አምላክን የሚያስደስት ልግስና
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በቢታንያ ማርያምን፣ ማርታንና በቅርቡ ከሞት የተነሣውን አልዓዛርን ጨምሮ ከተወሰኑ የቅርብ ወዳጆቻቸው ጋር በማዕድ ዙሪያ ተቀምጠው ነበር። ማርያም ከሦስት መቶ ግራም በላይ የሚመዝን ዋጋው ውድ የሆነ ሽቱ አምጥታ የኢየሱስን እግር ስትቀባ የአስቆሮቱ ይሁዳ በነገሩ ተቆጥቶ “ይህ ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር [የአንድ ዓመት ደመወዝ ያህላል] ተሽጦ ለድሆች ያልተሰጠ ስለ ምን ነው?” ሲል ተቃውሞ አሰማ። ወዲያው ሌሎችም እርሱን ተከትለው ቅሬታቸውን ገለጹ።—ዮሐንስ 12:1-6፤ ማርቆስ 14:3-5
ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ተዉአት . . . ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፣ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፣ እኔ ግን ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም” የሚል መልስ ሰጣቸው። (ማርቆስ 14:6-9) የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ለሰዎች ምጽዋት መስጠት መልካም ተግባር ከመሆኑም በላይ የኃጢአት ይቅርታ እንደሚያስገኝ ያስተምሩ ነበር። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ አምላክ የሚደሰትበት ልግስና ለድሆች ምጽዋት በመስጠት ብቻ የተወሰነ አለመሆኑን በግልጽ ተናግሯል።
በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ እርዳታ ይሰጥ የነበረበትን መንገድ በአጭሩ መመልከታችን አሳቢነታችንን መግለጽ እንዲሁም አምላክን የሚያስደስት ልግስና ማድረግ የምንችልባቸውን አንዳንድ ተግባራዊ መንገዶች ያጎላልናል። ከዚህም በላይ ከሁሉ የላቀ ጥቅም ስለሚያስገኝ ለየት ያለ የልግስና መግለጫ እንመለከታለን።
‘ምጽዋት ስጡ’
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ‘ምጽዋት እንዲሰጡ’ በተለያዩ አጋጣሚዎች አበረታቷቸዋል። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ‘ምጽዋት ስጡ’ የሚለውን ሐረግ ‘ለድሆች ገንዘብ ስጡ’ ብለው ተርጉመውታል። (ሉቃስ 12:33፣ የ1980 ትርጉም ) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከአምላክ ይልቅ ሰጪው እንዲከበር ተብሎ የሚደረግ የይታይልኝ ስጦታ ተገቢ እንዳልሆነ አስጠንቅቋል። “ምጽዋት ስታደርግ፣ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኵራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ” ብሏል። (ማቴዎስ 6:1-4) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህን ምክር ተግባራዊ በማድረግ በወቅቱ የነበሩት ግብዝ የሃይማኖት መሪዎች ካንጸባረቁት የይታይልኝ ባሕርይ በመራቅ የተቸገሩትን ሰዎች የሚጠቅም ሥራ ለማከናወን ወይም በግል ስጦታ ለመስጠት መርጠዋል።
ለምሳሌ ያህል ሉቃስ 8:1-3 መግደላዊት ማርያም፣ ዮሐና፣ ሶስና እና ሌሎችም ያለ ግብዝነት ኢየሱስንና ሐዋርያቱን “በገንዘባቸው” እንዳገለገሉ ይናገራል። ምንም እንኳ እነዚህ ሰዎች ድሆች ባይሆኑም ትኩረታቸውን ሙሉ በሙሉ በአገልግሎቱ ላይ ለማድረግ ሲሉ መተዳደሪያቸውን ትተዋል። (ማቴዎስ 4:18-22፤ ሉቃስ 5:27, 28) ከአምላክ የተቀበሉትን አገልግሎት መፈጸም እንዲችሉ በመርዳት እነዚህ ሴቶች አምላክን አክብረዋል። አምላክም ያሳዩትን ልግስና ወደፊት የሚመጣው ትውልድ በሙሉ እንዲያነብበው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ እንዲቆይ በማድረግ በልግስናቸው መደሰቱን ገልጿል።—ምሳሌ 19:17፤ ዕብራውያን 6:10
