“እውነትንና ሰላምን ውደዱ”!
“የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ . . . እውነትንና ሰላምን ውደዱ።”—ዘካርያስ 8:18, 19
1, 2. (ሀ) የሰው ልጆች ሰላምን በተመለከተ ምን ታሪክ አስመዝግበዋል? (ለ) በአሁኑ ጊዜ ዓለም እውነተኛ ሰላም በጭራሽ ሊያገኝ የማይችለው ለምንድን ነው?
“ዓለም ሰላም አግኝቶ አያውቅም። በሆነ ቦታ፣ አብዛኛውን ጊዜም ተመሳሳይ በሆነ ወቅት በብዙ ቦታዎች ውስጥ ጦርነት ያልነበረበት ጊዜ የለም።” ይህን የተናገሩት በአሜሪካ ውስጥ የሚገኘው የማሳቹሴትስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሚልተን ማየር ናቸው። የሰውን ዘር በተመለከተ የሰጡት ይህ አስተያየት እንዴት የሚያሳዝን ነው! እርግጥ ሰዎች ሰላም ይፈልጋሉ። የፖለቲካ ሰዎች ከሮም ፓክስ ሮማና ዘመን ጀምሮ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት እስከ ተነደፈው “ላለመጠፋፋት እርስ በርስ ተፈራርቶ መኖር” የተባለው ፖሊሲ ድረስ ሰላምን ለማምጣት ያላደረጉት ጥረት የለም። በመጨረሻ ግን ያደረጓቸው ጥረቶች ሁሉ ሳይሳኩ ቀሩ። ኢሳይያስ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት እንደገለጸው ራሳቸው ‘የሰላም መልእክተኞች መራራ ልቅሶ አልቅሰዋል።’ (ኢሳይያስ 33:7) ይህ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ይህ የሆነው ዘላቂ ሰላም የሚገኘው ጥላቻና ስግብግብነት ሲጠፋ ብቻ ስለሆነ ነው፤ ሰላም በእውነት ላይ መመሥረት ይኖርበታል። ሰላም በውሸት ላይ ሊመሠረት አይችልም። ይሖዋ ለጥንቷ እስራኤል “እነሆ፣ ሰላምን እንደ ወንዝ፣ የአሕዛብንም ክብር እንደሚጎርፍ ፈሳሽ እመልስላታለሁ” የሚል ተስፋ የሰጠው ለዚህ ነው። (ኢሳይያስ 66:12) አሁን ላለው ሥርዓት አምላክ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ “ነፍሰ ገዳይ” ከመሆኑም በተጨማሪ “ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነው።” (ዮሐንስ 8:44፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4) እንዲህ ዓይነት አምላክ ያለው ዓለም እንዴት ሰላም ሊኖረው ይችላል?
3. የአምላክ ሕዝቦች ሁከት በበዛበት ዓለም ውስጥ ቢኖሩም እንኳ አምላክ ለሕዝቡ ምን አስደናቂ ስጦታ ሰጥቷቸዋል?
3 ይሁን እንጂ የይሖዋ ሕዝቦች በጦርነት በሚታመስ የሰይጣን ዓለም ውስጥ ቢኖሩም ይሖዋ ለሕዝቡ ሰላም መስጠቱ በጣም ያስደንቃል። (ዮሐንስ 17:16) በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በኤርምያስ በኩል የሰጠውን ተስፋ በመፈጸም ወደ ትውልድ አገራቸው ሲመልሳቸው ለልዩ ሕዝቡ “ሰላምንና እውነትን” ሰጥቷቸዋል። (ኤርምያስ 33:6) በተጨማሪም በዚህ የመጨረሻ ቀን የሚኖሩት የአምላክ ሕዝቦች በዓለም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ከታዩት የመከራ ወቅቶች ሁሉ በከፋው ዘመን ቢሆንም በራሳቸው “ምድር” ወይም በምድር ላይ ባላቸው መንፈሳዊ ርስት ውስጥ “እውነትንና ሰላምን” ሰጥቷቸዋል። (ኢሳይያስ 66:8፤ ማቴዎስ 24:7-13፤ ራእይ 6:1-8) ዘካርያስ ምዕራፍ 8ን መመርመራችንን ስንቀጥል አምላክ ስለሚሰጠው ሰላምና እውነት ጥልቅ አድናቆት ያድርብናል፤ በተጨማሪም ይህን ሰላም ጠብቀን ለማቆየት ምን ማድረግ እንዳለብን እንመለከታለን።
“እጃችሁን አበርቱ”
4. ዘካርያስ እስራኤላውያን ሰላምን ለማግኘት ከፈለጉ ምን እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል?
