ታማኝ እና ልባም የሆነ “ባሪያ”
“እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው?”—ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም
1, 2. በጊዜያችን መንፈሳዊ ምግብ በቋሚነት ማግኘታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ኒሳን 11, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ኢየሱስ “የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” የሚል ለጊዜያችን ትልቅ ትርጉም ያለው ጥያቄ ከደቀ መዛሙርቱ ቀረበለት። ለጥያቄው መልስ ሲሰጥ ከባባድ ጦርነቶች፣ ረሃብ፣ የመሬት መንቀጥቀጥና ቸነፈር እንደሚኖር የሚጠቁም አንድ ልዩ ትንቢት ተናገረ። ይህ ሁሉ ግን “የምጡ መጀመሪያ” ብቻ ነው። ሁኔታው ከዚህም እየከፋ ይሄዳል። መጪው ጊዜ ምንኛ አስፈሪ ነው!—ማቴዎስ 24:3, 7, 8, 15-22፤ ሉቃስ 21:10, 11
2 ኢየሱስ የተናገረው ይህ ትንቢት ከ1914 ወዲህ በአብዛኛው ተፈጽሟል። ‘ምጡ’ ይበልጥ እየተፋፋመ መጥቷል። ቢሆንም እውነተኛ ክርስቲያኖች ይህ ሁኔታ ሊያስፈራቸው አይገባም። ኢየሱስ ገንቢ መንፈሳዊ ምግብ እንደሚያቀርብላቸው ቃል ገብቶላቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ ያለው በሰማይ ስለሆነ በምድር ላይ ላለነው መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብልን እንዴት ነው?
3. ኢየሱስ ‘በጊዜው ምግብ’ እንድናገኝ ምን ዝግጅት አድርጎልናል?
3 የዚህን ጥያቄ መልስ ኢየሱስ ራሱ ጠቁሞናል። ከላይ ያለውን ታላቅ ትንቢት በተናገረበት ወቅት እንዲህ በማለት ጠይቆ ነበር፦ “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው?” ከዚያም እንዲህ አለ፦ “ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፣ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል።” (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም) አዎን፣ መንፈሳዊ ምግብ የማቅረብ ኃላፊነት የተጣለበት ታማኝ እና ልባም የሆነ “ባሪያ” ይኖራል። ይህ ባሪያ የሚያመለክተው አንድን ግለሰብ ወይም በየጊዜው የሚነሱ ሰዎችን ነው? ወይስ አንድን ቡድን? ይህ ታማኝ ባሪያ የሚያቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ በእጅጉ የሚያስፈልገን ስለሆነ ማንነቱን ለይተን ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው።
አንድ ግለሰብ ወይስ ቡድን?
4. ‘ታማኝና ልባሙ ባሪያ’ አንድ ግለሰብ ሊሆን እንደማይችል እንዴት እናውቃለን?
4 ይህ “ታማኝና ልባም ባሪያ” አንድ ግለሰብ ሊሆን አይችልም። ለምን? ምክንያቱም ባሪያው መንፈሳዊ ምግብ ማቅረብ የጀመረው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሲሆን ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ጌታው በ1914 በሚመጣበት ጊዜም ይህንኑ ኃላፊነቱን እየተወጣ መገኘት አለበት። በሌላ አባባል ባሪያው 1,900 ለሚያህሉ ዓመታት በታማኝነት እያገለገለ መቆየት አለበት ማለት ነው። ማቱሳላ እንኳን ይህን ያህል ረጅም ዕድሜ አልኖረም!—ዘፍጥረት 5:27
5. “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚለው አጠራር እያንዳንዱን ክርስቲያን የማያመለክተው ለምን እንደሆነ አብራራ።
5 ታዲያ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚለው አጠራር እያንዳንዱን ክርስቲያን የሚያመለክት ይሆን? ሁሉም ክርስቲያኖች ታማኝና ልባም መሆን እንደሚኖርባቸው እሙን ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ስለ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሲናገር በአእምሮው የያዘው ይህን አልነበረም። ይህን እንዴት እናውቃለን? ምክንያቱም ‘ጌታው በሚመጣበት ጊዜ’ ባሪያውን ‘ባለው ሁሉ ላይ እንደሚሾመው’ ኢየሱስ ተናግሯል። እያንዳንዱ ክርስቲያን በጌታው ንብረት “ሁሉ” ላይ እንዴት ሊሾም ይችላል? ይህ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም!
