በመጨረሻ—ሁሉም ሰው ፍትሕ ያገኛል
“የተጎዱ፣ የተጨነቁና ሰሚ ጆሮ በመነፈጋቸው ተስፋ የቆረጡ ሰዎችን ድምፅ በአዲስ መልክ ለመስማት እንጥራለን። . . . አሁን የሚቀረው ነገር በሕግ ላይ ሰፍሮ የሚገኘውን ነገር ተግባራዊ ማድረግ፣ ይኸውም ማንኛውም ሰው በአምላክ ፊትም ሆነ በሰው ፊት እኩል ክብር ያለው ሆኖ እንደተወለደ ሁሉም ሰው እንዲገነዘብ ማድረግ ነው።”—የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሪቻርድ ሚልሆስ ኒክሰን ሥልጣን በተረከቡበት ጊዜ ያደረጉት ንግግር፣ ጥር 20, 1969
ነገሥታት፣ ፕሬዚዳንቶችና ጠቅላይ ሚንስትሮች ሥልጣን በሚረከቡበት ጊዜ በአብዛኛው ስለ ፍትሕ መናገራቸው አይቀርም። የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰንም ያደረጉት ይህንኑ ነበር። ይሁን እንጂ ታሪክ እንደሚያሳየው እነዚያ ያማሩ ቃላት ትርጉም የለሽ ሆነው ቀርተዋል። ኒክሰን ‘ሕግን ተግባራዊ ለማድረግ’ እንደሚጥሩ ይናገሩ እንጂ ወደ ኋላ ላይ ሕግን ጥሰው በመገኘታቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል። ይህ ከሆነ ከሦስት አሥርተ ዓመታት በኋላም ‘የተጎዱ፣ የተጨነቁና ተስፋ የቆረጡ ሰዎች ድምፆች’ የሰሚ ያለህ እያሉ ናቸው።
ጥሩ ለማድረግ አስበው የተነሱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መሪዎች እንደተገነዘቡት እንዲህ ያሉትን ድምፆች መስማትና ለችግራቸው መፍትሔ መስጠት ቀላል አይደለም። ‘ፍትሕ ለሁሉም’ የሚለው መፈክር የማይደረስበት ግብ ሆኗል። ሆኖም ፍትሕን በተመለከተ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባን ከብዙ ሺህ ዘመናት በፊት የተሰጠ አንድ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ተስፋ አለ።
አምላክ ራሱ የመረጠውን ‘አገልጋይ’ እንደሚልክላቸው በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ለሕዝቡ አረጋግጦላቸው ነበር። ይሖዋ “መንፈሴ በእርሱ እንዲያድርበት አደርጋለሁ” ብሏቸዋል። “እርሱ ለሕዝቦች ሁሉ ትክክለኛ ፍትሕን ያስገኛል።” (ኢሳይያስ 42:1-3 የ1980 ትርጉም) የትኛውም ሰብዓዊ መሪ እንዲህ ያለውን ለሁሉም ብሔር ዘላቂ ፍትሕ የሚያስገኝ መጠነ ሰፊ አዋጅ ሊያስነግር አይችልም። ይህ ተስፋ እምነት ሊጣልበት የሚችል ነው? እንዲህ ያለው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ነገር ፍጻሜውን ሊያገኝ ይችላልን?
እምነት ልንጥልበት የምንችል ተስፋ
የአንድ ተስፋ አስተማማኝነት ተስፋውን በሰጠው አካል ላይ የተመካ ነው። እዚህ ላይ ‘አገልጋዩ’ በዓለም ዙሪያ ፍትሕን እንደሚያሰፍን የተናገረው ሁሉን ቻይ አምላክ እንጂ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ይሖዋ እንደ ፖለቲካ ሰዎች አይደለም፤ የገባውን ቃል አቅልሎ አይመለከትም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ ሊዋሽ አይችልም’ ሲል ያረጋግጥልናል። (ዕብራውያን 6:18) አምላክ “ያቀድሁት ነገር ሁሉ ተፈጻሚ ይሆናል” በማለት ጠበቅ አድርጎ ተናግሯል።—ኢሳይያስ 14:24 የ1980 ትርጉም
በዚህ ተስፋ ላይ ያለን እምነት በአምላክ በተመረጠው ‘አገልጋይ’ ማለትም በኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወት ታሪክ ይበልጥ ሊጠናከር ይችላል። ፍትሕን የሚያሰፍነው አካል ፍትሕን መውደድና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መኖር አለበት። ኢየሱስ ‘ጽድቅን በመውደድና ዓመፅን በመጥላት’ እንከን የሌለበት ታሪክ ትቶልናል። (ዕብራውያን 1:9) የተናገረው፣ ያደረገውና የሞተበት ሁኔታ እንኳ ሳይቀር በትክክል የፍትሕ ሰው መሆኑን አረጋግጧል። ኢየሱስ ሲፈረድበትና ሲገደል የተመለከተ አንድ የሮማ ሠራዊት ሹም ኢየሱስ ሲሞት “ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ” ብሎ ለመናገር ተገፋፍቶ ነበር።—ሉቃስ 23:47
