‘ሂዱና ደቀ መዛሙርት አድርጉ’
“ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ሂዱና . . . ደቀ መዛሙርት አድር[ጉ]።”—ማቴዎስ 28:18, 19
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምን ሥራ ሰጣቸው? (ለ) ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
ጊዜው 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የጸደይ ወቅት ሲሆን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በእስራኤል፣ ገሊላ በሚገኝ አንድ ተራራ ላይ ተሰብስበዋል። ከሞት የተነሣው ጌታቸው ወደ ሰማይ የሚያርግበት ጊዜ በጣም ተቃርቧል። ከዚያ በፊት ግን የሚነግራቸው አንድ በጣም አስፈላጊ ነገር ይኸውም ለእነርሱ ሊሰጣቸው ያሰበው ሥራ አለ። ሥራው ምንድን ነው? ደቀ መዛሙርቱ የተሰጣቸውን ሥራ እንዴት ተወጡት? በዚህ ረገድ እኛስ ምን እንድናደርግ ይጠበቅብናል?
2 ኢየሱስ የተናገረው ነገር በማቴዎስ 28:18-20 ላይ ይገኛል፦ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” ኢየሱስ “ሥልጣን ሁሉ፣” “ሕዝቦችን ሁሉ፣” “ያዘዝኋችሁንም ሁሉ” እና “ሁልጊዜ” የሚሉትን አባባሎች ተጠቅሟል። በሰጣቸው ትእዛዝ ውስጥ የተካተቱት እነዚህ አራት ነጥቦች አንዳንድ አስፈላጊ ጥያቄዎች ያስነሳሉ። ጥያቄዎቹን ለምን? የት? ምን? እና መቼ? በሚሉት ቃላት ጠቅለል አድርጎ ማስቀመጥ ይቻላል። እስቲ እነዚህን ጥያቄዎች አንድ በአንድ እንመርምር።a
“ሥልጣን ሁሉ . . . ተሰጥቶኛል”
3. ደቀ መዛሙርት አድርጉ የሚለውን ትእዛዝ ማክበር ያለብን ለምንድን ነው?
3 በመጀመሪያ፣ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠንን ትእዛዝ ማክበር ያለብን ለምንድን ነው? ኢየሱስ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ሂዱና . . . ደቀ መዛሙርት አድር[ጉ]” ብሏል። “ስለዚህ” የሚለው ቃል ይህን ትእዛዝ ማክበር ያለብን ለምን እንደሆነ አንድ ዐቢይ ምክንያት ይሰጠናል። ደቀ መዛሙርት አድርጉ በማለት ትእዛዝ የሰጠው ኢየሱስ “ሥልጣን ሁሉ” ስለያዘ ነው። ኢየሱስ ምን ያህል ሥልጣን አለው?
4. (ሀ) ኢየሱስ ምን ያህል ሥልጣን አለው? (ለ) የኢየሱስን ሥልጣን መገንዘባችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ ሲል ለሰጠን ትእዛዝ ምን ምላሽ እንድንሰጥ ሊያነሳሳን ይገባል?
4 ኢየሱስ በጉባኤው ላይ ሥልጣን የነበረው ሲሆን ከ1914 ወዲህ ደግሞ አዲስ በተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ላይ ሥልጣን ተሰጥቶታል። (ቆላስይስ 1:13፤ ራእይ 11:15) የመላእክት አለቃ እንደመሆኑ መጠን በሰማይ ያሉ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የመላእክት ሠራዊት በእርሱ ሥር ናቸው። (1 ተሰሎንቄ 4:16፤ 1 ጴጥሮስ 3:22፤ ራእይ 19:14-16) የጽድቅ መመሪያዎችን የሚጻረር “ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ” እንዲደመስስ ከአባቱ ሥልጣን ተሰጥቶታል። (1 ቆሮንቶስ 15:24-26፤ ኤፌሶን 1:20-23) ኢየሱስ ሥልጣን ያለው በሕያዋን ላይ ብቻ አይደለም። “በሕያዋንና በሙታንም ላይ እንዲፈርድ” ሥልጣን የተሰጠው በመሆኑ በሞት ያንቀላፉትን ለማስነሣት መለኮታዊ ኃይል አለው። (የሐዋርያት ሥራ 10:42፤ ዮሐንስ 5:26-28) እንዲህ ዓይነት ከፍተኛ ሥልጣን ያለው አካል የሰጠው ትእዛዝ ትልቅ ክብደት ሊሰጠው እንደሚገባ እሙን ነው። በመሆኑም ክርስቶስ ‘ሂዱና ደቀ መዛሙርት አድርጉ’ ሲል የሰጠንን ትእዛዝ በአክብሮትና በፈቃደኝነት መንፈስ እንፈጽማለን።
5. (ሀ) ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ የሰጠውን መመሪያ በታዛዥነት የፈጸመው እንዴት ነው? (ለ) ጴጥሮስ ኢየሱስን መታዘዙ ምን በረከት አስገኘለት?