6. የእስራኤል ብሔር የአምላክ ‘ባሪያ’ የመሆን ዕድል ተከፍቶለት የነበረው እንዴት ነው?
6 እንግዲያው አሳማኝ የሚሆነው ኢየሱስ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሲል ስለ አንድ የክርስቲያኖች ቡድን እየተናገረ ነበር የሚለው መደምደሚያ ብቻ ነው። ታዲያ በርካታ ግለሰቦችን ባሪያ ብሎ በነጠላ ቁጥር መጥራት ይቻላል? አዎን። ክርስቶስ ከመወለዱ ከሰባት መቶ ዓመታት በፊት ይሖዋ መላውን የእስራኤል ብሔር “ምስክሮቼ” እና “የመረጥሁትም ባሪያዬ” በማለት ጠርቶት ነበር። (ኢሳይያስ 43:10) የሙሴ ሕግ ከተሰጠበት ከ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት አንስቶ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እስከተከበረው የጰንጠቆስጤ ዕለት ድረስ የነበረው እያንዳንዱ እስራኤላዊ የዚህ ባሪያ ክፍል ነበር። አብዛኞቹ እስራኤላውያን በአስተዳደርም ሆነ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረቡ ሥራ ቀጥተኛ ተሳትፎ አልነበራቸውም። ይሖዋ እነዚህን ኃላፊነቶች የሰጠው ለነገሥታት፣ ለመሳፍንት፣ ለነቢያት፣ ለካህናትና ለሌዋውያን ነበር። ያም ሆኖ ግን እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ የይሖዋ ሉዓላዊነት መገለጫ የነበሩ ሲሆን በአሕዛብ መካከል እርሱን የማወደስ መብት ነበራቸው። እያንዳንዱ እስራኤላዊ የይሖዋ ምሥክር እንዲሆን ይጠበቅበት ነበር።—ዘዳግም 26:19፤ ኢሳይያስ 43:21፤ ሚልክያስ 2:7፤ ሮሜ 3:1, 2
‘ባሪያው’ መብቱን አጣ
7. የጥንቱ የእስራኤል ብሔር የአምላክ ‘ባሪያ’ የመሆን መብቱን ያጣው ለምንድን ነው?
7 እስራኤላውያን ከብዙ ዘመናት በፊት የአምላክ ‘ባሪያ’ ከነበሩ ኢየሱስ ባሪያ ያለው እነርሱን ነበር? በፍጹም። ምክንያቱም የጥንቶቹ እስራኤላውያን ታማኝም ሆነ ልባም ሳይሆኑ ቀርተዋል። ጳውሎስ፣ ይሖዋ “በእናንተ ምክንያት የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ ዘንድ ይሰደባል” በማለት ለእስራኤላውያን የተናገረውን ሐሳብ በመጥቀስ ሁኔታውን ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል። (ሮሜ 2:24) አዎን፣ እስራኤላውያን ኢየሱስን አንቀበልም ባሉ ጊዜ ዓመጸኝነታቸው በግልጽ ታይቷል። ይሖዋም በዚህ ወቅት ትቷቸዋል።—ማቴዎስ 21:42, 43
8. እስራኤላውያንን የሚተካ “ባሪያ” የተሾመው መቼ ነው? እንዴት?
8 እስራኤላውያን ታማኝ ‘ባሪያ’ ሆነው አለመገኘታቸው የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ከዚያ በኋላ መንፈሳዊ ምግብ እስከ መጨረሻው አይቀርብላቸውም ማለት አይደለም። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ከ50 ቀናት በኋላ ማለትም በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተከበረው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም ፎቅ ላይ ባለ አንድ ክፍል ውስጥ ተሰብስበው በነበሩት 120 ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። በዚህ ወቅት አንድ አዲስ ብሔር ተወለደ። የዚህ አዲስ ብሔር መወለድ ይፋ የሆነው አባላቱ በኢየሩሳሌም “የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ” በድፍረት መናገር በጀመሩበት ጊዜ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:11) ይህ አዲስ መንፈሳዊ ብሔር የይሖዋን ክብር ለአሕዛብ የሚናገርና በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብ “ባሪያ” ሆነ። (1 ጴጥሮስ 2:9) ይህ “ባሪያ” ከጊዜ በኋላ ‘የአምላክ እስራኤል’ ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነው።—ገላትያ 6:16
9. (ሀ) “ታማኝና ልባም ባሪያ” ማን ነው? (ለ) ‘ቤተ ሰዎቹ’ የተባሉትስ እነማን ናቸው?
9 ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት በሙሉ ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው የተጠመቁና በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ሲሆኑ ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ያላቸው ናቸው። በመሆኑም ከ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት አንስቶ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እስከተከበረው የጰንጠቆስጤ ዕለት ድረስ የኖረው እያንዳንዱ እስራኤላዊ የባሪያው ክፍል እንደነበረ ሁሉ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚለውም አገላለጽ ከ33 አንስቶ እስከ ጊዜያችን ድረስ በምድር ላይ የኖሩትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ በቡድን ደረጃ ያመለክታል። ይሁን እንጂ ባሪያው የሚያቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ የሚመገቡት ‘ቤተ ሰዎች’ እነማን ናቸው? በመጀመሪያው መቶ ዘመን እያንዳንዱ ክርስቲያን ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ነበረው። በዚህም ምክንያት ቤተ ሰዎች የተባሉት እነዚሁ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በቡድን ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ሲታዩ ነው። በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ያላቸውን ጨምሮ ሁሉም ባሪያው የሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልጋቸው ነበር።—1 ቆሮንቶስ 12:12, 19-27፤ ዕብራውያን 5:11-13፤ 2 ጴጥሮስ 3:15, 16
እያንዳንዱ የራሱ የሥራ ድርሻ አለው
10, 11. ሁሉም የባሪያው ክፍል አባላት ተመሳሳይ የሥራ ድርሻ እንደማይኖራቸው እንዴት እናውቃለን?
10 ‘የአምላክ እስራኤል’ የተባለው ታማኝና ልባም ባሪያ በቡድን ደረጃ የሚያከናውነው ሥራ ቢኖረውም እያንዳንዱ አባል በግል የሚያከናውናቸው ኃላፊነቶች አሉት። በማርቆስ 13:34 [የ1954 ትርጉም] ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ይህን ግልጽ ያደርጉልናል። እንዲህ ብሎ ነበር፦ “[ይህም] ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደሄደ ሰው ነው፣ ለባሮቹም ሥልጣን ለእያንዳንዱም ሥራውን ሰጥቶ በረኛውን እንዲተጋ አዘዘ።” ስለዚህ እያንዳንዱ የባሪያው ክፍል አባል የክርስቶስ ምድራዊ ንብረት እየበዛ እንዲሄድ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎበታል። ይህን ኃላፊነቱን የሚወጣበት መንገድ የተመካው በችሎታውና በሚያገኘው አጋጣሚ ላይ ነው።—ማቴዎስ 25:14, 15 የ1954 ትርጉም
11 ከዚህም በላይ ሐዋርያው ጴጥሮስ በዘመኑ ለነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች “እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል” ብሏቸው ነበር። (1 ጴጥሮስ 4:10) በመሆኑም እነዚያ ቅቡዓን ክርስቲያኖች አምላክ የሰጣቸውን የጸጋ ስጦታ በመጠቀም አንዳቸው ሌላውን የማገልገል ኃላፊነት ነበራቸው። በተጨማሪም የጴጥሮስ ቃላት ሁሉም ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ችሎታ፣ ኃላፊነት ወይም መብት እንደማይኖራቸው ይጠቁማሉ። ይሁን እንጂ እያንዳንዱ የባሪያው ክፍል አባል ለመላው መንፈሳዊ ብሔር እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል። እንዴት?
12. ወንድ ሴት ሳይል እያንዳንዱ የባሪያው ክፍል አባል ለቡድኑ እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?
12 በመጀመሪያ ደረጃ እያንዳንዱ ቅቡዕ ክርስቲያን የመንግሥቱን ወንጌል በመስበክ ለይሖዋ የመመስከር ኃላፊነት አለበት። (ኢሳይያስ 43:10-12፤ ማቴዎስ 24:14) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ታማኝ ደቀ መዛሙርቱን በሙሉ ወንድ ሴት ሳይል አስተማሪዎች እንዲሆኑ አዟቸው ነበር። እንዲህ አለ፦ “ስለዚህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”—ማቴዎስ 28:19, 20
13. በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በሙሉ ምን መብት ነበራቸው?
13 አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ሲገኙ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ያዘዛቸውን ሁሉ እንዲጠብቁ በሚገባ ይማራሉ። ውሎ አድሮ ትምህርቱን የተቀበሉት ሌሎችን ለማስተማር ብቁ ይሆናሉ። በበርካታ አገሮች ለሚኖሩ የባሪያው ክፍል እጩ አባላት ገንቢ መንፈሳዊ ምግብ ይቀርብ ነበር። ወንድ ሴት ሳይል ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ይካፈሉ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:17, 18) ይህ ሥራ ባሪያው ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ድረስ የሚቀጥል ነው።
14. በጉባኤ ውስጥ የማስተማሩ ኃላፊነት የተሰጠው ለእነማን ብቻ ነበር? በመንፈስ የተቀቡት ሴቶች ለዚህ ምን አመለካከት ነበራቸው?
14 አዲስ የተጠመቁ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች የባሪያው ክፍል የሚሆኑ ሲሆን መጀመሪያ ያስተማራቸው ማንም ይሁን ማን ሽማግሌዎች ሆነው ለማገልገል ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶቹን ከሚያሟሉት የጉባኤው አባላት ተጨማሪ መንፈሳዊ ትምህርት ይቀበሉ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-7፤ ቲቶ 1:6-9) እነዚህ የተሾሙ ወንዶች ለብሔሩ እድገት ልዩ አስተዋጽኦ የማበርከት መብት ነበራቸው። በመንፈስ የተቀቡት ታማኝ ክርስቲያን ሴቶች በጉባኤ ውስጥ የማስተማሩ ኃላፊነት ለክርስቲያን ወንዶች ብቻ መሰጠቱ ቅር አላሰኛቸውም። (1 ቆሮንቶስ 14:34, 35) ወንዶቹ በሚያከናውኑት ትጋት የታከለበት ሥራ ተጠቃሚ በመሆናቸውና ለሌሎች ምሥራቹን መናገርን ጨምሮ ሌሎች መብቶች ስለነበሯቸው ደስተኞችና አመስጋኝ ነበሩ። በዛሬው ጊዜ የሚገኙት ቀናተኛ ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ጉባኤውን እንዲያገለግሉ የተሾሙት ሽማግሌዎች በመንፈስ የተቀቡ ሆኑም አልሆኑ የጥንቶቹ ክርስቲያን ሴቶች ያሳዩትን ዓይነት የትሕትና መንፈስ ያንጸባርቃሉ።
15. በመጀመሪያው መቶ ዘመን መንፈሳዊ ምግብ በዋነኝነት ይቀርብ የነበረው በምን አማካኝነት ነበር? ይህን ምግብ በማከፋፈሉ ሥራ ግንባር ቀደም የነበሩት እነማን ናቸው?
15 በመጀመሪያው መቶ ዘመን መሠረታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ይቀርብ የነበረው ሐዋርያትና ሥራውን በግንባር ቀደምትነት ይመሩ የነበሩ ሌሎች ደቀ መዛሙርት በሚጽፏቸው ደብዳቤዎች አማካኝነት ነበር። በተለይ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በሚባሉት 27 በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ደብዳቤዎች ለየጉባኤው ይዳረሱ ስለነበር የየጉባኤው ሽማግሌዎች በእነዚህ ደብዳቤዎች ላይ ተመርኩዘው ያስተምሩ እንደነበር አያጠራጥርም። በዚህ መንገድ ባሪያውን ይወክሉ የነበሩት ሽማግሌዎች ቅን ልብ ላላቸው ክርስቲያኖች የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ በታማኝነት ያቀርቡ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው ባሪያ የተጣለበትን አደራ በታማኝነት ተወጥቷል።
‘ባሪያው’ ከ1,900 ዓመታት በኋላ
16, 17. እስከ 1914 ባሉት ዓመታት የባሪያው ክፍል የተጣለበትን ኃላፊነት በታማኝነት እንደተወጣ ያሳየው እንዴት ነው?
16 በዘመናችንስ? ኢየሱስ በ1914 በድጋሚ ሲመጣ መንፈሳዊ ምግብ በተገቢው ጊዜ በታማኝነት የሚያቀርብ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን አግኝቶ ነበር? አዎን፣ አግኝቷል። ይህ ቡድን በሚያፈራቸው መልካም ፍሬዎች በግልጽ ተለይቶ ሊታወቅ ይችላል። (ማቴዎስ 7:20) ከዚያ ወዲህ የተፈጸመው ታሪክ እንዲህ ብለን መደምደም እንደምንችል ያረጋግጣል።
17 ኢየሱስ በመጣበት ወቅት 5,000 የሚያህሉ ቤተ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማሰራጨቱ ሥራ በትጋት ይካፈሉ ነበር። ሠራተኞቹ ጥቂቶች ቢሆኑም ባሪያው ምሥራቹን በሰፊው ለማዳረስ የተለያዩ የረቀቁ ዘዴዎችን ተጠቅሟል። (ማቴዎስ 9:38) ለምሳሌ ያህል በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ንግግሮች እስከ 2,000 በሚደርሱ ጋዜጦች ላይ እንዲወጡ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። በዚህ መንገድ የአምላክ ቃል እውነት በአንድ ጊዜ በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ አንባቢዎች ሊዳረስ ችሏል። በተጨማሪም ባለ ቀለም ስላይዶችንና ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን የያዘ የስምንት ሰዓት ድራማ ተዘጋጅቶ ነበር። በዚህ የተዋጣለት ትዕይንት አማካኝነት በሦስት አህጉራት የሚገኙ ከዘጠኝ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ከዓለም ፍጥረት አንስቶ እስከ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ድረስ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ለመማር ችለዋል። ጥቅም ላይ የዋለው ሌላው ዘዴ ጽሑፎችን አትሞ ማሰራጨት ነበር። ለምሳሌ ያህል በ1914 መጠበቂያ ግንብ 50,000 በሚያህሉ ቅጂዎች ታትሞ ነበር።
18. ኢየሱስ ባሪያውን ባለው ንብረት ሁሉ ላይ የሾመው መቼ ነው? ለምንስ?
18 በእርግጥም ጌታው በመጣ ጊዜ ታማኙ ባሪያ ቤተ ሰዎቹን በመመገቡም ሆነ ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ በትጋት ሲካፈል አግኝቶታል። ስለዚህ ይህ ባሪያ ተጨማሪ ኃላፊነቶች ሊሰጡት ነው። ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፣ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:47 የ1954 ትርጉም) ኢየሱስ ይህን ያደረገው ባሪያው በፈተና ውስጥ ካለፈ በኋላ ማለትም በ1919 ነበር። ይሁን እንጂ ‘ታማኝና ልባሙ ባሪያ’ ተጨማሪ ኃላፊነቶች የተሰጡት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ጌታው ያለው ንብረት ስለጨመረ ነው። ኢየሱስ በ1914 ንጉሣዊ ሥልጣን ተሰጥቶታል።
19. ‘የእጅግ ብዙ ሰዎች’ አባላት መንፈሳዊ ፍላጎታቸው ይሟላላቸው የነበረው እንዴት እንደሆነ አብራራ።
19 ንጉሣዊ ሥልጣኑን የተቀበለው ኢየሱስ ታማኙን ባሪያ የሾመው በየትኞቹ ንብረቶች ላይ ነው? በምድር ላይ ባሉት መንፈሳዊ ንብረቶቹ ሁሉ ላይ ነው። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ በ1914 ዙፋኑ ላይ ከተቀመጠ ከሁለት አሥርተ ዓመታት በኋላ ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” እነማን እንደሆኑ ተለይተው ታውቀዋል። (ራእይ 7:9 የ1954 ትርጉም፤ ዮሐንስ 10:16) እነዚህ ሰዎች በመንፈስ የተቀቡት ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት ሳይሆኑ ይሖዋን የሚወድዱና ልክ እንደ ቅቡዓኑ እርሱን ማገልገል የሚፈልጉ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ቅን የሆኑ ወንዶችና ሴቶች ናቸው። ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና አብረን እንሂድ” እንዳሉ ያህል ነው። (ዘካርያስ 8:23) እነዚህ አዲስ የተጠመቁ ክርስቲያኖች በመንፈስ ለተቀቡት ቤተ ሰዎች ከሚቀርብላቸው ገንቢ መንፈሳዊ ምግብ የሚካፈሉ ሲሆን እስከ አሁንም ድረስ እነዚህ ሁለት ቡድኖች ከዚህ መንፈሳዊ ገበታ አብረው ይመገባሉ። ይህ ‘ለእጅግ ብዙ ሰዎች’ አባላት እንዴት ያለ በረከት ሆኖላቸዋል!
20. ‘የእጅግ ብዙ ሰዎች’ አባላት የጌታ ንብረቶች እንዲበዙ በማድረግ ረገድ ምን ሚና ተጫውተዋል?
20 ‘የእጅግ ብዙ ሰዎች’ አባላት ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ለመካፈል በመንፈስ ከተቀባው ባሪያ ጎን በደስታ ተሰልፈዋል። ምሥራቹ እየተስፋፋ ሲሄድ የጌታው ምድራዊ ንብረቶች በመብዛታቸው ‘የታማኝና ልባም ባሪያ’ ኃላፊነቶች ጨምረዋል። የእውነት ፈላጊዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አቅርቦት ከፍ ለማድረግ የህትመት ሥራውን ማስፋፋት አስፈላጊ ሆነ። የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች በበርካታ አገሮች ተከፈቱ። ሚስዮናውያን “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ” ተልከዋል። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) አምላክን የሚያወድሱ ሰዎች ቁጥር በ1914 ከነበሩት 5,000 ገደማ የሚሆኑ ቅቡዓን ተነስቶ በዛሬው ጊዜ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሆነ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ‘የእጅግ ብዙ ሰዎች’ ክፍል ናቸው። አዎን፣ ንጉሡ ዘውድ ከደፋበት ከ1914 ወዲህ ንብረቶቹ በብዙ እጥፍ ጨምረዋል።
21. የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ በየትኞቹ ሁለት ምሳሌዎች ላይ ያተኮረ ነው?
21 ይህ ሁሉ ባሪያው “ታማኝና ልባም” እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ኢየሱስ ስለ ‘ታማኝና ልባሙ ባሪያ’ ከተናገረ በኋላ እነዚህን ባሕርያት የሚያጎሉ ሁለት ምሳሌዎች የተናገረ ሲሆን እነርሱም የልባሞቹና የሰነፎቹ ቆነጃጅት እንዲሁም የመክሊቱ ምሳሌዎች ናቸው። (ማቴዎስ 25:1-30 የ1954 ትርጉም) እነዚህ ምሳሌዎች በዚህ ዘመን ለምንኖረው ምን ትርጉም አላቸው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ መጓጓታችን አይቀርም! የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ይሆናል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• “ታማኝና ልባም ባሪያ” የተባለው ማን ነው?
• ‘ቤተ ሰዎቹ’ እነማን ናቸው?
• ታማኙ ባሪያ በጌታው ንብረቶች ሁሉ ላይ የተሾመው መቼ ነው? በዚያ ጊዜ ተጨማሪ ኃላፊነት የተሰጠውስ ለምንድን ነው?
• በቅርብ ዓመታት የጌታ ንብረቶች እየበዙ እንዲሄዱ በማድረጉ ሥራ እነማንም ተካፍለዋል? እንዴት?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው ባሪያ ኃላፊነቱን በታማኝነት ተወጥቷል