ለዘላለም ሕይወት ዝንባሌ ያላቸውን መፈለግ
“ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ አመኑ።”—ሥራ 13:48
1. ይሖዋ የሰውን ልብ በሚመለከት ምን ችሎታ አለው?
ይሖዋ አምላክ ልብን ማንበብ ይችላል። ይህም ነቢዩ ሣሙኤል የእሴይን ልጅ በእሥራኤል ላይ ንጉሥ እንዲሆን ሊቀባው በሄደ ጊዜ በግልጽ ታይቶአል። ሣሙኤል ኤልያብን እንዳየ “በእውነት [ይሖዋ (አዓት)] የሚቀባው በፊቱ ነው አለ። [ይሖዋ (አዓት)] ግን ሣሙኤልን ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ [ይሖዋ (አዓት)] አያይምና ናቅሁት። ሰው ፊትን ያያል፣ [ይሖዋ (አዓት)] ግን ልብን ያያል አለው።” በዚህም መሠረት ሣሙኤል ለይሖዋ ልብ የተስማማውን ዳዊትን እንዲቀባ ታዘዘ።—1 ሳሙኤል 13:13, 14፤ 16:4-13
2. በሰው ምሳሌያዊ ልብ ውስጥ ምን ነገር ተተክሎ ይገኛል? ስለዚህስ ጉዳይ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ምን እናነባለን?
2 እያንዳንዱ ሰው አንድ አይነት ዋነኛ ዝንባሌ ይኖረዋል። በምሳሌያዊ ልቡ ውስጥ ሥር የሰደደ ዝንባሌ ይኖረዋል። (ማቴዎስ 12:34, 35፤ 15:18-20) በዚህም ምክንያት “በልቡ ግን ሠልፍ ነበረ” የሚል ቃል እናነባለን። (መዝሙር 55:21) “የግልፍተኝነት ዝንባሌ ያለው ሰው ብዙ በደል ይፈጽማል” (አዓት) ይላል። በተጨማሪም “እርስ በርሳቸው የመለያየት ዝንባሌ ያላቸው ባልንጀራሞች አሉ፣ ይሁን እንጂ ከወንድም የበለጠ የሚጠጋ ወዳጅ አለ” የሚል ቃል እናነባለን። (ምሳሌ 18:24፤ 29:22 አዓት) ብዙ ሰዎች በጥንትዋ የጵስድያ አንጾኪያ ይኖሩ እንደነበሩት አንዳንድ አሕዛብ መሆናቸው ያስደስታል። ስለ ይሖዋ የደኅንነት ዝግጅት ሲሰሙ ደስ አላቸው። [የይሖዋንም (አዓት)] ቃል አከበሩ። ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ አመኑ። [የይሖዋም (አዓት)] ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ።”—ሥራ 13:44-48
አማኞች ልበ ንጹሐን ናቸው
3, 4. (ሀ) ልበ ንጹሐን እነማን ናቸው? (ለ) ልባቸው ንጹሕ የሆኑ አምላክን የሚያዩት እንዴት ነው?
3 እነዚህ የአንጾኪያ አማኞች የተጠመቁ ክርስቲያኖች ሆኑ። በታማኝነት የጸኑትም “ልባቸው ንጹሕ የሆኑ ደስተኞች ናቸው፤ አምላክን ያዩታልና” የሚለውን የኢየሱስ ቃል በራሳቸው ላይ ሊጠቅሱ ይችላሉ። (ማቴዎስ 5:8 አዓት) ይሁን እንጂ “ልባቸው ንጹሕ የሆኑ” እነማን ናቸው? አምላክንስ የሚያዩት እንዴት ነው?