4 በዘካርያስ ምዕራፍ 8 ላይ ይሖዋ ለስድስተኛ ጊዜ እንዲህ የሚል አስደሳች መግለጫ ሲሰጥ እንሰማለን፦ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መቅደሱ ይሠራ ዘንድ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቤት ከተመሠረተበት ቀን ጀምሮ ከነቢያት አፍ ይህን ቃል በዚህ ዘመን የሰማችሁ እናንተ ሆይ፣ እጃችሁን አበርቱ። ከዚያ ወራት አስቀድሞ ለሰውና ለእንስሳ ዋጋ አልነበረምና፤ እኔም ሰውን ሁሉ በወንድሙ ላይ አስነሥቼ ነበርና ከአስጨናቂው የተነሣ ለሚገባውና ለሚወጣው ሰላም አልነበረም።”—ዘካርያስ 8:9, 10
5, 6. (ሀ) እስራኤላውያን ተስፋ በመቁረጣቸው ምክንያት በእስራኤል ውስጥ ምን ሁኔታ ተከስቶ ነበር? (ለ) ይሖዋ እስራኤላውያን አምልኮቱን ካስቀደሙ ምን ለውጥ እንደሚመጣላቸው ቃል ገብቶ ነበር?
5 ዘካርያስ እነዚህን ቃላት የተናገረው ቤተ መቅደሱ በኢየሩሳሌም ውስጥ በመሠራት ላይ እያለ ነበር። ቀደም ሲል ከባቢሎን የተመለሱ እስራኤላውያን ተስፋ ቆርጠው ቤተ መቅደሱን መሥራታቸውን አቁመው ነበር። በግል ምቾታቸው ላይ ትኩረት ስላደረጉ ከይሖዋ በረከትም ሆነ ሰላም አላገኙም ነበር። መሬታቸውን ያረሱና የወይን ቦታቸውን የተንከባከቡ ቢሆንም ብልጽግና አላገኙም። (ሐጌ 1:3-6) ሁኔታው ‘ያለ አንዳች ደመወዝ’ የሠሩ ያህል ሆኖ ነበር።
6 አሁን ቤተ መቅደሱ እንደገና በመሠራት ላይ ነው፤ ዘካርያስ ‘እንዲበረቱ’ እና በድፍረት የይሖዋን አምልኮ እንዲያስቀድሙ አይሁዳውያንን አበረታታቸው። የይሖዋን አምልኮ ካስቀደሙ ምን ይሆናል? “አሁን ግን እንደ ቀድሞው ዘመን በዚህ ሕዝብ ቅሬታ ላይ አልሆንም፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ነገር ግን ሰላምን እዘራለሁ፤ ወይኑ ፍሬውን ይሰጣል፣ ምድርም አዝመራዋን ታወጣለች፣ ሰማያትም ጠላቸውን ይሰጣሉ፣ ለዚህም ሕዝብ ቅሬታ ይህን ነገር ሁሉ አወርሳለሁ። የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፣ በአሕዛብ ዘንድ እርግማን እንደ ነበራችሁ፣ እንዲሁ አድናችኋለሁ፣ በረከትም ትሆናላችሁ፣ አትፍሩ፣ እጃችሁንም አበርቱ።” (ዘካርያስ 8:11-13) እስራኤላውያን የተሰጣቸውን ሥራ በቆራጥነት ካከናወኑ ብልጽግና ያገኛሉ። ቀደም ሲል አሕዛብ ለእርግማን ምሳሌ የሚሆን ከተማ ለመጥቀስ ሲፈልጉ እስራኤልን ይጠቅሱ ነበር። አሁን ግን እስራኤል የበረከት ምሳሌ ትሆናለች። ‘እጃቸውን የሚያበረቱበት’ እንዴት ያለ ግሩም ምክንያት ነበራቸው!
7. (ሀ) የይሖዋ ሕዝቦች በ1995 የአገልግሎት ዓመት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ምን አስደሳች ለውጦች አጋጥመዋቸዋል? (ለ) ዓመታዊ ሪፖርቱን ስትመለከት በአስፋፊዎች፣ በአቅኚዎች ቁጥርና በአማካይ ሰዓት ረገድ አስደናቂ ውጤት ያስመዘገቡ አገሮች የትኞቹ ናቸው?
7 ዛሬ ያለው ሁኔታስ ምን ይመስላል? ከ1919 በፊት በነበሩት ዓመታት የይሖዋ ሕዝቦች በተወሰነ ደረጃ ቅንዓት ይጎድላቸው ነበር። በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ሙሉ በሙሉ የገለልተኛነት አቋም አልያዙም ነበር፤ በተጨማሪም ንጉሣቸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ከመከተል ይልቅ ሰውን የመከተል ዝንባሌ ነበራቸው። በዚህ ምክንያት ከድርጅቱ ውስጥና ከድርጅቱ ውጪ የተነሡት ተቃውሞዎች አንዳንዶችን ተስፋ አስቆረጧቸው። ከዚያ በኋላ በ1919 በይሖዋ እርዳታ እጃቸውን አበረቱ። (ዘካርያስ 4:6) ይሖዋ ሰላም ስለሰጣቸው በጣም በልጽገዋል። ይህም በ1995 የአገልግሎት ዓመት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰው ባለፉት 75 ዓመታት ባስመዘገቡት ታሪክ ታይቷል። የይሖዋ ምሥክሮች በሕዝብ ደረጃ ከብሔራዊ ስሜት፣ ከጎሠኝነት፣ ከዘር ጥላቻና ከሌሎች የጥላቻ መንስኤዎች በሙሉ ይርቃሉ። (1 ዮሐንስ 3:14-18) በእውነተኛ የቅንዓት ስሜት ተነሣስተው ይሖዋን በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ያገለግሉታል። (ዕብራውያን 13:15፤ ራእይ 7:15) ባለፈው ዓመት ብቻ ስለ ሰማያዊ አባታቸው ለሌሎች በመናገር ከአንድ ቢልዮን በላይ ሰዓት አሳልፈዋል! በየወሩ 4,865,060 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መርተዋል። በየወሩ በአማካይ 663,521 ሰዎች በአቅኚነት አገልግሎት ተካፍለዋል። አንዳንድ ጊዜ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ለአምልኮታቸው ልባዊ ቅንዓት ስላላቸው ሰዎች ምሳሌ ለመጥቀስ ሲፈልጉ የይሖዋ ምሥክሮችን ይጠቅሳሉ።
8. እያንዳንዱ ክርስቲያን ‘ከሰላም ዘር’ ሊጠቀም የሚችለው እንዴት ነው?
8 በቅንዓታቸው ምክንያት ይሖዋ ለሕዝቡ ‘የሰላምን ዘር’ ሰጥቷቸዋል። ይህን የሰላም ዘር የሚኮተኩት እያንዳንዱ ግለሰብ ሰላም በልቡና በሕይወቱ ውስጥ ሲያብብ ይመለከታል። ከይሖዋና ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ሰላም እንዲኖረው ጥረት የሚያደርግ እያንዳንዱ ክርስቲያን በይሖዋ ስም የተጠሩት ሕዝቦች ከሚያገኙት እውነትና ሰላም ተካፋይ ይሆናል። (1 ጴጥሮስ 3:11፤ ከያዕቆብ 3:18 ጋር አወዳድር።) ይህ በጣም የሚያስደስት አይደለምን?
“አትፍሩ”
9. ይሖዋ ከሕዝቦቹ ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ረገድ ምን ለውጥ እንደሚመጣ ተስፋ ሰጥቷል?
