“ታላቁ የይሖዋ ቀን ቀርቧል”—ወደ ጉልምስና ግፉ
“ወደ ጉልምስና እንግፋ።”—ዕብ. 6:1
1, 2. በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የኖሩት ክርስቲያኖች ‘ወደ ተራሮች ለመሸሽ’ የሚያስችል ምን አጋጣሚ ተከፍቶላቸው ነበር?
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ ቀርበው ‘የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምንድን ነው?’ በማለት ጠይቀውት ነበር። ኢየሱስ ለጥያቄያቸው መልስ ሲሰጥ የተናገረው ትንቢት በአንደኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ ፍጻሜውን አግኝቷል። ኢየሱስ የሥርዓቱ መጨረሻ በጣም መቃረቡን የሚጠቁም ያልተለመደ ክንውን እንደሚፈጸም ተናግሮ ነበር። “በይሁዳ ያሉ” ሰዎች ይህ ክንውን መፈጸሙን ሲመለከቱ “ወደ ተራሮች [መሸሽ]” ነበረባቸው። (ማቴ. 24:1-3, 15-22) ታዲያ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምልክቱን አስተውለው እሱ እንዳላቸው ያደርጉ ይሆን?
2 ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከሦስት አሥርተ ዓመታት ገደማ በኋላ ይኸውም በ61 ዓ.ም. ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሩሳሌምና በአካባቢዋ ለሚኖሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤ ጻፈ፤ ጳውሎስ የላከው ጠንከር ያለ መልእክት እነዚያ ክርስቲያኖች አመለካከታቸውን እንዲያስተካክሉ የሚረዳ ነበር። በወቅቱ ጳውሎስም ሆነ የእምነት ባልንጀሮቹ ባያውቁትም ‘የታላቁን መከራ’ የመጀመሪያ ምዕራፍ የሚጠቁመው ምልክት ሊፈጸም የቀረው አምስት ዓመት ብቻ ነበር። (ማቴ. 24:21) በ66 ዓ.ም. በሴስቲየስ ጋለስ የሚመራው የሮም ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ሰነዘረ፤ በዚህ ወቅት ሠራዊቱ ከተማዋን ድል ለማድረግ ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ሳይታሰብ ወደኋላ ተመለሰ። በዚህ ጊዜ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የነበሩት ክርስቲያኖች ከተማዋን ለቅቀው ለመሸሽ የሚያስችል አጋጣሚ ተከፈተላቸው።
3. ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ምን ምክር ሰጥቷቸዋል? ይህንን ምክር ለመስጠት ያነሳሳውስ ምንድን ነው?
3 እነዚያ ክርስቲያኖች፣ በወቅቱ እየተከናወኑ ያሉት ነገሮች ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ እንደሆኑና መሸሽ እንደሚገባቸው ለመገንዘብ ጥልቅ ማስተዋል እንዲሁም መንፈሳዊ እይታ ያስፈልጋቸው ነበር። ይሁንና አንዳንዶች ‘ጆሯቸው ደንዝዞ’ ነበር። በመንፈሳዊ ሁኔታ “ወተት” እንደሚያስፈልጋቸው ሕፃናት ሆነው ነበር። (ዕብራውያን 5:11-13ን አንብብ።) ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በእውነት ጎዳና ሲመላለሱ የቆዩ አንዳንድ ክርስቲያኖች እንኳ “ሕያው ከሆነው አምላክ [የመራቅ]” አዝማሚያ እየታየባቸው ነበር። (ዕብ. 3:12) ጥፋት የሚመጣበት ‘ቀን እየቀረበ’ በነበረበት በዚያ ወቅት ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መቅረትን ‘ልማድ ያደረጉም’ ነበሩ። (ዕብ. 10:24, 25) ጳውሎስ፣ “ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን መሠረታዊ ትምህርት አልፈን ስለመጣን ወደ ጉልምስና እንግፋ” በማለት ወቅታዊ የሆነ ምክር ሰጥቷቸዋል።—ዕብ. 6:1
4. በመንፈሳዊ ሁኔታ ንቁ መሆን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህንን ለማድረግስ ምን ሊረዳን ይችላል?
