የይሖዋ ቤት ያገኘው ታላቅ ክብር
“ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” አዓት]።”— ሐጌ 2:7
1. መንፈስ ቅዱስ ከእምነትና ከሥራ ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?
አንዲት የይሖዋ ምሥክር ከቤት ወደ ቤት ስትሰብክ የጰንጠቆስጤ ሃይማኖት ተከታይ የሆነች አንዲት ሴት ታገኛለች። ሴትየዋ ‘መንፈስ ቅዱስ የተሰጠን እኛ ነን፤ ሥራውን ግን የምትሠሩት እናንተ ናችሁ’ ስትል የተሰማትን ተናገረች። ከዚያም ምሥክሯ አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስ ካለው የአምላክን ሥራ ለመሥራት እንደሚያነሳሳው በዘዴ አብራራችላት። ያዕቆብ 2:17 “ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው” ይላል። የይሖዋ መንፈስ ምሥክሮቹ ጠንካራ እምነት እንዲያዳብሩ ከመርዳቱም ሌላ የጽድቅ ሥራዎችን እንዲሠሩ በማድረግ ‘ቤቱን በክብር ሞልቶታል።’ ዋነኛው ሥራ ‘ለአሕዛብ ሁሉ ምሥክር እንዲሆን የመንግሥቱን ወንጌል በዓለም ሁሉ መስበክ’ ነው። ሥራው ይሖዋ የሚፈልገው ደረጃ ላይ ሲደርስ ‘ፍጻሜው ይመጣል።’— ማቴዎስ 24:14
2. (ሀ) ራሳችንን በይሖዋ ሥራ ማስጠመዳችን ምን በረከት ያስገኝልናል? (ለ) መጨረሻው ‘የዘገየ’ ቢመስለን እንኳ ደስተኞች መሆን የሚገባን ለምንድን ነው?
2 እነዚህ የኢየሱስ ቃላት ዛሬ የምንሠራው ሥራ “የደስተኛውን አምላክ ታላቅ ምሥራች” በመናገር ላይ ማተኮር እንዳለበት ያስገነዝቡናል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት) በአምላክ ሥራ ውስጥ ይበልጥ ራሳችንን በደስታ ባስጠመድን መጠን መጨረሻው በፍጥነት እየቀረበ እንዳለ ሆኖ ይሰማናል። በዕንባቆም 2:2, 3 ላይ እንዲህ የሚሉትን የይሖዋ ቃላት እናነባለን:- “አንባቢው ይፈጥን ዘንድ ራእዩን ጻፍ፣ በጽላትም ላይ ግለጠው። ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፣ ወደ ፍጻሜውም ይቸኩላል፣ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው እርሱም አይዘገይም።” አዎን፣ “ራእዩ” “ቢዘገይም” ይፈጸማል። የኢየሱስ ንጉሣዊ መንግሥት 83ኛ ዓመቱን በያዘበት በአሁኑ ጊዜ አንዳንዶች እንደዘገየ ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል። ይሁንና መጨረሻው እስካሁን ድረስ ባለ መምጣቱ ደስተኞች ልንሆን አይገባንምን? በእነዚህ በ1990ዎቹ አሥርተ ዓመታት ውስጥ እንደ ተዓምር በሚቆጠር መንገድ በምሥራቅ አውሮፓ፣ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች እንዲሁም ሌሎች ቦታዎች በምሥራቹ ስብከት ሥራ ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነሥቷል። ‘የዘገየ’ መስሎ የታየው ይህ ጊዜ በቅርቡ በተከፈቱት የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ ያሉትን ብዙ “በግ” መሰል ሰዎች ለመሰብሰብ ጊዜ እንዲገኝ አስችሏል።— ዮሐንስ 10:16
3. “ይህ ትውልድ” ስለሚለው አነጋገር ያገኘነው አዲስ እውቀት የአምላክን ሥራ በጥድፊያ ስሜት ለመሥራት ሊያነቃቃን የሚገባው ለምንድን ነው?