9 አሁን ይሖዋ የሰጠውን ሰባተኛ መግለጫ እናነባለን። መግለጫው ምን ነበር? “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ አባቶቻችሁ እጅግ ባስቆጡኝ ጊዜ ክፉ ለማድረግ እንዳሰብኩ፣ እንዳልተጸጸትሁም፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እንዲሁ ዳግመኛ ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ቤት በዚህ ወራት በጎነትን አደርግ ዘንድ አስቤአለሁ፤ አትፍሩ።”—ዘካርያስ 8:14, 15
10. የይሖዋ ምሥክሮች እንደማይፈሩ የሚያሳየው የትኛው ያስመዘገቡት ታሪክ ነው?
10 በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት የይሖዋ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ሁኔታ ተበታትነው የነበሩ ቢሆኑም የአምላክን ፈቃድ የማድረግ ፍላጎት ነበራቸው። ስለዚህ ይሖዋ ጥቂት ተግሣጽ ከሰጣቸው በኋላ ከእነሱ ጋር ግንኙነት የሚያደርግበትን መንገድ ለወጠ። (ሚልክያስ 3:2-4) በዛሬው ጊዜ መለስ ብለን ወደ ኋላ ስናስብ ላደረገልን ነገር ታላቅ ምስጋና እናቀርብለታለን። እርግጥ ‘በአሕዛብ ሁሉ የተጠላን ሆነናል።’ (ማቴዎስ 24:9) ብዙዎች ለእምነታቸው ሲሉ ታስረዋል፤ አንዳንዶችም ሞተዋል። ብዙውን ጊዜ ሰዎች የግዴለሽነትና የጥላቻ ስሜት ያሳዩናል። ይሁን እንጂ አንፈራም። ይሖዋ ከማንኛውም የሚታይ ወይም የማይታይ ተቃዋሚ የበለጠ ኃይል እንዳለው እናውቃለን። (ኢሳይያስ 40:15፤ ኤፌሶን 6:10-13) “እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፣ ልብህም ይጽና” የሚሉትን ቃላት መታዘዛችንን አናቋርጥም።—መዝሙር 27:14
“ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ”
11, 12. ይሖዋ ለሕዝቡ ከሚሰጣቸው በረከቶች ሙሉ በሙሉ ለመካፈል ከፈለግን በግለሰብ ደረጃ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?
11 ይሖዋ ከሚሰጣቸው በረከቶች ሙሉ በሙሉ ለመካፈል ማስታወስ የሚኖሩብን ነገሮች አሉ። ዘካርያስ እንዲህ ይላል፦ “የምትሠሩት ነገር ይህ ነው፤ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ በበር አደባባያችሁም የእውነትንና የሰላምን ፍርድ ፍረዱ፤ ሁላችሁም በባልንጀራችሁ ላይ ክፉን ነገር በልባችሁ አታስቡ፤ የሐሰትንም መሐላ አትውደዱ፤ ይህን ነገር ሁሉ እጠላለሁና፣ ይላል እግዚአብሔር።”—ዘካርያስ 8:16, 17
12 ይሖዋ እውነትን እንድንናገር አጥብቆ ያሳስበናል። (ኤፌሶን 4:15, 25) መጥፎ ነገር ለማድረግ የሚዶልቱ፣ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ እውነትን የሚደብቁ ወይም በሐሰት የሚምሉ ሰዎች የሚያቀርቧቸውን ጸሎቶች አይሰማም። (ምሳሌ 28:9) ክህደትን ስለሚጠላ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አጥብቀን እንድንከተል ይፈልጋል። (መዝሙር 25:5፤ 2 ዮሐንስ 9-11) ከዚህም በላይ በእስራኤል ከተሞች መግቢያ ላይ ይቀመጡ እንደ ነበሩት ሽማግሌዎች ሁሉ የፍርድ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ሽማግሌዎች የሚሰጡት ምክርና ውሳኔ በግል አመለካከታቸው ላይ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። (ዮሐንስ 17:17) ክርስቲያን ሽማግሌዎች በተጣሉ ሁለት ወገኖች መካከል እርቅ ለመፍጠርና ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች እንደገና ከአምላክ ጋር ሰላም እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲሞክሩ ይሖዋ “የሰላምን ፍርድ” እንዲሹ ይፈልጋል። (ያዕቆብ 5:14, 15፤ ይሁዳ 23) በተመሳሳይም ሆን ብለው በመጥፎ ተግባራቸው በመቀጠል የጉባኤውን ሰላም ለማደፍረስ የሚሞክሩ ሰዎችን በድፍረት በማስወገድ የጉባኤውን ሰላም ይጠብቃሉ።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10
“ደስታና ተድላ”
13. (ሀ) ዘካርያስ ጾምን በተመለከተ ምን ለውጥ እንደሚመጣ ተንብዮአል? (ለ) በእስራኤል ውስጥ የትኞቹ ጾሞች ነበሩ?
13 አሁን ከበድ ያለውን ስምንተኛ መግለጫ እንሰማለን። እንዲህ ይላል፦ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአራተኛው ወር ጾም የአምስተኛውም የሰባተኛውም የአሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሐሴትም በዓላት ይሆናል፤ ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ውደዱ።” (ዘካርያስ 8:19) በሙሴ ሕግ ሥር እስራኤላውያን በኃጢአታቸው ማዘናቸውን ለመግለጽ በስርየት ቀን ይጾሙ ነበር። (ዘሌዋውያን 16:29-31) ዘካርያስ የጠቀሳቸው አራት ጾሞች ኢየሩሳሌም ድል ከመደረጓና ከመጥፋቷ ጋር በተያያዘ እስራኤላውያን ያለቀሱባቸው ጊዜያት የነበሩ ይመስላል። (2 ነገሥት 25:1-4, 8, 9, 22-26) አሁን ግን ቤተ መቅደሱ እንደገና በመሠራት ላይ ሲሆን ኢየሩሳሌም እንደገና በሕዝብ ተሞልታለች። ልቅሶ ወደ ደስታ ጾሞች ደግሞ ወደ በዓላት ወቅቶች በመለወጥ ላይ ነበሩ።
14, 15. (ሀ) የመታሰቢያው በዓል ለደስታ ታላቅ ምክንያት የሆነው እንዴት ነው? ይህስ ምን ሊያስታውሰን ይገባል? (ለ) ከዓመታዊው ሪፖርት ለመመልከት እንደሚቻለው በመታሰቢያው በዓል ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተገኙት በየትኞቹ አገሮች ውስጥ ነው?
14 በአሁኑ ጊዜ ዘካርያስ የጠቀሳቸውን ጾሞችም ሆነ ሕጉ የሚያዝዘውን ጾም አንጾምም። ኢየሱስ ኃጢአታችንን ለማስወገድ ሲል ሕይወቱን ለእኛ አሳልፎ ስለሰጠን ታላቁ የስርየት ቀን የሚያስገኛቸውን በረከቶች በመቋደስ ላይ ነን። ኃጢአታችን በከፊል ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ተሸፍኗል። (ዕብራውያን 9:6-14) ሰማያዊ ሊቀ ካህን የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ በመከተል ክርስቲያኖች የሚያከብሩትን ብቸኛ በዓል ማለትም የሞቱን መታሰቢያ እናከብራለን። (ሉቃስ 22:19, 20) በየዓመቱ ይህን በዓል ለማክበር ስንሰበሰብ “ደስታና ተድላ” አናገኝምን?
15 ባለፈው ዓመት 13,147,201 በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙ ሲሆን ይህ ቁጥር ከ1994 በ858,284 ይበልጣል። እጅግ ብዙ ሰዎች ናቸው! ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በዓሉን ለማክበር ወደ 78,620 ጉባኤዎች ሲጎርፉ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። በእርግጥም በበዓሉ ላይ የተገኙት ሁሉ “መንገድና እውነት ሕይወትም” የሆነውንና በአሁኑ ወቅት ይሖዋ የሾመው ታላቅ ‘የሰላም መስፍን’ ሆኖ በመግዛት ላይ የሚገኘውን የኢየሱስን ሞት ሲያስቡ “እውነትንና ሰላምን” ለመውደድ ተገፋፍተዋል። (ዮሐንስ 14:6፤ ኢሳይያስ 9:6) ሁከትና ጦርነት ከፍተኛ ሥቃይ ባስከተሉባቸው አገሮች ውስጥ ይህን በዓል ላከበሩ ሰዎች በዓሉ ልዩ ትርጉም ነበረው። በ1995 አንዳንድ ወንድሞቻችን በቃላት ሊገለጽ የማይችል ሰቆቃ ተመልክተዋል። ያም ሆኖ ግን ‘አእምሮንም ሁሉ የሚያልፈው የእግዚአብሔር ሰላም ልባቸውንና ሐሳባቸውን በክርስቶስ ኢየሱስ ጠብቆላቸዋል።’—ፊልጵስዩስ 4:7
‘እግዚአብሔርን እንለምን’
16, 17. ከአሕዛብ የተውጣጡ ሰዎች ‘እግዚአብሔርን ሊለምኑ’ የሚችሉት እንዴት ነው?
16 ታዲያ በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት እነዚህ ሁሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከየት መጡ? ይሖዋ ለዘጠነኛ ጊዜ የተናገረው ነገር ይህን ግልጽ ያደርግልናል። “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በብዙ ከተሞች የሚቀመጡ አሕዛብ ገና ይመጣሉ፤ በአንዲትም ከተማ የሚኖሩ ሰዎች፦ እግዚአብሔርን እንለምን ዘንድ፣ የሠራዊትንም ጌታ እግዚአብሔርን እንፈልግ ዘንድ ኑ እንሂድ፤ እኔም እሄዳለሁ እያሉ ወደ ሌላ ከተማ ይሄዳሉ። ብዙ ወገኖችና ኃይለኞች አሕዛብ በኢየሩሳሌም የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ፣ እግዚአብሔርንም ይለምኑ ዘንድ ይመጣሉ።”—ዘካርያስ 8:20-22
17 በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙ ሰዎች ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ይፈልጋሉ።’ ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ ራሳቸውን ወስነው የተጠመቁ አገልጋዮቹ ናቸው። በበዓሉ ላይ የተገኙት ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ገና እዚህ የእድገት ደረጃ ላይ አልደረሱም። በአንዳንድ አገሮች በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት ሰዎች ቁጥር የመንግሥቱ አስፋፊዎችን ቁጥር አራት ወይም አምስት ጊዜ የሚያጥፍ ነበር። እነዚህ ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች እድገት ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ኢየሱስ ኃጢአታችንን ለማስወገድ እንደሞተና በአሁኑ ወቅት በአምላክ መንግሥት በመግዛት ላይ መሆኑን በማወቃቸው እንዲደሰቱ እናስተምራቸው። (1 ቆሮንቶስ 5:7, 8፤ ራእይ 11:15) በተጨማሪም ራሳቸውን ለይሖዋ አምላክ እንዲወስኑና እሱ ለሾመው ንጉሥ እንዲታዘዙ እናበረታታቸው። በዚህ መንገድ ‘ይሖዋን ለመለመን’ ይችላሉ።—መዝሙር 116:18, 19፤ ፊልጵስዩስ 2:12, 13
“ከአሕዛብ ቋንቋ ሁሉ አሥር ሰዎች”
18, 19. (ሀ) በዘካርያስ 8:23 ፍጻሜ መሠረት በአሁኑ ወቅት ‘አንዱ አይሁዳዊ’ የሆኑት እነማን ናቸው? (ለ) በአሁኑ ጊዜ “የአንዱን አይሁዳዊ ሰው የልብስ ዘርፍ” የያዙት “አሥር ሰዎች” እነማን ናቸው?
