ከምንጊዜውም በበለጠ ነቅተን እንጠብቅ
“ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።”—ማቴዎስ 24:42
1, 2. በዚህ ሥርዓት መጨረሻ ላይ እንደምንኖር የሚያሳዩት ማስረጃዎች ምንድን ናቸው?
ቢል ኢመት የተባሉ አንድ ደራሲ “የጦርነትን ያህል በሃያኛው መቶ ዘመን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ ነገር የለም” ብለዋል። መላው የሰው ዘር ታሪክ በጦርነትና በዓመፅ የተሞላ መሆኑን ያልካዱት እኚህ ሰው አክለውም እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “በሃያኛው መቶ ዘመን የታየው ጦርነትና ዓመፅ ቀደም ሲል በነበሩት መቶ ዘመናትም ነበር፤ ሃያኛውን መቶ ዘመን የተለየ የሚያደርገው ግን የእነዚህ ክስተቶች መብዛት ነው። ይህ መቶ ዘመን ዓለም አቀፋዊ ይዘት አለው ሊባል የሚችል ጦርነት ለማስተናገድ የመጀመሪያው ሲሆን . . . እንዲህ ዓይነቱ ግጭት ከአንዴም ሁለቴ መከሰቱ ደግሞ ከሌሎች መቶ ዘመናት የተለየ መሆኑን ያረጋግጥልናል።”
2 ኢየሱስ ክርስቶስ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ” የሚነሳባቸው ጦርነቶች እንደሚደረጉ ትንቢት ተናግሯል። ይሁን እንጂ ጦርነት ‘የክርስቶስን መገኘትና የዓለም መጨረሻ’ መቅረቡን ከሚያሳዩት ምልክቶች መካከል አንዱ ገጽታ ብቻ ነው። ኢየሱስ በዚህ ታላቅ ትንቢት ላይ ረሃብን፣ ቸነፈርንና የምድር መናወጥንም ጨምሮ ጠቅሷል። (ማቴዎስ 24:3, 7, 8፤ ሉቃስ 21:6, 7, 10, 11) እነዚህ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ነው። ሰዎች ለአምላክም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ካላቸው አመለካከት ለመረዳት እንደሚቻለው የሰው ልጆች ክፋት በእጅጉ ጨምሯል። የሥነ ምግባር ውድቀት እንዲሁም የወንጀልና የዓመፅ መጨመር በግልጽ የሚታዩ ችግሮች ናቸው። ሰዎች ከአምላክ ይልቅ ገንዘብንና ተድላን ይወድዳሉ። ይህ ሁሉ ‘በሚያስጨንቅ ዘመን’ ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳይ ማስረጃ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
3. ‘የዘመኑ ምልክቶች’ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሱን ይገባል?
3 የሰው ልጆች ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ ሲሄዱ ስትመለከት ምን ይሰማሃል? ብዙ ሰዎች በጊዜያችን ለሚፈጸሙት አስጨናቂ ክስተቶች ግድ አይሰጣቸውም፤ እንዲያውም ልባቸው ደንድኗል። በዓለም ጉዳዮች ወሳኝ ቦታ ያላቸውና ምሑራን የሚባሉ ሰዎች ‘የዘመኑ ምልክቶች’ ምን ትርጉም እንዳላቸው የማያስተውሉ ሲሆን ሃይማኖታዊ መሪዎችም በዚህ ረገድ ተገቢውን መመሪያ አይሰጡም። (ማቴዎስ 16:1-3) ኢየሱስ ግን ተከታዮቹን “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ማቴዎስ 24:42) እዚህ ላይ ኢየሱስ ያሳሰበን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እንድንነቃ ሳይሆን ‘ነቅተን’ እንድንጠብቅ ነው። ነቅተን ለመጠበቅ ምንጊዜም ዝግጁና ትጉ መሆን አለብን። ይህ ደግሞ የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን ላይ መሆኑን አምነን ከመቀበልና የጊዜውን አስከፊነት ከመገንዘብ የበለጠ ነገርን ይጨምራል። ‘የነገር ሁሉ መጨረሻ እንደቀረበ’ የጸና እምነት ሊኖረን ይገባል። (1 ጴጥሮስ 4:7) ነቅተን እየጠበቅን ነው ማለት የምንችለው እንዲህ ያለ እምነት ሲኖረን ብቻ ነው። እዚህ ላይ ልናስብበት የሚገባ አንድ ጥያቄ ይነሳል:- ‘መጨረሻው እንደቀረበ ያለንን ጽኑ እምነት እንድናጠናክር ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው?’
