በክርስቶስ መገኘት ዘመን እየሰፋ የሄደው የሥራ እንቅስቃሴ
“ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ እናንተ የአባቴ ብሩካን፣ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።”—ማቴዎስ 25:34
1. የክርስቶስ ፓሩሲያ ‘እንደ ኖኅ ዘመን’ የሚሆነው በምን መንገድ ነው?
የክርስቶስ መገኘት ለብዙ ዘመን ሲጠበቅ የኖረ ክንውን ነው! ኢየሱስ ስለ ‘ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ሲናገር “የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ ይሆናል” ብሎ የተናገረለት ጊዜ በ1914 ላይ መጣ። (ማቴዎስ 24:3, 37) ይሁን እንጂ የክርስቶስ መገኘት ወይም ፓሩሲያ ‘ለታማኝና ልባም ባሪያ’ ቀሪዎች ምን ትርጉም ይኖረዋል? (ማቴዎስ 24:45) በብርሃን አብሪነታቸው በይበልጥ ተግተው መሥራት ይኖርባቸዋል! ወደፊት የሚፈጸሙ ብዙ አስደናቂ ነገሮች ከፊታቸው ተደቅነው ነበር! ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቅ ታላቅ የመሰብሰብ ሥራ የሚጀምርበት ጊዜ ከፊታቸው ተደቅኖ ነበር።
2. የሚልክያስ 3:1-5ን ትንቢት በመፈጸም ምን ዓይነት የማጽዳት ሥራ ተከናውኗል?
2 ይሁን እንጂ እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመጀመሪያ መንጻት ነበረባቸው። በሚልክያስ 3:1-5 ላይ አስቀድሞ እንደተተነበየው ይሖዋ አምላክና “የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ” ኢየሱስ ክርስቶስ በ1918 የጸደይ ወራት መንፈሳዊውን ቤተ መቅደስ ለመመርመር መጡ። ‘ፍርድ ከአምላክ ቤት የሚጀምርበት ጊዜ’ ደርሶ ነበር። (1 ጴጥሮስ 4:17) ሚልክያስ 3:3 “እርሱም [ይሖዋ] ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፣ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፣ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል” በማለት ተንብዮ ነበር። ጊዜው ቅቡዓኑ የሚጠሩበትና የሚጸዱበት ጊዜ ነበር።
3. መንፈሳዊ የማጽዳት ሥራ መካሄዱ አስፈላጊ የነበረው ለምን ነበር?
3 የባሪያው ክፍል ቀሪዎች በ1918 ከፍተኛው ደረጃ ላይ በደረሰው በዚህ የፍርድ ጊዜ በማለፍ ከዓለማዊና ከሃይማኖታዊ እድፈት ጸድተዋል። ይሖዋ ያጸዳቸው ለምን ነበር? ምክንያቱም ነገሩ መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱን የሚመለከት ስለሆነ ነበር። ይህ ቤተ መቅደስ ምሕረት በሚያስገኘው የኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕት መሠረት ይሖዋ የሚመለክበት ቤተ መቅደስ መሰል የአምልኮ ዝግጅት ነው። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው በጣም ብዙ አምላኪዎች ወደፊት ሲመጡ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት የሚከበርበት፣ መለኮታዊ ስሙ የሚቀደስበትና የጽድቅ ሕግጋቱ የሚከበሩበት ቦታ ተዘጋጅቶላቸው እንዲቆይ ቤተ መቅደሱ ንጹሕ በሆነ ሁኔታ እንዲገኝ ፈለገ። ይህ ከሆነ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ያለ ቦታ ሲያገኙ ይሖዋን ለማወቅና ለማድነቅ እንዲሁም ከቀሪዎቹ ጋር ተሰልፈው ታላላቅ ዓላማዎቹን ለማሳወቅ ይችላሉ።
ተጨማሪ መብቶች
4, 5. (ሀ) በኢየሱስ ክርስቶስ የቀረበው ጥያቄ በአሁኑ ጊዜ ያለውን እያንዳንዱን የባሪያውን ክፍል የሚፈታተነው በምን መንገድ ነው? (ለ) “ታማኝና ልባም ባሪያ” እና ‘ቤተሰቦቹ’ የሚሉትን አገላለጾች ልንረዳቸው የሚገባን በምን መንገዶች ነው? (ሐ) ኢየሱስ ለባሪያው ምን ሥራን ሰጥቶታል?
