“እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም”
“ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር፣ ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ ይደነቁ ነበር።”—ሉቃስ 4:22
1, 2. (ሀ) ኢየሱስን ይዘው እንዲመጡ የተላኩት ሎሌዎች ባዶ እጃቸውን የተመለሱት ለምንድን ነው? (ለ) በኢየሱስ የማስተማር ችሎታ የተገረሙት ሎሌዎቹ ብቻ እንዳልሆኑ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
ሎሌዎቹ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ሳይፈጽሙ ቀሩ። ኢየሱስ ክርስቶስን ይዘው እንዲመጡ ቢላኩም ባዶ እጃቸውን ተመለሱ። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም “ያላመጣችሁት ስለ ምን ነው?” በማለት ጠየቋቸው። በእርግጥም ሎሌዎቹ ራሱን ለማዳን ምንም ዓይነት ኃይል የማይጠቀመውን ይህን ሰው ይዘው መምጣት ያቃታቸው ለምን ይሆን? ሎሌዎቹም “እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም” በማለት መለሱ። በኢየሱስ ትምህርቶች በጣም ከመገረማቸው የተነሳ እንዲህ ያለውን ሰላማዊ ሰው ይዘው ማምጣት በጣም ከበዳቸው።a—ዮሐንስ 7:32, 45, 46
2 በኢየሱስ የማስተማር ችሎታ የተገረሙት እነዚህ ሎሌዎች ብቻ አልነበሩም። ኢየሱስን ለማዳመጥ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ይጎርፉ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። በትውልድ ከተማው የሚኖሩ ሰዎች “ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ” ተደንቀዋል። (ሉቃስ 4:22) ጀልባ ላይ ሆኖ በገሊላ የባሕር ዳርቻ ለተሰበሰቡ እጅግ ብዙ ሰዎች ከአንድ ጊዜ በላይ ትምህርት ሰጥቷል። (ማርቆስ 3:9፤ 4:1፤ ሉቃስ 5:1-3) በአንድ ወቅት ደግሞ “ብዙ ሕዝብ” ምግብ የሚባል ነገር በአፋቸው ሳይዞር ለብዙ ቀናት አብረውት ቆይተዋል።—ማርቆስ 8:1, 2
3. ኢየሱስ ተወዳዳሪ የማይገኝለት አስተማሪ እንዲሆን ያደረገው ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው?
3 ኢየሱስን ተወዳዳሪ ያልተገኘለት አስተማሪ ያደረገው ምንድን ነው? ዋነኛው ምክንያት ፍቅር ነው።b ኢየሱስ ለሚያስተምረው እውነትና ለሚያስተምራቸው ሰዎች ፍቅር ነበረው። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ የተለያዩ የማስተማሪያ ዘዴዎችን የመጠቀም ልዩ የሆነ ችሎታ ነበረው። በዚህና በሚቀጥሉት ሁለት የጥናት ርዕሶች ላይ ኢየሱስ የተጠቀመባቸውን አንዳንድ ውጤታማ የማስተማሪያ ዘዴዎች እንመለከታለን፤ እንዲሁም እንዴት ልንኮርጃቸው እንደምንችል እንማራለን።
ቀላልና ግልጽ
4, 5. (ሀ) ኢየሱስ ሲያስተምር ግልጽ የሆኑ ቃላትን የተጠቀመው ለምን ነበር? እንዲህ ማድረጉ የሚያስደንቅ ነገር የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የተራራው ስብከት ኢየሱስ ቀለል ባለ መንገድ ያስተምር እንደነበር የሚያሳየው እንዴት ነው?