4, 5. (ሀ) ይህ ክፉ ሥርዓት መጥፊያው እንደቀረበ ያለንን እምነት የሚያጠናክርልን ምንድን ነው? ለምንስ? (ለ) የኖኅን ጊዜ የሰው ልጅ ከሚመጣበት ዘመን ጋር የሚያመሳስለው አንደኛው ነጥብ ምንድን ነው?
4 በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ በአንድ ወቅት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ክስተት ተፈጽሞ የነበረ ሲሆን ይህም በኖኅ ዘመን የደረሰው ታላቁ የውኃ ጥፋት ነው። እስቲ የጥፋት ውኃ ከመምጣቱ በፊት የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበረ እንመልከት። ከሰዎች ክፋት የተነሳ ይሖዋ ‘በልቡ አዝኖ’ ነበር። በዚህም ምክንያት “የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ” በማለት ተናገረ። (ዘፍጥረት 6:6, 7) እንዳለውም አድርጎታል። ኢየሱስ ያለንበትን ጊዜ ከኖኅ ዘመን ጋር በማወዳደር “የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና” ብሏል።—ማቴዎስ 24:37
5 ይሖዋ አሁን ላለንበት ዓለም ያለው ስሜት ከጥፋት ውኃ በፊት ለነበረው ዓለም ከተሰማው ስሜት ጋር ተመሳሳይ ነው ብንል አልተሳሳትንም። በኖኅ ዘመን የነበረውን ኃጢአተኛ ዓለም እንዳጠፋው ሁሉ ዛሬ ያለውንም ክፉ ዓለም እንደሚያጠፋው አያጠራጥርም። አሁን የምንኖርበት ዓለም ከኖኅ ዘመን ጋር ያለውን ተመሳሳይነት በግልጽ መገንዘባችን ይህ ዓለም መጥፊያው እንደቀረበ ያለንን ጽኑ እምነት ያጠናክርልናል። ታዲያ የኖኅን ዘመንና ያለንበትን ጊዜ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ቢያንስ አምስት ነጥቦችን መጥቀስ እንችላለን። የመጀመሪያው፣ ጥፋት እየቀረበ እንዳለ የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ በማያሻማ ሁኔታ መነገሩ ነው።
‘ገና ስለማይታየው ነገር’ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
6. ይሖዋ በኖኅ ዘመን ምን ለማድረግ ወስኖ ነበር?
6 በኖኅ ዘመን ይሖዋ “መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፣ እርሱ ሥጋ ነውና፤ ዘመኖቹም መቶ ሀያ ዓመት ይሆናሉ” በማለት ተናግሮ ነበር። (ዘፍጥረት 6:3) በ2490 ከክርስቶስ ልደት በፊት የተሰጠው ይህ መለኮታዊ ፍርድ በወቅቱ የነበረው ኃጢአተኛ ዓለም መጥፊያው እንደቀረበ የሚጠቁም ነበር። ይህ በወቅቱ ለነበሩ ሰዎች ምን ማለት እንደነበር እስቲ አስበው! ልክ ከ120 ዓመታት በኋላ ይሖዋ “ከሰማይ በታች የሕይወት ነፍስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃን” ያመጣል።—ዘፍጥረት 6:17
7. (ሀ) ኖኅ የውኃ ጥፋትን በሚመለከት ለተሰጠው ማስጠንቀቂያ የሰጠው ምላሽ ምን ነበር? (ለ) ይህ ሥርዓት እንደሚጠፋ ለተሰጡን ማስጠንቀቂያዎች ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል?
