“ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው?”
“የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?”—ማቴ. 24:3
1. እንደ ሐዋርያቱ ሁሉ እኛም ስለ ምን ነገር ለማወቅ እንጓጓለን?
የኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ሊጠናቀቅ ተቃርቧል፤ ደቀ መዛሙርቱም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ በጣም ጓጉተዋል። በመሆኑም ከመሞቱ ጥቂት ቀናት በፊት አራቱ ሐዋርያት እንዲህ በማለት ጠየቁት፦ “እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?” (ማቴ. 24:3፤ ማር. 13:3) ኢየሱስ የዚህን ጥያቄ መልስ የሰጠው በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ብዙ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ትንቢት በመናገር ነው። በዚህ ትንቢት ላይ ኢየሱስ ትኩረት የሚስቡ በርካታ ክንውኖች እንደሚፈጸሙ ገልጿል። በዛሬው ጊዜ የምንኖር ክርስቲያኖችም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ስለምንጓጓ ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ለእኛም ትልቅ ትርጉም አለው።
2. (ሀ) ባለፉት በርካታ ዓመታት ይበልጥ ግልጽ የሆነ መረዳት ለማግኘት ጥረት ስናደርግ የነበረው ስለ የትኛው ጉዳይ ነው? (ለ) የትኞቹን ሦስት ጥያቄዎች እንመረምራለን?
2 ባለፉት በርካታ ዓመታት የይሖዋ አገልጋዮች ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት የተናገረውን ትንቢት በጸሎት ታግዘው ሲያጠኑ ቆይተዋል። ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት የሚፈጸምበትን ጊዜ በተመለከተ ይበልጥ ግልጽ የሆነ መረዳት ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት አስመልክቶ ያገኘነው መረዳት ይበልጥ ግልጽ እየሆነ የሄደው እንዴት እንደሆነ ለማየት እስቲ ከጊዜ ጋር የተያያዙትን የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች እንመርምር፦ ‘ታላቁ መከራ’ የሚጀምረው መቼ ነው? ኢየሱስ ‘በበጎቹ’ እና ‘በፍየሎቹ’ ላይ የሚፈርደው መቼ ነው? ኢየሱስ ‘የሚመጣው’ መቼ ነው?—ማቴ. 24:21፤ 25:31-33
ታላቁ መከራ የሚጀምረው መቼ ነው?
3. ከዚህ በፊት ስለ ታላቁ መከራ የነበረን መረዳት ምንድን ነው?
3 ታላቁ መከራ የጀመረው በ1914 አንደኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ እንደሆነ አድርገን ለበርካታ ዓመታት እናስብ ነበር፤ እንዲሁም ቅቡዓን ቀሪዎቹ ምሥራቹን ለብሔራት ሁሉ እንዲሰብኩ ሲል ይሖዋ ‘ቀኖቹን እንዲያጥሩ’ ያደረገው በ1918 ጦርነቱ ሲያበቃ እንደሆነ እናምን ነበር። (ማቴ. 24:21, 22) የስብከቱ ሥራ ሲጠናቀቅ የሰይጣን አገዛዝ እንደሚጠፋም ይታሰብ ነበር። በመሆኑም ታላቁ መከራ ሦስት ምዕራፎች እንዳሉት ይታመን ነበር፤ እነሱም፦ መከራው የሚጀምርበት (ከ1914 እስከ 1918)፣ የሚቋረጥበት (ከ1918 ጀምሮ) እና በአርማጌዶን የሚደመደምበት ጊዜ ናቸው።
4. ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት የተናገረውን ትንቢት ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ እንድንረዳ ያስቻለን የትኛውን ጉዳይ ማስተዋላችን ነው?
4 ኢየሱስ በተናገረው ትንቢት ላይ ጥልቀት ያለው ምርምር ማድረጋችን ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት ከሚናገረው ትንቢት ውስጥ የተወሰነው ክፍል ሁለት ፍጻሜዎች እንዳሉት ለመረዳት አስችሎናል። (ማቴ. 24:4-22) ይህ የትንቢቱ ክፍል የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. በይሁዳ ሲሆን ሁለተኛ ፍጻሜውን የሚያገኘው ደግሞ በዘመናችን በዓለም ዙሪያ ነው። ይህን ማስተዋላችን፣ ሌሎች በርካታ ነገሮች ግልጽ እንዲሆኑልን አድርጓል።a
5. (ሀ) በ1914 የጀመረው የትኛው አስቸጋሪ ወቅት ነው? (ለ) ይህ አስጨናቂ ጊዜ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ከነበረው ከየትኛው ወቅት ጋር ይመሳሰላል?