3 ነቢዩ “አይዘገይም” ብሏል። ኢየሱስ “ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ” ዛሬ ያለው ክፉ ትውልድ እንደማያልፍ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:34) ስለ እነዚህ የኢየሱስ ቃላት ያገኘነው አዲስ እውቀት የስብከት ሥራችን አጣዳፊ እንዳልሆነ የሚጠቁም ነውን?a ከእውነታው ለመረዳት እንደሚቻለው ሁኔታው ከዚህ ተቃራኒ ነው! በእኛ ዘመን ያለው ትውልድ ከአሁን ቀደም በየትኛውም የታሪክ ወቅት ታይቶ በማያውቅ መጠን በክፋትና በምግባረ ብልሹነት ማጥ ውስጥ ተዘፍቋል። (ከሥራ 2:40 ጋር አወዳድር።) ሥራችንን በጥድፊያ ስሜት ልናከናውን ይገባናል። (2 ጢሞቴዎስ 4:2 አዓት) ስለ ታላቁ መከራ መምጣት የሚናገሩት ትንቢቶች በሙሉ እንደሌባ በድንገት፣ ሳይታሰብ፣ አድብቶ እንደሚመጣ ይገልጻሉ። (1 ተሰሎንቄ 5:1-4፤ ራእይ 3:3፤ 16:15) “ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።” (ማቴዎስ 24:44) ይህ አምላክ የለሽ የሰው ዘር ትውልድ ከምድር ገጽ ተጠራርጎ ሊጠፋ በቋፍ ላይ ባለበት በአሁኑ ጊዜ በሚያባብሉ ዓለማዊ ነገሮች ውስጥ ገብተን ‘በጭቃ ወደ መንከባለል’ በመመለስ ውድ የሆነውን የዘላለም ሕይወት ተስፋችንን አሽቀንጥረን ልንጥለው እንደማንፈልግ የታወቀ ነው!— 2 ጴጥሮስ 2:22፤ 3:10፤ ሉቃስ 21:32-36
4. ‘በተገቢው ጊዜ የሚቀርበውን ምግብ’ መጠን መጨመር ያስፈለገው ለምንድን ነው? ይህንንስ ለማሟላት ምን ተደርጓል?
4 ኢየሱስ በትክክል እንደተነበየው የሰው ዘር “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ወደሆነው ዘመን በገባበት በ1914 “የምጥ ጣር” ጀምሯል። በጊዜያችን ሰቆቃ፣ እልቂትና ዓመፅ በእጅጉ ተበራክተዋል። (ማቴዎስ 24:3-8, 12) በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ‘የታማኝና ልባም ባሪያ’ ክፍል የሆኑትን ቅቡዓን ለጌታው ለክርስቶስ ቤተ ሰዎች መንፈሳዊ ‘ምግብ በጊዜው’ የማቅረብ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 24:45-47) በአሁኑ ጊዜ ይህ መሲሐዊ ንጉሡ ከሰማያዊ ዙፋኑ ሆኖ በምድር ዙሪያ የሚካሄደውን አስገራሚ የሆነ የመንፈሳዊ ምግብ አቅርቦት መርሐ ግብር በመምራት ላይ ይገኛል።
የተትረፈረፈ ‘የምግብ አቅርቦት’
5. ዋነኛው “ምግብ” ምን ትኩረት ተሰጥቶታል?
5 ‘ምግቡ’ እንዴት እንደሚዘጋጅ ተመልከት። (ሉቃስ 12:42) በክርስቲያናዊ ማዕድ ላይ የሚቀርበው ዋነኛው ምግብ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተማር እንዲቻል ለማንበብ የሚጋብዝና ትክክለኛ ትርጉም ማግኘቱ አስፈላጊ ነው። የአዲሲቱ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በእንግሊዝኛ ከወጣበት ከ1950 ወዲህ ይህ ነገር ደረጃ በደረጃ ሲሟላ ቆይቷል። በ1961 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ተዘጋጀ፤ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በሌሎች ዋና ዋና ቋንቋዎች ተዘጋጀ። በ1996 የአገልገሎት ዓመት የወጡት 3 ጥራዞች ጠቅላላ ቁጥሩን 27 ያደረሱት ሲሆን ከእነዚህ መካከል 14 የሚያክሉት ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱሱንም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ሌሎች ጽሑፎችን ለማዘጋጀት 1,174 የሚያክሉ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች በ77 አገሮች ውስጥ በትርጉም ሥራ በሙሉ ጊዜ በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
6. መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ለማግኘት ሰዎች ያሳዩትን ፍላጎት ለማሟላት ማኅበሩ ምን አድርጓል?
6 የኅትመት ሥራ የሚያከናውኑት 24 የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮዎች ይህን የተርጓሚዎች ሠራዊት በመደገፍ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ጽሑፎች በማተም ላይ ናቸው። ለዚህም ሲባል ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸው ተጨማሪ የሮታሪ ማተሚያዎች በዋና ዋና ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ተተክለዋል። የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ኅትመት ከወር ወደ ወር እየጨመረ የሚሄድ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በጠቅላላ 943,892,500 ደርሷል፤ ይህም በዓመቱ ውስጥ የ13.4 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ማለት ነው። በዩናይትስ ስቴትስ፣ በብራዚል፣ በፊንላንድ፣ በጀርመን፣ በኢጣሊያ፣ በጃፓን፣ በኮሪያና በሜክሲኮ ብቻ የታተሙት የመጽሐፍ ቅዱስና ጠንካራ ሽፋን ያላቸው መጻሕፍት ብዛት በ1995 ከነበረው 40 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፤ በ1996 በጠቅላላ 76,760,098 ቅጂዎች ታትመዋል። ሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎችም ጠቅላላው የኅትመት ቁጥር ከፍ እንዲል የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
7. ኢሳይያስ 54:2 ዛሬ ይበልጥ አጣዳፊ የሆነው እንዴት ነው?
7 ጭማሪ ማድረግ ያስፈለገበት አንዱ ዐቢይ ምክንያት በምሥራቅ አውሮፓና በአፍሪካ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ በ1990ዎቹ ዓመታት በመነሳቱ ነው። በእነዚህ ቦታዎች ለመንፈሳዊ ነገሮች የሚታየው ጥማት ከፍተኛ ነው። በመሆኑም “የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፣ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቆጥቢ፤ አውታሮችሽን አስረዝሚ ካስሞችሽንም አጽኚ” የሚለው ጥሪ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አሁን እያስተጋባ ነው።— ኢሳይያስ 54:2
8. አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በኩል ምን የልግስና ተግባር እየተከናወነ ነው?
8 በመሆኑም 104 ከሚያክሉት የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች መካከል በብዙዎቹ ውስጥ ተጨማሪ የግንባታ ሥራ ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በአብዛኞቹ አዲስ በተከፈቱት የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ ይህ መስፋፋት፣ የሚጠይቀው ወጪ በአብዛኛው የሚሸፈነው ለዓለም አቀፉ ሥራ ሲባል ከበለጸጉት አገሮች በሚደረገው መዋጮ ነው። የሚያስደስተው ጉባኤዎችም ሆኑ ግለሰቦች በዘጸአት 35:21 ላይ ያለውን መንፈስ በማንጸባረቅ በሙሉ ልባቸው ምላሽ ሲሰጡ ቆይተዋል:- “ከእነርሱም ሰው ሁሉ ልቡ እንዳነሣሣው መንፈሱም እሺ እንዳሰኘው ለመገናኛው ድንኳን ሥራ ለማገልገያውም ሁሉ ለተቀደሰውም ልብስ ለአምላክ ስጦታ አመጡ።” በዚህ አጋጣሚ በልግስና ስጦታው የተካፈሉትን ሁሉ ልናመሰግናቸው እንወዳለን።— 2 ቆሮንቶስ 9:11
9. ሮሜ 10:13, 18 ዛሬ በመፈጸም ላይ ያለው እንዴት ነው?
9 የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሚያወጣቸው ጽሑፎች በ1996 በእርግጥ እስከ ምድር ዳር ድረስ የይሖዋን ስምና ዓላማ አስከብረዋል። ሁኔታው ሐዋርያው ጳውሎስ አስቀድሞ እንደተናገረው ነው። የኢዩኤልን ትንቢትና መዝሙር 19ን በመጥቀስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና። ዳሩ ግን:- ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ። በእውነት:- ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።” (ሮሜ 10:13, 18) ሕዝቦቹ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ በማድረግ ወዲያውም የአምልኮ ቤቱ በክብር እንዲሞላ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ይሁንና ይህ መንግሥቱን የማወጁ ሥራ በተለይ በ1996 ይበልጥ የጎለበተው እንዴት ነው? እባክህ ከገጽ 18 እስከ 21 ድረስ ያለውን ሠንጠረዥ ተመልከት።
በምድር ዙሪያ መከር መሰብሰብ
10. ከገጽ 18 እስከ 21 ላይ ባለው ሠንጠረዥ ላይ ተጠቃልሎ እንደተገለጸው የይሖዋ ሕዝቦች ካደረጉት እንቅስቃሴ ምን ጎላ ብለው የሚታዩ ገጽታዎችን መጥቀስ ትችላለህ?
10 “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዴህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” የሚሉት በሉቃስ 10:2 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት የአሁኑን ያህል ክብደት ያገኙበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም። ለዚህ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ እየሰጠህ ነውን? በምድር ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ላይ ናቸው። በ1996 የመስክ አገልገሎታቸውን ሪፖርት ያደረጉ 5,413,769 አዲስ የአስፋፊዎች ከፍተኛ ቁጥር መገኘቱ ይህን የሚያረጋግጥ ነው። ከዚህም ሌላ 366,579 አዲስ ወንድሞችና እህቶች ተጠምቀዋል። ‘የይሖዋን የአምልኮ ቤት በክብር እንዲሞላ’ አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን እነዚህን ‘ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጡ ዕቃዎች’ እንደ ውድ ነገር አድርገን በደስታ እንቀበላቸዋለን!— ሐጌ 2:7
11. ሁላችንም የምንደሰትበት ምክንያት አለን የምንለው ለምንድን ነው?
11 በቅርቡ በተከፈቱት የአገልግሎት መስኮች የተደረገው ጭማሪም አስገራሚ ነው። ሌሎቻችን እንዲህ ዓይነት እድገት ባገኙት እንቀናለንን? አንቀናም፤ እንዲያውም ከእነርሱ ጋር ደስ ይለናል። ሁሉም አገሮች ሲጀምሩ ቁጥራቸው ጥቂት ነበር። በሐጌ ዘመን የኖረው ነቢዩ ዘካርያስ “የጥቂቱን ነገር ቀን የናቀ ማን ነው?” ሲል ጽፏል። (ዘካርያስ 4:10) የምሥክርነቱ ሥራ በደንብ በተስፋፋባቸው አገሮች ውስጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በመኖራቸውና የአገልግሎት ክልሎችም በተደጋጋሚ እንዲያውም በብዙ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ በየሳምንቱ መሸፈን በመቻላቸው በጣም ደስ ይለናል። ይሖዋ ካሁን ቀደም ችግር ወደ ነበረባቸው አካባቢዎች የመዳንን አጋጣሚ በሚዘረጋበት በአሁኑ ጊዜ እጃችን የሚዝልበት ምክንያት ይኖራልን? በፍጹም አይኖርም! ኢየሱስ “እርሻውም ዓለም ነው” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:38) የጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት በአይሁድ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ላይ እንዳደረጉት ሁሉ እኛም የአገልግሎት ክልላችንን አጣርተን በመሸፈን ምሥክርነት መስጠታችንን መቀጠል ይኖርብናል።— ሥራ 2:40፤ 10:42፤ 20:24፤ 28:23
አሁንም ወደፊት መግፋት
12. ‘ቀጥ ብለን ወደፊት’ እንድንገፋ የሚያበረታታን ምንድን ነው? (“‘ከምድር ዳርቻ’ መከር መሰብሰብ” የሚለውንም ሣጥን ተመልከት።)
12 አዎን፣ የመላእክት ስብስብ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ሰማያዊ ሰረገላ እኩል ‘ቀጥ ብለን ወደፊት’ መጓዝ ይኖርብናል። (ሕዝቅኤል 1:12) ሐዋርያው ጴጥሮስ የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት እናስታውሳለን:- “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።” (2 ጴጥሮስ 3:9) በኢኮኖሚ በተደቆሱ አገሮች ውስጥ የሚገኙት ወንድሞቻችን የሚያሳዩት ምሳሌ የሚሆን ቅንዓት ሊያነሳሳን ይገባል። አርማጌዶን የዘገየ መስሎ ቢታየን እንኳ ይህ ጊዜ በእነዚህ አገሮችም ሆነ በደንብ በተሠራባቸው ሌሎች የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ የሚገኙ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲመጡ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። አትሳሳቱ:- “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኗል።” (ሶፎንያስ 1:14) እኛም የአገልግሎት ክልላችንን አጣርተን በመሸፈን ምሥክርነት ለመስጠት መፍጠን ይኖርብናል!
13, 14. (ሀ) በ1996 ስለነበረው የጽሑፎች ሥርጭት ምን ማለት ይቻላል? (ለ) ጉባኤዎች በየዓመቱ ምን ልዩ ዕቅድ ሊያወጡ ይችላሉ? በዚህስ ለመሳተፍ ምን ዕቅድ አውጥተሃል?
13 በዚህ የሪፖርት ሠንጠረዥ ላይ ዝርዝር ሁኔታው አይገለጽ እንጂ ባለፈው ዓመት በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በመጽሐፎች እና በመጽሔቶች ሥርጭት ረገድ ከፍተኛ ጭማሪ ተገኝቷል። ለምሳሌ ያህል በዓለም ዙሪያ የተበረከቱት መጽሔቶች ቁጥር 19 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን በጠቅላላው 543,667,923 ቅጂዎች ተበርክተዋል። መጽሔቶቻችን በመንገድ ላይ፣ በመናፈሻ ቦታዎች፣ በአውቶቡስ ማቆሚያዎችና በገበያ አካባቢዎች ምሥክርነት ለመስጠት ተስማሚ ሆነው የሚዘጋጁ ናቸው። ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ተደጋግሞ በተሠራባቸው አንዳንድ የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ የሚገኙ በተለያየ ሙያ የሠለጠኑ ሰዎች በመጽሔቶቻችን ይዘት በመገረም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው ፈቃደኛ ሆነዋል።
14 ጉባኤዎች ብዙውን ጊዜ በየዓመቱ በሚያዝያ ወር ውስጥ አንድ ሙሉ ቀን ከቤት ወደ ቤትና ሕዝብ በሚያዘወትርባቸው ቦታዎች እየሄዱ መጽሔት ማበርከትን የሚጨምር ልዩ የመጽሔት ዘመቻ ያካሂዳሉ። ጉባኤያችሁ በሚያዝያ 1997 በዚህ ዘመቻ ይካፈል ይሆን? የሚያዝያ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች እትም ግሩም ሆኖ ተዘጋጅቷል። በምድር ዙሪያ እነዚህን መጽሔቶች በተመሳሳይ ወቅት ማሠራጨት በጣም አስገራሚ እንደሚሆን ምንም አያጠራጥርም! በቆጵሮስ ደሴት የሚገኙት ጉባኤዎች “የመንግሥቱን መልእክት በተቻለ መጠን ለእያንዳንዱ ሰው ማዳረስ” የሚል መርሕ በመያዝ በየወሩ ሳይቀር ለመጽሔት ፕሮግራም አውጥተው በዚያ መሠረት በመሥራታቸው በዓመት ውስጥ 275,359 መጽሔቶችን በማበርከት አዲስ ከፍተኛ ቁጥር ያገኙ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት 54 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
የሐጌ የመጨረሻ መልእክቶች
15. (ሀ) ይሖዋ በሐጌ አማካኝነት ተጨማሪ መልእክት የላከው ለምን ነበር? (ለ) ከሦስተኛው የሐጌ መልእክት ምን ልንማር ይገባል?
15 ሐጌ ሁለተኛውን መልእክት ካደረሰ ከ63 ቀናት በኋላ ይሖዋ ዛሬ እኛም ልብ ልንለው የሚገባውን ሦስተኛ መልእክት አስይዞ ልኮት ነበር። ሐጌ አይሁዳውያኑ ከ17 ዓመታት በፊት ጥለውት የነበረውን የቤተ መቅደሱን መሠረት ገና እየጣሉ እንዳሉ አድርጎ ተናግሯል። ይሖዋ በድጋሚ የማጽዳት እርምጃ መውሰዱን ተገቢ ሆኖ አግኝቶት ነበር። ካህናቱም ሆኑ ሕዝቡ እጆቻቸውን አላልተው ስለነበር በይሖዋ ዓይን ረክሰው ታይተዋል። ዛሬስ ይሖዋ ከሕዝቦች መካከል አንዳንዶቹ እጆቻቸውን አላልተውና ጭራሹኑ ልቅ በሆነው እንዲሁም ፍቅረ ነዋይ በተጠናወተው ዓለማዊ ጎዳና ራሳቸውን አጠላልፈው ይሆን? ሁላችንም ይሖዋ “ከዚህች ቀን ጀምሬ እባርካችኋለሁ” ሲል በገባው ቃል ላይ እምነት በማሳደር ‘ከዛሬ ጀምሮ በሚመጣው ዘመን’ ሁሉ ልባችን ለይሖዋ ስም ክብር በማምጣት ላይ እንዲያተኩር ማድረጋችን አጣዳፊ ነው።— ሐጌ 2:10-19፤ ዕብራውያን 6:11, 12
16. የትኛው ‘መናወጥ’ በጣም ቀርቧል? ውጤቱስ ምን ይሆናል?
16 በዚያው ዕለት ‘የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቃል’ ለአራተኛና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ሐጌ መጣ። ‘ሰማይንና ምድርን ሲያናውጥ’ ምን እንደሚከሰት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የመንግሥታትንም ዙፋን እገለብጣለሁ፣ የአሕዛብንም መንግሥታት ኃይል አጠፋለሁ፤ ሰረገሎችንና የሚቀመጡባቸውንም እገለብጣለሁ፤ ፈረሶችና ፈረሰኞቻቸውም እያንዳንዳቸው በወንድማቸው ሰይፍ ይወድቃሉ።” (ሐጌ 2:6, 21, 22) ይሖዋ በአርማጌዶን ላይ ምድርን ሙሉ በሙሉ ሲያጸዳ ይህ ‘መናወጥ’ ወደ ፍጻሜው ይደርሳል። ከዚህ በፊት ግን በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለሰብዓዊው ኅብረተሰብ ማዕከል የሚሆኑት ‘ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጡት ዕቃዎች’ ተሰብስበው ማለቅ አለባቸው። ሐሴት የምናደርግበትና ይሖዋን የምናወድስበት ብዙ ምክንያት አለን!— ሐጌ 2:7፤ ራእይ 19:6, 7፤ 21:1-4
17. ኢየሱስ ‘የቀለበት ማተሚያ’ የሆነው እንዴት ነው?
17 ሐጌ ትንቢቱን ሲደመድም እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ዘሩባቤል ሆይ፣ በዚያ ቀን እወስድሃለሁ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ . . . እንደ ቀለበት ማተሚያ አደርግሃለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” (ሐጌ 2:23) በአሁኑ ጊዜ ክርስቶስ ኢየሱስ በምድራዊቷ ኢየሩሳሌም ገዥው ዘሩባቤልና ሊቀ ካህናቱ ኢያሱ በተናጠል ይዘውት የነበረውን ቦታ አንድ ላይ በማጣመር የይሖዋ ታላቅ መሲሐዊ ንጉሥና ሊቀ ካህናት ሆኖ በማገልገል ላይ ነው። ኢየሱስ በይሖዋ ቀኝ እጅ እንዳለ የአንድ ባለ ሥልጣን የቀለበት ማተሚያ በመሆን ‘አምላክ የሰጣቸው ብዙዎቹ ተስፋዎች’ እውን እንዲሆኑ እንደ መሣሪያ ሆኖ በማገልገል “አዎን” ሆኗል። (2 ቆሮንቶስ 1:20፤ ኤፌሶን 3:10, 11፤ ራእይ 19:10) መላው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢታዊ መልእክት ያተኮረው ክርስቶስ ንጉሥና የሚቤዥ ካህን እንዲሆን ይሖዋ ባደረገው ዝግጅት ላይ ነው።— ዮሐንስ 18:37፤ 1 ጴጥሮስ 1:18, 19
18. ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ የተናገረው’ የመደምደሚያ ቃል አስደሳች ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?
18 በእርግጥም በዚህ በእኛ ዘመን ከሁሉ የላቀው ክብር የሚገኘው ደማቅ ብርሃን በፈነጠቀበት በይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ነው! ይሖዋ የሰይጣንን የነገሮች ሥርዓት ጠራርጎ ካጠፋ በኋላ ሐጌ 2:9 ወዲያውኑ ሌላውን አስደሳች ፍጻሜውን ያገኛል:- “በዚህም ስፍራ ሰላምን እሰጣለሁ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” አዎን፣ በመጨረሻ ‘አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም፤ የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል’ በተባለለት የሰላም መስፍንና የይሖዋ ‘የቀለበት ማተሚያ’ በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት በመላው አጽናፈ ዓለም ዘላቂ ሰላም ይሰፍናል። (ኢሳይያስ 9:6, 7) የይሖዋ የአምልኮ ቤት ክብር ሰላም በሰፈነበት በይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ ለዘላለም ይንጸባረቃል። በዚህ ቤት እስከ መጨረሻ ለመኖር ያብቃን!— መዝሙር 27:4፤ 65:4፤ 84:10
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በኅዳር 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡትን “‘ከክፉ ትውልድ’ መዳን” እና “ነቅቶ መጠበቅ የሚያስፈልግበት ጊዜ” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ዛሬ የይሖዋ ቤት ‘በክብር እየተሞላ’ ያለው እንዴት ነው?
◻ ምሥራቹን መስበክ የዛሬውን ያክል አጣዳፊ ያልነበረው ለምንድን ነው?
◻ የ1996 የአገልግሎት ሪፖርት በጥድፊያ ስሜት መስበክን የሚያበረታታ ምን ነገር ይጠቁማል?
◻ ክርስቶስ የይሖዋ ‘የቀለበት ማተሚያ’ ሆኖ የሚያገለግለው እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ከምድር ዳርቻ” መከር መሰብሰብ
ኢሳይያስ 43:6 ላይ “አትከልክል፤ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ . . . አምጣ” በማለት ይሖዋ የተናገረውን ትእዛዝ እናነባለን። ይህ ጥቅስ በአሁኑ ጊዜ በተለይ በምሥራቅ አውሮፓ ለየት ባለ መንገድ እየተፈጸመ ነው። ለምሳሌ ያህል ቀደም ሲል ኮምኒስት አገር የነበረችውን ሞልዶቫን እንውሰድ። በአሁኑ ጊዜ ግማሽ የሚያክሉት ነዋሪዎች የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑባቸው መንደሮች አሉ። ለስብከት የሚሆን የአገልግሎት ክልል ለማግኘት ረዥም ርቀት መጓዝ አለባቸው። ለዚህም ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው! በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ብዙ አስፋፊዎች በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደ ሳይቤሪያ ተግዘው የተወሰዱት ቤተሰቦች ልጆች ናቸው። አሁን እነዚያ ልጆች በመከሩ ሥራ ግንባር ቀደም ሆነው ይሳተፋሉ። ከ12,565 አስፋፊዎች መካከል 1,917 የሚያክሉት የተጠመቁት ባለፈው ዓመት ነው። ከጉባኤዎቹ መካከል አርባ ሦስቱ 150 የሚያህሉ አስፋፊዎች ያሏቸው ሲሆን አራት የነበሩት ወረዳዎች በአዲሱ የአገልግሎት ዓመት ወደ ስምንት ከፍ ብለዋል።
በአልባኒያ የሚታየው ጭማሪም እጅግ አስደናቂ ነው። ለ50 ዓመታት ያህል በነበረው በጭካኔው ተወዳዳሪ የሌለው አምባ ገነን አገዛዝ የደረሰባቸውን ሁሉ በጽናት ያለፉት እፍኝ የማይሞሉ ታማኝ ምሥክሮች በአልባኒያ ይገኛሉ። ብዙዎቹ ተገድለዋል። ይህም ኢየሱስ እንዲህ ብሎ የገባውን ቃል ያስታውሰናል:- “ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፣ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፣ . . . እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።” (ራእይ 2:10፤ በተጨማሪም ዮሐንስ 5:28, 29፤ 11:24, 25ን ተመልከት።) በአሁኑ ጊዜ በአልባኒያ ምን ነገሮችን እናያለን? ይሖዋ በኢሳይያስ 60:22 ላይ የገባው ቃል ፍጻሜውን በማግኘት ‘ታናሹ ለሺህ . . . ሆኗል’! በ1990 በአልባኒያ የአገልግሎት ሪፖርት የመለሰው አንድ አስፋፊ ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . እያጠመቃችኋቸው . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሎ ላቀረበው ጥሪ ከኢጣሊያና ከሌሎች አገሮች ብዙ “ሠራተኞች” አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። (ማቴዎስ 28:19፤ ሉቃስ 10:2) በ1996 በተከበረው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ 773 አስፋፊዎች በመስኩ ተሰማርተው ነበር። እነርሱም ከአስፋፊዎች ቁጥር ስምንት ጊዜ የሚያጥፍ ማለትም 6,523 ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ስብሰባ ላይ እንዲገኙ አድርገዋል! ገለልተኛ ከሆኑ አካባቢዎች ያልተጠበቀ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ሪፖርት ተደርጓል። በከተማው ውስጥ የሚኖሩ አስፋፊዎች ባይኖሩም እንኳ በኩክስ ከተማ 192 በዲቭዬክ ከተማ ደግሞ 230 ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል። አንድ አስፋፊ ባለበት በክሩጃ ከተማ 212 ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል። በኮርቼ የሚኖሩ 30 አስፋፊዎች ከ300 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች ሊይዝ የሚችል አዳራሽ ተከራዩ። እነዚህ ተሰብሳቢዎች ወደ አዳራሹ ከገቡ በኋላ ተጨማሪ ክፍት ቦታ ሊገኝ ባለመቻሉ ሌሎች 200 ሰዎች መመለስ ግድ ሆኖባቸዋል። በእርግጥም መከሩ ለአጨዳ ደርሷል!
ከሩማኒያ የሚከተለው ሪፖርት መጥቷል:- “ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ቀደም ብለን ምንም ምሥክር አይኖርም ብለን በገመትነው ትንሽ ከተማ ውስጥ የሚኖር የይሖዋ ምሥክር ነኝ ከሚል ሰው ጋር ተገናኘን። በዚያች ከተማ ሐሙስና እሁድ ለብዙ ዓመታት ስብሰባ ያደርጉ የነበሩና ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክ የጀመሩ ከእርሱ ሌላ 15 ሰዎች እንዳሉ ነገረን። በሚቀጥለው ቀን ወደዚያ ከተማ ሄድን። 15 ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በሁለት ክፍል ውስጥ ሆነው ይጠብቁን ነበር። እነርሱም 20 መጻሕፍትና 20 አዳዲስ መጽሔቶች ወሰዱ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመራው እንዴት እንደሆነ አሳየናቸው። አብረናቸው ዘመርን እንዲሁም ለነበሯቸው አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ ሰጠናቸው። ቡድኑን ይመራ የነበረው ሰው እንዲህ በማለት ተናገረ:- ‘ከጥቂት ቀናት በፊት ይሖዋ እረኛ እንዲልክልን እያለቀስኩ ጸልዬ ነበር። ለጸሎቴም መልስ አገኘሁ።’ እኛም በደስታ ተፍለቅልቀን ተመልሰን ለመሄድ ስንነሳ ወላጆቹን በሞት አጥቶ በመጨረሻ ላይ አባት እንዳገኘ ልጅ:- ‘እባካችሁ አትርሱን። እንደገና መጥታችሁ እዩን!’ በማለት ተናገረ። እኛም ተመልሰን ሄድን። በአሁኑ ጊዜ በዚህች ከተማ ሰባት ጥናቶች እየተመሩ ነው። በብዙ አዳዲስ የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አማካኝነት ሥራው አስደናቂ በሆነ መንገድ ተጀመሯል። ሥራውም ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል። ይህም ሥራው መለኮታዊ ድጋፍ እንዳለው ያሳያል።”
[በገጽ 18-21 ላይ የሚገኝ ግራፍ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የይሖዋ ምሥክሮች የ1996 የአገልግሎት ዓመት ዓለም አቀፍ ሪፖርት
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
‘ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጡት ዕቃዎች’ እየተሰበሰቡ ነው በባሕር ደሴቶች (1)፣ በደቡብ አሜሪካ (2)፣ አፍሪካ (3)፣ እስያ (4)፣ ሰሜን አሜሪካ (5)፣ እንዲሁም አውሮፓ (6)