አስፈሪው የይሖዋቀን ቀርቧል
“እግዚአብሔርንም ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ።”—ሚልክያስ 3:16
1, 2. ሚልክያስ አስቀድሞ ያስጠነቀቀው ስለ የትኛው እጅግ አስፈሪ የሆነ ቀን ነው?
በጣም አስፈሪ ነበር! ነሐሴ 6 ቀን 1945 ገና ጎሕ እንደ ቀደደ አንዲት ትልቅ ከተማ በቅጽበት ወደመች። 80,000 የሚያክሉ ሰዎች ሞቱ! በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት በሚያደርስ ሁኔታ ቆሰሉ! ከተማዋ እንዳለች ነደደች! ይህን ሁሉ ጥፋት ያስከተለው የኑክሌር ቦምብ ፍንዳታ ነበር። በዚህ ታላቅ እልቂት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ምን ደረሰባቸው? በዚያ ጊዜ በሂሮሺማ ከተማ የነበረው በክርስቲያናዊ ገለልተኝነቱ ምክንያት ታስሮ በወህኒ ቤት ቅጥር ውስጥ የነበረ አንድ የይሖዋ ምሥክር ብቻ ነበር። እስር ቤቱ ወድሞ የፍርስራሽ ክምር ቢሆንም በወንድማችን ላይ ግን ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰም። ራሱ እንደተናገረው የአቶም ቦምቡ ፍንዳታ ከእስር አውጥቶታል። ምናልባት ቦምቡ ያስገኘው ጥሩ ነገር ይህ ብቻ ሳይሆን አይቀርም።
2 ይህ ፍንዳታ አስፈሪ መሆኑ ባይካድም ከፊታችን ከሚጠብቀን ‘ከታላቁና ከሚያስፈራው የይሖዋ ቀን’ ጋር ሲወዳደር ከቁጥር የሚገባ አይደለም። (ሚልክያስ 4:5) አዎን፣ ባለፉት ዘመናት ብዙ አስፈሪ ቀኖች ታይተዋል፤ ይሁን እንጂ ይሄኛው የይሖዋ ቀን ካለፉት ሁሉ የበለጠ ይሆናል።—ማርቆስ 13:19
3. ‘ሥጋን በለበሰ ሁሉና’ በኖኅ ቤተሰብ መካከል እስከ ጥፋት ውኃው ጊዜ ድረስ በነበረው ሁኔታ ምን ልዩነት ነበር?
3 በኖኅ ዘመን “ሥጋን የለበሰ ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ” ነበር፤ አምላክም “ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ” ሲል ተናግሯል። (ዘፍጥረት 6:12, 13) በማቴዎስ 24:39 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው “የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ” ኢየሱስ ተናግሯል። “የጽድቅ ሰባኪ” የነበረው ታማኙ ኖኅ ግን ፈሪሃ አምላክ ከነበረው ቤተሰቡ ጋር ከጥፋት ውኃው ድኗል።—2 ጴጥሮስ 2:5
4. በሰዶምና ገሞራ ላይ የደረሰው ሁኔታ ምን ዓይነት የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆነናል?
4 ይሁዳ 7 “እንዲሁም . . . ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል” በማለት ይገልጻል። እነዚህ ለአምላክ አክብሮት የሌላቸው ሰዎች በጣም በረከሰ አኗኗራቸው የተነሣ ጠፍተዋል። የጾታ ብልግና ክፉኛ የተጠናወታቸው የዚህ የዘመናዊው ዓለም ማኅበረሰቦች ይጠንቀቁ! ይሁን እንጂ የይሖዋ አምላኪዎች በጣም እየቀረበ ባለው ታላቅ መከራ ወቅት ጥበቃ እንደሚያገኙ ሁሉ ሎጥና ሴቶች ልጆቹ በሕይወት ተጠብቀው ከዚያ ጥፋት እንደተረፉ ልብ በል።—2 ጴጥሮስ 2:6–9
5. በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው ፍርድ ምን ልንማር እንችላለን?