7 ኖኅ መጪውን ጥፋት በሚመለከት ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ከብዙ አሥርተ ዓመታት በፊት ስለነበር ጊዜውን ሕይወት ማትረፍ የሚቻልበትን ዝግጅት ለማድረግ በሚገባ ተጠቅሞበታል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ” በማለት ተናግሯል። (ዕብራውያን 11:7) እኛስ? የዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ከጀመሩበት ከ1914 አንስቶ ወደ 90 የሚጠጉ ዓመታት አልፈዋል። በእርግጥም የምንገኘው ‘በፍጻሜው ዘመን’ ውስጥ ነው። (ዳንኤል 12:4) የምንኖርበትን ዘመን አስመልክቶ ለተሰጡን ማስጠንቀቂያዎች ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል? መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት ይናገራል። (1 ዮሐንስ 2:17) ስለዚህ የጊዜውን አጣዳፊነት ተገንዝበን የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ ያለብን አሁን ነው።
8, 9. ይሖዋ በጊዜያችን ምን ማስጠንቀቂያዎች ሰጥቷል? እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች እየታወጁ ያሉትስ እንዴት ነው?
8 በዘመናችን ቅን ልብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህ ሥርዓት ጥፋት እንደተፈረደበት በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት ከቅዱሳን ጽሑፎች ተገንዝበዋል። አንተስ ይህን ታምናለህ? ኢየሱስ ክርስቶስ “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና” በማለት የሰጠውን ግልጽ ማስጠንቀቂያ ልብ በል። (ማቴዎስ 24:21) በተጨማሪም ኢየሱስ በአምላክ የተሾመ ፈራጅ ሆኖ እንደሚመጣና አንድ እረኛ በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ ሰዎችን እንደሚለያቸው ተናግሯል። ኃጢአተኞች “ወደ ዘላለም ቅጣት፣ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።”—ማቴዎስ 25:31-33, 46
9 ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ወቅታዊ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ ሕዝቦቹ እነዚህን ማስጠንቀቂያዎች ልብ እንዲሉ ሲያበረታታ ቆይቷል። (ማቴዎስ 24:45-47) ከዚህም በላይ ለእያንዳንዱ ሕዝብ፣ ነገድ፣ ቋንቋና ወገን “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት” የሚል ጥሪ ቀርቧል። (ራእይ 14:6, 7) የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ሰብዓዊ አገዛዝን ጠራርጎ እንደሚያስወግድ የሚገልጸው ማስጠንቀቂያ የይሖዋ ምሥክሮች በምድር ዙሪያ የሚሰብኩት የመንግሥቱ መልእክት ዓቢይ ክፍል ነው። (ዳንኤል 2:44) ይህ ማስጠንቀቂያ ቸል ሊባል የሚገባው አይደለም። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ምንጊዜም ቃሉን ይጠብቃል። (ኢሳይያስ 55:10, 11) በኖኅ ጊዜ ቃሉን ጠብቋል፤ በጊዜያችንም እንዲሁ ያደርጋል።—2 ጴጥሮስ 3:3-7
ልቅ የጾታ ብልግና ተስፋፍቷል
10. በኖኅ ዘመን የነበረው ልቅ የጾታ ብልግና ምን ይመስል ነበር?
