የይሖዋ ንብረት ነን
“ይሖዋ አምላኩ የሆነ ብሔር፣ የራሱ ንብረት አድርጎ የመረጠው ሕዝብ ደስተኛ ነው።”—መዝ. 33:12
1. ሁሉም ነገር የይሖዋ ንብረት ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
ሁሉም ነገር የይሖዋ ነው! “ሰማያት፣ ሌላው ቀርቶ ሰማየ ሰማያት እንዲሁም ምድርና በውስጧ ያለው ነገር ሁሉ” የይሖዋ ነው። (ዘዳ. 10:14፤ ራእይ 4:11) ሁሉም ሰዎች ወደ ሕልውና የመጡት በይሖዋ ስለሆነ የእሱ ንብረት ናቸው። (መዝ. 100:3) ሆኖም በታሪክ ዘመናት ሁሉ እንደታየው አምላክ ከሰው ልጆች መካከል ለየት ባለ መንገድ የእሱ ንብረት የሚሆኑ የተወሰኑ ሰዎችን መርጧል።
2. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የይሖዋ “ልዩ ንብረት” እንደሆኑ የተገለጹት እነማን ናቸው?
2 ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙር 135 በጥንቷ እስራኤል የነበሩትን ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች “ልዩ ንብረቱ” በማለት ይጠራቸዋል። (መዝ. 135:4) በተጨማሪም የሆሴዕ መጽሐፍ እስራኤላዊ ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ሕዝብ እንደሚሆኑ የሚገልጽ ትንቢት ይዟል። (ሆሴዕ 2:23) ይሖዋ አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች ወደፊት ከክርስቶስ ጋር አብረው ከሚገዙት ሰዎች መካከል እንዲካተቱ ሲያደርግ የሆሴዕ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። (ሥራ 10:45፤ ሮም 9:23-26) ይህ “ቅዱስ ብሔር” የይሖዋ “ልዩ ንብረት” ነው ሊባል ይችላል፤ ምክንያቱም አባላቱ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ከመሆናቸውም ሌላ ሰማይ ላይ እንዲኖሩ የተመረጡ ናቸው። (1 ጴጥ. 2:9, 10) በዛሬው ጊዜ ካሉት ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች መካከል አብላጫውን ቁጥር ስለሚይዙት ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችስ ምን ማለት ይችላል? እነሱንም ቢሆን ይሖዋ “ሕዝቤ” እንዲሁም “የመረጥኳቸው” በማለት ጠርቷቸዋል።—ኢሳ. 65:22
3. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ከይሖዋ ጋር ልዩ ዝምድና የመመሥረት መብት ያገኙት እነማን ናቸው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
3 በዛሬው ጊዜ የሚገኙት ‘የትንሹ መንጋ’ አባላት የሆኑ በሰማይ የመኖር ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችና ‘የሌሎች በጎች’ አባላት የሆኑ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች በአንድነት ይሖዋ እንደ ሕዝቡ በመቁጠር ከፍ አድርጎ የሚመለከተውን “አንድ መንጋ” ያስገኛሉ። (ሉቃስ 12:32፤ ዮሐ. 10:16) ይሖዋ ከእሱ ጋር እንዲህ ያለ ውድ ዝምድና እንድንመሠርት ስላስቻለን አመስጋኝነታችንን መግለጽ እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። ይህ ርዕስ ይሖዋ ለሰጠን ለዚህ ውድ መብት አመስጋኞች መሆናችንን ማሳየት የምንችልባቸውን የተለያዩ መንገዶች ያብራራል።
ራሳችንን ለይሖዋ እንወስናለን
4. ይሖዋ ከእሱ ጋር ዝምድና እንድንመሠርት ስላስቻለን አመስጋኝነታችንን መግለጽ የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? ኢየሱስስ ምን ተመሳሳይ ነገር አድርጓል?
