‘ጻድቃን እንደ ፀሐይ ደምቀው ያበራሉ’
“በዚያ ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ደምቀው ያበራሉ።”—ማቴ. 13:43
1. ኢየሱስ ምሳሌዎችን የተጠቀመው የትኞቹን የመንግሥቱን ገጽታዎች ለማብራራት ነው?
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አምላክ መንግሥት የተለያዩ ገጽታዎች ለማብራራት በርካታ ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። መጽሐፍ ቅዱስ “ኢየሱስ ለሕዝቡ . . . በምሳሌ ተናገረ። እንዲያውም ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር” ይላል። (ማቴ. 13:34) ኢየሱስ የመንግሥቱን የእውነት ዘር ስለ መዝራት በተናገረው ምሳሌ ላይ አንድ ሰው መልእክቱን ለመቀበል የልቡ ሁኔታ ትልቅ ድርሻ እንዳለው እንዲሁም ግለሰቡ በመንፈሳዊ እንዲያድግ ይሖዋ የሚጫወተውን ሚና ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ማር. 4:3-9, 26-29) በተጨማሪም ኢየሱስ እድገቱ በመጀመሪያ ላይ በግልጽ ባይታይም እንኳ ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር በምሳሌ ተናግሯል። (ማቴ. 13:31-33) ከዚህም ሌላ የመንግሥቱን መልእክት የሚቀበሉ ሰዎች ሁሉ የዚህ መንግሥት ጥሩ ዜጋ ላይሆኑ እንደሚችሉ ጎላ አድርጎ ገልጿል።—ማቴ. 13:47-50a
2. ኢየሱስ በተናገረው የስንዴውና የእንክርዳዱ ምሳሌ ላይ ጥሩው ዘር ምን ያመለክታል?
2 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች መካከል አንደኛው ኢየሱስ በመንግሥቱ ከእሱ ጋር የሚገዙ ሰዎችን በመሰብሰቡ ሥራ ላይ ያተኮረ ነው። ይህ ምሳሌ ብዙውን ጊዜ የስንዴውና የእንክርዳዱ ምሳሌ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በማቴዎስ ምዕራፍ 13 ላይ ይገኛል። ኢየሱስ በአንድ ሌላ ምሳሌ ላይ የተዘራው ዘር ‘የመንግሥቱ ቃል’ እንደሆነ የተናገረ ሲሆን በዚህ ምሳሌ ላይ ግን ጥሩው ዘር አንድን ለየት ያለ ነገር ማለትም ‘የመንግሥቱን ልጆች’ እንደሚያመለክት ገልጿል። (ማቴ. 13:19, 38) እነዚህ ልጆች የመንግሥቱ ተገዢዎች ሳይሆኑ የመንግሥቱ “ልጆች” ወይም ወራሾች ናቸው።—ሮም 8:14-17፤ ገላትያ 4:6, 7ን አንብብ።
የስንዴውና የእንክርዳዱ ምሳሌ
3. በምሳሌው ላይ የተገለጸው ሰው ምን ችግር እንዳጋጠመውና ችግሩን ለመፍታት ያደረገውን ውሳኔ ግለጽ።
3 ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ የሚከተለው ነው፦ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው ላይ ጥሩ ዘር ከዘራ ሰው ጋር ይመሳሰላል። ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው ላይ እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ቡቃያው አድጎ ፍሬ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም አብሮ ታየ። ስለሆነም የባለቤቱ ባሪያዎች ወደ እሱ ቀርበው ‘ጌታ ሆይ፣ በእርሻህ ላይ የዘራኸው ጥሩ ዘር አልነበረም እንዴ? ታዲያ እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት። እሱም ‘ይህን ያደረገው አንድ ጠላት የሆነ ሰው ነው’ አላቸው። እነሱም ‘ታዲያ ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?’ አሉት። እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ‘አይ፣ አይሆንም፤ ምክንያቱም እንክርዳዱን ስትነቅሉ ስንዴውንም አብራችሁ ልትነቅሉ ትችላላችሁ። ተዉት፣ እስከ መከር ጊዜ ድረስ አብሮ ይደግ፤ የመከር ወቅት ሲደርስ አጫጆቹን፣ በመጀመሪያ እንክርዳዱን ሰብስቡና እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩ፤ ከዚያም ስንዴውን ሰብስባችሁ ወደ ጎተራዬ አስገቡ እላቸዋለሁ።’”—ማቴ. 13:24-30
4. (ሀ) በምሳሌው ላይ የተገለጸው ሰው ማነው? (ለ) ኢየሱስ ይህን ዘር በመዝራቱ ሥራ መካፈል የጀመረው መቼና እንዴት ነው?