5 ይሖዋ ወራሪ ሠራዊቶች በአንድ ወቅት “የምድር ሁሉ ደስታ” የነበረችውን ታላቂቱን ከተማ ኢየሩሳሌም ጠራርገው እንዲያጠፉ ባደረገ ጊዜ የተፈጸሙትን የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች የሚሆኑ ሁኔታዎችንም ተመልከት። (መዝሙር 48:2) እነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች የተከሰቱት በመጀመሪያ በ607 ከዘአበ ከዚያም በ70 እዘአ ሲሆን ይህ የሆነው የአምላክ ሕዝቦች እውነተኛ አምልኮን በመተዋቸው ምክንያት ነበር። ደስ የሚለው ግን ከይሖዋ ጎን በታማኝነት የቆሙ አገልጋዮቹ በሕይወት መትረፋቸው ነው። በ70 እዘአ የደረሰው ጥፋት (ከታች በሥዕላዊ መግለጫ የሚታየው) “እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ” ተብሎ ተገልጿል። የከሃዲውን የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ያጠፋና ከዚህ አንጻርም ሲታይ ‘እንደገና የማይሆን’ መከራ ነበር። (ማርቆስ 13:19) ይሁን እንጂ ይህ መለኮታዊ ፍርድ መላው የነገሮች ሥርዓት ዓለም በአሁኑ ጊዜ ለተደቀነበት ‘ታላቅ መከራ’ ጥላ ነበር።—ራእይ 7:14
6. ይሖዋ ከፍተኛ ጥፋቶች እንዲደርሱ የሚፈቅደው ለምንድን ነው?
6 አምላክ የብዙ ሰዎች ሕይወት እንዲቀጠፍ ያደረጉ አሠቃቂ ጥፋቶች እንዲደርሱ የፈቀደው ለምንድን ነው? በኖኅ ዘመን፣ በሰዶምና ገሞራ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ላይ ይሖዋ የጥፋት ፍርድ የበየነው በምድር ላይ አካሄዳቸውን ባበላሹ፣ ይቺን ውብ ምድር ቃል በቃል በመበከልና በረከሰ ሥነ ምግባር ባበላሹና እውነተኛ አምልኮን በካዱ ወይም ወደ ጎን ገሸሽ ባደረጉ ሰዎች ላይ ነው። በዛሬው ጊዜ ዓለምን በሙሉ የሚያጥለቀልቀው አጠቃላይ የጥፋት ፍርድ የሚፈጸምበት ጊዜ በደጅ በቀረበበት ወቅት ላይ እንገኛለን።—2 ተሰሎንቄ 1:6–9
“በመጨረሻው ዘመን”
7. (ሀ) በጥንት ዘመን የደረሱት መለኮታዊ ፍርዶች ለምን ነገር ትንቢታዊ ጥላ ነበሩ? (ለ) ከፊታችን ምን ታላቅ ተስፋ ተዘርግቷል?
7 እነዚህ በጥንት ዘመን የደረሱ ጥፋቶች በ2 ጴጥሮስ 3:3–13 ላይ ለተገለጸው እጅግ አስፈሪ የሆነ ታላቅ መከራ ትንቢታዊ ጥላ ነበሩ። ሐዋርያው እንዲህ ብሏል፦ “በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ።” ከዚያም በኖኅ ዘመን ላይ በማተኮር ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤ አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል።” ከዚህ ታይቶ ከማያውቀው ታላቅ መከራ በኋላ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የኖረው የመሲሑ መንግሥት አገዛዝ አዲስ መልክ በመያዝ “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ይዘረጋል። እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ነው!
8. በዓለም ላይ የሚከሰቱት ነገሮች ወደ ፍጻሜ እየገፉ ያሉት እንዴት ነው?
8 በዚህ ባለንበት በ20ኛው መቶ ዘመን በዓለም ላይ የሚከሰቱት ነገሮች ደረጃ በደረጃ ወደ ፍጻሜ እየተጓዙ ነው። ምንም እንኳ በሂሮሽማ ላይ የደረሰው ጥፋት መለኮታዊ ተልዕኮ ያለው ባይሆንም ኢየሱስ በፍጻሜው ዘመን ይሆናሉ ብሎ በተነበያቸው ‘የሚያስፈሩ ነገሮች’ ውስጥ የሚካተት ሊሆን ይችላል። (ሉቃስ 21:11) ይህ ጥፋት እስከ አሁንም ድረስ በሰው ዘር ላይ እንደ ጥቁር ዳመና አጥልቶ የሚገኘውን የኑክሌር ሥጋት ፈጥሯል። በመሆኑም በኅዳር 29, 1993 የወጣው ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በርዕሰ አንቀጹ ላይ “ጠመንጃዎች አርጅተው ሊሆን ይችላል፤ የኑክሌር መሣሪያዎች ግን አሁንም ቢሆን እርምጃ ለመውሰድ በተጠንቀቅ ላይ ናቸው” ብሏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአገሮች መካከል የሚካሄዱ ጦርነቶች እንዲሁም የዘርና የጎሣ ጦርነቶች ዘግናኝ የሆነ መከር ማጨዳቸውን እንደቀጠሉ ነው። ቀደም ባሉት ዘመናት አብዛኛዎቹ የጦርነት ሰለባዎች ወታደሮች ነበሩ። ዛሬ ግን ከጦርነት ሰለባዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ሲቪሎች እንደሆኑ ተዘግቧል፤ ስደተኞች በመሆን አገራቸውን እየለቀቁ የሚሄዱትንማ ቤቱ ይቁ ጠረው።
9. ሃይማኖታዊ መሪዎች ከዓለም ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ያሳዩት እንዴት ነው?
9 ሃይማኖታዊ መሪዎች የጦርነቶችና የብዙ ሰዎች ደም የፈሰሰባቸው አብዮቶች ተዋናይ በመሆን ‘የዓለም ወዳጆች’ መሆናቸውን ብዙውን ጊዜ አሳይተዋል፤ እያሳዩም ነው። (ያዕቆብ 4:4) አንዳንድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን የጦር መሣሪያዎች በማምረትና አደንዛዥ ዕፅን የሚሸቅጡና ሰዎች በአደንዛዥ ዕፅ እንዲጠቀሙ በስፋት የሚቀሰቅሱ ትልልቅ ድርጅቶችን በማቋቋም የንግዱን ዓለም እንደፈለጉ ከሚያሾሩት ራስ ወዳድ ሰዎች ጋር አብረዋል። ለምሳሌ ያህል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የአደንዛዥ ዕፅ ቱጃር የሆነ አንድ የደቡብ አሜሪካ ሰው ስለተገደለበት ሁኔታ ሲዘግብ እንዲህ ብሏል፦ “የሚያካሄደውን የአደንዛዥ ዕፅ ንግድ በሕጋዊ ንግድ ስምና በበጎ እርዳታ ሽፋን በመደበቅ በራሱ ወጪ የሚተላለፍ የራዲዮ ፕሮግራም ነበረው፤ ብዙውን ጊዜ ደግሞ በሮማ ካቶሊክ ቄሶች ይደገፍ ነበር።” የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኞች የሆኑ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ከማበላሸቱም በተጨማሪ ይህ የአደንዛዥ ዕፅ ቱጃር ራሱ ባቀነባበረው ሴራ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በግፍ እንዲገደሉ እንዳደረገ ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ሪፖርት አድርጓል። በለንደን የሚታተመው ዘ ታይምስ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙውን ጊዜ ገዳዮቹ ልዩ የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት እንዲደረግላቸው ገንዘብ ይከፍላሉ . . . በዚያው ጊዜ ደግሞ በሌላ ሥፍራ ለተገደለው ሰው በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ፍታት ይካሄዳል።” እንዴት ያለ ክፋት ነው!
10. በዓለም ላይ ያሉት ሁኔታዎች እየተባባሱ መሄዳቸውን እንዴት ልንመለከተው ይገባል?
10 በአጋንንት መንፈስ የሚመሩ ሰዎች አሁንም ቢሆን በዚህች ምድር ላይ ምን ዓይነት ጥፋት ሊያደርሱ እንደሚችሉ ማን ያውቃል? 1 ዮሐንስ 5:19 እንደሚገልጸው “ዓለምም በሞላው በክፉው” በሰይጣን ዲያብሎስ ተይዟል። ዛሬ “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና” የተባለበት ጊዜ ነው። (ራእይ 12:12) ይሁን እንጂ ሮሜ 10:13 የሚከተለውን ማረጋገጫ መስጠቱ ደስ ያሰኛል፦ “የጌታን [“የይሖዋን” አዓት] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።”
አምላክ በቅርቡ ለፍርድ ይመጣል
11. የሚልክያስ ትንቢት እንዲነገር ያደረጉት በእስራኤል ውስጥ የነበሩት የትኞቹ ሁኔታዎች ናቸው?
11 የሰው ልጅ በቅርቡ የሚጠብቀውን ሁኔታ በተመለከተ የሚልክያስ ትንቢት ምን ነገር እንደሚከሰት ይገልጻል። ሚልክያስ በጥንት ዘመን ከተነሡት በርካታ ዕብራውያን ነቢያት መካከል መጨረሻ ላይ የሚገኝ ነቢይ ነው። እስራኤላውያን በ607 ከዘአበ የኢየሩሳሌምን ጥፋት ተመልክተው ነበር። ይሁን እንጂ ከ70 ዓመታት በኋላ ይሖዋ ይህን ሕዝብ ወደ አገሩ በመመለስ ምሕረት የተሞላበት ፍቅራዊ ደግነት አሳይቷል። ሆኖም እስራኤላውያን በመቶ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደገና ወደ ክህደትና ወደ ክፋት ተመልሰዋል። ሕዝቡ የይሖዋን የጽድቅ ሕግጋት ሆን ብለው ችላ በማለትና ዕውር፣ አንካሳና በሽተኛ እንስሳትን ለመሥዋዕት እያቀረቡ ቤተ መቅደሱን በማርከስ የይሖዋን ስም ያዋርዱ ነበር። የባዕድ አገር ሴቶችን ለማግባት ሲሉ የልጅነት ሚስቶቻቸውን ይፈቱ ነበር።—ሚልክያስ 1:6–8፤ 2:13–16
12, 13. (ሀ) የቅቡዓን ካህናት ክፍል ምን የማንጻት ሥራ አስፈልጎት ነበር? (ለ) እጅግ ብዙ ሰዎችም በማንጻቱ ሥራ የሚጠቀሙት እንዴት ነው?
12 የማንጻት ሥራ አስፈልጎ ነበር። ይህም በሚልክያስ 3:1–4 ላይ ተገልጿል። ልክ እንደ ጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ የይሖዋ ዘመናዊ ምሥክሮች መንጻት አስፈልጓቸዋል። ስለዚህ በሚልክያስ የተገለጸው የማንጻት ሥራ በእነርሱ ላይ ሊሠራ ይችላል። የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወደ ማብቂያው በተቃረበበት ጊዜ በዚያን ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩት አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለማዊ ጉዳዮች ቁርጥ ያለ የገለልተኝነት አቋም አልያዙም ነበር። በ1918 ይሖዋ አነስተኛ ቁጥር የነበራቸውን አምላኪዎቹን ከዓለማዊ ዕድፍ እንዲያነጻቸው “የቃል ኪዳኑን መልእክተኛ” ክርስቶስ ኢየሱስን ወደ መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ልኮታል። ይሖዋ ትንቢታዊ በሆነ መንገድ እንዲህ ሲል ጠይቋል፦ “እርሱ [መልእክተኛው] እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና የሚመጣበትን ቀን መታገሥ የሚችል ማን ነው? እርሱስ በተገለጠ ጊዜ የሚቆም ማን ነው? እርሱም ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፣ የሌዊንም ልጆች [የቅቡዓን ካህናት ቡድን] ያጠራል፣ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቁርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ።” በደንብ የነጹ ሰዎች በመሆን ይህንኑ አድርገዋል!