5 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ ሥልጣኑን አምኖ መቀበልና ትእዛዙን ማክበር በረከት እንደሚያስገኝ ለደቀ መዛሙርቱ ፈጽሞ የማይረሳ ትምህርት ሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ ዓሣ አጥማጅ የነበረውን ጴጥሮስን በአንድ ወቅት “ወደ ጥልቁ ውሃ ፈቀቅ በልና ዓሣ ለመያዝ መረባችሁን ጣሉ” ብሎት ነበር። ጴጥሮስ ዓሣ ሊያገኙ እንደማይችሉ እርግጠኛ ስለነበር ኢየሱስን “መምህር ሆይ፤ ሌሊቱን ሙሉ ስንደክም አድረን ምንም አልያዝንም” አለው። ይሁንና ጴጥሮስ ራሱን ዝቅ በማድረግ “አንተ ካልህ ግን መረቦቹን እጥላለሁ” አለ። ጴጥሮስ፣ ክርስቶስ የሰጠውን መመሪያ ታዝዞ መረቦቹን በጣለ ጊዜ “እጅግ ብዙ ዓሣ” ያዘ። ጴጥሮስ በሁኔታው ስሜቱ በጥልቅ ስለተነካ “በኢየሱስ ጉልበት ላይ ወድቆ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ እኔ ኀጢአተኛ ሰው ነኝና ከእኔ ተለይ’ አለው።” ይሁንና ኢየሱስ “አትፍራ፤ ከእንግዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” ሲል መለሰለት። (ሉቃስ 5:1-10፤ ማቴዎስ 4:18) ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?
6. (ሀ) ብዙ ዓሣ ስለመያዛቸው የሚተርከው ዘገባ እንደሚያሳየው ኢየሱስ ምን ዓይነት ታዛዥነት እንድናሳይ ይፈልጋል? (ለ) የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ ለጴጥሮስ፣ ለእንድርያስና ለሌሎች ሐዋርያት “ሰው አጥማጆች” እንዲሆኑ ተልዕኮ የሰጣቸው በተዓምር ብዙ ዓሣ ከመያዛቸው በፊት ሳይሆን ከያዙ በኋላ ነበር። (ማርቆስ 1:16, 17) ኢየሱስ በጭፍን እንዲታዘዙት እንዳልጠበቀባቸው በግልጽ ማየት ይቻላል። እርሱን መታዘዝ ያለባቸው ለምን እንደሆነ አሳማኝ ምክንያት አቅርቦላቸዋል። ኢየሱስ መረባቸውን እንዲጥሉ የሰጣቸውን መመሪያ መታዘዛቸው ብዙ ዓሣ እንዲይዙ እንዳስቻላቸው ሁሉ ‘ሰዎችን እንዲያጠምዱ’ የሰጣቸውን መመሪያ መታዘዛቸውም ከፍተኛ በረከት ያስገኝላቸዋል። ሐዋርያቱ እርሱ የነገራቸውን በሙሉ አምነው ተቀበሉ። “እነርሱም ጀልባዎቹን ወደ ምድር ካስጠጉ በኋላ ሁሉን ትተው ተከተሉት” በማለት ዘገባው ይደመድማል። (ሉቃስ 5:11) በዛሬው ጊዜ ሌሎች ሰዎች ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንዲካፈሉ ስናበረታታ የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን። ሰዎች የነገርናቸውን በጭፍን እንዲከተሉ አንጠብቅባቸውም። ከዚህ ይልቅ የክርስቶስን ትእዛዝ እንዲከተሉ አሳማኝ ማስረጃ እናቀርብላቸዋለን።
