አምላክ እርምጃ በሚወስድበት ወቅት ከጥፋት ትድን ይሆን?
“እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።”—ማቴዎስ 24:22
1, 2. (ሀ) ወደፊት ስለሚገጥመን ነገር ለማወቅ መፈለጋችን ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ትክክለኛ የሆነ የማወቅ ፍላጎት ተንጸባርቆባቸዋል ሊባሉ የሚችሉት ዐበይት ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
ለራስህ ምን ያህል ትጨነቃለህ? በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ከልክ በላይ የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱና ለራሳቸው ብቻ የሚያስቡ ሆነዋል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እኛን ለሚነካን ነገር ተገቢውን ትኩረት መስጠታችን ስሕተት ነው አይልም። (ኤፌሶን 5:33) ይህም ወደፊት ምን እንደሚገጥመን ለማወቅ መፈለግን ይጨምራል። ስለዚህ የወደፊቱ ጊዜ ምን እንደያዘልህ ለማወቅ መፈለግህ ምክንያታዊ ነው። ታዲያ ለማወቅ ትፈልጋለህን?
2 የኢየሱስ ሐዋርያት ወደፊት ስለሚያጋጥማቸው ነገር እንዲህ ያለ የማወቅ ፍላጎት እንደ ነበራቸው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (ማቴዎስ 19:27) ከእነሱ መካከል አራቱ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ከኢየሱስ ጋር በነበሩበት ወቅት ጥያቄ ያቀረቡበት አንዱ ምክንያት ይህ ሳይሆን አይቀርም። “ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው?” ብለው ጠይቀው ነበር። (ማርቆስ 13:4) ኢየሱስ እነሱም ሆኑ እኛ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ያለንን ትክክለኛ ፍላጎት ችላ አላለም። በተደጋጋሚ ጊዜያት ተከታዮቹ በወደፊቱ ሁኔታዎች እንዴት እንደሚነኩና የመጨረሻው ውጤት ምን እንደሚሆን ጎላ አድርጎ ገልጿል።
3. የኢየሱስን መልስ ከጊዜያችን ጋር የምናገናኘው ለምንድን ነው?
3 ኢየሱስ በመልሱ ላይ በጊዜያችን ዋነኛ ተፈጻሚነት የሚኖረውን ትንቢት ተናግሯል። በዚህ መቶ ዘመን ከተፈጸሙት የዓለም ጦርነቶችና ሌሎች ግጭቶች፣ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ከቀጠፉት የምድር ነውጦች፣ በሽታና ሞት ከሚያስከትሉት የምግብ እጥረቶች እንዲሁም በ1918 በብዙ ቦታዎች ተሰራጭቶ ከነበረው የስፓኒሽ እንፍሉዌንዛ አንሥቶ በዘመናችን እስካለው የኤድስ መቅሠፍት ድረስ ከተከሰቱት ወረርሽኝ በሽታዎች ይህን መረዳት እንችላለን። ሆኖም አብዛኛው የኢየሱስ መልስ ሮማውያን በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ ያደረሱትን ጥፋት ጨምሮ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በተከናወኑት ሁኔታዎችም ላይ ፍጻሜውን አግኝቷል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል በምኵራብም ትገረፋላችሁ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ” በማለት አስጠንቅቋቸው ነበር።—ማርቆስ 13:9
ኢየሱስ የተናገረው ትንቢትና ፍጻሜው
4. ኢየሱስ በሰጠው መልስ ውስጥ የተካተቱት አንዳንድ ማስጠንቀቂያዎች ምንድን ናቸው?
4 ኢየሱስ የተነበየው ሌሎች ሰዎች በደቀ መዛሙርቱ ላይ ስለሚያደርሱባቸው ነገር ብቻ አልነበረም። እነሱ ራሳቸው ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ እንደሚኖርባቸውም አስጠንቅቋቸዋል። ለምሳሌ ያህል “የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፣ አንባቢው ያስተውል፣ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ” ብሏቸው ነበር። (ማርቆስ 13:14) በሉቃስ 21:20 ላይ የሚገኘው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ታሪክ “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ” ይላል። ይህ በመጀመሪያው ጊዜ በትክክል የተፈጸመው እንዴት ነበር?
5. በ66 እዘአ በይሁዳ በነበሩት አይሁዳውያን ላይ ምን ደረሰባቸው?
