ገርነት—ጥበብ የሚንጸባረቅበት ጎዳና
ለአረጋውያን እንክብካቤ የምትሰጠው አንቶኒያ፣ ለሥራ የሄደችበትን ቤት ደወል ስትደውል በ50ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ሴት በሩን ከፈተች። ከዚያም ሴትየዋ፣ አረጋዊት እናቷን ለመንከባከብ አንቶኒያ ቀደም ብላ ባለመምጣቷ ኃይለ ቃል ተናገረቻት፤ እንዲሁም ሰደበቻት። አንቶኒያ ወደ ሥራዋ የመጣችው አርፍዳ ባይሆንም ስለተፈጠረው አለመግባባት ሴትየዋን ረጋ ብላ ይቅርታ ጠየቀቻት።
አንቶኒያ በቀጣዩ ጊዜ ወደዚያ ቤት ስትሄድም ሴትየዋ በድጋሚ ጮኸችባት። አንቶኒያ ምን ዓይነት ምላሽ ሰጠች? “እርግጥ ሁኔታው በጣም ከባድ ነበር። እንደዚያ እንድትሰድበኝ የሚያደርግ ምንም ምክንያት አልነበረም” በማለት ተናግራለች። ሆኖም አንቶኒያ በድጋሚ ይቅርታ የጠየቀች ሲሆን ሴትየዋ ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ እንደምትረዳላት ገለጸች።
አንተ በአንቶኒያ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ምላሽ የምትሰጥ ይመስልሃል? ገርነት ለማሳየት ይኸውም የለዘበ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ታደርግ ነበር? ወይስ ቁጣህን ለመቆጣጠር ትቸገር ነበር? እርግጥ፣ ከላይ እንደተጠቀሰው ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ መረጋጋት ቀላል እንዳልሆነ አይካድም። ውጥረት ውስጥ ስንሆን ወይም የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥመን ገርነት ማሳየት በጣም ከባድ ነው።
ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቲያኖች የገርነት መንፈስ እንዲያንጸባርቁ በሌላ አባባል ልዝብና ለስላሳ እንዲሆኑ ያበረታታል። እንዲያውም የአምላክ ቃል ይህ ባሕርይ ከጥበብ ጋር ተያያዥነት እንዳለው ይገልጻል። ያዕቆብ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ከእናንተ መካከል ጥበበኛና አስተዋይ ሰው ማን ነው? ሥራውን የሚያከናውነው ከጥበብ በመነጨ ገርነት መሆኑን በመልካም ምግባሩ ያሳይ።” (ያዕ. 3:13 ግርጌ) ገርነት ከሰማይ የሆነው ጥበብ መገለጫ የሆነው በምን መንገድ ነው? ይህን አምላካዊ ባሕርይ ለማዳበርስ ምን ሊረዳን ይችላል?