5 ከዚህም በተጨማሪ ታላቁ መከራ በ1914 እንዳልጀመረ ማስተዋል ቻልን። እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረስነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መረዳት እንደሚቻለው ታላቁ መከራ የሚጀምረው በብሔራት መካከል በሚደረግ ጦርነት ሳይሆን በሐሰት ሃይማኖት ላይ በሚፈጸም ጥቃት ነው። በመሆኑም ከ1914 አንስቶ የተፈጸሙት ክንውኖች የታላቁ መከራ መጀመሪያ ሳይሆኑ “የምጥ ጣር መጀመሪያ” ናቸው። (ማቴ. 24:8) ‘በምጥ ጣር’ የተመሰሉት እነዚህ ክንውኖች ከ33 ዓ.ም. እስከ 66 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ከተፈጸሙት ክንውኖች ጋር ይመሳሰላሉ።
6. ታላቁ መከራ መጀመሩን የሚጠቁመው ክንውን የትኛው ነው?
6 ታዲያ ታላቁ መከራ መጀመሩን የሚጠቁመው ክንውን የትኛው ነው? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በነቢዩ ዳንኤል በተነገረው መሠረት ጥፋት የሚያመጣው ርኩስ ነገር በተቀደሰ ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል፤ በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ።” (ማቴ. 24:15, 16) “በተቀደሰ ስፍራ ቆሞ” የሚለው የትንቢቱ ክፍል የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው በ66 ዓ.ም. የሮም ሠራዊት (“ጥፋት የሚያመጣው ርኩስ ነገር”) በኢየሩሳሌምና በቤተ መቅደሷ (በአይሁዶች ዘንድ እንደ ቅዱስ ነገር ተደርጎ በሚቆጠረው ቦታ) ላይ ጥቃት ሲሰነዝር ነው። ይኸው የትንቢቱ ክፍል ታላቅ ፍጻሜውን የሚያገኘው ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (የዘመናችን “ጥፋት የሚያመጣው ርኩስ ነገር”) በሕዝበ ክርስትና (ክርስቲያን ነን በሚሉት ዘንድ እንደ ቅዱስ ነገር ተደርጋ በምትቆጠረው) እና በተቀረው የታላቂቷ ባቢሎን ክፍል ላይ ጥቃት ሲሰነዝር ነው። ይህ ጥቃት በራእይ 17:16-18 ላይም ተጠቅሷል። ይህ ክንውን የታላቁ መከራ መጀመሪያ ይሆናል።
7. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ‘ሥጋ የዳነው’ እንዴት ነው? (ለ) ወደፊት ምን ነገር እንደሚከናወን ልንጠብቅ እንችላለን?
7 በተጨማሪም ኢየሱስ ‘ቀኖቹ እንደሚያጥሩ’ ትንቢት ተናግሯል። ይህ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው በ66 ዓ.ም. የሮም ሠራዊት ጥቃቱን ‘ባሳጠረበት’ ጊዜ ነው። በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ሥጋቸውን ማለትም ሕይወታቸውን ለማዳን’ ሸሽተዋል። (ማቴዎስ 24:22ን አንብብ፤ ሚል. 3:17) ታዲያ በመጪው ታላቅ መከራ ወቅት ምን ነገር እንደሚከናወን እንጠብቃለን? ይሖዋ፣ እውነተኛው ሃይማኖት ከሐሰተኞቹ ጋር እንዳይጠፋ ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሐሰት ሃይማኖት ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት ‘ያሳጥረዋል።’ ይህ ደግሞ የአምላክ ሕዝቦች እንደማይጠፉ ዋስትና ይሰጣል።
8. (ሀ) የታላቁ መከራ የመጀመሪያ ምዕራፍ ካለፈ በኋላ ምን ነገሮች ይከናወናሉ? (ለ) የ144,000ዎቹ የመጨረሻ አባላት ወደ ሰማይ በመሄድ ሽልማታቸውን የሚቀበሉት መቼ ሊሆን ይችላል? (ተጨማሪ መረጃውን ተመልከት።)
8 ታዲያ የታላቁ መከራ የመጀመሪያ ምዕራፍ ካለፈ በኋላ ምን ነገሮች ይከናወናሉ? ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ እንደሚጠቁመው ከታላቁ መከራ የመጀመሪያ ምዕራፍ አንስቶ አርማጌዶን እስኪጀምር ድረስ የተወሰነ ጊዜ ያልፋል። በዚያ ጊዜ ውስጥ ምን ነገሮች ይከናወናሉ? የዚህ ጥያቄ መልስ በሕዝቅኤል 38:14-16 እና በማቴዎስ 24:29-31 (ጥቅሱን አንብብ።) ላይ ተመዝግቦ ይገኛል።b ከዚያ በኋላ የታላቁ መከራ መደምደሚያ የሆነው አርማጌዶን ሲጀምር የማየት አጋጣሚ እናገኛለን፤ ከዚህ ጋር የሚመሳሰለው ክንውን በ70 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ጥፋት ነው። (ሚል. 4:1) ታላቁ መከራ “ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ” መከራ የሚሆነው በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ነው። (ማቴ. 24:21) ከአርማጌዶን በኋላ የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ይጀምራል።
9. ኢየሱስ ስለ ታላቁ መከራ የተናገረው ትንቢት በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል?