4 በ1919 የባሪያው ክፍል ከዕድፈት ከነጻ በኋላ ከምን ጊዜውም የበለጠ እየሰፋ የሚሄድ የሥራ እንቅስቃሴ ከፊቱ እንደሚጠበቀው ሊመለከት ችሎ ነበር። የታማኞቹ ባሪያዎች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 ሰማያዊ መንግሥቱን ተቀብሏል። ‘ቤተሰቦቹን’ ለመቆጣጠር ወደ ቤቱ በተመለሰበት ጊዜ በምድር ላይ ሳለ ያልነበረውን ንጉሣዊ ክብር ተቀዳጅቶ ነበር። ታዲያ በቤቱ ውስጥ ምን አገኘ? የባሪያው ክፍል የጌታውን ጉዳዮች ተግቶ ሲያከናውን ተገኝቶ ይሆን? ኢየሱስ በማቴዎስ 24:45-47 ላይ እያንዳንዱ ደቀ መዛሙር ይሖዋ ለቀባው መሲሕ ያደረ ስለመሆኑ ራሱን እንዲመረምር የሚያደርገው ጥያቄ አቅርቦ ነበር፦ “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ [ደስተኛ አዓት] ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፣ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል።”
5 ኢየሱስ ስለ ታማኙ ባሪያ የሰጠውን መግለጫ የሚያሟላ አንድ ግለሰብ ሊኖር እንደማይችል ግልጽ ነው። መግለጫው የሚያመለክተው የክርስቶስን ታማኝ ቅቡዓን ጉባኤ በአጠቃላይ ወይም በቡድን ነው። ቤተሰቦቹ የተባሉትም እነዚህ የክርስቶስ ተከታዮች በግለሰብ ደረጃ ሲጠሩ ነው። ኢየሱስ እነዚህን ቅቡዓን በደሙ እንደሚገዛቸው ያውቅ ስለነበር እነርሱን በአጠቃላይ ባሪያ ብሎ መጥራቱ ተገቢ ነው። 1 ቆሮንቶስ 7:23 ስለ እነዚህ ሰዎች ሲናገር “በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ” ይላል። የባሪያው ክፍል ሌሎች ሰዎችን ለመሳብና ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ብርሃኑን እንዲያበራና ለቤተሰቦቹም በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ እየሰጠ እንዲያሳድጋቸው ኢየሱስ አዞታል።
6. ኢየሱስ ባካሄደው ምርመራ ሳቢያ ባሪያው የታማኝነቱን ዋጋ ያገኘው እንዴት ነው?
6 የባሪያው ክፍል ጥላቻ፣ ስደትና አንዳንድ ግራ መጋባት ቢደርስበትም የክርስቶስ መገኘት ከጀመረ ጊዜ አንስቶ እስከ 1918 ድረስ ለቤተሰቦቹ በወቅቱ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ለመስጠት ሲጥር ነበር። ጌታው ምርመራውን በጀመረበት ጊዜ ያገኘው ይህንን ሁኔታ ነበር። በ1919 ጌታ ኢየሱስ በታማኙ ባሪያ ክፍል ስለተደሰተ ብፁዕ ወይም ደስተኛ ብሎታል። ባሪያው የተሰጠውን የጌታ ሥራ በመፈጸሙ ያገኘው አስደሳች ሽልማት ምን ነበር? የሥራ ዕድገት አገኘ! የጌታውን ጉዳዮች ለማስፋፋት የሚያስችለው ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጠው። በተለይ አሁን ጌታቸው ሰማያዊ ንጉሥ ስለሆነ ምድራዊ ንብረቶቹን በጣም ውድ አድርጎ ይመለከታቸዋል።
7, 8. (ሀ) የጌታ ‘ንብረቶች ሁሉ’ ምንድን ናቸው? (ለ) ባሪያው በእነዚህ ንብረቶች ሁሉ ላይ ተቆጣጣሪ መሆኑ ምን ይጠይቅበታል?