የገርነት መንፈስ ማሳየት ጥበብ ነው
ገርነት ማሳየት ወይም የለዘበ ምላሽ መስጠት ውጥረትን ያረግባል። “የለዘበ መልስ ቁጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቁጣን ያነሳሳል።”—ምሳሌ 15:1
አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ በቁጣ ምላሽ መስጠት በእሳት ላይ ጭድ እንደመጨመር ስለሚሆን ነገሩን ያባብሰዋል። (ምሳሌ 26:21) በአንጻሩ ግን፣ የለዘበ ምላሽ ሁኔታው እንዲረጋጋ ያደርጋል። እንዲህ ዓይነት ምላሽ፣ በጣም የተበሳጨ ሰውም እንኳ ረገብ እንዲል ሊያደርግ ይችላል።
አንቶኒያ የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት ተመልክታለች። አንቶኒያ በለዘበ መንገድ ምላሽ ስትሰጣት ሴትየዋ ማልቀስ ጀመረች። በግል ሕይወቷና በቤተሰቧ ውስጥ ብዙ ችግሮች እንደገጠሟት ገለጸች። አንቶኒያ ጥሩ ምሥክርነት መስጠት የቻለች ሲሆን ሴትየዋ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች፤ ይህ ሊሆን የቻለው አንቶኒያ በተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ስላነጋገረቻት ነው።
ገርነት ደስታ ያስገኛል። “ገሮች ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።”—ማቴ. 5:5
ገሮች ደስተኞች የሆኑት ለምንድን ነው? ቁጡ የነበሩ ብዙ ሰዎች ገርነትን በማዳበራቸው ደስተኞች ሆነዋል። የተሻለ ሕይወት መምራት ከመቻላቸውም ሌላ አስደናቂ ተስፋ እንዳላቸው ያውቃሉ። (ቆላ. 3:12) በስፔን የሚኖር አዶልፎ የተባለ የወረዳ የበላይ ተመልካች ወደ እውነት ከመምጣቱ በፊት ሕይወቱ ምን ይመስል እንደነበረ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦
“ሕይወቴ ምንም ዓላማ አልነበረውም። ትዕቢተኛና ግልፍተኛ በመሆኔ አንዳንድ ጓደኞቼ እንኳ ይፈሩኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ሕይወቴን የሚቀይር ነገር ተፈጠረ። በአንድ ወቅት በተፈጠረ ጠብ ስድስት ቦታ በጩቤ ተወጋሁ፤ ብዙ ደም ስለፈሰሰኝ ሕይወቴ አደጋ ላይ ወድቆ ነበር።”
አሁን ግን አዶልፎ ሌሎች ገርነት እንዲያንጸባርቁ በንግግሩም ሆነ በተግባሩ ለማስተማር ይጥራል። ወዳጃዊ መንፈስና ደስ የሚል ባሕርይ ስላለው ብዙዎች ይቀርቡታል። አዶልፎ እንዲህ ዓይነት ለውጥ በማድረጉ ደስተኛ እንደሆነ ይናገራል። በተጨማሪም ይሖዋ ገርነትን እንዲያዳብር ስለረዳው አመስጋኝ ነው።
ገርነት ይሖዋን ያስደስተዋል። “ልጄ ሆይ፣ ለሚነቅፈኝ መልስ መስጠት እችል ዘንድ ጥበበኛ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኘው።”—ምሳሌ 27:11
ይሖዋ፣ ዋነኛ ጠላቱ ከሆነው ከዲያብሎስ ነቀፋ እየተሰነዘረበት ነው። ዲያብሎስ የሚሰነዝረው ስድብ አምላክን ሊያስቆጣው የሚችል ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ይሖዋ “ለቁጣ የዘገየ” ነው። (ዘፀ. 34:6) ለቁጣ የዘገየንና ገሮች በመሆን አምላክን የምንመስል ከሆነ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ጎዳና የምንከተል ሲሆን ይህም ይሖዋን በእጅጉ ያስደስተዋል።—ኤፌ. 5:1
የምንኖርበት ዓለም መጥፎ ባሕርይ ባላቸው ሰዎች የተሞላ ነው። አብዛኞቹ ሰዎች “ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ . . . ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ [እና] ጨካኞች” ናቸው፤ በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ያላቸው ሰዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። (2 ጢሞ. 3:2, 3) ያም ቢሆን አንድ ክርስቲያን የገርነት መንፈስ እንዳያሳይ ይህ ምክንያት ሊሆነው አይገባም። የአምላክ ቃል ‘ከሰማይ የሆነው ጥበብ ሰላማዊና ምክንያታዊ’ እንደሆነ ይናገራል። (ያዕ. 3:17) እኛም ሰላማዊና ምክንያታዊ ከሆንን አምላካዊ ጥበብ እንዳለን እናሳያለን። እንዲህ ያለው ጥበብ፣ የሚያበሳጭ ሁኔታ ሲያጋጥመን ገርነት የሚንጸባረቅበት ወይም የለዘበ ምላሽ እንድንሰጥ የሚያነሳሳን ከመሆኑም ሌላ ወደር የሌለው ጥበብ ምንጭ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል።