞ ደስ ይበልህ’
4. ለይሖዋ ሕዝቦች የደስታ ምንጭ የሆነው አንዱ ዐቢይ ነገር ምንድን ነው?
4 አንዱ ለደስታ ጉልህ ምክንያት የሆነው ነገር ይሖዋ ያደረገልን አንድ ላይ መሰብሰብ የሚቻልበት ዝግጅት ነው። እስራኤላውያን ያከናውኗቸው የነበሩት ዓመታዊ በዓላት ልባቸውን ደስ ያሰኟቸው እንደነበረ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች ትልልቅ ስብሰባዎችም በዛሬው ጊዜ ደስታ ይሰጧቸዋል። የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ተብሎ ነበር፦ “አምላክህ እግዚአብሔር በፍሬህ ሁሉ በእጅህም ሥራ ሁሉ ይባርክሃልና እግዚአብሔር በመረጠው ሥፍራ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰባት ቀን በዓል [የዳስ በዓል] ታደርጋለህ፤ አንተም ፈጽሞ ደስ ይልሃል።” (ዘዳግም 16:13–15) አዎን፣ አምላክ ‘ፈጽሞ ደስ እንዲላቸው’ ፈልጎ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እሱን መሰል የሆኑትን አማኞች “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፣ ደስ ይበላችሁ” በማለት አጥብቆ ስለመከራቸው ለክርስቲያኖችም ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም።—ፊልጵስዩስ 4:4
5. (ሀ) ደስታ ምንድን ነው? ክርስቲያኖች ሊያገኙት የሚችሉትስ እንዴት ነው? (ለ) ፈተናዎች ቢኖሩም እንኳ ደስታ ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው?
5 ይሖዋ ደስተኞች እንድንሆን ስለሚፈልግ የቅዱስ መንፈሱ ፍሬ የሆነውን ደስታ ይሰጠናል። (ገላትያ 5:22, 23) ደስታስ ምንድን ነው? ደስታ ጥሩ ነገርን አገኛለሁ ብሎ በማሰብ ወይም በማግኘት የሚፈጠር ጥሩ ስሜት ነው። ደስታ እውነተኛ እርካታ ነው፤ አልፎ ተርፎም እጅግ መፈንደቅ ማለት ሊሆን ይችላል። ይህ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ በፈተና ጊዜ ደግፎ ያቆመናል። “እርሱ [ኢየሱስ] ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” (ዕብራውያን 12:2) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወንድሞቼ ሆይ፣ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት” ሲል ጽፏል። ይሁን እንጂ አንድን ፈተና በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ ቢገባንስ? በዚህ ጊዜ ፈተናውን ለመወጣት የሚያስችል ጥበብ እንድናገኝ ሙሉ እምነት ኖሮን መጸለይ እንችላለን። ከሰማያዊ ጥበብ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰዳችን የይሖዋን ደስታ ሳናጣ ችግሮችን ለመፍታት ወይም የማያቋርጡ ፈተናዎችን ተቋቁመን እንድናሸንፍ ይረዳናል።—ያዕቆብ 1:2–8
6. በደስታና በእውነተኛ አምልኮ መካከል ምን ዝምድና አለ?
6 ይሖዋ የሚሰጠን ደስታ እውነተኛ አምልኮን እንድናስፋፋ ያበረታናል። በነህምያና በዕዝራ ዘመን የተፈጸመው ሁኔታም እንደዚሁ ነው። የይሖዋን ደስታ ምሽጋቸው ያደረጉ በዚያ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን የእውነተኛ አምልኮን ጥቅሞች ለማራመድ ብርታት አግኝተው ነበር። የይሖዋን አምልኮ ሲያስፋፉ ደግሞ ደስታቸው ይጨምር ነበር። በዛሬውም ጊዜ እንደዚሁ ነው። የይሖዋ አምላኪዎች እንደ መሆናችን መጠን ታላቅ ደስታ እንዲሰማን የሚያደርጉን ምክንያቶች አሉን። እንድንደሰት ከሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች መካከል ሌሎቹን ደግሞ እስቲ አሁን እንመልከት።
በክርስቶስ በኩል ከአምላክ ጋር የመሠረትነው ዝምድና
7. ይሖዋን በተመለከተ ክርስቲያኖች ምን ለደስታ የሚሆን ምክንያት አላቸው?