5 ዘ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፔድያ (1982) እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “አይሁዳውያን በሮማውያን አገዛዝ ላይ ያሰሙት ተቃውሞ እየጨመረ ከመሄዱም በላይ ገዢዎቻቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ኃይለኞች፣ ጨካኞችና አጭበርባሪዎች ሆነው ነበር። በ66 ዓ.ም. ግልጽ የሆነ ዓመፅ ፈነዳ። . . . በዘመኑ የነበሩት አይሁዳውያን አክራሪዎች ማሳዳን ከያዙ በኋላ በሜናኼም መሪነት ወደ ኢየሩሳሌም ዘመቱ። በዚያው ጊዜ የአስተዳደር ማዕከል በሆነችው በቂሣርያ ከተማ ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን ከፍተኛ እልቂት ደረሰባቸው፤ ይህ አሠቃቂ ወሬ በመላው አገሪቷ ተሰራጨ። ዓመፁ ከተካሄደበት ከመጀመሪያው ዓመት አንሥቶ እስከ አምስተኛው ዓመት ድረስ አዳዲስ ሳንቲሞች ታትመው ነበር።”
6. ሮማውያን ለአይሁዳውያን ዓመፅ ምን ምላሽ ሰጡ?
6 በሴስትየስ ጋለስ የሚመራው አሥራ ሁለተኛው የሮማውያን ክፍለ ጦር ከሶርያ ተነሥቶ ገሊላና ይሁዳን አወደመ፤ ከዚያም በዋና ከተማዋ ላይ ጥቃት አደረሰ፤ እንዲያውም ‘የቅድስቲቱን ከተማ የኢየሩሳሌምን’ ላይኛውን ክፍል ያዘ። (ነህምያ 11:1፤ ማቴዎስ 4:5፤ 5:35፤ 27:53) ዘ ሮማን ሲይጅ ኦቭ ጀሩሳሌም የተባለው መጽሐፍ የተፈጸመውን ሁኔታ ባጭሩ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሮማውያን አምስት ቀን ሙሉ በመሰላል የኢየሩሳሌምን ግንብ በመውጣት ለማጥቃት ቢሞክሩም በተደጋጋሚ ጊዜያት አይሁዳውያን እየመከቱ እንዲያፈገፍጉ አድርገዋቸው ነበር። በመጨረሻ ተከላካዮቹ የሚደርስባቸውን የፍላጻዎች ውርጅብኝ መቋቋም ስለ ተሳናቸው ውጊያቸውን አቆሙ። የሮም ወታደሮች ራሳቸውን ለመከላከል ተስቱዶ የተባለውን ዘዴ ተጠቅመው ከጭንቅላታቸው በላይ ጋሻዎቻቸውን እርስ በርስ በማገጣጠም ግንቡን ሰርስረው ካፈረሱ በኋላ በሩን በእሳት ለመለኮስ ሞክረው ነበር። ጥቃቱን ይከላከሉ የነበሩት ሰዎች ፍርሃት ዋጣቸው።” በከተማዋ ውስጥ የነበሩት ክርስቲያኖች የክርስቶስን ቃላት ሊያስታውሱና ርኩሰቱ በተቀደሰው ቦታ መቆሙን ሊያስተውሉ ችለው ነበር።a ይሁን እንጂ ከተማው ተከቦ እያለ እነዚህ ክርስቲያኖች ኢየሱስ በሰጣቸው ምክር መሠረት መሸሽ የሚችሉት እንዴት ነው?
7. ሮማውያን በ66 እዘአ ድል ሊያደርጉ ሲቃረቡ ምን አደረጉ?
7 ታሪክ ጸሐፊው ፍላቭየስ ጆሴፈስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሴስትየስ [ጋለስ] የተከበቡትን ሰዎች ተስፋ መቁረጥም ሆነ የሕዝቡን ስሜት ሳያውቅ በድንገት ወታደሮቹ ውጊያቸውን እንዲያቆሙ አዘዘ። ምንም ዓይነት ሽንፈት የደረሰበት ባይሆንም እንኳ ሐሳቡን በመቀየር አላንዳች በቂ ምክንያት ከተማይቱን ለቆ ሄደ።” (ዘ ጁዊሽ ዋር ጥራዝ II, 540 [xix, 7]) ጋለስ ወደ ኋላ ያፈገፈገው ለምንድን ነው? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ወደ ኋላ ማፈግፈጉ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ትእዛዝ በማክበር ወደ ተራራዎች ሸሽተው ራሳቸውን እንዲያድኑ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል።
8. ሮማውያን በኢየሩሳሌም ላይ ያደረጉት ጥቃት ሁለተኛ ክፍል ምን ነበር? በሕይወት የተረፉት ምን ደረሰባቸው?
8 ታዛዥ መሆን የራስን ሕይወት ለማዳን ያስችል ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሮማውያን ዓመፁን ለማስቆም ተንቀሳቀሱ። በጄኔራል ቲቶ የተመራው ጦር ከሚያዝያ እስከ ግንቦት 70 እዘአ ባለው ጊዜ ውስጥ ኢየሩሳሌምን ከበባት። ጆሴፈስ በአይሁዳውያን ላይ ስለ ደረሰው መከራ የጻፈውን ዘገባ ማንበብ እጅግ የሚያሠቅቅ ነው። ከሮማውያን ጋር ሲዋጉ ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች አይሁዳውያን በተቀናቃኝ አይሁዳውያን ቡድኖች ተጨፍጭፈዋል፤ በተጨማሪም የምግብ እጥረት የሰው ሥጋ እንዲበሉ አድርጓቸው ነበር። ሮማውያን ድል ባደረጉበት ወቅት 1,100,000 አይሁዳውያን ሞተዋል።b በሕይወት ከተረፉት 97,000 ሰዎች መካከል አንዳንዶች ወዲያውኑ ተገድለዋል፤ ሌሎች ደግሞ ለባርነት ተወስደዋል። ጆሴፈስ እንዲህ ብሏል፦ “ከአሥራ ሰባት ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው እጃቸው በካቴና ታስሮ በግብፅ ውስጥ ከባድ ሥራ እንዲሠሩ የተላኩ ሲሆን ሌሎች ብዙ ሰዎችን ደግሞ ቲቶ በቲያትር ቤቶች ውስጥ በሰይፍ ወይም በአራዊት እንዲገደሉ ለየጠቅላይ ግዛቱ ገጸ በረከት አድርጎ ሰጥቷቸዋል።” የመጨረሻ ዕጣቸውን ለመወሰን ይህ የመለየት ሥራ በሚካሄድበት ወቅትም 11,000 እስረኞች በረሃብ አልቀዋል።
9. ክርስቲያኖች አይሁዳውያን የደረሰባቸው ዓይነት መከራ ያልደረሰባቸው ለምን ነበር? ሆኖም የትኞቹ ጥያቄዎች ይነሣሉ?
9 ክርስቲያኖች የጌታን ማስጠንቀቂያ በመስማታቸውና የሮም ሠራዊት ተመልሶ ከመምጣቱ በፊት ከከተማዋ ሸሽተው በመውጣታቸው ሊደሰቱ ይችላሉ። በዚህ መንገድ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ላይ “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል” በማለት ከጠራው መከራ ድነዋል። (ማቴዎስ 24:21) ኢየሱስ “እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ” ሲል አክሏል። (ማቴዎስ 24:22) በዚያን ጊዜ ይህ ምን ትርጉም ነበረው? አሁንስ ምን ትርጉም አለው?
10. ቀደም ሲል በማቴዎስ 24:22 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የምናብራራው እንዴት ነበር?
10 ‘የሚድኑት ሥጋ ለባሾች’ በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው መከራ በሕይወት የተረፉትን አይሁዳውያን እንደሚያመለክቱ ቀደም ባሉት ጊዜያት ተገልጾ ነበር። ክርስቲያኖች ሸሽተው አምልጠው ስለ ነበር አምላክ ሮማውያን አፋጣኝ ጥፋት እንዲያመጡ ሊፈቅድላቸው ይችላል። በሌላ አባባል የ“ተመረጡት” ከአደጋ አምልጠው ስለ ነበር አይሁዳውያን ‘ሥጋ ለባሾች’ እንዲድኑ የመከራው ቀን ሊያጥር ይችላል። በሕይወት የተረፉት አይሁዳውያን በጊዜያችን ከሚመጣው ታላቅ መከራ በሕይወት ለሚተርፉት ሰዎች ጥላ ናቸው ተብሎ ይታሰብ ነበር።—ራእይ 7:14
11. በማቴዎስ 24:22 ላይ የተሰጠው ማብራሪያ እንደገና መመርመር ያስፈለገው ለምንድን ነው?