4 ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ብዙ ሰዎች በንግግራቸው ውስጥ ከአድማጮቻቸው የመረዳት አቅም በላይ በሆኑ ቃላት ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው። ሰዎች የምንናገረውን ለመረዳት የሚቸግራቸው ከሆነ ከምንሰጣቸው ትምህርት እንዴት መጠቀም ይችላሉ? ኢየሱስ አድማጮቹ ለመረዳት በሚያስቸግራቸው መንገድ አላስተማረም። ኢየሱስ ምን ያህል ቃላት ሊያውቅ እንደሚችል ለአንድ አፍታ አስብ። ከፍተኛ እውቀት የነበረው ቢሆንም እንኳ ሲያስተምር የአድማጮቹን የትምህርት ደረጃ ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር። ከአድማጮቹ መካከል ብዙዎቹ “መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ” እንደነበሩ ያውቃል። (ሥራ 4:13) የእነዚህን ሰዎች ልብ ለመንካት ሊገባቸው በሚችል መንገድ ይናገር ነበር። የተጠቀመባቸውን ቃላት በቀላሉ መረዳት የሚቻል ቢሆንም የሚያስተላልፉት እውነት ግን ከፍተኛ ነበር።
5 ከማቴዎስ 5:3 እስከ 7:27 ድረስ ተመዝግቦ የሚገኘውን የኢየሱስ የተራራ ስብከት እንደ ምሳሌ አድርገን እንመልከት። ኢየሱስ ይህን ንግግር ለማቅረብ ከ20 ደቂቃ የሚበልጥ ጊዜ አልወሰደበት ይሆናል። ሆኖም ትምህርቶቹ ጥልቅ ከመሆናቸውም በላይ እንደ ዝሙት፣ ፍቺና ፍቅረ ነዋይን የመሰሉ ጉዳዮችን ከሥረ መሠረታቸው የሚያብራሩ ናቸው። (ማቴዎስ 5:27-32፤ 6:19-34) እንደዚያም ሆኖ ትምህርቶቹ የተወሳሰቡ ወይም ለመረዳት የሚከብዱ አልነበሩም። የተጠቀመባቸው ቃላት አንድ ትንሽ ልጅ እንኳ ሳይቀር በቀላሉ ሊረዳቸው የሚችላቸው ናቸው! ትምህርቱን ከተከታተሉት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ገበሬዎች፣ እረኞችና ዓሣ አጥማጆች ሳይሆኑ አይቀርም። አስተምሮ ሲጨርስ ‘በትምህርቱ መገረማቸው’ የሚያስደንቅ አይደለም።—ማቴዎስ 7:28
6. ኢየሱስ ቀላል ሆኖም ጥልቅ ትርጉም ያላቸው አባባሎችን ይናገር እንደነበር የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ጥቀስ።
6 ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ ግልጽና አጠር፣ አጠር ያሉ ሐረጎችን በመጠቀም ቀላል ሆኖም ጥልቅ ትርጉም የነበራቸውን ሐሳቦች ያስተላልፍ ነበር። መጻሕፍት በማይታተሙበት በዚያ ዘመን መልእክቱን በአድማጮቹ አእምሮና ልብ ላይ እንዲታተም አድርጓል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት:- “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ . . . ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።” “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ።” “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።” “ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም።” “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ።” “የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ።” ‘ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ደስተኛ ነው።’c (ማቴዎስ 6:24፤ 7:1, 20፤ 9:12፤ 26:52፤ ማርቆስ 12:17፤ ሥራ 20:35) ኢየሱስ እነዚህን ኃይል ያላቸው አባባሎች ከተናገረ ወደ 2, 000 የሚጠጉ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም እንኳ ትምህርቶቹን በዛሬው ጊዜም በቀላሉ ማስታወስ ይቻላል።
በጥያቄዎች መጠቀም
7. ኢየሱስ ጥያቄዎችን ይጠይቅ የነበረው ለምንድን ነው?
7 ኢየሱስ ግሩም በሆነ መንገድ በጥያቄዎች ይጠቀም ነበር። ጊዜ ሳያባክን ለአድማጮቹ ነጥቡን ብቻ ነግሮ ዞር ማለት ሲችል በተደጋጋሚ በጥያቄዎች ይጠቀም ነበር። ታዲያ ጥያቄዎችን ይጠይቅ የነበረው ለምንድን ነው? አንዳንድ ጊዜ የተቃዋሚዎቹን የውስጥ ስሜት ለማጋለጥና አፋቸውን ለማስያዝ ልብ የሚነኩ ጥያቄዎችን ይጠይቅ ነበር። (ማቴዎስ 12:24-30፤ ማቴዎስ 21:23-27፤ ማቴዎስ 22:41-46) ብዙውን ጊዜ ግን ኢየሱስ እውነትን ለማስተላለፍ፣ አድማጮቹ የልባቸውን አውጥተው እንዲናገሩ ለማደፋፈር እንዲሁም የደቀ መዛሙርቱን አስተሳሰብ ለመቀስቀስና ለማሰልጠን ጊዜ ወስዶ ጥያቄዎችን ይጠይቅ ነበር። እስቲ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ያቀረቡለትን ሁለት ጥያቄዎች እንደ ምሳሌ አድርገን እንመልከት።
8, 9. ለቤተ መቅደስ ግብር መክፈልን በተመለከተ ኢየሱስ ጥያቄዎችን በመጠቀም ጴጥሮስ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ የረዳው እንዴት ነው?