4 ለይሖዋ ያለንን አመስጋኝነት ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ በሙሉ ልባችን ራሳችንን ለእሱ መወሰን ነው። በውኃ ስንጠመቅ የይሖዋ ንብረት መሆናችንን አምነን እንደተቀበልንና ራሳችንን ለእሱ ለማስገዛት ፈቃደኞች እንደሆንን በሕዝብ ፊት እናሳያለን። (ዕብ. 12:9) ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜም ተመሳሳይ ነገር አድርጓል፤ “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል” ብሎ ለይሖዋ የተናገረ ያህል ነበር። (መዝ. 40:7, 8 ግርጌ) ኢየሱስ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ፣ ራሱን ለአምላክ የወሰነ ብሔር አባል የነበረ ቢሆንም የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን አቅርቧል።
5, 6. (ሀ) ኢየሱስ ሲጠመቅ ይሖዋ ምን ተሰማው? (ለ) ይሖዋ ሁሉም ነገር ንብረቱ ቢሆንም ራሳችንን ለእሱ ስንወስን የሚደሰተው ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
5 ኢየሱስ በመጠመቁ ይሖዋ ምን ተሰማው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃው ወጣ፤ እነሆ፣ ሰማያት ተከፈቱ፤ የአምላክም መንፈስ በእሱ ላይ እንደ ርግብ ሲወርድ አየ። ደግሞም ‘በጣም የምደሰትበት የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ድምፅ ከሰማያት ተሰማ።” (ማቴ. 3:16, 17) ምንም እንኳ ኢየሱስ ቀድሞውንም ቢሆን በሰማይ ያለው አባቱ ንብረት የነበረ ቢሆንም ይሖዋ፣ ልጁ የእሱን ፈቃድ ብቻ ለማድረግ ራሱን በፈቃደኝነት በማቅረቡ ተደስቷል። ይሖዋ እኛም ራሳችንን ስንወስን የሚደሰት ከመሆኑም ሌላ በረከቱን ያፈስልናል።—መዝ. 149:4
6 ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በአትክልት ቦታው ብዙ የሚያማምሩ አበቦች ስለተከለ ሰው ለማሰብ እንሞክር። አንድ ቀን ትንሿ ልጁ ከእነዚህ አበቦች መካከል አንዱን ቀጥፋ ስጦታ ሰጠችው። አበባው ቀድሞውንም ቢሆን የእሱ ንብረት አይደል? ታዲያ የእሱ ንብረት የሆነን ነገር ልትሰጠው የምትችለው እንዴት ነው? አፍቃሪ የሆነ አባት እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን ጨርሶ እንደማያነሳ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ ስጦታውን የልጁ ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርጎ በመቁጠር በደስታ ይቀበለዋል። ልጁ የሰጠችውን አበባ በአትክልት ቦታው ውስጥ ካሉት ሌሎች አበቦች ሁሉ አብልጦ እንደሚመለከተው ምንም ጥርጥር የለውም። ይሖዋም እሱን ብቻ ለማምለክ ራሳችንን በፈቃደኝነት ስናቀርብ እንዲህ እንደሚሰማው የታወቀ ነው።—ዘፀ. 34:14
7. ሚልክያስ፣ ይሖዋ በፈቃደኝነት ለሚያገለግሉት ሰዎች ምን አመለካከት እንዳለው ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?
7 ሚልክያስ 3:16ን አንብብ። እስካሁን ድረስ ራስህን ለአምላክ ወስነህ ካልተጠመቅክ ይህን እርምጃ መውሰድህ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። እርግጥ ነው፣ ወደ ሕልውና ከመጣህበት ጊዜ አንስቶ እንደ ሌላው የሰው ዘር ሁሉ አንተም የይሖዋ ንብረት እንደሆንክ የታወቀ ነው። ያም ሆኖ የይሖዋን ሉዓላዊ ገዢነት ተገንዝበህ ራስህን ለእሱ መወሰንህና ፈቃዱን ማድረግህ ይሖዋን ምን ያህል ሊያስደስተው እንደሚችል አስብ። (ምሳሌ 23:15) በምላሹም ይሖዋ፣ በፈቃደኝነት ለሚያገለግሉት ሰዎች እውቅና የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ ስማቸው ‘በመታሰቢያ መጽሐፍ’ ላይ እንዲጻፍ ያደርጋል።
8, 9. ይሖዋ እሱ ባዘጋጀው “የመታሰቢያ መጽሐፍ” ላይ ስማቸው የተጻፈ ሰዎች ምን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል?