9 ስለ ታላቁ መከራ የሚናገረው ይህ ትንቢት እምነታችንን ያጠናክርልናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የይሖዋ ሕዝቦች ምንም ዓይነት መከራ ቢያጋጥማቸው በቡድን ደረጃ ከታላቁ መከራ እንደሚተርፉ ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ራእይ 7:9, 14) ከሁሉ በላይ ደስታ የሚሰጠን ግን ይሖዋ በአርማጌዶን አማካኝነት፣ ሉዓላዊነቱን የሚጠቀምበት መንገድ ትክክል መሆኑ እንዲረጋገጥ ብሎም ስሙ እንዲቀደስ የሚያደርግ መሆኑን ማወቃችን ነው።—መዝ. 83:18፤ ሕዝ. 38:23
ኢየሱስ በበጎቹና በፍየሎቹ ላይ የሚፈርደው መቼ ነው?
10. ሰዎችን በግ ወይም ፍየል ብሎ የመፍረዱ ሂደት የሚከናወንበትን ጊዜ በተመለከተ ቀደም ሲል የነበረን መረዳት ምንድን ነው?
10 እስቲ አሁን ደግሞ ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ሌላኛው ክፍል ማለትም ስለ በጎችና ፍየሎች የሚናገረው ምሳሌ መቼ እንደሚፈጸም እንመልከት። (ማቴ. 25:31-46) ቀደም ሲል በነበረን መረዳት መሠረት ሰዎችን በግ ወይም ፍየል ብሎ የመፍረዱ ሂደት የሚከናወነው ከ1914 ጀምሮ ባሉት የመጨረሻ ቀናት ውስጥ እንደሆነ እናስብ ነበር። የመንግሥቱን መልእክት ለመቀበል አሻፈረኝ ያሉና ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት የሞቱ ሰዎች ፍየል እንደሆኑ ማለትም የትንሣኤ ተስፋ እንደሌላቸው ተደርጎ ይታመን ነበር።
11. ሰዎችን በግ ወይም ፍየል ብሎ የመፍረዱ ሥራ በ1914 ሊጀምር አይችልም የምንለው ለምንድን ነው?
11 ማቴዎስ 25:31ን በድጋሚ በማጤን የተገኘው ግንዛቤ በ1995 መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቶ ነበር፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ በክብራማ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል።” መጽሔቱ ኢየሱስ በ1914 የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ቢሾምም ‘በሕዝቦች ሁሉ’ ላይ ለመፍረድ ‘በክብራማ ዙፋኑ ላይ እንዳልተቀመጠ’ ገልጿል። (ማቴ. 25:32፤ ከዳንኤል 7:13 ጋር አወዳድር።) ይሁንና ስለ በጎችና ፍየሎች በሚናገረው ምሳሌ ላይ ኢየሱስ በዋነኝነት የተገለጸው ፈራጅ ተደርጎ ነው። (ማቴዎስ 25:31-34, 41, 46ን አንብብ።) ኢየሱስ በ1914 በሕዝቦች ሁሉ ላይ መፍረድ ገና ስላልጀመረ ሰዎችን በግ ወይም ፍየል ብሎ የመፍረዱ ሥራ በዚያ ዓመት ሊጀምር አይችልም።c ታዲያ ኢየሱስ መፍረድ የሚጀምረው መቼ ነው?
12. (ሀ) ኢየሱስ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝቦች ላይ ፈራጅ የሚሆነው መቼ ነው? (ለ) በማቴዎስ 24:30, 31 እና በማቴዎስ 25:31-33, 46 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት ክንውኖች የትኞቹ ናቸው? (ተጨማሪ መረጃውንም ተመልከት።)
12 ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት የሚናገረው ትንቢት፣ ኢየሱስ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝቦች ላይ ፈራጅ የሚሆነው የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ እንደሆነ ያስገነዝበናል። አንቀጽ 8 ላይ እንደተገለጸው በዚያ ወቅት የሚከናወኑት አንዳንድ ነገሮች በማቴዎስ 24:30, 31 ላይ ተመዝግበው ይገኛሉ። እነዚህን ቁጥሮች በደንብ ስትመረምራቸው ኢየሱስ ስለ በጎችና ፍየሎች በተናገረው ምሳሌ ላይ ከጠቀሳቸው ክንውኖች ጋር የሚመሳሰሉ ክንውኖች በዚህ ጥቅስ ላይ እንደሚገኙ ታስተውላለህ። ለምሳሌ ያህል፣ የሰው ልጅ ከመላእክት ጋር በክብር ይመጣል፤ የምድር ወገኖችና ሕዝቦች ሁሉ ይሰበሰባሉ፤ እንዲሁም በግ እንደሆኑ የሚፈረድላቸው ከፊታቸው ‘የዘላለም ሕይወት’ ስለተዘረጋላቸው ‘ራሳቸውን ቀና ያደርጋሉ።’d ፍየል እንደሆኑ የሚፈረድባቸው ደግሞ ‘የዘላለም ጥፋት’ እንደሚጠብቃቸው ስለሚገነዘቡ “እያለቀሱ ደረታቸውን ይደቃሉ።”—ማቴ. 25:31-33, 46
13. (ሀ) ኢየሱስ በግ ወይም ፍየል በማለት ሰዎች ላይ የሚፈርደው መቼ ነው? (ለ) ስለ በጎችና ስለ ፍየሎች ያገኘነው ይህ መረዳት ለአገልግሎት ያለንን አመለካከት የሚነካው እንዴት ነው?
13 ታዲያ ምን ብለን መደምደም እንችላለን? ኢየሱስ በሕዝቦች ሁሉ ላይ በግ ወይም ፍየል በማለት የሚፈርደው በታላቁ መከራ ወቅት ሲመጣ ነው። ከዚያም የታላቁ መከራ መደምደሚያ በሆነው በአርማጌዶን፣ በፍየል የተመሰሉት ሰዎች “ወደ ዘላለም ጥፋት” ይሄዳሉ። ይህን መረዳታችን ለአገልግሎት ያለንን አመለካከት የሚነካው እንዴት ነው? የስብከቱ ሥራችን ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ታላቁ መከራ እስኪጀምር ድረስ ሰዎች አስተሳሰባቸውን ለመለወጥና ‘ወደ ሕይወት በሚያስገባው’ ቀጭን መንገድ ላይ ጉዞ ለመጀመር ጊዜ አላቸው። (ማቴ. 7:13, 14) በአሁኑ ጊዜም ሰዎች የበግ ወይም የፍየል ዓይነት ባሕርይ እንደሚያሳዩ የታወቀ ነው። ያም ቢሆን ሰዎች በግ ወይም ፍየል ተብለው የሚፈረድባቸው በታላቁ መከራ ወቅት መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። እንግዲያው በተቻለ መጠን በርካታ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ሰምተው ምላሽ የሚሰጡበትን አጋጣሚ ለመክፈት የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን የምንቀጥልበት በቂ ምክንያት አለን።
ኢየሱስ የሚመጣው መቼ ነው?
14, 15. ክርስቶስ ወደፊት ፈራጅ ሆኖ እንደሚመጣ የሚያመለክቱት አራቱ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?
14 ኢየሱስ በተናገረው ትንቢት ላይ ያደረግነው ምርምር ሌሎች ወሳኝ ክንውኖች የሚፈጸሙበትን ጊዜ በተመለከተ ባለን መረዳት ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ነው? ትንቢቱ ራሱ መልሱን ይሰጠናል። ይህ እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
15 ከማቴዎስ 24:29 እስከ 25:46 ተመዝግቦ በሚገኘው የትንቢቱ ክፍል ላይ ኢየሱስ በዋነኝነት ትኩረት ያደረገው በመጨረሻዎቹ ቀናትና በታላቁ መከራ ወቅት በሚከናወኑ ነገሮች ላይ ነው። በዚህ የትንቢቱ ክፍል ውስጥ ኢየሱስ በስምንት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ‘ስለ መምጣቱ’ ወይም ስለ መድረሱ ገልጿል።e ከእነዚህ መካከል ከታላቁ መከራ ጋር በተያያዘ የጠቀሳቸው የሚከተሉት አባባሎች ይገኙበታል፦ “የሰው ልጅም በኃይልና በታላቅ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል።” “ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ [አታውቁም]።” “የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት [ይመጣል]።” ሌላው ደግሞ ስለ በጎችና ፍየሎች በተነገረው ምሳሌ ላይ የሚገኘው ሲሆን ጥቅሱ ‘የሰው ልጅ በክብሩ ይመጣል’ ይላል። (ማቴ. 24:30, 42, 44፤ 25:31) አራቱም ጥቅሶች ክርስቶስ ወደፊት ፈራጅ ሆኖ የሚመጣበትን ጊዜ የሚያመለክቱ ናቸው። ኢየሱስ በተናገረው ትንቢት ውስጥ ስለ እሱ መምጣት የሚገልጹት የተቀሩት አራት ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?
16. ስለ ኢየሱስ መምጣት የሚናገሩት ሌሎቹ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?
16 ኢየሱስ ታማኝና ልባም ባሪያን አስመልክቶ ሲናገር “ጌታው ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ ካገኘው ያ ባሪያ ደስተኛ ነው!” ብሏል። ስለ ደናግሎቹ በተናገረው ምሳሌ ላይ ኢየሱስ “[ደናግሎቹ ዘይት] ሊገዙ ሄደው ሳሉም ሙሽራው ደረሰ [“መጣ፣” አዲሱ መደበኛ ትርጉም]” ብሏል። ስለ ታላንት በተናገረው ምሳሌ ላይ “ከረጅም ጊዜ በኋላ የእነዚያ ባሪያዎች ጌታ [መጣ]” በማለት ተናግሯል። በዚያው ምሳሌ ላይ ጌታው “እኔም ተመልሼ ስመጣ ገንዘቡን ከነወለዱ እወስደው ነበር” ብሏል። (ማቴ. 24:46፤ 25:10, 19, 27) ስለ ኢየሱስ መምጣት የሚናገሩት እነዚህ ጥቅሶች የሚያመለክቱት የትኛውን ጊዜ ነው?
17. በማቴዎስ 24:46 ላይ የተጠቀሰውን የኢየሱስ መምጣት አስመልክቶ በጽሑፎቻችን ላይ ምን ተገልጾ ነበር?
17 መጨረሻ ላይ የተጠቀሱት ስለ ኢየሱስ መምጣት የሚናገሩት አራቱ ጥቅሶች ኢየሱስ በ1918 መምጣቱን የሚያመለክቱ እንደሆነ ቀደም ሲል በጽሑፎቻችን ላይ ተገልጾ ነበር። ስለ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚናገረውን ጥቅስ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። (ማቴዎስ 24:45-47ን አንብብ።) በቁጥር 46 ላይ የተገለጸው የኢየሱስ መምጣት፣ ኢየሱስ በ1918 የቅቡዓኑን መንፈሳዊ ሁኔታ ለመመርመር የመጣበትን ጊዜ እንደሚያመለክትና ባሪያው በጌታው ንብረት ላይ የተሾመው በ1919 እንደሆነ እናምን ነበር። (ሚል. 3:1) ይሁንና የኢየሱስን ትንቢት በጥልቀት ስንመረምር የትንቢቱ አንዳንድ ገጽታዎች የሚፈጸሙበትን ጊዜ በተመለከተ ያለን መረዳት መስተካከል እንዳለበት እንገነዘባለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
18. የኢየሱስን ትንቢት ሙሉ ሐሳብ ስንመለከት፣ ኢየሱስ የሚመጣበትን ጊዜ በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያደርገናል?
18 ከማቴዎስ 24:46 በፊት ባሉት ጥቅሶች ውስጥ የሚገኘው ‘መምጣት’ የሚለው ቃል በሁሉም ቦታዎች ላይ የሚያመለክተው ኢየሱስ በታላቁ መከራ ወቅት ፍርድ ለመስጠትና ለማስፈጸም የሚመጣበትን ጊዜ ነው። (ማቴ. 24:30, 42, 44) በተጨማሪም አንቀጽ 12 ላይ እንደተመለከትነው በማቴዎስ 25:31 ላይ የተጠቀሰው የኢየሱስ መምጣት የሚያመለክተው ይህንኑ ጊዜ ማለትም ኢየሱስ ለፍርድ የሚመጣበትን ጊዜ ነው። በመሆኑም በማቴዎስ 24:46, 47 ላይ በተጠቀሰው መሠረት ኢየሱስ ታማኙን ባሪያ በንብረቱ ሁሉ ላይ ለመሾም የሚመጣውም ወደፊት ነው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። በእርግጥም ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት ሙሉ ሐሳብ ስንመለከት፣ ስለ ኢየሱስ መምጣት የሚናገሩት ከላይ ያየናቸው ስምንቱም ጥቅሶች የሚያመለክቱት እሱ በታላቁ መከራ ወቅት ለፍርድ የሚመጣበትን ጊዜ እንደሆነ ግልጽ ያደርግልናል።
19. ቀደም ሲል ከነበረን መረዳት ጋር በተያያዘ የትኞቹን ማስተካከያዎች ተመልክተናል? በቀጣዩ ርዕስ ላይ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
19 እስቲ እስካሁን የተመለከትናቸውን ነጥቦች ለመከለስ እንሞክር። በዚህ የጥናት ርዕስ መግቢያ ላይ ከጊዜ ጋር የተያያዙ ሦስት ጥያቄዎችን አንስተን ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ታላቁ መከራ በ1914 እንዳልጀመረ፣ ከዚህ ይልቅ ታላቁ መከራ የሚጀምረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ጥቃት በሚሰነዝርበት ወቅት እንደሆነ ተመለከትን። በመቀጠል ደግሞ፣ ኢየሱስ በበጎቹና በፍየሎቹ ላይ መፍረድ የጀመረው በ1914 ሳይሆን ይህ የሚፈጸመው በታላቁ መከራ ወቅት መሆኑን ተመለከትን። በመጨረሻም ‘ኢየሱስ ታማኝና ልባም ባሪያን በንብረቱ ሁሉ ላይ ለመሾም የመጣው በ1919 አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ይህ የሚሆነው ወደፊት በታላቁ መከራ ወቅት ነው’ የምንልበትን ምክንያት ተመልክተናል። እንግዲያው ከጊዜ ጋር በተያያዘ የተነሱት የሦስቱም ጥያቄዎች መልስ ተመሳሳይ ሲሆን መልሱም ‘ወደፊት በታላቁ መከራ ወቅት ነው’ የሚል ነው። ይሁን እንጂ ይህ አዲስ ማስተካከያ ከታማኙ ባሪያ ጋር በተያያዘ ያለንን መረዳት የሚነካው እንዴት ነው? በዚህ በመጨረሻው ዘመን ላይ እየተፈጸሙ ያሉትን ሌሎች የኢየሱስ ምሳሌዎች በተመለከተ ያለንን መረዳት የሚነካውስ እንዴት ነው? እነዚህን ወሳኝ ጥያቄዎች በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንመረምራለን።
a አንቀጽ 4፦ ለበለጠ መረጃ የየካቲት 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 8-21 እና የግንቦት 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 8-20 ተመልከት።
b አንቀጽ 8፦ በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ከተገለጹት ክንውኖች አንዱ ‘የተመረጡትን መሰብሰብ’ ነው። (ማቴ. 24:31) በመሆኑም የታላቁ መከራ የመጀመሪያ ምዕራፍ ካለፈ በኋላ በምድር ላይ የሚገኙ ቅቡዓን በሙሉ የአርማጌዶን ጦርነት ከመፈንዳቱ በፊት የሆነ ጊዜ ላይ ወደ ሰማይ የሚሄዱ ይመስላል። ይህ ሐሳብ በነሐሴ 15, 1990 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 30 (16-111 ገጽ 30) ላይ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ “የአንባቢያን ጥያቄዎች” በሚል ዓምድ ሥር የወጣውን ትምህርት የሚያስተካክል ነው።
c አንቀጽ 11፦ የጥቅምት 15, 1995 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 18-28 ተመልከት።
e አንቀጽ 15፦ ‘መምጣት’ እና ‘መድረስ’ የሚሉት ቃላት የተተረጎሙት ኤርኮማይ ከሚለው የግሪክኛ ግስ ነው።