8 በመጀመሪያ፣ ግብር የሚቀበሉ ሰዎች ኢየሱስ ለቤተ መቅደሱ ይገብር እንደሆነ ለጴጥሮስ ጥያቄ ያቀረቡለትን ጊዜ እናስታውስ።d ጴጥሮስ እንደተለመደው በችኮላ “አዎን ይገብራል” በማለት መለሰ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ኢየሱስ ለጴጥሮስ እንዲህ በማለት የሚያመራምሩ ጥያቄዎች አቀረበለት:- “ስምዖን ሆይ፣ ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥና ግብር ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸውን ወይስ ከእንግዶች? አለው። ጴጥሮስም:- ከእንግዶች ባለው ጊዜ ኢየሱስ:- እንኪያስ ልጆቻቸው ነጻ ናቸው” አለው። (ማቴዎስ 17:24-27) ኢየሱስ ጥያቄ በመጠየቅ ሊያስተላልፍ የፈለገው ነገር ለጴጥሮስ ግልጽ ሆኖለት መሆን አለበት። ለምን?
9 በኢየሱስ ዘመን የነገሥታት ቤተሰቦች ግብር ከመክፈል ነፃ እንደነበሩ ይታወቅ ነበር። በመሆኑም በቤተ መቅደሱ አምልኮ የሚቀርብለት የሰማያዊው ንጉሥ አንድያ ልጅ ኢየሱስ ግብር እንዲከፍል አይጠበቅበትም ነበር። ኢየሱስ ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄዎችን በመጠቀም ጴጥሮስ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ረድቶታል እንዲሁም ምናልባትም ከመናገር በፊት ማሰብ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝቦታል።
10, 11. ጴጥሮስ በ33 እዘአ የማለፍ በዓል ምሽት የአንድን ሰው ጆሮ በቆረጠ ጊዜ ኢየሱስ ምን አለ? ኢየሱስ በጥያቄዎች የመጠቀምን አስፈላጊነት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ይህ እንዴት ያሳያል?
10 ሁለተኛው ምሳሌ በ33 እዘአ የማለፍ በዓል በተከበረበት ምሽት አንድ የሰዎች ቡድን ኢየሱስን ለመያዝ በመጡ ጊዜ የደረሰውን አንድ ክንውን የሚመለከት ነው። ደቀ መዛሙርቱ ተዋግተው እንዲያድኑት ይፈልግ እንደሆነ ኢየሱስን ጠየቁት። (ሉቃስ 22:49) ጴጥሮስ መልስ እስኪሰጣቸው ድረስ ሳይጠብቅ ተጣድፎ የአንዱን ሰው ጆሮ በሰይፍ ቆረጠው። (ጴጥሮስ ከዚህ የባሰ ከባድ ጉዳት ለማድረስ የሰነዘረ ይመስላል።) ኢየሱስ ራሱን አሳልፎ ለመስጠት ተዘጋጅቶ ስለነበር የጴጥሮስ ድርጊት ከጌታው ፈቃድ ጋር ፈጽሞ የሚቃረን ነበር። ኢየሱስ ምን ምላሽ ሰጠ? በተለመደ እርጋታው ለጴጥሮስ ሦስት ጥያቄዎችን አቀረበለት:- “አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣትምን?” “አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን? እንዲህ ከሆነስ:- እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?”—ዮሐንስ 18:11፤ ማቴዎስ 26:52-54
11 እስቲ ቆም ብለን በዚህ ታሪክ ላይ ጥቂት እናስብ። በቁጣ ገንፍለው በመጡ ሰዎች መካከል ይገኝ የነበረው ኢየሱስ እንደሚሞትና በእርሱ ሞት አማካኝነት የአባቱ ስም ከስድብ እንደሚጠራና ሰብዓዊው ቤተሰብ እንደሚድን ያውቅ ነበር። ሆኖም በዚያች ወቅት ጥያቄዎችን በመጠቀም ለጴጥሮስ አስፈላጊ የሆኑ እውነቶችን ለማስጨበጥ ፈለገ። ኢየሱስ በጥያቄዎች የመጠቀምን አስፈላጊነት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ይህ በግልጽ አያሳይምን?