7 ከይሖዋ ጋር ያለን የቀረበ ዝምድና በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ የበለጠ ደስተኞች አድርጎናል። ክርስቲያኖች ከመሆናችን በፊት ‘በአእምሮ ጨለማ ውስጥ የሚገኘውና ከአምላክ ሕይወት የራቀው’ ዓመፀኛ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ክፍል ነበርን። (ኤፌሶን 4:18) ከይሖዋ ርቀን የነበርንበት ዘመን ያከተመ በመሆኑ ምንኛ ደስተኞች ነን! እርግጥ ነው፣ ሞገሱን ሳያጡ ለመቀጠል ጥረት ይጠይቃል። ‘ከሰማነው ከወንጌል ተስፋ ሳንናወጥ በሃይማኖት ጸንተን መኖር’ አለብን። (ቆላስይስ 1:21–23) ኢየሱስ ራሱ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” በማለት ከተናገረው ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ይሖዋ ወደ ልጁ ስለሚስበን መደሰት እንችላለን። (ዮሐንስ 6:44) በክርስቶስ በኩል ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ውድ ዝምድና ከልብ የምናደንቅ ከሆነ ይህን ዝምድና ሊያበላሽ ከሚችል ከማንኛውም ነገር እንጠብቀዋለን።
8. ኢየሱስ ደስተኞች እንድንሆን አስተዋጽኦ ያበረከተው እንዴት ነው?
8 በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ በማመን የሚገኘው የኃጢአት ይቅርታ ለደስታ የሚሆን ታላቅ ምክንያት ነው፤ ምክንያቱም ከአምላክ ጋር ዝምድና እንዲኖረን ያስቻለን ይህ ነው። የቀድሞ አባታችን አዳም በውዴታው በተከተለው የኃጢአት ጎዳና በሰው ዘር ሁሉ ላይ ሞት አምጥቷል። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ “ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል” ሲል ገልጿል። በተጨማሪም ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኩነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደ መጣ፣ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ስጦታው ሕይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ። በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።” (ሮሜ 5:8, 18, 19) ይሖዋ አምላክ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅራዊ ዝግጅት የሚጠቀሙበትን የአዳም ዘሮች ለመቤዠት ፈቃደኛ በመሆኑ ምን ያህል ደስተኞች መሆን እንችላለን!
ሃይማኖታዊ ነጻነትና የእውቀት ብርሃን
9. ከሃይማኖት አንጻር ሲታይ ደስተኞች የሆንነው ለምንድን ነው?
9 የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን ነጻ መውጣት ሌላው ለደስታ ምክንያት የሚሆን ነገር ነው። ነጻ ያወጣን መለኮታዊ እውነት ነው። (ዮሐንስ 8:32) ከዚህች ሃይማኖታዊ ጋለሞታ ነጻ መውጣት ማለት ደግሞ በኃጢአትዋ አንተባበርም፤ በእርስዋ ላይ የሚደርሰው መቅሰፍት አይደርስብንም፤ እንዲሁም አብረናት ወደ ጥፋት አዘቅት አንወርድም ማለት ነው። (ራእይ 18:1–8) ከዚህ ሁሉ ማምለጡ ፈጽሞ ሊያሳዝን አይችልም!
10. የይሖዋ ሕዝብ በመሆናችን ምን የእውቀት ብርሃን አግኝተናል?
10 የአምላክን ቃል መረዳትና በሕይወት ውስጥ በሥራ ማዋል ለታላቅ ደስታ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች ናቸው። ከሐሰት ሃይማኖት ተጽዕኖ ስለተላቀቅን በ“ታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል ሰማያዊ አባታችን የሚሰጠንን ከጊዜ ወደ ጊዜ ብሩህ እየሆነ የመጣ መንፈሳዊ ማስተዋል አግኝተናል። (ማቴዎስ 24:45–47) በምድር ላይ ከሚኖሩት ሰዎች ሁሉ የይሖዋ ቅዱስ መንፈስና የቃሉና የፈቃዱ ቅዱስ ማስተዋል ያላቸው ራሳቸውን ለእርሱ የወሰኑት ብቻ ናቸው። ልክ ጳውሎስ እንዳለው ነው፦ “መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል [አምላክ ለሚያፈቅሩት ያዘጋጀላቸውን ነገር] ገለጠው።” (1 ቆሮንቶስ 2:9, 10) በምሳሌ 4:18 ላይ ባሉት “የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፣ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል” በሚሉት ቃላት እንደተገለጸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን እውቀት እያገኘን በመሆኑ አመስጋኞችም ደስተኞችም መሆን እንችላለን።
የመንግሥት ተስፋና ዘላለማዊ ሕይወት
11. አስደሳቹ የመንግሥቱ ተስፋ ለሌሎችም ሲነገር የቆየው እንዴት ነው?
11 የመንግሥቱ ተስፋችንም ደስተኞች ያደርገናል። (ማቴዎስ 6:9, 10) የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ለሰው ዘር በሙሉ ብቸኛዋ ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኗን ለረጅም ጊዜ ስናውጅ ቆይተናል። ለምሳሌ ያህል በ1931 በዓለም ዙሪያ በተካሄዱ 51 ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ በደስታ ስሜት ከፍተኛ ተቀባይነት ባገኘ ውሳኔ አማካኝነት የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም ስንቀበል የነበረውን ሁኔታ እስቲ አስበው። (ኢሳይያስ 43:10–12) ያ ውሳኔና ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ (የወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት) በስብሰባው ላይ የሰጠው ታሪካዊ ንግግር የዓለም ተስፋ የሆነው መንግሥት የሚል ርዕስ ባለው የእንግሊዝኛ ቡክሌት ላይ ታትሞ ወጣ። በውስጡም ሕዝበ ክርስትናን በፈጸመችው ክህደትና የይሖዋን ምክር በማቃለሏ የሚወነጅል ሌላ በስብሰባው ላይ የጸደቀ ውሳኔ ተካቷል። በተጨማሪም የተላለፈው ውሳኔ “የዓለም ተስፋ የአምላክ መንግሥት ናት፤ ሌላ ምንም ተስፋ የለም” በማለት አውጆአል። በጥቂት ወራት ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ከአምስት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ የዚህን ቡክሌት ቅጂዎች በሁሉም የምድር ክፍሎች አሰራጩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መንግሥቲቱ የሰው ዘር ብቸኛ ተስፋ መሆኗን ለብዙ ጊዜ ደጋግመን ስንናገር ቆይተናል።
12. ይሖዋን ከሚያገለግሉ ሰዎች ፊት የተዘረጉት አስደሳች የሕይወት ተስፋዎች ምንድን ናቸው?
12 በመንግሥቲቱ አገዛዝ ሥር በምናገኘው የዘላለም ሕይወት ተስፋም እንደሰታለን። የቅቡዓን ክርስቲያኖች “ታናሽ መንጋ” አስደሳች ሰማያዊ ተስፋ አለው። “በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ምክንያት ሕያው የሆነውን ተስፋ የሰጠን በታላቅ ምሕረቱ በአዲስ ልደት ልጆቹ ያደረገን፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት የሆነ አምላክ ይመስገን፤ እርሱ በሰማይ ያለውን የማይጠፋና የማይበላሽ፣ የማያረጅም ርስት እንድንወርስ አድርጎናል” ሲል ሐዋርያው ጴጥሮስ ጽፏል። (ሉቃስ 12:32፤ 1 ጴጥሮስ 1:3, 4 የ1980 ትርጉም) በዛሬው ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል አብዛኞቹ በመንግሥቲቱ ግዛት ውስጥ በገነት ለዘላለም ለመኖር በጉጉት ይጠባበቃሉ። (ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 17:3) በምድር ላይ ያለ የትኛውም ሕዝብ እኛ ካሉን አስደሳች ተስፋዎች ጋር የሚወዳደር ነገር ፈጽሞ የለውም። እነዚህን ተስፋዎች ምን ያህል ከፍ ያለ ዋጋ ልንሰጣቸው ይገባል!
የተባረከ ወንድማማችነት
13. ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነታችንን መመልከት የሚኖርብን እንዴት ነው?
