ታማኙ መጋቢና የበላይ አካሉ
“ጌታው የሚያስፈልጋቸውን በቂ ምግብ በተገቢው ጊዜ እንዲሰጣቸው በአገልጋዮቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም መጋቢ በእርግጥ ማን ነው?”—ሉቃስ 12:42
1, 2. ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት ምልክት ሲናገር የትኛውን አስፈላጊ ጥያቄ አንስቶ ነበር?
ኢየሱስ፣ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት ምልክት ሲናገር እንደሚከተለው በማለት ጠይቆ ነበር፦ “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ጌታው በአገልጋዮቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?” ኢየሱስ በመቀጠል እንደተናገረው ይህ ባሪያ ታማኝ ሆኖ በመገኘቱ ጌታው በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል።—ማቴ. 24:45-47
2 ኢየሱስ ከላይ ያለውን ከመናገሩ ከተወሰኑ ወራት በፊት ተመሳሳይ ጥያቄ አንስቶ ነበር። (ሉቃስ 12:42-44ን አንብብ።) በዚያ ወቅት ባሪያውን “መጋቢ” ብሎ ጠርቶታል። መጋቢ የሚለው ቃል በባሪያዎች ላይ የተሾመ የቤት አስተዳዳሪን ያመለክታል። ያም ቢሆን መጋቢው ራሱ ባሪያ ነው። ታዲያ ይህ ባሪያ ወይም መጋቢ ማን ነው? ‘በተገቢው ጊዜ ምግብ’ የሚያቀርበውስ እንዴት ነው? ሁላችንም ብንሆን ይሖዋ፣ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ የሚጠቀምበትን አካል ለይተን ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው።
3. (ሀ) የሕዝበ ክርስትና ምሑራን፣ ኢየሱስ ስለ ‘ባሪያው’ የተናገረውን ሐሳብ የሚያብራሩት በምን መንገድ ነው? (ለ) “መጋቢ” ወይም “ባሪያ” የተባለው ማን ነው? “አገልጋዮቹ” የተባሉትስ እነማን ናቸው?
3 አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና ምሑራን፣ ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ክርስቲያን ነን በሚሉ ሰዎች መካከል የሚገኙ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎችን እንደሚያመለክት ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው “ጌታ” ማለትም ኢየሱስ፣ በተለያዩ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ውስጥ ተሰበጣጥረው የሚገኙ በርካታ ባሪያዎች እንደሚኖሩ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ በንብረቱ ሁሉ ላይ የሚሾመው “መጋቢ” ወይም “ባሪያ” አንድ ብቻ እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። በመሆኑም ይህ መጽሔት በተደጋጋሚ ጊዜያት እንዳብራራው መጋቢው፣ “ትንሽ መንጋ” ተብለው የተጠሩትን ቅቡዓን ደቀ መዛሙርት በቡድን ደረጃ የሚያመለክት መሆን አለበት። ሉቃስ ባሰፈረው የወንጌል ዘገባ ላይ ኢየሱስ ስለ መጋቢው ከመናገሩ ቀደም ብሎ ስለ ትንሹ መንጋ ጠቅሶ ነበር። (ሉቃስ 12:32) “አገልጋዮቹ” የሚለው አገላለጽም ይህንን ትንሽ መንጋ የሚያመለክት ሲሆን የዚህ ቡድን አባላት በግለሰብ ደረጃ ያላቸውን ሚና ያጎላል። እዚህ ላይ ትኩረት የሚስብ አንድ ጥያቄ ይነሳል፦ በባሪያው ቡድን ውስጥ የታቀፉት ሁሉም ሰዎች በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ ረገድ በግለሰብ ደረጃ የሚጫወቱት ሚና ይኖራል? ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥልቀት ስንመረምር መልሱ ግልጽ ይሆንልናል።
በጥንት ዘመን የነበረው የይሖዋ ባሪያ
4. ይሖዋ፣ የጥንቱን የእስራኤል ብሔር ምን በማለት ጠርቶታል? ከዚህ ብሔር ጋር በተያያዘ ልብ ልንለው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
4 ይሖዋ፣ ሕዝቡ የነበረውን የጥንቱን የእስራኤል ብሔር እንደ አንድ ባሪያ አድርጎ ገልጾታል። እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ ምስክሮቼ፣ የመረጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ።” (ኢሳ. 43:10) እዚህ ላይ የተገለጸው ባሪያ፣ የብሔሩን አባላት በሙሉ ያቀፈ ነበር። ይሁን እንጂ ብሔሩን የማስተማር ኃላፊነት የተጣለባቸው ካህናቱና ካህናት ያልነበሩት ሌዋውያን ብቻ እንደነበሩ ልብ ልንል ይገባል።—2 ዜና 35:3፤ ሚል. 2:7
5. ኢየሱስ ምን ታላቅ ለውጥ እንደሚከናወን ተናግሮ ነበር?
5 ኢየሱስ የጠቀሰው ባሪያ የእስራኤል ብሔር ነበር? አልነበረም። ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩት አይሁዳውያን የተናገረው ሐሳብ ይህንን ለማወቅ ያስችለናል፤ “የአምላክ መንግሥት ከእናንተ ተወስዶ ፍሬውን ለሚያፈራ ሕዝብ ይሰጣል” ብሏቸው ነበር። (ማቴ. 21:43) በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ይሖዋ ለውጥ ሊያካሂድ ነበር። በሌላ አባባል በአዲስ ብሔር ሊጠቀም ነበር። ያም ቢሆን መንፈሳዊ ትምህርት በመስጠት ረገድ፣ ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው ባሪያ የሚያከናውነው ሥራ በጥንቷ እስራኤል የነበረው የአምላክ “ባሪያ” ከሚያከናውነው ተግባር ጋር ይመሳሰላል።
ታማኙ ባሪያ ታወቀ
6. በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት የተቋቋመው የትኛው አዲስ ብሔር ነው? በዚህ ብሔር ውስጥ የተካተቱት እነማን ናቸው?
6 አዲሱ ብሔር ማለትም ‘የአምላክ እስራኤል’ መንፈሳዊ እስራኤላውያንን ያቀፈ ነው። (ገላ. 6:16፤ ሮም 2:28, 29፤ 9:6) ይህ ብሔር የተቋቋመው የአምላክ መንፈስ በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት በደቀ መዛሙርት ላይ በፈሰሰበት ወቅት ነበር። ከዚህ ጊዜ በኋላ፣ በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች በሙሉ በጌታው ማለትም በኢየሱስ ክርስቶስ የተሾመ ባሪያ ሆኖ በአሁኑ ጊዜ የሚያገለግለው ብሔር አባላት ሆኑ። እያንዳንዱ የዚህ ብሔር አባል ምሥራቹን የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ተልዕኮ ተሰጥቶት ነበር። (ማቴ. 28:19, 20) ይሁን እንጂ እያንዳንዱ የዚህ ቡድን አባል በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረቡ ሥራ መካፈል ይኖርበታል ማለት ነው? ቅዱሳን መጻሕፍት ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡትን መልስ እስቲ እንመልከት።
7. መጀመሪያ ላይ የሐዋርያት ዋነኛ ሥራ ምን ነበር? ከጊዜ በኋላስ ምን ተጨማሪ ተልዕኮ ተሰጣቸው?
7 ኢየሱስ 12ቱን ሐዋርያት ሲሾም ዋነኛ ዓላማው ምሥራቹን ለሰዎች ለመስበክ እንዲልካቸው ነበር። (ማርቆስ 3:13-15ን አንብብ።) ይህ ተልዕኮ ሐዋርያ ተብሎ ከተተረጎመው አፖስቶሎስ ከሚለው የግሪክኛ ቃል መሠረታዊ ፍቺ ጋር የሚስማማ ነው፤ ቃሉ “መላክ” የሚል ትርጉም ካለው ግስ የመጣ ነው። ከጊዜ በኋላ ግን ሐዋርያት ተጨማሪ ተልዕኮ ተሰጣቸው፤ የክርስቲያን ጉባኤ ከመቋቋሙ ትንሽ ቀደም ብሎ የሐዋርያት ተልዕኮ ‘የበላይ ተመልካችነት ኃላፊነትንም’ የሚያካትት ሆነ።—ሥራ 1:20-26
8, 9. (ሀ) አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በዋነኝነት ትኩረት ያደረጉት በምን ላይ ነበር? (ለ) ተጨማሪ ኃላፊነት የተሰጣቸው እነማን ናቸው?