አጋንኖ የማቅረብ ዘዴ
12, 13. (ሀ) ግነት ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ የወንድሞቻችንን ጥቃቅን ጉድለቶች እያነሱ መተቸት ሞኝነት እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ለመግለጽ አጋንኖ በመናገር ዘዴ የተጠቀመው እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት ሌላ ዓይነት ውጤታማ የማስተማሪያ ዘዴ ይጠቀም ነበር። ይህም ግነት ይባላል። ይህ አንድን ጉዳይ ጠበቅ አድርጎ ለመግለጽ ሆን ተብሎ አጋንኖ የመናገር ዘዴ ነው። ኢየሱስ አንድ ጉዳይ ፈጽሞ ሊረሳ በማይችል መንገድ በአእምሮ ውስጥ ሕያው ሆኖ እንዲቀመጥ ለማድረግ አጋኖ የማቅረብ ዘዴ ይጠቀም ነበር። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።
13 ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ‘በሌሎች ላይ መፍረድ’ ተገቢ እንዳልሆነ ጠበቅ አድርጎ ለማስገንዘብ “በወንድምህም ዓይን ያለውን ጕድፍ ስለ ምን ታያለህ፣ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም?” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:1-3) ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ መመልከት ትችላለህ? በትንሽ በትልቁ ሌሎችን የመንቀፍ ዝንባሌ ያለው ሰው ከወንድሙ “ዓይን” ውስጥ ጉድፍ ለማውጣት የሚሞክር ያህል ነው። ይህ ሰው ወንድሙ ነገሮችን አጥርቶ የማየት ችግር ስላለበት አመዛዝኖ ጥሩ ፍርድ መስጠት አይችልም የሚል አመለካከት አለው። ሆኖም ይህን ትችት የሚሰነዝረው ሰው በራሱ ዓይን ውስጥ “ምሰሶ” ማለትም የቤትን ጣሪያ ደግፎ ለማቆም የሚያገለግል ረዥም ግንድ ስላለ ፍርድ የመስጠት ችሎታው ተዛብቶበታል። እኛ ራሳችን ከፍተኛ ጉድለት እያለብን የወንድሞቻችንን ጥቃቅን ጉድለቶች እየለቃቀምን መተቸት ሞኝነት እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ለመግለጽ ይህ እንዴት ያለ ግሩም የማስተማሪያ ዘዴ ነው!
14. ኢየሱስ ትንኝን ስለማጥራትና ግመልን ስለመዋጥ የተናገረው አባባል የፈሪሳውያንን ሁኔታ ሕያው አድርጎ የሚገልጽ ግነት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
14 በሌላ ወቅት ደግሞ ኢየሱስ ፈሪሳውያንን ሲያወግዝ “እናንተ ዕውሮች መሪዎች፣ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 23:24) ይህ በተለይ ፈሪሳውያን ያሉበትን ሁኔታ ሕያው አድርጎ የሚገልጽ ግነታዊ ዘይቤ ነው። እንዴት? በአንዲት ትንሽ ትንኝና ኢየሱስን ያዳምጡ በነበሩት ሰዎች ዘንድ እንደ ትልቅ እንስሳ ተደርጎ በሚታየው በግመል መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው። መካከለኛ ክብደት ያለው አንድ ግመል ከ70 ሚልዮን ትንኞች ጋር እኩል እንደሚሆን ይገመታል! እንዲሁም ፈሪሳውያን የሚጠጡትን ወይን ጠጅ በጨርቅ እንደሚያጠልሉ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። እነዚህ ሕግ አጥባቂዎች እንዲህ የሚያደርጉት ከወይኑ ጋር ትንኝ እንዳይውጡና በሕጉ መሠረት እንደ ርኩስ እንዳይታዩ ነበር። የሚያሳዝነው ግን ርኩስ የሆነውን ግመል ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ይውጡ ነበር። (ዘሌዋውያን 11:4, 21-24) የኢየሱስ መልእክት ግልጽ ነው። ፈሪሳውያን ሕጉ የሚጠይቀውን እያንዳንዱን ጥቃቅን ነገር ሲጠብቁ “ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም” የመሳሰሉ ከበድ ያሉ ጉዳዮችን ግን ችላ ይሉ ነበር። (ማቴዎስ 23:23) ኢየሱስ እውነተኛ ማንነታቸውን ግልጽ በሆነ መንገድ አጋልጧል!