11 ይሁን እንጂ ይህ ማብራሪያ በ70 እዘአ ከተፈጸመው ነገር ጋር የሚስማማ ነውን? ኢየሱስ ሰብዓዊ “ሥጋ” ከመከራው ‘ይድናል’ ብሏል። በሕይወት ከተረፉት 97,000 ሰዎች መካከል በሺህ የሚቆጠሩት በረሃብ ከመሞታቸው ወይም በቲያትር ቤት ውስጥ ከመገደላቸው አንፃር ሲታይ እነዚህ ሰዎች ‘ድነዋል’ ብለህ መናገር ትችላለህን? ጆሴፈስ በቂሣርያ የሚገኝ አንድ ቲያትር ቤትን አስመልክቶ ሲናገር “ከአራዊት ጋር ተፋልመው ወይም እርስ በርሳቸው ታግለው ወይም ከነሕይወታቸው ተቃጥለው የሞቱት ከ2,500 በላይ ይሆናሉ” ብሏል። ምንም እንኳ እነዚህ ሰዎች በከበባው ወቅት ባይሞቱም ‘ድነዋል’ ማለት አይቻልም። በተጨማሪም ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች “ከታላቁ መከራ” በሕይወት ከሚተርፉት ደስተኛ ሰዎች ጋር ተመሳሳይ እንደሆኑ አድርጎ ያስባልን?
ሥጋ ለባሾች የዳኑት እንዴት ነው?
12. አምላክ ትኩረት ያደረገባቸው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ‘የተመረጡ ሰዎች’ እነማን ናቸው?
12 በ70 እዘአ አምላክ ሥጋዊ አይሁዳውያንን የተመረጡ ሕዝቦቹ እንደሆኑ አድርጎ መመልከቱን አቆመ። ኢየሱስ አምላክ ያንን ሕዝብ እንደተወውና ዋና ከተማውን፣ ቤተ መቅደሱንና የአምልኮ ሥርዓቱን ወደ ፍጻሜው እንደሚያመጣው ገልጿል። (ማቴዎስ 23:37-24:2) አምላክ መንፈሳዊ እስራኤልን እንደ አዲስ ብሔር አድርጎ መረጠ። (ሥራ 15:14፤ ሮሜ 2:28, 29፤ ገላትያ 6:16) ይህ ብሔር ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡና በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ወንዶችንና ሴቶችን ያቀፈ ነው። (ማቴዎስ 22:14፤ ዮሐንስ 15:19፤ ሥራ 10:1, 2, 34, 35, 44, 45) ሴስትየስ ጋለስ ጥቃቱን ከማድረሱ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጴጥሮስ ‘በእግዚአብሔር አብ አስቀድሞ ለተወሰኑትና ለተመረጡት በመንፈስ ቅዱስም ለተቀደሱት’ ጽፏል። እነዚህ በመንፈስ የተቀቡ ሰዎች “የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ” ነበሩ። (1 ጴጥሮስ 1:1, 2 የ1980 ትርጉም፤ 2:9፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) አምላክ እነዚህን የተመረጡ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር እንዲገዙ ወደ ሰማይ ይወስዳቸዋል።—ቆላስይስ 1:1, 2፤ 3:12፤ ቲቶ 1:1፤ ራእይ 17:14
13. በማቴዎስ 24:22 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ምን ትርጉም ሊኖራቸው ይችላል?
13 ኢየሱስ የመከራው ቀናት “ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ” ስላለ የተመረጡትን ሰዎች ማንነት ማወቅ ጠቃሚ ነው። “ስለ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ለእነሱ ሲባል” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። (ማርቆስ 2:27፤ ዮሐንስ 12:30፤ 1 ቆሮንቶስ 8:11፤ 9:10, 23፤ 11:9፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:10፤ ራእይ 2:3) ስለዚህ ኢየሱስ ‘እነዚህ ቀኖች ካላጠሩ በስተቀር ሥጋ የለበሰ ሁሉ ሊድን አይችልም፤ ሆኖም እነዚያ ቀኖች ለተመረጡት ሰዎች ሲባል ያጥራሉ’ ማለቱ ሊሆን ይችላል።c (ማቴዎስ 24:22) በኢየሩሳሌም ውስጥ ማምለጫ አጥተው የነበሩትን የተመረጡ ክርስቲያኖች የጠቀመ ወይም ‘ለእነሱ ሲባል’ የተፈጸመ ነገር ነበርን?