7 ታዲያ “ባለው ሁሉ ላይ” የተባለው ነገር ምንድን ነው? ክርስቶስ ሰማያዊ ንጉሥ በመሆን ካገኘው ሥልጣን ጋር ግንኙነት ያላቸው ንብረቶቹ የሆኑት መንፈሳዊ ነገሮች ሁሉ ናቸው። ይህም ለተቋቋመው የአምላክ መንግሥት በዓለም ብሔራት ሁሉ ወኪል ከመሆን ታላቅ መብት ጋር ለክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የማድረግን ተልዕኮ እንደሚጨምር የተረጋገጠ ነው።
8 የባሪያው ክፍል የጌታውን ንብረቶች በበላይነት እንዲቆጣጠር የተሰጠው ይህ የሥራ ዕድገት የባሪያው ክፍል የመንግሥቱን ሥራ ለመፈጸም የበለጠ ጊዜና ትኩረት እንዲሰጥ ለዚህ ሥራ የሚያገለግሉ መሣሪያዎችንና ሕንፃዎችን እንዲያስፋፋ ጠይቆበታል። አሁን ሥራውን የሚያከናውንበትን መስክ ከበፊቱ የበለጠ ሰፍቶ መላውን ምድር የሚያጠቃልል ሆኗል።
በጎቹን መሰብሰብ
9. ከባሪያው የሥራ እንቅስቃሴ መስፋት ምን ውጤት ተገኝቷል?
9 የክርስቶስ ታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል በታዛዥነት የሥራ እንቅስቃሴውን አሰፋ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? የ144,000ዎቹ ክፍል የሆኑ የመጨረሻ ቀሪዎች ተሰበሰቡ። ከዚያም በራእይ 7:9-17 ላይ የተመዘገበው ራእይ ዛሬ ከፍተኛ የደስታ ስሜት የሚቀሰቅስ እውን ነገር ሆኗል። በተለይ ከ1935 ጀምሮ የባሪያው ክፍል ይህ ራእይ ያለማቋረጥ እየተፈጸመ መሆኑን በመመልከት ሲደሰት ቆይቷል። ከመላው ምድር የተውጣጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ “እጅግ ብዙ ሰዎች” የይሖዋ አምላኪዎች በመሆን ወደ መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ አደባባይ በመጉረፍ ላይ ይገኛሉ። የይሖዋ መልአክ እነዚህን እጅግ ብዙ ሰዎች ማንም ሊቆጥራቸው እንደማይችል ለዮሐንስ ነግሮት ነበር። ይህም ማለት የባሪያው ክፍል ወደ ይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ የሚያመጣቸው ሰዎች ቁጥር አልተወሰነም ማለት ነው። በሩ ክፍት ሆኖ እስከቆየ ድረስ እነርሱን የመሰብሰቡ ሥራ ይቀጥላል።
10. በዛሬው ጊዜ ባሪያው በምን ፍቅራዊ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ተሠማርቷል?
10 እነዚህ ከብሔራት ሁሉ የሚውጣጡት በግ መሰል ሰዎች በጌታቸው በኢየሱስ ዘንድ በጣም ውድ እንደሆኑ የታማኙ ባሪያ ክፍል ስለሚያውቅ በቁጥር እየጨመሩ የሚሄዱትን “ሌሎች በጎች” ለመንከባከብ በጣም ከባድ ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑን ይገነዘባል። እነዚህ በጎች የኢየሱስ መንጋ ክፍል ናቸው። (ዮሐንስ 10:16፤ የሐዋርያት ሥራ 20:28፤ 1 ጴጥሮስ 5:2-4) ስለዚህ የባሪያው ክፍል ለጌታውና ለበጎቹ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ የእጅግ ብዙ ሰዎችን መንፈሳዊ ፍላጎት በደስታ ያሟላላቸዋል።
11-13. የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው የባሪያውን የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ምን ተገቢ አስተያየት ሰጥቶ ነበር?
11 አዎ፤ ባሪያው የሚያካሂደው ብርሃን የማብራት ሥራ በአብዛኛው እነዚህን የአምላክ መንግሥት ምድራዊ ተገዢዎች መሰብሰብን ይመለከታል። የማኅበሩ ፕሬዘዳንት የነበረው ኤፍ ፍራንዝ በ1992 በታኅሣሥ ወር ከመሞቱ በፊት እየጨመረ የሄደውን የታማኙን ባሪያ የሥራ እንቅስቃሴ ሲያብራራ እንዲህ ብሎ ነበር፦
12 “በ99 ዓመታት የሕይወት ተሞክሮዬ ሁሉ እንዳየሁት ኢየሱስ ክርስቶስ ምንጊዜም በጣም አስደናቂ በሆነ መንገድ በድርጅቱ ተጠቅሟል። ድርጅቱን የሚመራው አንድ ተራ ሰው አይደለም። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ካሰብነውና ከገመትነው የበለጠ አስደናቂ ሥራ ሊከናወን ችሏል። ዛሬ በመላው ምድር ላይ የተስፋፋ ድርጅት አለን። ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ በሰሜኑም ሆነ በደቡቡ ንፍቀ ክበብ በምሥራቁም ሆነ በምዕራቡ የምድር ክፍል ይንቀሳቀሳል። ይህን የመሰለ ታላቅ መስፋፋት ሊያመጣ የሚችል አንድ አካል ብቻ ነው። እርሱም ታማኝና ልባም ባሪያን የሚቆጣጠረው የአምላክ ልጅ ነው። ይህ ባሪያ ኃላፊነቱን በሚገባ በመወጣት ላይ ነው። ይህ የምንመለከተው ታላቅ ጭማሪ ሊገኝ የቻለውም በዚህ ምክንያት ነው።
13 “ሥራው በአንድ ሰው ላይ የተመካ አይደለም። ድርጅታችን ቲኦክራቲካዊ ነው። የሚሠራውም ቲኦክራቲካዊ በሆነ መንገድ በአምላክ እየተመራ ነው። ማንም ሰው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበርን የመሠረተው ሰውም እንኳን ቢሆን ይህን መላውን ዓለም ያጥለቀለቀውን ሥራ አከናውኛለሁ ሊል ወይም አከናውኗል ሊባል አይችልም። በአጭሩ በጣም አስደናቂ ነው።” የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት የሆኑ ሁሉ ሟቹ ወንድም ፍራንዝ ከገለጸው ሐሳብ ጋር በሙሉ ልብ አይስማሙምን? አዎ፤ ታማኙ ባሪያ የሚያካሂደው የሥራ እንቅስቃሴ እየሰፋ በመምጣቱ በጣም አመስጋኞች ናቸው።
የመንግሥቱ ተገዢዎች
14, 15. (ሀ) ኢየሱስ በመክሊቱ ምሳሌ የገለጸው ምን ነበር? (ማቴዎስ 25:14-30)? (ለ) ተገቢ በሆነ መንገድ በማቴዎስ ምዕራፍ 25 ላይ ከመክሊቱ ምሳሌ በማስከተል የተገለጸው ምንድን ነው?
14 በማቴዎስ ምዕራፍ 25 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ ስለ በጎችና ስለ ፍየሎች የሰጠው ምሳሌ ይህን የአምላክ መንግሥት ምድራዊ ተገዢዎች የመሰብሰብ ሥራ ይገልጻል። ከዚህ ምሳሌ ቀደም ብሎ በተገለጸው የመክሊት ምሳሌ ላይ ከኢየሱስ ጋር በሰማያዊ መንግሥት ለመግዛት ተስፋ የሚያደርጉ ታማኝ ደቀ መዛሙርት በሙሉ ምድራዊ ንብረቱን ለማስፋት ተግተው መሥራት እንደሚኖርባቸው ይገልጻል። እንግዲያውስ ኢየሱስ በሚቀጥለው ምሳሌ የሰማያዊ መንግሥቱ ተገዢዎች ለመሆን የሚፈልጉ ሁሉ ማሟላት የሚኖርባቸውን ብቃት መግለጹ ተገቢ ነው።
15 በማቴዎስ 25:31-33 ላይ እርሱ የተናገረውን ልብ በሉ፦ “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፣ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል።”
16. አሕዛብ የተሰበሰቡትና ሕዝቦችም በሁለት ወገን የተለዩት እንዴት ነው?
16 ኢየሱስ በክብሩ የመጣው በ1914 ነው። በዚያ ጊዜ የማጥቃት እርምጃ በመውሰድ ከመላእክቱ ጋር ሆኖ አጋንንታዊ ጠላቶቹን ከሰማይ አስወግዷል። ከዚህ በመቀጠል እንደሚፈጸም በምሳሌ የተገለጸው ነገር ኢየሱስ በክብር ዙፋን መቀመጡ በመገኘቱ ጊዜ የፍርድ ሥራ የሚያከናውን መሆኑን እንደሚያመለክት እንድንገነዘብ ይረዳናል። አሕዛብ በሙሉ በፊቱ መሰብሰባቸው የሚያመለክተው ኢየሱስ አሕዛብን በሙሉ በምሳሌያዊ አባባል የወደፊት መንጎቹ እንደሆኑ አድርጎ የሚመለከታቸው መሆኑን ነው። ይህ መንጋ ፍየሎችና በጎች የተቀላቀሉበት ነው። ቃል በቃል ፍየሎችና በጎች የተደባለቁበትን መንጋ ለመለየት የአንድ ቀን ከፊል ጊዜ ይወስድ ይሆናል። የምርጫ ነፃነት ያላቸውን ሰዎች የመለየቱ ምድር አቀፍ ሥራ ግን ከዚህ የበለጠ ጊዜ ይፈጃል። ይህም የሆነበት ምክንያት የመለየቱ ሥራ የሚከናወነው ሰዎች በግለሰብ ደረጃ በሚከተሉት መንገድ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ነው።
17. ዛሬ ሁኔታው ለሁሉም ሕዝቦች አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው?
17 በምሳሌው ላይ እረኛው ንጉሥ በግ መሰሎቹን በቀኙ ፍየል መሰሎቹን ደግሞ በግራው እንደሚያቆማቸው ተገልጿል። በቀኝ በኩል መቆሙ በመጨረሻው ላይ ጥሩ ውጤት ይኸውም የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ ፍርድ ያመጣል። በግራ ጎን መቆሙ ግን ክፉ ፍርድ ይኸውም የዘላለም ጥፋት የሚያመጣ ይሆናል። የንጉሡ ቁርጥ ውሳኔ አሳሳቢ ውጤት የሚያስከትል ነው።
18. ንጉሡ በዓይን የማይታይ መሆኑ ለማንም ሰበብ ሊሆንለት የማይችለው ለምንድን ነው?
18 የሰው ልጅ መገኘት ወይም ፓሩሲያ በዓይን የማይታይ መሆኑ ለማንም ሰው ሰበብ ማቅረቢያ ምክንያት ሊሆን አይችልም። በዛሬው ጊዜ ከባሪያው ክፍል ጎን በመሰለፍ የአምላክን የመንግሥት ምሥራች በዓለም በሙሉ እየሰበኩ ብርሃናቸው እንዲበራ የሚያደርጉት በግ መሰል ሰዎች ቁጥር በየጊዜው በማደግ ላይ ነው። በእርግጥም ምስክርነታቸው በምድር ማዕዘናት በሙሉ ተዳርሷል።—ማቴዎስ 24:14
19. በበጎችና በፍየሎች ምሳሌ ላይ የተገለጹት የበጎቹ ባሕርያት ምንድን ናቸው?
19 እረኛው ንጉሥ ለበጎቹ ክፍል ወደፊት የተባረከ ሕይወት የሚሸልማቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ለመንግሥቱ ስብከት ሥራ የሙሉ ልብ ድጋፍ በመስጠታቸውና ኢየሱስ ለራሱ እንደተደረገለት የሚቆጥረውን ደግነት ለቅቡዓን ወንድሞቹ በማሳየታቸው ነው። ንጉሣዊው የሰው ልጅ “እናንተ የአባቴ ብሩካን፣ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” ይላቸዋል።—ማቴዎስ 25:34፤ 28:19, 20
ንጉሡን መርዳት
20, 21. በጎቹ በመንግሥቱ ጎን ለመቆማቸው ምን ማስረጃ ይታይባቸዋል?