8 አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በዋነኝነት ትኩረት ያደረጉት በምን ላይ ነበር? ከጴንጤቆስጤ ዕለት በኋላ የተከናወኑትን ነገሮች መመልከታችን ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ይረዳናል። በየዕለቱ ከሚከናወነው ለመበለቶች ምግብ የማከፋፈል ሥራ ጋር በተያያዘ አለመግባባት በተፈጠረበት ወቅት 12ቱ ሐዋርያት ደቀ መዛሙርትን ሰብስበው “በማዕድ ምግብ ለማከፋፈል ስንል የአምላክን ቃል የማስተማር ሥራችንን ብንተው ተገቢ አይሆንም” አሏቸው። (የሐዋርያት ሥራ 6:1-6ን አንብብ።) ከዚያም ሐዋርያት፣ ይህንን “አስፈላጊ ሥራ” እንዲያከናውኑ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ሌሎች ወንድሞችን ሾሙ፤ ይህንንም ያደረጉት እነሱ “ቃሉን በማስተማሩ ሥራ ላይ ሙሉ በሙሉ [ለማተኮር]” ሲሉ ነበር። እንዲህ ዓይነት ዝግጅት መደረጉ የይሖዋን በረከት አስገኝቷል፤ ዘገባው “የአምላክ ቃል እያደገ ሄደ፤ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሄደ” ይላል። (ሥራ 6:7) በመሆኑም መንፈሳዊ ምግብ የማቅረቡን ሥራ በዋነኝነት የሚያከናውኑት ሐዋርያት ነበሩ።—ሥራ 2:42
9 ከጊዜ በኋላ ሌሎች ክርስቲያኖችም ከበድ ያሉ ኃላፊነቶች ተሰጧቸው ነበር። በአንጾኪያ የሚገኘው ጉባኤ በመንፈስ ቅዱስ በመመራት ጳውሎስና በርናባስን በሚስዮናዊነት እንዲያገለግሉ ልኳቸዋል። ጳውሎስና በርናባስም ከመጀመሪያዎቹ 12 ሐዋርያት መካከል ባይሆኑም ሐዋርያት ተብለው ተጠርተዋል። (ሥራ 13:1-3፤ 14:14፤ ገላ. 1:19) በኢየሩሳሌም የሚገኘው የበላይ አካልም የእነሱን ሹመት ተቀብሎታል። (ገላ. 2:7-10) ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረቡ ሥራ መካፈል የጀመረ ሲሆን በመንፈስ መሪነት ከጻፋቸው ደብዳቤዎች የመጀመሪያውን ጽፏል።
10. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በሙሉ መንፈሳዊ ምግብ በማዘጋጀቱ ሥራ ይካፈሉ ነበር? አብራራ።
10 ይሁን እንጂ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በሙሉ የስብከቱን ሥራ በበላይነት በመምራቱና መንፈሳዊ ምግብ በማዘጋጀቱ ሥራ ይካፈሉ ነበር? አልነበረም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉም ሐዋርያት አይደሉም፤ ናቸው እንዴ? ሁሉም ነቢያት አይደሉም፤ ናቸው እንዴ? ሁሉም አስተማሪዎች አይደሉም፤ ናቸው እንዴ? ሁሉም ተአምር አይሠሩም፤ ይሠራሉ እንዴ?” (1 ቆሮ. 12:29) በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በሙሉ በስብከቱ ሥራ ቢካፈሉም 27ቱን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የጻፉት ግን ስምንት ሰዎች ብቻ ናቸው።
በዘመናችን የሚገኘው ታማኝ ባሪያ
11. ባሪያው የተሾመው በየትኛው የጌታው ‘ንብረት’ ላይ ነው?
11 ኢየሱስ በማቴዎስ 24:45 ላይ የተናገረው ሐሳብ በግልጽ እንደሚጠቁመው በመጨረሻዎቹ ቀኖችም በምድር ላይ የታማኝና ልባም ባሪያ ቡድን ይኖራል። ራእይ 12:17 የዚህን ቡድን አባላት ከሴቲቱ ዘር “የቀሩ” በማለት ጠርቷቸዋል። በቡድን ደረጃ እነዚህ ቀሪዎች በምድር ላይ ባለው የክርስቶስ ንብረት ሁሉ ላይ ተሹመዋል። ታማኙ መጋቢ እንዲንከባከበው በኃላፊነት የተሰጠው ‘ንብረት’፣ የንጉሡን ምድራዊ ተገዢዎችና ምሥራቹን ለመስበክ የሚያገለግሉትን ቁሳዊ ንብረቶች ያካትታል።
12, 13. አንድ ክርስቲያን ሰማያዊ ጥሪ እንዳገኘ የሚያውቀው እንዴት ነው?
12 አንድ ክርስቲያን፣ ሰማያዊ ተስፋ እንዳለውና የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች አባል እንደሆነ የሚያውቀው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ እሱው ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ላላቸው ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ መልሱን ይሰጠናል፤ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “በአምላክ መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የአምላክ ልጆች ናቸውና። እንደገና ለፍርሃት የሚዳርጋችሁን የባርነት መንፈስ አልተቀበላችሁም፤ ከዚህ ይልቅ እንደ ልጅ የመቆጠር መብት የሚያስገኝ መንፈስ ተቀብላችኋል፤ ይህም መንፈስ ‘አባ፣ አባት!’ ብለን እንድንጣራ ይገፋፋናል። የአምላክ ልጆች መሆናችንን ይህ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሠክራል። እንግዲህ ልጆች ከሆንን ወራሾች ይኸውም የአምላክ ወራሾች ነን፤ ይሁንና የምንወርሰው ከክርስቶስ ጋር ነው፤ አሁን አብረነው መከራ ከተቀበልን፣ በኋላ ደግሞ አብረነው ክብር እንጎናጸፋለን።”—ሮም 8:14-17
13 በቀላል አነጋገር እነዚህ ግለሰቦች የሚቀቡት በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ሲሆን ሰማያዊ “ጥሪ” ያገኛሉ። (ዕብ. 3:1) በግለሰብ ደረጃ እንዲህ ያለ ጥሪ የሚያቀርብላቸው አምላክ ነው። እነሱም የአምላክ ልጆች ሆነው መቆጠራቸውን ምንም ሳይጠራጠሩ ወይም እንዲህ ዓይነት መብት በማግኘታቸው ሳይፈሩ ይህን ጥሪ ይቀበላሉ። (1 ዮሐንስ 2:20, 21ን አንብብ።) በመሆኑም ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ራሳቸው የሚመርጡት ነገር አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ማኅተም የሚያደርግባቸው ወይም በመንፈስ ቅዱስ የሚቀባቸው ይሖዋ ነው።—2 ቆሮ. 1:21, 22፤ 1 ጴጥ. 1:3, 4
ተገቢ የሆነው አመለካከት
14. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለቀረበላቸው ጥሪ ምን አመለካከት አላቸው?
14 እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ሽልማታቸውን እየተጠባበቁ ባሉበት ጊዜ ለራሳቸው ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? የቀረበላቸው ጥሪ አስደናቂ ቢሆንም ሽልማታቸውን ገና እንዳላገኙ ይገነዘባሉ። ሽልማታቸውን ለማግኘት እስከ ሞት ድረስ ታማኝ በመሆን መጽናት ይኖርባቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ትሑቶች በመሆን እንደሚከተለው በማለት የተናገረውን የጳውሎስን ሐሳብ ይጋራሉ፦ “ወንድሞች፣ እኔ ገና እንደያዝኩት አድርጌ ራሴን አልቆጥርም፤ ነገር ግን አንድ የማደርገው ነገር አለ:- ከኋላዬ ያሉትን ነገሮች እየረሳሁ ከፊቴ ወዳሉት ነገሮች እንጠራራለሁ፤ አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የሚሰጠውን የላይኛውን ጥሪ ሽልማት አገኝ ዘንድ ግቡ ላይ ለመድረስ እየተጣጣርኩ ነው።” (ፊልጵ. 3:13, 14) ቅቡዓን ቀሪዎች ‘ከተጠሩበት ጥሪ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ለመመላለስና በፍጹም ትሕትና’ ለመኖር “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ” የተቻላቸውን ሁሉ ሊያደርጉ ይገባል።—ኤፌ. 4:1, 2፤ ፊልጵ. 2:12፤ 1 ተሰ. 2:12
15. ክርስቲያኖች፣ በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይኑ ለሚካፈሉ ሰዎች ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? ቅቡዓን ክርስቲያኖችስ ለራሳቸው ምን አመለካከት አላቸው?
15 በሌላ በኩል ደግሞ፣ አንድ ሰው በመንፈስ እንደተቀባ ቢናገርና በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይኑ ቢካፈል ሌሎች ክርስቲያኖች ለግለሰቡ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? በግለሰቡ ላይ መፍረድ አይኖርባቸውም። ይህ በግለሰቡና በይሖዋ መካከል ያለ ጉዳይ ነው። (ሮም 14:12) ይሁንና እውነተኛ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለየት ያለ ትኩረት እንዲሰጣቸው አይጠይቁም። በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በመሆናቸው ተሞክሮ ካካበቱ ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት እንኳ የበለጠ ማስተዋል እንደሚያገኙ አይሰማቸውም። (ራእይ 7:9) እነዚህ ክርስቲያኖች የተቀቡ ስለሆኑ ብቻ ‘የሌሎች በጎች’ አባላት ከሆኑ ባልንጀሮቻቸው የበለጠ መንፈስ ቅዱስ እንዳላቸው አያስቡም። (ዮሐንስ 10:16) እንዲሁም ለየት ያለ አክብሮት እንዲሰጣቸው አይፈልጉም፤ ከዚህም በላይ ከቂጣና ከወይኑ ስለሚካፈሉ በጉባኤ ውስጥ ካሉ የተሾሙ ሽማግሌዎች እንደሚበልጡ አይናገሩም።
16-18. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ አዳዲስ መንፈሳዊ እውነቶችን በመግለጥ ረገድ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ? በምሳሌ አስረዳ። (ለ) የበላይ አካሉ፣ ቅቡዓን ነን የሚሉ ክርስቲያኖችን በሙሉ ማማከር የማያስፈልገው ለምንድን ነው?
16 በምድር ዙሪያ የሚገኙት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ እርስ በርስ እየተወያዩ አዳዲስ መንፈሳዊ እውነቶችን ይገልጣሉ ማለት ነው? አይደለም። በቡድን ደረጃ ታማኙ ባሪያ፣ ለተቀቡ የክርስቶስ ተከታዮች መንፈሳዊ ምግብ የማቅረብ ኃላፊነት ቢኖርበትም የታማኙ ባሪያ አባላት በሙሉ ተመሳሳይ ኃላፊነት ወይም የሥራ ምድብ ይኖራቸዋል ማለት አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 12:14-18ን አንብብ።) ቀደም ብሎ እንደተገለጸው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ በጣም አስፈላጊ በሆነው የስብከት ሥራ ይካፈሉ ነበር። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑ መጻሕፍትን የጻፉት እንዲሁም የክርስቲያን ጉባኤን ይመሩ የነበሩት በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው።
17 ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ቅዱሳን መጻሕፍት “ጉባኤው” ከፍርድ ነክ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ እርምጃ እንደወሰደ የሚናገሩበት ጊዜ አለ። (ማቴ. 18:17) እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ጉባኤውን በመወከል እርምጃውን የወሰዱት ሽማግሌዎች ናቸው። ሽማግሌዎቹ ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት የጉባኤ አባላት ስለ ጉዳዩ ያላቸውን አመለካከት ለማወቅ እያንዳንዳቸውን አያማክሯቸውም። ከዚህ ይልቅ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ ይወጣሉ፤ መላውን ጉባኤ በመወከል ውሳኔ ያደርጋሉ።
18 በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የባሪያውን ቡድን ወክለው የሚያገለግሉት የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ቅቡዓን ወንድሞች ናቸው። እነዚህ ወንድሞች የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ሆነው ያገለግላሉ። በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት እነዚህ ወንድሞች ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችንና መንፈሳዊ ምግብ የማቅረቡን ሥራ በበላይነት ይከታተላሉ። ሆኖም የበላይ አካሉ አንድ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት እያንዳንዱን የባሪያው ቡድን አባል አያማክርም፤ ይህም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው አሠራር ጋር የሚመሳሰል ነው። (የሐዋርያት ሥራ 16:4, 5ን አንብብ።) ይሁንና ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች በአሁኑ ጊዜ እየተከናወነ ባለው በጣም አስፈላጊ የሆነ የመከር ሥራ ሙሉ ተሳትፎ ያደርጋሉ። “ታማኝና ልባም ባሪያ” በቡድን ደረጃ አንድ አካል ቢሆንም አባላቱ በግለሰብ ደረጃ የተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አሏቸው።—1 ቆሮ. 12:19-26
19, 20. እጅግ ብዙ ሕዝቦች፣ ስለ “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንዲሁም ስለ በላይ አካሉ ምን ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?
19 ቁጥራቸው እየጨመረ ያለው በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው እጅግ ብዙ ሕዝቦች፣ ከላይ ከተብራሩት ነጥቦች አንጻር ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? እነዚህ ክርስቲያኖች ከንጉሡ ንብረቶች መካከል የሚቆጠሩ እንደመሆናቸው መጠን ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ የሚወክለው የበላይ አካል የሚያደርጋቸውን ዝግጅቶች በሙሉ በደስታ ይደግፋሉ። የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት፣ በበላይ አካሉ አመራር ለሚዘጋጀው መንፈሳዊ ምግብ አድናቆት አላቸው። የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት፣ ታማኙን ባሪያ በቡድን ደረጃ ቢያከብሩትም የዚህ ባሪያ አባል እንደሆነ ለሚናገር ለማንኛውም ግለሰብ ከመጠን ያለፈ አክብሮት ላለመስጠት ይጠነቀቃሉ። እውነተኛ ቅቡዕ ክርስቲያን እንዲህ ያለ አክብሮት እንዲሰጠው አይፈልግም ወይም አይጠብቅም።—ሥራ 10:25, 26፤ 14:14, 15
20 ‘አገልጋዮች’ ተብለው የተገለጹት የቅቡዓን ቀሪዎች ክፍልም ሆንን የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት፣ ከታማኙ መጋቢና ከበላይ አካሉ ጋር ሙሉ በሙሉ ለመተባበር ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ሁላችንም ‘ምንጊዜም ነቅተን በመጠበቅ’ እስከ መጨረሻው ታማኝ እንሁን።—ማቴ. 24:13, 42
ታስታውሳለህ?
• “ታማኝና ልባም ባሪያ” ማን ነው? አገልጋዮች የተባሉትስ እነማን ናቸው?
• አንድ ክርስቲያን፣ ሰማያዊ ጥሪ እንዳለው የሚያውቀው እንዴት ነው?
• አዳዲስ መንፈሳዊ እውነቶችን መግለጥ በዋነኝነት የማን ኃላፊነት ነው?
• ቅቡዕ የሆነ አንድ ክርስቲያን ለራሱ ምን አመለካከት ሊኖረው ይገባል?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ ያለው የበላይ አካል ታማኝና ልባም ባሪያን ይወክላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ተመሳሳይ አሠራር ነበር