የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 39—ሚልክያስ
ጸሐፊው:- ሚልክያስ
የተጻፈበት ቦታ:- ኢየሩሳሌም
ተጽፎ ያለቀው:- ከክ. ል. በፊት ከ443 በኋላ
ሚልክያስ ማን ነበር? ስለ ትውልዱም ሆነ ስለ ግል ታሪኩ የሚገልጽ አንድም ነገር የለም። ይሁን እንጂ ከትንቢቱ ይዘት በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ሚልክያስ ለይሖዋ አምላክ ያደረ፣ የይሖዋን ስምም ሆነ ንጹሕ አምልኮውን የሚያስከብር እንዲሁም አምላክን እናገለግላለን እያሉ ራሳቸውን ብቻ የሚያገለግሉት ሰዎች ሁኔታ በጣም የሚያስቆጣው ሰው ነበር። በበኩረ ጽሑፉ ላይ በአራቱም ምዕራፎች ውስጥ የይሖዋ ስም 48 ጊዜ ተጠቅሷል።
2 ስሙ በዕብራይስጥ ማላክሃይ ሲሆን ትርጉሙም “መልእክተኛዬ” ማለት ሳይሆን አይቀርም። የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ የሰብዐ ሊቃናት ትርጉምም ሆነ መጻሕፍቱን በተጻፉበት ዘመን ቅደም ተከተል የሚዘረዝሩ ሌሎች መጻሕፍት፣ ሚልክያስን ንዑሳን ነቢያት በመባል ከሚጠሩት 12 መጻሕፍት መጨረሻ ላይ ያስቀምጡታል። በታላቁ ምኩራብ ውስጥ በሚገኘው መረጃ መሠረት ሚልክያስ የኖረው ሐጌና ዘካርያስ ከሚባሉት ነቢያት በኋላ፣ በነህምያ ዘመን ነው።
3 ትንቢቱ የተጻፈው መቼ ነበር? በአንድ አገረ ገዥ የአስተዳደር ዘመን ሲሆን ይህም ይሁዳ ባድማ ሆና ከቆየችበት 70 ዓመት በኋላ ኢየሩሳሌም እንደገና ትገነባ ወደነበረበት ዘመን ይወስደናል። (ሚል. 1:8) ያም ሆኖ ግን መጽሐፉ የተጻፈው በየትኛው ገዥ ዘመን ነው? በቤተ መቅደሱ ስለሚካሄደው አገልግሎት ቢጠቀስም ከቤተ መቅደሱ ግንባታ ጋር ተያይዞ የተገለጸ ነገር ባለመኖሩ፣ የሚልክያስ መጽሐፍ የተጻፈው ከገዥው ከዘሩባቤል ዘመን በኋላ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም የቤተ መቅደሱ ግንባታ የተጠናቀቀው በዘሩባቤል የሥልጣን ዘመን ነው። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በዚያ ዘመን እንደነበረ የተጠቀሰው ሌላ ገዥ ደግሞ ነህምያ ብቻ ነው። ትንቢቱ ከነህምያ ዘመን ጋር ይስማማልን? በሚልክያስ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ኢየሩሳሌምም ሆነ ስለ ቅጥሯ እንደገና መገንባት የተጠቀሰ ነገር አለመኖሩ ትንቢቱ የተጻፈው በነህምያ የግዛት ዘመን መጀመሪያ አካባቢ እንዳልሆነ ያሳያል። ይሁን እንጂ ስለ ካህናቱ ብልሹ ምግባር የሚገልጽ ሰፊ ሐሳብ ጽፏል፤ ይህም የሚልክያስ መጽሐፍ፣ ነህምያ በ443 ከክርስቶስ ልደት በፊት በንጉሡ በአርጤክስስ 32ኛ ዓመት የግዛት ዘመን ወደ ባቢሎን ከሄደ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ከነበረው ሁኔታ ጋር እንደሚመሳሰል ያሳየናል። (ሚል. 2:1፤ ነህ. 13:6) በሚልክያስና በነህምያ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት ተመሳሳይ ሐሳቦች ትንቢቱ በዚህ ወቅት እንደተጻፈ ይጠቁማሉ።—ሚል. 2:4-8, 11, 12—ነህ. 13:11, 15, 23-26፤ ሚል. 3:8-10—ነህ. 13:10-12
4 የሚልክያስን መጽሐፍ ትክክለኛነት በተመለከተ በአይሁዳውያን ዘንድ ጥያቄ ተነስቶ አያውቅም። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚልክያስ መጽሐፍ ላይ የተወሰዱ ጥቅሶች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የትንቢቱን ፍጻሜ የሚያሳዩ በርካታ ሐሳቦች እናገኛለን። ይህም የሚልክያስ መጽሐፍ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈና በክርስቲያን ጉባኤ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል እንደሆነ ያረጋግጣል።—ሚል. 1:2, 3—ሮሜ 9:13፤ ሚል. 3:1—ማቴ. 11:10 እንዲሁም ሉቃስ 1:76 እና 7:27፤ ሚል. 4:5, 6—ማቴ. 11:14 እና 17:10-13 እንዲሁም ማር. 9:11-13 እና ሉቃስ 1:17