4 በእርሻው ላይ ጥሩ ዘር የዘራው ሰው ማነው? ኢየሱስ ቆየት ብሎ የምሳሌውን ትርጉም ለደቀ መዛሙርቱ ባብራራላቸው ጊዜ “ጥሩውን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው” በማለት መልሱን ተናግሯል። (ማቴ. 13:37) “የሰው ልጅ” ተብሎ የተጠራው ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እርሻውን አለስልሶ ለዘር አዘጋጅቷል። (ማቴ. 8:20፤ 25:31፤ 26:64) ከዚያም በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የጴንጤቆስጤ ዕለት አንስቶ ጥሩ ዘር የሆኑትን ‘የመንግሥቱን ልጆች’ መዝራት ጀመረ። ይህ የመዝራት ሥራ የተከናወነው ኢየሱስ የይሖዋ ወኪል ሆኖ በደቀ መዛሙርቱ ላይ መንፈስ ቅዱስን ማፍሰስ በጀመረበትና የአምላክ ልጆች አድርጎ በቀባቸው ጊዜ እንደነበረ ግልጽ ነው።b (ሥራ 2:33) ከጊዜ በኋላ ጥሩው ዘር ማለትም ስንዴው አድጎ ጎመራ። ስለዚህ ጥሩ ዘር የሚዘራበት ዓላማ ከኢየሱስ ጋር በመንግሥቱ ተባባሪ ወራሾችና ገዥዎች የሚሆኑት ሰዎች ቁጥር እስኪሟላ ድረስ እነሱን በጊዜ ሂደት ለመሰብሰብ ነው።
5. በምሳሌው ላይ የተገለጸው ጠላት ማን ነው? በእንክርዳዱስ የተመሰሉት እነማን ናቸው?
5 ጠላት የተባለው ማን ነው? እንክርዳድ የተባሉትስ እነማን ናቸው? ኢየሱስ ጠላት የተባለው “ዲያብሎስ ነው” በማለት ተናግሯል። እንክርዳዶቹ ደግሞ “የክፉው ልጆች” እንደሆኑ ተገልጿል። (ማቴ. 13:25, 38, 39) እንክርዳድ መርዛማ እህል ሲሆን በቡቃያነት ደረጃ ከስንዴ ጋር በጣም ይመሳሰላል። የመንግሥቱ ልጆች እንደሆኑ ቢናገሩም እውነተኛ ፍሬ የማያፈሩ አስመሳይ ክርስቲያኖች በእንክርዳድ መመሰላቸው ምንኛ የተገባ ነው! እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የክርስቶስ ተከታይ እንደሆኑ የሚናገሩት እነዚህ ግብዝ ክርስቲያኖች የሰይጣን ዲያብሎስ ‘ዘር’ ክፍል ናቸው።—ዘፍ. 3:15
6. እንክርዳዱ መታየት የጀመረው መቼ ነው? በወቅቱ ሰዎች ‘ተኝተው’ የነበሩት እንዴት ነው?
6 በእንክርዳድ የተመሰሉት እነዚህ ክርስቲያኖች መታየት የጀመሩት መቼ ነው? በእንክርዳድ የተመሰሉት እነዚህ ክርስቲያኖች መታየት የጀመሩት “ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ” እንደሆነ ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴ. 13:25) ይህ የሆነው መቼ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች እንደሚከተለው ብሎ በተናገረው ሐሳብ ላይ መልሱን እናገኛለን፦ “እኔ ከሄድኩ በኋላ ጨካኝ ተኩላዎች በመካከላችሁ እንደሚገቡና መንጋውን በርኅራኄ እንደማይዙ አውቃለሁ፤ ከእናንተ ከራሳችሁ መካከል እንኳ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች ይነሳሉ።” (ሥራ 20:29, 30) ቀጥሎም እነዚህን ሽማግሌዎች ምንጊዜም በመንፈሳዊ ንቁ እንዲሆኑ አሳስቧቸዋል። ክህደት እንዳይገባ ‘አግደው’ የነበሩት ሐዋርያት በሞት ካንቀላፉ በኋላ በርካታ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ አንቀላፍተው ነበር። (2 ተሰሎንቄ 2:3, 6-8ን አንብብ።) ታላቁ ክህደት የተጀመረው በዚህ ጊዜ ነው።
7. አንዳንድ ስንዴዎች ተቀይረው እንክርዳድ ሆነው ነበር? አብራራ።
7 ኢየሱስ እዚህ ምሳሌ ላይ ስንዴው ተቀይሮ እንክርዳድ ይሆናል አላለም፤ ከዚህ ይልቅ እሱ የተናገረው በስንዴው መካከል እንክርዳድ እንደተዘራ ነው። በመሆኑም ይህ ምሳሌ ከእውነት የወጡትን እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሰይጣን ክፉ ሰዎች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሰርገው እንዲገቡ በማድረግ ሆን ብሎ ጉባኤውን ለመበከል የሚያደርገውን ጥረት ያመለክታል። የመጨረሻ ሐዋርያ የነበረው ዮሐንስ ዕድሜው በገፋበት ወቅት ክህደቱ በግልጽ መታየት ጀምሮ ነበር።—2 ጴጥ. 2:1-3፤ 1 ዮሐ. 2:18
“ተዉት፣ እስከ መከር ጊዜ ድረስ አብሮ ይደግ”
8, 9. (ሀ) ጌታው ለባሪያዎቹ የሰጠው ትእዛዝ ለኢየሱስ አድማጮች እንግዳ አልነበረም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) በምሳሌው ፍጻሜ መሠረት ስንዴውና እንክርዳዱ አብረው የሚያድጉት እንዴት ነው?
8 ባሪያዎቹ ምን ችግር እንደተከሰተ ለጌታቸው ከነገሩት በኋላ “ታዲያ ሄደን [እንክርዳዱን] እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?” በማለት ጠየቁት። (ማቴ. 13:27, 28) ጌታው ለባሪያዎቹ የሰጠው መልስ የሚያስገርም ይመስላል። ጌታው እስከ መከር ወቅት ድረስ ስንዴውና እንክርዳዱ አብረው እንዲያድጉ ነገራቸው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስንዴውን ከእንክርዳዱ መለየት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ስለሚያውቁ ይህ ትእዛዝ የተሰጠበት ምክንያት ገብቷቸው ነበር። ስለ ግብርና የተወሰነ እውቀት ያላቸው ሰዎችም የእንክርዳድ ሥር ከስንዴ ሥር ጋር እንደሚጠላለፍ ያውቃሉ።c ጌታው እስከ መከር ወቅት ድረስ እንዲጠብቁ ማዘዙ ምንም አያስገርምም።
9 በተመሳሳይም ክህደቱ ብቅ ካለበት ጊዜ ጀምሮ በነበሩት መቶ ዓመታት የተለያዩ የሕዝበ ክርስትና ቡድኖች ማለትም በመጀመሪያ የሮም ካቶሊክና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከጊዜ በኋላ ደግሞ እንደ አሸን የፈሉት የፕሮቴስታንት ሃይማኖታዊ ቡድኖች እንክርዳድ መሰል ክርስቲያኖችን በብዛት አፍርተዋል። በዚሁ ጊዜ ጥቂት እውነተኛ የስንዴ ዘሮች በእርሻ በተመሰለው ዓለም ላይ ተዘርተዋል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው የእርሻው ባለቤት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አጭር የሆነው የመከር ወቅት እስኪደርስ ድረስ ዘሩ የሚያድግበትን ረጅም ጊዜ በትዕግሥት አሳልፏል።
ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የመከር ወቅት
10, 11. (ሀ) የመከሩ ወቅት መቼ ነው? (ለ) ምሳሌያዊው ስንዴ ወደ ይሖዋ ጎተራ እየገባ ያለው እንዴት ነው?