አሳማኝ ምክንያቶችና ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ
7, 8. (ሀ) በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የምንካፈልባቸው አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? (ለ) በስብከቱ ሥራ እንድትቀጥል በተለይ አንተን የሚገፋፋህ ጥቅስ የትኛው ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
7 የክርስቶስን ሥልጣን ስለምንቀበል የመንግሥቱን ምስራች በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ድርሻ ሊኖረን ችሏል። ሰዎች መልካሙን ሥራ እንዲጀምሩ ለማነሳሳት ምን ተጨማሪ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች ልናቀርብላቸው እንችላለን? በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ አንዳንድ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች የተናገሩትን ሐሳብና ጥቅሶቹ ሐሳባቸውን እንዴት እንደሚደግፉ ተመልከት።
8 በ1951 የተጠመቀው ሮይ፦ “ራሴን ለይሖዋ ስወስን በሕይወቴ ዘመን ሁሉ እርሱን ለማገልገል ቃል ገብቻለሁ። የገባሁትን ቃል ማክበር እፈልጋለሁ።” (መዝሙር 50:14፤ ማቴዎስ 5:37) በ1962 የተጠመቀችው ሄተር፦ “ይሖዋ ስላደረገልኝ ነገር ሁሉ ሳስብ እርሱን በታማኝነት በማገልገል አመስጋኝነቴን የመግለጽ ፍላጎት ያድርብኛል።” (መዝሙር 9:1, 9-11፤ ቈላስይስ 3:15) በ1954 የተጠመቀችው ሃነሎረ፦ “አገልግሎት በወጣን ቁጥር መላእክት ድጋፍ ይሰጡናል፤ ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!” (የሐዋርያት ሥራ 10:30-33፤ ራእይ 14:6, 7) በ1969 የተጠመቀችው አነር፦ “የይሖዋ የፍርድ ቀን ሲጀምር ማንም ሰው ‘ማስጠንቀቂያውን አልሰማሁም!’ በሚል ይሖዋም ሆነ አገልጋዮቹ ቸልተኞች ናቸው ብሎ የሚወቅስበት ምክንያት እንዲያገኝ አልፈልግም።” (ሕዝቅኤል 2:5፤ 3:17-19፤ ሮሜ 10:16, 18) በ1974 የተጠመቀው ክላውዲዮ፦ “በስብከቱ ሥራ ስንካፈል ‘በይሖዋ ፊት’ የምንታይ ከመሆኑም ሌላ ‘ክርስቶስ አብሮን ይሆናል።’ እስቲ አስቡት አገልግሎት ስንወጣ እነዚህ ውድ ወዳጆቻችን ከእኛ ጋር ናቸው!”—2 ቆሮንቶስ 2:17b
9. (ሀ) ጴጥሮስና ጓደኞቹ ብዙ ዓሣ እንደያዙ የሚገልጸው ዘገባ ክርስቶስን መታዘዝን በተመለከተ ምን ይገልጻል? (ለ) በዛሬው ጊዜ አምላክንና ክርስቶስን እንድንታዘዝ የሚገፋፋን ትክክለኛው ዝንባሌ ምን መሆን ይኖርበታል? ለምንስ?
9 ጴጥሮስና ጓደኞቹ ብዙ ዓሣ እንደያዙ የሚገልጸው ዘገባ ክርስቶስን የምንታዘዘው በትክክለኛ የልብ ዝንባሌ መሆን እንዳለበትም ያሳያል። ታዛዥነታችን ከፍቅር የመነጨ መሆን አለበት። ጴጥሮስ “እኔ ኀጢአተኛ ሰው ነኝና ከእኔ ተለይ” ባለው ጊዜ ኢየሱስ ከእርሱ ተለይቶ አልሄደም እንዲሁም ይህን ኀጢአት ፈጽመሃል ብሎ አልወቀሰውም። (ሉቃስ 5:8) ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ፣ ከእርሱ ተለይቶ እንዲሄድ ጴጥሮስ ስለጠየቀው እንኳ አልነቀፈውም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ በደግነት “አትፍራ” ብሎታል። ኢየሱስን ከፍርሃት የተነሳ መታዘዝ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ሊሆን አይችልም። ኢየሱስ ጴጥሮስንና ጓደኞቹን ሰውን የማጥመድ ትልቅ ሥራ እንደሚያከናውኑ ነግሯቸዋል። በዛሬው ጊዜ እኛም ሰዎች ፍርሃት ወይም የበደለኝነትና የእፍረት ስሜት ተሰምቷቸው ክርስቶስን እንዲታዘዙ ለማስገደድ አንሞክርም። ይሖዋ የሚደሰተው ለእርሱና ለክርስቶስ ካለን ፍቅር የተነሳ በፍጹም ነፍሳችን የምንታዘዝ ከሆነ ብቻ ነው።—ማቴዎስ 22:37
“ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው”
10. (ሀ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አድርጉ ሲል ከሰጠው ትእዛዝ ውስጥ ለተከታዮቹ በጣም ተፈታታኝ የሆነባቸው የትኛው ነጥብ ነው? (ለ) ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ለሰጣቸው ትእዛዝ ምን ምላሽ ሰጡ?
10 ክርስቶስ ከሰጠው ትእዛዝ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ሁለተኛ ጥያቄ ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ የት መካሄድ አለበት የሚል ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል ነግሯቸዋል። ኢየሱስ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት በነበሩት ዓመታት ይሖዋን ለማገልገል ወደ እስራኤል እስከመጡ ድረስ የየትኛውም አገር ሕዝቦች ተቀባይነት ያገኙ ነበር። (1 ነገሥት 8:41-43) ኢየሱስ ራሱ በአብዛኛው የሰበከው ለሥጋዊ አይሁዳውያን ነበር። አሁን ግን ተከታዮቹን ወደ ተለያዩ አገር ሕዝቦች እንዲሄዱ ነገራቸው። በሌላ አባባል ደቀ መዛሙርቱ የተሰማሩበት የማጥመጃ ቦታ ወይም የስብከት ክልል በትንሽ “ኩሬ” ማለትም በሥጋዊ አይሁዶች ላይ ብቻ ተገድቦ የነበረ ቢሆንም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን መላውን የሰው ልጆች “ባሕር” የሚያጠቃልል ይሆናል። ምንም እንኳ ይህ ሁኔታ ለደቀ መዛሙርቱ ተፈታታኝ ቢሆንም የኢየሱስን መመሪያ በደስታ ተቀብለዋል። ኢየሱስ ከሞተ 30 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ምስራቹ ለአይሁዳውያን ብቻ ሳይሆን “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ” ተሰብኳል በማለት ሊጽፍ ችሏል።—ቈላስይስ 1:23
11. ከ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ አንስቶ ‘የማጥመጃው ክልል’ እየተስፋፋ የመጣው እንዴት ነው?
11 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከዚያ ባልተናነሰ የአገልግሎት ክልል መስፋፋት ታይቷል። በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ‘የማጥመጃው ክልል’ በጥቂት አገሮች ውስጥ ብቻ የተወሰነ ነበር። ይሁንና በዚያ ወቅት የነበሩ የክርስቶስ ተከታዮች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች የተዉትን ምሳሌ በመከተል ይሰብኩበት የነበረውን ክልል አስፋፍተዋል። (ሮሜ 15:20) በ1930ዎቹ መጀመሪያ ላይ ደቀ መዛሙርት የሚያደርጉት አንድ መቶ በሚያህሉ አገሮች ውስጥ ነበር። በዛሬው ጊዜ ግን ‘የማጥመጃው ክልል’ 235 አገሮችን ያቀፈ ሆኗል።—ማርቆስ 13:10
“ከየቋንቋው”
12. ዘካርያስ 8:23 ላይ የሚገኘው ትንቢት ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ እንደሚኖር ይገልጻል?