4 እኛም የምንኖረው የኢየሱስ ትንቢት የመጨረሻ ፍጻሜውን በሚያገኝበት ዘመን ላይ ነው። መላው የሰይጣን ሥርዓት የሚጠፋበት “ታላቁ የይሖዋ ቀን ቀርቧል።” (ሶፎ. 1:14 NW) በመሆኑም ከምንጊዜውም ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ፍጻሜ በንቃት መከታተልና ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ማጠናከር ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 5:8) ታዲያ እንዲህ እያደረግን ነው? ክርስቲያናዊ ጉልምስና ያለንበትን ጊዜ በንቃት እንድንከታተል ይረዳናል።
ክርስቲያናዊ ጉልምስና ምንድን ነው?
5, 6. (ሀ) መንፈሳዊ ጉልምስና ምን ነገሮችን ያካትታል? (ለ) ወደ ጉልምስና ለመግፋት የትኞቹን ሁለት ነገሮች ማዳበር ይኖርብናል?
5 ጳውሎስ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ዕብራውያን ክርስቲያኖች ወደ ጉልምስና እንዲገፉ በማበረታታት ብቻ ሳይወሰን መንፈሳዊ ጉልምስና ምን ነገሮችን እንደሚያካትትም ነግሯቸዋል። (ዕብራውያን 5:14ን አንብብ።) “ጎልማሳ ሰዎች” “ወተት” በመጠጣት ብቻ ከመርካት ይልቅ “ጠንካራ ምግብ” ይመገባሉ። በዚህም ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት “መሠረታዊ ነገሮች” ብቻ ሳይሆን የእውነትን “ጥልቅ ነገር” ጭምር ያውቃሉ። (1 ቆሮ. 2:10) ከዚህም በላይ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት አሠልጥነውታል፤ ይህን የሚያደርጉት የሚያውቁትን ነገር በተግባር በማዋል ሲሆን የማስተዋል ችሎታቸውን በዚህ መንገድ ማሠልጠናቸው ደግሞ ትክክልና ስህተት የሆነውን ለመለየት ያስችላቸዋል። እንዲህ ያለው ሥልጠና፣ ውሳኔ የሚጠይቅ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ከሁኔታው ጋር የሚያያዙት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ እንደሆኑና ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚችሉትም እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ይረዳቸዋል።
6 ጳውሎስ “ከእምነት ጎዳና ቀስ በቀስ እየራቅን እንዳንሄድ ለሰማናቸው ነገሮች ከወትሮው የተለየ ትኩረት መስጠታችን አስፈላጊ . . . ነው” ሲል ጽፏል። (ዕብ. 2:1) እኛም ሳይታወቀን ከእምነት ጎዳና ቀስ በቀስ እየራቅን ልንሄድ እንችላለን። መንፈሳዊ እውነቶችን ስናጠና “ከወትሮው የተለየ ትኩረት” በመስጠት እንዲህ ያለውን አደጋ ማስቀረት እንችላለን። እንግዲያው እያንዳንዳችን እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልገናል፦ ‘አሁንም ገና መሠረታዊ ከሆኑ ትምህርቶች አልፌ መሄድ አልቻልኩም? መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን የማደርገው ከልብ ተነሳስቼ ሳይሆን እንዲያው በዘልማድ ነው? እውነተኛ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?’ ወደ ጉልምስና ለመግፋት ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ለማዳበር ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። እነዚህም ከአምላክ ቃል ጋር በሚገባ መተዋወቅና ታዛዥነትን መማር ናቸው።
ከአምላክ ቃል ጋር በሚገባ ተዋወቁ
7. ከአምላክ ቃል ጋር ይበልጥ መተዋወቃችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