10 ኢየሱስ “መከሩ የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ሲሆን አጫጆቹ ደግሞ መላእክት ናቸው” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 13:39) በዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች የመለየቱ ሥራ ይካሄዳል፤ ይኸውም የመንግሥቱ ልጆች ተሰብስበው በእንክርዳድ ከተመሰሉት ሰዎች ይለያሉ። ይህን በተመለከተ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ፍርድ ከአምላክ ቤት የሚጀምርበት አስቀድሞ የተወሰነው ጊዜ ይህ ነው። እንግዲህ ፍርድ በቅድሚያ በእኛ የሚጀምር ከሆነ ለአምላክ ምሥራች ታዛዥ ያልሆኑ ሰዎች መጨረሻ ምን ይሆን?”—1 ጴጥ. 4:17
11 የመጨረሻዎቹ ቀኖች ወይም “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደሆኑ በሚናገሩ ሰዎች ላይ ፍርድ ጀምሯል፤ ይህ ፍርድ እነዚህ ሰዎች በእርግጥ “የመንግሥቱ ልጆች” ወይም “የክፉው ልጆች” መሆናቸውን ያረጋግጣል። “በመጀመሪያ” ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፤ “ከዚያም” በመከሩ ወቅት መጀመሪያ ላይ የመንግሥቱ ልጆች በአንድነት ተሰበሰቡ። (ማቴ. 13:30) ታዲያ ምሳሌያዊው ስንዴ ወደ ይሖዋ ጎተራ እየገባ ያለው እንዴት ነው? እነዚህ የተሰበሰቡት ክርስቲያኖች የአምላክን ሞገስና ጥበቃ በሚያገኙበት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ታቅፈዋል ወይም በሰማይ ሽልማታቸውን አግኝተዋል።
12. መከሩ የሚቀጥለው ለምን ያህል ጊዜ ነው?
12 ፍርዱ የሚቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው? ኢየሱስ ስለ መከሩ ሲናገር “ወቅት” የሚለውን ቃል መጠቀሙ ፍርዱ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቀጥል መሆኑን ያሳያል። (ራእይ 14:15, 16) ለእያንዳንዱ ቅቡዕ የሚሰጠው ፍርድ በመጨረሻው ዘመን ሁሉ ይቀጥላል። ይህ ፍርድ የሚጠናቀቀው ቅቡዓኑ ለመጨረሻ ጊዜ ማኅተም ሲደረግባቸው ነው።—ራእይ 7:1-4
13. እንክርዳዶቹ እንቅፋት የሚፈጥሩት በምን መንገድ ነው? ዓመፅ የሚፈጽሙትስ እንዴት ነው?
13 ከመንግሥቱ የሚለቀሙት እነማን ናቸው? እንቅፋት የሚፈጥሩትና ዓመፅ የሚፈጽሙትስ እንዴት ነው? (ማቴ. 13:41) በእንክርዳድ የተመሰሉት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ለብዙ መቶ ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሲያስቱ ቆይተዋል። እነዚህ ሰዎች ይህን ያደረጉት ለአምላክ ክብር የማያመጡና “እንቅፋት የሚፈጥሩ” ትምህርቶችን በማስተማር ነው፤ ከእነዚህ መካከል ገሃነመ እሳት ዘላለማዊ የቅጣት ቦታ ነው የሚለው እንዲሁም ግራ የሚያጋባውና ሚስጥር የሆነው የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ይገኙበታል። በርካታ የሃይማኖት መሪዎች ከዚህ ዓለም ጋር ወዳጅነት መሥርተው ምሳሌያዊ ምንዝር በመፈጸም አንዳንድ ጊዜም ዓይን ያወጣ የሥነ ምግባር ብልግና በመፈጸም ለመንጎቻቸው መጥፎ ምሳሌ ሆነዋል። (ያዕ. 4:4) ከዚህም በላይ ሕዝበ ክርስትና ምእመናኖቿ የሚፈጽሙትን የሥነ ምግባር ብልግና በቸልታ ማለፏ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። (ይሁዳ 4ን አንብብ።) ይህን ሁሉ እያደረጉ ቅዱስና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው መስለው ለመታየት ጥረት ያደርጋሉ። የመንግሥቱ ልጆች እንደ እንክርዳድ መጥፎ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩና እንቅፋት ከሚፈጥሩ በካይ ትምህርቶች መለየት በመቻላቸው በጣም ደስተኞች ናቸው!