14. በ66 እዘአ የሮም ሠራዊት ባልተጠበቀ ሁኔታ ከኢየሩሳሌም ወደ ኋላ ሲያፈገፍግ ‘ሥጋ ለባሾች’ የዳኑት እንዴት ነው?
14 በ66 እዘአ ሮማውያን አገሪቱ ውስጥ ዘልቀው በመግባት የላይኛውን የኢየሩሳሌም ክፍል ከያዙ በኋላ ግንቡን መሰርሰር እንደ ጀመሩ አስታውስ። ጆሴፈስ “ጋለስ ከበባውን ለጥቂት ጊዜ ቢቀጥል ኖሮ ከተማዋን በአንዴ በቁጥጥሩ ሥር ያውል ነበር” የሚል አስተያየት ሰንዝሯል። ‘ኃያሉ የሮማውያን ሠራዊት በድንገት የጦር ዘመቻውን አቁሞ “ያለ ምንም በቂ ምክንያት” ወደ ኋላ ሊያፈገፍግ የቻለው ለምንድን ነው?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። ሩፐርት ፈርኖ የተባሉ የወታደራዊ ታሪክ ተንታኝ “ማንኛውም ታሪክ ጸሐፊ ጋለስ ያልተለመደና አደገኛ ውሳኔ እንዲያደርግ ያነሣሣው ምን እንደሆነ በቂ ምክንያት ሊያቀርብ አልቻለም” የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን መከራው እንዲያጥር ተደርጓል። ሮማውያን አፈግፍገው ወደኋላ ሲመለሱ አይሁዳውያን ከበስተጀርባቸው ጥቃት እየሰነዘሩባቸው ነበር። ማምለጫ አጥተው የነበሩት ‘የተመረጡት’ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን አደረጉ? ከበባው ማቆሙ በመከራው ወቅት ተደቅኖባቸው ከነበረው የእልቂት አደጋ እንዲድኑ አስችሏቸዋል። ስለዚህ በማቴዎስ 24:22 ላይ የተገለጹት ‘ሥጋ ለባሾች’ በ66 እዘአ የደረሰው መከራ በማጠሩ ምክንያት ተጠቃሚ የሆኑት እነዚህ ክርስቲያኖች ናቸው።
የወደፊቱ ጊዜህ ምን ይዞልሃል?
15. በዘመናችን ማቴዎስ ምዕራፍ 24 የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የምትለው ለምንድን ነው?
15 አንድ ሰው ‘በኢየሱስ ቃላት ላይ ለተሰጠው ለዚህ ግልጽ የሆነ ማብራሪያ ልዩ ትኩረት መስጠት ያለብኝ ለምንድን ነው?’ ብሎ ሊጠይቅ ይችል ይሆናል። የኢየሱስ ትንቢት በ70 እዘአ እና ከዚያ በፊት በነበረው ጊዜ ካገኘው ፍጻሜ በተጨማሪ ሌላ ከፍተኛ ተፈጻሚነት እንዳለው ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት ስላለ ነው።d (ከማቴዎስ 24:7፤ ሉቃስ 21:10, 11፤ ራእይ 6:2-8 ጋር አወዳድር።) በጊዜያችን በመታየት ላይ የሚገኘው ከፍተኛ ፍጻሜ ከፊታችን መጠነ ሰፊ የሆነ “ታላቅ መከራ” ልንጠብቅ እንደምንችል የሚያረጋግጥ መሆኑን የይሖዋ ምሥክሮች ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሲሰብኩ ቆይተዋል። በዚህ መከራ ወቅት በማቴዎስ 24:22 ላይ የሚገኙት ትንቢታዊ ቃላት ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት እንዴት ነው?
16. ራእይ መጪውን ታላቅ መከራ በተመለከተ የሚሰጠው ማበረታቻ ምንድን ነው?
16 በኢየሩሳሌም ላይ መከራው ከደረሰ ከሁለት አሥርተ ዓመታት ገደማ በኋላ ሐዋርያው ዮሐንስ የራእይ መጽሐፍን ጻፈ። ራእዩ ወደፊት ታላቅ መከራ እንደሚመጣ ያረጋግጣል። በግለሰብ ደረጃ በእኛ ላይ የሚደርስብን ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ ስለምንፈልግ ራእይ ከመጪው ታላቅ መከራ የሚተርፉ ሥጋ ለባሽ ሰዎች እንደሚኖሩ ትንቢታዊ በሆነ መንገድ የሚያረጋግጥ መሆኑ እፎይታ ሊሰጠን ይችላል። ዮሐንስ “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” እንደሚኖሩ አስቀድሞ ተናግሯል። እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? ከሰማይ የመጣ አንድ ድምፅ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው” የሚል መልስ ሰጥቷል። (ራእይ 7:9, 14) አዎን፣ እነዚህ ሰዎች በሕይወት ይተርፋሉ! በተጨማሪም ራእይ በመጪው ታላቅ መከራ ወቅት ነገሮች ምን ዓይነት መልክ እንደሚኖራቸውና ማቴዎስ 24:22 እንዴት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ጠለቅ ያለ ማስተዋል ይሰጠናል።
17. የታላቁ መከራ የመክፈቻ ክፍል ምንን ይጨምራል?
17 የዚህ መከራ የመጀመሪያው ክፍል “ታላቂቱ ባቢሎን” ተብላ በምትጠራዋ ምሳሌያዊ ጋለሞታ ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይሆናል። (ራእይ 14:8፤ 17:1, 2) ታላቂቱ ባቢሎን ይበልጥ ተነቃፊ የሆነችውን ሕዝበ ክርስትና ያቀፈች ዓለም አቀፍ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ናት። በራእይ 17:16-18 ላይ በሚገኙት ቃላት መሠረት አምላክ በፖለቲካ ኃይሎች ልብ ውስጥ ይህችን ምሳሌያዊ ጋለሞታ የማጥቃት ሐሳብ ያስገባል።e አምላክ የቀባቸው ‘ምርጦች’ እና ጓደኞቻቸው የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ይህ ጥቃት ሲሰነዘር ምን ሊሰማቸው እንደሚችል አስብ። በሃይማኖት ላይ የሚሰነዘረው ይህ ከፍተኛ ጥፋት የሚያስከትል ጥቃት እየቀጠለ ሲሄድ የይሖዋ ሕዝቦችን ጨምሮ ሁሉንም ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ጠራርጎ የሚያጠፋ ሊመስል ይችላል።
18. በታላቁ መከራ የመክፈቻ ክፍል ‘ሥጋ የለበሰ’ ሁሉ መዳን የሚችል የማይመስለው ለምንድን ነው?
18 በማቴዎስ 24:22 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት በከፍተኛ ደረጃ የሚፈጸሙት በዚህ ጊዜ ነው። በኢየሩሳሌም ውስጥ የነበሩት ምርጦች ሕይወት አደጋ ላይ የወደቀ መስሎ እንደነበረ ሁሉ በሃይማኖት ላይ ጥቃት በሚሰነዘርበት ወቅት ጥቃቱ ‘ሥጋ የለበሱትን’ የአምላክ ሕዝቦችን በሙሉ ጠራርጎ የሚያጠፋና የይሖዋ አገልጋዮች የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ሊመስል ይችላል። ሆኖም በ66 እዘአ የሆነውን ነገር አንርሳ። ሮማውያን ያደረሱት መከራ በማጠሩ የተመረጡት የአምላክ ቅቡዓን ማምለጥና ሕይወታቸውን ማዳን የሚችሉበት በቂ ጊዜ ሊያገኙ ችለዋል። በመሆኑም በሃይማኖት ላይ የሚሰነዘረው ከፍተኛ ጥፋት የሚያስከትል ጥቃት የእውነተኛ አምላኪዎችን ዓለም አቀፍ ጉባኤ እንዲያጠፋ እንደማይፈቀድለት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። “በአንድ ቀን” የሆነ ያህል ቶሎ ያልፋል። የአምላክ ሕዝቦች ‘ለመዳን’ እንዲችሉ ጥቃቱ ዓላማውን ሙሉ በሙሉ ሳያከናውን በሆነ መንገድ እንዲያጥር ይደረጋል።—ራእይ 18:8
19. (ሀ) ከታላቁ መከራ የመጀመሪያ ክፍል በኋላ ምን ነገር ግልጽ ይሆናል? (ለ) ይህ ወደ ምን ይመራል?
