‘በጌታ ሥራ የሚደክሙ’ ሴቶች
“በጌታ ሆነው ለሚደክሙ ለፕሮፊሞናና ለጢሮፊሞሳ ሰላምታ አቅርቡልኝ።”—ሮሜ 16:12
1. የኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ለሴቶች በረከት የሆነላቸው በምን መንገድ ነው?
የኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ለአይሁዳውያን ሴቶች እውነተኛ በረከት ሆኖላቸው ነበር። ኢየሱስ የጀመረው ሥራ ለማንኛውም ዘር ሴቶች መጽናናት፣ ተስፋና አዲስ ክብር የሚያመጣላቸው ሆነ። ኢየሱስ ‘የአምላክን ቃል ከንቱ ለሚያደርገው’ የአይሁድ ወግ ምንም ቦታ አልሰጠውም። (ማቴዎስ 15:6) ከእነዚህ ወጎች ውስጥ አምላክ ለሴቶች የሰጣቸውን መብት የሚጻረሩ ብዙ ነበሩ።
ኢየሱስ ለሴቶች የነበረው ዝንባሌ
2. ኢየሱስ ለሴቶች የነበረው ዝንባሌ ለነበረበት ዘመን ስር ነቀል ለውጥ አምጥቷል ለማለት የሚቻለው ለምንድን ነው?
2 ኢየሱስ ለሴቶች በነበረው ዝንባሌና አይሁዳውያን የሃይማኖት መሪዎች በነበራቸው ዝንባሌ መካከል ጉልህ ልዩነት ታይቷል። ኢንሳይክሎፒድያ ጁዳይካ የሚለውን ብንጠቅስ አይሁዳውያን የሃይማኖት መሪዎች ሴቶች “ስግብግቦች፣ ወሬኞች፣ ሰነፎችና ምቀኞች ናቸው” የሚል አመለካከት ነበራቸው። ከሴት ጋር መነጋገር እንደ ቀፋፊ ነገር ይቆጠር ነበር። “ሴትን በመንገድ ዳር ማነጋገር ለአንድ ምሁር እንደ ውርደት ይቆጠር ነበር።” (ኢየሩሳሌም በኢየሱስ ዘመን በጆአኪም ጀርምያስ፣ ከዮሐንስ 4:27 ጋር አወዳድር) የአይሁድ መሪዎች ሴቶችን ስለማጥላላታቸው ብዙ መናገር ይቻል ነበር። ቢሆንም ኢየሱስ ለሴቶች የነበረው ዝንባሌ ለነበረበት ዘመን ሥር ነቀል ለውጥ እንደነበረ ለማሳየት ከላይ የጠቀስነው ይበቃል።
3. ኢየሱስ ለሴቶች ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ ነገሮችን የማስተማር ፍላጎት እንደነበረው የሚያረጋግጡልን የትኞቹ በአገልግሎቱ ዘመናት ያጋጠሙት ሁኔታዎች ናቸው?
3 ወንዶች ከሴቶች ጋር ሞቅ ያለና ንጹሕ የሆነ የኑሮ ግንኙነት ማድረግ እንደሚችሉ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ ይሆነናል። ኢየሱስ ከሴቶች ጋር ከመነጋገሩም ሌላ ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን አስተምሮአቸዋል። እንዲያውም መሲሕነቱን ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጽ የተናገረው ለሴት ነበር፤ ያውም ለሣምራዊት። (ዮሐንስ 4:7, 25, 26) ከዚህም በላይ የማርያምና የማርታ ጉዳይ እንደሚያሳየው ኢየሱስ ሴት ምጣድዋንና ድስትዋን ጥላ መንፈሳዊ እውቀትዋን ለመጨመር ቁጭ ብላ ለማዳመጥ መብት የላትም የሚል አስተያየት እንዳልነበረው በግልጽ አሳይቶአል። የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች አቋም ግን የተለየ ነበር። በዚያን ጊዜ ማርያም መንፈሳዊ ነገሮችን በማስቀደምዋ ‘መልካም ነገር እንደመረጠች’ ተነግሮላታል። (ሉቃስ 10:38-42) ይሁን እንጂ ከጥቂት ወራት በኋላ ወንድማቸው በሞተበት ጊዜ ከጌታ ጋር ለመገናኘት የበለጠ ጉጉት ያሳየችው ማርታ እንጂ ማርያም አልነበረችም። ዛሬም እንኳን ኢየሱስና ማርታ ስለ ትንሣኤ የተነጋገሩትን ጥልቅ መንፈሳዊ ጉዳይ ስናነብ ልባችን በደስታ ይፈነድቃል! (ዮሐንስ 11:20-27) ይህስ ለማርታ እንዴት ያለ መብት ነበር!
ኢየሱስን ያገለገሉ ሴቶች
4, 5. ኢየሱስ በገሊላ ያገለግል በነበረበት ጊዜ ከሐዋርያቱ ሌላ እነማን ይከተሉት ነበር? እንዴትስ ያገለግሉት ነበር?
4 በተጨማሪም ኢየሱስ በይሁዳ ምድር ሲዘዋወር ሴቶች እንዲያገለግሉት ይፈቅድላቸው ነበር። ማርቆስ በወንጌሉ ውስጥ ኢየሱስ “በገሊላ ሳለ ይከተሉትና ያገለግሉት” ስለነበሩ ሴቶች ተናግሮአል። (ማርቆስ 15:40, 41) እነዚህ ሴቶች እነማን ነበሩ? ኢየሱስንስ ያገለገሉት እንዴት ነው? የሁሉንም ስም አናውቅም። ቢሆንም ሉቃስ የአንዳንዶቹን ስም ከጠቀሰልን በኋላ ኢየሱስን እንዴት ያገለግሉት እንደነበሩ ይገልጽልናል።
5 ሉቃስ እንደሚከተለው በማለት ጽፎአል፦ “ከዚህም በኋላ እየሰበከና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች እየተናገረ በየከተማይቱ በየመንደሩም ያልፍ ነበር። አሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ። ከክፉዎች መናፍስትና ከደዌም ተፈውሰው የነበሩ አንዳንድ ሴቶች እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የምትባል ማርያም፣ የሄሮድስ አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐናም ሶስናም ብዙዎች ሌሎችም ሆነው በገንዘባቸው ያገለግሉት ነበር።” (ሉቃስ 8:1-3) ኢየሱስ እነዚህ ሴቶች እንዲከተሉትና እርሱም ሆነ ሐዋርያቱ በሴቶቹ ንብረት እንዲገለገሉ ፈቃደኛ ሆኖ ነበር።
6. (ሀ) ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዝ በነበረበት ጊዜ እነማን ተከትለው ነበር? (ለ) ኢየሱስ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ከጎኑ ያልተለዩት እነማን ነበሩ? አንዳንዶቹስ ለዚህ አድራጎታቸው ምን ወሮታ አግኝተዋል? (ሐ) በዮሐንስ 20:11-18 ላይ የተመዘገበው ታሪክ ከአይሁዳውያን ወግ አንጻር ሲታይ አስደናቂ የሚሆነው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ በተገደለበት ጊዜም “ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ። ከእነርሱም መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ነበሩ።” (ማቴዎስ 27:55, 56) ስለዚህ ኢየሱስ በሞተበት ጊዜ ከጎኑ የቆሙ ብዙ ታማኝ ሴቶች ነበሩ። በተጨማሪም ለኢየሱስ ከሙታን መነሳት የመጀመሪያዎቹ የዐይን ምሥክሮች ሴቶች መሆናቸው ሊጠቀስ የሚገባው ነው። (ማቴዎስ 28:1-10) ይህ ራሱ የአይሁዳውያንን ወግ የሚቃወም ነበር፤ ምክንያቱም በአይሁዳውያን ሥርዓት መሠረት ሴቶች የሕግ ምሥክሮች የመሆን ብቃት አልነበራቸውም። ይህን በአእምሮህ ያዝና ዮሐንስ 20:11-18 እያነበብህ ከሙታን የተነሳው ጌታ ለመግደላዊት ማርያም ሲገለጥላትና በስምዋ ጠርቶ ሕያው መሆኑን ለደቀመዛሙርቱ እንድትመሰክር ሲነግራት ምን ተሰምቶአት እንደነበረ ለመገመት ሞክር።
