የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የሐጌ እና የዘካርያስ መጻሕፍት ጎላ ያሉ ነጥቦች
ጊዜው 520 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። ከባቢሎን ግዞት የተመለሱት አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የይሖዋ ቤተ መቅደስ መሠረት ከጣሉ አሥራ ስድስት ዓመታት አልፈዋል። ያም ሆኖ ቤተ መቅደሱ አላለቀም፤ እንዲሁም የግንባታው ሥራ እንዳይከናወን እገዳ ተጥሎበታል። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ቃሉን እንዲናገሩ መጀመሪያ ነቢዩ ሐጌን፣ ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ ነቢዩ ዘካርያስን ላከ።
ሐጌና ዘካርያስ ዓላማቸው ሕዝቡ የቤተ መቅደሱን ግንባታ እንዲቀጥል ማበረታታት ነው። እነዚህ ነቢያት ያደረጉት ጥረት የተሳካ ሲሆን ቤተ መቅደሱም ከአምስት ዓመታት በኋላ ተጠናቀቀ። ሐጌና ዘካርያስ የተናገሩት መልእክት በስማቸው በተሰየሙት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል። የሐጌ መጽሐፍ ተጽፎ ያበቃው በ520 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን የዘካርያስ መጽሐፍ ደግሞ የተጠናቀቀው በ518 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። እንደነዚህ ነቢያት ሁሉ እኛም አሁን ያለው ሥርዓት ከማብቃቱ በፊት መጠናቀቅ ያለበት መለኮታዊ ሥራ ተሰጥቶናል። ይህ ሥራ ስለ አምላክ መንግሥት መስበክና ደቀ መዛሙርት ማድረግ ነው። እስቲ ከሐጌና ከዘካርያስ መጻሕፍት ምን ዓይነት ማበረታቻ ማግኘት እንደምንችል እንመልከት።
“መንገዳችሁን ልብ በሉ”
ሐጌ በ112 ቀናት ውስጥ ለተግባር የሚያነሳሱ አራት መልእክቶችን ተናገረ። የመጀመሪያው መልእክት እንዲህ የሚል ነበር:- “‘እስቲ መንገዳችሁን ልብ በሉ፤ ወደ ተራራ ውጡ፤ ዕንጨት አምጡ፤ ቤቱን ሥሩ፤ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል፤ እከበርበታለሁም’ ይላል እግዚአብሔር።” (ሐጌ 1:7, 8) ሕዝቡም ለመልእክቱ ጥሩ ምላሽ ሰጠ። ሁለተኛው መልእክት ደግሞ ይሖዋ “ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ” የሚል ተስፋ እንደሰጠ የሚገልጽ ነው።—ሐጌ 2:7
ሦስተኛው መልእክት፣ ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን እንደገና የመገንባቱን ሥራ ችላ በማለታቸው በይሖዋ ፊት እነሱም ሆኑ ‘የእጃቸው ሥራ ሁሉ የረከሱ’ እንደሆኑ የሚገልጽ ነው። ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱን የመገንባቱን ሥራ ከጀመሩበት ቀን አንስቶ ይሖዋ ‘ይባርካቸዋል።’ አራተኛው መልእክት ደግሞ ይሖዋ ‘የባዕዳንን መንግሥታት ኀይል እንደሚያጠፋ’ እንዲሁም ገዥው ዘሩባቤልን ‘እንደ ማተሚያ ቀለበት’ እንደሚያደርገው ይገልጻል።—ሐጌ 2:14, 19, 22, 23
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
2:6, 7, 21, 22—ሕዝቦችን የሚያናውጠው ማን ወይም ምንድን ነው? መናወጡስ ምን ያስከትላል? ይሖዋ የመንግሥቱ መልእክት በዓለም ዙሪያ እንዲሰበክ በማድረግ ‘ሕዝቦችን ሁሉ እያናወጠ’ ነው። ከዚህም በላይ የስብከቱ ሥራ “የሕዝቦችም ሀብት ሁሉ” ወደ ይሖዋ ቤት እንዲመጣ በማድረግ ቤቱን በክብር እየሞላው ነው። በቅርብ ጊዜ ደግሞ “ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ጸባኦት . . . ሰማያትንና ምድርን፣ ባሕሩንና የብሱን” በማናወጥ ይህን ክፉ ሥርዓት ድምጥማጡን ያጠፋዋል።—ዕብራውያን 12:26, 27
2:9—“የአሁኑ ቤት” ማለትም የሁለተኛው ቤት ‘ክብር ከቀድሞው ቤት ክብር የሚበልጠው’ በየትኞቹ መንገዶች ነው? ይህ የሆነው ቢያንስ በሦስት መንገዶች ነው። የቤተ መቅደሱ ዕድሜ፣ ይሖዋን ለማምለክ ወደዚያ የጎረፉት ሰዎች እንዲሁም ታላቁ አስተማሪ በዚያ ማስተማሩ የሁለተኛው ቤት ክብር ከቀድሞው ቤት እንዲበልጥ አድርጓል። ታላቁ የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ከ1027 እስከ 607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ለ420 ዓመታት ያገለገለ ቢሆንም “የአሁኑ ቤት” የተባለው ሁለተኛው ቤተ መቅደስ በ515 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከተጠናቀቀበት ጊዜ አንስቶ በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እስከጠፋበት ጊዜ ድረስ ለ580 ዓመታት አገልግሏል። ከዚህም በላይ መሲሑ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው “የአሁኑ ቤት” በተባለው ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲሆን “ከቀድሞው ቤት” ይበልጥ ብዙ ሰዎች ይሖዋን ለማምለክ ወደዚህኛው ቤተ መቅደስ መጥተዋል።—የሐዋርያት ሥራ 2:1-11
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:2-4፦ ሰዎች የስብከቱን ሥራችንን መቃወማቸው ‘አስቀድመን የእግዚአብሔርን መንግሥት ከመሻት’ ይልቅ የራሳችንን ፍላጎት እንድናስቀድም ሊያደርገን አይገባም።—ማቴዎስ 6:33
1:5, 7፦ ‘መንገዳችንን ልብ ማለታችን’ እንዲሁም ሕይወታችንን የምንመራበት መንገድ ከአምላክ ጋር ያለንን ግንኙነት እንዴት እንደሚነካው ማሰባችን የጥበብ አካሄድ ነው።
1:6, 9-11፤ 2:14-17፦ በሐጌ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን የግል ጉዳዮቻቸውን ለማከናወን ይሯሯጡ የነበረ ቢሆንም የድካማቸውን ፍሬ አላገኙም። ቤተ መቅደሱን ችላ ብለውት ስለነበር የአምላክን በረከት አላገኙም። እኛም ያለን ቁሳዊ ነገር ብዙም ይሁን ጥቂት ‘ብልጽግናን የሚያመጣው የእግዚአብሔር በረከት’ እንደሆነ በማስታወስ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ቅድሚያ መስጠትና ለአምላክ የምናቀርበውን አገልግሎት በሙሉ ነፍስ ማከናወን ይኖርብናል።—ምሳሌ 10:22
2:15, 18፦ አይሁዳውያን ቸልተኞች የነበሩበትን ጊዜ ከማሰብ ይልቅ ከዚያን ቀን ጀምሮ ቤተ መቅደሱን እንደገና የመገንባቱን ሥራ ልብ ብለው እንዲያስቡ ይሖዋ አጥብቆ መክሯቸዋል። እኛም በተመሳሳይ ከዚህ ቀን ጀምሮ ለይሖዋ በምናቀርበው አምልኮ ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን።
‘በመንፈሴ እንጂ በብርታት አይደለም’