8 ይሖዋ ባዘጋጀው “የመታሰቢያ መጽሐፍ” ላይ ስማችን መጻፉ የሚያስከትለው ኃላፊነት አለ። ሚልክያስ ‘ይሖዋን መፍራትና በስሙ ላይ ማሰላሰል’ እንዳለብን ገልጿል። ከይሖዋ ውጭ ለማንኛውም አካል ወይም ለማንኛውም ነገር አምልኮታዊ ክብር ማሳየታችን ስማችን ይሖዋ ካዘጋጀው የሕይወት መጽሐፍ ላይ እንዲደመሰስ ያደርጋል።—ዘፀ. 32:33፤ መዝ. 69:28
9 በመሆኑም ራስን ለይሖዋ መወሰን፣ የእሱን ፈቃድ ለማድረግ ቃል ከመግባትና በውኃ ከመጠመቅ ያለፈ ነገርን ይጨምራል። እነዚህ አንድ ጊዜ ተደርገው የሚያልፉ ነገሮች ናቸው። የይሖዋ ሕዝቦች በመሆን ከእሱ ጎን ለመቆም ያደረግነው ውሳኔ ግን አሁንም ሆነ ወደፊት በሕይወት እስካለን ድረስ ለእሱ ታዛዥ መሆናችንን ምንጊዜም ማሳየትን ይጠይቃል።—1 ጴጥ. 4:1, 2
ዓለማዊ ምኞቶችን አጥብቀን እንቃወማለን
10. ይሖዋን በሚያገለግሉና በማያገለግሉ ሰዎች መካከል ምን ግልጽ ልዩነት ሊኖር ይገባል?
10 ከዚህ በፊት ያለው ርዕስ ስለ ቃየን፣ ስለ ሰለሞንና ስለ እስራኤላውያን የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች አብራርቷል። ሁሉም ይሖዋን እንደሚያመልኩ ቢናገሩም አምልኳቸው ከሙሉ ልብ የመነጨ አልነበረም። የእነዚህ ሰዎች ታሪክ የይሖዋ ንብረት የሆኑ ሰዎች ከጽድቅ ጎን ጸንተው መቆምና ክፋትን አጥብቀው መቃወም እንዳለባቸው በግልጽ ያሳያል። (ሮም 12:9) በእርግጥም ሚልክያስ ስለ ‘መታሰቢያው መጽሐፍ’ ከገለጸ በኋላ ይሖዋ “በጻድቁና በክፉው እንዲሁም አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው ሰው መካከል [ስላለው] ልዩነት” መናገሩ ተገቢ ነው።—ሚል. 3:18
11. ይሖዋን ብቻ እንደምናመልክ ለሌሎች በግልጽ መታየት ያለበት ለምንድን ነው?
11 በመሆኑም ይሖዋ ሕዝቡ አድርጎ ስለመረጠን አመስጋኞች እንደሆንን ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ መንፈሳዊ እድገታችን ለሌሎች “በግልጽ እንዲታይ” ማድረግ ነው። (1 ጢሞ. 4:15፤ ማቴ. 5:16) ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘በሙሉ ልቤ ለይሖዋ ታማኝ እንደሆንኩ ለሌሎች በግልጽ ይታያል? የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ለሌሎች ማሳወቅ የምችልባቸውን አጋጣሚዎች እፈልጋለሁ?’ የይሖዋ ንብረት እንደሆንን ለሌሎች መናገር የሚያሳፍረን ከሆነ ሕዝቡ አድርጎ የመረጠን ይሖዋ በዚህ በጣም እንደሚያዝን ምንም ጥርጥር የለውም።—መዝ. 119:46፤ ማርቆስ 8:38ን አንብብ።
12, 13. አንዳንዶች የይሖዋ ምሥክር መሆናቸው በግልጽ እንዳይታይ ያደረጉት እንዴት ነው?
12 የሚያሳዝነው አንዳንድ ክርስቲያኖች “የዓለምን መንፈስ” ስለሚያንጸባርቁ ‘አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለው ልዩነት’ በግልጽ እንዳይታይ አድርገዋል። (1 ቆሮ. 2:12) “የዓለም መንፈስ” ሰዎች ‘በሥጋቸው ፍላጎት’ ላይ እንዲያተኩሩ ያበረታታል። (ኤፌ. 2:3) ለምሳሌ ያህል፣ አለባበስንና አጋጌጥን በተመለከተ በተደጋጋሚ ምክር ቢሰጥም አንዳንዶች አሁንም አለባበሳቸውና አጋጌጣቸው ልከኝነት የጎደለው ነው። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሳይቀር በጣም የተጣበቁና ሰውነትን የሚያጋልጡ ልብሶችን ይለብሳሉ። አሊያም ወጣ ያለ የፀጉር አቆራረጥ ወይም አሠራር ስታይል ይከተላሉ። (1 ጢሞ. 2:9, 10) በዚህም የተነሳ ከሌሎች ሰዎች ጋር አብረው ሲሆኑ ማን የይሖዋ ንብረት፣ ማን ደግሞ “የዓለም ወዳጅ” እንደሆነ መለየት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።—ያዕ. 4:4
13 አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም የሚያንጸባርቀውን ምግባር አጥብቀው እንደማይቃወሙ የሚታይባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች በግብዣዎች ላይ ሲገኙ ከክርስቲያኖች የማይጠበቅ ጭፈራ የሚጨፍሩ ከመሆኑም ሌላ ተገቢ ያልሆነ ምግባር ያሳያሉ። በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚያወጧቸው ፎቶዎችና የሚጽፏቸው አስተያየቶች ከአንድ መንፈሳዊ ሰው የማይጠበቁ ናቸው። እነዚህ ክርስቲያኖች ከባድ ኃጢአት ፈጽመዋል በሚል በጉባኤ ውስጥ ተግሣጽ አልተሰጣቸው ይሆናል፤ ሆኖም በይሖዋ ሕዝቦች መካከል መልካም ምግባር ለማሳየት ጥረት በሚያደርጉ እኩዮቻቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።—1 ጴጥሮስ 2:11, 12ን አንብብ።
14. ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ልዩ ዝምድና ጠብቀን መቀጠል ከፈለግን አኗኗራችን ምን ዓይነት መሆን ይኖርበታል?
14 በዚህ ዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች በሙሉ ‘የሥጋ ምኞትን፣ የዓይን አምሮትንና ኑሮዬ ይታይልኝ ማለትን’ ለማበረታታት ታስበው የተዘጋጁ ናቸው። (1 ዮሐ. 2:16) እኛ ግን የይሖዋ ንብረት ስለሆንን “ፈሪሃ አምላክ በጎደለው መንገድ መኖርና ዓለማዊ ምኞቶችን መከተል ትተን አሁን ባለው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ፣ በጽድቅና ለአምላክ በማደር እንድንኖር” ማበረታቻ ተሰጥቶናል። (ቲቶ 2:12) አነጋገራችን፣ ከምግብና ከመጠጥ ጋር በተያያዘ ያለን ልማድ፣ አለባበሳችንና አጋጌጣችን፣ የሥራ ሥነ ምግባራችን እንዲሁም የምናደርገው ሌላ ማንኛውም ነገር ይሖዋን ብቻ የምናመልክ ሰዎች መሆናችንን በግልጽ የሚያሳይ መሆን አለበት።—1 ቆሮንቶስ 10:31, 32ን አንብብ።
‘አንዳችን ለሌላው የጠለቀ ፍቅር’ እናሳያለን
15. ለእምነት ባልንጀሮቻችን ደግነትና ፍቅር ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?
15 የእምነት ባልንጀሮቻችንን የምንይዝበት መንገድ ከይሖዋ ጋር ለመሠረትነው ልዩ ወዳጅነት አድናቆት እንዳለንና እንደሌለን ያሳያል። እነሱም የይሖዋ ንብረት ናቸው። ሁሌም ይህን ሐቅ የምናስታውስ ከሆነ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ምንጊዜም ደግነትና ፍቅር እናሳያለን። (1 ተሰ. 5:15) ኢየሱስ ተከታዮቹን “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏቸዋል።—ዮሐ. 13:35
16. በሙሴ ሕግ ውስጥ ከሚገኘው ሐሳብ ይሖዋ ለሕዝቡ ስላለው አመለካከት ምን እንማራለን?