12 ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ እጅግ ተፈታታኝ የሚያደርገው የክልሉ ስፋት ብቻ ሳይሆን የቋንቋው ብዛትም ነው። ይሖዋ በነቢዩ ዘካርያስ በኩል ይህን ትንቢት ተናግሯል፦ “በእነዚያም ቀናት ከየወገኑና ከየቋንቋው ዐሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ አጥብቀው በመያዝ፣ ‘እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና አብረን እንሂድ’ ይሉታል።” (ዘካርያስ 8:23) ይህ ትንቢት ባለው ሁለተኛ ፍጻሜ መሠረት ‘አንዱ አይሁዳዊ’ በመንፈስ የተቀቡ ቀሪዎችን የሚያመለክት ሲሆን ‘ዐሥሩ ሰዎች’ ደግሞ ‘እጅግ ብዙ ሰዎችን’ ያመለክታሉ።c (ራእይ 7:9, 10፤ ገላትያ 6:16) የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሆኑት እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች በበርካታ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ከመሆኑም ሌላ ዘካርያስ እንደገለጸው ቋንቋቸው የተለያየ ነው። በዚህ ዘመን ያሉት የአምላክ ሕዝቦች ከተለያየ አገርና ቋንቋ የተውጣጡ ናቸው? እንዴታ!
13. (ሀ) በዚህ ዘመን በአምላክ ሕዝቦች መካከል በቋንቋ ረገድ ምን ለውጥ ታይቷል? (ለ)በተለያዩ ቋንቋዎች መንፈሳዊ ምግብ ባስፈለገበት ወቅት የታማኙ ባሪያ ክፍል ምን አደረገ? (“ማየት ለተሳናቸው የተዘጋጁ ጽሑፎች” የሚለውን ሣጥን ጨምረህ መልስ።)
13 በ1950 በዓለም ዙሪያ ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ከአምስቱ ሦስቱ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንግሊዝኛ ነበር። በ1980 ይህ አኃዝ ተቀይሮ ከአምስት ሁለት የሆነ ሲሆን በዛሬው ጊዜ ደግሞ ከአምስት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አፍ መፍቻ ቋንቋው እንግሊዝኛ የሆነው አንድ ብቻ ሆኗል። ታማኝና ልባም ባሪያ በቋንቋ ረገድ የታየውን ይህን ለውጥ ለማስተናገድ ምን ያደረገው ነገር አለ? ከምንጊዜውም በበለጠ በብዙ ቋንቋዎች መንፈሳዊ ምግብ አዘጋጅቷል። (ማቴዎስ 24:45) ለምሳሌ ያህል በ1950 በ90 ቋንቋዎች ጽሑፎች ይዘጋጁ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን ቁጥሩ ወደ 400 ገደማ ደርሷል። የተለያየ ቋንቋ ላላቸው ሰዎች እንዲህ ዓይነት ትኩረት መሰጠቱ ያስገኘው ፍሬ አለ? አዎን! በዓመቱ ውስጥ፣ በእያንዳንዱ ሳምንት ‘ከቋንቋ ሁሉ’ በአማካይ ወደ 5,000 ገደማ ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ይሆናሉ! (ራእይ 7:9) እድገቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ‘መረቦቹ’ ብዙ ዓሣ እያጠመዱ ነው!—ሉቃስ 5:6፤ ዮሐንስ 21:6
አስደሳች በሆነው የስብከት ሥራ አንተም መሳተፍ ትችላለህ?
14. በክልላችን ውስጥ የሚገኙትን የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪዎች መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? (“ደቀ መዛሙርት ለማድረግ በምልክት ቋንቋ መጠቀም” የሚለውን ሣጥን ጨምረህ መልስ።)
14 በበርካታ ምዕራባውያን አገሮች ውስጥ የውጭ አገር ዜጎች እየተበራከቱ መምጣታቸው ነዋሪዎቹ ከመኖሪያ አገራቸው ሳይንቀሳቀሱ ‘ከቋንቋ ሁሉ’ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት የማድረግ ከባድ ሥራ አስከትሎባቸዋል። (ራእይ 14:6) በክልላችን ውስጥ ከእኛ የተለየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ብናገኝ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? (1 ጢሞቴዎስ 2:4) በምሳሌያዊ አነጋገር ትክክለኛውን የማጥመጃ መሣሪያ መጠቀም እንችላለን። ለእነዚህ ሰዎች በቋንቋቸው የተዘጋጀ ጽሑፍ አበርክትላቸው። የሚቻል ከሆነ ደግሞ ቋንቋቸውን የሚያውቅ አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲያነጋግራቸው ዝግጅት አድርግ። (የሐዋርያት ሥራ 22:2) የውጭ አገር ዜጎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት ሲሉ ተጨማሪ ቋንቋ የተማሩ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ስላሉ እንዲህ ዓይነት ዝግጅት ማድረግ አስቸጋሪ አይደለም። ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ሰዎችን በዚህ መንገድ መርዳት መቻል ከፍተኛ ደስታ ያስገኛል።
15, 16. (ሀ) የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎችን መርዳት ደስታ እንደሚያስገኝ የትኞቹ ምሳሌዎች ያሳያሉ? (ለ) በውጭ አገር ቋንቋ ማገልገልን በተመለከተ ልናስብባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
15 የመንግሥቱ ስብከት ሥራ በተደራጀ መልክ በ34 ቋንቋዎች እየተካሄደ ካለባት ከኔዘርላንድ የተገኙትን ሁለት ተሞክሮዎች ተመልከት። አንድ ባልና ሚስት ወደ አገራቸው ለመጡ የፖሊሽ ቋንቋ ተናጋሪዎች በመስበክ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ለመካፈል ራሳቸውን አቀረቡ። ጥረታቸው ከፍተኛ ውጤት ያስገኘላቸው ከመሆኑ የተነሳ ባልየው ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ማስጠናት የሚችልበት በሳምንቱ ውስጥ አንድ ተጨማሪ ቀን ለማግኘት ሲል ተቀጥሮ የሚሠራባቸውን ቀናት ለመቀነስ ወሰነ። ባልና ሚስቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በየሳምንቱ ከ20 በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራት ጀመሩ። “በአገልግሎታችን በጣም ተደስተናል” ሲሉ ተናግረዋል። ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የሚካፈሉ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በራሳቸው ቋንቋ የደረሳቸው ሰዎች አድናቆታቸውን ሲገልጹ መስማት በጣም ያስደስታቸዋል። ለምሳሌ ያህል በቬትናም ቋንቋ በሚካሄድ የጉባኤ ስብሰባ ላይ አንድ አረጋዊ ሰው ከመቀመጫቸው ተነስተው ጥቂት ሐሳብ ለመናገር እንዲፈቀድላቸው ጠየቁ። እንባቸው በዓይናቸው ግጥም ብሎ ለምሥክሮቹ እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፦ “በጣም አስቸጋሪ የሆነውን ቋንቋዬን ለመማር ላደረጋችሁት ጥረት ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። በስተ እርጅናዬ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብዙ አስደናቂ ነገሮች መማር በመቻሌ በጣም አመስጋኝ ነኝ።”
16 በመሆኑም በውጭ አገር ቋንቋ በሚካሄዱ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ አስፋፊዎች ከፍተኛ በረከት እንዳገኙ ቢሰማቸው ምንም አያስገርምም። በብሪታንያ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት እንዲህ ብለዋል፦ “ምሥራቹን በማወጅ ባሳለፍናቸው 40 ዓመታት ውስጥ በጣም አስደሳች ሆነው ካገኘናቸው የአገልግሎት ዘርፎች አንዱ ለውጭ አገር ዜጎች መስበክ ነው።” በዚህ አስደሳች የአገልግሎት ዘርፍ መሳተፍ እንድትችል በሕይወትህ ውስጥ አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ ትችላለህ? በአሁኑ ጊዜ ተማሪ ከሆንክ ወደፊት በዚህ የአገልግሎት መስክ መካፈል እንድትችል አንድ የውጭ አገር ቋንቋ መማር ትችላለህ? እንዲህ ማድረግህ በረከት የሞላበት አስደሳች ሕይወት ሊያስገኝልህ ይችላል። (ምሳሌ 10:22) ይህን ጉዳይ ለምን ከወላጆችህ ጋር አትወያይበትም?
የተለያዩ ዘዴዎች መጠቀም
17. በጉባኤያችን የአገልግሎት ክልል ውስጥ ከበፊቱ የበለጠ ብዙ ሰዎች ማነጋገር የምንችለው እንዴት ነው?
17 አብዛኞቻችን የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑ ክልሎች ውስጥ ‘መረቦቻችንን’ ለመጣል ሁኔታችን እንደማይፈቅድልን የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በራሳችን የጉባኤ ክልል ውስጥ አሁን ከምናደርገው የበለጠ ብዙ ሰዎች አግኝተን ማነጋገር የምንችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። እንዴት? የምንሰብከውን መልእክት ሳይሆን የምንሰብክበትን መንገድ በመቀያየር ነው። በብዙ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች በቀላሉ መግባት በማይቻልባቸው ሕንፃዎች ውስጥ ይኖራሉ። ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ቤታቸው አናገኛቸውም። በመሆኑም ‘መረባችንን’ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ቦታዎች ላይ መጣል ሊያስፈልገን ይችላል። እንዲህ በማድረግ የኢየሱስን ምሳሌ እንኮርጃለን። ኢየሱስ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ላገኛቸው ሰዎች ምስራቹን ለመንገር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።—ማቴዎስ 9:9፤ ሉቃስ 19:1-10፤ ዮሐንስ 4:6-15
18. በተለያዩ ቦታዎች መመስከር ውጤታማ መሆኑ የታየው እንዴት ነው? (“በሥራ ቦታ ደቀ መዛሙርት ማድረግ” ከሚለው ሣጥን ጨምረህ መልስ።)
18 በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ምስራቹን መስብክ ደቀ መዛሙርት ማድረግ የሚቻልበት ጠቃሚ ዘዴ ሆኖ ተገኝቷል። ደቀ መዛሙርት በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አስፋፊዎች በተለያዩ ቦታዎች ምሥክርነት ለመስጠት ከበፊቱ የበለጠ ጥረት እያደረጉ ናቸው። ከቤት ወደ ቤት ከማገልገል በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ የምስራቹ አስፋፊዎች በአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ በቢሮዎች፣ በገበያ አዳራሾች፣ በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች፣ በአውቶቡስ ፌርማታዎች፣ በመንገድ ላይ፣ በመናፈሻዎች ውስጥ፣ በባሕር ዳር ባሉ መዝናኛዎችና በሌሎች ቦታዎች ይመሰክራሉ። በሃዋይ በቅርቡ ከተጠመቁት መካከል አብዛኞቹ መጀመሪያ የተመሰከረላቸው በእነዚህ ቦታዎች ነው። የተለያዩ ዘዴዎች መጠቀማችን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የሰጠንን ትእዛዝ በተሟላ መልኩ እንድንፈጽም ያስችለናል።—1 ቆሮንቶስ 9:22, 23
19. በሚቀጥለው ርዕስ የሚብራሩት ኢየሱስ ከሰጠን ተልእኮ ውስጥ የትኞቹ ዘርፎች ናቸው?
19 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የሰጠን ተልእኮ ለምን እና የት መስበክ እንዳለብን የሚገልጹትን ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን ምን መስበክ እንዳለብንና እስከ መቼ ድረስ መስበካችንን መቀጠል እንዳለብን የሚገልጹትንም ነጥቦች ያካትታል። ኢየሱስ የሰጠን ተልእኮ የሚያካትታቸው እነዚህ ሁለት ገጽታዎች በሚቀጥለው ርዕስ ይብራራሉ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ጥያቄዎች እንመረምራለን። የመጨረሻዎቹ ሁለት ጥያቄዎች ደግሞ በሚቀጥለው ርዕስ ይብራራሉ።
b ምሳሌ 10:5፤ አሞጽ 3:8፤ ማቴዎስ 24:42፤ ማርቆስ 12:17 እና ሮሜ 1:14, 15 ላይ በስብከቱ ሥራ እንድንካፈል የሚያደርጉ ተጨማሪ ምክንያቶች ተጠቅሰዋል።
c የዚህን ትንቢት ፍጻሜ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የግንቦት 15, 2001 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 12ን እና የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 2 ገጽ 408ን ተመልከት።
ታስታውሳለህ?
• በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የምንሳተፍበት ምክንያትና የልብ ዝንባሌ ምን መሆን አለበት?
• በዛሬው ጊዜ የይሖዋ አገልጋዮች ኢየሱስ ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጉ ሲል የሰጠውን ተልእኮ ምን ያህል አከናውነዋል?
• ‘የማጥመጃ ዘዴዎቻችንን’ መቀያየር የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግ ያለብንስ ለምንድን ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ማየት ለተሳናቸው የተዘጋጁ ጽሑፎች
በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው አልበርት ማየት የተሳነው ወንድም ቢሆንም የጉባኤ ሽማግሌና የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኖ ያገለግላል። በብሬይል የተዘጋጁ ጽሑፎችን መጠቀሙ አገልግሎቱንም ሆነ የአገልግሎት የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያከናውነውን ሥራ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲወጣ አስችሎታል። ታዲያ የጉባኤ ኀላፊነቱን እንዴት እየተወጣ ነው?
ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች የሆነው ጄምስ “ጉባኤያችን የአልበርትን ያህል ውጤታማ የሆነ የአገልግሎት የበላይ ተመልካች አግኝቶ አያውቅም” ብሏል። አልበርት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በእንግሊዝኛና በስፓንኛ በብሬይል የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ዓመቱን በሙሉ ከሚደርሷቸው 5,000 ገደማ ማየት የተሳናቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነው። የታማኙ ባሪያ ክፍል ከ1912 አንስቶ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ጽሑፎች በብሬይል አዘጋጅቷል። በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ዘመናዊ የማተሚያ መሣሪያዎችን በመጠቀም ከአሥር በሚበልጡ ቋንቋዎች በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በብሬይል የተዘጋጁ ገጾች አትመው ከ70 ወደሚበልጡ አገሮች ይልካሉ። ማየት ለተሳናቸው ከተዘጋጁት ጽሑፎች ሊጠቀም የሚችል የምታውቀው ሰው አለ?
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ደቀ መዛሙርት ለማድረግ በምልክት ቋንቋ መጠቀም
በዓለም ዙሪያ፣ ቀናተኛ የሆኑ በርካታ ወጣቶችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች መስማት የተሳናቸው ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት የምልክት ቋንቋ ተምረዋል። ከዚህም የተነሳ በብራዚል ብቻ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 63 መስማት የተሳናቸው ሰዎች የተጠመቁ ሲሆን መስማት የተሳናቸው 35 የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ በአሁኑ ጊዜ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ሆነው እያገለገሉ ናቸው። በዓለም ዙሪያ ከ1,200 የሚበልጡ የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎችና ቡድኖች አሉ። በሩሲያ የሚገኘው ብቸኛው የምልክት ቋንቋ ወረዳ መላውን ሩሲያ የሚያካትት ስለሆነ ከስፋቱ አንጻር ሲታይ በዓለም ላይ ያለው ትልቁ ወረዳ ነው!
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በሥራ ቦታ ደቀ መዛሙርት ማድረግ
በሃዋይ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ከቢሮ ወደ ቢሮ እያገለገለች በነበረበት ወቅት የትራንስፖርት ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሆነ ሰው ጋር ተገናኘች። ግለሰቡ ሥራ የሚበዛበት ቢሆንም እንኳ በሳምንት ለ30 ደቂቃ ቢሮው ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማ። በየሳምንቱ ረቡዕ ጠዋት፣ ሐሳቡ ሳይበታተን ማጥናት እንዲችል ስልክ ቢፈልገው እንኳን እንዳይጠሩት ለሠራተኞቹ ይነግራቸዋል። በሃዋይ የምትኖር ሌላ የይሖዋ ምሥክር ደግሞ የጫማ ማደሻ ሱቅ ባለቤት የሆነችን ሴት በሳምንት አንድ ቀን መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናለች። የሚያጠኑት ሱቅ ውስጥ ደንበኞቿን የምታስተናግድበት ጠረጴዛ ጋር ሆነው ነው። ደንበኛ ሲመጣ እህት ከቦታው ዞር ትላለች፤ ከዚያም ግለሰቡ ከሄደ በኋላ ጥናታቸውን ይቀጥላሉ።
ሥራ አስኪያጁም ሆነ የሱቁ ባለቤት ሊገኙ የቻሉት ምሥክሮቹ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ‘መረባቸውን’ ለመጣል ጥረት በማድረጋቸው ነው። በጉባኤህ የአገልግሎት ክልል ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ቤታቸው የማይገኙ ሰዎችን ማግኘት የምትችልበት ቦታ አለ?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በውጭ አገር ቋንቋ የአገልግሎት መስክ ማገልገል ትችላለህ?