13 ይህ የቅቡዓን ካህናት ቡድን 144,000 ሰዎችን ብቻ ያቀፈ ነው። (ራእይ 7:4–8፤ 14:1, 3) ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ያሉት ሌሎች ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖችስ? በአሁኑ ጊዜ በሚልዮን ወደሚቆጠር ደረጃ እያደጉ ያሉት እነዚህ ሰዎች “እጅግ ብዙ ሰዎች” ሆነዋል፤ እነዚህም ‘ልብሳቸውን አጥበው በበጉ ደም በማንጻት’ ከዓለማዊ መንገዶች የነጹ መሆን አለባቸው። (ራእይ 7:9, 14) በመሆኑም በበጉ በክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋም ለመጠበቅ ችለዋል። አስፈሪውን የይሖዋ ቀን ማለትም ታላቁን መከራ በሕይወት እንደሚያልፉ ቃል ተገብቶላቸዋል።—ሶፎንያስ 2:2, 3
14. የአምላክ ሕዝቦች በዛሬው ጊዜ አዲሱን ሰውነት ኮትኩተው ማሳደጋቸውን ሲቀጥሉ የትኞቹን ቃላት መታዘዝ አለ ባቸው?
14 እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች የካህናት ክፍል ከሆኑት ቀሪዎች ጋር በመሆን አምላክ ጨምሮ የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት መታዘዝ አለባቸው፦ “ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በመተተኞችና በአመንዝሮች፣ በሐሰትም በሚምሉ፣ የምንደኛውን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቲቱንና ድሀ አደጉን በሚያስጨንቁ፣ የመጻተኛውንም ፍርድ በሚያጣምሙ፣ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ . . . እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም።” (ሚልክያስ 3:5, 6) የይሖዋ የአቋም ደረጃዎች አይለወጡም፤ ስለዚህ በዛሬው ጊዜ ያሉት ሕዝቦቹ ክርስቲያናዊውን ባሕርይ እየኮተኮቱ በሚያሳድጉበት ጊዜ ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ መራቅና ሐቀኞችና ለጋሶች መሆን አለባቸው።—ቆላስይስ 3:9–14
15. (ሀ) ይሖዋ ምን የምሕረት ጥሪ አቅርቧል? (ለ) ይሖዋን ‘ከመስረቅ’ መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?
15 ይሖዋ ከጽድቅ መንገዶቹ ዞር ላሉ ሰዎች “ወደ እኔ ተመለሱ፣ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” በማለት ጥሪ ያቀርባል። እነዚህ ሰዎች “የምንመለሰው በምንድር ነው?” ብለው ከጠየቁ “እኔን ሰርቃችሁኛል” በማለት ይመልስላቸዋል። “የሰረቅንህ በምንድር ነው?” ለሚለው ተጨማሪ ጥያቄ ይሖዋ መልስ ሲሰጥ ካላቸው ነገር ሁሉ ምርጥ የሆነውን ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት ባለማምጣታቸው እንደ ሰረቁት ገልጿል። (ሚልክያስ 3:7, 8) በይሖዋ ሕዝብ መካከል የምንገኝ እንደ መሆናችን መጠን ካለን ኃይል፣ ችሎታና ቁሳዊ ጥሪት ምርጡን ለይሖዋ አገልግሎት ለማቅረብ መፈለግ ይኖርብናል። በዚህ መንገድ አምላክን ከመስረቅ ይልቅ ‘ያለ ማቋረጥ መንግሥቱንና ጽድቁን እንፈልጋለን።’—ማቴዎስ 6:33
16. በሚልክያስ 3:10–12 ላይ ምን ማበረታቻ እናገኛለን?