ዘካርያስ ትንቢቱን መናገር የጀመረው አይሁዳውያን ‘ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ’ ጥሪ በማቅረብ ነው። (ዘካርያስ 1:3) ከዚህ ጥሪ በኋላ የተመዘገቡት ስምንት ራእዮች ቤተ መቅደሱን በድጋሚ በመገንባቱ ሥራ አምላክ እንደሚደግፋቸው ዋስትና ይሰጣሉ። (“ዘካርያስ የተመለከታቸው ስምንት ምሳሌያዊ ራእዮች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) የግንባታው ሥራ የሚጠናቀቀው “[በይሖዋ መንፈስ] እንጂ በኀይልና በብርታት አይደለም።” (ዘካርያስ 4:6) ቅርንጫፍ ተብሎ የተጠራው ሰው ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይሠራል’፤ “በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል።”—ዘካርያስ 6:12, 13
የቤቴል ሰዎች የኢየሩሳሌምን መጥፋት ለማስታወስ ስለሚደረገው ጾም ካህናቱን እንዲጠይቁ መልእክተኞች ላኩ። ይሖዋም በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰውን ጥፋት ለማስታወስ ተብለው የሚደረጉት አራት የጾም ወቅቶች “የተድላና የሐሤት በዓላት” እንደሚሆኑ ለዘካርያስ ነገረው። (ዘካርያስ 7:2፤ 8:19) ከዚያ በኋላ ያሉት ሁለት መልእክቶች በብሔራትና በሐሰተኛ ነቢያት ላይ የተነገረ ፍርድ፣ ስለ መሲሑ የሚገልጹ ትንቢቶች እንዲሁም የአምላክ ሕዝቦች ተመልሰው እንደሚቋቋሙ የሚገልጽ ሐሳብ ይዘዋል።—ዘካርያስ 9:1፤ 12:1
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
2:1—መለኪያ የያዘው ሰው ኢየሩሳሌምን በገመድ የለካት ለምን ነበር? ይህን ማድረጉ በከተማዋ ዙሪያ የመከላከያ ቅጥር እንደሚሠራ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። መልአኩ፣ ኢየሩሳሌም እንደምትሰፋና የይሖዋን ጥበቃ እንደምታገኝ ለሰውየው ነገረው።—ዘካርያስ 2:3-5
6:11-13—ለሊቀ ካህናቱ ኢያሱ አክሊል መደረጉ ንጉሥና ካህን እንደነበር ያሳያል? አያሳይም፤ ኢያሱ የመጣው ከዳዊት የንግሥና መስመር አልነበረም። ይሁን እንጂ አክሊል በማድረጉ ለመሲሑ ትንቢታዊ ጥላ ሆኗል። (ዕብራውያን 6:20) “ቅርንጫፍ” የተባለውን ሰው በተመለከተ የተነገረው ትንቢት በሰማይ ንጉሥና ካህን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ፍጻሜውን አግኝቷል። (ኤርምያስ 23:5) ኢያሱ፣ ወደ አገራቸው ለተመለሱት አይሁዳውያን እንደገና በተገነባው ቤተ መቅደሱ ውስጥ ሊቀ ካህን ሆኖ እንደነበረ ሁሉ ኢየሱስም በይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ ለሚካሄደው እውነተኛ አምልኮ ሊቀ ካህን ነው።
8:1-23—በዚህ ምዕራፍ ላይ የተጠቀሱት አሥር አዋጆች ፍጻሜያቸውን ያገኙት መቼ ነው? ከእያንዳንዱ አዋጅ በፊት “እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል” የሚል መግለጫ የሚገኝ ሲሆን አዋጁም አምላክ ለሕዝቡ ሰላም እንደሚያመጣ የገባውን ቃል ይዟል። ከእነዚህ አዋጆች አንዳንዶቹ በስድስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል፤ ሁሉም አዋጆች ከ1919 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ጀምሮ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል አሊያም በጊዜያችን ፍጻሜያቸውን እያገኙ ነው።a
8:3—ኢየሩሳሌም “የእውነት ከተማ” ተብላ የተጠራችው ለምንድን ነው? ኢየሩሳሌም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከመጥፋቷ ቀደም ብሎ፣ ምግባረ ብልሹ የሆኑ ነቢያትና ካህናት እንዲሁም ታማኝ ያልሆኑ ሰዎች የሚኖሩባት ‘የጨቋኞች ከተማ’ ነበረች። (ሶፎንያስ 3:1፤ ኤርምያስ 6:13፤ 7:29-34) ቤተ መቅደሱ በድጋሚ ከተገነባና ሕዝቦቿ ይሖዋን ማምለክ ከጀመሩ በኋላ ግን የንጹሕ አምልኮ እውነት በዚህች ከተማ ስለሚነገር ኢየሩሳሌም “የእውነት ከተማ” ተብላ ተጠርታለች።