10 ያለንበትን ጊዜ ከኖኅ ዘመን ጋር የሚያመሳስለው ሌላም ነጥብ አለ። ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ክቡር በሆነ የጋብቻ ትስስር ውስጥ ከአምላክ ያገኙትን ተራክቧዊ ስጦታ ተጠቅመው መሰላቸውን በማፍራት ‘ምድርን እንዲሞሏት’ አዝዟቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) በኖኅ ዘመን ዓመፀኛ መላእክት ከተፈጥሮ ውጪ በሆነ የጾታ ፍላጎት የሰውን ዘር በከሉት። እነዚህ መላእክት ሥጋ ለብሰው ወደ ምድር በመውረድ ቆንጆ የሆኑ ሴቶች ልጆችን ያገቡ ሲሆን የሰውና የመላእክት ዲቃላ የነበሩትን ኔፊሊሞች ወለዱ። (ዘፍጥረት 6:2, 4) የእነዚህ ሴሰኛ መላእክት ኃጢአት በሰዶምና ገሞራ ከነበረው ርኩሰት ጋር ተመሳሳይ ነበር። (ይሁዳ 6, 7) በዚህም የተነሳ በዚያ ዘመን ልቅ የጾታ ብልግና ተስፋፍቶ ነበር።
11. በሥነ ምግባር ረገድ ያለንበት ጊዜ ከኖኅ ዘመን ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
11 በዛሬውስ ጊዜ ያለው የሥነ ምግባር ሁኔታ ምን ይመስላል? በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የብዙ ሰዎች ሕይወት በወሲብ ዙሪያ ያተኮረ ነው። ጳውሎስ እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች ‘ደንዝዘዋል’ ብሏቸዋል። ብዙዎች “በመመኘት ርኵሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው” ሰጥተዋል። (ኤፌሶን 4:19) ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች፣ ከጋብቻ በፊት የሚፈጸም የጾታ ግንኙነት፣ በልጆች ላይ የሚፈጸም የወሲብ ጥቃት እንዲሁም ግብረሰዶም በጣም ተስፋፍተዋል። አንዳንዶች በዚህ ድርጊታቸው የተነሳ ለአባለዘር በሽታ፣ ለቤተሰብ መፈራረስና ለሌሎች ማኅበራዊ ቀውሶች ተዳርገው ‘የሚገባቸውን ብድራት ተቀብለዋል።’—ሮሜ 1:26, 27
12. ክፉ የሆነውን ነገር መጥላት የሚኖርብን ለምንድን ነው?
12 በኖኅ ዘመን ይሖዋ የጥፋት ውኃ በማምጣት ለጾታ ከፍተኛ ግምት ይሰጥ የነበረውን ዓለም አጥፍቷል። እኛም የምንኖርበት ጊዜ ከኖኅ ዘመን ጋር እንደሚመሳሰል ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም። መጪው “ታላቅ መከራ” ‘ሴሰኞችን፣ አመንዝሮችን፣ ቀላጮችንና ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩትን’ ከምድር ላይ ያጸዳል። (ማቴዎስ 24:21፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:8) እንግዲያው ክፉ የሆኑ ነገሮችን መጥላታችንና ወደ ሥነ ምግባር ብልግና ሊመሩን ከሚችሉ ሁኔታዎች መራቃችን ምንኛ አጣዳፊ ነው!—መዝሙር 97:10፤ 1 ቆሮንቶስ 6:18
‘ምድር በግፍ ተሞልታለች’
13. በኖኅ ዘመን ምድር ‘በግፍ የተሞላችው’ ለምን ነበር?
13 መጽሐፍ ቅዱስ የኖኅ ዘመን ተለይቶ የሚታወቅበትን ሌላውን ሁኔታ ሲናገር “ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸች፤ ምድርም ግፍን ተሞላች” ይላል። (ዘፍጥረት 6:11) በእርግጥ ዓመፅ በጊዜው አዲስ አልነበረም። የአዳም ልጅ የነበረው ቃየን ጻድቅ ወንድሙን ገድሏል። (ዘፍጥረት 4:8) ላሜሕም ራስን ለመከላከል በሚል ሰበብ አንድን ወጣት እንዴት እንደገደለ በግጥም የገለጸ ሲሆን ይህም በጊዜው የነበረውን የዓመፀኝነት ዝንባሌ ያንጸባርቃል። (ዘፍጥረት 4:23, 24) የኖኅን ዘመን ግን የተለየ ያደረገው የዓመፅ መብዛት ነው። ታዛዥ ያልነበሩት የአምላክ መላእክታዊ ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች አግብተው ኔፊሊም የተባሉትን ዲቃላዎች የወለዱ ሲሆን ዓመፅ ከዚያ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን ጨመረ። ግዙፍ የነበሩትን እነዚህን ዓመፀኞች ለማመልከት የገባው የዕብራይስጥ ቃል “የሚዘርሩ” ወይም “ሰዎችን አንስተው የሚያፈርጡ” የሚል ትርጉም አለው። (ዘፍጥረት 6:4 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) በዚህም ምክንያት ምድር ‘በግፍ ተሞልታ’ ነበር። (ዘፍጥረት 6:13) ኖኅ እንዲህ ባለ አካባቢ ልጆቹን ማሳደግ ምን ያህል ፈታኝ እንደሚሆንበት መገመት አያዳግትም! ቢሆንም ኖኅ ‘በዚያ ትውልድ መካከል በይሖዋ ፊት ጻድቅ’ መሆኑን አስመስክሯል።—ዘፍጥረት 7:1
14. በዛሬው ጊዜ ምድር ‘በግፍ የተሞላችው’ እንዴት ነው?
