“እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ” ቀን
“እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል።”—ሚልክያስ 4:1
1. ከሚልክያስ 4:1 ጋር በተያያዘ ምን ጥያቄዎች ይነሣሉ?
በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ይሖዋ ስማቸውን በመታሰቢያ መጽሐፉ ውስጥ ለመጻፍ የመረጣቸው ደስተኞች ናቸው። ይሁን እንጂ ለዚህ መብት ብቁ ያልሆኑት ሰዎችስ? ገዥዎችም ሆኑ ተራ ሰዎች የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎችንና መልእክታቸውን ቢያቃልሉ ምን ይሆናሉ? ሚልክያስ ፍርዳቸውን የሚቀበሉበት ቀን እንደሚመጣ ይናገራል። በምዕራፍ 4 ቁጥር 1 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “እነሆ፣ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፣ ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”
2. ሕዝቅኤል ስለ ይሖዋ ፍርድ ምን ግልጽ መግለጫ ሰጥቷል?
2 ሌሎች ነቢያትም ይሖዋ በአሕዛብ ላይ የሚያመጣውን ፍርድ እጅግ ከፍተኛ በሆነው የምድጃ እሳት መስለዋል። ሕዝቅኤል 22:19–22 በከሃዲዎቹ የሕዝበ ክርስትና ኑፋቄዎች ላይ የሚወርደውን የአምላክ ፍርድ እንዴት ጥሩ አድርጎ ገልጾታል! እንዲህ ይነበባል፦ “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁላችሁ አተላ ሆናችኋልና ስለዚህ . . . እሰበስባችኋለሁ። እንዲያቀልጡት እሳት ያናፉበት ዘንድ ብርንና መዳብን ብረትንና እርሳስን ቆርቆሮንም በከውር እንደሚሰበስቡ፣ እንዲሁ በቁጣዬና በመዓቴ እሰበስባችኋለሁ፣ በዚያም ውስጥ እጨምራችኋለሁ አቀልጣችሁማለሁ። እሰበስባችሁማለሁ የመዓቴንም እሳት አናፋባችኋለሁ በውስጡም ትቀልጣላችሁ። ብርም በከውር ውስጥ እንደሚቀልጥ፣ እንዲሁ በውስጡዋ ትቀልጣላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር መዓቴን እንዳፈሰስሁባችሁ ታውቃላችሁ።”
3, 4. (ሀ) ቀሳውስት ምን እናደርጋለን ብለው በግብዝነት ተናግረዋል? (ለ) ሃይማኖት ምን አስነዋሪ ታሪክ አለው?
3 በእርግጥም በጣም ኃይለኛ የሆነ ምሳሌያዊ አገላለጽ ነው! የይሖዋን ስም ለመጥራት ፈቃደኛ ያልሆኑት አልፎ ተርፎም ቅዱስ ስሙን እስከ መሳደብ የደረሱት ቀሳውስት ይህን የፍርድ ቀን ለመጋፈጥ ይገደዳሉ። እነርሱና የፖለቲካ አጫፋሪዎቻቸው የአምላክን መንግሥት በምድር ላይ እናቋቁማለን ወይም ቢያንስ ቢያንስ ምድርን ለመንግሥቱ መምጣት አመቺ እንድትሆን እናደርጋለን በማለት በትዕቢት ሲናገሩ አያፍሩም።
4 ከሃዲዋ ሕዝበ ክርስትና ከፖለቲካ ገዥዎች ጋር በመጣመር በጣም አሠቃቂ የሆኑ ጦርነቶችን አካሂዳለች። የመካከለኛው ዘመን የመስቀል ጦርነቶች፣ በስፓኒሽ ኢንኩዊዝሽን አማካኝነት የተካሄደው በግድ የማሳመን ድርጊት፣ በጀርመን ግዛቶች በሚኖሩ የሮማ ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች መካከል በተደረገ የእርስ በርስ ጦርነት ጀምሮ ቀስ በቀስ አብዛኞቹን የአውሮፓ አገሮች ያካተተውና በ17ኛው መቶ ዘመን መላውን አውሮፓ ያወደመው የሠላሳ ዓመት ጦርነት እንዲሁም ስፔይን ለካቶሊክ እምነት ምቹ እንድትሆን ለማድረግ በ1930ዎቹ በስፔይን የተደረጉት የእርስ በርስ ጦርነቶች በታሪክ የተመዘገቡ ናቸው። ከሁሉም ይበልጥ ደም የፈሰሰው ግን በዚህ በኛው መቶ ዘመን ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች አለአንዳች ምርጫ መሰል አማኞችንም ሆነ የሌሎች ሃይማኖት አባሎችን በመጨፍጨፍ እርስ በርስ በተጋደሉባቸው ሁለት የዓለም ጦርነቶች ነው። በቅርቡ ደግሞ በአየርላንድ በሚገኙ ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች መካከል፣ በህንድ አገር በሚገኙ ሃይማኖታዊ ክፍሎች መካከልና በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ በሚገኙ ሃይማኖታዊ ቡድኖች መካከል የእርስ በርስ ጦርነት ተደርጎ ብዙ ደም ፈስሷል። ከዚህም በላይ ሃይማኖታዊ የታሪክ ገጾች በሰማዕትነት በሞቱ በሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ደም የቀለሙ ናቸው።—ራእይ 6:9, 10
5. የሐሰት ሃይማኖት ምን ፍርድ ይጠብቀዋል?
5 በቅርቡ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው በታላቂቱ ባቢሎንና በደጋፊዎችዋ ላይ የሚፈጸመው የይሖዋ ፍርድ ፍትሐዊ እንደሚሆን መገንዘብ ከባድ አይሆንብንም። ይህ ፍርድ በራእይ 18:21, 24 ላይ ተገልጿል፦ “አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅን ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንሥቶ ወደ ባሕር ወረወረው እንዲህ ሲል፦ ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም። በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት።”
6. (ሀ) እንደ ገለባ መሆን ያለባቸው እነማን ናቸው? ለምንስ? (ለ) ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎች ምን ዋስትና ተሰጥቷቸዋል?
6 ከጊዜ በኋላ የጽድቅ ጠላቶች በሙሉና አጫፋሪዎቻቸው “ገለባ ይሆናሉ።” የይሖዋ ቀን እንደ ምድጃ እሳት አቃጥሎ ያጠፋቸዋል። “ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም።” በዚያ የፍርድ ቀን ልጆች ወይም ቅርንጫፎች ይሖዋ ሥሮቻቸውን ማለትም እነዚህን ልጆች በበላይነት የሚቆጣጠሩትን ወላጆች መዝኖ በሚያስተላልፈው ብያኔ መሠረት ፍትሐዊ ፍርድ ይሰጣቸዋል። ክፉ ወላጆች የክፋት መንገዳቸውን የሚቀጥልላቸው ትውልድ አይኖራቸውም። በአምላክ መንግሥት ተስፋዎች የሚታመኑ ግን አይናወጡም። በዚህም ምክንያት ዕብራውያን 12:28, 29 የሚከተለውን ምክር ይሰጣል፦ “በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ፤ አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና።”
ይሖዋ ጨካኝ አምላክ ነውን?
7. የይሖዋ ፍቅር በፍርዱ ውስጥ የታየው እንዴት ነው?
7 ታዲያ እንዲህ ሲባል ይሖዋ ጨካኝና ተበቃይ አምላክ ነው ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም! በ1 ዮሐንስ 4:8 ላይ ሐዋርያው “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት አንድ መሠረታዊ እውነት ገልጿል። ከዚያም በቁጥር 16 ላይ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል” በማለት መሠረታዊውን እውነት ጠበቅ አድርጎ ገልጾታል። ይሖዋ ይህችን ምድር ከማንኛውም ዓይነት ክፋት ለማጽዳት ያሰበው ለሰው ልጆች ባለው ፍቅር ምክንያት ነው። አፍቃሪና መሐሪ የሆነው አምላካችን እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፣ . . . ተመለሱ፣ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ?”—ሕዝቅኤል 33:11
8. ዮሐንስ ፍቅርን ጠበቅ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው? ሆኖም እሱ ራሱ የነጎድጓድ ልጅ መሆኑንስ ያሳየው እንዴት ነው?
8 ዮሐንስ በመሠረታዊ ሥርዓት ላይ የተመሠረተውን የአጋፔ ፍቅር ከሦስቱም የወንጌል ጸሐፊዎች በበለጠ ጠቅሶታል። ሆኖም ዮሐንስ በማርቆስ 3:17 ላይ ‘የነጎድጓድ ልጅ’ ተብሏል። ይህ የነጎድጓድ ልጅ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ ክፍል የሆነውንና ይሖዋ ፍትሕን የሚያስፈጽም አምላክ እንደሆነ የሚገልጸውን የራእይ መጽሐፍ የጻፈው በይሖዋ መንፈስ አነሣሽነት ነበር። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ለይሖዋ ፍርድ መግለጫነት ያገለገሉ ብዙ አገላለጾች አሉ። ‘ታላቁ የእግዚአብሔር ቁጣ መጥመቂያ፣’ ‘ሰባቱ የእግዚአብሔር ቁጣ ጽዋዎች፣’ ‘ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሔር ብርቱ ቁጣ’ የሚሉት መግለጫዎች ከእነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው።—ራእይ 14:19፤ 16:1፤ 19:15
9. ኢየሱስ የይሖዋን ፍርድ በተመለከተ ምን አገላለጾች ተጠቅሟል? ትንቢቶቹስ የተፈጸሙት እንዴት ነው?
9 ‘የማይታየው አምላክ ምሳሌ’ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እዚህ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የይሖዋን ፍርድ በድፍረት አውጆአል። (ቆላስይስ 1:15) ለምሳሌ ያህል በዘመኑ ለነበሩት ሃይማኖታዊ ግብዞች ፊት ለፊት የተናገራቸው የማቴዎስ ምዕራፍ 23 ሰባት ወዮታዎች አሉ። ይህን የውግዘት ፍርዱን የደመደመው በሚከተሉት ቃላት ነበር፦ “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፣ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ፣ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።” ይህ ፍርድ ከሰላሳ ሰባት ዓመታት በኋላ በጀኔራል ቲቶ ይመራ በነበረው የሮማ ሠራዊት ተፈጸመ። በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ታይቶ ለማያውቀውና በቅርቡ ለሚመጣው እጅግ አስፈሪ የይሖዋ ቀን በትንቢታዊ ጥላነት የሚያገለግል አስፈሪ ቀን ነበር።
“ፀሐይ” ይወጣል
10. “የጽድቅ ፀሐይ” ለአምላክ ሕዝቦች ደስታን የሚያመጣላቸው እንዴት ነው?
10 ይሖዋ ከእሱ ቀን በሕይወት የሚተርፉ እንደሚኖሩ አሳውቋል። እነዚህን ሰዎች በሚልክያስ 4:2 ላይ እንዲህ በማለት ጠቅሷቸዋል፦ “ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች፣ ፈውስም በክንፎችዋ ውስጥ ይሆናል።” ይህ የጽድቅ ፀሐይ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። እርሱ መንፈሳዊ “የዓለም ብርሃን” ነው። (ዮሐንስ 8:12) ታዲያ ኢየሱስ ብርሃኑን የሚያበራው እንዴት ነው? በክንፎቹ ፈውስ ይዞ በመነሳት መጀመሪያ በአሁኑ ጊዜ እንኳን እያገኘን ያለነውን መንፈሳዊ ፈውስ፣ በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ ደግሞ ለአሕዛብ ሁሉ አካላዊ ፈውስ ያስገኛል። (ማቴዎስ 4:23፤ ራእይ 22:1, 2) በምሳሌያዊ አነጋገር ሚልክያስ እንዳለው ፈውስ ያገኙት ሰዎች ከበረቱ እንደተለቀቀ ‘የሰባ እምቦሳ ይፈነጫሉ።’ የሙታን ትንሣኤ የሚያገኙትም ሰብዓዊ ፍጽምና የማግኘት ተስፋ አግኝተው ሲነሱ እንዴት ያለ ደስታ ይሆናል!
11, 12. (ሀ) ክፉዎች ምን ዕድል ይጠብቃቸዋል? (ለ) የአምላክ ሕዝቦች ‘ክፉዎችን የሚረግጧቸው’ እንዴት ነው?
11 ክፉዎቹስ? በሚልክያስ 4:3 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “በምሠራበት ቀን በደለኞች ከእግራችሁ ጫማ በታች አመድ ይሆናሉና እናንተ ትረግጡአቸዋላችሁ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” ተዋጊው አምላካችን እርሱን የሚወዱትን በመጠበቅ ጨካኝ ጠላቶቹን ከምድር ገጽ ጠራርጎ ያጠፋል። ሰይጣንና አጋንንቱም ይታሠራሉ።—መዝሙር 145:20፤ ራእይ 20:1–3
12 የአምላክ ሕዝቦች ክፉዎችን በማጥፋት ሥራ አይካፈሉም። ታዲያ ‘ክፉዎችን የሚረግጡት’ በምን መንገድ ነው? ታላቅ በሆነ የድል በዓል በመካፈል በምሳሌያዊ ሁኔታ ይረግጧቸዋል። ዘጸአት 15:1–21 ይህን ስለመሰለው በዓል ይገልጻል። ይህ በዓል የተከበረው ፈርዖንና ሠራዊቱ በቀይ ባሕር ከጠፉ በኋላ ነበር። በኢሳይያስ 25:3–9 ፍጻሜ መሠረት “ጨካኞች” ከጠፉ በኋላ ቀጥሎ ከተገለጸው የአምላክ ተስፋ ጋር የተያያዘ ታላቅ የድል ግብዣ ይደረጋል፦ “ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፣ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና። በዚያም ቀን፦ እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል . . . በማዳኑ ደስ ይለናል፣ ሐሤትም እናደርጋለን ይባላል።” ይህ ደስታ የይሖዋ ስም ሲቀደስና ምድር አንድነት ላገኘ የሰው ልጅ ሰላማዊ መኖሪያ እንድትሆን ስትጸዳ ከማየት የመነጨ እንጂ ከተበቃይነት መንፈስ ወይም ከጉረኝነት የመነጨ አይደለም።
ታላቅ የትምህርት ፕሮግራም
13. ‘በአዲሲቷ ምድር’ ምን ትምህርት ይካሄዳል?
13 በሚልክያስ 4:4 ላይ አይሁዳውያን ‘የሙሴን ሕግ እንዲያስቡ’ ተመክረዋል። ስለዚህ እኛም ዛሬ በገላትያ 6:2 ላይ የተጠቀሰውን “የክርስቶስን ሕግ” መከተል ያስፈልገናል። ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች በዚህ የክርስቶስ ሕግ ላይ የተመሠረተ ተጨማሪ ትምህርት እንደሚሰጣቸው አያጠራጥርም። እነዚህም ተጨማሪ ትምህርቶች በትንሣኤ ጊዜ በሚከፈቱት የራእይ 20:12 “ጥቅልሎች” ውስጥ ሊጻፉ ይችላሉ። ከሙታን የሚነሡት ሰዎች ‘የአዲሲቷን ምድር’ የአኗኗር ሥርዓት እንዲከተሉ የሚያስችላቸው ትምህርት ሲሰጣቸው ምንኛ ታላቅ ቀን ይሆናል!—ራእይ 21:1
14, 15. (ሀ) ዘመናዊው ኤልያስ ተለይቶ ሊታወቅ የቻለው እንዴት ነው? (ለ) የኤልያስ ክፍል ምን ኃላፊነት ያከናውናል?
14 በሚልክያስ 4:5 ላይ የተመዘገበው ይሖዋ የተናገረለት የማስተማር ሥራ ወደዚያው ዘመን ይዘልቃል። ይህ ጥቅስ “እነሆ፣ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ” ይላል። ይህ ዘመናዊ ኤልያስ ማን ነው? በማቴዎስ 16:27, 28 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ ‘በመንግሥቱ ስለሚመጣበት ሁኔታ’ በመጥቀስ እንዲህ ብሏል፦ “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል።” ከስድስት ቀናት በኋላ በአንድ ተራራ ላይ ከጴጥሮስ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር እንዳለ አካሉ “ተለወጠ፣ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፣ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ።” በዚህ ጊዜ ብቻውን ነበርን? የለም አልነበረም። “እነሆም፣ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።”—ማቴዎስ 17:2, 3
15 የዚህ ትርጉም ምንድን ነው? ኢየሱስ ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ አስቀድሞ ትንቢት የተነገረለት ታላቁ ሙሴ እንደሚሆን ያመለክታል። (ዘዳግም 18:18, 19፤ ሥራ 3:19–23) በዚህ ጊዜ አስፈሪ የሆነው የይሖዋ ቀን ሳይመጣ የመንግሥቱ ምሥራች በመላዋ ምድር እንዲሰበክ ለማድረግ ከዘመናዊው ኤልያስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ይኖረዋል። ሚልክያስ 4:6 የዚህን “ኤልያስ” ሥራ በመግለጽ እንዲህ ይላል፦ “መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል።” በመሆኑም “ኤልያስ” ጌታው ኢየሱስ ንብረቱን በሙሉ በአደራ የሰጠው በምድር ላይ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያቀፈ የታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል እንደሆነ ማወቅ ተችሏል። ለዚህ ባሪያ የተሰጠው ሥራ ለእምነት ቤተሰቦች የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ‘ምግብ በጊዜው መስጠትን’ ይጨምራል።—ማቴዎስ 24:45, 46
16. የኤልያስ ክፍል በሚሠራው ሥራ ምን አስደሳች ውጤቶች ተገኝተዋል?
16 ይህ የመመገብ ሥራ በዛሬው ጊዜ በመላው ምድር ላይ ያስገኘውን አስደሳች ውጤት ለመመልከት እንችላለን። በ16,100,000 ቅጂዎችና በ120 ቋንቋዎች የሚታተመው መጠበቂያ ግንብ የተባለው መጽሔት ምድርን ‘በመንግሥቱ ምሥራች’ በማጥለቅለቅ ላይ ይገኛል፤ ከእነዚህም መካከል በ97 ቋንቋዎች የሚዘጋጁት እትሞች በአንድ ጊዜ የሚወጡ ናቸው። (ማቴዎስ 24:14) በበርካታ ቋንቋዎች የሚዘጋጁ ሌሎች ጽሑፎችም የይሖዋ ምሥክሮች በሚያከናውኑት የተለያየ የስብከትና የማስተማር ሥራ በማገልገል ላይ ናቸው። የኤልያስ ክፍል፣ ማለትም ታማኝና ልባም ባሪያ ‘በመንፈሳዊ የጎደላቸው ነገር እንዳለ ለሚታወቃቸው’ ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን አትረፍርፎ ለማቅረብ ንቁ ነው። (ማቴዎስ 5:3 አዓት) ከዚህም በላይ ይህን የመንግሥቱን ተስፋ ተቀብለው እርምጃ የሚወስዱ ሁሉ በአስደናቂው ዓለም አቀፋዊ አንድነት ይታቀፋሉ። ይህ ዓለም አቀፋዊ አንድነት “ከሕዝብ፣ ከነገድ ከቋንቋ የተውጣጡ” እጅግ ብዙ ሰዎችን የያዘ ነው። (ራእይ 7:9) ይህ ሥራ ይሖዋ በሚፈልገው መጠን ሲከናወን መጨረሻው በታላቁና በአስፈሪው የይሖዋ ቀን ላይ ይመጣል።
17. እጅግ አስፈሪ የሆነው የይሖዋ ቀን የሚጀምረው መቼ ነው?
17 ይህ አስፈሪ ቀን የሚመጣው መቼ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል መልስ ይሰጠናል፦ “የጌታ ቀን ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፣ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። [ምናልባትም በዓይነቱ ልዩ በሆነ መንገድ ሊሆን ይችላል] ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።”—1 ተሰሎንቄ 5:2, 3
18, 19. (ሀ) “ሰላምና ደህንነት” የሚታወጀው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ሕዝቦች እፎይታ የሚያገኙት መቼ ነው?