19 ከዚህ በኋላ የሰይጣን ዲያብሎስ ምድራዊ ድርጅት ሌሎች ክፍሎች ከአሮጊቷ ሃይማኖታዊ ጋለሞታ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በመቋረጡ እያለቀሱ ለተወሰነ ጊዜ ይቆያሉ። (ራእይ 18:9-19) ከዚያም አንድ ወቅት ላይ የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች ‘ቅጥር በሌላቸው ከተሞች ያለ ስጋት እንደተቀመጡ’ በማስተዋል በቀላሉ ሊያጠቋቸው እንደሚችሉ ሆኖ ይሰማቸዋል። ጥቃት ሰንዛሪዎቹ ያልጠበቁት ሁኔታ ይገጥማቸዋል! አምላክ በአገልጋዮቹ ላይ ለሚደርሰው ጥቃትም ሆነ ዛቻ ምላሽ በመስጠት በታላቁ መከራ የመጨረሻ ክፍል ወቅት በጠላቶቹ ላይ ለመፍረድ ይነሣል።—ሕዝቅኤል 38:10-12, 14, 18-23
20. የታላቁ መከራ ሁለተኛ ክፍል የአምላክ ሕዝቦችን አደጋ ላይ የማይጥላቸው ለምንድን ነው?
20 ይህ የታላቁ መከራ ሁለተኛ ክፍል ሮማውያን በ70 እዘአ ለሁለተኛ ጊዜ ባደረሱት ጥቃት ወቅት በኢየሩሳሌምና ነዋሪዎቿ ላይ ከደረሰው ነገር ጋር ይመሳሰላል። ይህም “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ” ይሆናል። (ማቴዎስ 24:21) ሆኖም አምላክ የመረጣቸው ሰዎችና ተባባሪዎቻቸው ለሕይወታቸው በሚያሰጋ አደገኛ ክልል ውስጥ እንደማይሆኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ወደ አንድ መልከዓ ምድራዊ ቦታ መሸሽ አያስፈልጋቸውም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች በዮርዳኖስ ማዶ እንደሚገኘው እንደ ፔላ ወዳሉ ተራራማ ቦታዎች ሊሸሹ ይችሉ ነበር። ወደፊት ግን ታማኝ የአምላክ ምሥክሮች በመላው ዓለም ስለሚኖሩ ደኅንነትና ጥበቃ የሚያገኙት ወደ አንድ መልከዓ ምድራዊ ቦታ በመሸሽ አይሆንም።
21. በመጨረሻው ጦርነት ላይ የሚዋጉት እነማን ናቸው? ውጤቱስ ምን ይሆናል?
21 ጥፋቱ የሚመጣው በሮም ሠራዊት ወይም በሌላ ሰብዓዊ ወኪል አማካኝነት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የራእይ መጽሐፍ ፍርድ አስፈጻሚ ኃይሎቹ ከሰማይ እንደሚመጡ ይገልጻል። አዎን፣ የታላቁ መከራ የመጨረሻ ክፍል የሚከናወነው በማንኛውም ሰብዓዊ ሠራዊት ሳይሆን “የእግዚአብሔር ቃል” በሆነው በንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራው ‘የሰማይ ሠራዊት’ አማካኝነት ነው። ከእነዚህም መካከል ከሞት የተነሡ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይገኙበታል። “የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ” ሮማውያን በ70 እዘአ ካደረጉት በላቀ ሁኔታ ፍርዱን ሙሉ በሙሉ ያስፈጽማል። የአምላክ ተቃዋሚ የሆኑ ነገሥታትን፣ የጦር አዛዦችን፣ ጌታዎችንና ባሪያዎችን እንዲሁም ታናናሾችንና ታላላቆችን በሙሉ ያጠፋል። የሰይጣን ዓለም ሰብዓዊ ድርጅቶች ሳይቀሩ ከሕልውና ውጪ ይሆናሉ።—ራእይ 2:26, 27፤ 17:14፤ 19:11-21፤ 1 ዮሐንስ 5:19
22. ‘ሥጋ ለባሾች’ የሚድኑት በምን ሌላ መንገድ ነው?
22 ‘ሥጋ ለባሽ’ የሆኑት ቅቡዓን ቀሪዎችም ሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” በመጀመሪያው የመከራው ክፍል ታላቂቱ ባቢሎን በአንድ ጊዜ ስትደመሰስ ከጥፋቱ ሙሉ በሙሉ የሚድኑ መሆኑን አስታውስ። በተመሳሳይም በመከራው የመጨረሻ ክፍል ወደ ይሖዋ የሸሸ ‘ሥጋ ለባሽ’ ሁሉ ይድናል። ይህ በ70 እዘአ አምፀው በነበሩት አይሁዳውያን ላይ ከደረሰው ጥፋት ምንኛ የተለየ ነው!
23. ከመከራው በሕይወት የተረፉት ‘ሥጋ ለባሾች’ ምን ነገር በጉጉት ሊጠባበቁ ይችላሉ?
23 አንተና የምትወዳቸው ሰዎች ልታገኙ የምትችሏቸውን ነገሮች በማሰብ በራእይ 7:16, 17 ላይ የተሰጠውን የሚከተለውን ተስፋ አስተውል፦ “ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፣ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፣ ፀሐይም ትኵሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም፤ በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፣ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።” በእርግጥም አስደሳችና ዘላቂ በሆነ መንገድ ‘መዳን’ ማለት ይኼ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ሰኔ 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 14-19 ተመልከት።
b ጆሴፈስ እንዲህ ብሏል፦ “ቲቶ ወደ ውስጥ ሲገባ በከተማዋ ጥንካሬ ተደንቆ ነበር። . . . ‘አምላክ ከጎናችን ነበር፤ አይሁዳውያንን ከእነዚህ ጠንካራ ምሽጎች አውጥቶ የጣላቸው አምላክ ነው፤ አለዚያማ የሰው እጆች ወይም መሣሪያዎች በእነዚህ ትላልቅ ግንቦች ላይ ምን ሊያደርጉ ይችሉ ነበር?’ በማለት ጮክ ብሎ ተናግሯል።”
c የሼምቶብ ጽሑፍ በማቴዎስ 24:22 ላይ “ለ . . . ሲባል፣ ስለ . . .፣ . . . እንዲሆን” የሚል ትርጉም ባለው አቩር በሚለው የዕብራይስጥ ቃል መጠቀሙ ትኩረት የሚስብ ነው።—በገጽ 13 ላይ የሚገኘውን ከዚህ በፊት ያለውን ርዕስ ተመልከት።
d የካቲት 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 11 እና 12ን እንዲሁም በማቴዎስ ምዕራፍ 24፣ በማርቆስ ምዕራፍ 13 እና በሉቃስ ምዕራፍ 21 ላይ የሚገኘውን የኢየሱስ ትንቢታዊ መልስ ትይዩ በሆኑ አምዶች የሚያስቀምጠውን በገጽ 14 እና 15 ላይ የሚገኘውን ሠንጠረዥ ተመልከት።
e በ1988 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኀበር የታተመውን ራእይ—ታላቁ መደምደምያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 235-58 ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የሮማውያን ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ ያደረሰው ጥቃት ምን ሁለት ክፍሎች ነበሩት?
◻ በ70 እዘአ ከደረሰው መከራ በሕይወት የተረፉት 97,000 አይሁዳውያን በማቴዎስ 24:22 ላይ የተገለጹት ‘ሥጋ ለባሾች’ ሊሆኑ የማይችሉት ለምንድን ነው?
◻ የኢየሩሳሌም የመከራ ቀናት እንዲያጥሩ የተደረገው እንዴት ነበር? በዚህ መንገድ ‘ሥጋ ለባሾች’ የዳኑት እንዴት ነበር?
◻ በመጪው ታላቅ መከራ ቀኖቹ የሚያጥሩትና ‘ሥጋ ለባሾች’ የሚድኑት እንዴት ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከዓመፁ በኋላ የተቀረጸ የአይሁዳውያን ሳንቲም። የዕብራይስጡ ፊደላት “ሁለተኛ ዓመት” ይላሉ፤ ይህም የራስ ገዝ መንግሥት የመሠረቱበትን ሁለተኛ ዓመት ማለትም 67 እዘአን የሚያመለክት ነው
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ71 እዘአ የተቀረጸ የሮማውያን ሳንቲም። በስተግራ አንድ የታጠቀ ሮማዊ፣ በስተቀኝ ደግሞ አንዲት አይሁዳዊት ስታለቅስ። ዩዲአ ካፕታ የሚሉት ቃላት “የተማረከችው ይሁዳ” የሚል ትርጉም አላቸው
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.