16 በጉባኤ ውስጥ አንዳችን ሌላውን መያዝ ያለብን እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበሩት ዕቃዎች ለንጹሕ አምልኮ ብቻ እንዲውሉ የተወሰኑ ወይም የተለዩ ነበሩ። የሙሴ ሕግ እነዚህ ዕቃዎች እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ የሚሰጥ ሲሆን ይህን መመሪያ የጣሰ ሰው በሞት እንዲቀጣ ይደረግ ነበር። (ዘኁ. 1:50, 51) ይሖዋ ለእሱ አምልኮ የሚያገለግሉትን ሕይወት የሌላቸው ዕቃዎች ይህን ያህል የሚጠነቀቅላቸው ከሆነ ሕዝቡ አድርጎ የመረጣቸውንና ራሳቸውን ለእሱ የወሰኑትን ታማኝ አገልጋዮቹን ምን ያህል አብልጦ እንደሚጠነቀቅላቸው መገመት አያዳግትም! በአንድ ወቅት ይሖዋ ስለ ሕዝቡ ሲናገር “እናንተን የሚነካ ሁሉ የዓይኔን ብሌን ይነካል” ብሏል።—ዘካ. 2:8
17. ይሖዋ ምን ነገሮችን ‘በትኩረት ያዳምጣል?’
17 ሚልክያስ፣ አገልጋዮቹ እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ ይሖዋ ‘በትኩረት እንደሚያዳምጥ’ ገልጿል። (ሚል. 3:16) በእርግጥም ይሖዋ “የእሱ የሆኑትን ያውቃል።” (2 ጢሞ. 2:19) የምንናገረውንና የምናደርገውን እያንዳንዱን ነገር ጠንቅቆ ያውቃል። (ዕብ. 4:13) የእምነት ባልንጀሮቻችንን ደግነት በጎደለው መንገድ ስንይዛቸው ወይም ስንናገራቸው ይሖዋ ‘በትኩረት ያዳምጣል።’ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳችን ለሌላው ይቅር ባዮች ስንሆን እንዲሁም የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ፣ ልግስናና ደግነት ስናሳይም እንደሚያስተውል እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዕብ. 13:16፤ 1 ጴጥ. 4:8, 9
“ይሖዋ ሕዝቡን አይጥልም”
18. ይሖዋ ሕዝቡ አድርጎ ስለቆጠረን አመስጋኝነታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
18 ይሖዋ ሕዝቡ አድርጎ በመቁጠር ስላከበረን አመስጋኝነታችንን ማሳየት እንደምንፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። በፈቃደኝነት ራሳችንን በመወሰን የእሱ ንብረት መሆናችንን አምነን መቀበላችን የጥበብ አካሄድ እንደሆነ እንገነዘባለን። የምንኖረው “በጠማማና በወልጋዳ ትውልድ መካከል” ቢሆንም “እንከንና እድፍ [የሌለብን]” እንደሆንን እንዲሁም ‘እንደ ብርሃን አብሪዎች እንደምናበራ’ በግልጽ እንዲታይ እንፈልጋለን። (ፊልጵ. 2:15) ክፋትን አጥብቀን እንቃወማለን። (ያዕ. 4:7) በተጨማሪም የእምነት ባልንጀሮቻችንም የይሖዋ ንብረት እንደሆኑ ስለምንገነዘብ ለእነሱ ፍቅርና አክብሮት እናሳያለን።—ሮም 12:10
19. ይሖዋ የእሱ ንብረት ለሆኑት ሰዎች ወሮታቸውን የሚከፍለው እንዴት ነው?
19 መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ ሕዝቡን አይጥልም” በማለት ቃል ይገባልናል። (መዝ. 94:14) ይህ አስተማማኝ ዋስትና ነው፤ በማንኛውም ዓይነት መከራ ውስጥ ብንሆን ይሖዋ ከጎናችን ይሆናል። ሌላው ቀርቶ ሞትም እንኳ ይሖዋ ለእኛ ካለው ፍቅር ሊነጥለን አይችልም። (ሮም 8:38, 39) “ብንኖር የምንኖረው ለይሖዋ ነውና፤ ብንሞትም የምንሞተው ለይሖዋ ነው። ስለዚህ ብንኖርም ሆነ ብንሞት የይሖዋ ነን።” (ሮም 14:8) በእርግጥም ይሖዋ በሞት ያንቀላፉትን ታማኝ ወዳጆቹን በሙሉ ዳግመኛ ሕያው የሚያደርግበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። (ማቴ. 22:32) በአሁኑ ጊዜም እንኳ የተትረፈረፉ በረከቶችን እያገኘን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ይሖዋ አምላኩ የሆነ ብሔር፣ የራሱ ንብረት አድርጎ የመረጠው ሕዝብ ደስተኛ ነው።”—መዝ. 33:12