ድል የሚያስገኝ ጽናት
“የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋል”—ዕብራውያን 10:36
1. በዛሬው ጊዜ ይሖዋን ለሚያገለግል ለማንኛውም ሰው ጽናት የግድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
መላው ዓለም ዓመፅ አነሣሽ በሆነ አምላክ ቁጥጥር ስር የሚገኝ ነው። የማይታየው የዓለም ገዥው ሰይጣን ዲያብሎስን ጥረቶቹ ሁሉ ይሖዋን በመቃወምና የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ የበላይ ገዥነት በመሲሐዊ መንግሥቱ አማካኝነት እንዳይረጋገጥ በመዋጋት ላይ እንዲያተኩር አድርጓል። ይህም ራሱን ለአምላክ ለሚወስንና በበላይ ገዥነቱ ጥያቄ ረገድም ከአምላክ ጎን ለሚቆም ለማንኛውም ሰው ከዚህ ዓለም ተቃውሞ መድረሱ የማይቀር ነገር ይሆናል። (ዮሐንስ 15:18-20፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ስለዚህ እያንዳንዳችን ይህ ዓለም በአርማጌዶን ተሸንፎ ግብአተ መሬቱ እስከሚፈጸም ድረስ ጸንተን ለመኖር መዘጋጀት አለብን። በእምነታቸውና በፍጹም አቋም ጠባቂነታቸው ዓለምን ከሚያሸንፉት የአምላክ ድል አድራጊ ሕዝቦች መሃል ለመገኘት እስከፍጻሜው ድረስ ለመታገሥ ቁርጥ ውሣኔ ማድረግ አለብን። (1 ዮሐንስ 5:4) ይህን ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው?
2, 3. ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍተኛ የጽናት ምሳሌ የሆኑት እንዴት ነው?
2 መጀመሪያ ነገር ማበረታቻ ለማግኘት ሁለት ታላላቅ የጽናት ምሳሌዎችን መመልከት እንችላለን። እነዚህ ሁለት የጽናት ምሳሌዎች እነማን ናቸው? አንደኛው “የፍጥረት በኩር” የሆነውና ወደ መኖር ከመጣበት ቁጥሩ የማይታወቅ እጅግ ብዙ ዘመን አንሥቶ በአምላክ አገልግሎት በታማኝነት የጸናው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ አምላክን በታማኝነት በማገልገል መጽናቱ ከእርሱ በኋላ ወደ ሕልውና ለመጡት በሰማይም ሆነ በምድር ለሚኖሩ አስተዋይ ፍጡሮች ሁሉ ምሳሌ ሆኗል። (ቆላስይስ 1:15, 16) ይሁን እንጂ ከሁሉ የበለጠው የጽናት ምሳሌያችን በጽንፈ ዓለማዊ ልዕልናው ላይ የተነሣበትን ዓመፅ ለረጅም ጊዜ የታገሠውና የበላይ ገዥነቱን አከራካሪ ጉዳይ ለመጨረሻ ጊዜ መደምደሚያ እስከሚያበጅለት ጊዜ ድረስ ጸንቶ የኖረው ይሖዋ አምላክ ነው።
3 ይሖዋ ክብሩና ጥልቅ የግል ስሜቱ ተነክቶበትም እንኳ አርዓያ ባለው መንገድ ታግሷል። የሚሰድቡት ፍጥረታት ሁሉ ሰይጣን ዲያብሎስም ጭምር በከፍተኛ ሁኔታ እያስቆጡት እንኳ እርምጃ ከመውሰድ ራሱን ገትቷል። ለአምላክ ታጋሽነትና ምህረት አመስጋኞች መሆን አለብን። እነዚህ ጠባዮቹ ባይኖሩ ኖሮ ይህችን በቅጽበት የምታልፍ ሕልውና እንኳ አናገኝም ነበር። እውነትም ይሖዋ ወደር የማይገኝለት ትዕግሥትና ጽናት ያለው መሆኑን አስመስክሯል።
4, 5. (ሀ) የጳውሎስ የሸክላ ምሳሌ የአምላክን ጽናትና ምሕረት የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ ምሕረት ያለአግባብ የባከነ ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው?