4 ልበ ንጹሐን የተባሉት በውስጣቸው ንጹሕ የሆኑት ናቸው። የአድናቆት፣ የፍቅር፣ የፍላጎትና የዓላማ ንጽሕና አላቸው። (1 ጢሞቴዎስ 1:5) አምላክ ለፍጹም አቋም ጠባቂዎች የሚያደርግላቸውን ሁሉ ለመመልከት ስለሚችሉ አምላክን ያያሉ። (ከዘፀዓት 33:20፤ ኢዮብ 19:26፤ 42:5 ጋር አወዳድር) እዚህ ላይ “ማየት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “በዓይነ ልቡና ማየት፣ ማስተዋል፣ ማወቅ” የሚል ትርጉም አለው። ኢየሱስ የአምላክን ባሕርይ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ስላንፀባረቀ “ልባቸው ንፁሕ” ሆኖ በክርስቶስና ኃጢአት በሚያስተሠርየው መሥዋዕቱ ያመኑ፣ የኃጢአት ሥርየት ያገኙና ተቀባይነት ያለው አምልኮ ለአምላክ ለማቅረብ የቻሉ ሁሉ የአምላክን ባሕርይ ለማየት ችለዋል። (ዮሐንስ 14:7-9፤ ኤፌሶን 1:7) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ትንሣዔ አግኝተው አምላክንና ክርስቶስን ፊት ለፊት ማየት ሲችሉ አምላክን ማየታቸው የመጨረሻውን ከፍተኛ ደረጃ ይይዛል። (2 ቆሮንቶስ 1:21, 22፤ 1 ዮሐንስ 3:2) ይሁን እንጂ ልባቸው ንጹሕ የሆኑ ሁሉ በትክክለኛ ዕውቀትና በእውነተኛ አምልኮ አማካኝነት አምላክን ለማየት ይችላሉ። (መዝሙር 24:3, 4፤ 1 ዮሐንስ 3:6፤ 3 ዮሐንስ 11) በሰማይ ወይም በገነቲቱ ምድር የዘላለም ህይወት ለማግኘት ጥሩ ዝንባሌ አላቸው።—ሉቃስ 23:43፤ 1 ቆሮንቶስ 15:50-57፤ 1 ጴጥሮስ 1:3-5
5. አንድ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታይና አማኝ ሊሆን የሚችለው እንዴት ብቻ ነው?
5 ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ የሌላቸው ሁሉ አማኞች አይሆኑም። ማመን አይቻላቸውም። (2 ተሰሎንቄ 3:2) ለመማር ፈቃደኛ ያልሆነና በልብ ውስጥ ያለውን ለማየት የሚችለው ይሖዋ ያልሳበው ማንኛውም ሰው የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን አይችልም። (ዮሐንስ 6:41-47) እርግጥ ነው የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ በሚሰብኩበት ጊዜ በማንም ሰው ላይ አስቀድመው አይፈርዱም። የሰዎችን ልብ ለማንበብ ስለማይችሉ የስብከታቸውን ውጤት አፍቃሪ ለሆነው አምላክ ይተዋሉ።
6. (ሀ) ከቤት ወደ ቤት ከሰዎች ጋር ግንባር ለግንባር ተገናኝቶ ስለመነጋገር ምን ተብሎአል? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች ለዘላለም ሕይወት በትክክል ያዘነበሉ ሰዎችን ፈልገው እንዲያገኙ የሚረዳቸው ምን ዝግጅት ተደርጎላቸዋል?
6 አንድ ምሑር የሚከተለውን በማለት ጥሩ ሐሣብ ሰጥተዋል፣ “[ጳውሎስ] በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት እየሄደ እውነትን አስተምሮአል። ከመድረክ ብቻ ሳይሆን ከሰዎች ጋር በግል እየተገናኘ ክርስቶስን ሰብኮአል። ሰዎችን ለመንካት ከግለሰቦች ጋር ግንባር ለግንባር ከመገናኘት የበለጠ ዘዴ አይኖርም።” (ኦገስት ቫን ሪን) እንደ ቲኦክራቲክ አገልግሎት ትምህርት ቤት መምሪያ፣ ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክንያቱን ማስረዳት፣ የመንግሥት አገልግሎታችን የመሰሉት ጽሑፎች የይሖዋ ምሥክሮች ንግግር እንዲያደርጉና በመስክ አገልግሎታቸው ከሰዎች ጋር ተገናኝተው በሚነጋገሩበት ጊዜ ጥሩ ውጤት እንዲያገኙ ይረዱአቸዋል። በተጨማሪም በአገልግሎት ስብሰባ የሚታዩት ትዕይንቶችና በቲኦክራቲክ አገልግሎት ትምህርት ቤት የሚሰጠው ምክር በጣም ይጠቅማቸዋል። በዚህ ትምህርት ቤት የሚካፈሉ ሁሉ ስለ ጥሩ መግቢያ፣ ስለ ትክክለኛ የጥቅስ አጠቃቀም፣ ስለ ምክንያታዊ አቀራረብ፣ አሳማኝ የመከራከሪያ ነጥብ ስለማቅረብ፣ ስለ ምሳሌ አጠቃቀም፣ ጥሩ መደምደሚያ ስለማቅረብና ስለመሳሰሉት የጥሩ ንግግር ባሕርያት ጠቃሚ ማሰልጠኛ ይሰጣቸዋል። የአምላክ ሕዝቦች ለዘላለም ሕይወት ጥሩ ዝንባሌ ያላቸውን በሚፈልጉበት ጊዜ የበለጠ ውጤት እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን ይህን ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚያጠናክረው እንመልከት።
ሐሳብ የሚቀሰቅስ መግቢያ
7. ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ስብከቱ የተጠቀመባቸው የመግቢያ ቃላት ስለ ጥሩ መግቢያ ምን ያስተምሩናል?
7 ከቤት ወደ ቤት ለመመስከር የሚዘጋጁ ሁሉ ፍላጎት ስለሚቀሰቅስ መግቢያ ከኢየሱስ ምሳሌ ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ። ኢየሱስ የተራራ ስብከቱን ሲከፍት “ደስተኛ” የሚለውን ቃል ዘጠኝ ጊዜ ተጠቅሞበታል። ለምሳሌ ያህል “ለሚያስፈልጋቸው መንፈሣዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው፤ የሰማያት መንግሥት የእነርሱ ናትና። . . . የዋሆች ደስተኞች ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና” ብሎአል። (ማቴዎስ 5:3-12 አዓት) ዐረፍተ ነገሮቹ ቀጥተኛና ግልጽ ነበሩ። ይህ መግቢያ የአድማጮቹን ፍላጎት ቀስቅሶና አነሳስቶ እንደነበረ አያጠራጥርም። ደስተኛ ለመሆን የማይፈልግ ሰው ሊኖር አይችልምና።
8. ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ለመነጋገሪያ ርዕሳችን እንዴት ያለ መግቢያ መጠቀም ይገባናል?
8 ከቤት ወደ ቤት በምናደርገው አገልግሎት የምንጠቀምበት መነጋገሪያ ርዕስ ሁልጊዜ በሚገነባና በሚጥም መንገድ መቅረብ ይኖርበታል። ነገር ግን ማንኛችንም ብንሆን የሚያስደነግጥ መግቢያ መጠቀም አይገባንም። ለምሳሌ “ከላይኛው ዓለም መልእክት ይዤልዎት መጥቼአለሁ” በሚልና ይህን በመሰለ መግቢያ መጠቀም ተገቢ አይደለም። እርግጥ ምሥራቹ ከላይ ከሰማይ የመጣ ነው። ቢሆንም እንዲህ ያለው መግቢያ የምናነጋግረው ባለቤት ጤነኛ መሆናችንን እንዲጠራጠርና በተቻለ ፍጥነት ከእኛ ለመላቀቅ እንዲፈልግ ሊያደርገው ይችላል።
በአምላክ ቃል እንደሚገባ መጠቀም
9. (ሀ) በምናገለግልበት ጊዜ ጥቅሶችን እንዴት ማስተዋወቅ፣ ማንበብና ማብራራት ይገባናል? (ለ) ኢየሱስ በጥያቄዎች እንዴት እንደተጠቀመ ለማሳየት ምን ምሳሌ ተጠቅሶአል?
9 መድረክ ላይ ሆነን በምንናገርበት ጊዜ ጥቅሶችን በሚገባ ማስተዋወቅ፣ በተገቢ ቦታ ላይ ጠበቅ አድርጎ ማንበብ፣ ትርጉሙን በግልጽና በትክክል ማብራራት እንደሚገባን ሁሉ በመስክ አገልግሎታችንም እንደዚያው ማድረግ አለብን። ባለቤቱ በጥቅሶቹ ስለተገለጹት ነጥቦች እንዲያስብ የሚያደርጉት ጥያቄዎች መጠየቅም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በዚህም ላይ የኢየሱስ ዘዴ ትምህርት ይሰጠናል። አንድ ጊዜ የሙሴን ሕግ በደንብ የሚያውቅ ሰው “መምህር ሆይ፣ የዘላለምን ህይወት እንድወርስ ምን ላድርግ” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም መልሶ “በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ?” አለው። ሰውዬው ሊመልሰው የሚችል ጥያቄ እንደሆነ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። “[ይሖዋ (አዓት)] አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም፣ በፍጹም ኃይልህም፣ በፍጹም አሳብህም ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ” በማለት በትክክል መለሰለት። ይህን በመመለሱም ኢየሱስ አመሰገነው። በዚህም ምክንያት ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ተቻለ።—ሉቃስ 10:25-37
10. በመነጋገሪያ ርዕሳችን ረገድ ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል? ባለቤቶችን ጥያቄ በምንጠይቅበት ጊዜ ከምን መቆጠብ ይኖርብናል?
10 ከቤት ወደ ቤት በመሄድ የሚመሰክሩ ሁሉ አጠቃላይ መልዕክት አድርገው የሚጠቀሙበትን መነጋገሪያ ርዕስ ጎላ አድርገው መግለጽና የሚናገሩትን ለማብራራት የሚጠቅሱአቸውን ጥቅሶች ለምን እንደጠቀሱ ግልጽ ማድረግ ይገባቸዋል። ምሥክሩ የሰዎችን ልብ ለመንካት ስለሚሞክር ሰዎቹን የሚያሳፍር ጥያቄ ከመጠየቅ መቆጠብ ይኖርበታል። በአምላክ ቃል በምንጠቀምበት ጊዜ ሁሉ ’ንግግራችን በጸጋና በጨው የተቀመመ ይሁን።’—ቆላስይስ 4:6
11. የተሳሳተ አስተያየት ለማረም በጥቅሶች በመጠቀም ረገድ ኢየሱስ በሠይጣን በተፈተነ ጊዜ ያደረገው እንዴት ምሳሌ ይሆነናል?
11 በተለይ ተመላልሶ መጠየቅ በምናደርግበት ጊዜ ቅዱሳን ጽሑፎች ምንና ለምን እንደሚሉ በማሳየት የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ማስተካከል ሊያስፈልግ ይችላል። ኢየሱስም ሰይጣንን አሳፍሮ ለመመለስ እንዲሁ ማድረግ አስፈልጎት ነበር። ሠይጣን “መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፣ እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሱሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔርስ ልጅ ከሆንህ ወደ ታች [ራስን የመግደል ያህል ከመቅደሱ ጫፍ] ወርውር” አለው። ሠይጣን የጠቀሰው የመዝሙር 91:11, 12 ጥቅስ የአምላክ ሥጦታ የሆነውን ሕይወት አደጋ ላይ መጣልን አይደግፍም። ኢየሱስም ሕይወቱን ሆን ብሎ አደጋ ላይ በመጣል ይሖዋን መፈታተን ተገቢ አለመሆኑን በመገንዘብ “[ይሖዋ (አዓት)] አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል” ሲል ለሠይጣን መልሶአል። (ማቴዎስ 4:5-7) እርግጥ ሠይጣን እውነት ፈላጊ አይደለም። ምክንያታዊ የሆኑ ሰዎች ግን መንፈሣዊ እድገታቸውን የሚያሰናክልባቸው የተሳሳተ አስተያየት ሲገልጹ የአምላክ ቃል አገልጋይ ቅዱሳን ጽሑፎች ምን እንደሚሉና ምን ማለታቸው እንደሆነ በዘዴ ማሳየት ይኖርበታል። ይህ ሁሉ ’በአምላክ ቃል በሚገባ የመጠቀም’ ክፍል ነው። ይህም በቲኦክራቲክ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጡት በጣም ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶች አንዱ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 2:15
ለማሳመን መጣር ተገቢ ቦታ አለው
12, 13. በአገልግሎታችን በማሳመን ችሎታችን መጠቀም ትክክል የሚሆነው ለምንድን ነው?
12 ለማሳመን መጣር በክርስቲያናዊ አገልግሎት ውስጥ ተገቢ ቦታ አለው። ለምሳሌ ጳውሎስ የሥራ ባልደረባው የነበረውን ጢሞቴዎስን በተማረውና “እንዲያምን በተደረገው” ነገር እንዲጸና መክሮት ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:14 አዓት) በቆሮንቶስም ጳውሎስ “በየሰንበቱ በምኩራብ ውስጥ ንግግር ያደርግና አይሁድንም ሆነ የግሪክ ሰዎችን ለማሳመን ይጥር ነበር።” (ሥራ 18:1-4 አዓት) በኤፌሶንም ‘ንግግር ያደርግና ስለ አምላክ መንግሥት ያሳምን ነበር።’ (ሥራ 19:8) በሮማ በቤት ውስጥ ታስሮ በነበረበት ጊዜ ሐዋርያው ሰዎችን ወደ እርሱ ይጠራና ‘ሊያሳምናቸው እየጣረ’ ምሥክርነት ይሰጣቸው ነበር። አንዳንዶችም አማኞች ሆነዋል።—ሥራ 28:23, 24
13 እርግጥ ነው፣ ምሥክሩ ምንም ያህል ለማሳመን ቢጥር አማኞች የሚሆኑት ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው ብቻ ናቸው። በዘዴ የቀረበ አሳማኝ ምክንያትና ግልጽ ማብራሪያ እንዲያምኑ ሊገፋፋቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ምን ተጨማሪ ነገር እንዲያምኑ ሊረዳቸው ይችላል?
ምክንያታዊና አሳማኝ መሆን
14. (ሀ) ምክንያታዊና የተያያዘ ንግግር ማቅረብ ምን ማድረግን ይጠይቃል? (ለ) አሳማኝ መከራከሪያ ነጥብ ለማቅረብ ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
14 በቲኦክራቲክ አገልግሎት ትምህርት ቤት ትኩረት ከሚሰጥባቸው የጥሩ ንግግር ባሕርያት አንዱ ምክንያታዊና የተያያዘ ሐሣብ ያለው ንግግር ማቅረብ ነው። ይህም ቁልፍ ሐሳቦችንና አግባብነት ያላቸውን ነጥቦች በሙሉ በምክንያታዊ ቅደም ተከተል ማስቀመጥን ይጠይቃል። በተጨማሪም አሳማኝ መከራከሪያ ነጥብ ማቅረብ ያስፈልጋል። ለዚህም በመጀመሪያ ጥሩ መሠረት መጣልና አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል። ከዚህ ተነጥሎ የማይታየው ደግሞ የጋራ መስማሚያ ነጥብ ይዞ መወያየት፣ ፍሬ ሐሳቡን በሚገባ የማብራራትና ለሰውየው ምን ትርጉም እንዳለው የማስረዳት ጉዳይ ነው። በዚህም ረገድ ቅዱሳን ጽሑፎች ጥሩ መምሪያ ይሰጡናል።
15. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ በማርስ ኮረብታ ላይ ንግግር ባደረገ ጊዜ የአድማጮቹን ትኩረት የሳበውና ሁሉም የሚስማሙበት ነጥብ ያስጀመረው እንዴት ነው? (ለ) የጳውሎስ ንግግር ምክንያታዊና የተያያዘ የሆነው እንዴት ነው?
15 እነዚህ የንግግር ባሕርያት ሐዋርያው ጳውሎስ በማርስ ኮረብታ ላይ ባደረገው እውቅ ንግግሩ በግልጽ ታይተዋል። (ሥራ 17:22-31) መግቢያው የአድማጮቹን ትኩረት ከመሳቡም በላይ በጋራ የሚስማሙበት ነጥብ አስጀምሯል። “የአቴና ሰዎች ሆይ፣ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እንደምትፈሩ እመለከታለሁ” አላቸው። በዚህ አባባሉ ያመሰገናቸው መስሎ እንደታያቸው አያጠራጥርም። ጳውሎስ “ለማይታወቅ አምላክ” ስለተሠራ መሠዊያ ከነገራቸው በኋላ ምክንያታዊ፣ አሳማኝና ሐሳቡ ያልተቆራረጠ ንግግሩን አቀረበ። ይህ ያላወቁት አምላክ “ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ” እንደሆነ ገለጸላቸው። እርሱ ግን እንደ አቴናና እንደ ሌሎቹ የግሪክ አማልክት ሰው በሠራው መቅደስ አይኖርም ወይም በሰው እጅ አይገለገልም። ሐዋርያው በመቀጠል አምላክ ሕይወት እንደሰጠንና እርሱን በጭፍን እንድንፈልግ እንዳላደረገ አመለከተ። ከዚያም በጣኦት አምልኮ ድንቁርና ያለፈውን ጊዜ በትዕግሥት ተመልክቶ ያሳለፈው ፈጣሪያችን ’በየቦታው ያሉትን ሰዎች ንሥሐ እንዲገቡ እንደሚጠይቅ’ ገለጸ። ይህም በቅደም ተከተሉ መሠረት ’ከሙታን አስነስቶ ባዘጋጀው ሰው እጅ አምላክ የምድርን ነዋሪዎች በሙሉ እንደሚፈርድ’ወደሚገልጸው ነጥብ አደረሰው። ጳውሎስ “የኢየሱስንና የትንሣዔውን ወንጌል” ይሰብክ ስለነበረ እነዚህ የአቴና ሰዎች ይህ ፈራጅ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚሆን ያውቁ ነበር።—ሥራ 17:18
16. የአንድ ክርስቲያን አገልግሎት ጳውሎስ በማርስ ኮረብታ ባደረገው ንግግርና በቲኦክራቲክ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በሚያገኘው ሥልጠና እንዴት ይነካል?
