የአንባብያን ጥያቄዎች
በ1 ጴጥሮስ 2:9, 10 ላይ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “የተመረጠ ትውልድ” ተብለው ተጠርተዋል።ይህ አገላለጽ ኢየሱስ በማቴዎስ 24:34 ላይ ስለተጠቀመበት “ትውልድ” ስለሚለው ቃል ያለንን አመለካከት ይነካዋልን?
በአንዳንድ ትርጉሞች በሁለቱም ጥቅሶች ላይ “ትውልድ” የሚለው ቃል ይገኛል። በ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መሠረት ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ።” ኢየሱስ ደግሞ እንዲህ በማለት ትንቢት ተናግሯል፦ “እውነት እላችኋለሁ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።”—1 ጴጥሮስ 2:9፤ ማቴዎስ 24:34
በመጀመሪያው ጥቅስ ላይ ሐዋርያው ጴጥሮስ የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል ጄኖስ ሲሆን ኢየሱስ በተናገረበት ጥቅስ ላይ ግን ጄኒያ የሚለውን ቃል እናገኛለን። እነዚህ ሁለት የግሪክኛ ቃላት ተመሳሳይና ሥረ መሠረታቸው አንድ ዓይነት ቢመስሉም የተለያዩ ቃላት ከመሆናቸውም በላይ ትርጉማቸው ለየቅል ነው። ባለማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ለ1 ጴጥሮስ 2:9 በሚሰጠው የግርጌ ማስታወሻ ላይ እንዲህ ይላል፦ “‘ዘር’ የሚል ትርጉም ያለው ጄኖስ የሚለው ግሪክኛ ቃል በማቴ. 24:34 ላይ ከሚገኘው ‘ትውልድ’ የሚል ፍቺ ካለው ጄኒያ የተለየ ነው።” በማቴዎስ 24:34 ላይም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል የግርጌ ማስታወሻ ይገኛል።
እነዚህ የግርጌ ማስታወሻዎች እንደሚያሳዩት ጄኖስ የሚለው ቃል በአብዛኞቹ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች ውስጥ እንደሚገኘው በእንግሊዝኛ “ሬስ (ዘር)” ተብሎ በተገቢ ሁኔታ ተተርጉሟል። ጴጥሮስ በ1 ጴጥሮስ 2:9 ላይ በኢሳይያስ 61:6 የሚገኘውን ትንቢት ሰማያዊ ተስፋ ላላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ተጠቅሞበታል። እነዚህ ከብዙ ብሔራትና ነገዶች የተውጣጡ ቢሆኑም የመንፈሳዊ እስራኤል ክፍል ስለሚሆኑ የመጡበት ዘር ትርጉም የለውም። (ሮሜ 10:12፤ ገላትያ 3:28, 29፤ 6:16፤ ራእይ 5:9, 10) ጴጥሮስ በመንፈሳዊ ሁኔታ የተለየ ቡድን ማለትም “የተመረጠ ትውልድ [“ዘር” አዓት]፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን” እንደሆኑ አድርጎ ገልጿቸዋል።
በማቴዎስ 24:34 ላይ የሚገኙትን ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት በግሪክኛ ስናነብ ጄኒያ የሚል ቃል እናገኛለን። ኢየሱስ የተናገረው ስለ አንድ የሰዎች “ዘር” ሳይሆን በተወሰነ የጊዜ ርዝመት ውስጥ ስለሚኖሩ ሰዎች መሆኑ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል።
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት የነበረው ቻርልስ ቲ ራስል አንድ መቶ ከሚያክሉ ዓመታት በፊት እንዲህ በማለት ግልጽ የሆነ ሐሳብ ጽፏል፦ “ ‘ትውልድ’ እና ‘ዘር’ የሚሉት ቃላት አንድ ዓይነት ሥረ መሠረት ወይም መነሻ አላቸው ሊባል ቢችልም እነዚህ ቃላት ተመሳሳይ አይደሉም። ሁለቱ ቃላት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ባላቸው አጠቃቀም ረገድ ፈጽሞ የተለያዩ ናቸው። . . . ይህ ትንቢት በተመዘገበባቸው ሦስት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ጌታችን ሙሉ በሙሉ ልዩ በሆነ ግሪክኛ ቃል (ጄኒያ) ተጠቅሟል። ይህ ቃል ትውልድ ከሚለው የአማርኛ ቃል ጋር ተመሳሳይ የሆነ ትርጉም አለው እንጂ ዘር ማለት አይደለም። የዚህ ግሪክኛ ቃል (ጄኒያ) ሌሎች አጠቃቀሞች ዘርን ለማመልከት ሳይሆን በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ የኖሩ ሰዎችን ለማመልከት እንደሚያገለግል ያሳያሉ።”—የበቀል ቀን (በእንግሊዝኛ የሚገኝ) ገጽ 602–3
ለመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የተዘጋጀ ኤ ሀንድ ቡክ ኦን ዘ ጎስፕል ኦቭ ማቲው (1988) የተባለ መምሪያ መጽሐፍ በቅርቡ እንዲህ ብሏል፦ “[ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን] ይህ ትውልድ በማለት ቃል በቃል ከተረጎመ በኋላ በግርጌ ማስታወሻው ላይ ‘ወይም ዘር’ በማለት አስፍሯል። በተጨማሪም አንድ የአዲስ ኪዳን ምሁር ‘ማቴዎስ ለመግለጽ የፈለገው ኢየሱስን ያልተቀበሉትን ጠቅላላውን የአይሁድ ትውልድ እንጂ ከኢየሱስ በኋላ የነበረውን የመጀመሪያ ትውልድ ብቻ እንዳልሆነ’ ያምናሉ። ነገር ግን ከእነዚህ መደምደሚያዎች የትኛው ትክክል እንደሆነ የሚያሳይ የቋንቋ ማስረጃ ስለሌለ ግልጽ የሆነውን ትርጉም ለማጥፋት እንደተደረጉ ሙከራዎች ታይተው ወደ ጎን ገሸሽ መደረግ አለባቸው። ቃሉ በበኩረ ጽሑፉ ውስጥ ባለው አቀማመጥ ኢየሱስ በኖረበት ጊዜ ውስጥ የኖሩ ሰዎችን ያመለክታል።”
ከገጽ 10 እስከ 15 እንደተመለከትነው ኢየሱስ እርሱ በኖረበት ዘመን ይኖር የነበረውን እርሱን ያልተቀበለውን የአይሁድ ትውልድ አውግዟል። (ሉቃስ 9:41፤ 11:32፤ 17:25) ብዙውን ጊዜ “ክፉና አመንዝራ፣” ‘የማያምን ጠማማ’ እና ‘ዘማዊና ኃጢአተኛ’ እንደሚሉት ባሉ ቅጽሎች ተጠቅሟል። (ማቴዎስ 12:39፤ 17:17፤ ማርቆስ 8:38) ኢየሱስ “ትውልድ” የሚለውን ቃል የመጨረሻውን ጊዜ ለማመልከት ሲጠቀምበት ከአራት ደቀ መዛሙርቱ ጋር በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ነበር። (ማርቆስ 13:3) እነዚህ ሰዎች በዚያን ጊዜ ገና በመንፈስ ካለመቀባታቸውም በላይ የክርስቲያን ጉባኤ አባል ስላልነበሩ በፍጹም አንድ “ትውልድ” ወይም አንድ ዘር ሊወክሉ አይችሉም። ቢሆንም ኢየሱስ “ትውልድ” የሚለውን ቃል እርሱ በኖረበት ጊዜ የሚኖሩትን ሰዎች ለማመልከት እንደሚጠቀምበት አሳምረው ያውቁ ነበር። ስለዚህ “ይህ ትውልድ” የሚለውን ቃል የመጨረሻውን ጊዜ ለማመልከት ሲጠቀምበት ምን ለማለት እንዳሰበ ከሁኔታው ይረዱ ነበር።a በዚያ ተገኝቶ የነበረው ሐዋርያው ጴጥሮስ ከዚያ ጥቂት ቆየት ብሎ “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ” በማለት አይሁዶችን አሳስቧቸው ነበር።—ሥራ 2:40
ኢየሱስ በዚህ ንግግሩ ላይ የተነበያቸው አብዛኞቹ ነገሮች (እንደ ጦርነት፣ የመሬት መንቀጥቀጥና ረሀብ የመሳሰሉት) ትንቢቱን በተናገረበትና ኢየሩሳሌም በ70 እዘአ በጠፋችበት ጊዜ መካከል ተፈጽመው እንደነበር በተደጋጋሚ ማስረጃዎች አቅርበናል። ብዙዎቹ በዚያን ጊዜ ቢፈጸሙም ሙሉ በሙሉ አልተፈጸሙም። ለምሳሌ ያህል ሮማውያን ኢየሩሳሌምን ከወረሩ በኋላ (66–70 እዘአ) “የምድር ወገኖች ሁሉ” ዋይ ዋይ እንዲሉ ያደረጋቸው “የሰው ልጅ ምልክት” እንደታየ የሚያረጋግጥ ማስረጃ የለም። (ማቴዎስ 24:30) ስለዚህ በ33 እዘአ እና በ70 እዘአ የተከናወነው ኢየሱስ ያመለከተው ሙሉው ወይም ስፋት ያለው ፍጻሜ ሳይሆን የመጀመሪያው ፍጻሜ መሆን አለበት።
ጂ ኤ ዊሊያምሰን ዘ ጁዊሽ ዎር የተባለውን የጆሴፈስ ጽሑፍ ሲተረጉም መግቢያው ላይ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ማቴዎስ እንደሚነግረን ደቀ መዛሙርቱ [ኢየሱስን] ድርብ ጥያቄ ጠይቀውት ነበር። የጠየቁት ጥያቄ የቤተ መቅደሱን መጥፋት በተመለከተና ኢየሱስ በመጨረሻ ስለመምጣቱ ነው። እርሱም ድርብ መልስ ሰጣቸው። በመጀመሪያ ደረጃ እንደሚፈጸሙ በግልጽ የተተነበዩትን ሁኔታዎች ጆሴፈስ ሙሉ በሙሉ ገልጿቸዋል።”