13 በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ብቸኛ ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር አባል መሆንም ራሱ ለታላቅ ደስታ ምክንያት የሚሆን ነገር ነው። በምድር ላይ ካሉት ሁሉ የተሻሉ ባልንጀሮች ያሉን መሆኑ በጣም ደስ ያሰኛል። ይሖዋ አምላክ ራሱ ያለንበትን ዘመን በማስመልከት እንዲህ ብሏል፦ “አሕዛብን ሁሉ አናውጣለሁ፣ በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውም ዕቃ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ።” (ሐጌ 2:7) እውነት ነው፣ ማንኛውም ክርስቲያን ቢሆን ፍጹም አይደለም። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ግለሰቦችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እርሱ አስጠግቷል። (ዮሐንስ 14:6) ይሖዋ ወደ እርሱ ያስጠጋቸው ምርጥ ናቸው ያላቸውን ሰዎች ስለሆነ ወንድማዊ ፍቅር ብናሳያቸው፣ ከፍ አድርገን ብንመለከታቸው፣ በአምላካዊ ሥራዎች ብንተባበራቸው፣ ፈተናዎች ሲደርሱባቸው ብንደግፋቸውና ስለ እነርሱ ብንጸልይ ደስታችን እጥፍ ድርብ ይሆናል።
14. ከ1 ጴጥሮስ 5:5–11 ምን ማበረታቻ ልናገኝ እንችላለን?
14 ይህ ሁሉ ለደስታችን ተጨማሪ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በእርግጥም በምድር ዙሪያ ላለው መንፈሳዊ ወንድማማችነታችን ምሽግ የሆነው የይሖዋ ደስታ ነው። አዎን፣ ሁላችንም ስደትም ሆነ ሌሎች መከራዎች ይደርሱብናል። ይሁን እንጂ በምድር ላይ ያለው ብቸኛ እውነተኛ የአምላክ ድርጅት አካል እንደመሆናችን መጠን ይህ ሊያቀራርበንና የአንድነት ስሜት እንዲኖረን ሊያደርገን ይገባል። ልክ ጴጥሮስ እንዳለው አምላክ ስለ እኛ እንደሚያስብ በማወቅ ጭንቀታችንን ሁሉ በእርሱ ላይ ጥለን ራሳችንን ከኃያል ክንዱ በታች ዝቅ ማድረግ ይኖርብናል። ሰይጣን ሊውጠን ስለሚፈልግ ንቁዎች መሆን ያስፈልገናል፤ ይሁን እንጂ ጴጥሮስ “በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” በማለት አክሎ ስለተናገረ ይህ የሚደርሰው በእኛ ላይ ብቻ አይደለም። “አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል” የሚል ዋስትና ስለተሰጠን ይህ ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት በፍጹም አይከስምም። (1 ጴጥሮስ 5:5–11) እስቲ አስበው። አስደሳቹ ወንድማማችነታችን ለዘላለም የሚዘልቅ ነው!
ዓላማ ያለው ሕይወት
15. የይሖዋ ምሥክሮች ዓላማ ያለው ሕይወት አላቸው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
15 በዚህ በችግር በተሞላ ዓለም ውስጥ ብንኖርም እንኳ ዓላማ ያለው ሕይወት ስላለን ደስተኞች ነን። እኛንም ሆነ ሌሎችን ደስተኛ የሚያደርግ አገልግሎት ተሰጥቶናል። (ሮሜ 10:10) ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ መሆናችን በእርግጥም አስደሳች መብት ነው። ይህን አስመልክቶ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “አጵሎስ . . . ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደ ሰጣቸው ያገለግላሉ። እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም። የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፣ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል። የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና።”—1 ቆሮንቶስ 3:5–9
16, 17. የይሖዋ ሕዝቦች ዓላማ ያለው አስደሳች ሕይወት እንዳላቸው የሚያሳዩ ምን ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል?
16 ተግባራችንን በታማኝነት እያከናወንን ይሖዋን ማገልገል በደስታ ላይ ደስታ የሚያጎናጽፍ ዓላማ ያለው ሕይወት እንደሚሰጠን ለማሳየት ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። የሚከተለው አባባል ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው፦ “[በምረቃ ፕሮግራሙ ወቅት] ጢም ብሎ የሞላውን የመንግሥት አዳራሽ ግራና ቀኝ ተመለከትኩ፤ እኔንና ሚስቴን እንዲሁም ሦስቱን ልጆቻችንንና የትዳር ጓደኞቻቸውን ጨምሮ ስምንት የቤተሰቤን አባላት ተመለከትኩ። . . . በእርግጥም እኔና ሚስቴ በአምላክ አገልግሎት አስደሳች የሆነና ዓላማ ያለው ሕይወት መኖር ችለናል።”
17 አንድ ሰው በማንኛውም ዕድሜ ላይ እያለ በይሖዋ አገልግሎት እውነተኛ ዓላማ ያለው አስደሳች ሕይወት መጨበጥ እንደሚችል መገንዘቡም ራሱ ደስ የሚያሰኝ ነው። ለምሳሌ ያህል አረጋውያን በሚጦሩበት ተቋም ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የደረሳቸው አንዲት ሴት የይሖዋ ምሥክር በመሆን በ102 ዓመታቸው ተጠምቀዋል። በዚህ መንገድ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ‘እውነተኛውን አምላክ በመፍራትና ትእዛዛቱን በመጠበቅ’ አስደሳች የሆነ ዓላማ ይዘው ቀጥለዋል።—መክብብ 12:13
ምን ጊዜም የማይከዳ ምሽግ
18. የሐዘን ስሜትን ለማሸነፍና ደስታችንን ለመጨመር ምን ማድረግ ይቻላል?