20 በጎቹ የአምላክን መንግሥት ምድራዊ ግዛት እንዲወርሱ ንጉሡ ሲጋብዛቸው ይህ ያልጠበቁት ነገር መሆኑን በአድናቆት መናገራቸውን አስተውሉ። ‘ጌታ ሆይ እነዚህን ነገሮች መቼ አደረግንልህ?’ ብለው ይጠይቁታል። እርሱም ሲመልስላቸው “እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል።” (ማቴዎስ 25:40) ኢየሱስ ከሙታን በተነሣበት ዕለት ለመግደላዊት ማርያም በተገለጠላት ጊዜ “ወደ ወንድሞቼ” ሂጂ በማለት ስለ መንፈሳዊ ወንድሞቹ ተናግሯል። (ዮሐንስ 20:17) ኢየሱስ በሰማይ በማይታይ ሁኔታ በሚገኝበት ዘመን በምድር ላይ የነበሩት የ144,000 መንፈሳዊ ወንድሞቹ ጥቂት ቀሪዎች ብቻ ናቸው።
21 ኢየሱስ በሰማይ ስለሚኖርና በዓይን ስለማይታይ እነዚህ በግ መሰል ሰዎች እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉለት በተዘዋዋሪ መንገድ ነው። በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ የሚያዩት በእምነት ዓይናቸው ብቻ ነው። በሰማይ ተባባሪ ወራሾቹ የሚሆኑትን መንፈሳዊ ወንድሞቹን ለመርዳት በሚያደርጉት ጥረት ኢየሱስ በጣም ይደሰታል። ለወንድሞቹ የተደረገውን ሁሉ ለራሱ እንደተደረገ ይቆጥረዋል። በግ መሰሎቹ ሰዎች ለክርስቶስ ወንድሞች መልካም ያደረጉት የክርስቶስ ወንድሞች መሆናቸውን አውቀውና ሆን ብለው ብለው ነው። የኢየሱስ መንፈሣዊ ወንድሞች የይሖዋ መንግሥት አምባሳደሮች መሆናቸውን ስለሚገነዘቡ በመንግሥቱ ጎን የተሰለፉ መሆናቸውን ተጨባጭ በሆነ መንገድ ለማረጋገጥ ይፈልጋሉ።
22. የበጎቹ ክፍል ለታማኝነቱ ዋጋውን የሚያገኘው እንዴት ነው? (ከራእይ 7:14-17 ጋር አወዳድር።)
22 ይሖዋ ይህ የበግ መሰሎች ክፍል በዚህ ልጁ በሚገኝበት ዘመን ብቅ እንደሚል አስቀድሞ ተመልክቶ ነበር። ለእነርሱም ይሖዋ የተባረከ ሽልማት አዘጋጅቶላቸዋል! እጅግ ብዙ ሰዎች ይሖዋ የሾመው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገዛበት የሺህ ዓመት ዘመን በዚህች ምድር ላይ የሰላም በረከቶችን ይወርሳሉ።
23. በጎቹ ሆን ብለው የንጉሡን ወንድሞች የሚረዱት በምን መንገዶች ነው?
23 ኢየሱስ ስለ በጎችና ስለ ፍየሎች የተናገረውን ምሳሌ ጨምሮ በክርስቶስ መገኘት ዘመን ተፈጻሚነት የሚኖራቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ስንመለከት ምን እናስተውላለን? የሚከተለውን እናስተውላለን፦ አንድን ሰው በአምላክና በንጉሡ ፊት የጽድቅ አቋም ያገኘ በግ እንዲሆን የሚያስችለው ሳያውቅ በድንገት ከንጉሡ መንፈሣዊ ወንድሞች ለአንዱ መልካም ማድረጉ አይደለም። የበጎቹ ክፍል አባሎች የሆኑ ሁሉ በሥጋዊ ዓይናቸው የነገሠውን ንጉሥ ለመመልከት ባይችሉም የሚያደርጉትን ነገር ያውቃሉ። የንጉሡን ወንድሞች በሥጋዊ ነገሮች ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ መንገድም ለመርዳት ይጥራሉ። እንዴት? የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክና ለክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በሚያስገኝለት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራቱ ሥራ በመርዳት ነው። ይህም በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ የአምላክን መንግሥት የሚያውጁ ከአራት ሚልዮን የሚበልጡ ብርሃን አብሪዎች አሉ።
የሥራ እንቅስቃሴው ሰፋ
24. በአሁኑ ጊዜ የባሪያውን ክፍል ተወዳዳሪ የማይገኝለት ደስተኛ ሕዝብ ያደረጉት ምን ፍቅራዊ የሥራ እንቅስቃሴዎች ናቸው?