16 ሚልክያስ 3:10–12 እንደሚያመለክተው ለራስ ጥቅም ብቻ የሚደከምባቸውን የዓለም የፍቅረ ነዋይ መንገዶች ወደ ኋላ ገሸሽ የሚያደርጉ ሁሉ ታላቅ ወሮታ ይጠብቃቸዋል፦ “የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፣ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” ይሖዋ አመስጋኞች ለሆኑ ሁሉ መንፈሳዊ ብልጽግናንና ፍሬያማነትን እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል። “የተድላ ምድር ትሆናላችሁና አሕዛብ ሁሉ ብፁዓን [“ደስተኞች” አዓት] ብለው ይጠሩአችኋል” ሲል አክሎ ተናግሯል። ይህ በዛሬው ጊዜ በመላዋ ምድር ላይ በሚገኙ አመስጋኞች በሆኑ በሚልዮን በሚቆጠሩ የአምላክ ሕዝቦች መካከል አልተፈጸመምን?
በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩ ንጹሕ አቋም የጠበቁ ሰዎች
17–19. (ሀ) በሩዋንዳ የደረሰው ምስቅልቅል በዚያ የሚገኙ ወንድሞቻችንን የነካው እንዴት ነው? (ለ) እነዚህ ታማኝ ወንድሞች በሙሉ የትኛውን ጠንካራ እምነት በመያዝ ወደፊት ገፍተዋል?
17 እዚህ ላይ የሩዋንዳ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስላሳዩት ንጹሕ አቋም ሐሳብ መስጠት እንችላለን። ወደ ይሖዋ መንፈሳዊ የአምልኮ ቤት ሁልጊዜ ከሁሉ የላቀ መንፈሳዊ ስጦታ ያመጡ ነበር። ለምሳሌ ያህል በታኅሣሥ 1993 ባካሄዱት “መለኮታዊ ትምህርት” የአውራጃ ስብሰባ ላይ 2,080 የሚሆኑት የመንግሥቱ አስፋፊዎቻቸው 4,075 የደረሰ አጠቃላይ የተሰብሳቢዎች ቁጥር አግኝተዋል። 230 አዳዲስ ምሥክሮች ተጠምቀዋል፤ ከእነዚህም መካከል ወደ 150 የሚጠጉት በቀጣዩ ወር ረዳት አቅኚ ሆነው ለማገልገል ተመዝግበዋል።
18 ሚያዝያ 1994 ላይ የዘር ጥላቻ ሲገነፍል በዋና ከተማዋ በኪጋሊ የከተማ የበላይ ተመልካች የነበረውን ወንድምና መላ ቤተሰቡን ጨምሮ ቢያንስ ቢያንስ 180 ምሥክሮች ተገድለዋል። በኪጋሊ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቢሮ ከነበሩት ስድስት ተርጓሚዎች አራቱ ሁቱዎች ሲሆኑ ሁለቱ ቱትሲዎች ነበሩ፤ ቱትሲዎቹ መሸሽ እስከ ነበረባቸው ጊዜ ድረስ ከባድ ስጋት በነበረበት ሁኔታ ውስጥ በርከት ላሉ ሳምንታት ሥራቸውን ቀጥለው ነበር፤ እርግጥ ቱትሲዎቹ በአንድ የፍተሻ ጣቢያ ላይ መገደላቸው አልቀረም። በመጨረሻ የቀሩት አራቱ የኮምፒዩተር መሣሪያቸውን ይዘው በዛየር ወደምትገኘው ወደ ጎማ ሸሹ፤ በዚያም በታማኝነት መጠበቂያ ግንብ ወደ ኪንያሩዋንዳ ቋንቋ መተርጎማቸውን ቀጥለዋል።—ኢሳይያስ 54:17
19 እነዚህ ስደተኛ ምሥክሮች ምንም እንኳ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ያሉ ቢሆንም ከቁሳዊ ነገሮች በፊት መንፈሳዊ ምግብ ማግኘት የዘወትር ጥያቄያቸው ነው። በበርካታ አገሮች የሚገኙ አፍቃሪ ወንድሞች ትልቅ መሥዋዕት በመክፈል የእርዳታ ቁሳቁሶችን ሊያደርሱላቸው ችለዋል። እነዚህ ስደተኞች በንግግርም ሆነ በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ እያሉ በሚያሳዩት ሥርዓታማነት ግሩም ምሥክርነት ሰጥተዋል። በእርግጥም ለይሖዋ አምልኮ ካላቸው ነገር ሁሉ ምርጡን ማቅረባቸውን ቀጥለዋል። በሮሜ 14:8 ላይ የተገለጸው የጳውሎስ ዓይነት ጠንካራ እምነት አሳይተዋል፦ “በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፣ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን።”