5 የሚልክያስ መጽሐፍ፣ ቤተ መቅደሱ እንደገና በተገነባበት ወቅት ሕዝቡ በነቢያቱ በሐጌና በዘካርያስ አነሳሽነት አሳይተውት የነበረው ሃይማኖታዊ ቅንዓትና ግለት እንደቀዘቀዘ ይጠቁማል። ካህናቱ ግዴለሾች፣ ኩሩዎችና ራሳቸውን የሚያመጻድቁ ሆነው ነበር። የቤተ መቅደሱ አገልግሎት መቀለጃ ሆኖ ነበር። አምላክ ስለ እስራኤል ደንታ የለውም በሚል ስሜት አሥራት ማውጣትና መሥዋዕት ማቅረብ ቀርቶ ነበር። ሕዝቡ በዘሩባቤል ላይ አሳድረዋቸው የነበሩት ተስፋዎች እውን ሳይሆኑ ቀርተዋል፤ እንዲሁም አንዳንዶች እንደጠበቁት መሲሑ አልመጣም። አይሁዳውያኑ በመንፈሳዊ ሁኔታ በጣም ተዳክመው ነበር። የመጽናናትና የተስፋ ምንጭ የሚሆን ምን ነገር ይገኝ ይሆን? ሕዝቡ ያለበትን መንፈሳዊ ሁኔታ እንዲገነዘብና ወደ ጽድቅ ጎዳና እንዲመለስ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ይሆን? የሚልክያስ ትንቢት መልሱን ይሰጠናል።
6 የሚልክያስ የአጻጻፍ ዘይቤ ቀጥተኛና ኃይለኛ ነው። በመጀመሪያ ጉዳዩን ካነሳ በኋላ መልእክቱ የተጻፈላቸው ሰዎች ለሚያነሱት ተቃውሞ መልስ ይሰጣል። በመጨረሻም በመጀመሪያ ያቀረበውን ሐሳብ በድጋሚ ጠበቅ አድርጎ ይገልጸዋል። ይህም ያነሳውን ነጥብ ለማጠናከርና ግልጽ ለማድረግ አስተዋጽኦ አድርጓል። የተራቀቀ የአጻጻፍ ስልት ለመጠቀም ከመጣር ይልቅ ጠንከር ባለና አሳማኝ በሆነ መንገድ ሐሳቡን አቅርቧል።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
13 የሚልክያስ መጽሐፍ የይሖዋ አምላክን የማይለወጡ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ምሕረት የተላበሰ ፍቅር እንድናስተውል ይረዳናል። ከመጀመሪያ አንስቶ ይሖዋ ለሕዝቡ ‘ለያዕቆብ’ ያለውን ታላቅ ፍቅር ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ለያዕቆብ ልጆች “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] አልለወጥም” ሲል ተናግሯል። ክፋታቸው ያለ ልክ በዝቶ የነበረ ቢሆንም እነርሱ ወደ እርሱ ከተመለሱ ይሖዋም ወደ እነርሱ ለመመለስ ፈቃደኛ ነበር። በእርግጥም መሐሪ አምላክ ነው! (ሚል. 1:2፤ 3:6, 7፤ ሮሜ 11:28፤ ዘፀ. 34:6, 7 የ1954 ትርጉም) አንድ ካህን “ከንፈሮቹ ዕውቀትን ሊጠብቁ” እንደሚገባ ይሖዋ በሚልክያስ አማካኝነት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። የአምላክን ቃል የማስተማር ኃላፊነት የተሰጣቸው ሁሉ ይህን ነጥብ ልብ ሊሉት ይገባል፤ ትክክለኛ እውቀት ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል። (ሚል. 2:7፤ ፊልጵ. 1:9-11፤ ከያዕቆብ 3:1 ጋር አወዳድር።) “ክፉ የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነው” የሚሉትን ግብዞች ይሖዋ በቸልታ አይመለከትም። ማንም ቢሆን ለዚህ ታላቅ ንጉሥ የይስሙላ መሥዋዕት በማቅረብ ይሖዋን አታልላለሁ ብሎ ሊያስብ አይገባም። (ሚል. 2:17፤ 1:14፤ ቆላ. 3:23, 24) ይሖዋ የጽድቅ ሕግጋቱንና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በሚጥሱ ሁሉ ላይ ፈጣን ምሥክር ይሆንባቸዋል፤ ማንም ሰው ኃጢአት ሠርቼ ሳልቀጣ አመልጣለሁ ብሎ ሊያስብ አይችልም። ይሖዋ ይፈርድባቸዋል። (ሚል. 3:5፤ ዕብ. 10:30, 31) ጻድቃን፣ ይሖዋ የሠሩትን እንደማይረሳና መልሶ እንደሚክሳቸው ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ኢየሱስ ራሱ እንዳደረገው ለሙሴ ሕግ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፤ ምክንያቱም ሕጉ በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙ ብዙ ነገሮችን ይዟል።—ሚል. 3:16፤ 4:4፤ ሉቃስ 24:44, 45