ኢየሱስ ራሱ በጽድቅ መንገድ ከመመላለሱም በላይ በዘመኑ ተስፋፍቶ የነበረውን የፍትሕ መጓደልም ተቃውሟል። ይህን ያደረገው በኅቡዕ በመንቀሳቀስ ወይም አብዮት በማካሄድ ሳይሆን ጆሮ ለሚሰጠው ሁሉ እውነተኛ ፍትሕን በማስተማር ነበር። የተራራ ስብከቱ እውነተኛ ፍትሕና ጽድቅ እንዴት ተግባራዊ ሊደረጉ እንደሚገባ የሚገልጽ ድንቅ ማብራሪያ ነው።—ማቴዎስ ምዕራፍ 5-7
ኢየሱስ የሚሰብከውን ነገር ተግባራዊ ያደርግ ነበር። የአይሁድ ማኅበረሰብ “የሚጸየፋቸውን” ምስኪን ለምጻሞች አልናቀም። ከዚህ ይልቅ ያነጋግራቸው፣ ይዳስሳቸውና ይፈውሳቸው ነበር። (ማርቆስ 1:40-42) ድሆችንና የተጨቆኑ ሰዎችን ጨምሮ የሚያገኛቸው ሰዎች በሙሉ ለእሱ ተፈላጊዎች ነበሩ። (ማቴዎስ 9:36) “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” ብሏቸዋል።—ማቴዎስ 11:28
ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢየሱስ በዙሪያው የነበረው የፍትሕ መጓደል እንዲበክለው ወይም እንዲያስመርረው አልፈቀደም። ክፉን በክፉ አልመለሰም። (1 ጴጥሮስ 2:22, 23) አሰቃቂ በሆነ ሥቃይ ውስጥ በነበረበት ጊዜ እንኳ የሰቀሉትን ወታደሮች አስመልክቶ ሰማያዊው አባቱ ጸልዮአል። “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለት ለምኗል። (ሉቃስ 23:34) በእርግጥም ኢየሱስ ‘ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነ ለአሕዛብ ሁሉ ግልጽ አድርጓል።’ (ማቴዎስ 12:18) አምላክ ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም ለማምጣት ፍላጎት እንዳለው ለማረጋገጥ ከገዛ ልጁ ሕያው ምሳሌነት የበለጠ ምን ማስረጃ ያስፈልገናል?
የፍትሕ መጓደል ሊወገድ ይችላል
የፍትሕ መጓደል ሊወገድ እንደሚችል የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ በጊዜያችንም ይገኛል። በግለሰብም ሆነ በድርጅት ደረጃ የይሖዋ ምሥክሮች ጭፍን ጥላቻን፣ መድሎን፣ ጎሠኛነትንና ዓመፅን ለማስወገድ ይጥራሉ። የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት።
ፔድሮa በሚኖርበት የስፔይን ክፍለ ግዛት በሆነው በባስክ ክልል ፍትሕን ለማስፈን ብቸኛው መንገድ በኅቡዕ በመንቀሳቀስ መንግሥትን መገልበጥ ነው የሚል እምነት ነበረው። ውጥኑን ለማሳካት ሲልም የአንድ አሸባሪዎች ድርጅት አባል በመሆን በፈረንሳይ የውትድርና ሥልጠና ወሰደ። ሥልጠናውን ካጠናቀቀ በኋላ አንድ የአሸባሪዎች ቡድን እንዲያቋቁምና አንድ የፖሊሶች ሰፈር እንዲደመስስ ትእዛዝ ተሰጠው። ቡድኑ ፈንጂዎቹን በማዘጋጀት ላይ እያለ ፔድሮ በፖሊሶች ተይዞ ታሰረ። ለ18 ወራት ያህል በእስር ቤት ታስሮ ይቆይ እንጂ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረጉን አላቆመም ነበር። የረሃብ አድማ ያደርግ ነበር፤ እንዲሁም በአንድ ወቅት የእጆቹን አንጓዎች ቆርጦ ነበር።
ፔድሮ የሚታገለው ለፍትሕ እንደሆነ ያምን ነበር። ከዚያ በኋላ ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ይሰማል። ፔድሮ እስር ቤት ውስጥ በነበረበት ጊዜ ሚስቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራ ነበር። ከዚያም ባሏ ከእስር ሲለቀቅ በስብሰባቸው ላይ እንዲገኝ ጋበዘችው። በስብሰባው በመደሰቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግለት ጥያቄ አቀረበ። ጥናቱም አመለካከቱንና አኗኗሩን በእጅጉ እንዲለውጥ አደረገው። በመጨረሻም ፔድሮ ከባለቤቱ ጋር በ1989 ተጠመቀ።
ፔድሮ “አሸባሪ በነበርኩባቸው ዓመታት የማንንም ሰው ሕይወት ባለማጥፋቴ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ” በማለት ተናግሯል። “አሁን የእውነተኛ ሰላምና የፍትሕ መልእክት ስለሆነው ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ለመንገር የአምላክ መንፈስ ሰይፍ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን እጠቀማለሁ።” በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው ፔድሮ ቀደም ሲል ሊያጠፋው አስቦት ወደነበረው ሰፈር ከጥቂት ጊዜ በፊት ሄዶ ነበር። በዚህ ጊዜ የሄደው በዚያ አካባቢ ለሚኖሩ ቤተሰቦች የሰላም መልእክት ለመስበክ ነበር።
የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን ለውጦች የሚያደርጉት ጽድቅ የሚሰፍንበት ዓለም ለማየት ስለሚናፍቁ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:13) እንዲህ ያለውን ዓለም እንደሚያመጣ በሚገልጸው የአምላክ ተስፋ ሙሉ በሙሉ ቢታመኑም ከፍትሕ ጋር በሚስማማ መንገድ የመኖር ግዴታ እንዳለባቸውም ይገነዘባሉ። አምላክ የድርሻችንን እንድንወጣ እንደሚፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል።
የጽድቅ ዘሮችን መዝራት
እርግጥ ነው ፍትሕ ሲጓደልብን “የፍርድ [“የፍትሕ፣” NW] አምላክ ወዴት አለ?” ብለን ለመጮኽ ይዳዳን ይሆናል። ይህ በሚልክያስ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን ያሰሙት ጩኸት ነበር። (ሚልክያስ 2:17) ልመናቸው በአምላክ ፊት ተቀባይነት አግኝቶ ነበርን? አላገኘም፤ እንዲያውም ልመናቸው ‘ሰልችቶት’ ነበር። ምክንያቱም ሌሎች መጥፎ ነገሮችን መፈጸማቸው ሳያንስ በዕድሜ የገፉ ሚስቶቻቸውን በማታለል ሰንካላ በሆኑ ምክንያቶች ይፈቷቸው ነበር። ይሖዋ ‘የልጅነት ሚስቶቻቸው ባልንጀሮቻቸውና የቃል ኪዳናቸው ሚስቶች ሆነው ሳሉ እነርሱን ማታለላቸው’ አሳስቦት ነበር።—ሚልክያስ 2:14
ራሳችን ፍትሕ የጎደለው ድርጊት እየፈጸምን ስለ ፍትሕ መጓደል ቅሬታ ማሰማታችን ተገቢ ነውን? በሌላ በኩል ግን ጭፍን ጥላቻንና ዘረኝነትን ከልባችን ነቅለን በማውጣት፣ አድሏዊነትን በማስወገድና ሁሉንም ሰው በመውደድ እንዲሁም ክፉን በክፉ ባለመመለስ ኢየሱስን የምንኮርጅ ከሆነ በእውነት ፍትሕን የምንወድ መሆናችንን እናሳያለን።
መጽሐፍ ቅዱስ ፍትሕን ለማጨድ ከፈለግን ‘በጽድቅ መዝራት’ እንዳለብን ያሳስበናል። (ሆሴዕ 10:12) ምንም ያህል ትንሽ ቢመስል በፍትሕ መጓደል ላይ የምንቀዳጀው እያንዳንዱ ድል ተፈላጊ ነው። ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ሌተር ፍሮም በርሚንግሃም ጄይል በተባለው ጽሑፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት “በየትኛውም ቦታ የሚፈጸም የፍትሕ መጓደል በሁሉም ስፍራ ለሚገኝ ፍትሕ አስጊ ነው።” በቅርቡ የሚመጣውን ጽድቅ የሰፈነበትን አዲስ ዓለም እንዲወርሱ አምላክ የመረጣቸው ‘ጽድቅ ፈላጊዎች’ የሆኑትን ነው።—ሶፎንያስ 2:3
የሰው ልጆች ፍትሕ ለማስፈን በሚሰጡት አስተማማኝ ያልሆነ ተስፋ ልንታመን አንችልም። ሆኖም የአፍቃሪውን ፈጣሪያችንን ቃል ለማመን እንችላለን። ኢየሱስ ተከታዮቹ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ መጸለያቸውን እንዲቀጥሉ የነገራቸው ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10) በዚህ መንግሥት ላይ ንጉሥ ሆኖ የተሾመው ኢየሱስ “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል።”—መዝሙር 72:12, 13
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የፍትሕ መጓደል ዘላቂ የሆነ ነገር አይደለም። ክርስቶስ በምድር ሁሉ ላይ ሲገዛ የፍትሕ መጓደልን ለዘላለም እንደሚያስወግድ አምላክ እንደሚከተለው በማለት በነቢዩ ኤርምያስ በኩል ማረጋገጫ ሰጥቶናል:- “[የገባሁትን] የተስፋ ቃል የምፈጽምበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ በዚያን ጊዜ የዳዊት ዘር ቅርንጫፍ የሆነ አንድ ጻድቅ ንጉሥ እመርጣለሁ፤ ያም ንጉሥ በአገሪቱ ላይ ቅን የሆነውን ነገር ያደርጋል፤ ትክክለኛ ፍትሕም ይሰጣል።”—ኤርምያስ 33:14, 15 የ1980 ትርጉም
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሙ በሌላ ተተክቷል።