18 እዚህ ትንቢት ላይ የተጠቀሱት ሰዎች እነማን ናቸው? እነዚህ ሰዎች የዚህን ዓመፀኛ ዓለም የተበታተኑ ክፍሎች አንድ ላይ በማስተሳሰር አንድ አዲስ ሥርዓት እንገነባለን ብለው የሚፎክሩት የፖለቲካ መሪዎች ናቸው። የፈጠሯቸው ታላላቅ ድርጅቶች ማለትም የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርና የተባበሩት መንግሥታት ይህን ዓላማ ዳር ማድረስ አልቻሉም። የይሖዋ ነቢይ አስቀድሞ እንደተናገረው አሁንም እንኳ “ሰላም ሳይሆን፦ ሰላም ሰላም ይላሉ።”—ኤርምያስ 6:14፤ 8:11፤ 14:13–16
19 ይህ እስኪሆን ድረስ ግን የይሖዋ ሕዝቦች ይህ አምላክ የለሽ ዓለም የሚያመጣባቸውን ግፊትና ስደት በጽናት ይቋቋማሉ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ 2 ተሰሎንቄ 1:7, 8 ላይ እንደተገለጸው እፎይታ ያገኛሉ። “ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ሲገለጥ፣ . . . እግዚአብሔርን የማያውቁትን፣ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል።”
20. (ሀ) ሶፎንያስና ዕንባቆም ‘እንደ ምድጃ እሳት ስለሚነድደው’ ቀን ምን ትንቢት ተናግረዋል? (ለ) እነዚህ ትንቢቶች ምን ምክርና ማበረታቻ ይሰጣሉ?
20 ይህ የሚሆንበት ጊዜ ምን ያህል ቀርቧል? ብዙዎቻችን ይህን ቀን ስንጠብቅ ረዘም ያለ ጊዜ አሳልፈናል። በዚህ ጊዜ ከጥፋቱ የሚድኑ ብዙ ቅን ሰዎች ሶፎንያስ 2:2, 3 ላይ ለሚገኘው “እግዚአብሔርን ፈልጉ፣ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ። ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል” ለሚለው ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ላይ ናቸው። ከዚያም ሶፎንያስ 3:8 የሚከተለውን ምክር ይዟል፦ “መዓቴንና የቁጣዬን ትኩሳት ሁሉ አፈስስባቸው ዘንድ ፍርዴ አሕዛብን ለመሰብሰብ፣ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነውና፣ ምድርም ሁሉ በቅንዓቴ እሳት ትበላለችና ስለዚህ ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ፣ ይላል እግዚአብሔር።” መጨረሻው በጣም ቀርቧል! ይሖዋ ቀኑንና ሰዓቱን ያውቃል፤ ፕሮግራሙንም ፈጽሞ አይለውጥም። ይህን ቀን በትዕግሥት ጸንተን እንጠባበቅ። “ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፣ ወደ ፍጻሜውም ይቸኩላል፣ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም።” (ዕንባቆም 2:3) እጅግ አስፈሪ የሆነው የይሖዋ ቀን ከምንጊዜውም በበለጠ ፍጥነት እየተቃረበ ነው። ቀኑ የማይዘገይ መሆኑን አትዘንጉ!
ለክለሳ ያህል፦
◻ እጅግ አስፈሪ በሆነው የይሖዋ ቀን ገዥዎችም ሆኑ ተገዢዎች ምን ይደረጋሉ?
◻ ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ ነው?
◻ ለአምላክ ሕዝቦች ምን ዓይነት ትምህርት ተገልጾላቸዋል?
◻ የፍጻሜውን መቅረብ በተመለከተ የአምላክ ነቢያት ምክር የሰጡን እንዴት ነው?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስፓኒሽ ኢንኩዊዝሽን ወቅት ብዙዎች በግድ ካቶሊኮች እንዲሆኑ ተደርጓል
[ምንጭ]
The Complete Encyclopedia of Illustration/ J. G. Heck