11:7-14—ዘካርያስ “ሞገስ” እና “አንድነት” የተባሉትን በትሮች መስበሩ ምን ያመለክታል? ዘካርያስ “ለዕርድ የተለዩትን በጎች” ማለትም በመሪዎቻቸው የሚበዘበዙትን በግ መሰል ሰዎች ‘ለማሰማራት’ እንደተላከ ተደርጎ ተገልጿል። ዘካርያስ እረኛ የነበረ መሆኑ ለኢየሱስ ክርስቶስ ጥላ ሆኗል፤ ኢየሱስ የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ ወደሆኑት ሰዎች ቢላክም ሕዝቡ አልተቀበሉትም። “ሞገስ” የተባለው በትር መሰበሩ፣ አምላክ ከአይሁዳውያን ጋር የገባው የሕግ ቃል ኪዳን እንደሚፈርስና ለእነሱ ሞገስ ማሳየቱን እንደሚያቆም ይጠቁማል። “አንድነት” የተባለው በትር መሰበሩ ደግሞ ይሁዳና እስራኤል የይሖዋ አምላኪዎች በመሆናቸው በመካከላቸው የተፈጠረው የወንድማማች ትስስር እንደሚቀር ያመለክታል።
12:11—“በመጊዶን ሜዳ ለሐዳድሪሞን እንደተለቀሰ” የሚገልጸው ዘገባ ምን ያመለክታል? የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ ከግብጹ ፈርዖን ኒካዑ ጋር ባደረገው ጦርነት “በመጊዶን ሜዳ” የተገደለ ሲሆን ‘የልቅሶ ግጥም’ ተጽፎለት ለበርካታ ዓመታት ይታወስ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 35:22-25) እንግዲያው “ለሐዳድሪሞን እንደተለቀሰ” የሚለው አባባል ኢዮስያስ ሲሞት የነበረውን ልቅሶ ሊያመለክት ይችላል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:2-6፤ 7:11-14፦ ይሖዋ፣ የሚሰጣቸውን እርማት ሰምተው ንስሐ በሚገቡና በሙሉ ነፍሳቸው በማምለክ ወደ እሱ በሚመለሱ ሰዎች የሚደሰት ከመሆኑም በላይ ወደ እነሱ ይመለሳል። በሌላ በኩል ግን መልእክቱን ‘መስማት የማይፈልጉ፣ በእልኸኝነት ጀርባቸውን የሚያዞሩ እንዲሁም ጆሮአቸውን የሚደፍኑ’ ሰዎች ለእርዳታ ቢጠሩትም አይሰማቸውም።
4:6, 7፦ ቤተ መቅደሱን እንደገና የመገንባቱ ሥራ ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዳይጠናቀቅ የሚያግደውን ማንኛውንም እንቅፋት የይሖዋ መንፈስ ያሸንፋል። ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎት ላይ ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥመን በይሖዋ ላይ እምነት በማሳደር ልንወጣው እንችላለን።—ማቴዎስ 17:20
4:10፦ ዘሩባቤልና ሕዝቦቹ ይሖዋ እየተመለከታቸው የእሱን ላቅ ያሉ መሥፈርቶች በመከተል የቤተ መቅደሱን ሥራ ለማጠናቀቅ ችለዋል። ፍጹማን ላልሆኑ ሰዎች ይሖዋ እንደሚጠብቅባቸው ሆኖ መኖር በጣም ከባድ አይደለም።
7:8-10፤ 8:16, 17፦ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ፍትሕን ማስፈን፣ ምሕረትንና ርኅራኄን ማሳየት እንዲሁም እርስ በርስ እውነት መነጋገር ይኖርብናል።
8:9-13፦ ይሖዋ ያዘዘንን ሥራ ለመሥራት ‘እጃችንን የምናበረታ’ ከሆነ ይባርከናል። ከምናገኛቸው በረከቶች መካከል ሰላም፣ ያለ ሥጋት መኖር እንዲሁም መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ይገኙበታል።
12:6፦ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል የኃላፊነት ቦታ ያላቸው ሰዎች እንደ “ፋና ነበልባል” መሆን ማለትም ከፍተኛ ቅንዓት ማሳየት ይኖርባቸዋል።