ዶርቃ “መልካም ነገር የሞላባት ምጽዋትም የምታደርግ” ሌላዋ ደግ ሴት ነበረች። በባሕር ዳርቻ በሚገኘው በኢዮጴ ላሉ ችግረኛ መበለቶች ልብስ ትሰፋ ነበር። ጨርቁንም ሆነ ሌላ የሚያስፈልገውን ነገር በሙሉ በራሷ ገንዘብ ትግዛ ወይም ደግሞ ምንም ሳታስከፍላቸው ልብሱን ብቻ ትስፋላቸው የምናውቀው ነገር የለም። ያም ሆነ ይህ መልካም ሥራዋ በረዳቻቸው መበለቶች ዘንድ ብቻ ሳይሆን ለደግነቷ ወሮታ በከፈላት በአምላክ ዘንድም ተወዳጅነት አትርፎላታል።—ሥራ 9:36-41
ትክክለኛ የውስጥ ግፊት በጣም አስፈላጊ ነው
እነዚህ ግለሰቦች ልግስና እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? ለሌሎች ደግነት ያደረጉት ቅጽበታዊ በሆነ የርኅራኄ ስሜት ተነሳስተው አይደለም። ድህነት፣ መከራ፣ በሽታ ወይም ሌሎች ችግሮች ላጋጠሟቸው ሰዎች በየዕለቱ የሚችሉትን እርዳታ የመስጠት ሥነ ምግባራዊ ግዴታ እንዳለባቸው ተሰምቷቸዋል። (ምሳሌ 3:27, 28፤ ያዕቆብ 2:15, 16) አምላክን የሚያስደስተው እንዲህ ዓይነቱ ስጦታ ሲሆን ይህም ለአምላክ ባለን ጥልቅ ፍቅር እንዲሁም ምሕረቱንና ለጋስነቱን ለመኮረጅ ባለን ፍላጎት ተነሳስተን የምናደርገው ነው።—ማቴዎስ 5:44, 45፤ ያዕቆብ 1:17
ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው በማለት ሲጠይቅ አስፈላጊ ለሆነው ለዚህ የልግስና ገጽታ አጽንኦት ሰጥቷል:- “የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፣ ወንድሙም የሚያስፈልገውን ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፣ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል?” (1 ዮሐንስ 3:17) መልሱ ግልጽ ነው፤ ሰዎች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር የልግስና መንፈስ እንዲያሳዩ ያነሳሳቸዋል። አምላክ እንደ እርሱ ለጋስ የሆኑትን ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸው ከመሆኑም በላይ ይባርካቸዋል። (ምሳሌ 22:9፤ 2 ቆሮንቶስ 9:6-11) ዛሬ እንዲህ ዓይነት ልግስና ይታያልን? በቅርቡ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የተከናወነውን ነገር ተመልከት።
የአንዲት አረጋዊት የይሖዋ ምሥክር ቤት ከፍተኛ እደሳ ያስፈልገው ነበር። እኚህ እህት የሚኖሩት ብቻቸውን ሲሆን የሚረዳቸው ቤተሰብም አልነበረም። ላለፉት በርካታ ዓመታት በቤታቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባ ይካሄድ የነበረ ከመሆኑም በላይ ወንድሞችን ቤታቸው በመጋበዝ የሚታወቁ እህት ናቸው። (ሥራ 16:14, 15, 40) የጉባኤው አባላት ችግራቸውን በመመልከት እርዳታ ለማድረግ አሰቡ። አንዳንዶች የገንዘብ መዋጮ ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ የጉልበት እርዳታ አበረከቱ። ፈቃደኛ ሠራተኞቹ በጥቂት ቅዳሜና እሁዶች ውስጥ የቤቱን ጣሪያ ቀየሩ፣ አዲስ የመታጠቢያ ገንዳ ገጠሙ፣ የመጀመሪያውን ፎቅ በሙሉ ለስነው ቀለም ቀቡ እንዲሁም ወጥ ቤቱ ውስጥ አዲስ የዕቃ መደርደሪያ ሣጥን አስገቡ። እንደዚህ ማድረጋቸው የእህትን ችግር ለማቃለል ከማስቻሉም በላይ የጉባኤውን አባላት ይበልጥ አቀራርቧል እንዲሁም ክርስቲያኖች እውነተኛ የልግስና መንፈስ የሚያሳዩት እንዴት እንደሆነ ጎረቤቶቻቸው መመልከት ችለዋል።
ሌሎችን በግል መርዳት የምንችልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። አባት ከሌላቸው ልጆች ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንችል ይሆን? ለአንዲት አረጋዊት መበለት ዕቃ መገዛዛት ወይም የሚሰፉ ነገሮችን መስፋት እንችላለን? ዝቅተኛ ኑሮ ያለውን ሰው ምግብ መጋበዝ ወይም ለአንዳንድ ነገሮች የሚያውለው ገንዘብ መስጠት እንችል ይሆን? ሌሎችን ለመርዳት የግድ ሃብታም መሆን አያስፈልገንም። ሐዋርያው ጳውሎስ “በጎ ፈቃድ ቢኖር፣ እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 8:12) ሆኖም አምላክ የሚባርከው እንዲህ ዓይነቱን በግለሰብ ደረጃ በቀጥታ የሚደረግ ስጦታ ብቻ ነውን? አይደለም።
በቡድን ደረጃ ስለሚሰጥ እርዳታስ ምን ማለት ይቻላል?
አንዳንድ ጊዜ በነፍስ ወከፍ የሚደረግ ጥረት ብቻውን በቂ አይሆንም። እንዲያውም ኢየሱስና ሐዋርያቱ ለድሆች የሚሰጥ ገንዘብ ያስቀምጡ የነበረ ሲሆን በአገልግሎታቸው ወቅት የሚያገኟቸው አሳቢ ሰዎች የሚሰጧቸውን የገንዘብ ድጋፍም ይቀበሉ ነበር። (ዮሐንስ 12:6፤ 13:29) በተመሳሳይም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ጉባኤዎች እርዳታ ባስፈለገ ጊዜ ገንዘብ አሰባስበዋል፤ መጠነ ሰፊ የእርዳታ ዝግጅትም አድርገዋል።—ሥራ 2:44, 45፤ 6:1-3፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:9, 10
በ55 እዘአ ገደማ እንዲህ ዓይነት እርዳታ ማሰባሰብ ያስፈለገበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። በይሁዳ የሚገኙ ጉባኤዎች በወቅቱ ተከስቶ በነበረው ከፍተኛ ረሃብ የተነሳ ሳይሆን አይቀርም ለድህነት ተዳረጉ። (ሥራ 11:27-30) ሁልጊዜም ለድሆች የሚያስበው ሐዋርያው ጳውሎስ በጣም ርቃ የምትገኘው መቄዶንያን ጨምሮ ከበርካታ ጉባኤዎች እርዳታ ጠየቀ። እርሱ ራሱ መዋጮ እንዲሰባሰብ ያደረገ ሲሆን ገንዘቡን እምነት የሚጣልባቸው ሰዎች እንዲያደርሱም አድርጓል። (1 ቆሮንቶስ 16:1-4፤ ገላትያ 2:10) ጳውሎስም ሆነ በሥራው የተሳተፉት ሌሎች ክርስቲያኖች ላከናወኑት አገልግሎት ክፍያ አልጠየቁም።—2 ቆሮንቶስ 8:20, 21
ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ በአፋጣኝ እርዳታ ይሰጣሉ። ለምሳሌ ያህል በ2001 የበጋ ወቅት በዩ ኤስ ኤ፣ ቴክሳስ፣ ሂዩስተን ነፋስ የቀላቀለ ኃይለኛ ዝናብ ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ አስከትሎ ነበር። በድምሩ 723 የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ክፉኛ ተጎድተው ነበር። ጥሩ ችሎታ ያላቸው ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ያቀፈ የመልሶ ማቋቋም ኮሚቴ ወዲያውኑ ተመሠረተ። የኮሚቴው ተግባር ወንድሞች ምን እንደሚያስፈልጋቸው መገምገምና ሁኔታውን ለመቋቋም የሚያስፈልጋቸውን እርዳታና ቤቶቻቸውን ለመጠገን የሚያስፈልገውን ገንዘብ መመደብ ነበር። ሥራውን ሁሉ ያከናወኑት በራሳቸው ተነሳሽነት በአቅራቢያው ከሚገኙ ጉባኤዎች የመጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች ናቸው። አንዲት ምሥክር ለተደረገላት እርዳታ ካደረባት የአመስጋኝነት ስሜት የተነሳ የኢንሹራንስ ኩባንያው ለቤቱ ጥገና የወጣውን ወጪ ለመሸፈን የሰጣትን የካሳ ክፍያ በአደጋው ለተጎዱ ሌሎች ወንድሞች እንዲውል ለመልሶ ማቋቋሙ እንቅስቃሴ አበረከተች።
ይሁን እንጂ በተደራጀ መልክ የሚካሄድ የእርዳታ ማሰባሰብ ሥራን በተመለከተ ድጋፍ እንድንሰጥ የሚቀርቡልንን በርካታ ጥያቄዎች በጥንቃቄ ማመዛዘን ይኖርብናል። አንዳንድ ድርጅቶች ለሥራ ማስኬጃ ወይም መዋጮ ለማሰባሰብ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚያወጡት ወጪ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ለታቀደው ዓላማ የሚተርፈው ገንዘብ በጣም ውስን ይሆናል። ምሳሌ 14:15 “የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል” ይላል። በመሆኑም ሁኔታውን በጥንቃቄ መመርመሩ ጥበብ ይሆናል።
ከሁሉ የላቀ ጥቅም የሚያስገኝ ልግስና
ከበጎ አድራጎት የበለጠ ጠቃሚ የሆነ የልግስና ዓይነት አለ። አንድ ሃብታም የሕዝብ አለቃ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለበት በጠየቀው ጊዜ ኢየሱስ “ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፣ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፣ መጥተህም ተከተለኝ” በማለት ይህን በተዘዋዋሪ መንገድ ገልጿል። (ማቴዎስ 19:16-22) ኢየሱስ ‘ለድሆች ከሰጠህ ሕይወት ታገኛለህ’ እንዳላለው ልብ በል። ከዚህ ይልቅ “መጥተህም ተከተለኝ” በማለት አክሎ ነግሮታል። በሌላ አባባል የበጎ አድራጎት ተግባር የሚያስመሰግንና ጠቃሚ ቢሆንም ክርስቲያን ደቀ መዝሙር መሆን ከዚህ የበለጠ ነገር ያካትታል።
ኢየሱስ በዋነኛነት ትኩረት ያደረገው ሰዎችን በመንፈሳዊ በመርዳት ላይ ነበር። ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለጲላጦስ “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ” ብሎታል። (ዮሐንስ 18:37) ኢየሱስ ድሆችን በመርዳት፣ የታመሙትን በመፈወስና የተራቡትን በመመገብ ይታወቅ የነበረ ቢሆንም ዋነኛው ሥራው ደቀ መዛሙርቱን ለስብከቱ ሥራ ማሠልጠን ነበር። (ማቴዎስ 10:7, 8) እንዲያውም መጨረሻ ላይ ከሰጣቸው መመሪያዎች መካከል “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለው ትእዛዝ ይገኝበታል።—ማቴዎስ 28:19, 20
እርግጥ ነው የስብከቱ ሥራ በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች በሙሉ አያስወግድም። ሆኖም የአምላክን መንግሥት ምስራች መስበክ የእርሱን ፈቃድ ስለሚያስፈጽምና መለኮታዊውን መልእክት ለሚቀበሉ ሰዎች ዘላለማዊ ጥቅም የሚያገኙበትን መንገድ ስለሚከፍትላቸው አምላክን ያስከብራል። (ዮሐንስ 17:3፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤትህ መጥተው በሚያነጋግሩህ ጊዜ ለምን አታዳምጣቸውም? ወደ አንተ የሚመጡት መንፈሳዊ ስጦታ ይዘው ነው። ደግሞም ሊሰጡህ የሚችሉት ከሁሉ የተሻለ ስጦታ ይህ እንደሆነ ያምናሉ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አሳቢነታችንን የምንገልጽባቸው በርካታ መንገዶች አሉ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምስራቹን ለሰዎች መስበካችን አምላክን የሚያስደስት ከመሆኑም በላይ ዘላለማዊ ጥቅሞች የሚያገኙበትን መንገድ ይከፍትላቸዋል