14 ሚልክያስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የመጨረሻ ክፍል እንደመሆኑ መጠን በመሲሑ መምጣት ዙሪያ ያሉትን ሁኔታዎች አስቀድሞ ጠቁሟል፤ ከአራት መቶ ዘመናት በኋላ መሲሑ መምጣቱ ደግሞ ለክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት መጻፍ ምክንያት ሆኗል። በሚልክያስ 3:1 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው የሠራዊት ጌታ ይሖዋ “እነሆ፤ በፊቴ መንገድ እንዲያዘጋጅ መልእክተኛዬን እልካለሁ” ሲል ተናግሯል። በዕድሜ የገፋው ዘካርያስ እነዚህ ቃላት በልጁ በመጥምቁ ዮሐንስ ላይ ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ በአምላክ መንፈስ ተነሳስቶ ተናግሯል። (ሉቃስ 1:76) ኢየሱስም እንደሚከተለው ብሎ በተናገረ ጊዜ የዚህን ሐሳብ ትክክለኛነት አረጋግጧል:- “እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ያለ አልተነሣም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።” ሚልክያስ አስቀድሞ እንደተናገረው ዮሐንስ የተላከው ‘መንገድ ለማዘጋጀት’ በመሆኑ ከጊዜ በኋላ ከኢየሱስ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን ከገቡት ሰዎች መካከል አልነበረም።—ማቴ. 11:7-12፤ ሉቃስ 7:27, 28፤ 22:28-30
15 ከዚህም በላይ በሚልክያስ 4:5, 6 ላይ ይሖዋ “እነሆ፤ . . . ነቢዩ ኤልያስን እልክላችኋለሁ” ሲል ቃል ገብቶ ነበር። ይህ “ኤልያስ” ማን ነው? ኢየሱስም ሆነ ለዘካርያስ የተገለጠለት መልአክ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ሲናገሩ በዚህ ስም የተጠቀሙ ሲሆን ‘ሁሉንም ነገር የሚያስተካክለው’ እንዲሁም ‘ለጌታ የተገባ ሕዝብ የሚያዘጋጀው’ እርሱ መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ሚልክያስ “ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ከመምጣቱ በፊት ነቢዩ ኤልያስ” እንደሚመጣ ስለገለጸ ስለ ኤልያስ የተነገረው ትንቢት በታላቁ መከራ ወቅትም ተጨማሪ ፍጻሜ ይኖረዋል።—ማቴ. 17:11፤ ሉቃስ 1:17፤ ማቴ. 11:14፤ ማር. 9:12
16 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ያንን ቀን አሻግሮ በመመልከት እንዲህ ብሏል:- “ከፀሓይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ፣ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናል፤ . . . እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝ፤ ስሜም በሕዝቦች ዘንድ ሊፈራ የሚገባ ነውና።” በእርግጥም የሚያስፈራ ነው! ምክንያቱም ቀኑ ‘እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ይሆናል፤ ትዕቢተኞች ሁሉና ክፉ አድራጊዎች በሙሉ ገለባ ይሆናሉ።’ ይሁን እንጂ የይሖዋን ስም ለሚፈሩ “የጽድቅ ፀሐይ በክንፎቿ ፈውስ ይዛ ትወጣለች” ስለተባለላቸው ደስተኞች ናቸው። ይህ ከሰው ልጆች ቤተሰብ መካከል ታዛዥ የሆኑት ሁሉ በመንፈሳዊ፣ በስሜታዊ፣ በአእምሯዊና በአካላዊ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የሚፈወሱበትን አስደሳች ጊዜ የሚያመለክት ነው። (ራእይ 21:3, 4) ሚልክያስ ስለዚያ ክብራማና የተባረከ ጊዜ ሲናገር ወደ ይሖዋ ቤት የምናመጣውን መሥዋዕት በሙሉ ልባችን እንድናቀርብ አበረታቶናል:- “‘እኔንም በዚህ እንድትፈትኑኝ ዐሥራቱን ሁሉ ወደ ጐተራ አስገቡ፤’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት፤ ‘የሰማይን መስኮት የማልከፍትላችሁ፣ የተትረፈረፈ በረከትንም ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የማላፈስላችሁ ከሆነ ተመልከቱ።’”—ሚል. 1:11, 14፤ 4:1, 2፤ 3:10
17 ይህ የነቢያት የመጨረሻው መጽሐፍ ‘በምድር ላይ ስለሚመጣው ጥፋት’ ከማስጠንቀቅ ወደኋላ ባይልም “የተድላ ምድር ስለምትሆኑ ሕዝቦች ሁሉ የተባረከ [“ደስተኛ፣” NW] ሕዝብ ብለው ይጠሯችኋል” በማለት ብሩህ አመለካከት እንድንይዝና ይሖዋ ለሕዝቦቹ በገባው ቃል ደስ እንዲለን ያበረታታል።—4:6፤ 3:12