አዎን፣ በዚህ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜ ላይ “ይህ ትውልድ” የሚለው አገላለጽ በሌሎች ጊዜያት ከሚሠራበት ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ግልጽ ነው። ይኸውም ኢየሱስ በኖረበት ጊዜ የነበሩትን የማያምኑ አይሁዶች ያመለክታል። ያ “ትውልድ” ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረውን ሳይመለከት አያልፍም ነበር። የዓይን ምሥክር የሆነው ጆሴፈስ እንደገለጸው ከኢየሩሳሌም ጥፋት በፊት ባሉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ተፈጽመዋል በማለት ዊሊያምሰን ተናግረዋል።
በሁለተኛው ወይም ስፋት ባለው የዚህ ትንቢት ፍጻሜም “ይህ ትውልድ” የሚለው አገላለጽ በአንድ የተወሰነ ጊዜ የሚኖሩ ሰዎችን ያመለክታል። በገጽ 16 ላይ የሚጀምረው ርዕስ እንደሚገልጸው ኢየሱስ አንድ “ትውልድ” ይህን ያህል ዓመት ርዝመት ይኖረዋል ብሎ እየተናገረ ነው ብለን መደምደም አያስፈልገንም።
ከዚህ ይልቅ “ትውልድ” ተብሎ ስለተጠቀሰ ማንኛውም ጊዜ ሁለት ቁልፍ ነገሮችን መናገር ይቻላል። (1) የጊዜ ስያሜዎች የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ዓመታት (አሥር ዓመት ወይም መቶ ዘመን) በውስጣቸው እንደሚይዙ አንድ ትውልድ የተወሰነ ዓመት ርዝመት እንዳለው ተደርጎ መታየት አይችልም። (2) አንጻራዊ በሆነ መንገድ ለአጭር ጊዜ የኖረ ትውልድ በጣም ረዥም ለሆኑ ዘመናት ኖሯል ማለት አይደለም።
ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” ብሎ ሲናገር ሐዋርያቱ ምን ተሰምቷቸው ነበር? እኛ ኢየሩሳሌም ‘በታላቁ መከራ’ የጠፋችው ከ37 ዓመት በኋላ መሆኑን ያስተዋልነው የተፈጸመውን ነገር መለስ ብለን በመመልከት ስለሆነ ኢየሱስን ያዳምጡ የነበሩ ሐዋርያት ይህንን ላያስተውሉ ይችላሉ። ከዚህ ይልቅ “ትውልድ” በማለት የሚናገረው እጅግ ብዙ ዓመታትን ስለሚሸፍን ጊዜ ሳይሆን አንጻራዊ በሆነ ሁኔታ ሲታይ በተወሰነ ጊዜ ስለሚኖሩ ሰዎች መሆኑን ተረድተው ነበር። ለእኛም ቢሆን ልክ እንደዚሁ ነው። ኢየሱስ ቀጥሎ የተናገራቸው ቃላት ምንኛ ተስማሚ ናቸው፦ “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም። . . . ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።”—ማቴዎስ 24:36, 44
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “ይህ ትውልድ” በሚለው አገላለጽ ውስጥ የገባው ሆቶስ የሚለው አመልካች ተውላጠ ስም “ይህ” ከሚለው የአማርኛ ቃል ጋር በጥሩ ሁኔታ ይስማማል። በዚያን ወቅት እየተፈጸመ ያለን ነገር ወይም ከተናጋሪው ፊት ያለን ሁኔታ ሊያመለክት ይችላል። ቢሆንም ሌላ ትርጉም ሊኖረውም ይችላል። ኤክሰጄቲከል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት (1991) እንዲህ ይላል፦ “[ሆቶስ] የሚለው ቃል በቅርቡ የሚፈጸም ሁኔታን ያመለክታል። በዚህ መሠረት [ኤዎን ሆቶስ] ‘አሁን ያለው ዓለም’ ማለት ሲሆን . . . [ጄኒያ ሆቴ] ደግሞ ‘አሁን ያለው ትውልድ’ ማለት ነው። (ለምሳሌ ማቴ. 12:41 የግርጌ ማስታወሻ፣ 45፤ 24:34 . . .)” ዶክተር ጆርጅ ቢ ዊነር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “[ሆቶስ] የሚለው ተውላጠ ስም አንዳንድ ጊዜ በአካባቢው ያለውን ሳይሆን ቀደም ብሎ የተጠቀሰውን ጸሐፊው በአእምሮው ውስጥ በመጀመሪያ ደረጃ ለያዘው ዋና ባለቤት በሐሳብ የሚቀርበውን ስም ያመለክታል።”—ኤ ግራመር ኦቭ ዘ ኢድየም ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት 7ኛ እትም፣ 1897