20, 21. (ሀ) በይሖዋ የመታሰቢያ መጽሐፍ ላይ ያልተጻፉት የእነማን ስሞች ናቸው? (ለ) በመጽሐፉ ላይ የሚጻፉት የእነማን ስሞች ናቸው? ለምንስ?
20 ይሖዋ ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው የሚያገለግሉትን ሁሉ ይመዘግባል። የሚልክያስ ትንቢት እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም አደመጠ፣ ሰማም፣ እግዚአብሔርንም ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ።”—ሚልክያስ 3:16
21 በዚህ ዘመን የይሖዋን ስም በማክበር አምላካዊ ፍርሃት ማሳየት ምንኛ አስፈላጊ ነው! ይህን ብናደርግ የዚህን ዓለም ሥርዓቶች በአድናቆት በሚደግፉ ላይ የሚደርሰው የቅጣት ፍርድ አይደርስብንም። ራእይ 17:8 “ስሞቻቸው . . . በሕይወት መጽሐፍ” አልተጻፈም ይለናል። በይሖዋ የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ከተጻፉት ስሞች ሁሉ ዋነኛው የሕይወት ማስገኛ የሆነው የአምላክ ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ማቴዎስ 12:21 “አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ” ይላል። የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ለሚያምኑበት ሁሉ የዘላለም ሕይወት ዋስትና ይሰጣል። የእያንዳንዳችን ስም በዚያ ጥቅልል ላይ ከኢየሱስ ስም ጎን መጻፉ እንዴት ያለ መብት ነው!
22. ይሖዋ ፍርዱን ሲያስፈጽም ምን ልዩነት ይታያል?
22 የአምላክ አገልጋዮች ፍርዱን የሚወጡት እንዴት ነው? ይሖዋ በሚልክያስ 3:17, 18 ላይ መልሱን ሰጥቷል፦ “ሰውም የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚምር፣ እንዲሁ እምራቸዋለሁ። ተመልሳችሁም በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል፣ ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል ትለያላችሁ።” ልዩነቱ ለሁሉም ግልጽ ይሆናል። ክፉዎቹ ለዘላለማዊ ጥፋት ይለያሉ፤ ጻድቆቹ ደግሞ በመንግሥቲቱ ግዛት ውስጥ ዘላለማዊ ሕይወት ይሰጣቸዋል። (ማቴዎስ 25:31–46) በዚህ መንገድ በግ መሰል የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች ታላቁንና አስፈሪውን የይሖዋ ቀን በሕይወት ያልፋሉ።
ታስታውሳለህን?
◻ ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ምን ፍርዶችን በይኗል?
◻ በዛሬው ጊዜ ያሉት ሁኔታዎች በጥንት ዘመን ከነበሩት ሁኔታዎች ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?
◻ በሚልክያስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ምን የማንጻት ሥራ ተከናወነ?
◻ በአምላክ የመታሰቢያ መጽሐፍ ላይ የሰፈሩት የእነማን ስሞች ናቸው?