7 ጳውሎስ “ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለሆነ ከጽድቅ ቃል ጋር ትውውቅ የለውም” በማለት ጽፏል። (ዕብ. 5:13) ወደ ጉልምስና ለመድረስ ከአምላክ ቃል ማለትም ይሖዋ ለእኛ ከሰጠን መልእክት ጋር በሚገባ መተዋወቅ ይኖርብናል። ይህ መልእክት የሚገኘው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመሆኑ ቅዱሳን መጻሕፍትንም ሆነ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በሚገባ ማጥናት ያስፈልገናል። (ማቴ. 24:45-47) እንዲህ ማድረጋችን የአምላክን አስተሳሰብ ለማወቅ የሚረዳን ሲሆን ይህም የማስተዋል ችሎታችንን ለማሠልጠን ያስችለናል። ኦርኪድ የተባለችን የአንዲት ክርስቲያን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት።a ኦርኪድ እንዲህ ብላለች፦ “ከሚሰጡን ማሳሰቢያዎች ሁሉ በሕይወቴ ላይ ትልቅ ለውጥ ያስከተለው መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን እንድናነብ የሚሰጠን ማሳሰቢያ ነው። ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብቤ ለመጨረስ ሁለት ዓመት ገደማ የፈጀብኝ ቢሆንም ይህን በማድረጌ ፈጣሪዬን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳወቅሁት ሆኖ ተሰምቶኛል። ስለ አምላክ መንገዶች፣ ስለሚወዳቸውና ስለሚጠላቸው ነገሮች እንዲሁም ስለ ታላቅ ኃይሉና ጥልቅ ስለሆነው ጥበቡ ማወቅ ችያለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበቤ በሕይወቴ ውስጥ ያጋጠሙኝን በጣም ከባድ ሁኔታዎች ለመቋቋም አስችሎኛል።”
8. የአምላክ ቃል ያለው ኃይል በሕይወታችን ውስጥ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል?
8 የአምላክን ቃል አዘውትረን ማንበባችን መልእክቱ ያለው ‘ኃይል’ በሕይወታችን ውስጥ እንዲሠራ ያደርጋል። (ዕብራውያን 4:12ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን ውስጣዊ ማንነታችንን የሚቀርጸው ከመሆኑም ሌላ ይሖዋን ይበልጥ የምናስደስት ሰዎች እንድንሆን ይረዳናል። አንተ በግልህ፣ መጽሐፍ ቅዱስን የምታነብበትና ባነበብከው ነገር ላይ የምታሰላስልበት ተጨማሪ ጊዜ መመደብ ያስፈልግህ ይሆን?
9, 10. ከአምላክ ቃል ጋር መተዋወቅ ምን ነገሮችን ይጨምራል? ምሳሌ ስጥ።
9 ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መተዋወቅ ሲባል በውስጡ የያዘውን ሐሳብ ከማወቅ የበለጠ ነገርን ይጨምራል። በጳውሎስ ዘመን የነበሩት በመንፈሳዊ ሁኔታ ሕፃናት የሆኑ ክርስቲያኖች በመንፈስ መሪነት ስለተጻፈው የአምላክ ቃል ምንም አያውቁም ማለት አልነበረም። ሆኖም የሚያውቁትን ነገር በሕይወታቸው ውስጥ በተግባር አላዋሉትም፤ እንዲሁም ቃሉን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስገኝላቸውን ጥቅም አላጣጣሙም። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው መልእክት በሕይወታቸው ውስጥ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ለማድረግ እንዲረዳቸው አልፈቀዱም፤ በዚህም ምክንያት ከቃሉ ጋር መተዋወቅ አልቻሉም።
10 ከአምላክ ቃል ጋር መተዋወቅ ሲባል ቃሉ ምን እንደሚል ማወቅ እና ይህንን እውቀት በተግባር ማዋል ማለት ነው። ካይል የተባለች አንዲት ክርስቲያን ያጋጠማት ሁኔታ ይህንን ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ያሳያል። በካይልና በአንዲት የሥራ ባልደረባዋ መካከል ግጭት ተፈጥሮ ነበር። ካይል የተፈጠረውን ቅራኔ ለመፍታት ምን አደረገች? እንዲህ ብላለች፦ “በዚህ ወቅት ወደ አእምሮዬ የመጣው ጥቅስ ‘ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ’ የሚለው ሮም 12:18 ነበር። በመሆኑም ይህቺን ሴት ከሥራ በኋላ እንድንገናኝ ጠየቅኋት።” ካይልና የሥራ ባልደረባዋ ጥሩ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ሴትየዋ ካይል የወሰደችው እርምጃ በጣም አስደነቃት። ካይል “ምንጊዜም ትክክለኛው አካሄድ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ እንደሆነ ተምሬያለሁ” ብላለች።
ታዛዥነትን ተማሩ
11. በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር መታዘዝ ከባድ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
11 ከቅዱሳን ጽሑፎች ያገኘነውን ትምህርት በተግባር ማዋል በተለይ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ከባድ ሊሆን ይችላል። ለአብነት ያህል፣ ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ካወጣቸው ብዙም ሳይቆይ ሕዝቡ ‘ሙሴን የተጣሉት’ ከመሆኑም ሌላ ‘ይሖዋን ተፈታተኑት።’ ይህን ያደረጉት ለምን ነበር? የሚጠጡት ውኃ በማጣታቸው ነበር። (ዘፀ. 17:1-4) እስራኤላውያን ከአምላክ ጋር ቃል ኪዳን ከገቡ እንዲሁም ‘የይሖዋን ቃሎች ሁሉ’ ለመፈጸም ከተስማሙ ሁለት ወር እንኳ ሳይሞላቸው ጣዖት በማምለክ ሕጉን አፈረሱ። (ዘፀ. 24:3, 12-18፤ 32:1, 2, 7-9) ይህን ያደረጉት ሙሴ፣ መመሪያ ለመቀበል ወደ ኮሬብ ተራራ ወጥቶ ረዘም ላለ ጊዜ በመቆየቱ ፍርሃት አድሮባቸው ይሆን? አማሌቃውያን በድጋሚ ጥቃት ቢሰነዝሩባቸው ቀደም ሲል እጆቹን ወደ ላይ በማንሳት እንዲያሸንፉ የረዳቸው ሙሴ አብሯቸው ባለመሆኑ የሚረዳቸው እንደማይኖር ተሰምቷቸው ይሆን? (ዘፀ. 17:8-16) እንደዚያ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል፤ ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን እስራኤላውያን “ለመታዘዝ ፈቃደኞች አልሆኑም።” (ሥራ 7:39-41) ጳውሎስ፣ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በፈሩበት ወቅት እንዳልታዘዙ ከገለጸ በኋላ ክርስቲያኖች ይህንን ‘ያለመታዘዝ ምሳሌ ተከትለው ላለመውደቅ የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ’ አሳስቧቸዋል።—ዕብ. 4:3, 11
12. ኢየሱስ መታዘዝን የተማረው እንዴት ነው? ይህስ ምን ጥቅም አስገኝቶለታል?
12 ወደ ጉልምስና መግፋት ከፈለግን ይሖዋን ለመታዘዝ የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ መመልከት እንደሚቻለው አብዛኛውን ጊዜ ከደረሰብን መከራ ታዛዥነትን እንማራለን። (ዕብራውያን 5:8, 9ን አንብብ።) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ለአባቱ ታዛዥ ነበር። ይሁንና በምድር ላይ እያለ የአባቱን ፈቃድ ማድረግ አካላዊ ሥቃይ ያስከተለበት ከመሆኑም ሌላ አእምሮውን አስጨንቆት ነበር። ኢየሱስ ከባድ መከራ ቢያጋጥመውም አባቱን መታዘዙ አምላክ ላዘጋጀለት አዲስ ኃላፊነት ማለትም ንጉሥና ሊቀ ካህናት ለመሆን “ፍጹም” እንዲሆን አስችሎታል።
13. ታዛዥነትን እንደተማርን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
13 እኛስ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንኳ ይሖዋን ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል? (1 ጴጥሮስ 1:6, 7ን አንብብ።) ሥነ ምግባርን፣ ሐቀኝነትን፣ አንደበትን በአግባቡ መጠቀምን፣ የግል ጥናትንና መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትንና በስብከቱ ሥራ መካፈልን በተመለከተ የአምላክ ቃል ግልጽ ምክር ይሰጣል። (ኢያሱ 1:8፤ ማቴ. 28:19, 20፤ ኤፌ. 4:25, 28, 29፤ 5:3-5፤ ዕብ. 10:24, 25) ታዲያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜም ጭምር በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ ይሖዋን እንታዘዛለን? ታዛዥ መሆናችን ወደ ጉልምስና እየገፋን እንዳለን ያሳያል።
ክርስቲያናዊ ጉልምስና ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
14. ወደ ጉልምስና መግፋት ጥበቃ የሚሆነው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።
14 አንድ ክርስቲያን ‘የሥነ ምግባር ስሜታቸው የደነዘዘ’ ሰዎች በሞሉበት በዚህ ዓለም ውስጥ ሲኖር ትክክልና ስህተት የሆነውን ለመለየት የሚረዳውን የማስተዋል ችሎታውን በሚገባ ማሠልጠኑ ጥበቃ ይሆንለታል። (ኤፌ. 4:19) ጄምስ የተባለውን ወንድም እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህ ወንድም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አዘውትሮ የሚያነብ ከመሆኑም ሌላ ለእነዚህ ጽሑፎች ከፍተኛ አድናቆት ነበረው። ጄምስ ሴቶች ብቻ በሚሠሩበት ቦታ ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ። እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “አብረውኝ ከሚሠሩት ሴቶች አብዛኞቹ ጥሩ ሥነ ምግባር እንደሌላቸው በግልጽ ይታይ ነበር፤ ከመካከላቸው አንዷ ግን መልካም ሥነ ምግባር ያላት ትመስል የነበረ ከመሆኑም በላይ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት አሳይታ ነበር። ይሁንና በምርት ክፍል ብቻችንን በምንሠራበት ወቅት የጾታ ብልግና እንድንፈጽም የሚጋብዙ ነገሮች ማድረግ ጀመረች። መጀመሪያ ላይ የምትቀልድ መስሎኝ ነበር፤ ሆኖም በቀላሉ ላስቆማት አልቻልኩም። ልክ በዚህ ጊዜ፣ በሥራ ቦታው ተመሳሳይ ፈተና አጋጥሞት ስለነበረ አንድ ወንድም የሚናገር በመጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣ ተሞክሮ ትዝ አለኝ። በመጠበቂያ ግንቡ ላይ የዮሴፍና የጲጥፋራ ሚስት ታሪክ ተጠቅሷል።b እኔም ወዲያውኑ ልጅቷን ከአጠገቤ ስገፈትራት ከክፍሉ ሮጣ ወጣች።” (ዘፍ. 39:7-12) ጄምስ ከዚህ ያለፈ ነገር ባለመፈጠሩና ንጹሕ ሕሊና ይዞ መቀጠል በመቻሉ አመስጋኝ ነው።—1 ጢሞ. 1:5
15. ወደ ጉልምስና መግፋት ምሳሌያዊ ልባችንን የሚያጠናክረው እንዴት ነው?
15 ከዚህም በተጨማሪ ጉልምስና ምሳሌያዊ ልባችንን ስለሚያጠናክረው “በልዩ ልዩና እንግዳ በሆኑ ትምህርቶች [እንዳንወሰድ]” ይረዳናል። (ዕብራውያን 13:9ን አንብብ።) መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ስንጥር አእምሯችን ‘ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች’ ላይ ያተኩራል። (ፊልጵ. 1:9, 10) ይህም ለአምላክና ለእኛ ጥቅም ሲል ላደረጋቸው ዝግጅቶች ያለን አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋል። (ሮም 3:24) ‘በማስተዋል ችሎታው የጎለመሰ’ ክርስቲያን እንዲህ ያለውን የአመስጋኝነት መንፈስ የሚያዳብር ሲሆን ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ይኖረዋል።—1 ቆሮ. 14:20
16. አንዲት እህት ‘ልቧን ለማጽናት’ የረዳት ምንድን ነው?
16 ሉዊዝ የተባለች አንዲት ክርስቲያን ከተጠመቀች በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ያህል በዋነኝነት የሚያሳስባት ሌሎች ስለ እሷ ያላቸው አመለካከት እንደነበረ ትናገራለች። ሉዊዝ እንዲህ ብላለች፦ “መጥፎ ነገር ባልሠራም ይሖዋን የማገልገል ልባዊ ፍላጎት አልነበረኝም። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን ይሖዋን በሙሉ ልቤ እያገለገልኩት እንዳለሁ እንዲሰማኝ ከፈለግሁ አንዳንድ ለውጦች ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። በመሆኑም በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ለውጥ በማድረግ ይሖዋን በሙሉ ልቤ ማምለክ ጀመርኩ።” ሉዊዝ እንዲህ ያለ ጥረት በማድረግ ‘ልቧን አጸናች’፤ ይህም ከባድ የጤና እክል ባጋጠማት ጊዜ ሁኔታውን ለመቋቋም ረድቷታል። (ያዕ. 5:8) ሉዊዝ “ብዙ ትግል የነበረብኝ ቢሆንም ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ ችያለሁ” በማለት ተናግራለች።
‘ከልብ ታዘዙ’
17. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ታዛዥነት በጣም አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?