18 የይሖዋ ደስታ ተግባራቸውን በታማኝነት ለሚያከናውኑ ሰዎች ምን ጊዜም የማይከዳ ምሽግ ነው። ሆኖም ይህ ደስታ ኢየሱስ በጌቴሴማኒ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች” ብሎ እንዲናገር እንዳስገደዱት ዓይነት አስከፊ ጊዜያት በጭራሽ አያጋጥሙንም ማለት አይደለም። (ማርቆስ 14:32–34) የስስት ጥቅሞችን በማሳደዳችን የተነሣ ከባድ ሐዘን ላይ ወድቀናል እንበል። ይህ ከሆነ አኗኗራችንን እንለውጥ። ራስ ወዳድ ባለመሆን ከባድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶችን በመሸከማችን ደስታችን ጠፍቶ ከሆነ ውጥረትን የሚያቃልሉና የደስተኝነት መንፈሳችንን እንደገና መልሰን እንድናገኝ የሚያስችሉ ማስተካከያዎችን ልናደርግ እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ ጠንካራ መንፈስ ይዘን ኃጢአተኛውን ሥጋችንን፣ ክፉውን ዓለምና ዲያብሎስን በመቃወም ይሖዋን ደስ ለማሰኘት የምንጥር ከሆነ እርሱ ደስታን በመስጠት ይባርከናል።—ገላትያ 5:24፤ 6:14፤ ያዕቆብ 4:7
19. በአምላክ ድርጅት ውስጥ ያለንን ማንኛውንም መብት እንዴት መመልከት ይኖርብናል?
19 በተወያየንባቸውና በሌሎች ብዙ ምክንያቶች የተነሣ ታላቅ ደስታ አለን። የጉባኤ አስፋፊዎችም ሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የምንሳተፍ ሁላችንም በጌታ ሥራ ብዙ የምንሠራው ነገር ሊኖረን ይችላል፤ ይህ ደግሞ ለደስታችን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ምንም አይጠረጠርም። (1 ቆሮንቶስ 15:58) በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያለን መብት ምንም ይሁን ምን ላለን መብት አመስጋኞች እንሁን፤ እንዲሁም ለአፍቃሪው ደስተኛ አምላካችን በደስታ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረባችንን እንቀጥል።—1 ጢሞቴዎስ 1:11
20. ከሁሉ የላቀው መብታችን ምንድን ነው? ስለ ምን ነገርስ እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
20 በተለይ ደግሞ ምሥክሮቹ ሆነን የይሖዋን ታላቅ ስም የመሸከም መብት በማግኘታችን ደስተኞች ነን። አዎን፣ ፍጹማን አይደለንም፤ እንዲሁም ብዙ ፈተናዎች ያጋጥሙናል፤ ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን የምናገኛቸውን ግሩም በረከቶች ፈጽሞ አንርሳ። ውዱ ሰማያዊ አባታችንም ከቶ እንደማይከዳን እናስታውስ። የይሖዋ ደስታ ምሽጋችን ከሆነ ምን ጊዜም እንደምንባረክ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ “የይሖዋ ደስታ” ምንድን ነው?
◻ ክርስቲያኖች እውነተኛ ደስታን የሚያገኙት እንዴት ነው?
◻ የይሖዋ ምሥክሮች ደስተኛ የሆኑባቸው አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
◻ የይሖዋ ደስታ ምን ጊዜም የማይከዳ ምሽግ የሆነው ለምንድን ነው?