ምዕራፍ 20
የክርስቲያን ጉባኤ አደረጃጀት ምን ይመስላል?
ይሖዋ የሥርዓት አምላክ ነው። (1 ቆሮንቶስ 14:33) ከዚህ አንጻር አገልጋዮቹም የተደራጁ ይሆናሉ ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ ነው። የክርስቲያን ጉባኤ የተደራጀው እንዴት ነው? እኛስ በዚህ ረገድ ምን ድርሻ ልናበረክት እንችላለን?
1. ጉባኤውን የሚመራው ማን ነው?
‘የጉባኤው ራስ ክርስቶስ ነው።’ (ኤፌሶን 5:23) ከሰማይ ሆኖ በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦችን እንቅስቃሴ ይመራል። ኢየሱስ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ ሾሟል፤ ታማኝና ልባም ባሪያ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ሽማግሌዎችን ያቀፈ አነስተኛ ቡድን ሲሆን የበላይ አካል ተብሎም ይታወቃል። (ማቴዎስ 24:45-47ን አንብብ።) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኢየሩሳሌም እንደነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ሁሉ የበላይ አካሉም ለዓለም አቀፉ ጉባኤ መመሪያ ይሰጣል። (የሐዋርያት ሥራ 15:2) ሆኖም እነዚህ ሰዎች የድርጅታችን መሪዎች አይደሉም። መመሪያ ለማግኘት ይሖዋን የሚጠይቁና ቃሉን የሚያነብቡ ከመሆኑም ሌላ የኢየሱስን አመራር ይከተላሉ።
2. ሽማግሌዎች የሚባሉት እነማን ናቸው? ምን ሥራስ ያከናውናሉ?
ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆኑ ክርስቲያን ወንዶች ናቸው፤ የአምላክን ቃል ያስተምራሉ እንዲሁም የአምላክን ሕዝብ በመርዳትና በማበረታታት እንደ እረኛ ሆነው ይንከባከባሉ። ለሥራቸው ምንም ዓይነት ክፍያ አይከፈላቸውም። ከዚህ ይልቅ ‘ለማገልገል በመጓጓት ሥራቸውን በአምላክ ፊት በፈቃደኝነት ይወጣሉ፤ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት አይመኙም።’ (1 ጴጥሮስ 5:1, 2) በጉባኤ ውስጥ፣ ሽማግሌዎችን የሚያግዙ የጉባኤ አገልጋዮችም አሉ፤ በጊዜ ሂደት እነዚህ አገልጋዮች ራሳቸው፣ ብቃቱን በማሟላት ሽማግሌ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ።
የበላይ አካሉ አንዳንድ ሽማግሌዎች የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ሆነው እንዲያገለግሉ ይሾማል። እነዚህ ወንድሞች የተለያዩ ጉባኤዎችን በመጎብኘት መመሪያና ማበረታቻ ይሰጣሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን ብቃት ያሟሉ ወንድሞችን ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች አድርገው ይሾማሉ።—1 ጢሞቴዎስ 3:1-10, 12፤ ቲቶ 1:5-9
3. እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር በጉባኤው ውስጥ ምን አስተዋጽኦ ያበረክታል?
በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ በስብሰባ ላይ ተሳትፎ በማድረግና አቅማቸው በፈቀደ መጠን በአገልግሎት በመካፈል ‘የይሖዋን ስም ያወድሳሉ።’—መዝሙር 148:12, 13ን አንብብ።
ጠለቅ ያለ ጥናት
ኢየሱስ ምን ዓይነት መሪ እንደሆነ፣ ሽማግሌዎች የእሱን ምሳሌ ለመከተል ጥረት የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ከኢየሱስና ከሽማግሌዎች ጋር ተባብረን መሥራት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
4. ኢየሱስ ደግ መሪ ነው
ኢየሱስ አስደሳች ግብዣ አቅርቦልናል። ማቴዎስ 11:28-30ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ኢየሱስ ምን ዓይነት መሪ ነው? እኛስ ምን እንዲሰማን ይፈልጋል?