4 ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት በተናገረ ጊዜ እነዚህን ሁለት የአምላክ ጠባዮች ማለትም ታጋሽነቱንና ምሕረቱን ማመልከቱ ነበር፦ “ሸክላ ሠሪ ከአንዱ ጭቃ ክፍል አንዱን ዕቃ ለክብር አንዱንም ለውርደት ሊሠራ በጭቃ ላይ ሥልጣን የለውምን? ነገር ግን እግዚአብሔር ቁጣውን ሊያሳይ ኃይሉንም ሊገልጥ ወዶ አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው በምሕረት ዕቃዎች ላይ የክብሩን ባለጠግነት ይገልጥ ዘንድ ለጥፋት የተዘጋጁትን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት ከቻለ እንዴት ነው? የምሕረቱ ዕቃዎችም ከአይሁድ ብቻ አይደሉም፤ ነገር ግን ከአሕዛብ ደግሞ የጠራን እኛ ነን።”—ሮሜ 9:21-24
5 እነዚህ ቃላት እንደሚገልጹት ይሖዋ በዚህ እስከ አሁን ድረስ በቆየው የታጋሽነቱ ዘመን ክብራማ ዓላማውን በማራመድ ለአንዳንድ ሰብዓዊ ሸክላዎች ምሕረቱን ይገልጻል። እነዚህን ሸክላዎች ለዘላለማዊ ክብር ያዘጋጃቸዋል፤ በዚህም የታላቁን ባላጋራውን የሰይጣን ዲያብሎስንና የጀሌዎቹን ክፉ ዓላማዎች ያከሽፋል። ጥፋት የሚገባቸው የቁጣ ዕቃዎች ወደ መሆን የተለወጡት ሁሉም የሰው ዘሮች አይደሉም። ይህም የሁሉን ቻይ አምላክ የትዕግሥት ጽናት የሚያስመሰግን ነው። ምሕረቱ ከንቱ ሆኖ አይቀርም፤ ምሕረቱ (1) በተወዳጅ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር የመተዳደር ክብራማ መንግሥታዊ ቤተሰብን በሰማይ (2) ሁሉም የዘላለም ሕይወት ወራሾች የሆኑ፣ በምድራዊ ገነት መዳንን ያገኙና ፍጹማን የተደረጉ ሰብዓዊ ፍጥረቶችን ያስገኛል።
እስከ መጨረሻ መጽናት
6. (ሀ) ክርስቲያኖች የጽናት ፈተና እንዳይደርስባቸው ለማድረግ የማይችሉት ለምንድን ነው? (ለ) “ጽናት” ለሚለው ቃል የግሪክኛው ቃል አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው ምንድን ነው?
6 ይህን የመሰለ ግሩም ተስፋ ስላለን “እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል” የሚሉት የኢየሱስ የሚያነቃቁ ቃላት ባለማቋረጥ በጆሮአችን ሊያቃጭሉ ይገባል። (ማቴዎስ 24:13) የክርስቲያን ደቀመዝሙርነትን ጉዞ በጥሩ ሁኔታ መጀመር አስፈላጊ ነው። በመጨረሻ ላይ ዋጋ የሚያስገኝልን ግን መጽናታችን ጉዞውን በጥሩ ሁኔታ መጨረሳችን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና” ብሎ በተናገረ ጊዜ የመጽናትን አስፈላጊነት አጥብቆ ገልጿል። (ዕብራውያን 10:36) እዚህ ላይ “መጽናት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ሃይፖሞኔ” ነው። ይህም ቃል አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው እንቅፋት፣ ስደት፣ መከራና ፈተና በሚደርስበት ጊዜ ሁሉ ተስፋ የማይቆርጥን ደፋርነት፣ ፍንክች ያለማለትን ወይም ታጋሽነትን ነው። በመጨረሻው ላይ ደህንነት ለማግኘት ከፈለግን ለዚህ መዳን አስፈላጊ ከሆኑ ዝግጅቶች አንዱ ለሆነው ለጽናት ፈተና መገዛት ይኖርብናል።
7. ማስወገድ ያለብን ምን ዓይነት ራስን የማሞኘት ከንቱ ሐሳብ ነው? ለመጽናት የማን ምሳሌ ይረዳናል?