14 በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ዓመፅ ያልታየበት ጊዜ አልነበረም። ሆኖም ልክ በኖኅ ዘመን እንደነበረው በጊዜያችንም ታይቶ በማይታወቅ መጠን ጨምሯል። በቤተሰብ ውስጥ ስለሚፈጸም ድብደባ፣ ስለ ሽብር ጥቃት፣ ስለ ዘር ማጽዳት ዘመቻዎችና መሣሪያ በታጠቁ ሰዎች ስለሚፈጸሙ የጅምላ ጭፍጨፋዎች በየዕለቱ እንሰማለን። በጦርነት ሳቢያ የሚፈጸመው የደም መፋሰስም ተጠቃሽ ነው። ዛሬም እንደጥንቱ ምድራችን በዓመፅ ተሞልታለች። ለምን? ለዓመፅ መጨመር አስተዋጽኦ ያደረገው ምንድን ነው? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ያለንበት ጊዜ ከኖኅ ዘመን ጋር የሚመሳሰልበትን ሌላ ነጥብ ይገልጽልናል።
15. (ሀ) በመጨረሻው ዘመን ዓመፅ እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያደረገው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ስለምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
15 የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት በ1914 በሰማይ ሲቋቋም በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ በታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እርምጃ ወስዷል። ሰይጣን ዲያብሎስና አጋንንቱ ከሰማይ ወደ ምድር ተጥለዋል። (ራእይ 12:9-12) ከጥፋት ውኃ በፊት ዓመፀኛ መላእክት በሰማይ የነበረውን መኖሪያቸውን የተዉት በገዛ ፈቃዳቸው ነበር፤ በዚህ ዘመን ግን ወደ ምድር የመጡት ተባርረው ነው። ከዚህም በላይ ልቅ በሆኑ የጾታ ድርጊቶች ለመካፈል እንደቀድሞው ሥጋ የመልበስ ችሎታ የላቸውም። ስለዚህ በተስፋ መቁረጥ፣ በንዴትና የሚመጣባቸውን ጥፋት በመፍራት ከኖኅ ዘመን የከፋ ዓመፅና ወንጀል እንዲፈጽሙ ሰዎችንና ድርጅቶችን ይገፋፋሉ። ይሖዋ ክፉዎቹ መላእክትና ልጆቻቸው በሚፈጽሙት ክፋት የተሞላውን ከጥፋት ውኃ በፊት የነበረ ዓለም አጥፍቶታል። በዘመናችንም ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስድ ቅንጣት ታክል አንጠራጠርም! (መዝሙር 37:10) እንዲያውም በጊዜያችን ነቅተው የሚጠባበቁ ሁሉ መዳን የሚያገኙበት ጊዜ በጣም እንደቀረበ ይገነዘባሉ።
የመልእክቱ መሰበክ
16, 17. የኖኅን ዘመን ከምንኖርበት ጊዜ ጋር የሚያመሳስለው አራተኛው ነጥብ ምንድን ነው?