15. ኢየሱስ ግነትን ተጠቅሞ ያስተማራቸው አንዳንዶቹ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው?
15 ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ ግነት ይጠቀም ነበር። ጥቂት ምሳሌዎችን ተመልከት። ኢየሱስ “የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት” ተራራን ሊያንቀሳቅስ እንደሚችል ተናግሯል። ኢየሱስ በጣም ትንሽ የሆነ እምነት ትልቅ ነገር ሊያከናውን እንደሚችል ጠበቅ አድርጎ ለመግለጽ ከዚህ በተሻለ መንገድ ሊናገር አይችልም። (ማቴዎስ 17:20) በአንዲት የመርፌ ቀዳዳ ለማለፍ ሙከራ የሚያደርግ አንድ ግዙፍ ግመል ቁሳዊ ሃብትን እያሳደደ አምላክን ለማገልገል ጥረት የሚያደርግ ሰው ያለበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ጥሩ አድርጎ የሚያሳይ ነው! (ማቴዎስ 19:24) ሕያው በሆነው በኢየሱስ ምሳሌያዊ አነጋገርና በጥቂት ቃላት ከፍተኛ ቁም ነገር በማስጨበጥ ችሎታው አትደነቅም?
አሳማኝ ምክንያቶች
16. ኢየሱስ የማገናዘብ ችሎታውን የተጠቀመበት ለምን ዓላማ ብቻ ነው?
16 ፍጹም አእምሮ የነበረው ኢየሱስ ትክክለኛ ነጥቦችን በማቅረብ ሰዎችን የማሳመን ልዩ ተሰጥዖ ነበረው። ሆኖም ይህን ችሎታውን ተገቢ ባልሆነ መንገድ አልተጠቀመበትም። በሚያስተምርበት ጊዜ የማገናዘብ ችሎታውን የተጠቀመበት እውነትን ለማስፋፋት ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎቹ የሚሰነዝሩበትን የሐሰት ክስ ውድቅ ለማድረግ አሳማኝ ምክንያቶችን ይጠቀም ነበር። አብዛኛውን ጊዜ አስፈላጊ የሆኑ ትምህርቶችን ለደቀ መዛሙርቱ ለማስጨበጥ አሳማኝ ምክንያቶችን ተጠቅሟል። ኢየሱስ አሳማኝ ምክንያቶችን የመጠቀም ከፍተኛ ችሎታ እንዳለው የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
17, 18. ኢየሱስ ፈሪሳውያን ያስነሱበትን የሃሰት ክስ ውድቅ ለማድረግ የተጠቀመው አሳማኝ ምክንያት ምን ነበር?
17 ኢየሱስ ዓይነ ስውርና ዲዳ የነበረን በአጋንንት የተያዘ አንድ ሰው ሲፈውስ የተከሰተውን ሁኔታ ተመልከት። ፈሪሳውያን ኢየሱስ ሰውዬውን እንደፈወሰው ሲሰሙ “ይህ በብዔል ዜቡል [በሰይጣን] በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም አሉ።” ሰይጣን የሚቆጣጠራቸውን አጋንንት ለማውጣት ከሰው የሚበልጥ ኃይል እንደሚያስፈልግ ፈሪሳውያን ያምኑ እንደነበር ልብ በል። ይሁን እንጂ ሕዝቡ በኢየሱስ እንዳያምኑ ለማድረግ ኃይሉን ያገኘው ከሰይጣን እንደሆነ ተናገሩ። እንዲህ ያለው ክርክራቸው ወደምን መደምደሚያ ሊያደርሳቸው እንደሚችል ለማሳየት ኢየሱስ “እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፣ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፣ እርስ በርሱ ተለያየ፣ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች?” በማለት መለሰላቸው። (ማቴዎስ 12:22-26) ኢየሱስ ‘እናንተ እንደምትሉት እኔ የሰይጣንን ሥራ የማፈርስ የሰይጣን አገልጋይ ከሆንኩ እንግዲያው ሰይጣን የሚሠራው ለራሱ ጉዳትና ውድቀት ነው’ ማለቱ ነበር። እንዴት ያለ አሳማኝ ምክንያት ነው!
18 ኢየሱስ ይህን ጉዳይ በማስመልከት ተጨማሪ አሳማኝ ምክንያት አቀረበ። ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ ሰዎች አጋንንት እንደሚያወጡ ያውቅ ነበር። ስለዚህ “እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፣ ልጆቻችሁ [ወይም ደቀ መዛሙርቶቻችሁ] በማን ያወጡአቸዋል?” የሚል በጣም ቀላል ሆኖም አስደንጋጭ ጥያቄ አቀረበ። (ማቴዎስ 12:27) ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት መከራከሩ ነበር:- ‘እኔ አጋንንትን የማወጣው በሰይጣን ኃይል ከሆነ የእናንተም ደቀ መዛሙርት አጋንንትን የሚያወጡት በሰይጣን ኃይል ነው ማለት ነው።’ ፈሪሳውያን ምን ምላሽ ሰጡ? ደቀ መዛሙርቶቻቸው አጋንንትን የሚያወጡት በሰይጣን ኃይል ነው ብለው እንደማይቀበሉ የታወቀ ነው። ኢየሱስ ሊታበል የማይችል አሳማኝ ምክንያት በማቅረብ በእርሱ ላይ ያነሱት ክስ መሠረት የሌለው መሆኑን አሳይቷል።
19, 20. (ሀ) ኢየሱስ አሳማኝ ምክንያቶችን አዎንታዊ በሆነ መንገድ ለማስተማር የተጠቀመው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ መጸለይ እንዲያስተምራቸው ለጠየቁት ጥያቄ ለደቀ መዛሙርቱ መልስ ሲሰጥ ‘እንዴት አብልጦ’ በሚል አሳማኝ አባባል የተጠቀመው እንዴት ነው?
19 ኢየሱስ አሳማኝ ምክንያቶችን የማቅረብ ችሎታውን የተቃዋሚዎቹን አፍ ለማዘጋት ከመጠቀሙም በተጨማሪ ስለ ይሖዋ አዎንታዊና ልብን የሚነካ እውነት ለማስተማርም ተጠቅሞበታል። አድማጮቹ በሚያውቁት እውነት ላይ የጸና እምነት እንዲያዳብሩ ለመርዳት ብዙውን ጊዜ ‘እናንተንማ እንዴት አብልጦ’ እንደሚሉ ያሉ የማሳመኛ ምክንያቶችን ይጠቀም ነበር። ቢያንስ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት።
20 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ መጸለይ እንዲያስተምራቸው በጠየቁት ጊዜ የፈለገውን ነገር ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነውን ወዳጁን ‘ሳይታክት ነዝንዞ’ ስላሳመነ አንድ ሰው የሚገልጽ ምሳሌ ተናገረ። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ወላጆች ለልጆቻቸው ‘መልካም ስጦታ ለመስጠት’ ምን ያህል ፈቃደኛ እንደሆኑ ተናገረ። ከዚያም እንዲህ በማለት ደመደመ:- ‘እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፣ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?’ (ሉቃስ 11:1-13) ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተጠቀመው በይሖዋና በሰብዓዊ ፍጡራን መካከል ያለውን ተመሳሳይ ባሕርይ ጠቅሶ ለማስተማር ሳይሆን በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በማሳየት አንድ ነጥብ ለማስጨበጥ ነው። ፈቃደኛ ያልነበረ ወዳጅ ሐሳቡን ለውጦ የጎረቤቱን ጥያቄ ለማሟላት ከተነሳሳ፣ ፍጽምና የጎደላቸው ወላጆች ደግሞ የልጆቻቸውን ፍላጎት የሚያሟሉ ከሆነ አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ራሳቸውን ዝቅ አድርገው በጸሎት ወደ እርሱ ለሚቀርቡት ታማኝ አገልጋዮቹ መንፈስ ቅዱሱን ምን ያህል አብልጦ ይሰጣቸው!
21, 22. (ሀ) ኢየሱስ ለቁሳዊ ነገሮች መጨነቅን በተመለከተ ምክር ሲሰጥ ምን አሳማኝ ምክንያት አቀረበ? (ለ) ኢየሱስ የተጠቀመባቸውን አንዳንድ የማስተማሪያ ዘዴዎች በአጭሩ መከለሳችን ምን መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ይረዳናል?
21 ኢየሱስ ለቁሳዊ ነገሮች መጨነቅን አስመልክቶ ምክር ሲሰጥ ተመሳሳይ ዘዴ ተጠቅሟል። እንዲህ አለ:- ‘ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም፣ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፣ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፤ እናንተስ ከወፎች እንዴት ትበልጣላችሁ? አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ . . . እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የሆነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፣ እናንተንማ ይልቁን እንዴት?’ (ሉቃስ 12:24, 27, 28) ይሖዋ ወፎችንና አበቦችን እንኳን የሚንከባከብ ከሆነ አገልጋዮቹንማ ምን ያህል ይንከባከባቸው ይሆን! እንዲህ ያለው አሳቢነት የተሞላበት ሆኖም አሳማኝ ምክንያት የማቅረብ ዘዴ የኢየሱስን አድማጮች ልብ እንደነካ ምንም ጥርጥር የለውም።
22 ኢየሱስ ስለተጠቀመባቸው ስለ አንዳንዶቹ የማስተማሪያ ዘዴዎች መመልከታችን ይዘውት እንዲመጡ የተላኩት ሎሌዎች “እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም” ያሉበትን ምክንያት በቀላሉ እንድንረዳ ያስችለናል። ኢየሱስ ከተጠቀመባቸው የማስተማሪያ ዘዴዎች መካከል ይበልጥ የሚታወቀው በምሳሌ አጠቃቀሙ ሳይሆን አይቀርም። በምሳሌዎች የተጠቀመው ለምንድን ነው? ምሳሌዎቹ ያን ያህል ውጤታማ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምንድን ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ መልስ ይሰጥባቸዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እነዚህ ሎሌዎች በካህናት አለቆች ሥልጣን ሥር የሚያገለግሉ የአይሁድ የፍርድ ሸንጎ ወኪሎች ሳይሆኑ አይቀርም።
b በነሐሴ 15, 2002 የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የወጡትን “ምሳሌ ትቼላችኋለሁ” የሚለውንና ‘አለማቋረጥ ይከተለኝ’ የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።
c ‘ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ደስተኛ ነው’ የሚለው በሐዋርያት ሥራ 20:35 ላይ የሚገኘው አባባል ሐሳቡ በወንጌሎች ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም እንኳ ዓረፍተ ነገሩን በቀጥታ ጠቅሶ የተናገረው ሐዋርያው ጳውሎስ ብቻ ነው። ጳውሎስ ይህን ዓረፍተ ነገር የሰማው (ኢየሱስ ሲናገር ካዳመጠ አንድ ደቀ መዝሙር ወይም ትንሣኤ ካገኘው ኢየሱስ) ወይም በራእይ ተነግሮት ሊሆን ይችላል።—ሥራ 22:6-15፤ 1 ቆሮንቶስ 15:6, 8
d አይሁዳውያን በየዓመቱ ለቤተ መቅደሱ ሁለት ዲናር (ለሁለት ቀን ሥራ ከሚከፈል ደሞዝ ጋር ይመጣጠናል) ግብር መክፈል ነበረባቸው። በግብር የሚሰበሰበው ገንዘብ ለቤተ መቅደሱ ጥገና፣ በውስጡ ለሚከናወኑ አገልግሎቶችና ለሕዝቡ በየዕለቱ ለሚቀርበው መሥዋዕት የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ይውል ነበር።
ታስታውሳለህን?
• የኢየሱስ ትምህርቶች ቀላልና ግልጽ እንደነበሩ የትኞቹ ምሳሌዎች ያሳያሉ?
• ኢየሱስ ሲያስተምር በጥያቄዎች ይጠቀም የነበረው ለምንድን ነው?
• ግነት ምንድን ነው? ኢየሱስ ይህን የማስተማሪያ ዘዴ የተጠቀመው ለምንድን ነው?
• ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ልብ የሚነኩትን የይሖዋን እውነቶች ለማስተማር አሳማኝ ምክንያት የማቅረብ ዘዴ የተጠቀመው እንዴት ነው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊገባው በሚችል ቃል ተጠቅሟል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፈሪሳውያን ‘ትንኝን የሚያጠሩና ግመልን የሚውጡ ነበሩ’