14. በእንክርዳድ የተመሰሉት ሰዎች የሚያለቅሱትና ጥርሳቸውን የሚያፋጩት እንዴት ነው?
14 በእንክርዳድ የተመሰሉት ሰዎች የሚያለቅሱትና ጥርሳቸውን የሚያፋጩት እንዴት ነው? (ማቴ. 13:42) በእንክርዳድ የተመሰሉት ሰዎች ያሉበትን በመንፈሳዊ መርዛማ የሆነ ሁኔታ “የመንግሥቱ ልጆች” ስለሚያጋልጡ “የክፉው ልጆች” ይሠቃያሉ። በተጨማሪም ከቤተ ክርስቲያን አባሎቻቸው የሚያገኙት ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመቀነሱ እንዲሁም ምእመኖቻቸውን ለመቆጣጠር የሚያስችላቸው ኃይል በመዳከሙ ይበሳጫሉ።—ኢሳይያስ 65:13, 14ን አንብብ።
15. በእንክርዳድ የተመሰሉት በእሳት ይቃጠላሉ ሲባል ምን ማለት ነው?
15 እንክርዳዱ ተሰብስቦ በእሳት ይቃጠላል ሲባል ምን ማለት ነው? (ማቴ. 13:40) ይህ አነጋገር እንክርዳዶቹ መጨረሻ ላይ የሚያጋጥማቸውን ውጤት የሚያመለክት ነው። ወደ እቶን እሳት በምሳሌያዊ ሁኔታ መጣላቸው ዘላለማዊ ጥፋት እንደሚያጋጥማቸው ይጠቁማል። (ራእይ 20:14፤ 21:8) በእንክርዳድ የተመሰሉት ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ይጠፋሉ።—ማቴ. 24:21
“እንደ ፀሐይ ደምቀው ያበራሉ”
16, 17. ሚልክያስ የአምላክን ቤተ መቅደስ አስመልክቶ ምን ትንቢት ተናግሯል? ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ማግኘት የጀመረው መቼ ነው?
16 በስንዴ የተመሰሉት ክርስቲያኖች ‘እንደ ፀሐይ ደምቀው የሚያበሩት’ መቼ ነው? (ማቴ. 13:43) ሚልክያስ የአምላክ ቤተ መቅደስ ስለ መንጻቱ አስመልክቶ እንዲህ በማለት ትንቢት ተናግሯል፦ “‘የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል፤ ደስ የምትሰኙበትም የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ ይመጣል’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት። እርሱ የሚመጣበትን ቀን ማን ሊቋቋመው ይችላል? በሚገለጥበትስ ጊዜ በፊቱ መቆም የሚችል ማን ነው? እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳት ወይም እንደ ልብስ አጣቢ ሳሙና ነውና። ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያነጻ ሰው ይቀመጣል፤ ሌዋውያንንም አንጽቶ እንደ ወርቅና እንደ ብር ያጠራቸዋል፤ ከዚያም እግዚአብሔር ቍርባንን በጽድቅ የሚያቀርቡ ሰዎች ይኖሩታል።”—ሚል. 3:1-3
17 ይህ ትንቢት በዘመናችን ፍጻሜውን ማግኘት የጀመረው ይሖዋ በ1918 “የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ” ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መንፈሳዊውን ቤተ መቅደስ ለመመርመር በመጣበት ጊዜ እንደሆነ ግልጽ ነው። ሚልክያስ ይህ የማንጻት ሥራ ሲጠናቀቅ የሚሆነውን ነገር አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “በዚያን ጊዜም እንደ ገና በጻድቁና በኀጢአተኛው መካከል፣ እግዚአብሔርን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት ታያላችሁ።” (ሚል. 3:18) እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደገና ተነቃቅተው ሥራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው የመከሩ ሥራ እንደ ጀመረ ይጠቁማል።
18. ዳንኤል በዘመናችን ስለሚሆነው ነገር ምን ትንቢት ተናግሯል?
