ይሖዋ—ከሁሉ የላቀው የጥሩነት ምሳሌ
“ይሖዋ ጥሩ ነውና የሠራዊት ጌታ ይሖዋን አወድሱ!”—ኤርምያስ 33:11 NW
1. አምላክን ስለ ጥሩነቱ ለማወደስ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?
ይሖዋ አምላክ በጥሩነቱ አቻ አይገኝለትም። ነቢዩ ዘካርያስ “ጥሩነቱ እንዴት ታላቅ ነው!” ሲል በአድናቆት ተናግሯል። (ዘካርያስ 9:17 NW ) በእርግጥም አምላክ ምድርን ለእኛ አስደሳች አድርጎ ለማዘጋጀት የፈጠራቸው ነገሮች ሁሉ ጥሩነት የተንጸባረቀባቸው ናቸው። (ዘፍጥረት 1:31) አምላክ አጽናፈ ዓለሙን ሲፈጥር የተጠቀመባቸውን ውስብስብ ሕግጋት ሙሉ በሙሉ መረዳት ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። (መክብብ 3:11፤ 8:17) ይሁንና የምናውቀው ትንሹም ነገር አምላክን ስለ ጥሩነቱ እንድናወድሰው ያነሳሳናል።
2. ጥሩነትን እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ?
2 ጥሩነት (በእንግሊዝኛ ጉድነስ ) ምንድን ነው? ግብረ መልካምነት ነው። ይሁን እንጂ ከክፋት ድርጊት ሁሉ የጠራ ከመሆን የበለጠ ነገርንም ይጨምራል። ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ የሆነው ጥሩነት በአዎንታዊ ድርጊት የሚገለጽ ባሕርይ ነው። (ገላትያ 5:22, 23 NW ) ለሌሎች በጎና ጠቃሚ ተግባራትን በማከናወን ጥሩነትን ማሳየት እንችላለን። በዚህ የነገሮች ሥርዓት በአንዳንዶች ዘንድ ጥሩ ተደርጎ የሚታየው ነገር በሌሎች ዘንድ መጥፎ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ ሰላምና ደስታ እንዲኖረን ከተፈለገ አንድ የጥሩነት መስፈርት ሊኖር ይገባል። ይህን መስፈርት የማውጣት መብት ያለው ማን ነው?
3. የጥሩነትን መስፈርት በተመለከተ ከዘፍጥረት 2:16, 17 ምን እንገነዘባለን?
3 የጥሩነትን መስፈርት የሚያወጣው አምላክ ነው። የሰው ዘር ታሪክ ገና ሲጀምር ለመጀመሪያው ሰው የሚከተለውን ትእዛዝ የሰጠው ይሖዋ ነበር:- “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።” (ዘፍጥረት 2:16, 17) አዎን፣ የሰው ልጅ መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር ለማወቅ ፊቱን ወደ ፈጣሪው መመለስ ይኖርበታል።
ይገባናል የማንለው የጥሩነት መግለጫ
4. አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላ አምላክ ለሰው ዘር ምን አድርጓል?
4 አዳም ኃጢአት በመሥራት አምላክ ያለውን ለጥሩነት መስፈርት የማውጣት መብት በተጋፋ ጊዜ የሰው ልጅ በፍጽምና ለዘላለም ተደስቶ የመኖር ተስፋው አደጋ ላይ ወደቀ። (ዘፍጥረት 3:1-6) ይሁንና የአዳም ልጆች ኃጢአትና ሞትን ወርሰው ከመወለዳቸው በፊት አምላክ ወደፊት ስለሚመጣው አንድ ፍጹም ዘር ተናግሯል። ይሖዋ ‘የቀደመውን እባብ’ ሰይጣን ዲያብሎስን እንዲህ ብሎታል:- “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።” (ራእይ 12:9፤ ዘፍጥረት 3:15) የይሖዋ ዓላማ ኃጢአተኛውን የሰው ዘር መቤዠት ነበር። ይሖዋ ይገባናል በማንለው የጥሩነት መግለጫው በውድ ልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያምኑ ሁሉ የሚድኑበትን ዝግጅት አድርጓል።—ማቴዎስ 20:28፤ ሮሜ 5:8, 12
5. መጥፎ የልብ ዝንባሌ የወረስን ቢሆንም በተወሰነ መጠን ጥሩነትን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
5 እርግጥ በአዳም ኃጢአት ምክንያት መጥፎ የልብ ዝንባሌ ወርሰናል። (ዘፍጥረት 8:21) ደስ የሚለው ግን ይሖዋ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ጥሩነት ማሳየት እንድንችል ይረዳናል። ውድ ከሆኑት ቅዱሳን መጻሕፍቱ መማራችንን መቀጠላችን ‘መዳን የሚገኝበትን ጥበብ’ ከማስጨበጡም በላይ በአምላክ ዓይን ጥሩ የሆነውን ነገር ማድረግ እንድንችል ያስታጥቀናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:14-17 NW ) ከቅዱስ ጽሑፋዊው ትምህርት ለመጠቀምና ጥሩነትን ለማንጸባረቅ ግን “አቤቱ፣ [ይሖዋ] አንተ ጥሩ ነህ፤ የምታደርገውም ጥሩ ነው። እንግዲህ ሥርዓትህን አስተምረኝ” ሲል እንደጸለየው መዝሙራዊ ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል።—መዝሙር 119:68 NW
የይሖዋ ጥሩነት ተወድሷል
6. ንጉሥ ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ካስመጣ በኋላ ሌዋውያኑ የትኛውን ስንኝ የያዘ መዝሙር ዘምረዋል?
6 የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት የአምላክን ጥሩነት በመገንዘብ የእርሱን አመራር ለማግኘት ጠይቋል። “እግዚአብሔር ቸር [“ጥሩ፣” NW ] ነው፤ ስለዚህ ኃጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 25:8) ለእስራኤላውያን የተሰጠው መለኮታዊ መመሪያ አሥርቱ ትእዛዛት በመባል የሚታወቁትንና በድንጋይ ጽላት ተቀርጸው የቃል ኪዳን ታቦት በተባለው ቅዱስ የእንጨት ሣጥን ውስጥ የተቀመጡትን አሥር ዋና ዋና ሕግጋት ያካተተ ነበር። ዳዊት ታቦቱን የእስራኤል መዲና ወደነበረችው ኢየሩሳሌም ካስመጣ በኋላ ሌዋውያን በዘመሩት መዝሙር ውስጥ የሚከተለው ስንኝ ይገኝ ነበር:- “ጥሩ ነውና፣ ፍቅራዊ ደግነቱም ለዘላለም ነውና ይሖዋን አመስግኑ።” (1 ዜና መዋዕል 16:34, 37-41 NW ) ሌዋውያኑ ዘማሪዎች እነዚህን ቃላት ሲያዜሙ መስማት ምንኛ አስደሳች ይሆን!
7. ታቦቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ሲገባም ሆነ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ለአምላክ አገልግሎት ለመወሰን ጸሎት ካቀረበ በኋላ ምን ነገር ተከናውኗል?
7 የዳዊት ልጅ ሰሎሞን የገነባው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ለአምላክ አገልግሎት ሲወሰንም እነዚሁ ቃላት ጎላ ተደርገው ተገልጸዋል። የቃል ኪዳኑ ታቦት ተሠርቶ በተጠናቀቀው አዲስ ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከገባ በኋላ “ይሖዋ ጥሩ ነው፤ ፍቅራዊ ደግነቱም ለዘላለም ነው” እያሉ አወድሰውታል። በዚህ ወቅት ቤተ መቅደሱ የይሖዋን ክብራማ መገኘት በሚያመለክተው ደመና በተአምራዊ መንገድ ተሞልቷል። (2 ዜና መዋዕል 5:13, 14 NW ) ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ለአምላክ አገልግሎት ለመወሰን ያቀረበውን ጸሎት እንደጨረሰ “እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕቱን በላ።” (2 ዜና መዋዕል 7:1-3) ይህንን ሲያዩ “የእስራኤልም ልጆች ሁሉ . . . በወለሉም ላይ በግምባራቸው ወደ ምድር ተደፍተው ሰገዱ:- እርሱ ጥሩ ነውና፣ ፍቅራዊ ደግነቱም ለዘላለም ነውና ብለውም ይሖዋን አመሰገኑ።” (2 ዜና መዋዕል 7:1-3 NW ) ከ14 ቀን በዓል በኋላ እስራኤላውያኑ “እግዚአብሔር ለዳዊትና ለሰሎሞን ለሕዝቡም ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት [“ጥሩነት፣” NW ] ደስ ብሎአቸው ሐሤትን እያደረጉ” ወደየመጡበት ተመልሰዋል።—2 ዜና መዋዕል 7:10
8, 9. (ሀ) እስራኤላውያኑ ይሖዋን ስለ ጥሩነቱ ቢያወድሱትም የኋላ ኋላ ምን ዓይነት ጎዳና ተከትለዋል? (ለ) በኤርምያስ አማካኝነት ስለ ኢየሩሳሌም ምን ትንቢት ተነግሯል? ይህስ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
8 የሚያሳዝነው ግን እስራኤላውያኑ አምላክን ለማወደስ ከዘመሩት መዝሙር ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለሳቸውን አልቀጠሉም። የኋላ ኋላ የይሁዳ ሕዝብ ‘ይሖዋን የሚያከብረው በከንፈሩ ብቻ’ ሆኖ ነበር። (ኢሳይያስ 29:13) ከአምላክ የጥሩነት መስፈርት ጋር ተስማምተው ከመመላለስ ይልቅ ክፉ የሆነውን ማድረግ ጀመሩ። የክፋት ድርጊታቸው ምን ይጨምር ነበር? የጣዖት አምልኮ፣ የፆታ ብልግና፣ ድሆችን መጨቆንና ሌሎችንም ከባድ ኃጢአቶች ይፈጽሙ ነበር! ከዚህም የተነሣ ኢየሩሳሌም ጠፋች፤ የይሁዳም ነዋሪዎች በ607 ከዘአበ ወደ ባቢሎን በምርኮ ተጋዙ።
9 አምላክ በዚህ መንገድ ሕዝቡን ቀጥቷል። ይሁን እንጂ በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት “ይሖዋ ጥሩ ነውና፣ ፍቅራዊ ደግነቱም ለዘላለም ነውና የሠራዊት ጌታ ይሖዋን አመስግኑ” የሚሉ ሰዎች ድምፅ በኢየሩሳሌም እንደሚሰማ ትንቢት አስነግሮ ነበር። (ኤርምያስ 33:10, 11 NW ) ይህም ተፈጽሟል። ምድሪቱ ለ70 ዓመት ባድማ ሆና ከቆየች በኋላ በ537 ከዘአበ አይሁዳውያን ቀሪዎች ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰዋል። (ኤርምያስ 25:11፤ ዳንኤል 9:1, 2) ቤተ መቅደሱ በነበረበት የሞሪያ ተራራ ላይ መሠዊያውን መልሰው በመገንባት በዚያ ስፍራ መሥዋዕት ማቅረብ ጀመሩ። የቤተ መቅደሱ መሠረት የተጣለው በተመለሱ በሁለተኛው ዓመት ነው። ይህ እንዴት አስደሳች ጊዜ ነበር! ዕዝራ እንዲህ ብሏል:- “አናጢዎቹም የእግዚአብሔርን መቅደስ በመሠረቱ ጊዜ ካህናቱ ልብሳቸውን ለብሰው መለከቱን ይዘው፣ የአሳፍም ልጆች ሌዋውያን ጸናጽል ይዘው እንደ እስራኤል ንጉሥ እንደ ዳዊት ሥርዓት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ቆሙ። ደግሞ:- ቸር [“ጥሩ፣” NW ] ነውና፣ ለእስራኤልም ምሕረቱ [“ፍቅራዊ ደግነቱ፣” NW ] ለዘላለም ነውና እያሉ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑና እያከበሩ እርስ በእርሳቸው ያስተዛዝሉ ነበር።”—ዕዝራ 3:1-11
10. መዝሙር 118 የሚጀመረውና የሚደመደመው በየትኛው ጉልህ ትርጉም ያለው መግለጫ ነው?
10 ይሖዋን ስለ ጥሩነቱ ለማወደስ የቀረበ ተመሳሳይ መግለጫ በበርካታ መዝሙሮች ውስጥ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል አንዱ መዝሙር 118 ሲሆን ይህ መዝሙር እስራኤላውያን ቤተሰቦች በማለፍ በዓል መደምደሚያ ላይ የሚዘምሩት ነበር። መዝሙሩ የሚጀመረውም ሆነ የሚደመደመው “እናንተ ሕዝቦች ሆይ ይሖዋን አመስግኑ፣ ጥሩ ነውና፤ ፍቅራዊ ደግነቱም ለዘላለም ነውና” በሚሉት ቃላት ነው። (መዝሙር 118:1, 29 NW ) ኢየሱስ ክርስቶስ በ33 እዘአ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ከታመኑ ሐዋርያቱ ጋር ሆኖ የዘመራቸው የመጨረሻ የውዳሴ ቃላት እነዚህ ሳይሆኑ አይቀሩም።—ማቴዎስ 26:30
“እባክህ ክብርህን አሳየኝ”
11, 12. ሙሴ የአምላክን ክብር ጭላንጭል በተመለከተ ጊዜ ምን መግለጫ ሲነገር ሰምቷል?
11 በይሖዋ ጥሩነትና በፍቅራዊ ደግነቱ መካከል ያለው ዝምድና ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው ከዕዝራ ዘመን ብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ነበር። እስራኤላውያን በምድረ በዳ የወርቅ ጥጃ ሠርተው ካመለኩና ጥፋተኞቹ ከተገደሉ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሙሴ ይሖዋን “እባክህ ክብርህን አሳየኝ” ሲል ጠይቆታል። ይሖዋም ሙሴ ፊቱን አይቶ በሕይወት ሊኖር እንደማይችል በመገንዘብ “መልካምነቴን [“ጥሩነቴን፣” NW ] ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ” አለው።—ዘጸአት 33:13-20
12 በሚቀጥለው ቀን በሲና ተራራ ላይ የይሖዋ ጥሩነት በሙሴ ፊት አለፈ። በዚህ ወቅት ሙሴ የአምላክን ክብር በመጠኑ የተመለከተ ሲሆን የሚከተለውን መግለጫም ሰምቷል:- “ይሖዋ፣ ይሖዋ መሐሪ፣ ደግ፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ፍቅራዊ ደግነቱና እውነቱ የበዛ፣ እስከ ሺህ ትውልድም ፍቅራዊ ደግነትን የሚጠብቅ፣ ስህተትና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፣ [በደለኛውን] ሳይቀጣ የማያልፍ፣ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆችና በልጅ ልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ የሚያመጣ አምላክ ነው።” (ዘጸአት 34:6, 7 NW ) እነዚህ ቃላት የይሖዋ ጥሩነት ከፍቅራዊ ደግነቱና ሌሎች ባሕርያቱ ጋር የተዛመደ መሆኑን ይጠቁማሉ። እነዚህን ባሕርያት መመርመራችን የጥሩነትን ባሕርይ ለማንጸባረቅ ይረዳናል። በመጀመሪያ ስለ አምላክ ጥሩነት በተነገረው በዚህ አስገራሚ መግለጫ ውስጥ ሁለት ጊዜ የተጠቀሰውን ባሕርይ እንመልከት።
‘ፍቅራዊ ደግነቱ የበዛ አምላክ’
13. ስለ አምላክ ጥሩነት በተሰጠው መግለጫ ውስጥ ሁለት ጊዜ የተጠቀሰው ባሕርይ የትኛው ነው? ይህስ ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው?
13 “ይሖዋ . . . ፍቅራዊ ደግነቱ . . . የበዛ . . . እስከ ሺህ ትውልድም ፍቅራዊ ደግነትን የሚጠብቅ . . . አምላክ ነው።” “ፍቅራዊ ደግነት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ታማኝ ፍቅር” የሚል ትርጉምም አለው። አምላክ ለሙሴ በሰጠው መግለጫ ውስጥ ሁለት ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኘው ብቸኛ ባሕርይ ይህ ነው። የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ ፍቅር ከመሆኑ አንጻር ይህ ምንኛ ተስማሚ ነው! (1 ዮሐንስ 4:8) “ጥሩ ነውና፤ ፍቅራዊ ደግነቱም ለዘላለም ነውና” የሚለው ለይሖዋ የሚቀርበው በሰፊው የታወቀ የውዳሴ መግለጫ ይህንን ባሕርይ ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ነው።
14. የአምላክን ጥሩነትና ፍቅራዊ ደግነት የሚያገኙት በተለይ እነማን ናቸው?
14 “ፍቅራዊ ደግነቱ የበዛ” መሆኑ የይሖዋ ጥሩነት አንዱ መግለጫ ነው። በተለይ ራሳቸውን ለወሰኑ የታመኑ ሰብዓዊ አገልጋዮቹ የሚያደርገው እንክብካቤ ይህንን በግልጽ ያሳያል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) የእርሱ ምሥክሮች የሆኑ ሰዎች እንደሚያረጋግጡት ይሖዋ ለሚወድዱትና ለሚያገለግሉት ሰዎች ‘ፍቅራዊ ደግነትን ይጠብቃል።’ (ዘጸአት 20:6) የሥጋዊ እስራኤል ብሔር የይሖዋን ልጅ ለመቀበል እምቢተኛ በመሆኑ የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነት ወይም ታማኝ ፍቅር ተነፍጓል። ይሁን እንጂ አምላክ ከሁሉም ብሔራት ለተውጣጡ የታመኑ ክርስቲያኖች የሚያሳየው ፍቅራዊ ደግነት ለዘላለም ይቀጥላል።—ዮሐንስ 3:36
ይሖዋ—መሐሪና ደግ አምላክ
15. (ሀ) ሙሴ በሲና ተራራ የሰማው መግለጫ የሚጀምረው በየትኞቹ ቃላት ነው? (ለ) ምሕረት ምንን ይጨምራል?
15 ሙሴ በሲና ተራራ ላይ የሰማው መግለጫ የሚጀምረው “ይሖዋ፣ ይሖዋ መሐሪ፣ ደግ” በማለት ነው። “ምሕረት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ‘አንጀትንም’ ሊያመለክት ይችላል። ይህ ደግሞ “ማሕፀን” ከሚለው ቃል ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው። በመሆኑም ምሕረት አንድ ሰው የሚሰማውን ጥልቅ የመራራት ስሜት ይጨምራል። ይሁንና ምሕረት ልባዊ አዘኔታ ከማሳየት የበለጠ ነገርንም ይጠይቃል። የሌሎችን ሥቃይ ለማቃለል ስንል አንድ ነገር እንድናደርግ የሚያነሳሳ ባሕርይ ነው። ለምሳሌ ያህል አፍቃሪ የሆኑ ክርስቲያን ሽማግሌዎች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለእምነት ወንድሞቻቸው ‘በደስታ ምሕረት’ በማሳየት መሐሪዎች ሆነው መገኘታቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይገነዘባሉ።—ሮሜ 12:8፤ ያዕቆብ 2:13፤ ይሁዳ 22, 23
16. ይሖዋ ደግ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
16 የአምላክ ጥሩነት በደግነት ባሕርይውም ተንጸባርቋል። ደግ የሆነ ሰው “ለሌሎች ስሜት በእጅጉ ያስባል” እንዲሁም ለሌሎች በተለይም ‘ከእርሱ ለሚያንሱት ርኅራኄ ያሳያል።’ ከታመኑ አገልጋዮቹ ጋር ባለው ግንኙነት ደግነት በማሳየት ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ግሩም ምሳሌ ነው። ለምሳሌ ያህል መልአክ በመላክ አረጋዊውን ዳንኤልን በደግነት አበርትቶታል እንዲሁም ድንግል ልጃገረድ የነበረችውን ማርያምን ስላገኘችው ኢየሱስን የመውለድ መብት በደግነት አብስሯታል። (ዳንኤል 10:19፤ ሉቃስ 1:26-38) የይሖዋ ሕዝብ እንደመሆናችን መጠን ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች አማካኝነት እኛን የሚያነጋግርበትን ደግነት የተንጸባረቀበት መንገድ እንደምናደንቅ የታወቀ ነው። ስላሳየን ጥሩነት እናወድሰዋለን፤ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ደግ ሆነን ለመገኘት እንጥራለን። መንፈሳዊ ብቃቱ ያላቸው ወንዶች የእምነት ወንድማቸውን “በየውሃት መንፈስ” ሲያቀኑ ደግነት ለማሳየት ይጥራሉ።—ገላትያ 6:1
ለቁጣ የዘገየ አምላክ
17. ይሖዋ “ለቁጣ የዘገየ” በመሆኑ አመስጋኝ የምንሆነው ለምንድን ነው?
17 “ለቁጣ የዘገየ . . . አምላክ ነው።” እነዚህ ቃላት ደግሞ ሌላኛውን የይሖዋ ጥሩነት ገጽታ ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። ይሖዋ ስህተቶቻችንን በመታገስ ከባድ ድክመቶቻችንን አሸንፈን መንፈሳዊ መሻሻል እንድናደርግ ጊዜ ይሰጠናል። (ዕብራውያን 5:12–6:3፤ ያዕቆብ 5:14, 15) የአምላክ ትዕግሥት ገና የእርሱ አምላኪ ያልሆኑትንም ሰዎች ይጠቅማል። ለመንግሥቱ መልእክት ምላሽ ሰጥተው ንስሐ ለመግባት አሁንም በሩ ክፍት ነው። (ሮሜ 2:4) ይሖዋ ታጋሽ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ጥሩነቱ እስራኤላውያን በሲና ተራራ የወርቅ ጥጃ ባመለኩ ጊዜ እንዳደረገው ቁጣውን እንዲገልጽ ያነሳሳዋል። አምላክ በቅርቡ የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው ሲያመጣ ቁጣውን በሰፊው ይገልጣል።—ሕዝቅኤል 38:19, 21-23
18. እውነትን በተመለከተ በይሖዋና በሰብዓዊ መሪዎች መካከል የሚታየው ልዩነት ምንድን ነው?
18 “ባለ ብዙ . . . እውነት [የሆነ] አምላክ።” ይሖዋ ያለ የሌለ ተስፋ ሰጥተው ቃላቸውን መጠበቅ ከሚሳናቸው ሰብዓዊ መሪዎች ምንኛ የተለየ ነው! በተቃራኒው ግን ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች በመንፈስ አነሳሽነት በሰፈረው ቃሉ ውስጥ ባለው ነገር ሁሉ ላይ እምነት ሊጥሉ ይችላሉ። አምላክ ባለ ብዙ እውነት ስለሆነ ምንጊዜም በሚሰጠው የተስፋ ቃል ላይ ልንታመን እንችላለን። ሰማያዊው አባታችን መንፈሳዊ እውነትን አትረፍርፎ በመስጠት ይህን እውነት ለማግኘት ለምናቀርበው ጸሎት ምላሽ እንደሚሰጠን የተረጋገጠ ነው። ይህም የጥሩነቱ መግለጫ ነው።—መዝሙር 43:3፤ 65:2
19. ይሖዋ ንስሐ ለሚገቡ ኃጢአተኞች ምን ድንቅ ጥሩነት አሳይቷል?
19 “ይሖዋ . . . ስህተትና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል . . . አምላክ ነው።” ይሖዋ በጥሩነቱ የተነሳ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው። አፍቃሪ የሆነው ሰማያዊ አባታችን በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅርታ ማግኘት የምንችልበትን ዝግጅት በማድረጉ በጣም አመስጋኝ ነን። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) በቤዛው ላይ እምነት ያላቸው ሁሉ ቃል በተገባው አዲስ ዓለም ውስጥ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት የማግኘት ተስፋ መጨበጣቸውና በይሖዋ ፊት ሞገስ አግኝተው ከእርሱ ጋር መወዳጀት መቻላቸው ያስደስተናል። ለሰው ልጅ ያሳየው ይህ ጥሩነት ይሖዋን የምናወድስበት እንዴት ያለ ግሩም ምክንያት ነው!—2 ጴጥሮስ 3:13
20. አምላክ የክፋት ድርጊትን አቅልሎ እንደማይመለከት ምን ማረጋገጫ አለን?
20 “ይሖዋ . . . ሳይቀጣ የማያልፍ፣ . . . አምላክ ነው።” ይህም ቢሆን ይሖዋን ስለ ጥሩነቱ እንድናወድሰው የሚያደርግ ሌላ ምክንያት ነው። ለምን? ምክንያቱም የጥሩነት አንዱ መሠረታዊ ገጽታ በምንም ዓይነት መንገድ ክፉ ድርጊትን አቃልሎ አለመመልከቱ ነው። ከዚህም በተጨማሪ “ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር . . . ሲገለጥ . . . እግዚአብሔርን የማያውቁትን፣ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል።” ‘በዘላለምም ጥፋት ይቀጣሉ።’ (2 ተሰሎንቄ 1:6-9) ከዚያ በኋላ በሕይወት የሚተርፉት የይሖዋ አምላኪዎች ‘ጥሩ የሆነውን በማይወዱ’ አምላካዊ አክብሮት የሌላቸው ሰዎች ሳይታወኩ ሕይወትን ያጣጥሟታል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-3
የይሖዋን ጥሩነት ኮርጁ
21. ጥሩነትን ማሳየት የሚገባን ለምንድን ነው?
21 ይሖዋን ስለ ጥሩነቱ የምናወድስበትና የምናመሰግንበት ብዙ ምክንያት እንዳለን አያጠያይቅም። የእርሱ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን እኛስ አቅማችን የፈቀደውን ያህል ይህን ባሕርይ ለማንጸባረቅ ልንጥር አይገባንምን? አዎን፣ ይገባናል። ሐዋርያው ጳውሎስም ክርስቲያን ወንድሞቹን “እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ” ሲል አጥብቆ አሳስቧል። (ኤፌሶን 5:1 አ.መ.ት ) ሰማያዊው አባታችን ጥሩነት ተለይቶት አያውቅም። እኛም እንዲሁ ልንሆን ይገባናል።
22. በሚቀጥለው ርዕስ የምንወያየው ስለ ምን ነገር ይሆናል?
22 በሙሉ ልባችን ለይሖዋ ያደርን ሰዎች ከሆንን የእርሱን ጥሩነት ለመኮረጅ ከልባችን እንደምንመኝ ምንም ጥርጥር የለውም። የኃጢአተኛው አዳም ልጆች በመሆናችን ጥሩ የሆነውን ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይሆንልንም። በሚቀጥለው ርዕስ ግን ጥሩነትን ማሳየት የምንችለው ለምን እንደሆነ እንወያያለን። በተጨማሪም ከሁሉ የላቀውን የጥሩነት ምሳሌ ይሖዋን በምን የተለያዩ መንገዶች ልንመስለው እንደምንችልና እንደሚገባም እንመለከታለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ጥሩነት ምንድን ነው?
• የአምላክን ጥሩነት የሚያጎላው የትኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ መግለጫ ነው?
• አንዳንዶቹ የይሖዋ ጥሩነት መግለጫዎች ምንድን ናቸው?
• የይሖዋን የጥሩነት ምሳሌ መኮረጅ ያለብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ የጥንት ሕዝቦቹ ለእርሱ ካቀረቡት የውዳሴ ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ሳይመላለሱ በመቅረታቸው ቀጥቷቸዋል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የታመኑ ቀሪዎች ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰዋል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙሴ ስለ አምላክ ጥሩነት የተሰጠውን ድንቅ መግለጫ ሰምቷል
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች አማካኝነት እኛን ያነጋገረበት መንገድ ጥሩነቱን ያንጸባርቃል