24 አሁን የታማኙ ባሪያ ክፍል የሚያከናውናቸውን ብዙ መልካም ሥራዎች አንድ በአንድ እንዘርዝር። አንደኛ የባሪያው ክፍል በጌታ ንብረት ሁሉ ላይ ማለትም በምድር ላይ በሚገኙት የመንግሥቱ ጉዳዮች ላይ ተሹሞአል። እነዚህም ንብረቶች እየተስፋፉና እየጨመሩ ሄደዋል። ሁለተኛ ይህ የባሪያ ክፍል እየመገበ ያለው የቅቡዓንን ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆን በቁጥር በጣም እየጨመሩ የሄዱትን እጅግ ብዙ ሰዎች ጭምር ነው። ሦስተኛ ባሪያው የመንግሥቱን ብርሃን በማሰራጨቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት ተሰልፏል። አራተኛ የባሪያው ከፍተኛ የሥራ እንቅስቃሴ ያተኮረው የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑትን እጅግ ብዙ ሰዎች ወደ ይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ በመሰብሰብ ላይ ነው። አምስተኛ ባሪያው በበግ መሰል ሰዎች የሙሉ ልብ ድጋፍ በምድር ሁሉ ላይ የሚገኙትን የቅርንጫፍ ድርጅቶች እና በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘውን ዋና መሥሪያ ቤት ተጨማሪ ሕንፃዎችና መሣሪያዎች እንዲኖራቸው በማድረግ ላይ ነው። እንዲህ ያለው ፍቅራዊ ሥራ የባሪያው ክፍል በምድር ላይ ተወዳዳሪ የሌለው ደስተኛ ሕዝብ እንዲሆን አስችሎታል። ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም ደስተኞች እንዲሆኑ ለማድረግ አስችሏቸዋል። እነዚህ ሁሉ ሕዝቦች የልባም ባሪያውን የሥራ እንቅስቃሴ እንዲስፋፋ ላደረጉት ለይሖዋ አምላክና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና ይሰጣሉ!
25. በጎቹ ባሪያውን መደገፋቸውን ሊቀጥሉ የሚችሉት እንዴት ነው? ከምንስ ተስፋ ጋር?
25 በአሁኑ ጊዜ የባሪያው ክፍል አምላክ የሰጠውን ሥራ በመፈጸም ረገድ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ በትጋት ይሠራል። ‘ታላቁ መከራ’ ሊጀምር የቀረው ጊዜ አልቋል ለማለት ይቻላል። (ማቴዎስ 24:21) የአምላክ በጎች የሆኑ ሁሉ ከእረኛው ንጉሥ ቀኝ በኩል መቆየታቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው! ስለዚህ ሁላችንም በቅንዓት ታማኝና ልባም ባሪያን በመደገፍ እንቀጥል። በግ መሰል ሰዎች በቅርብ ጊዜ ውስጥ “እናንተ የአባቴ ብሩካን፣ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” የሚሉትን አስደሳች ቃላት ሊሰሙ የሚችሉት ይህን ካደረጉ ብቻ ነው።
ልትመልስ ትችላለህን?
◻ ንጉሡ በዙፋን ላይ ከተቀመጠ በኋላ ምን የመጀመሪያ ፍርድ ተከተለ?
◻ ማቴዎስ 24:45-47 ዘመናዊ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
◻ የሥራ እንቅስቃሴ መስፋፋትን በተመለከተ ባሪያውና እጅግ ብዙ ሰዎች አመስጋኞች መሆን ያለባቸው ለምን ነገሮች ነው?
◻ ማቴዎስ 25:34-40 በፓሩሲያው ዘመን የተፈጸመ እንዴት ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጌታው ንብረቱን ሁሉ ለታማኙ ባሪያ አደራ ሰጥቷል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ለሰው ልጆች ፍርድ ለመስጠት በታላቅ ዙፋኑ ላይ ተቀምጧል