13:3፦ ለእውነተኛው አምላክና ለድርጅቱ ያለን ታማኝነት፣ በጣም ለምንቀርበው ሰው ካለን ታማኝነት የበለጠ መሆን አለበት።
13:8, 9፦ ይሖዋ ያልተቀበላቸው ከሃዲዎች የምድር ሁለት ሦስተኛ እንደሆኑ ስለተገለጸ በጣም ብዙ ነበሩ። በእሳት ነጥሮ የጠራው አንድ ሦስተኛው ክፍል ብቻ ነበር። በዘመናችን ክርስቲያን ነን ከሚሉት ሰዎች አብዛኞቹን የያዘችው ሕዝበ ክርስትና በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት አጥታለች። ‘የይሖዋን ስም የጠሩት’ እንዲሁም እሱ እንዲያጠራቸው ራሳቸውን ያቀረቡት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። እነዚህ ክርስቲያኖችም ሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻቸው በስም ብቻ የይሖዋ ምሥክሮች ከመሆን የበለጠ ነገር ያደርጋሉ።
ቅንዓት የተሞላበት ሥራ ለማከናወን ልንነሳሳ ይገባል
ሐጌና ዘካርያስ የተናገሩት መልእክት በዛሬው ጊዜ የሚጠቅመን እንዴት ነው? እነዚህ ነቢያት የተናገሩት መልእክት አይሁዳውያን ለቤተ መቅደሱ ግንባታ ትኩረት እንዲሰጡ እንዴት እንዳነሳሳቸው ስናስብ ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት ለመካፈል አንገፋፋም?
ዘካርያስ፣ መሲሑ “በአህያ ላይ ተቀምጦ” እንደሚመጣ፣ ‘በሠላሳ ብር’ ለጠላቶቹ እንደሚሰጥ እንዲሁም እሱ እንደሚመታና ‘በጎቹ እንደሚበተኑ’ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ዘካርያስ 9:9፤ 11:12፤ 13:7) ዘካርያስ ስለ መሲሑ በተናገራቸው እንደነዚህ ባሉት ትንቢቶች ፍጻሜ ላይ ማሰላሰላችን እንዴት እምነት የሚገነባ ነው! (ማቴዎስ 21:1-9፤ 26:31, 56፤ 27:3-10) በይሖዋ ቃልና ለእኛ መዳን ባደረጋቸው ዝግጅቶች ላይ ያለን እምነት ይጠናከራል።—ዕብራውያን 4:12
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የጥር 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 9-22ን ተመልከት።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ዘካርያስ የተመለከታቸው ስምንት ምሳሌያዊ ራእዮች
1:8-17፦ የቤተ መቅደሱ ግንባታ እንደሚጠናቀቅ እንዲሁም ኢየሩሳሌምና ሌሎች የይሁዳ ከተሞች በረከት እንደሚያገኙ ዋስትና ይሰጣል።
1:18-21፦ ‘ይሁዳን የበታተኑት ቀንዶች’ ማለትም የይሖዋን አምልኮ የተቃወሙት መንግሥታት በሙሉ እንደሚጠፉ ቃል ይገባል።
2:1-13፦ ኢየሩሳሌም እንደምትሰፋና ይሖዋ “በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር” በመሆን እንደሚጠብቃት ይጠቁማል።
3:1-10፦ ሰይጣን የቤተ መቅደሱን ሥራ እንደተቃወመ፣ ሊቀ ካህኑ ኢያሱ ኃጢአቱ እንደተወገደለት እንዲሁም ጥበቃ እንደተደረገለት ያሳያል።
4:1-14፦ ተራራ መሰል እንቅፋቶች እንደ ደልዳላ ሜዳ እንደሚሆኑና ገዥው ዘሩባቤል የቤተ መቅደሱን ግንባታ እንደሚያጠናቅቅ ማረጋገጫ ይሰጣል።
5:1-4፦ በክፉ አድራጊዎች ላይ የሚመጣውን እርግማን ይናገራል።
5:5-11፦ ክፋት እንደሚያበቃ ይናገራል።
6:1-8፦ የመላእክት አመራርና ጥበቃ እንደሚኖር ቃል ይገባል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሐጌና የዘካርያስ መልእክቶች ዓላማ ምን ነበር?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኃላፊነት ቦታ ያላቸው ሰዎች እንደ “ፋና ነበልባል” የሆኑት እንዴት ነው?