16 እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ በማርስ ኮረብታ ላይ ከቤት ወደ ቤት እየሄደ እየመሰከረ አልነበረም። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ ንግግሩና በቲኦክራቲክ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ማሠልጠኛ የመስክ አገልግሎታቸውን የሚያጠናክርላቸው ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ። የጳውሎስ ምክንያታዊ አቀራረብና አሳማኝ ክርክር አንዳንድ አቴናውያን አማኞች እንዲሆኑ እንደገፋፋቸው ሁሉ ይህ ሁሉ እርዳታ ውጤታማ አገልጋዮች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።—ሥራ 17:32-34
ትምህርት ሰጪ በሆኑ ምሳሌዎች መጠቀም
17. በአገልግሎት እንዴት ባሉ ምሳሌዎች መጠቀም ይገባል?
17 በተጨማሪም ቲኦክራቲክ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የአምላክ አገልጋዮች በቤት ወደ ቤት የምሥክርነት ሥራቸውና በሌሎቹ የአገልግሎት መስኮች በጥሩ ምሳሌዎች እንዲጠቀሙ ይረዳቸዋል። ዋና ዋና ነጥቦችን አጠንክሮ ለመግለጽ ቀላልና የሚጥም ምሳሌ መጠቀም ይገባል። ምሳሌዎቹ ከተለመዱ ሁኔታዎች የተወሰዱ መሆን አለባቸው። ለምን እንደጠቀሳቸውም ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል። የኢየሱስ ምሳሌዎች እነዚህን ብቃቶች በሙሉ የሚያሟሉ ነበሩ።
18. ማቴዎስ 13:45, 46 በአገልግሎት ሊጠቅም የሚችለው እንዴት ነው?
18 ለምሳሌ የሚከተለውን የኢየሱስ ቃል እንመልከት። “መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች። ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት እንቁ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት።” (ማቴዎስ 13:45, 46) እዚህ ላይ እንቁ የተባለው ኦይስተር በሚባለውና በሌሎች መሰል የባሕር ፍጥረታት ሽፋን ውስጥ የሚገኝ ጌጥ ነው። ውድ ዋጋ ያላቸው ግን አንዳንዶቹ ብቻ ናቸው። ነጋዴው የዚህን እንቁ ከፍተኛ ዋጋ ለማወቅ የሚያስችለው አስተዋይነት ስለነበረው ይህን አንድ እንቁ ለማግኘት ያለውን ሁሉ ለመሸጥ ፈቃደኛ ሆነ። ተመላልሶ መጠየቅ ወይም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምናደርግበት ጊዜ የአምላክን መንግሥት ከልቡ የሚያደንቅ ሰው እንደዚህ ነጋዴ እንደሚያደርግ ለማስገንዘብ በዚህ ምሳሌ ለመጠቀም እንችላለን። እንዲህ ያለው ሰው መንግሥቱ ማንኛውም ዓይነት መሥዋዕት ሊከፈልለት እንደሚገባ በመገንዘብ በሕይወቱ ውስጥ የመጀመሪያውን ደረጃ ይሰጠዋል።
በቀስቃሽ መደምደሚያ ማጠቃለል
19. ከቤት ወደ ቤት በምናገለግልበት ጊዜ መደምደሚያችን ለባለቤቱ ምን ሊያሳየው ይገባል?
19 በተጨማሪም የአምላክ ሕዝቦች በቲኦክራቲክ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የአንድ ንግግር ወይም የአንድ ውይይት መደምደሚያ ከአጠቃላዩ መልዕክት ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ ሊኖረው እንደሚገባና አድማጮቹ ምን እንደሚያደርጉ የሚያስገነዝብና እርምጃም እንዲወስዱ የሚያነሳሳ መሆን እንደሚኖርበት ይማራሉ። ከቤት ወደ ቤት በምናገለግልበት ጊዜ ባለቤቱ ምን እንዲያደርግ እንደሚፈለግበት በግልጽ ማወቅ ይኖርበታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ እንዲወስድ ወይም ተመላልሶ መጠየቅ እንዲደረግለት ፈቃደኛ እንዲሆን እንደምንፈልግ በግልጽ ማሳወቅ ያስፈልገናል።
20. በማቴዎስ 7:24-27 ላይ ምን ጥሩ የቀስቃሽ መደምደሚያ ምሳሌ እናገኛለን?
20 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ የተጠቀመበት መደምደሚያ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። በቀላሉ ሊገባ በሚችል ምሳሌ በመጠቀም የተናገራቸውን ቃላት በሥራ ላይ ማዋል የጥበብ መንገድ መሆኑን ገልጾአል። እንዲህ በማለት ደመደመ፣ “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ፣ ጎርፍም መጣ፣ ነፋስም ነፈሰ፣ ያንም ቤት ገፋው። በዓለት ላይም ስለተመሰረተ አልወደቀም። ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሰራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ፣ ጎርፍም መጣ፣ ነፋስም ነፈሰ፣ ያንም ቤት መታው፣ ወደቀም። አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።” (ማቴዎስ 7:24-27) የአምላክ አገልጋዮች የሚያነጋግሩአቸውን ባለቤቶች ለተግባር መቀስቀስ እንደሚገባቸው የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው።
21. ውይይታችን ምን ነገር አስረድቶናል? ይሁን እንጂ ምን ነገር መገንዘብ ይኖርብናል?
21 ከላይ የተመለከትናቸው ነጥቦች ቲኦክራቲክ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ብዙ ሰዎች ብቃት ያላቸው የመንግሥቱ ሰባኪዎች እንዲሆኑ እንዴት እንደሚረዳቸው ያሳያሉ። እርግጥ ብቃታችን በአንደኛ ደረጃ የሚገኘው ከአምላክ ነው። (2 ቆሮንቶስ 3:4-6) በተጨማሪም አገልጋዩ ምንም ያህል ከፍተኛ ብቃት ቢኖረው አንድ ሰው አምላክ በኢየሱስ በኩል ካልሳበው በስተቀር አማኝ ሊሆን አይችልም። (ዮሐንስ 14:6) ቢሆንም የአምላክ ሕዝቦች ለዘላለም ሕይወት በትክክል ያዘነበለ ልብ ያላቸውን በሚፈልጉበት ጊዜ ይሖዋ በሰጣቸው ዝግጅት ሁሉ መጠቀም ይገባቸዋል።
መልስህ ምን ይሆናል?
◻ “ልበ ንጹሐን” እነማን ናቸው? አምላክንስ የሚያዩት እንዴት ነው?
◻ ከቤት ወደ ቤት አገልግሎታችን የመንግሥቱን መልእክት በምናስተዋውቅበት ጊዜ ስለምን ነገሮች ማሰብ ይኖርብናል?
◻ በምናገለግልበት ጊዜ የአምላክን ቃል በሚገባ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
◻ በመስክ አገልግሎት ምክንያታዊና አሳማኝ አቀራረብ እንዲኖረን የሚረዳን ምንድን ነው?
◻ በመስክ አገልግሎት ስለምንጠቀምበት ምሳሌ ምን ማሰብ ይገባል?
◻ ምሥክርነት በምንሰጥበት ጊዜ የምንጠቀምበት መደምደሚያ ምን ዓላማ ማከናወን ይኖርበታል?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ልበ ንጹሐን አምላክን ያዩታል ብሏል፤ ይህ አባባል ምን ማለት ነበር?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥቅሶችን በትክክል አስተዋውቀን ማንበብ፣ በተገቢ ቦታ ላይ እያጠበቁ ማንበብና ለምን እንደተጠቀሱ ግልጽና ትክክል በሆነ መንገድ ማስረዳት ያስፈልጋል።