የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 59—ያዕቆብ
ጸሐፊው:- ያዕቆብ
የተጻፈበት ቦታ:- ኢየሩሳሌም
ተጽፎ ያለቀው:- ከ62 ከክ.ል.በኋላ፣ ቀደም ብሎ
ኢየሱስን ዘመዶቹ ‘አእምሮውን እንደሳተ’ አድርገው ቆጥረውት የነበረ ከመሆኑም ሌላ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት “የገዛ ወንድሞቹ እንኳ አላመኑበትም ነበር።” በመሆኑም ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖንና ይሁዳ ከመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል አልነበሩም። (ማር. 3:21፤ ዮሐ. 7:5፤ ማቴ. 13:55) ታዲያ ያዕቆብ የሚል ስያሜ የተሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የጻፈው የኢየሱስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ነው የምንለው ከምን ተነስተን ነው?
2 የጽሑፍ ዘገባው እንደሚገልጸው ኢየሱስ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ለያዕቆብ ተገልጦለታል። ይህ ደግሞ ያዕቆብ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ሙሉ በሙሉ እንዲያምን እንዳደረገው ጥርጥር የለውም። (1 ቆሮ. 15:7) የሐዋርያት ሥራ 1:12-14 እንደሚገልጸው ከጰንጠቆስጤ ዕለት ቀደም ብሎ ማርያምና የኢየሱስ ወንድሞች ኢየሩሳሌም በሚገኝ በአንድ ቤት ሰገነት ላይ ሆነው ከሐዋርያት ጋር ይጸልዩ ነበር። ይሁን እንጂ ደብዳቤውን የጻፈው ያዕቆብ የሚባለው ሐዋርያ አይደለም? አይደለም። ምክንያቱም ገና በመልእክቱ መግቢያ ላይ ጸሐፊው ራሱን ያስተዋወቀው “የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ” ብሎ እንጂ ሐዋርያ እንደሆነ በመግለጽ አይደለም። ከዚህም በላይ ከያዕቆብ አነጋገር ጋር የሚመሳሰሉት ይሁዳ የተጠቀመባቸው የመግቢያ ቃላት፣ እሱም “የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይና የያዕቆብ ወንድም” መሆኑን ይገልጻሉ። (ያዕ. 1:1፤ ይሁዳ 1) ከዚህ በመነሳት በስማቸው የተጠሩትን መጻሕፍት የጻፉት የኢየሱስ ወንድሞች የነበሩት ያዕቆብና ይሁዳ ናቸው ብለን መደምደማችን ምክንያታዊ ነው።
3 ያዕቆብ ለክርስቲያን ጉባኤ ምክር ያዘለ ደብዳቤ ለመጻፍ ብቃት እንደነበረው አያጠያይቅም። በኢየሩሳሌም ጉባኤ ውስጥ እጅግ የተከበረ የበላይ ተመልካች ነበር። ጳውሎስ ‘የጌታ ወንድም ስለሆነው ስለ ያዕቆብ’ ሲናገር ልክ እንደ ኬፋ (ጴጥሮስ) እና ዮሐንስ የጉባኤው “አዕማድ” ተደርጎ ይቆጠር እንደነበር ገልጿል። (ገላ. 1:19፤ 2:9) ጴጥሮስ ከእሥር ከተፈታ በኋላ ወዲያውኑ “ለያዕቆብና ለወንድሞች” ሁኔታውን እንዲነግሯቸው መልእክተኞችን መላኩ ያዕቆብ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ እንደነበረው ይጠቁማል። ጳውሎስና በርናባስ ግርዘትን አስመልክቶ ለተነሳው ጥያቄ ውሳኔ ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም በሄዱ ጊዜ ‘ለሐዋርያትና ለሽማግሌዎች’ እንደ ቃል አቀባይ ሆኖ ያገለገለውስ ያዕቆብ አልነበረም? የሚገርመው ነገር፣ የውሳኔው ሐሳብም ሆነ የያዕቆብ መልእክት የሚጀምሩት በተመሳሳይ መንገድ ይኸውም “ሰላምታ ይድረሳችሁ!” በማለት ነው። ይህ ደግሞ የሁለቱም ጸሐፊ አንድ መሆኑን የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።—ሥራ 12:17፤ 15:13, 22, 23 NW፤ ያዕ. 1:1 NW
4 ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ እንዳለው ከሆነ ያዕቆብ በድንጋይ ተወግሮ እንዲሞት ያደረገው ሰዱቃዊው ሊቀ ካህናት ሐና (ሐናንያ) ነው። ይህ የሆነው ሮማዊው ገዥ ፊስጦስ ከሞተ በኋላና እሱን የተካው አልባይነስ ሥልጣን ከመጨበጡ በፊት ባለው ጊዜ ማለትም በ62 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ነው።a ይሁን እንጂ ያዕቆብ ደብዳቤውን የጻፈው መቼ ነበር? ያዕቆብ ከኢየሩሳሌም ሆኖ መልእክቱን የላከው ቃል በቃል በየቦታው “ለተበተኑት ለአሥራ ሁለቱ ነገዶች” ነበር። (ያዕ. 1:1 NW) በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት አንስቶ ክርስትና እስኪስፋፋ ድረስ የተወሰነ ጊዜ ያስፈልግ ነበር። በተጨማሪም በመልእክቱ ውስጥ የተገለጹት አሳሳቢ ጉዳዮች ብቅ እስኪሉ ድረስ የተወሰነ ጊዜ ማለፉ ግልጽ ነው። ከዚህም ባሻገር፣ ደብዳቤው እንደሚጠቁመው ክርስቲያኖች ትንንሽ ቡድኖች ከመሆን አልፈው ለደካሞች መጸለይና እነሱን መርዳት የሚችሉ የጎለመሱ “ሽማግሌዎች” ያሉባቸው ጉባኤዎች በመሆን ተደራጅተው ነበር። በተጨማሪም በተወሰነ መጠንም ቢሆን ይታይ የነበረው መዘናጋትና የታይታ አምልኮ ወደ ጉባኤው ሰርጎ እስኪገባ የተወሰነ ጊዜ አልፎ እንደነበር ግልጽ ነው። (2:1-4፤ 4:1-3፤ 5:14፤ 1:26, 27) ስለሆነም ጆሴፈስ፣ ፊስጦስ በሞተበት ጊዜ ስለነበሩት ሁኔታዎች ያሰፈረው ዘገባና ፊስጦስ የሞተው በ62 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው የሚሉት ምንጮች ትክክል ከሆኑ፣ ያዕቆብ መልእክቱን የጻፈው በሕይወት ዘመኑ መገባደጃ አካባቢ ምናልባትም ከ62 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ትንሽ ቀደም ብሎ መሆን አለበት ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው።
5 የያዕቆብ መልእክት በቫቲካን ቁ. 1209፣ በሳይናይቲክ እንዲሁም በአሌክሳንድራይን ጥንታዊ ቅጂዎች ውስጥ መገኘቱ ትክክለኛነቱን ያረጋግጣል። በ397 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከተደረገው የካርቴጅ ጉባኤ በፊት በተዘጋጁ ቢያንስ አሥር በሚያክሉ ጥንታዊ የመጻሕፍት ዝርዝሮች ውስጥ ይገኛል። ጥንት የነበሩ ሃይማኖታዊ ጸሐፊዎችም በተደጋጋሚ ከዚህ መልእክት ጠቅሰው ጽፈዋል። የያዕቆብ መልእክት ከቀሩት በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ቅዱሳን መጻሕፍት ጋር ያለው ጥብቅ ስምምነት በግልጽ ይታያል።
6 ያዕቆብ መልእክቱን የጻፈው ለምን ነበር? መልእክቱን በጥንቃቄ ስንመረምር በአንዳንድ ጉዳዮች ምክንያት በወንድሞች መካከል ችግሮች ተፈጥረው እንደነበር መረዳት እንችላለን። ክርስቲያናዊ የአቋም ደረጃዎች አሽቆልቁለው፣ አልፎ ተርፎም ቸል ተብለው ስለነበር አንዳንዶቹ ከዓለም ጋር በመወዳጀት መንፈሳዊ ምንዝር መፈጸም ጀምረው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የማይጣጣሙ ሐሳቦችን ይዟል የሚል ትችት ለማቅረብ የሚቸኩሉ አንዳንድ ሰዎች የያዕቆብ መልእክት በሥራ የተደገፈ እምነትን ማበረታታቱ ጳውሎስ መዳን የሚገኘው በሥራ ሳይሆን በእምነት እንደሆነ የገለጸውን ሐሳብ የሚሽር እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ያዕቆብ ይጠቅስ የነበረው እምነት በቃላት ብቻ ሳይሆን በሥራም ጭምር መደገፍ እንዳለበት ሲሆን ጳውሎስ ይናገር የነበረው ደግሞ ስለ ሙሴ ሕግ ሥራዎች ነው። እንዲያውም ያዕቆብ እምነት እንዴት በተግባር ሊገለጽ እንደሚችል ተጨማሪ ሐሳብ በመስጠት የጳውሎስን ሐሳብ አጠናክሯል። ያዕቆብ ክርስቲያኖች ዕለት ተዕለት የሚገጥሟቸውን ችግሮች በተመለከተ የሰጠው ምክር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
7 ያዕቆብ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚታዩትን እንደ እንስሳት፣ ጀልባ፣ ገበሬና ዕፅዋት ያሉትን ነገሮች ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም ስለ እምነት፣ ትዕግሥትና ጽናት የተናገረውን ሐሳብ ማራኪ በሆነ መንገድ አቅርቦታል። የኢየሱስን ውጤታማ የማስተማር ዘዴ መኮረጁም ለምክሩ ከፍተኛ ኃይል ጨምሮለታል። ይህን መልእክት የሚያነብ ሰው፣ ብዙዎች አንድ ነገር እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸውን ውስጣዊ ግፊት በተመለከተ ያዕቆብ የነበረውን ጥልቅ ማስተዋል ሲገነዘብ መደነቁ አይቀርም።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
15 ያዕቆብ የኢየሱስን ስም የጠቀሰው ሁለት ጊዜ ብቻ (1:1፤ 2:1) ቢሆንም የጻፈውን መልእክትና የተራራውን ስብከት በጥንቃቄ በማወዳደር፣ የጌታ ትምህርቶች በተግባር ሊውሉ የሚችሉባቸውን በርካታ መንገዶች መጥቀሱን መረዳት እንችላለን። በተመሳሳይም የይሖዋ ስም 13 ጊዜ (NW) ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን አምላክ ቃል የገባቸው ነገሮች እምነታቸውን ለሚጠብቁ ክርስቲያኖች የተዘጋጁ ሽልማቶች መሆናቸው ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። (4:10፤ 5:11) ያዕቆብ ተግባራዊ የሆነውን ምክሩን ይበልጥ ለማዳበር ምሳሌዎችንና ተስማሚ ጥቅሶችን ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ ጠቅሷል። ሐሳቡን የወሰደበትን ምንጭ ለመጠቆም “በመጽሐፍ . . . ተብሎ የተጻፈው፣” “የመጽሐፍ ቃል ተፈጸመ” እና “መጽሐፍ የተናገረው” እንደሚሉ ያሉትን መግለጫዎች ተጠቅሟል። ከዚያም እነዚህ ጥቅሶች በክርስቲያናዊ አኗኗር ውስጥ ምን ትርጉም እንዳላቸው ገልጿል። (2:8, 23፤ 4:5) ያዕቆብ፣ አብርሃም ስለሠራቸው የእምነት ሥራዎች፣ ረዓብ እምነቷን በሥራ ስለ ማሳየቷ፣ ኢዮብ የታመነ ሆኖ ስለ መጽናቱና ኤልያስ በጸሎት ስለ መታመኑ በመጥቀስ ግልጽ ምክር የሰጠን ከመሆኑም ሌላ የአምላክ ቃል እርስ በርሱ ስምምነት ያለው መጽሐፍ ስለመሆኑ ያለንን እምነት ይበልጥ ያጠናክርልናል።—ያዕ. 2:21-25፤ 5:11, 17, 18፤ ዘፍ. 22:9-12፤ ኢያሱ 2:1-21፤ ኢዮብ 1:20-22፤ 42:10፤ 1 ነገ. 17:1፤ 18:41-45
16 ያዕቆብ የቃሉ ሰሚዎች ብቻ ሳንሆን አድራጊዎች ጭምር እንድንሆን፣ የጽድቅ ሥራዎችን በመፈጸም እምነታችንን ማሳየታችንን እንድንቀጥል፣ የተለያዩ ፈተናዎችን በጽናት በመቋቋም ደስታ እንድናገኝ፣ አምላክ ጥበብ እንዲሰጠን ሳናቋርጥ እንድንለምንና ዘወትር በጸሎት ወደ እሱ እንድንቀርብ እንዲሁም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” የሚለውን ክቡር ሕግ እንድንታዘዝ የሰጣቸው ምክሮች እጅግ ታላቅ ጠቀሜታ አላቸው። (ያዕ. 1:22፤ 2:24፤ 1:2, 5፤ 4:8፤ 5:13-18፤ 2:8) የተሳሳተ ትምህርት ማስተማርን፣ ምላስን ሌሎችን በሚጎዳ መንገድ መጠቀምን፣ በጉባኤ ውስጥ የመደብ ልዩነት መፍጠርን፣ ለሥጋዊ ደስታ ከፍተኛ ጉጉት ማሳደርን እንዲሁም ጠፊ በሆነ ሀብት መታመንን በሚመለከትም ጠንካራ ማስጠንቀቂያዎች ሰጥቷል። (3:1, 8፤ 2:4፤ 4:3፤ 5:1, 5) ያዕቆብ ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን መንፈሳዊ ምንዝር መፈጸም እንደሆነና ከአምላክ ጋር እንደሚያጣላ በግልጽ ከተናገረ በኋላ በአምላክ ፊት ንጹሕ የሆነው አምልኮ “ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳትና ከዓለም ርኵሰት ራስን መጠበቅ” እንደሆነ ገልጿል። (4:4፤ 1:27) በጣም ጠቃሚና ለመረዳት ቀላል የሆነው ይህ ሁሉ ምክር ለጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ እንደ “አዕማድ” ከነበረ ሰው ልንጠብቅ የምንችለው ነገር ነው። (ገላ. 2:9) ደግነት የሚንጸባረቅበት መልእክቱ “መልካም ፍሬ” የሚያፈራው ‘የላይኛው ጥበብ’ ክፍል በመሆኑ በችግር በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ ለሚኖሩት ክርስቲያኖችም መመሪያ ሆኖ ያገለግላል።—3:17, 18
17 ያዕቆብ ወንድሞቹ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ሕይወት የማግኘት ግባቸው ላይ እንዲደርሱ የመርዳት ልባዊ ፍላጎት ነበረው። በመሆኑም “እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቦአል” በማለት አጥብቆ አሳስቧቸዋል። የአምላክን ሞገስ ማግኘት ማለት ይሖዋ ‘ለሚወዱት የሰጠውን ተስፋ [ይኸውም] የሕይወትን አክሊል’ መቀበል ማለት በመሆኑ በፈተና ከጸኑ የተባረኩ ወይም ደስተኞች ይሆናሉ። (5:8፤ 1:12) በመሆኑም አምላክ ያዘጋጀው የሕይወት አክሊል ማለትም በሰማይ የማይሞት ሕይወት ማግኘትም ይሁን በምድር ላይ ለዘላለም መኖር የታመኑ ሥራዎችን በመሥራት ለመጽናት የሚያነሳሳ ጠንካራ ምክንያት መሆኑ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። በእርግጥም ይህ ግሩም መልእክት ሁላችንም በሰማይ ወይም ይሖዋ ባዘጋጀው አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ግብ ላይ ለመድረስ እንድንጥር የሚያበረታታ ነው። ይህ አዲስ ዓለም የሚተዳደረው በመንግሥቱ ዘር ማለትም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው።—2:5
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ጁዊሽ አንቲኩዊቲ XX 197-200 (ix, 1)፤ ዌብስተርስ ኒው ባዮግራፊካል ዲክሽነሪ፣ 1983 ገጽ 350