18 ነቢዩ ዳንኤል ስለ ዘመናችን ሲናገር “ጥበበኞች እንደ ሰማይ ጸዳል፣ ብዙዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ” ብሏል። (ዳን. 12:3) እንዲህ ደምቀው የሚያበሩት እነማን ናቸው? ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ የተናገረው ምሳሌ ላይ ከጠቀሳቸው በእውነተኛ ስንዴ ከተመሰሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም! በበጎች የተመሰሉት የታላቅ መንጋ አባላት ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ በእንክርዳድ የተመሰሉት ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ‘እንደተለቀሙ’ በግልጽ ያሳያል። እነዚህ የወደፊቱ የመንግሥቱ ተገዢዎች ከመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች ጋር ሲተባበሩ እነሱም በዚህ ድቅድቅ ጨለማ ዓለም ውስጥ ብርሃናቸውን ያበራሉ።—ዘካ. 8:23፤ ማቴ. 5:14-16፤ ፊልጵ. 2:15
19, 20. “የመንግሥቱ ልጆች” በጉጉት የሚጠባበቁት ምንድን ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
19 በዘመናችን “የመንግሥቱ ልጆች” በሰማይ ክብራማ የሆነውን ሽልማት የሚያገኙበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። (ሮም 8:18, 19፤ 1 ቆሮ. 15:53፤ ፊልጵ. 1:21-24) እስከዚያው ድረስ ግን ደምቀው ማብራታቸውን በመቀጠልና ‘ከክፉው ልጆች’ ፈጽሞ የተለዩ በመሆን በታማኝነት መጽናት ይኖርባቸዋል። (ማቴ. 13:38፤ ራእይ 2:10) ሁላችንም እንክርዳዶቹ በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደተለቀሙ የሚያሳየውን ውጤት በዘመናችን የማየት አጋጣሚ በማግኘታችን ምንኛ ደስተኞች ነን!
20 ይሁንና በመንግሥቱ ልጆችና የመንግሥቱ ተገዢዎች ሆነው በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ባላቸውና ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በሄደው ታላቅ መንጋ መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? የሚቀጥለው ርዕስ የዚህን ጥያቄ መልስ ይዟል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የእነዚህን ምሳሌዎች ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ሐምሌ 15, 2008 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 12-21 ተመልከት።
b በዚህ ምሳሌ ላይ የመዝራቱ ሥራ፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንዲገኙ ለማድረግ የሚከናወነውን የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ የሚያመለክት አይደለም። ኢየሱስ በእርሻው ላይ የተዘራውን ጥሩ ዘር በተመለከተ ሲናገር “የመንግሥቱ ልጆች ናቸው” እንጂ የመንግሥቱ ልጆች ይሆናሉ አላለም። የመዝራቱ ሥራ እነዚህ የመንግሥቱ ልጆች በዓለም እርሻ ላይ መቀባታቸውን ያመለክታል።
c የእንክርዳድ ሥር ከስንዴ ሥር ጋር በጣም ይጠላለፋል፤ በመሆኑም አንድ ሰው ከመከር በፊት እንክርዳዱን ለመንቀል ከሞከረ ስንዴውም አብሮ ይነቀላል።—ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 1178ን ተመልከት።
ታስታውሳለህ?
ኢየሱስ በተናገረው የስንዴውና የእንክርዳዱ ምሳሌ ላይ የሚከተሉት ነገሮች ምን ያመለክታሉ?
• ጥሩው ዘር
• ዘሩን የዘራው ሰው
• የዘሩ መዘራት
• ጠላቱ
• እንክርዳዱ
• የመከሩ ወቅት
• ጎተራው
• ለቅሶውና ጥርስ ማፋጨቱ
• እቶኑ እሳት
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥሩው ዘር መዘራት የተጀመረው በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት ነው
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሁኑ ጊዜ ምሳሌያዊው ስንዴ ወደ ይሖዋ ጎተራ እየገባ ነው
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.