ከጴንጠቆስጤ በኋላ ይኖሩ የነበሩ ታማኝ ክርስቲያን ሴቶች
7, 8. (ሀ) በጴንጠቆስጤ ቀን መንፈስ ቅዱስ ሲፈስስ ሴቶችም በሥፍራው እንደነበሩ እንዴት ልናውቅ እንችላለን? (ለ) ክርስቲያን ሴቶች ክርስትናን ማስፋፋት በተጀመረ ጊዜ በሥራው የተካፈሉት እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ ካረገ በኋላ አምላክን የሚያከብሩ ሴቶች ከታማኞቹ ሐዋርያት ጋር በኢየሩሳሌም ከተማ በአንድ ሰገነት ውስጥ ተቀምጠው ነበር። (ሥራ 1:12-14) በጴንጠቆስጤ ቀን መንፈስ ቅዱስ ከፈሰሰላቸው ደቀመዛሙርት መካከል ሴቶች እንደነበሩ ግልጽ ነው። ለምን? ምክንያቱም ጴጥሮስ በዚያ ቀን የተፈጸመው ነገር ምን እንደሆነ ሲገልጽ “ሴት ልጆችን” እና “ሴት ባሪያዎችን” የሚጠቅሰውን የኢዩኤል 2:28-30 ትንቢት ጠቅሶአል። (ሥራ 2:1, 4, 14-18) ስለዚህ የክርስቲያን ጉባኤ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በመንፈስ የተወለዱ ቅቡዓን ሴት ክርስቲያኖች በአባልነት ይገኙበት ነበር።
8 በክርስትና መስፋፋት ረገድም ሴቶች ዋነኛ ባይሆኑም በቀላሉ የማይታይ ድርሻ ነበራቸው። የማርቆስ እናትና የበርናባስ አክስት የነበረችው ማርያም ሰፊ ቤትዋን የኢየሩሳሌም ጉባኤ እንዲገለገልበት ሰጥታ ነበር። (ሥራ 12:12) ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነችው በክርስቲያኖች ላይ አዲስ ስደት በተነሳሳበት ጊዜ ነበር። (ሥራ 12:1-5) የወንጌላዊው ፊሊጶስ አራት ሴት ልጆች ክርስቲያን ነቢያት የመሆን መብት አግኝተው ነበር።—ሥራ 21:9፤ 1 ቆሮንቶስ 12:4, 10
ጳውሎስ ለሴቶች የነበረው ዝንባሌ
9. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ሁለተኛ መልእክቱ ላይ ስለ ክርስቲያን ሴቶች ምን ምክር ሰጥቶአል? ሴቶች የትኛውን መለኮታዊ ሥርዓት እንዲያከብሩ አበረታቶአቸዋል?
9 ሐዋርያው ጳውሎስ በሴቶች ላይ ጥላቻና ጥርጣሬ ነበረው እየተባለ የሚከሰስበት ጊዜ አለ። እውነት ነው፤ ሴቶች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ተገቢ ቦታቸውን እንዲጠብቁ አጠንክሮ የተናገረው ጳውሎስ ነው። አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ሴቶች በጉባኤ ስብሰባዎች ማስተማር አይገባቸውም። (1 ቆሮንቶስ 14:33-35) ክርስቲያን ወንድ ሳይኖር ቀርቶ ወይም በመንፈስ ቅዱስ አስገዳጅነት ትንቢት ለመናገር ወይም በክርስቲያን ስብሰባ ላይ ማስተማር ቢኖርባት ግን ራስዋን መሸፋፈን ነበረባት። መሸፈኛው የአምላክን የራስነት ዝግጅት መቀበልዋን የሚያሳይ “የሥልጣን ምልክት” ይሆናታል።—1 ቆሮንቶስ 11:3-6, 10
10. አንዳንዶች ሐዋርያው ጳውሎስን ምን ብለው ይከሱታል? ይሁን እንጂ ይህ ክስ ሐሰት መሆኑን የሚያረጋግጥልን ምንድን ነው?
10 ጳውሎስ ለጥንቶቹ ክርስቲያኖች ስለእነዚህ ቲኦክራቲካዊ ሥርዓቶች ማሳሰብ አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ‘በሥርዓትና በአገባብ’ እንዲከናወኑ ሲል እንደሆነ ግልጽ ነው። (1 ቆሮንቶስ 14:40) ታዲያ እንዲህ ስላለ ጳውሎስ አንዳንዶች እንደሚሉት ጸረ ሴት ነበር ማለት ነውን? አይደለም። ለሮማ ክርስቲያኖች የጻፈውን ደብዳቤ ሲደመድም ለዘጠኝ ክርስቲያን ሴቶች ሞቅ ያለ ሰላምታ የላከው ጳውሎስ አይደለምን? ፌበንን፣ ጵርስቅላን፣ ፕሮፊሞናንና ጢሮፊሞሳን ከልቡ አድንቆ የለምን? እንዲያውም እነዚህን የመጨረሻዎቹን ሁለት ሴቶች “በጌታ የሚደክሙ” ሴቶች በማለት አመስግኖአቸው የለምን? (ሮሜ 16:1-4, 6, 12, 13, 15) በተጨማሪም በመንፈስ አነሳሽነት የሚከተለውን ቃል የጻፈው ጳውሎስ ነው፦ “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና። አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፣ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፣ ወንድም ሴትም የለም። ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።” (ገላትያ 3:27, 28) ጳውሎስ ከባድ ስደት በደረሰበት ጊዜ በምሳሌነት የሚጠቀስ አቀባበል ያደረገችለትን ሊድያን ጨምሮ ክርስቲያን እህቶቹን ይወድና ያደንቅ እንደነበረ ግልጽ ነው።—ሥራ 16:12-15, 40፤ ፊልጵስዩስ 4:2, 3
በዘመናችን ለጌታ የሚደክሙ ሴቶች
11, 12. (ሀ) መዝሙር 68:11 በዛሬው ዘመን ቃል በቃል የተፈጸመው እንዴት ነው? (ለ) ብዙዎቹ እህቶቻችን በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ? ፍቅራችንና ጸሎታችንስ የሚያስፈልጋቸው ለምንድንነው?
11 ዛሬም ቢሆን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ “በጌታ የሚደክሙ” ብዙ ክርስቲያን ሴቶች አሉ። እንዲያውም “ምሥራቹን የሚናገሩ ሴቶች ታላቅ ሠራዊት” እንደሆኑና ይሖዋ በዚህ የፍጻሜ ዘመን ከሚገለገልባቸው የምሥክሮች ሠራዊት ውስጥ አብዛኛውን ክፍል የያዙት ሴቶች መሆናቸውን በአሐዝ የተደገፈ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል። (መዝሙር 68:11 አዓት) እነዚህ በሥራ የሚደክሙ ክርስቲያን ሴቶች የሚስትነት፣ የእናትነት፣ የቤት እመቤትነት፣ የቤት አስተዳዳሪነትና የክርስቲያን አገልጋይነት ግዴታቸውን ለመወጣት ተግተው ስለሚሰሩ ለራሳቸው መልካም ስምና ዝና አትርፈዋል።
12 ከእነዚህ ታማኝ እህቶች መካከል የማያምኑ ባሎች ያሉአቸው ብዙ ናቸው። ይህን አመቺ ያልሆነ ሁኔታ በየቀኑ ለ24 ሰዓት መቋቋም ይኖርባቸዋል። አንዳንዶች ለብዙ ዓመታት ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ያወጣውን ብቃት አሟልተው እየኖሩ ጥሩ ሚስቶችም ሆነው ለመገኘት ሲታገሉ ቆይተዋል። ይህ ሁሉ ቀላል ነገር አይደለም። ቢሆንም ሁልጊዜ በሚያሳዩት ጥሩ ክርስቲያናዊ ምግባር ምክንያት ‘ባሎቻቸው አለ ቃል ይመለሱ ይሆናል’ ብለው ተስፋ በማድረግ ለብዙ ዓመታት ጸንተዋል። እንዲህ ያለው ባል አንድ ቀን በነገሩ ተነክቶ ሲለወጥ ለቤተሰብ እንዴት ያለ ደስታ ይሆናል! (1 ጴጥሮስ 3:1, 2) ይህ እስኪሆን ድረስ ግን እነዚህ ታማኝ እህቶች የሌሎቹ የጉባኤ አባሎች ጸሎትና ፍቅር በጣም ያስፈልጋቸዋል። የሚያሳዩት ‘ዝግተኛና የዋህ መንፈስ’ በአምላክ ፊት እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ሲሆን በአቋማቸው ሳያወላውሉ መጽናታቸው ደግሞ በሁላችንም ዐይን ውድ ነገር ነው።—1 ጴጥሮስ 3:3-6
13. አቅኚ እህቶቻችን በጌታ ሥራ የሚደክሙ ናቸው ሊባል የሚችለው ለምንድንነው? በየጉባኤያቸውስ እንዴት ባለ መንፈስ ሊታዩ ይገባቸዋል?
13 በአቅኚነት የሚያገለግሉ እህቶች “በጌታ የሚደክሙ ናቸው” ሊባሉ ይችላሉ። ብዙዎቹ ከስብከት ሥራቸው በተጨማሪ ቤት፣ ባልና የሚያሳድጉአቸው ልጆች ያሉአቸው ናቸው። አንዳንዶች ለሥጋዊ ኑሮአቸው የሚያስፈልጋቸውን ለማግኘት ትንሽ ትንሽ ይሠራሉ። ይህ ሁሉ የግል ጉዳዮችን ማደራጀትን፣ ቆራጥነትን፣ ትጋትንና ብዙ አድካሚ ሥራን የሚጠይቅ ነው። እነዚህ ክርስቲያን ሴቶች ለስብከቱ ሥራ የአቅኚነት ሰዓት ለማሳለፍ ሁኔታቸው ከማይፈቅድላቸው ሁሉ ድጋፍና ፍቅር ማግኘት ይኖርባቸዋል።
14. (ሀ) ምን ዓይነት ጥሩ የጽናትና የትጋት ምሳሌ ተጠቅሶአል? (ለ) ምሥጋና ሊሰጣቸው የሚገቡ የትኞቹ ሌሎች ሴት ክርስቲያኖች ናቸው? ለምንስ? በአካባቢህ ምሳሌ የሚሆኑ ካሉ ጥቀስ።
14 አንዳንድ ክርስቲያን ሴቶች በአቅኚነት አገልግሎት ከፍተኛ ጥንካሬ አሳይተዋል። በካናዳ አገር የምትኖረው ግሬስ ሉንስበሪ አቅኚነትን ለመጀመሪያ ጊዜ የቀመሰችው በ1914 ነበር። በ1918 ስለታመመች ከአቅኚነት ሥራ ለመውጣት ተገድዳ ነበር። ይሁን እንጂ በ1924 ወደ ሙሉ ጊዜ አገልጋይነትዋ ተመለሰች። ይህ ጽሑፍ በሚዘጋጅበት ጊዜ 104 ዓመት ዕድሜ የሞላት ቢሆንም አቅኚነትዋን አላቋረጠችም! በ1940ዎቹ ዓመታት በመጠበቂያ ግንብ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ከሰለጠኑት ከመጀመሪያዎቹ ሚሲዮናውያን እህቶች መካከል ብዙዎቹ አሁንም በሚሲዮናዊነት ወይም በብሩክሊን ወይም በመጠበቂያ ግንብ ማህበር ቅርንጫፍ ቢሮዎች የቤቴል ቤተሰብ አባሎች ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው። እነዚህ ክርስቲያን እህቶች፣ እንዲያውም በቤቴል አገልግሎት የሚደክሙት እህቶች በሙሉ ራሳቸውን መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ስላላቸው ለሁላችንም ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው። በጣም እንደምንወዳቸውና እንደምናደንቃቸው ገልጸንላቸው እናውቃለንን?
የተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሚስቶች
15, 16. ሞቅ ያለ ምሥጋና ማግኘት የሚገባቸው በተለይ የትኞቹ ክርስቲያን ሴቶች ናቸው? ለምንስ?
15 ሞቅ ያለ ምሥጋናና ማበረታቻ ሊሰጣቸው ከሚገቡ ክርስቲያን ሴቶች መካከል የተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሚስቶች ይገኛሉ። እነዚህ የተወደዱ እህቶች ወንድሞቻቸውን በመንፈሳዊ ለማነጽ ከጉባኤ ወደ ጉባኤ፣ ከክልል ወደ ክልል የሚዘዋወሩትን ባሎቻቸውን ተከትለው ለመሄድ ሁልጊዜ ዝግጁ ሆነው የሚኖሩ ናቸው። አብዛኞቹ በራስ ቤት የመኖርን ምቾት አግኝተው አያውቁም። በየሣምንቱ አዳዲስ አልጋ ላይ ይተኛሉ፤ ደግሞም ሁልጊዜ ጥሩ አልጋ አያጋጥማቸውም። ቢሆንም ወንድሞቻቸው ሊያዘጋጁላቸው የቻሉትን ሁሉ በደስታ ይቀበላሉ። ለመንፈሳዊ እህቶቻቸው ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው።
16 እነዚህ ክርስቲያን ሴቶች ለባሎቻቸው ከፍተኛ ድጋፍ ይሰጣሉ። ኢየሱስ እየተከተሉ ያገለግሉት የነበሩትን አምላካዊ ሴቶች ይመስላሉ። (ማርቆስ 15:41) ባሎቻቸው ‘ሁልጊዜ የጌታ ሥራ የሚበዛላቸው ስለሆኑ’ ከባሎቻቸው ጋር ለብቻ የሚያሳልፉት ብዙ ጊዜ የላቸውም። (1 ቆሮንቶስ 15:58) አንዳንዶቹ በ1948 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንደ ጀመረችው እንደ ፈረንሣዊቷ ሮዛ ዙሚጋ ለ30 ወይም ለ40 ዓመታት ለባሎቻቸው ሻንጣ ሲያዘጋጁና አብረዋቸው ሲጓዙ ኖረዋል። ለይሖዋ፣ ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው ሲሉ ማንኛውንም ነገር መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው። ፍቅራችንን፣ አድናቆታችንንና ጸሎታችንን ማግኘት የሚገባቸው ናቸው።
የሽማግሌዎች ሚስቶች
17, 18. (ሀ) የአገልጋዮች ሚስቶች ምን ዓይነት ባሕርይ እንዲኖራቸው ይፈለግባቸዋል? (ለ) የሽማግሌዎች ሚስቶች ለይሖዋና ለወንድሞቻቸው ሲሉ ምን ዓይነት መሥዋዕትነት ለመቀበል ፈቃደኞች ሆነዋል? ሌሎች ሚስቶችስ ባሎቻቸውን ሊረዱ የሚችሉት እንዴት ነው?
17 ሐዋርያው ጳውሎስ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ሆነው የሚሾሙ ወንድሞች ማሟላት የሚኖርባቸውን ብቃቶች በሚዘረዝርበት ጊዜ “እንዲሁም ሴቶች ጭምቶች፣ የማያሙ፣ ልከኞች፣ በነገር ሁሉ የታመኑ ሊሆኑ ይገባቸዋል” በማለት ስለ ሴቶች ጽፎአል። (1 ጢሞቴዎስ 3:11) እርግጥ ነው፣ ይህ አጠቃላይ ምክር ለሁሉም ክርስቲያን ሴቶች የሚሰራ ነው። ቢሆንም ከጥቅሱ ዙሪያ ያሉትን ሐሳቦች ስንመለከት የአገልግሎት ምድብ የተሰጣቸው ወንድሞች ሚስቶች በእነዚህ ጠባዮች ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆን እንደሚገባቸው እንረዳለን።
18 በብዙ ሺህ የሚቆጠሩት የክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ሚስቶች በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆናቸውን ስንመለከት በጣም ደስ ይለናል። በልማዳቸውና በአለባበሳቸው ልከኞች ናቸው። በክርስቲያናዊ አኗኗር ረገድ ጭምቶች ናቸው። ስለሚናገሩት ነገር በጣም ጥንቁቆች ናቸው። በሁሉም ነገር ታማኝ ሆነው ለመገኘት ይጥራሉ። በተጨማሪም ባሎቻቸው ከእነርሱ ጋር ሊያሳልፉት ይችሉት የነበረውን ጊዜ ለጉባኤ ጉዳዮች እንዲያውሉ በመፍቀዳቸው መስዋዕትነትን ለመቀበል ተስማምተዋል። እነዚህ ታማኝ ክርስቲያን ሴቶች ሞቅ ያለ ፍቅርና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ብዙ ወንድሞች ሚስቶቻቸው እንዲህ ያለውን መሥዋዕትነት ለመቀበል ፈቃደኛ ቢሆኑና ጊዜያቸውን ለመላው ጉባኤ ጥቅም እንዲያውሉ በትህትና ቢፈቅዱ ብዙ በሆኑት ጉባኤዎቻችን ለአገልጋይነት መብት የሚበቁ ብዙ ወንድሞች ማግኘት ይቻላል።
ታማኝ አሮጊቶች
19. ታማኝ አሮጊቶች በጉባኤዎቻቸው ውስጥ የሚወደዱትና የሚደነቁት ለምንድንነው? እኛስ ስለ እነርሱ እንዴት ያለ ስሜት ሊኖረን ይገባል?
19 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱ ሴቶች ካደረግነው ጥናት እርጅና የእምነት ሴቶችን ይሖዋን ከማገልገል ሊያግዳቸው እንደማይችል ለመረዳት ችለናል። ለዚህም ሣራ፣ ኤልሳቤጥና ሐና ምሳሌ ሊሆኑን ይችላሉ። ዛሬም ቢሆን በእምነትና በጽናት ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ በዕድሜ የገፉ ብዙ እህቶች አሉ። እነዚህ እህቶች ወጣት እህቶችን በመርዳት የሽማግሌዎችን ጥረት በአስተዋይነት ሊደግፉ ይችላሉ። ከራሳቸው የብዙ ዓመት ተሞክሮ በመነሳት ለወጣት ሴቶች የጥበብ ምክር ሊሰጡ ይችላሉ። ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል ሥልጣን ከቅዱሳን ጽሑፎች ተሰጥቶአቸዋል። (ቲቶ 2:3-5) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በዕድሜ ጠና ያለች እህት ራስዋ መመከር ሊያስፈልጋት ይችላል። በዚህ ጊዜ ምክሩን የሚሰጣት ሽማግሌ ‘እንደ እናት’ ሊይዛት ይገባል። ሽማግሌዎች መበለቶችን ማክበር ይኖርባቸዋል። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ሥጋዊ እርዳታ የሚያገኙበትን መንገድ ሊያዘጋጁላት ይገባል። (1 ጢሞቴዎስ 5:1-3, 5, 9, 10) በዕድሜ የገፉት ውድ እህቶቻችን ተፈላጊና ተወዳጅ መሆናቸውን እንዲሰማቸው ማድረግ ይገባል።
ከክርስቶስ ጋር አብረው የሚገዙ ሴቶች
20. ለብዙ ክርስቲያን ሴቶች ምን ከፍተኛ መብት ተሰጥቶአቸዋል? ስለዚህስ ጉዳይ ሌሎች በጎች በጣም መደሰት የሚችሉት ለምንድንነው?
20 አምላክ በዘር ወይም በጾታ እንደማያዳላ ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ ያስረዳሉ። (ሮሜ 2:10, 11፤ ገላትያ 3:28) ይሖዋ ከልጁ ጋር በመንግሥቱ አገዛዝ የሚካፈሉትን ሰዎች በመረጠበት ሁኔታም ላይ ይህ እውነት በግልጽ ይታያል። (ዮሐንስ 6:44) የሌሎች በጎች አንዱ ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች የኢየሱስ እናት እንደነበረችው እንደ ማርያም፣ መግደላዊት ማርያም፣ ጵርስቅላ፣ ፕሮፊሞና፣ ጢሮፊሞሳና በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ የነበሩ ብዙ እህቶች የመሰሉት ታማኝ ሴቶች በመንግሥቱ አስተዳደር በመካፈል ይህንን መንግሥት ስለሴትነት ባሕርያት፣ ስሜቶችና ተሞክሮዎች ባላቸው ዕውቀትና ማስተዋል ለማበልጸግ በመቻላቸው በጣም አመስጋኞች ለመሆን ይችላሉ!—ሮሜ 11:33-36
21. በዛሬው ዘመን ‘በጌታ ለሚደክሙ’ ሴቶች ያለን ዝንባሌ እንዴት ያለ ነው?
21 በዛሬው ዘመን የምንኖረውም ለእህቶቻችን ሐዋርያው ጳውሎስ “በወንጌል ከእኔ ጋር አብረው ተጋድለዋል” በማለት አድናቆቱንና ፍቅሩን ለገለጸላቸው ክርስቲያን ሴቶች የተሰማው ዓይነት ስሜት ይሰማናል። (ፊልጵስዩስ 4:3) የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች፣ ምሥራቹን ከሚያውጀው የሴቶች ሠራዊት ጋር፣ አዎ፣ ‘በጌታ ከሚደክሙት ሴቶች’ ጋር ጎን ለጎን ተሰልፈው ለመሥራት መቻላቸውን እንደ ታላቅ ደስታና መብት ይቆጥሩታል።—መዝሙር 68:11፤ ሮሜ 16:12
የክለሣ ጥያቄዎች
◻ ኢየሱስ እንደ አይሁዳውያን የሃይማኖት መሪዎች በሴቶች ላይ ጥላቻ ወይም ንቀት እንዳልነበረው ያሳየው እንዴት ነው?
◻ ፈሪሐ አምላክ የነበራቸው ሴቶች ኢየሱስን ያገለገሉት እንዴት ነው? አንዳንዶቹስ ምን ታላቅ መብት አግኝተዋል?
◻ ጳውሎስ በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ ሴቶች ማክበር ስለሚኖርባቸው ሥርዓት ምን ተናግሮአል?
◻ የተለየ ፍቅርና ድጋፍ ሊሰጣቸው የሚገቡ እህቶች የትኞቹ ናቸው? ለምንስ?
◻ በዛሬው ጊዜ ‘በጌታ ለሚደክሙ’ሴቶች ሁሉ እንዴት ያለ ስሜት ሊኖረን ይገባል?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሴቶች ኢየሱስንና ሐዋርያቱን አገልግለዋል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የግል ጥቅማቸውን የሚሰዉ የተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና የሌሎች ሽማግሌዎች ሚስቶች ለአምላክ ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