7 ፈተናውን በፍጥነት እናልፈዋለን በሚል አስተሳሰብ ራሳችንን አናሞኝ። ይሖዋ እንኳ በጽንፈ ዓለም የበላይ ገዥነትና በሰው ታማኝነት ላይ የተነሳው ወሳኝ ጥያቄ በሆነ መንገድ መልስ እንዲያገኝ ሲል ራሱን ከጽናት ፈተና አላዳነም። መጥፎ ነገሮችን በቅጽበት ሊያጠፋቸው ሲችል ታግሶአቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስም ለጽናት ጥሩ ምሳሌ ሆኖ ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:21፤ ከሮሜ 15:3-5 ጋር አወዳድር) እኛም በፊታችን እነዚህን የመሰሉ አንጸባራቂ ምሳሌዎች ስላሉን እስከ መጨረሻው ለመጽናት ፈቃደኞች እንሆናለን።—ዕብራውያን 12:2, 3
አስፈላጊው ብቃት
8. ሐዋርያው ጳውሎስ የገለጸው ለሁላችን የሚያስፈልግ ምን ባሕርይ ነው?
8 ከቀድሞ ዘመን ጀምሮ ታማኝነቱን በጽናት ማረጋገጥ ያላስፈለገው የአምላክ አገልጋይ አይገኝም። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ጐላ ብለው የሚታዩ እስከ ሞት ታማኞች የሆኑና በሰማይ ዘላለማዊ ሕይወት ለማግኘት ብቁ የሆኑ ግለሰቦች ጽናታቸውን ማረጋገጥ አስፈልጓቸዋል። ለምሳሌ ያህል አስቀድሞ ፈሪሳዊ የነበረው የጠርሴሱ ሳውል ለቆሮንቶስ ሰዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እኔ ምንም ባልሆን እንኳ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በምንም አላንስም። በእርግጥ የሐዋርያነት ምልክት በመካከላችሁ በምልክትና በድንቅ ነገር በተአምራትም በሁሉ ትዕግሥት ተደረገ።” (2 ቆሮንቶስ 12:11, 12) ጳውሎስ የሥራ ጫና ቢኖርበትም አገልግሎቱን እጅግ ይወድ ስለነበረ በብዙ ችግር ጸንቷል። ነቀፌታ እንዳያመጣበትም ከልቡ ጥሯል።—2 ቆሮንቶስ 6:3, 4, 9
9. (ሀ) ቅቡዓን ቀሪዎች ጽናት ያሳዩት እንዴት ነው? ከምንስ ውጤት ጋር? (ለ) በመለኮታዊ አገልግሎት በታማኝነት እንድንቀጥል የሚረዳን ምን ማበረታቻ ነው?
9 ቅርብ በሆነ ዘመን ማለትም ከመጀመሪያው ዓለም ጦርነት ቀደም ብሎ አምላክን ያገለግሉ የነበሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች 1914 የአሕዛብ ዘመን የሚፈጸምበት መሆኑን አውቀው ነበር። ከእነሱም መካከል ብዙዎቹ በዚያ የማይረሳ ዓመት ሰማያዊ ሽልማታቸውን እንደሚቀበሉ ተስፋ አድርገው ነበር። ነገር ግን ይህ ተስፋቸው አልተፈጸመም። አሁን ሐቁ እንደሚያሳየው ገና ብዙ አሥር ዓመታት ይቀራቸው ነበር። በዚህ ባልጠበቁት ሁኔታ በተራዘመው የምድራዊ ሕይወታቸው ጊዜ በይሖዋ አምላክ እጅ ተጣርተዋል። (ዘካርያስ 13:9፤ ሚልክያስ 3:2, 3) በጽናት መቀጠላቸው እንዲሻሻሉ አስችሏቸዋል። የይሖዋ አገልጋዮች በመሆን በስሙ የሚጠሩ ሕዝቦች ለመሆን በመቻላቸው ተደስተዋል። (ኢሳይያስ 43:10-12፤ ሥራ 15:14) ዛሬ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶችና በርካታ አነስተኛ ውጊያዎች ውስጥ አልፈው ምሥራቹን አሁን ከአራት ሚልዮን በላይ በሆኑትና ቁጥራቸው እየጨመረ በሚሄደው የሌሎች በጎች እጅግ ብዙ ሕዝብ በመታገዝ ምሥራቹን በማሰራጨት ላይ በመሆናቸው በጣም ተደስተዋል። የሚደሰቱበት መንፈሳዊ ገነታቸው በመላው ምድር በጣም ሩቅ ወደሆኑት የባሕር ደሴቶችም ሳይቀር ተሰራጭቶአል። ዘመናት እያለፉ በሄዱ መጠን በበለጠ አድናቆት የምንመለከተው ይህን የመሰለ እጅግ የተወደደ አያያዝና መብት የይሖዋ ፈቃድና ዓላማ ሙሉ በሙሉ እስኪፈጸም ድረስ በመለኮታዊ አገልግሎት እንድንቀጥል ማበረታቻ ሆኖናል።
10. መዳከም እንዳይደርስብን ዘወትር የሚያስፈልገው ምንድን ነው?
10 ሽልማታችን የሚመካው በጽናታችን ላይ ስለሆነ በዚህ አስፈላጊ ጉዳይ ረገድ የማያቋርጥ ማሳሰቢያ ማግኘት ያስፈልገናል። (1 ቆሮንቶስ 15:58፤ ቆላስይስ 1:23) በይሖዋ ሕዝቦች መካከል መዳከም እንዳይኖር ልክ በአንደኛው መቶ ዘመን በጳውሎስና በበርናባስ ተመላልሶ መጠይቅ ይደረግላቸው እንደነበሩት አዲስ የተቋቋሙ ጉባኤዎች እኛም እውነትንና እውነትን የማሰራጨትን ውድ መብት አጥብቀን እንድንይዝ መበረታታት ይኖርብናል። (ሥራ 14:21, 22) ሐዋርያው ዮሐንስ እንደተናገረው እውነት በውስጣችን እንዲኖር ቁርጥ ውሣኔያችን ይሁን። “ከእኛ ጋርም ለዘላለም ይሆናል።”—2 ዮሐንስ 2
የማያወላውል ጽናት ይዞ መጠበቅ
11.አምላክ ለአገልጋዮቹ የሚሠራበት ደንብ ምን ይመስላል? ይህስ በዮሴፍ ረገድ የተገለጸው እንዴት ነው?
11 የሚያጋጥመን ፈተና እስኪያበቃ ድረስ ጊዜ ይወስዳል። የአምላክ ደንብ ከጥንት ጀምሮ አምላክ ለአገልጋዮቹ ያወጣው ደንብ በእምነት ለመቀጠል ያላቸው ቁርጠኝነት በሚፈተንበት ጊዜ ጠብቅ! ጠብቅ! ጠብቅ! የሚል ይመስላል። እነዚህ ታማኝ አገልጋዮች መጠበቃቸው በመጨረሻው ሽልማት አስገኝቶላቸዋል። ለምሳሌ ያህል ዮሴፍ ባሪያና እሥረኛ ሆኖ ለ13 ዓመታት መጠበቅ ነበረበት። ይህ ያጋጠመው ሁኔታ ግን ባሕርዩን አንጥሮለታል። መዝሙር 105:17-19
12, 13. (ሀ) አብርሃም የታማኝነት ጽናት ምሳሌ የሆነው እንዴት ነው? (ለ) የአብርሃም እምነትና ጽናት ለእኛ በምሳሌነት የሚጠቀሱት በምን መንገድ ነው?
12 አብርሃም አምላክ ከከለዳውያን ዑር ወጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲሄድ ሲጠራው ዕድሜው 75 ዓመት ነበር። አብርሃም በመሐላ የተደገፈውን የአምላክ ተስፋ ማረጋገጫ የተቀበለውን በ125 ዓመቱ ነበር። ይህም የሆነው የወለደውን ልጁን ይስሐቅን የይሖዋ መልአክ እጁን ይዞ እንዳያርደው ባይከለክለው ኖሮ መሥዋዕት አድርጎ እስከማቅረብ እምነቱን ካሳየ በኋላ ነበር። (ዘፍጥረት 22:1-18) አብርሃም በማያውቀው አገር በእንግድነት እየኖረ የጠበቀበት የ50 ዓመት ጊዜ በጣም ረዥም ሆኖበት ነበር። ቢሆንም በ175 ዓመቱ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ለሌላ 50 ዓመት ታግሶ ኖሯል። አብርሃም በዚያ ሁሉ ጊዜ የይሖዋ አምላክ ታማኝ ምስክርና ነቢይ ነበር።—መዝሙር 105:9-15
13 የአብርሃም ዘር በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተስፋ የተገባውን በረከት ለመቀበል ለሚፈልጉ የአምላክ አገልጋዮች ሁሉ የአብርሃም እምነትና ጽናት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው። (ዕብራውያን 11:8-10, 17-19) እሱን በሚመለከት በዕብራውያን 6:11-15 እንዲህ እናነባለን፦ “በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ ‘በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ፣ እያበዛሁም አበዛሃለሁ፣’ ብሎ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ በራሱ ማለ። እንዲሁም እርሱ ከታገሠ በኋል ተስፋውን አገኘ።”
14. የጽናት ፈተናው ማብቂያ እንደሌለውና ሽልማቱም የማይጨበጥ እንደሆነ አድርገን ልናስብ የማይገባን ለምንድን ነው?
14 ቀደም ብሎ ከቅቡዓን ቀሪዎች አንዳንዶቹ እውነተኛዋ የክርስቲያን ጉባኤ በሰማይ ትከብራለች ብለው ጠብቀውት የነበረው የአሕዛብ ዘመን ካበቃበት ከ1914 ወዲህ 77 ዓመት አልፈዋል። ቅቡዓኑ ከእንግዲህ በኋላ ለምን ያህል ጊዜ መጠበቅ እንደሚኖርባቸው አናውቅም። ታዲያ ማወላወልና የጥበቃው ጊዜ ፍጻሜ የሌለውና ሽልማቱም የማይጨበጥ ቅዠት ነው ብለን ማሰብ ይገባናልን? አይገባንም። እንዲህ ብናደርግ የአምላክን የበላይ ገዥነት መደገፍ ወይም ለስሙ ክብር የሚያመጣ አይሆንም። አምላክ ከዚህ ዓለም ለይቶ ድልና የድል ውጤት የሆነውን የዘላለም ሕይወት ሽልማት ለኛ ለመስጠት በቂ ምክንያት አይኖረውም። ቅቡዓኑና በግ መሰል ባልንጀሮቻቸው ጊዜ ምንም ያህል ይርዘም ይሖዋ በገዛ ራሱ ጊዜ እርምጃ እስኪወስድ ሊጠብቁት ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። እንዲህ ዓይነት ለአርዓያነት የሚበቃ ጽናት በማሳየት የአብርሃምን መንገድ ይከተላሉ።—ሮሜ 8:23-25
15. (ሀ) የይለፍ ቃላችን ወይም አማራጭ የማይገኝለት ጉዳይ ምንድን ነው? አምላክ በድል እንድናልፍ የረዳንስ በምን ገጠመኞች ወቅት ነው? (ለ) ምን የጳውሎስ ማሳሰቢያ ነው ለዘመናችንም ተስማሚ የሆነው?
15 እንግዲያውስ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ የማያወላውል ጽናት ማሳየት አማራጭ የማይገኝለት ጉዳይ ነው። (ሮሜ 2:6, 7) ከዚህ በፊት በእስራትና ማጎሪያ ካምፖችን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች በደረሰብን ከባድ መከራዎች ደግፎን ለስሙና ለዓላማው ክብር እንድናሸንፍ አስችሎናል።a ፈተናችን ከማለቁ በፊት በቀረው ጊዜም ይሖዋ ይህንኑ ማድረጉን ይቀጥላል። የጳውሎስ ማሳሰቢያ ለጊዜአችንም ተስማሚ ነው፦ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና።”—ዕብራውያን 10:36 ፤ ሮሜ 8:37
16. ሕይወታችንን ለይሖዋ መወሰናችንን ገደብ ልናበጅለት የማይገባን ለምንድን ነው?
16 ይሖዋ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ የሚያሠራን ሥራ እስካለን ድረስ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ይህ ሥራ እስኪፈጸም ድረስ በሥራው ለመጠመድ እንፈልጋለን። (ዮሐንስ 17:4) ሕይወታችንን ለይሖዋ የሰጠነው ጥቂት ጊዜ ካገለገልነው በኋል አርማጌዶን ቶሎ ብሎ ይመጣል ብለን አልነበረም። ሕይወታችንን የሰጠነው ለዘላለም ነው። አምላክ እንድንሠራ የሚፈልግብን ሥራ በአርማጌዶን ጦርነት አያበቃም። ይሁን እንጂ ከዚህ ታላቅ ጦርነት በኋላ የሚመጡትን አስደናቂ ነገሮች ለማየት የምንበቃው ከአርማጌዶን በፊት መሠራት ያለበትን ሥራ ከፈጸምን በኋላ ብቻ ነው። ያኔ ሥራውን ከመቀጠል አስደሳች መብት በተጨማሪ ቃል የገባልንንና ለረዥም ጊዜ ስንጠብቀው የኖርነውን በረከት እንሸለማለን። —ሮሜ 8:32
ለአምላክ ያለን ፍቅር እንድንጸና ይረዳናል
17, 18. (ሀ) በጭንቀት ጊዜ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት እንድንጸና የሚረዳን ምንድን ነው? (ለ) ድል እንድናገኝ የሚረዳን ምንድን ነው? ስለቀረው ጊዜስ ምን ማለት የለብንም?
17 ምናልባት ጊዜው አስጨናቂ ሲሆንብን ‘ከአሁን በኋላ ልንጸና የምንችለው እንዴት ነው?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። መልሱ ምንድን ነው? አምላክን በሙሉ ልባችን፣ ሐሳባችን፣ ነፍሳችንና ኃይላችን በመውደድ ነው። “ፍቅር ይታገሣል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፤ አይታበይም። ሁሉን ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል። ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም።” (1 ቆሮንቶስ 13:4, 7, 8) የምንጸናው ለአምላክ ካለን ፍቅር የተነሣ ካልሆነ ጽናታችን ዋጋ አይኖረውም። ነገር ግን ለይሖዋ በማደራችን ምክንያት ችግር ላይ ወድቀን ብንታገሥ ጽናታችን ለሱ ያለንን ፍቅር ጥልቅ የማድረግ ውጤት ይኖረዋል። ኢየሱስ እንዲጸና ያስቻለው ለአባቱ ለአምላክ የነበረው ፍቅር ነው። (ዮሐንስ 14:30, 31፤ ዕብራውያን 12:2) እውነተኛ የልባችን አንቀሳቃሽ ኃይል አባታችን ለሆነው አምላክ ያለን ፍቅር ከሆነ ልንታገሥ የማንችለው ምን ነገር ይኖራል?
18 በዚህ ከሁሉ የከፋ አስጨናቂ የፈተና ዘመን ዓለምን ድል አድርገን እንድንቆይ ያስችለን ለይሖዋ ያለን የማያወላውል ፍቅር ነው። ይህ አሮጌ የነገሮች ሥርዓት እንዲኖር የሚፈቀድለት ጊዜ የቱንም ያህል ረዥም ይሁን ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚያስፈልገንን ዕርዳታ መስጠቱን ይቀጥላል። (1 ጴጥሮስ 5:10) በእርግጥ ገና ምን ያህል ጊዜ እንደቀረው አንተነብይም። የተወሰነ ቀን አንመድብም። የጊዜውን ጉዳይ ለታላቁ የጊዜ ወይም የሰዓት አክባሪ ለይሖዋ አምላክ እንተዋለን።—መዝሙር 31:15
19, 20. (ሀ) የምንጸናበትን እያንዳንዱን ቀን እንዴት መመልከት ይኖርብናል? (ለ) ምን ሞኝነት ነው ልናስወግደው የምንፈልገው?
19 ይሁን እንጂ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ይፈጸምበታል ተብሎ በትንቢት የተነገረለት ትውልድ አሁን በዕድሜ ገፍቷል። (ማቴዎስ 24:3, 32-35) ስለዚህ የጸናንበት እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቅጥር ሰይጣንና አጋንንቱ በመኖራቸው ብቻ ጽንፈ ዓለምን ለማርከስ ከቀራቸው ጊዜ አንደ ቀን እየቀነስን እንዳለንና ይሖዋም “ለጥፋት የተዘጋጁትን የቁጣ ዕቃዎች” ከዚያ በላይ ሊታገሥ ወደማይችልበት ጊዜ በአንድ ቀን እየቀረብን እንዳለን አንርሳ። (ሮሜ 9:22) በቅርቡ የይሖዋ ትዕግሥት ወደ ፍጻሜው ሲደርስ አምላካዊ ባልሆኑ ወንዶችና ሴቶች ላይ ቁጣውን ያመጣል። ይህን በማድረጉም ክፉዎች ለዚህ ሁሉ ጊዜ እንዲኖሩ የፈቀደላቸው ቢሆንም አካሄዳቸውን ይጠላው እንደነበር መለኮታዊ ተቃውሞውን ይገልጻል።
20 በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የተዘረጋልንን ክብራማ ሽልማት ለማግኘት ፍቅራዊ ጥረት ማድረጋችንን ማቋረጥ ትልቅ ሞኝነት ይሆንብናል። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ራሱን የጽንፈ ዓለም ልዑል መሆኑን በሚያሳውቅበት በዚህ እጅግ ታላቅ ዘመን ለይሖዋ ምሥክሮቹ በመሆን በታማኝነት ለመቀጠል ቁርጥ ውሣኔ አድርገናል።
[የግርጌ ማስታወሻ
a ለምሳሌ ያህል ክርስቲን ኤልዛቤት ኪንግ እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “(የናዚ) መንግሥት ያልተሳካለት በምስክሮቹ ላይ ብቻ ነበር። ምክንያቱም በሺዎች የሚቆጠሩት የይሖዋ ምስክሮችን ቢገድልም ሥራው ቀጥሎ ስለነበር በ 1945 ብሔራዊ ሶሻሊዝም ሲጠፋ የይሖዋ ምስክሮች እንቅስቃሴ ግን ገና ሕያው ነበር። የምስክሮች ቁጥር ጨምሮ ነበር። በማንኛውም መንገድ አቋማቸውን አልለወጡም ነበር። የይሖዋ ምስክሮች እንቅስቃሴ ብዙ ሰማዕታት አገኘ። ይሖዋ አምላክ ባደረጋቸው ጦርነቶች አንድ ተጨማሪ ጦርነት በተሳካ ሁኔታ ተዋጋ።”—ዘ ናዚ ስቴትስ ኤንድ ዘ ኒው ሪሊጅንስ ፋይፍ ኬዝ እስታዲስ ኢን ነን ኮንፎርሚቲ ገጽ 193
እንዴት ብለህ መልስ ትሰጣለህ?
◻ የጽናታችንን መፈተን ልናመልጥ የማንችለው ለምንድን ነው?
◻ ምን ከንቱ ስሜትን ነው ማስወገድ የምንፈልገው?
◻ ማንኛውንም መዳከም እንድናስወግድ ምን ያስፈልገናል?
◻ የይለፍ ቃላችን ወይም አማራጭ የማይገኝለት ጉዳይ ምንድን ነው?
◻ በጭንቀት ጊዜ እንድንጸና የሚረዳን ምንድን ነው?
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ ሕዝቦች የስፔይን ወደብ በሆነችው በትሪኒዳድ እንደሚኖሩት እንደነዚህ የይሖዋ ምስክሮች አምላክን በተስፋ ለመጠባበቅ ፈቃደኞች ሆነዋል