18 በዘካርያስ ምዕራፍ ስምንት ላይ ለመጨረሻ ጊዜ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” የሚል እናነባለን። ይሖዋ በመጨረሻ የተናገረው ምንድን ነው? “በዚያን ዘመን ከአሕዛብ ቋንቋ ሁሉ አሥር ሰዎች የአንዱን አይሁዳዊ ሰው ልብስ ዘርፍ ይዘው፦ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ ይላሉ።” (ዘካርያስ 8:23) በዘካርያስ ዘመን ሥጋዊ እስራኤላውያን የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች ነበሩ። ሆኖም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እስራኤላውያን ይሖዋ የላከውን መሲሕ ሳይቀበሉ ቀሩ። ስለዚህ አምላካችን ከመንፈሳዊ አይሁዳውያን የተውጣጣውን “የአምላክ እስራኤል” እንደ ልዩ ሕዝቡ አድርጎ ‘አንድ አይሁዳዊ’ ማለትም አንድ አዲስ እስራኤል መረጠ። (ገላትያ 6:16፤ ዮሐንስ 1:11፤ ሮሜ 2:28, 29) በሰማያዊ መንግሥቱ ከኢየሱስ ጋር ለመግዛት ከሰው ልጆች መካከል የተመረጡት የእነዚህ “የአምላክ እስራኤል” አባላት የመጨረሻ ቁጥር 144,000 ነው።—ራእይ 14:1, 4
19 ከእነዚህ 144,000 ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በታማኝነት ሞተው ሰማያዊ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:51, 52፤ ራእይ 6:9-11) በአሁኑ ወቅት በምድር ላይ የቀሩት ጥቂቶች ሲሆኑ ‘ከአይሁዳዊው’ ጋር ለመሄድ የመረጡት “አሥር ሰዎች” በእርግጥም “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ” የተውጣጡ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ሲሆኑ በመመልከታቸው ተደስተዋል።—ራእይ 7:9፤ ኢሳይያስ 2:2, 3፤ 60:4-10, 22
20, 21. የዓለም ፍጻሜ እየተቃረበ ሲመጣ ከይሖዋ ጋር ያለንን ሰላም ጠብቀን ማቆየት የምንችለው እንዴት ነው?
20 የዚህ ዓለም ፍጻሜ እየተቃረበ ሲመጣ በኤርምያስ ዘመን እንደ ነበረችው ኢየሩሳሌም ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም “ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፣ መልካምም አልተገኘም፤ ፈውስን በተስፋ ተጠባበቅን፣ እነሆም፣ ድንጋጤ ሆነ” ትላለች። (ኤርምያስ 14:19) ብሔራት በሐሰት ሃይማኖት ላይ ፊታቸውን አዙረው የሐሰት ሃይማኖቶችን ሲያጠፉ ይህ ድንጋጤ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ብሔራት ራሳቸው በአምላክ የመጨረሻ ጦርነት ማለትም በአርማጌዶን ይጠፋሉ። (ማቴዎስ 24:29, 30፤ ራእይ 16:14, 16፤ 17:16-18፤ 19:11-21) ይህ ጊዜ ምንኛ ያስጨንቅ ይሆን!
21 በዚህ ጊዜ ሁሉ ይሖዋ እውነትን የሚወዱትንና ‘የሰላምን ዘር’ የሚዘሩ ሰዎችን ይጠብቃቸዋል። (ዘካርያስ 8:12፤ ሶፎንያስ 2:3) ስለዚህ ይሖዋን በሕዝብ ፊት በቅንዓት በማወደስና የተቻለንን ያህል ብዙ ሰዎች ‘እግዚአብሔርን እንዲለምኑ’ በመርዳት በአምላክ ሕዝቦች ምድር ውስጥ ከአደጋ ርቀን እንቆይ። ይህን ካደረግን ምን ጊዜም ቢሆን ከይሖዋ ሰላም እናገኛለን። አዎን “እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃይልን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን በሰላም ይባርካል።”—መዝሙር 29:11
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ የአምላክ ሕዝቦች በዘካርያስ ዘመን ‘እጃቸውን ያበረቱት’ እንዴት ነው? በአሁኑ ጊዜስ?
◻ ለስደት፣ ለጥላቻና ለግዴለሽነት ስሜት ምን ምላሽ እንሰጣለን?
◻ ‘ከባልንጀራዎቻችን ጋር እውነትን መነጋገራችን’ ምን ነገሮችን ይጨምራል?
◻ አንድ ሰው ‘እግዚአብሔርን መለመን’ የሚችለው እንዴት ነው?
◻ የዘካርያስ 8:23 ፍጻሜ ለደስታ ታላቅ ምክንያት የሚሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባለፈው ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ለሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት በመናገር 1,150,353,444 ሰዓታት አሳልፈዋል