16 ከጥፋት ውኃ በፊት የነበረውን ዓለምና የምንኖርበትን ጊዜ የሚያመሳስላቸው አራተኛው ነጥብ ኖኅ እንዲያከናውን ከተሰጠው ተልእኮ ጋር የሚያያዝ ነው። ኖኅ ግዙፍ መርከብ ገንብቷል፤ እንዲሁም ‘ሰባኪ’ ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:5) የሰበከው መልእክት ምን ነበር? ጥፋት እንደቀረበ ያስጠነቅቅና ንስሐ እንዲገቡ ግብዣ ያቀርብ እንደነበር ግልጽ ነው። በኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች ግን “የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ” ኢየሱስ ተናግሯል።—ማቴዎስ 24:38, 39
17 በተመሳሳይም የተሰጣቸውን የስብከት ሥራ በትጋት በመወጣት ላይ በሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች አማካኝነት የአምላክ መንግሥት ምሥራች በዓለም ዙሪያ እየተሰበከ ነው። በሁሉም የዓለም ክፍል ማለት ይቻላል ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት በራሳቸው ቋንቋ መስማትም ሆነ ማንበብ ችለዋል። የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቀው የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ከ140 በሚበልጡ ቋንቋዎች ታትሞ ከ25, 000, 000 ቅጂዎች በላይ ይሰራጫል። በእርግጥም የአምላክ መንግሥት ምሥራች “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን . . . በዓለም ሁሉ” እየተሰበከ ነው። ይህ ሥራ ይሖዋን በሚያረካ ሁኔታ ሲፈጸም መጨረሻው እንደሚመጣ አያጠራጥርም።—ማቴዎስ 24:14
18. በጊዜያችን ብዙዎች ለስብከቱ ሥራችን የሚሰጡት ምላሽ በኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች ከሰጡት ምላሽ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
18 ከጥፋት ውኃ በፊት የነበረው ዓለም በመንፈሳዊና በሥነ ምግባር ያዘቀጠ ከመሆኑ አንጻር ኖኅና ቤተሰቡ የተጠራጣሪ ጎረቤቶቻቸው ማላገጫና መዘባበቻ ሆነው እንደነበር መገመት አያዳግትም። ሆኖም መጨረሻው መምጣቱ አልቀረም። በተመሳሳይም በመጨረሻው ዘመን “ዘባቾች” በዝተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “[የይሖዋ] ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል” ይላል። (2 ጴጥሮስ 3:3, 4, 10) በተቀጠረው ጊዜ እንደሚመጣ አያጠራጥርም። ፈጽሞ አይዘገይም። (ዕንባቆም 2:3) ነቅተን መጠበቃችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው!
የሚድኑት ጥቂቶች ናቸው
19, 20. በኖኅ ዘመን የደረሰውን የጥፋት ውኃና የዚህን ዓለም ጥፋት የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው?