17 ጳውሎስ “ወደ ጉልምስና እንግፋ” በማለት የሰጠው ምክር በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች ሕይወት አትርፎላቸዋል። ይህን ምክር ሰምተው ተግባራዊ ያደረጉት ክርስቲያኖች ጥልቅ መንፈሳዊ ማስተዋል ስለነበራቸው ‘ወደ ተራሮች መሸሽ’ እንዳለባቸው የሚጠቁመውን ኢየሱስ የሰጣቸውን ምልክት ማስተዋል ችለው ነበር። እነዚህ ክርስቲያኖች “ጥፋት የሚያመጣው ርኩስ ነገር በተቀደሰ ስፍራ [መቆሙን]” ማለትም የሮም ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከብቦ ወደ ከተማዋ ለመግባት እየጣረ መሆኑን ሲያዩ የሚሸሹበት ጊዜ መድረሱን ተገነዘቡ። (ማቴ. 24:15, 16) ክርስቲያኖች ኢየሱስ አስቀድሞ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በመከተል ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት ከተማዋን ለቀው ወጡ፤ ከዚያም የክርስትና ሃይማኖት ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ዩሲቢየስ እንደተናገረው ተራራማ በሆነው በገለዓድ አካባቢ በምትገኝ ፔላ በተባለች ከተማ መኖር ጀመሩ። እንዲህ በማድረጋቸው በታሪክ ዘመናት በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሱት ሁሉ እጅግ አሰቃቂ ከሆነው ጥፋት መትረፍ ችለዋል።
18, 19. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ታዛዥነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኛውን ነጥብ እንመረምራለን?
18 ወደ ጉልምስና በመግፋታችን የምናዳብረው ታዛዥነት፣ ኢየሱስ ተወዳዳሪ የሌለው “ታላቅ መከራ [እንደሚከሰት]” የተናገረው ትንቢት ዋነኛ ፍጻሜውን ሲያገኝ በምናይበት በዛሬው ጊዜም ቢሆን ሕይወታችንን ያድንልናል። (ማቴ. 24:21) “ታማኝና ልባም መጋቢ” ወደፊት ለሚሰጠን አጣዳፊ እርምጃ ለሚያሻው ማንኛውም መመሪያ ታዛዥ እንሆናለን? (ሉቃስ 12:42) በእርግጥም ‘ከልብ መታዘዝን’ መማራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!—ሮም 6:17
19 ወደ ጉልምስና ለመድረስ የማስተዋል ችሎታችንን ማሠልጠን ያስፈልገናል። ለዚህ ደግሞ ከአምላክ ቃል ጋር በሚገባ ለመተዋወቅ እንዲሁም ታዛዥነትን ለመማር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና መድረስ በተለይ ለወጣቶች ተፈታታኝ ነው። የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በተሳካ መንገድ መቋቋም የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
b በጥቅምት 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን “መጥፎ ድርጊትን እምቢ ለማለት የሚያስችል ጥንካሬ ማግኘት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ምን ትምህርት አግኝተሃል?
• መንፈሳዊ ጉልምስና ምንድን ነው? ልንደርስበት የምንችለውስ እንዴት ነው?
• ከአምላክ ቃል ጋር መተዋወቃችን ወደ ጉልምስና ለመድረስ የሚረዳን እንዴት ነው?
• ታዛዥነትን መማር የምንችለው እንዴት ነው?
• ጉልምስና የሚጠቅመን በየትኞቹ መንገዶች ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ፣ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ጎልማሳ እንደሆንን በሚያሳይ መንገድ ለመወጣት ያስችለናል
[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ምክር መከተላቸው ሕይወታቸውን አትርፎላቸዋል