ሽማግሌዎች የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሽማግሌዎች ሥራቸውን ማከናወን ያለባቸው እንዴት እንደሆነ በግልጽ ይናገራል።
ኢሳይያስ 32:2ን እና 1 ጴጥሮስ 5:1-3ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ሽማግሌዎች ልክ እንደ ኢየሱስ ለሌሎች የእረፍት ምንጭ ለመሆን ጥረት እንደሚያደርጉ ማወቅህ ምን ስሜት ያሳድርብሃል?
ሽማግሌዎች ኢየሱስን እንደሚመስሉ የሚያሳዩባቸው ሌሎች አቅጣጫዎች የትኞቹ ናቸው?
5. ሽማግሌዎች እነሱ ራሳቸው ምሳሌ በመሆን ያስተምራሉ
ኢየሱስ፣ ሽማግሌዎች ለተሰጣቸው ሥራ ምን አመለካከት እንዲኖራቸው ይፈልጋል? ቪዲዮውን ተመልከቱ።
ኢየሱስ በጉባኤው ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጿል። ማቴዎስ 23:8-12ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
በዚህ ጥቅስ መሠረት ከሽማግሌዎች ምን ይጠበቃል? የሃይማኖት መሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን እየተከተሉ ያሉ ይመስልሃል?
ሀ. ሽማግሌዎች የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰባቸውን መንፈሳዊነት ለመጠበቅ ጥረት ያደርጋሉ
ለ. ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ላሉ ሁሉ አሳቢነት ያሳያሉ
ሐ. ሽማግሌዎች አዘውትረው ይሰብካሉ
መ. ሽማግሌዎች አስተማሪዎች ናቸው። በተጨማሪም እንደ ጽዳት ያሉ ሌሎች ሥራዎችን ይሠራሉ
6. ከሽማግሌዎች ጋር ተባብረን መሥራት አለብን
መጽሐፍ ቅዱስ ከሽማግሌዎች ጋር ተባብረን መሥራት ያለብን ለምን እንደሆነ ይነግረናል። ዕብራውያን 13:17ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
መጽሐፍ ቅዱስ አመራር ለሚሰጡን ሰዎች እንድንታዘዝና እንድንገዛ የሚመክረን መሆኑ ተገቢ ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
ሉቃስ 16:10ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ቀላል በሚመስሉ ጉዳዮች ጭምር ሽማግሌዎችን መታዘዛችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል መሆን አያስፈልግም።”
አንድ ሰው ከሌሎች ጋር አብሮ አምላክን ማገልገሉ ምን ጥቅም የሚያስገኝለት ይመስልሃል?
ማጠቃለያ
የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ኢየሱስ ነው። በኢየሱስ አመራር ሥር ሆነው የሚያገለግሉትን ሽማግሌዎች በደስታ እንታዘዛለን፤ ምክንያቱም እነዚህ ወንድሞች የእረፍት ምንጭ ይሆኑልናል። በተጨማሪም እነሱ ራሳቸው ምሳሌ በመሆን ያስተምሩናል።
ክለሳ
የጉባኤው ራስ ማን ነው?
ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ ምን ጠቃሚ ሥራ ያከናውናሉ?
እያንዳንዱ የይሖዋ አገልጋይ በጉባኤው ውስጥ ምን አስተዋጽኦ ያበረክታል?
ምርምር አድርግ
የበላይ አካሉና ሌሎች ሽማግሌዎች በዘመናችን ላሉ ክርስቲያኖች በጥልቅ እንደሚያስቡ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ስለሚያከናውኑት ሥራ ማወቅ ትፈልጋለህ?
ሴቶች በጉባኤው ውስጥ ምን ድርሻ አላቸው?
“በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ ሴቶች አገልጋይ መሆን ይችላሉ?” (መጠበቂያ ግንብ መስከረም 1, 2012)
ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለማበረታታት ምን ያህል ጠንክረው ይሠራሉ?
“‘ለደስታችን ከእኛ ጋር አብረው የሚሠሩት’ ክርስቲያን ሽማግሌዎች” (መጠበቂያ ግንብ ጥር 15, 2013)