19 የኖኅን ዘመን ከጊዜያችን ጋር የሚያመሳስለው ሰዎች በክፋት እየባሱ መሄዳቸውና ጥፋት መምጣቱ ብቻ አይደለም። ከጥፋት ውኃው በሕይወት የተረፉ ሰዎች እንደነበሩ ሁሉ በዚህ ሥርዓት ላይ ከሚደርሰው ጥፋትም በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች ይኖራሉ። ከጥፋት ውኃ የተረፉት በወቅቱ ብዙኃኑ ይከተለው የነበረውን አኗኗር ያልተከተሉት ቅን ሰዎች ብቻ ናቸው። መለኮታዊውን ማስጠንቀቂያ ሰምተው ራሳቸውን በጊዜው ከነበረው ክፉ ዓለም ለይተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ። በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ . . . ከበደል የራቀ ሰው ነበር” ይላል። (ዘፍጥረት 6:8, 9 አ.መ.ት) ከመላው የሰው ዘር መካከል አንድ ቤተሰብ ብቻ ይኸውም ‘ጥቂቶች ማለትም ስምንት ነፍስ ከውኃ ድነዋል።’ (1 ጴጥሮስ 3:20) ለእነርሱም ይሖዋ አምላክ “ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት” የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው።—ዘፍጥረት 9:1
20 የአምላክ ቃል “ከታላቁ መከራ” የሚተርፉ “እጅግ ብዙ ሰዎች” እንደሚኖሩ ያረጋግጥልናል። (ራእይ 7:9, 14) እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች በቁጥር ምን ያህል ይሆናሉ? ኢየሱስ ራሱ “ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:13, 14) በአሁኑ ወቅት በምድር ላይ ከሚኖሩት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አንጻር ከታላቁ መከራ የሚተርፉት ቁጥራቸው ጥቂት ይሆናል። ሆኖም በኖኅ ዘመን ከመጣው የጥፋት ውኃ ለተረፉ ሰዎች የተሰጠው ዓይነት መብት ለእነዚህም ይሰጣቸዋል። በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች የአዲሱ ምድራዊ ኅብረተሰብ አባላት የሚሆኑ ልጆችን ለተወሰነ ጊዜ መውለድ ይችላሉ።—ኢሳይያስ 65:23
“ነቅታችሁ ጠብቁ”
21, 22. (ሀ) በኖኅ ዘመን ስለደረሰው የጥፋት ውኃ መመርመራችን ምን ጥቅም አስገኝቶልሃል? (ለ) የ2004 የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው? የዓመቱ ጥቅስ የያዘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚኖርብንስ ለምንድን ነው?
21 የኖኅ የጥፋት ውኃ ካለፈ ዘመናት የተቆጠሩ ቢሆንም ፈጽሞ ችላ ልንለው የማይገባን ግልጽ ማስጠንቀቂያ ይዞልናል። (ሮሜ 15:4) የኖኅ ዘመንና የምንኖርበት ጊዜ ያላቸው ተመሳሳይነት በጊዜያችን እየተፈጸሙ ያሉ ነገሮች ያላቸውን ትርጉም እንድንገነዘብና ኢየሱስ በክፉዎች ላይ ፍርዱን ለማስፈጸም እንደሌባ ሆኖ በሚመጣበት ጊዜ ነቅተን እንድንገኝ ሊያደርገን ይገባል።
22 በዛሬው ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈሳዊ ታላቅ የግንባታ ሥራ እያከናወነ ነው። እውነተኛ አምላኪዎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ በሕይወት እንዲተርፉ ለማስቻል መርከብ መሰል መንፈሳዊ ገነት ተዘጋጅቷል። (2 ቆሮንቶስ 12:3, 4) ታላቁን መከራ በሕይወት ለማለፍ በዚህ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ መቆየት ይኖርብናል። ይህን መንፈሳዊ ገነት የከበበው በመንፈሳዊ ያሸለቡትን ለመዋጥ ተዘጋጅቶ የሚጠባበቀው የሰይጣን ዓለም ነው። በመሆኑም ንቁ መሆናችንና የይሖዋን ቀን ተዘጋጅተን መጠበቃችን በጣም አስፈላጊ ነው።—ማቴዎስ 24:42, 44
ታስታውሳለህ?
• ኢየሱስ የሚመጣበትን ጊዜ በሚመለከት ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል?
• ኢየሱስ የሚመጣበትን ጊዜ ያወዳደረው ከየትኛው ዘመን ጋር ነው?
• የምንኖርበትን ጊዜ ከኖኅ ዘመን ጋር የሚያመሳስሉት ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?
• የምንኖርበት ጊዜ ከኖኅ ዘመን ጋር በሚመሳሰልባቸው ነጥቦች ላይ ማሰላሰላችን የጊዜውን አጣዳፊነት እንድንገነዘብ የሚያደርገን እንዴት ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የ2004 የዓመት ጥቅስ “ንቁ . . . ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” የሚል ነው።—ማቴዎስ 24:42, 44
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኖኅ መለኮታዊውን ማስጠንቀቂያ ሰምቶ እርምጃ ወስዷል። እኛስ?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና”